Sunday, August 6, 2017

የጌታ ፈቃድ ይኹን ብለን ዝም አልን ሐዋ 21÷14



© መልካሙ በየነ

ነሐሴ 1/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/tomarthetewahido ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================
ይህን ድንቅ ቃል ሐዋርያት ተናግረውታል፡፡ ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን መንፈስ ቅዱስን በእሳት አምሳል ተቀብለው የሰማይ እና የምድር ምሥጢር ተገልጦላቸው በድፍረት ያለፍርሐት ስለክርስቶስ አምላክነት ያስተምሩ ነበር፡፡ እነርሱ ይናገሩት ከነበረው ቋንቋ በተጨማሪም ሌላ 71 ያህል ቋንቋ ተገልጦላቸው የተሰበሰበው ህዝብ ሁሉ በሚሰማው በፈለጉት ዓይነት ቋንቋ አስተምረዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ባስተማረው ትምህርት 3000 ነፍሳት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ተመልሰዋል፡፡ ጴጥሮስ በልቡ አምኖ በአፉ የካደ ሐዋርያ ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ጭፍሮች በተያዘ ጊዜ በሐዋርያት ዘንድ ከፍተኛ ፍርሐት እና ድንጋጤ ተፈጥሮባቸው ነበር፡፡ ይህንንም ወንጌል በሰፊው ይነግረናል፡፡ ጨርቁን ጥሎ የሮጠ ሐዋርያ እንደነበር ከዚህም በተጨማሪ በየሰፈሩ እየተሸሸጉ ከአይሁድ ጭፍሮች ለማምለጥ ሞክረው ነበር፡፡ ጴጥሮስም በተመሳሳይ መልኩ እሳት አንድደው ይሞቁ ወደ ነበሩት ሰዎች ቀርቦ አብሮ እሳት ይሞቅ ነበር፡፡ ከዚያም አነጋገሩን ተረድተው አንተ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር አልነበርህምን ብለው አፈጠጡበት፡፡ ጴጥሮስ ግን በፍጹም የምትሉትን አላውቅም አለ፡፡ ይህንንም ሦስት ጊዜ ደጋገመው ያን ጊዜ ነበር ዶሮ ሲጮኽ ጴጥሮስ አምላክን በአፉ እንደካደ የተረዳ፡፡ ወዲያውኑም አምላኬ ይቅር በለኝ ብሎ ምርር ብሎ አለቀሰ፡፡ እንግዲህ ይህንን ታሪክ ማንሣት ያስፈለገው ከዚህ ፍርሐታቸው ሁሉ ተላቀው ድፍረትን አግኝተው ያለፍርሐት በአደባባይ ስለጌታችን ማስተማር የጀመሩት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ነበር ለማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ደካሞች ሁሉ በረቱ፣ ፈሪዎች ሁሉ ደፋር ሆኑ፣ ምሥጢር ያልጠነቀቁት ሁሉ የሰማይ የምድር ምሥጢር ተገለጠላቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ የጌታ ፈቃድ ይኹን ብለን ዝም አልን ማለት የተገባቸው ሆኑ፡፡


ሐዋርያት ወንጌል ወዳልደረሰበት ዞረው ለማስተማር  ዕጣ በዕጣ ሲካፈሉ የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት አምልኮተ እግዚአብሔርን ለማስፋት አምልኮተ ጣዖትን ለማጥፋት ሲተጉ የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት  በእስር ቤት ሲጣሉ የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት ሲራቡ ሲጠሙ ሲቸገሩ መከራ ሲጸናባቸው የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት እንደ ሽንኩርት ሲከተፉ እንደ ጎመን ሲቀረደዱ የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት የቁልቁሊት ሲሰቀሉ  የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት ቆዳቸውን ገፈው ሌጦ ሲያወጧቸው የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት  ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች ሲላኩ የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት  እንደ አክርማ ሲሰነጠቁ የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት በሰይፍ በስለት ሲያስፈራሯቸው የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት  ወደ ሞት እየተጓዙ የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት እንደበሬ ሳር ካልበላችሁ ብለው ሲያንገላቷቸው የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡  ሐዋርያት መርከባቸው ተሰብሮ በባሕር ሲያድሩ የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡ ሐዋርያት ስለሆነላቸው ስለሚሆንባቸው ስለተደረገላቸው ስለሚደረግባቸው ነገር ሁሉ የጌታ ፈቃድ ይኹን አሉ፡፡


ዛሬስ እኛ ይህንን ቃል በቀን ስንት ጊዜ እንናገረው ይሆን? ግን የምንናገረው በአፋችን እንጅ በልባችን አምነን አይመስለኝም፡፡ ከልባችን በመነጨ እውነተኛ እምነት እንደ ሐዋርያት  የጌታ ፈቃድ ይኹን የምንል ከሆነ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከልባችን አምነን ነው የምንናገረው እንዳንልማ ይህንኑ በተናገርንበት አፋችን “ፈጣሪ ቢኖርማ ይህ አይደረግም ነበር” ስንል እንደመጣለና፡፡ ያም ሆነ ይህ ወደድንም ጠላንም የሚደረገው ነገር ሁሉ ከእኛ አይደለም ከፈጣሪ ብቻ ነው እንጅ፡፡ ይህንንም ዮሐ15÷5 ላይ ራሱ ባለቤቱ “ያለእኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ብሎናል፡፡ ስለዚህ የሚሆነው ሁሉ ከእርሱ የሚሆን እርሱ ፈቅዶ የሚደረግ እንጅ እኛ እንደወደድን የምናደርገው ነገር ከቶ የለም፡፡ በምንም በሉት በምን ለእኛ የተደረገው ሁሉ ከአምላካችን የተደረገልን ፈቃድ እንጅ በራሳችን ያደረግነው ነገር አይደለም፡፡ ከፈጣሪ ተሰውረን የምናደርገው አንዳች ነገር የለም፡፡ ዝሙት ብንፈጽም፣ ብንገድል፣ ብንሰርቅ፣ ጉቦ ብንሰጥ ብንቀበልም፣ መረጃዎችን ብንሰርዝ ብንደልዝም፣ ያለንን የለንም ብለን ብንደብቅ ምንም በሉት ምን ሁሉን ብናደርግ እርሱ ፈቅዶ ብቻ ነው፡፡ የእርሱ ፈቃድ ካልሆነ ምንም ልናደርግ አንችልም፡፡ እኛ ለመወፈር ሌሊት ከቀን እንደ ነቀዝ እንመገባለን እርሱ ግን እንደ ሸንበቆ ያቀጥነናል፡፡ እኛ ለመክሳት ከምግብ እንርቃለን እርሱ ግን እንደከበሮ ያድበለብለናል፡፡ እኛ በሽታ እንዳይነካን ንጽሕና ንጽሕና ስንል እንውላለን እርሱ ግን የአልጋ ቁራኛ አድርጎ ያስተኛናል፡፡ እኛ ለመሞት ገመድ ላይ እንጠለጠላለን እርሱ ገመዳችንን በጥሶ ሽሕ ዘመን ያኖረናል፡፡ እኛ ለመግደል መሣሪያችንን ታጥቀን እንሰለፋለን እርሱ ዳዊትን አስነሥቶ በጠጠር ይገድለናል፡፡ እኛ ለመታረድ እንነዳለን እርሱ ግን የታሰረውን በግ ስለእኛ ያቀርባል፡፡ እኛ ከቤተክርስቲያን ለመሸሽ እናቅዳለን እርሱ ደግሞ የመቅደሱ አገልጋይ አድርጎ ይሾመናል፡፡ እኛ ምሥጢር አዋቂዎች ለመሆን ሥር እንምሳለን ቅጠል እንበጥሳለን እርሱ አእምሮ ነስቶ ልብስ ያስጥለናል፡፡ እኛ ለመሞት እናቅዳለን እርሱ ለሕይወት ያቅድልናል፡፡ እኛ ለኃጢአት እናቅዳለን እርሱ ለንስሐ ያቅድልናል፡፡ እኛ ለመብላት እንወስናለን እርሱ ደግሞ አፋችንን ዘግቶ ከምግብ ያርቀናል፡፡ እኛ ገንዘባችንን እናጠራቅማለን እርሱ በብል በዝገት ያጠፋብናል፡፡ እኛ በጉልበታችን እንመካለን እርሱ በጠጠር ይጥለናል፡፡ እኛ በውበታችን እንመካለን እርሱ በበሽታ ያጠፋብናል፡፡ እኛ ሌት ከቀን እርሱን ለመቃወም እንተጋለን እርሱ እጅ እግራችንን አስሮ ምርጥ ዕቃ ናችሁ ይለናል፡፡ እኛ በዝሙት በርኩሰት በመዳራት እንባክናለን እርሱ ኃጢአታችሁ ተሰርዮላችኋል ዳግመኛ አትበድሉ ብሎ ይመርጠናል፡፡ እኛ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ እንሮጣለን እርሱ ግን ለቤቱ መርጦ ይሾመናል፡፡ እኛ ሚስት አግብቶ ልጅ ወልዶ በዓለም መኖር ስንመኝ እርሱ  ለምንኩስና ይመርጠናል፡፡ እኛ ለምንኩስና ደጅ ስንጠና እርሱ በትዳር ይወስነናል፡፡ እኛ ለዛሬ ስንል እርሱ ለዓመት እኛ ለዓመት ስንል እርሱ ለዛሬ ይለናል፡፡ እኛ ተስፋ ስንቆርጥ እርሱ ይቀጥልልናል፡፡ እኛ አንችልም ስንል እርሱ ሁሉን ያስችለናል፡፡ እኛ በሐብት ለመወዳደር ገንዘብ ስናካብት እርሱ መናጢ ደኃ ያደርገናል፡፡ እኛ ራሳችንን ከፍ ከፍ እናደርጋለን እርሱ ዝቅ ዝቅ ያደርገናል፡፡ እኛ በትህትና ዝቅ ዝቅ እንላለን እርሱ ከፍ ከፍ ያደርገናል፡፡ እኛ አይገባንም እንላለን እርሱ ይገባችኋል ይለናል፡፡ እኛ ይገባናል ብለን እንከራከራለን እርሱ አይገባችሁም ብሎ ያሳፍረናል፡፡ እኛ እህላችንን በጎተራ እናጠራቅማለን እርሱ ጎተራችንን አፍርሶ እህላችንን በትኖ በረሃብ አለንጋ ይቀጣናል፡፡ እኛ በተራቡት እንስቃለን እርሱ በረሃብ ያስለቅሰናል፡፡ እኛ በስልጣናችን ከሥራ እናባርራለን እርሱ በስልጣኑ ከምድረ ገጽ ያባርረናል፡፡

አረ ምን ልብል! በእውነት የጌታ ፈቃድ ይኹን ብለን ዝም አልን እንበል ሁላችን፡፡ ያለእርሱ ምንም አናደርግምና፡፡ እኛ ግራ ስንል እርሱ በቀኝ በኩል ያደርገናል፡፡ በየትም በሉ በየት ያለእርሱ ምንም አናደርግም ምንም!!!

=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment