Tuesday, August 8, 2017

የሊስትሮ ዕቃ



© መልካሙ በየነ

ነሐሴ 3/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/tomarthetewahido ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================


ይህ ዘመን እግር ያለጫማ መኖር የተቸገረበት ዘመን ነው፡፡ በመሆኑም እግር በጫማ ውስጥ መሽጎ እንዲኖር ህጋዊ ፈቃድ አግኝቷል፡፡ ከእሾኽ ከእንቅፋት ለመዳን ጫማ ሁነኛ መድኃኒት ነው፡፡ በርግጥ የሚረግጠውን አስተውሎ እና ዓይቶ ለሚራመድ ሰው እሾኽ እና እንቅፋት ፈተናዎቹ አይደሉም፡፡ ይህንን ስል  አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ አንዱ የእኔ ቢጤ ነው አሉ፡፡ ጫማውን ገዝቶ ወደቤቱ ይሄዳል፡፡ ጫማውን ከመውደዱ የተነሣ ጫማውን በእግሩ አላደረገውም ነበር ይልቁንም ተሸክሞት ይጓዝ ነበር እንጅ፡፡  ታዲያ ጫማውን ተሸክሞ ሲሄድ እንቅፋት ይመተዋል ወዲያውኑ ደሙ ይፈሳል ጥፍሩን ገልፍጦታል፡፡ ይኽን የጥፍሩን መገልፈጥ የጣቱን መድማት የተመለከተው ጫማ ገዥ “ጫማየንም ለብሸው ቢሆን ይኸው ነበር” አለ ይባላል፡፡ ሰውየው ከእግሩ ይልቅ ለጫማው አዝኗል ራርቷል፡፡

በቅዱሳኑ በኩል ጫማ መልበስ ከእንቅፋት ከእሾኽ ለመራቅ መሞከር አይታሰብም፡፡ እግራቸው ደም እስኪጎርፈው ድረስ በእሾኽ በእንቅፋት መካከል ይጓዙ ነበር እንጅ፡፡ እግር የተሠራው ዞረው ወንጌልን ሊያስተምሩበት አሕዛብን ሊያሳምኑበት አምልኮተ እግዚአብሔርን ሊያስፋፉበት አምልኮተ ጣዖትን ሊያጠፉበት ነውና “ለመሄጃ ያልሆነ እግር ይሰበር” የሚሉ ናቸው፡፡ እንቅፋት እና እሾኽ ለእነርሱ ምናቸውም አይደለም ምክንያቱም ወንጌልን ለማስተማር ነበር ዋና ትኩረታቸው፡፡ ገነት መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ነበርና ዓላማቸው፡፡ እኛ ግን በዓለም ስለምንኖር ዓለም ለማጌጥም ለመሸብረቅም ከአደጋ ለማምለጥም ሆነ ለማንኛውም አገልግሎት ስትጠቀምበት ስለምንመለከት እኛም እንዲሁ እንጠቀምበታለን፡፡ በርግጥ ይህን በማድረጋችን ኃጢአት ሠርተናል ማለት አይደለም፡፡ የቅዱሳኑን እና እኛን ልዩነት ለማሳየት ነው እንጅ፡፡

የሊስትሮ ዕቃ ምን እንደሚመስል እንመልከት፡፡ በመጀመሪያ ሊስትሮ ማለት ምን ማለት ነው፡፡ ሊስትሮ “ሊስት ሮው” የእንግሊዝኛ ቃል እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ምንም እንኳ ትርጉሙ ያን ያህል ሥራውን የሚገልጽ ባይሆንም “LEAST RAW” የሚል የእንግሊዝኛ ቃል ነው፡፡ በእውነት ጫማን የማስዋብ ሥራ “LEAST RAW” ያስብለዋልን? “LEAST RAW” ማለት በቀጥታ ትርጉሙ “ዝቅተኛ ምድብ” እንደማለት ነው፡፡ ግን እኔ አልስማማበትም፡፡ በዚያው በአማርኛችን “ሊስትሮ” ብለን አዲስ ስም ብንፈጥርለት ይሻላል፡፡ ምናልባትም ፈረንጆቹ ሥራን ስለሚንቁ ሊሆን ይችላል እኛ ግን አንቀበለውም፡፡ ሊስትሮ ጫማ የሚያሳምርባትና የሚያስውብባት ዕቃው ሳጥን የመሰለች በአንድ በኩል ክፍት የሆነች ከላይም የሚዋበው ጫማ የሚቀመጥበት ከፍ የሚያደርግ ዘንባይ ወለል አላት፡፡

የእኛ ሕይወት የሊስትሮ ዕቃ ነው፡፡ በሊስትሮ ዕቃ ሊስትሮው ጫማ ያስውብባታል፡፡ ጫማ ያሳምርበታል፡፡ የሚታጠበውን ያጥባል የሚቀባውን ይቀባል የሚቦረሸውን ይቦርሻል፡፡ ምን አደከማችሁ ጫማ የተባለች ሁሉ ውበቷን አግኝታ ተኳኩላ አምራ አሸብርቃ እንደምትወጣ ወጣት እንዲያ ሆና አምራ አሸብርቃ ትመለሳለች፡፡ በተለይ በዚህ በክረምቱማ ጫማ የማይረግጠው ነገር የለም፡፡ በዚህም የተነሣ ጫማን ለማስዋብ ወደ ሊስትሮ መመላለሳችን አይቀርም፡፡ ሊስትሮውም ጭቃውን ጠርጎ በውኃ እና በሳሙና አጥቦ ወልውሎ ካደረቀው በኋላ ቀለሙን ይቀባዋል፡፡ መቸም ያኔ ጫማችንን የተመለከተ ሁሉ መማረኩ አይቀርም፡፡ ጫማችን የፀሐይን ብርሃን እያንጸባረቀ የማታ ላይ ከዋክብትን ይመስላል፡፡ እኔ ግን ከጫማው እንዲህ ኮከብ ከምሰሉ በስተጀርባ ያለችውን የሊስትሮ ዕቃ ነው በልቤ ውስጥ የማስባት፡፡ የሊስትሮ ዕቃ የሴቱንም የወንዱንም የትልቁንም የትንሹንም ጫማ ያሳምሩባታል፡፡ እራሷን ግን የሚያሳምራት የለም፡፡ የጫማው ጭቃ የሚራገፍባት እርሷ ናት፡፡ የታጠበው ጫማ ቆሻሻ የሚፈስስባት እርሷ ናት፡፡ ጫማው አምሮ ነጽቶ ተውቦ ይሄዳል የሊስትሮዋ ዕቃ ግን ቆሽሻ ጎስቁላ ትገኛለች፡፡ ሊስትሮዎችም ጫማ የማስዋብ የማሳመር ሥራ እንጅ የሊስትሮን ዕቃ ከማስዋብ ላይ አያተኩሩም፡፡

የእኛ ሕይወትም እንደሊስትሮ ዕቃ ነው የምላችሁ ስለዚህ ነው፡፡ ስንቱን አንጽተናል ስንቱን አስውበናል ስንቱን አሳምረናል እኛ ግን አላማርንም አልተዋብንም አልነጻንም፡፡ ንስሐ ግቡ ብለን ስንቱን በንስሐ አንጽተናል፡፡ እኛ ግን እስካሁንም ድረስ በኃጢአት ቆሻሻ ላይ ነን፡፡ ስንቱን ቁረቡ ብለን አስተምረን አቁርበናል መሰላችሁ፡፡ እኛ ግን በኃጢአታችን ምክንያት ሥጋውን ደሙን ተቀብለን አናውቅም፡፡ ስንቱን ነው ጹሙ ጸልዩ ብለን አስተምረን በጾም እና በጸሎት እንዲተጉ ምክንያት የሆንንላቸው፡፡ እኛ ግን አንጾምም አንጸልይምም፡፡ በቃ ሕይወታችን ሁሉ የሊስትሮ ዕቃ ነው በእኛ ላይ በእኛ ምክንያት የሚዋብብን እኛ ግን ያልተዋብን ቆሻሻዎች፡፡ ዕድሜን ለንስሐ ዘመንን ለፍስሐ ይስጠን፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment