© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 8/2009
ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት (
facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/tomarthetewahido ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================
ከአንድ ቤተ ክርስቲያን በር አጠገብ ሳለሁ “በማየታችን ተጎድተናል፡፡ አዎ በጣም ችግር ውስጥ ወድቀናል” አሉ አንድ ሽማግሌ ሰው፡፡ ነገሩ ስላልገባኝ እብድ ናቸው እንዴ ብየ በውስጤ አሰብኩ፡፡ እርሳቸው ግን ልቤ በጎ ነገርን አወጣ ብሎ በከሳሾቹ እና በናቁት ፊት አዲስ ምስጋናን እናዳፈለቀው አባ ሕርያቆስ ልቡናቸው በጎ ነገርን ያፈለቀላቸው ሰው ናቸው፡፡ “ማየት እና መመልከት ለየቅል ናቸው” አሉ፡፡ ይህን ጊዜ እርሳቸው ረቂቅ ምሥጢር የተገለጠላቸው ልዩ ሰው መሰሉኝና ጉዳየን ሁሉ ወደኋላ ጣል አድርጌ ጆሮየን አዘነበልሁላቸው፡፡ እርሳቸው የሚናገሩትን መስማት ሳይማር መድረክ ላይ ወጥቶ ወዮልሽ ኮራዚን ወዮልሽ ቤተሳይዳ እያለ ከሚያሸብር ሰባኪ ይልቅ የተሻለ ስለመሰለኝ ሙሉ ቀልቤን ለእርሳቸው ሰጥቻለሁ፡፡
“ማየት የአፍአ ነው መመልከት የውስጥ ነው፡፡ ማየት በውጫዊው
ዓይን ነው መመልከት ግን በውስጣዊው ዓይን ነው” አሉ፡፡ አንድ አልፎ የሚሄድ ሰው “ማየት በውጫዊ ዓይን ነው የሚሉት ልክ ነው
መመልከት በውስጣዊ ዓይን ነው የሚሉት ግን ተረት ተረት መስሎ ታየኝ፡፡ የውጫዊ ዓይን አለን ሁሉም ያየዋል ይመለከተዋልም የውስጥ
ዓይን ግን የት ነው ያለ ይኼ እንግዳ ነገር ነው የሆነብኝ” አለ፡፡ እርሳቸውም በትህትና ማስረዳታቸውን ቀጠሉ፡፡ “ውጫዊ ዓይን
መኖሩን ያመንክ ስላየኸው ነው ውስጣዊውንም ዓይን የተጠራጠርከው ስላላየኸው ነው፡፡ ነፋስ አይታይም አይጨበጥም አይዳሰስም ረቂቅ
ነው ታዲያ ስላላየሁት ነፋስ የለም ብለህ ልትደመድም ትችላለህን፡፡ ፈጣሪህን አይተኸው ታውቃለህን! ታዲያ አይተኸው ስለማታውቅ ፈጣሪ
የለም ልትል ነውን፡፡ በፍጹም እንዲህ ማለት አይገባህም” አሉ፡፡ ይኼኔ አልፎ የሚሄደው ሰው “በቃኝ በቃኝ ገብቶኛል እርስዎ ነገር
የሚቻሉ ሰው አይደሉም፡፡ በሉ ደህና ሁኑ” ብሎ እየተገረመ ትቷቸው ሄደ፡፡
እርሳቸው ግን ቀጠሉ፡፡ “ይኼ ከግንባራችን ላይ ያለው ዓይን
እኮ ማየት እንጅ መመልከት አያውቅም፡፡ ትልቁ ዓይን የልቡና ዓይን ነው፡፡ ይህ የልቡና ዓይን ያያል ይመለከታልም፡፡ ስለዚህም ይህንን
ዓይን መጠበቅ ይገባል፡፡ የውጫዊው ዓይንማ ቢጠፋስ ምን ችግር አለው፡፡ መንግሥተ ሰማያት መግባት የሚከለክለው እኮ የልቡና ዓይን
እውርነት እንጅ የውጫዊው ዓይን እውርነት አይደለም፡፡ ወንጌል እንዲያውም ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ጣላት ሁለት ዓይን ይዘህ
ሲዖል ከምትገባ ዓይን ሳይኖርህ ገነት መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻላል ይላል፡፡ ስምዖን የተባለ ጫማ ሰፊ ይህንን በተግባር ቃል
በቃል ፈጽሞታል፡፡ ዓይኑን ጫማ በሚሰፋበት ወስፌ እኮ ነው አውጥቶ የጣላት፡፡ አየህ የሥጋህ ዓይን አለማየቱ ገነትን አይከለክልህም
የልቡናህ ዓይን አለማየቱ ግን ሲዖል ያስገባሃል፡፡ ስለዚህ የልቡናህ ዓይን እንዲበራልህ ፈጣሪህን ዕለት ዕለት መለመን አለብህ”
አሉ፡፡ እነኝህ ሰው በጣም የተማሩ ምሥጢር የጠነቀቁ ስለመሰሉኝ ጆሮየን ይበልጥ ሰጠኋቸው፡፡
“በጣም የሚገርም ታሪክ ልንገራችሁ፡፡ አንድ ወቅት አንድ ሺህ
ብር ለቤተክርስቲያን ልሰጥ ተነሣሁ፡፡ ከዚያ እኔም ራሴ ሄጀ እንዳላስገባ ከንቱ ውዳሴውን ፈራሁ፡፡ አሁን የምነግራችሁ እንድትማሩበት
ብየ ነው እንጅ ከንቱ ውዳሴ ሽቸ አይደለም፡፡ እና ብሩን ይዤ ስጠባበቅ አንድ ዓይነ ሥውር ምድሩን በዘንጋቸው እየደበደቡ መጡ፡፡
ይኼኔ አባቴ! ይህን ብር እዚያ ሙዳየ ምጽዋቱ ሥር ላሉት የሰበካ ጉባዔው አባላት ይስጡልኝ አልኳቸው፡፡ እርሳቸውም ቆጥረው ተቀበሉኝ፡፡
ዐሥር ብር ነው አሉኝ፡፡ አያችሁ አይደል አለማየታቸው እንዴት እንደጠቀማቸው፡፡ እርሳቸው የቆጠሩት የቅጠሉን ብዛት እንጅ እያንዳንዱ
ቅጠል ስንት ብር እንደሆነ አላወቁም፡፡ ቢያዩት ኖሮ እኮ አንድም ገንዘቡን ለራሳቸው ለማድረግ በተመኙ ነበር፡፡ አንድም ይህን ያህል
ብር እንዴት ትሰጣለህ ብለው በከንቱ ውዳሴ በጠለፉኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለማየታቸው እሽ ብለው እንደ ዐሥር ብር አንጠልጥለው
ወሰዱት” አሉ፡፡ እርሳቸው እየተናገሩት ያለው ነገር ገብቶኛል፡፡ ዓይነ ሥውሩ ዐሥር ብር ነው ብለው የቆጠሩት አንዱን ድፍን መቶ
ብር እንደ አንድ ብር ቆጥረውት ነው፡፡ ምክንያቱም አያዩማ! ቢያዩ ኖሮማ አንድ ሽህ ብርን ዐሥር ብር ነው ባላሉም ነበር፡፡
“ከዚያ እኒያ ዐይነ ሥውር ሰው እንደዐሥር ብር ጠቅልለው ለሰበካ
ጉባዔው አባላት አስረከቡ፡፡ ይህን ጊዜ አንድ ሽህ ብር! እርስዎ ነዎት ይህን ገንዘብ ገቢ ያደረጉ? እግዚአብሔር ይስጥልን አሏቸው፡፡
ያንጊዜ እኒያ ዐይነ ሥውር ለካ የመቶ ብር ቅጠሎችን ነው እንደ አንድ ብር ስቆጥር የነበረው፡፡ እኔ እኮ ዐሥር ብር ያስገባሁ መስሎኝ
ነው፡፡ የአንድ የአንድ ብር ቅጠል መስሎኝ ዐሥር ብር ቆጥሬ መስጠቴ ነበር ለካ የመቶ የመቶ ብር ነበር እንዴ እንዲህ የቆጠርሁት፡፡
በጣም ይቅርታ የደብራችን ሰበካዎች እባካችሁ ዐሥር ብር አስቀርታችሁ ትርፉን መልሱልኝ አሉ፡፡ የሰበካው አባላትም ዘጠኝ መቶውን
መልሰው ከመቶው ብር ላይ ዐሥር ብር ሊቆርጡ እየቆጠሩ ሳለ አባቴ ምነው እንዲህ ያደርጋሉ? የእርስዎ ያልሆነውን ገንዘብ እንዴት
የእኔ ነው ብለው ሊወስዱ ይደፍራሉ፡፡ ያውም የተወለዱበትን ደብር ገንዘብ ብየ እውነቱን ገለጥሁላቸው” አሉ፡፡ በጣም የሚገርም ታሪክ
ነው እየነገሩን ያለው፡፡ አባታችን ከዚያ በኋላ ምን ተፈጠረ ስል ጠየቅኋቸው እርሳቸውም መለሱልኝ፡፡ “ከዚያማ ዓይነ ሥውሩ በጣም
ደነገጡና በፊት እኮ በፍጹም ልቤ ገቢ ላደርገው የነበረው ዐሥር ብር እንደሆነ በልቤ ስለተመለከትሁ ነው፡፡ ዓይኔ ስለማያይ በፍጹም
እምነት ነበር ወደ ሰበካችን ገቢ ያደረግሁት፡፡ አንድ ሽህ ብር መሆኑን የነገሩኝ እነርሱ ናቸው፡፡ አንድ ሽህ ብር ነው ሲሉኝ ልቤ
ክፉን ነገር ተመለከተ፡፡ የውስጡ ዓይኔ በራልኝ፡፡ አንድ ሺህ ብር መሆኑን ተመለከተብኝ፡፡ ታዲያ አንድ ሺህ ብር እዚህ ከምጥል
ዐሥር ብር መስሎኝ ነው ብየ በአፍአዊው ዓይኔ አለማየት ምክንያት ፈጠርሁ፡፡ ዓይኔ ቢያይ ኖሮ እኮ አንዱን ሺህ ብር ዐሥር ብር
መስሎኝ ነው ብል አያምኑኝም ነበር ዘጠኝ መቶ ዘጠና ብርም ሊመልሱልኝ አይችሉም ነበር አለን” አሉ፡፡ በእውነት በጣም የሚገርም
ነገር ነው፡፡
ለካ በማየታችን ተጎድተናል ባለማየታችንም ተጠቅመናል አልሁ በልቤ፡፡
አለማየት ደግነት ነው አለመመልከት ድህነት ነው፡፡ ባለማየታችን ገንዘቡን ወረቀት ነው ብለን ንቀን ወርውረነዋል፡፡ ባለማየታችን
በመልካቸው በውበታቸው በሚመኩ ሰዎች በሐጸ ዝሙት አልወደቅንም፡፡ ባለማየታችን የቀዩን ውበት ከጥቁሩ ውበት መለየት አልቻልንም፡፡
ባለማየታችን በምግብ አመራረጥ ላይ ጊዜ አላባከንንም፡፡ ባለማየታችን ልብስ አላማረጥንም ያገኘነውን ሁሉ እንለብሳለን እንጅ፡፡ ባለማየታችን
ከኃጢአት በብዙ መልኩ ተቆጥበናል፡፡ በማየታችን ግን ብዙ ተጎድተናል፡፡ በማየታችን እንዘላለን ስንል ተሰብረናል፡፡ በማየታችን ፈተና
ኮርጀን የሀገር የወገን ሸክም ሆነናል፡፡ በማየታችን በሐጸ ዝሙት ተነድፈናል፡፡ በማየታችን ከማን አንሸ በሚል ስንቱን አድርገናል፡፡
በማየታችን ተጎድተናል፡፡
በማየታችን የተጎዳነው ባለማየታችንም የተጠቀምነው ማየታችንን
ለክፉ ሥራ አለማየታችንንም ለበጎ ነገር ካዋልነው ብቻ ነው፡፡ ማየታችን ሁሌ አይጎዳንም አለማየታችንም ሁሌ አይጠቅመንም፡፡ ስለዚህም
ከማየት እና ካለማየት ይልቅ መመልከት ላይ እናተኩር፡፡ ውጫዊውን ያደለ ውሳጣዊውን ዓይናችንን ያበራልን ዘንድ ፈጣሪያችንን እንለምነው፡፡
የውዳሴ ማርያም መክፈያው ሰዓ(አ)ሊ ለነ ቅድስት ሲተረጎም አልሰማችሁም፡፡ ጽንእት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን
ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝለን፡፡ አእምሮውን ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን የሚል ነው፡፡ በልቡናችን ሳይብን የምንለው
ምንድን ነው ካልን አንዱ የልቡና ዓይን ነው፡፡
No comments:
Post a Comment