© መልካሙ በየነ
ነሐሴ
24/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ነሐሴ 19/2009 ዓ.ም “አክሊሌን ተንጠልጥሎ አየሁት” በሚል በራሴ
ውስጥ ብቻ በኅሊናየ የሚመላለሰውን ጥያቄ መጻፌን ተከትሎ በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መነጋገሪያ እንደነበርሁ
በብዙዎች በውስጥ መስመር መረጃው ደርሶኛል፡፡ በተለይ ነሐሴ 21/2009 ዓ.ም በዕለተ ሰንበት በእናታችን በእግዝእትነ ቅድስት
ድንግል ማርያም በዓል ቀን አብማ ማርያም፣ ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል እና ግምጃ ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ይህንን ጽሑፍ ፕሪንት
በማድረግ ተአምረ ማርያምን አስተካክሎ በማንበብ ፈንታ የአንድን ግለሰብ ስሜት ሲያነብቡ እና መግለጫ ሲሰጡ እንደነበር ጠቁመውኛል፡፡
እኔ የጻፍሁት ለራሴ የተሰማኝን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ የእኔን አስተሳሰብ መከተል አለባችሁ ብየም ማንንም አልወተውትም ማንንም ለማሳመንም
ሆነ ወደ እኔ መስመር እንዲገባ አላስገድድም፡፡
#አብማ #ማርያም ላይ “አብማ አትቁረቡ አብማ የቅባት አገልጋዮች ብቻ
ናቸው የሚኖሩ” ብሏል በሚል መግለጫ ሲሰጡ እንደ ነበር አውቄያለሁ፡፡ እኔ #አብማ #ማርያምን እናቴን ያሳደገችኝን ከጥንት ጀምሬ
የማውቃትን ስባረክባት በረከትን ስቀበልባት የነበረችውን ቤተክርስቲያኔን እንዴት እንዲህ ልል እችላለሁ? በፍጹም ልል አልችልም ምናልባት
ግን ያልተገናኘንበት የአተረጓጎም ስልት እንዳለ ተረድቻለሁ፡፡ አብማን በተመለከተ የጻፍሁት እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ድሮ በንጹሕ ኅሊናየ ሳለሁ ቅባት ተዋሕዶ
የሚለው ምሥጢር ሳይገባኝ በነበርሁበት ወቅት አብማ ማርያምን ሳልሳለም ከዋልሁ ይጨንቀኝ ነበር፡፡ ከዚህች ቦታ የማገኘው የልብ ደስታ
ቀኑን ሙሉ በብሩኅ ገጽ እንድውል ያደርገኝ ነበረ፡፡ ዛሬ ግን ኅሊናየ ውስጥ የታጨቀው የሁለቱ እምነቶች ልዩነት ኅሊናየን እያረሰው
በረከትን ማግኘት አላስቻለኝም፡፡ ጸሎቴን በቤቴ አድርጌ በበዓላት ቀናት እንኳ የምወዳቸውን ቤተክርስቲያናት ሳልሳለማቸው ስውል እስከመቼ
በሚለው ጥያቄ ጽኑእ የኅሊና ክርክር ውስጥ እወድቃለሁ” የሚል ነው፡፡ ለምን ከደብረ ማርቆስ ከተማ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ #አብማ #ማርያምን አነሣህ ብትሉኝ መልካም ነበር፡፡ እኔ ከ1997 ዓ.ም
ጀምሬ ደብረማርቆስን አውቀዋለሁ፡፡ ከዛሬ 12 ዓመት በፊት መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ ያኔ ከአብማ በስተምእራብ በኩል የ3 ደቂቃ መንገድ
ያህል ነበር የምርቀው፡፡ እዛው #አብማ #ማርያም አጠገብ ነበርሁ፡፡ በ30 ብር በተከራየሁት ዶርሜ ውስጥ ስኖር #አብማ #ማርያም
ለእኔ እጅግ ቅርቤ ነበረች፡፡ እናም #አብማ #ማርያም ሳልሳለም ከዋልሁ ይጨንቀኝ ነበር ለማለት የቻልሁት ከዚህ አንጻር ነው እንጅ
ከሌላ አንጻር አይደለም፡፡ ዛሬ ግን “ቅባት” እና “ተዋሕዶ” የሚባሉ እምነቶች በአንድ ጥላ ሥር ተጠልለው ለየራሳቸው መጽሐፍ ሲደጉሱ
ቅኔ ሲያፈሱ ባይ ጊዜ ኅሊናየ ውስጥ ሙግት ተፈጠረብኝ፡፡ እነዚህ የእምነት ልዩነቶችያሉት ደግሞ አብማ ማርያም ውስጥ ብቻ ነው አላልሁም፡፡
አብማ ማርያም ውስጥ አንድም የቅባት አባት የለም ሊባል ይችል ይሆናል አላውቅም እኔ ውስጥ ግን ቢያንስ በደንብ የማውቀው አንድ
ቅባት የሆነ አባት አላጣም ባይ ነኝ፡፡ እርሱ ራሱን ይፈትሽ ካልሆነ አይመለከተውምና፡፡ የሚመለከተው ሰው ግን የግድ ይመለከተዋል፡፡
ስለዚህ አብማን ያነሣሁት በዚህ ምክንያት እንጅ አንድኛየን ጨርቅ ጥየ አብጀ አይደለም፡፡
#አብማ #ማርያም ላይ የእኔን ጽሑፍ ፕሪንት አድርጎ መድረክ ላይ ያነበበው
አካል “እኛ ተዋሕዶዎች ነን፡፡ ቅባት የሚባል እምነት የለም፡፡ ካለም ራሱን ይፈትሽ፡፡ የሰበካ ጉባዐየ መታወቂያችሁን አውጥታችሁ
እዩት እስኪ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እንጅ ኦርቶዶክስ ቅባት ይላል እንዴ” በማለት ቅባትን እንደማያውቁ አድርገው ተናግረዋል፡፡ ድከሙ
ቢላችሁ እንጅ ህዝቡ እኮ ይህን ልዩነት ያወቀው ድሮ ነው፡፡ ቆጋ ኪዳነ ምሕረት ወልደ አብ እና ምሥጢረ ሃይማኖት የተሰኑ የቅባት
የክህደት መጻሕፍት ሲታተሙ አልሰሙም አላዩምን ካልሰሙ ካላዩ ችግር አለ፡፡ ቅባት የለም የሚለው አነጋገር ተቀባይነት ባይኖረውም
ከተዋሕዶ ውጭ ሌላ የለም ብለው በመናገራቸው ግን አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ምን ያህል ውስጣቸውን እንደኮረኮርሁት የተረዳሁም ያኔ ነው፡፡
የሰበካ ጉባዔው መታወቂያማ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” እንደሚል ይታወቃል ምክንያቱም ይህን ያሳተመችው ጥንታዊቷ
ቤተክርስቲያናችን ናትና፡፡ የእኔስ ጠብ ምን ሆነና ነው፡፡ እኔ እኮ የማላዝነው ለምን በቤተክርስቲያናችን ስም ይነገድብናል ብየ
እንጅ ራሱን ችሎ ለሄደውማ መብቱ ነው አምላክ የፈቀደለት እኮ ነው፡፡ መታወቂያ ደግሞ ሥምን እንጅ ግብርን የሚገልጥ አይደለም፡፡
አባታችን አቡነ ማርቆስ ሲያስተምሩ #ቅባት #ተዋሕዶ #ካራ #ጸጋ የሚባል እምነት የለም ይህ እኮ ቃል ነው ቃል ሃይማኖት ይሆናል
እንዴ ብለው ማመን ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተወለደ ብሎ ነው ክርስቲያን መባል እንጅ #ቅባት #ተዋሕዶ #ካራ #ጸጋ መባል አያስፈልግም
ብለው አስተምረዋል፡፡ የዚህንም ቪዲዮ አያይዠላችኋለሁ ስሙት፡፡ ታዲያ እርሳቸው ሊቀ ጳጳስ የሚባሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተክርስቲያን አይደለምን ነው እንጅ፡፡ ታዲያ መታወቂያቸው ግብራቸውን እምነታቸውን ገለጠላቸውን አልገለጠላቸውም፡፡ መጠራት በማይፈልጉት
ስም እኮ ነው እየተጠሩ የሚገኙት፡፡ ስለዚህ አሁንም ራሳችንን እናት ራሻችንን እንፈትሽ፡፡ የንስሐ አባት እንዲሆኑኝ ከፈለጉ የግድ
በሃይማኖት እኔን መምሰል አለባቸው፡፡ በእጃቸው እንድቆርብ ከፈለጉ እምነታቸው እኔን መመስል አለበት፡፡ ልጆችን ክርስትና እንዲያነሡ
ካስፈለግ በመጀመሪያ እምነታቸው እኛን መምሰል አለበት ፡፡ እኔ አሁንም ወደፊትም አቋሜ ይኼው ነው፡፡ ይህንን አቋም የምይዘው ደግሞ
ዝም ብየ ሳይሆን ሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት አድርጌ የአባቶቻችንን ትምህርት ምክንያት አድርጌ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ የእምነት
ልዩነት ያልገባው ሰው በኅሊናው ንጹሕ ስለሆነ ቢቆርብ፣ ቢጸልይ፣ ቢሰግድ፣ ንስሐ ቢገባ በረከቱን ማንም አይቀማውም፡፡ እኔም እኮ
ይህንን እንድጽፍ ያደረገኝ ይኼው ነው፡፡ በፊት ልዩነቱን ሳላውቀው በረከትን አገኝበት የነበረውን ነገር ዛሬ ላይ በረከትን አጣሁበት
የበረከቴ አክሊል ከሰማይ ወርዳ እኔ ላይ ሳይሆን በንጹኅ ኅሊና ላስቀደሰው ሰው ተደረበችለት ነው፡፡ እዚህ ያስቀደሰ በረከትን አያገኝም እዚህ የቆረበ ዋጋ የለውም እዚህ የጸለየ
ኃጢአት ሰርቷል አላልኩም እኮ ወገኖቼ በደንብ አንብቡት እንጅ፡፡ ሳጠቃልል የተጠቀምሁበትን ቃል እነሆ አንብቡት፡፡
“ነጭ ነጠላውን አጣፍቶ መብሩቁን ለብሶ በጠዋቱ ተነሥቶ ቤተክርስቲያን ገብቶ ጸሎትን ጨርሶ ኪዳን አስደርሶ
ቅዳሴውን አስቀድሶ ቆርቦ መመለስ ምንኛ ውብ ነገር ነበር፡፡ ግን ምን ይሆናል አይ አለመታደል! ሁል ጊዜ የበረከት አክሊሌ ተንጠልጥላ
ትታየኛለች፡፡ ይችን አክሊል እንዳልቀዳጃት በቦታው የለውም ስለዚህም ይች አክሊል ለሌላው ትደረብለታለች ትጨመርለታለች፡፡ ይህ ሀገረ
ስብከት መቼ ይሆን ከዚህ ሁሉ ነገር ነጻ ወጥቶ በአባቶቻችን እየተባረክን በጸሎታችሁ አስቡን እያልን የምንባረከው” የሚል ነው፡፡
እዚህ ላይ ልብ በሉ “ይችን አክሊል እንዳልቀዳጃት በቦታው የለውም ስለዚህም ይች አክሊል ለሌላው ትደረብለታለች ትጨመርለታለች”
ነው ያልሁት ምን ማለት ይመስላችኋል፡፡ እኔ ይህ ልዩነት ኅሊናየ ውስጥ ሙግት ስለፈጠረብኝ በቦታው አልተገኘሁም በቦታው ባለመገኘቴም
ለእኔ የወረደችውን አክሊል አልተቀዳጀኋትም ስለዚህም ለሌላው ተጨመረችለት ማለቴ ነው፡፡ ለሌላው የሚጨመርለት እኮ በረከትን ስላገኘበት
ነው፡፡ እያስተዋልን እናንብብ እንጅ!
#ግምጃ #ቤት #ኪዳነ #ምሕረት ቤተክርስቲያን ግን የተላለፈው መልእክት
በፍጹም እኔ ያላልሁት እነርሱ ብቻ የሚያውቁት ሀሳብ ነው፡፡ በእርግጥ እነርሱ ያሉትን ጉዳይ እኔም ሰምቸዋለሁ ቀድሜ አውቄዋለሁ
ሆኖም ግን አደባባይ ላይ የምለጥፈው ሃሳብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ እኔ ያልሁትን ብላችሁ እንድነቀፍ እና እንድወገዝ ብታደርጉ
በተሸለ ነበር፡፡
#ገዳመ #ሕያዋን #ቅዱስ #ሚካኤል ቤተክርስቲያንም እንደ አብማው ተመሳሳይ
የሆነ ነገር ነው የተናገሩት፡፡ ሆኖም ግን እነርሱ የተረዱበት እና እኔ የጻፍሁበት መንገድ እና ስልት ለየቅል መሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡
በፌስ ቡክ የአባታችንን ስም እያጠፋሁ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ እኔ እርሳቸው ያላሉትን እርሳቸው ያልተናገሩትን ነገር በራሴ ፈጥሬ
ጽፌ ከሆነ ከላይ አንገቴን ከታችም ባቴን ቁረጡኝ፡፡ ይኼው ከዚህ ጋራ የተያያዘውን እንኳ ተመልከቱት እስኪ፡፡
#የዛሬው ደግሞ ይባስ #ገዳመ #አስቄጥ #አቡነ #ተክለሃይማኖት ዛሬ
በተከበረው የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት በዓል ላይ #ሊቀ #ሊቃውንት #ሰሎሞን ይህንኑ ተመሳሳይ መልእክት ሲያስተጋቡ መዋላቸው
አስደነቀኝ፡፡ ምን አደረጋችሁ ተብለው ሲጠየቁ እኔ ከላይ ታዝዠ ነው በማለት ሲመልሱ ደግሞ ይበልጥ በሳቅ ፈረስሁ፡፡ አይ! ወይኔ!
እርስዎም እንዲህ የእሳት ልጅ አመድ ይሆኑ! ከልቤ አዝንብዎታለሁ፡፡ ራስዎን ጥለው ጎስቁለው ስመለከትዎ ስለቤተክርስቲያናችን እየተጨነቁ
ይመስለኝ ነበር ለካ ጭንቀትዎ ከላይ የሚመጣልዎ ትእዛዝ ነው፡፡ እስከ ላይ እስከ ሀገረ ስብከቱ ድረስ እንዲህ መነጋገሪያ ያደረጋችሁኝ
ግን ምን ሳስተምር አግኝታችሁኝ ነው፡፡ እኔ ግን ከላይ ከአቡኑ እስከታችኛው ድረስ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ ምን እያስተማራችሁ እንደሆነ
የሚያሳይ ሙሉ መረጃ አለኝ፡፡ ግን አሁን አላወጣውም ምናልባትም ከወዴት እንደቆመ አስቦ ራሱን ለቤተክርስቲያን እውነተኛ አገልግሎት
አሳልፎ የሚሰጥ ሊሆን ይችላልና በትእግሥት እጠብቃለሁ፡፡
#ሊቀ #ሊቃውንት #ሰሎሞን የቅባትን ጉዳይ ያግዙናል ብለን ተስፋ ካደረግንባቸው
ሊቃውንት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ እኔ ከላይ እስከ ታች አውቃቸዋለሁ እርሳቸው ግን ከነመፈጠሬም አያውቁኝም ዛሬም ስሜን አሸምድደዋቸው
ካልሆነ በቀር በጭራሽ አያውቅኝም፡፡ “ወልደ አብ” እንደታተመ መልስ ይሰጡበታል ብለን መጽሐፉን ገዝተን ሰጠናቸው በዚያው የውኃ
ሽታ ሆነው ቀሩ፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ “ሚሥጢረ ሃይማኖት” የሚለው ሁለተኛው መጽሐፋቸው ሲታተም እንዲሁ ገዝተን እንድንሰጣቸው
በብርቱ ሲጥሩ ነበር፡፡ እኛ ግን ማንነታቸውን በሚገባ ስለተረዳን ሳንቲማችንን ማባከን አልፈለግንም ነበር፡፡ ዛሬ ግን “መልካሙ
በየነ” ስለቅባት የሚጽፈው ሁሉ ውሸት ነው ለማለት በቁና አረፉት፡፡ የዚህ ንግግራቸው እና የሌሎችንም እንዲሁ በምስል አቀናብሬ
የምልክላችሁ ይሆናል፡፡
በነገራችን ላይ ስማቸውን ወደፊት የምንገልጻቸው አንድ የገዳሙ የሰበካ
ጉባዔ አባል “ልጆቻችን ለምን በእኛ ላይ ተነሡብን ብላችሁ ራሳችሁን ፈትሹ” ብለው አባቶችን የገሰጹበት የዛሬው ንግግራቸው ወደ
እውነት ልንቀርብ ትንሽ ዳገት ብቻ እንደቀረችኝ ማሳያ ነው፡፡ የነገውን ደግሞ ማን ያውቃል ሁላችሁም ጸልዩልን!!!
ምንም በሉኝ ምን ግን በጣም ደስ የሚለኝ ነገር ቅባቶች በድብቅ የሚያካሄዱትን
ሴራ አደባባይ ላይ አውጥቼ ለተዋሕዶ ልጆች ግንዛቤ መፍጠሬ ነው፡፡ ደብረ ማርቆስ ከተማ እኮ ጥቂት የሚባሉ ከሌላ ቦታ እዚህ እንዲያገለግሉ
የተመደቡት ናቸው እንጅ ማኅበረሰቡማ እናውቀዋለን እኮ ጽድት ያለ ተዋሕዶ ነው፡፡ ለመቁረብ የሚያስቸግረው አንዳንድ የቅባት ካህናት
አብረው ስለሚቀድሱ ነው እንጅ የማርቆስ ሕዝብማ እያነው እኮ ነው፡፡ ሌት ከቀን ተዋሕዶ ተዋሕዶ ሲል የሚውል ምርጥ የእመብርሃን
ልጅ እኮ ነው፡፡ ከዚህ ህዝብስ በምንም ልትለዩኝ አትችሉም በፍጹም እኛ እና እነርሱ ተግባብተናል ያልተግባባነው ከቅባቶቹ ጋር ብቻ
ነው፡፡
No comments:
Post a Comment