Wednesday, August 2, 2017

ጅራፋዊ ማንነት


© መልካሙ በየነ

ሐምሌ 27/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት ( facebook.com/beyenemlkm ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================
ጅራፍ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍሎች ለብዙ ዓይነት አገልግሎት ይውላል፡፡ በዋናነት ግን ለእርሻ አገልግሎት በሬዎቹን እየገረፉ ፈር ለማስያዝ ጉልህ ቦታ አለው፡፡ በተለይ ደካማ ወይም ሰነፍ በሬን በተለምዶ “አበያ” የሚባለውን በመግረፍ ከጠንካራው በሬ ጋር እኩል እንዲስብ ጀርባው በጅራፍ ይገረፋል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት በሬዎች ጀርባቸው በግርፋት ብዛት ጸጉራቸው አልቆ አጥንታቸው ፈጥጦ ሻሽ ስለሚመስል “ቆርቆሮዎች” ይባላሉ፡፡ እረኞች መንጋዎቻቸውን ለመጠበቅም ይጠቀሙበታል፡፡ በተለይ ጠባብ በሆነ መንገድ ላይ መንጋዎችን ለመንዳት ጅራፍ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጅራፍ ድምጹ እንደ ጥይት የሚጮኽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እረኞች ይህን በማስጮኽ እንደመዝናኛም ይጠቀሙበታል፡፡

ጅራፍ ሁለት ልዩ ባሕርያት አሉት፡፡ የመጀመሪያው ሲርቁት መግረፉ ነው፡፡ ጅራፍ ሲርቁት ይገርፋል እንዲሉ ጅራፍ የሚጠጉትን እንጅ የሚርቁትን አይወድም፡፡ ጅራፍ ሁሉን ነገር ወደራሱ መሰብሰብ ይሻል፡፡ አባ አባ እያሉ እንዲያወድሱት በከንቱ ውዳሴ እንዲያሞጋግሱት ይወዳል፡፡ በሆነ ነገር እንድትቀርበው ያደርግህና ከእርሱ ልራቅ ባልህ ጊዜ የግል ምሥጢርህን አደባባይ ላይ አውጥቶ ይሳለቅብሃል፡፡ ይህ የጅራፍ ባሕርይ የግል ማንነት መገለጫቸው የሆኑ ግለሰቦች አሉ፡፡ እነርሱ የሚያደርጉት እነርሱ የሚከውኑት ብቻ ትክክል እንደሆነ ያስባሉ፡፡ የብዙውን ቀልብ ወደራሳቸው መሳብ ይፈልጋሉ፡፡ ማንኛውንም ነገር ከመሥራትህ በፊት እነርሱን እንድታማክራቸው ይሻሉ፡፡ “እንደእገሌ ያለ እኮ በዚህ ምድር የለም” እንዲባልላቸው ይወተውታሉ፡፡ አንድ ኃጢአት ያሠሩህና ከእነርሱ ጋራ ብቻ ተጣብቀህ እንድትኖር ያደርጉሃል፡፡  ተለይተህ እንዳትሄድ ኃጢአትህን ያወጡብህና በህዝቡ ዘንድ ትጠላለህ፡፡ በዚህም የተነሣ ሳትወድ በግድ ሎሌ አድርገው ይገዙሃል፡፡ እነዚህ ሰዎች አባ አባ እየተባሉ መኖርን የሚሹ ከንቱ ውዳሴ ናፋቂዎች ናቸው፡፡ ስትቀርባቸው አያስተምሩህም አይመክሩህም አይገስጹህም ስትርቃቸው ግን ይሰድቡሃል ያሰድቡሃል፡፡ ስትቀርባቸው አይጠቅሙህም ስትርቃቸው ግን ይጎዱሃል፡፡ ስትቀርባቸው ወደ ንስሐ አይመሩህም ስትርቃቸው ግን ወደ ኃጢአት ይጨምሩሃል፡፡ ስትቀርባቸው እውነትን አያሳዩህም ስትርቃቸው ግን በውሸት ጎርፍ ያለቀልቁሃል፡፡ እነርሱን በመቅረብህ ምናልባትም ስምህ እንዳይጠፋ ታደርግ እንደሆነ እንጅ ሌላ የምትጠቀመው ነገር የለም፡፡ አያስተምሩህ አልተማሩም፣ አይመክሩም አልተመከሩም፣ ወደ ጽድቅ አይመሩህ ጽድቅን አያውቁም ወደ እውነት አይመሩህ የውሸት አባቶች ናቸው በቃ ብቻ የእነርሱ ካባ ጎታች እንድትሆን ብቻ ነው የሚጥሩት፡፡ እነዚህ ሰዎች የጅራፍን ባሕርይ የግል ማንነታቸው አድርገው የያዙ ናቸው፡፡ ጅራፍን ስትርቀው እንደሚገርፍህ ሁሉ እነዚህን ሰዎችም ስትርቃቸው በምላሳቸው የሚገርፉ ናቸው፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን እውነት ወዳለበት ሂደህ ግርፋታቸውን መታገስ ይኖርብሃል፡፡

ሁለተኛው የጅራፍ ባሕርይ ገርፎህ መጮኹ ነው፡፡ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንዲሉ፡፡ ይህን የጅራፍ ሁለተኛ ባሕርይ የግል ማንነታቸው ያደረጉ ሰዎች ራሳቸው ችግር ፈጥረው ችግር ደረሰብኝ በማለት በየአቅጣጫው የሚባዝኑ ናቸው፡፡ ልክ በዮሴፍ ላይ ክስ እንደመሠረተችው የጲጥፋራ ሚስት ማለት ነው፡፡ አስገድዳ ፈቃዴን ፈጽምልኝ ከአንተ ጋራ መተኛት እፈልጋለሁ ብላ የታገለችው እርሷ ነበረች፡፡ ዮሴፍ ግን ሰው ባያየኝም እግዚአብሔር ያየኛል በማለት እምቢ አላት በዚህም የተነሣ አገልጋይ ባሪያ ብለህ ያመጣኸው ሰው ሊደፍረኝ ታገለኝ ብላ ራሷ ጮኸች፡፡ ይች ሴት ጅራፍ ናት ራሷ ገርፋ ራሷ የምትጮኽ፡፡ አሁንም ብዙ ሰዎች አሉ በዚህ ማንነት ውስጥ የተወሸቁ፡፡ ራሳቸው ይህን አድርግ ብለው ቆመው ያሠሩህና ነገ ከሳሾችህ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ሳትደርስባቸው ይደርሱብህና ራሳቸው ደግሞ በፍርድ አደባባይ ያቆሙሃል፡፡ ገንዘብህን ሙልጭ አድርገው ይወስዱና ገንዘቤን ዘረፈኝ ብለው ይከስሱሃል፡፡ በቃ እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ችግር ፈጣሪ ሆነው ሳለ ሌላውን ለመክሰስ የሚሯሯጡ ሃና እና ቀያፋዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ብትርቅም ብትቀርብ በእነርሱ ወንጀል አንተን መክሰሳቸው ስለማይቀር በጸጋ ተቀበለው፡፡ በእነዚህ ሰዎች ችግር ቢደርስብህ ዋጋህ በሰማያት እጥፍ ሆኖ ይጠብቅሃልና በጅራፋዊ ባሕርይ ማንነት ላይ በተመሠረቱ ሰዎች አትበሳጭ፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment