Sunday, December 10, 2017

መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? ክፍል ፲፮--ተፈጸመ



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፵፯ ጀምረን  እስከ መጨረሻ ገጽ ድረስ ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
ይህ የመጨረሻየ ክፍል ስለሆነ እስከ ረቡዕ ድረስ ቀስ ብላችሁ ተረጋግታችሁ እንድታነቡት ሰፋ አድርጌ ነው የጻፍሁላችሁ፡፡ ረዘመ እንዳትሉኝ ከወዲሁ እጠይቃለሁ፡፡
********************************

ዛሬ በዋናነት ስለጾመ ነቢያት እና ጾመ ሐዋርያት፣ ስለጥምቀት እና ስለጌታ ሁለት ልደታትት እንመለከታለን፡፡ ካሳሁን ምናሉ እና ሌሎችም የቅባት እምነት ተከታዮች ምንፍቅናቸውን ለመደበቅ የሚጠቀሙባቸው መገለጫዎች አሉ፡፡ እነዚህም የጾም መግቢያ እና መውጫ ናቸው፡፡ ሃይማኖታዊ የሆነውን ልዩነት ወደጎን ትተው ቀኖና ላይ ሥርዓት ላይ ብቻ ክርክር ሲፈጥሩ ይታያሉ፡፡ መጽሐፍ ግን ሁሉንም ነገር በማያሻማ መልኩ ነው እየደመደመ እያሰረ ያስቀመጠው፡፡
የመጀመሪያ ካሳሁን ምናሉ ስለነቢያት ጾም ይናገራል፡፡ የነቢያት ጾም መግቢው ኅዳር ፲፱ ነው ይላል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የሚያስቀምጠው ነቢያት የጾሙት ፵ ቀናትን ስለሆነ ኅዳር ፲፱ ጀምረን ታህሳስ ፳፱ ልደትን ስናከብር ጾማችንን ስንፈጽም ፵ ቀን ይሆናል ይላል፡፡ በመጀመሪያ ጾም ማለት ቀን መቁጠር ማለት አይደለም፡፡ እስኪ ዐቢይ ጾምን ተመልከት፡፡ ጌታ የጾመው ፵ መዓልት እና ፵ ሌሊት ነው እኛ ግን ፲፭ ቀናትን ጨምረን ፶፭ ቀናትን ነው የምንጾም ለምን? ይህን እንደማትመልስልኝ አውቃለሁ፡፡
ካሳሁን እኛ የምንሰማው ሠለስቱ ምእት የተናገሩትን እንጅ አብርሃም ሶርያዊ የጨመረውን ጾም አይደለም ብሎ ቅዱሳንን የመናቅ አባዜውን አሳይቶናል፡፡ አሁንም ልብ ካለህ እስኪ ዐቢይ ጾም ላይ ጾመ ሕርቃል ለምን ተጨመረ? መልስልኝ እስኪ ሠለስቱ ምእት እኮ የወሰኑት ጌታችን ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት እንደጾመ ሁሉ እናንተም በጥንቃቄ ጹሙት ብለው ነው፡፡ ታዲያ ጾመ ነቢያት ላይ ሲሆን ልብላ ልብላ ለምን አሰኘህ፡፡ በነገራችን ላይ ወገኖቼ! ቅባቶች ሃይማኖታዊ የሆነውን ልዩነት በቀኖና ለመደበቅ እየሞከሩ እንደሆነ ልብ በሉ፡፡
ስለጾመ ነቢያት እና ስለጾመ ሐዋርያት ጥቂት እንበል፡፡ በነገራችን ላይ የእነዚህ የሁለቱም አጽዋማት መግቢያ እና መውጫ ቀናት በግልጽ የታወቁ የተደመደሙ ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በእነዚህ አጽዋማት መግቢ ላይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ይህንን የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ አልቀበልም ያለ ሰው ራሱን መለየት መብቱ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በማያገባው ገብቶ ሊፈተፍት አይችልም፡፡
ጾመ ነቢያት የገና ጾም በመባልም ይጠራል፡፡ ነቢያት እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠውን ተስፋ እየጠበቁ አምላክ ይወርዳል ይወለዳል ብለው የጾሙት ነው፡፡ ይህ ጾም በሦስቱ ዘመናት ማለትም በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ እና በዘመነ ሉቃስ ኅዳር ፲፮ ይጀምርና ታህሳስ ፳፱ ይፈሰካል፤ በዘመነ ዮሐንስ ግን ኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ ታህሳስ ፳፰ ቀን ይፈሰካል፡፡  በአራቱም ዓመታት ፵፫ ቀናትን ይጾማል፡፡ ነገር ግን ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ኅዳር ፲፭ የሚገባው ጾም ስለሚረሳ ሁልጊዜ ኅዳር ፲፭ ይጀምራል ተብሎ በቅዱስ ሲኖዶስ በማያዳግም መልኩ ተወስኗል፡፡ በዚህ የተነሣ በሦስቱ ዘመናት ፵፬ ቀናት በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ፵፫ ቀናት ይጾማሉ፡፡ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የጾሙ ቀናት በ ፩ ቀን ይቀንሳል፤ በሦስቱ ዘመናት ፵፬ ቀናትን የምንጾመው ለጾም ማድላት ተገቢ ስለሆነ ነው፡፡ ይህንንም ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፹፬  ላይ “ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል፡፡ ከመብላት በጣም ይሻላል” ብለው አዘዙን። በጾም ወቅት እንብላ እና እንጹም የሚል  ክርክር ከተፈጠረ መጾም ይሻላል ምክንያቱም ከመብላት በጣም ይሻላልና ብለው በአንድ አረፍተ ነገር አሠሩልን። ከዚህ ወዴት እንሸሻለን? እንብላበት እና እንጹምበት የሚሉ ሰዎች ቢከራከሩ እንጹምበት ያለው እንዲረታ እወቁ።

በዚህ ጾም የሚነሣው መሠረታዊ ጉዳይ ነቢያቱ ዐርባ ቀናትን ብቻ ነው የጾሙት ይህ በትርፍነት የተጨመረው ዐራት ወይም ሦስት ቀን ከየት መጣ የሚል ነው፡፡ ለዚህ መልሱ፡-
፩ኛ. ፍትሐ ነገሥቱ  አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፰ ላይ “ከእነርሱም የሚያንስ እንደ ረቡዕና እንደ ዓርብ የሚሆን አለ፡፡ ይኸውም ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው፡፡ መጀመሪያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የገና በዓል ነው” በማለት መዝግቦት እናገኘዋለን፡፡ የዚህን ጾም መግቢያ ሲገልጽ የኅዳር እኩሌታ ስላለ ነው፡፡ የህዳር እኩሌታ ደግሞ ፴ ለሁለት ተክፍሎ ግማሹ ወደታች ግማሹ ወደ ላይ ሆኖ ነው፡፡ በዚህም መሠረት መንፈቅ የምንለው ህዳር ፲፮ን እንጅ ህዳር ፲፱ አይደለም፡፡
፪ኛ. ስንክሳሩ ኅዳር ፲፭ “ወበዛቲ ዕለት ጥንተ ጾመ ስብከተ ጌና ዘውእቱ ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት ዘሠርዕዎ ክርስቲያን ያዕቆባውያን ዘግብጽ፤ በዚችም ቀን የስብከተ ጌና ጾም መጀመሪያ ነው፡፡ ይህም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተወለደበት በግብጽ የሚኖሩ ያዕቆባውያን የሠሩት ነው” በማለቱ የህዳር እኩሌታ የሚለው በግልጽ ኅዳር ፲፭ ነው እንላለን፡፡ ስንክሳሩ ኅዳር ፲፱ን “ወበዛቲ ዕለት ኮነ ጾመ ስብከተ ጌና ዘሮም ወአፍርንጊ ወሶርያ ወአርማንያ ዘእንበለ ግብጽ ወኢትዮጵያ ወኖባ፤ በዚችም ዕለት የሮም፣ የአፍርንጊ፣ የሶርያ፣ የአርማንያ ክርስቲያን ከግብጽ ከኢትዮጵያና ከኖባ በቀር የስብከተ ጌና ጾምን የሚጀምሩበት ነው” ይለዋል፡፡

፫ኛ. ሐዋርያው ፊልጶስ ኅዳር ፲፮ በሰማእትነት ካሳረፉት በኋላ ሥጋውን ሊያቃጥሉ ሲነሡ መልአከ እግዚአብሔር ሥጋውን ሰወረባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ከዕለቱ ጀምረው ፫ ቀናትን እንደጾሙ  በኅዳር ፲፰ ሥጋውን ሰጣቸውና ቀበሩት፡፡ ስለዚህም ሦስቱ ጾም ጾመ ፊልጶስ ተብሎ ተጨመረም የሚሉ አሉ፡፡

 

፬ኛ. በዓለ ልደት ረቡዕና ዓርብ ቢውል ይበላበታልና ለዚያ ማካካሻ ወይም ምትክ የምትሆን ጾም የገሐድ ጾም አንድ ቀን ከጾመ ፊልጶስ በፊት ተጨመረችና ኅዳር ፲፭ ቀን እንዲጾም አዘዙን፡፡ ጌታ የጾመው ጾም ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ሆኖ ሳለ ፶፭ ቀናትን እንደምንጾመው ያለ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል የመጨረሻውን ሳምንት ደግሞ የሕማማት ሳምንት በማለት እንደምንጾመው ሁሉ ይህንንም እንዲሁ አደረግን፡፡ ይህም የአባቶቻችን ትእዛዝ የአባቶቻችን ሥርዓት ነውና እኛም ተቀበልነው፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው በጾም ምክንያት ክርክር ቢነሣ መጾም ከመብላት እጅግ ይሻላል እንዳሉን እንጾመው ዘንድ ይገባናል፡፡
፭ኛ. አብርሃም ሶሪያዊ ከህዳር ጾም አስቀድሞ እንዲጾም አዝዟልና ነው፡፡ በስምዖን ጫማ ሰፊው አማካኝነት ተራራውን ያፈለሱበትን ድንቅ ተአምር ማሰቢያ አድርገው ይጾሙታልና ጾመ አብርሃም ሶሪያዊ ተብሎም ተጨመረ ይላሉ፡፡
፮ኛ. ጾሙ መግቢያው ኅዳር ፲፭ ይሆንና ፵ ቀናት ተጨምረው ታህሳስ ፳፭ ያልቃል ከዚህ ጀምሮ እስከ ገና በዓል ድረስ ያሉ ቀናትን መርአዊ ብለን እንጾመዋለን የሚሉም አሉ፡፡
፯ኛ. የቤተክርስቲያናችን ትልቁ ወሳኝ አካል ጾመ ነቢያት በየዓመቱ ኅዳር ፲፭ ይጀመራል ብሎ ወስኗልና፡፡
በዚህም አለ በዚህ አባቶቻችን ሠለስቱ ምእት የጾሙ መግቢያን “መንፈቁ ለኅዳር” ብለው ወስነውታልና ፲፱ ይገባል ማለት ክህደት ነው የአበውን ሥርዓት እና እምነትም መንቀፍ ነውና ተመለሱ እንላለን፡፡
ሌላው አሁንም ለመብላት ብቻ የተነሡት ቅባቶች በሐዋርያት ጾም ላይም እንዲሁ ውዝግብ ሲፈጥሩ ይታያሉ፡፡
ጾመ ሐዋርያት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ይህ ጾም ሐዋርያት መንፈስቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለትምህርት ወደ ዓለም ከመሄዳቸው አስቀድመው ለሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገው የጾሙት ነው። ይህንን ሲገልጽ ፍትሐነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፹፮ ላይ “ዳግመኛም ስለ ሃምሳኛው ቀን አከባበር ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማር በፊት እንደጾመ ጌታችንም በርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የርሱን ሕግ ለሕዝብ ከማስተማሩ አስቀድሞ እንደዚሁ ጾመ፡፡ ሐዋርያትም በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሕገ ወንጌልን ለሕዝብ ከማስተማራቸው አስቀድሞ እንደዚሁ ጾሙ፡፡ እኛም በዚህ በእነርሱ ተመራን” ይላል። ስለዚህ ጾም መግቢያና መውጫም ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፱ ላይ “ከዚህም ቀጥሎ ከበዓለ ሃምሳ ቀጥሎ ያለ የሐዋርያት ጾም ነው፡፡ ፋሲካው በጴጥሮስና በጳውሎስ በዓል ሐምሌ ፭ ቀን ነው” ተብሏል። አባቶቻችን እንደሰሩልን ሥርዓት መሠረት የዚህ ጾም መጀመሪያ በዓለሃምሳ እንደተፈጸመ የመጀመሪያው ሰኞ ነው። ይህም ማለት አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ከጰራቅሊጦስ በዓል ቀጥሎ ባለው የመጀመሪያው ሰኞ ይጀመራል ማለት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ወገኖች ለመብላት ካላቸው ልዩ ፍቅር የተነሣ የፍትሐ ነገሥቱን ትእዛዝ በሙሉ ሳያነቡ ለራሳቸው እንደሚገባ አድርገው ተርጉመው ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ሌላ ፯ ቀናትን ይበላሉ። ይህንንስ ከየት አግኝተውት ነው ቢሉ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፹ ላይ “በዓለ ሃምሳን ከጨረሳችሁ በኋላ ዳግመኛ ሰባት ቀን ሌላ በዓል አድርጉ ከዚህም ቀጥሎ ከአረፋችሁ በኋላ ጹሙ” የሚለውን ይዘው ነው። ነገር ግን በዓልን በማድረግ የሚጾሙ አጽዋማት አሉና በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ለዚህም ሲያስረዳ ቁጥር ፭፻፹፩ ላይ  “እግዚአብሔር ይቅር ይበለውና ይህን መጽሐፍ ከሰበሰበው የተመረጠ ከሆነው መምህር ቃል የተገኘ ነው፡፡ የዚህ ሳምንት ምልክት ግን ልንበላበት እንደማይገባ እነሆ ረቡዕንና ዓርብን እንድንጾም ያዘዘበት አንቀጽ አለ ዳግመኛም በዓለ ሃምሳ ልደት ጥምቀት ቢውልባቸው አትጹሙ ብሎ ያዘዘበት አንቀጽ አለ፡፡ ስለዚህ ሳምንት ግን አልተናገረም፡፡ ሊበሉባቸው በሚገባ ቀኖች ውስጥ ሊጾሙባቸው የማይገባ ቢሆን ኖሮ እንደነዚያ መልሶ በተናገረ ነበር” ይላል። ረቡዕ እና አርብን ከዓመት እስከዓመት ጹሙ ነገር ግን ጥምቀት፣ በዓለ ልደት እና በዓለሃምሳ ካልዋሉባቸው በቀር ብሎ ተናግሮ ነበርና። ቁጥር ፭፻፷፮ ላይ “ዳግመኛም በእየሳምንቱ ሁሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ ፱ ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው” ብሎ አዘዘ። ከበዓለ ሃምሳ በኋላ በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ብሉበት ቢል ኖሮ ግን በዚህ ቁጥር ላይ “በዓለ ሃምሳ እና ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባሉት ሰባት ቀን” ባለ ነበር። በመጾም በዓል ማድረግ እንደሚገባ እዚሁ አንቀጽ ላይ  ቁጥር ፭፻፹፪ ላይ “ዳግመኛም እንዳንጾምባቸው እንዳንሰግድባቸው የታዘዝንባቸው ቀኖች እንደ እሁድ እንደ ሰንበት እንደ ጌታ በዓላት ያሉ ቀኖች አሉና ከእነርሱ ጋር ይህን ሳምንት አልተናገረም፡፡ ዳግመኛም የሰሙነ ሕማማትን ሥራ ሳይሠራ ላለፈበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ስለርሷ መጾም መስገድ ይገባ ዘንድ ታዘዘ፡፡ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሚውለው ሳምንት ይህ ቢሆን ኖሮ ከሃምሳ ቀኖች በኋላ ይበሉበት ዘንድ የሚገባ ቢሆን እንደገና ብሉበት በተባለ ነበር፡፡ በዓል አድርጉ ከማለቱ በቀር ብሉበት አላለምና” ይላል። እንደዚሁም ቁጥር ፭፻፹፫ ላይ “ይህስ በውስጡ ያሉትን የዓርብንና የረቡዕን ጾም ያስረዳል፡፡ እነርሱንም ይፈጽሟቸው ዘንድ አያስረዳም እነሆ ባስልዮስና አፈወርቅ እንዲህ አሉ፡፡ በዓል ማክበር በመብል አይደለምና ዳግመኛም በጾም በዓል ማክበር እንዲገባ የታወቀ ነው፡፡ ይኸውም ለበዓሉ የሚስማማው እንዲነበብ ነው እንጅ ሊበሉበት አይደለም፡፡ ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ ፫ ቀን እንድናከብር እነሆ ቀኖና አዘዘችን፡፡ በጾም ቀን እንኳ ቢሆን በእነዚህ በ፫ ቀኖች እንዳንበላ የታወቀ ነው በዓል ማክበር በመብል አይደለም”  በማለት እንድንጾም ያስረዳል። ነገርግን ለመብል ራሳቸውን የሰጡ ወገኖች ይህንን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ያለውን ፯ ቀን ይበሉበት ዘንድ በዓል አድርጉ ተብለናል ይላሉ። ከላይ እንደተመለከትነው በዓል የሚደረገው በመብል በመጠጥ ብቻ አይደለም በጾምም ጭምር ነው እንጅ። የሚበላበት ቢሆን ኖሮ  ቁጥር ፭፻፹፰ ላይ “አንድ ሰው በባሕር ቢኖር ሰሙነ ሕማማትን ባያውቅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ይጹም፡፡ ይኸውም ሰሙነ ሕማማትን የሚጠብቅ አይደለም፡፡ ምሳሌውን ብቻ ነው እንጅ ስለእርሱ መጾም ይገባዋል” ብለው ባላዘዙም ነበር። ነገር ግን መጾም እንዲገባ ጹሙ ብለው አዘዙ እንጅ። አባቶቻችን ይህን ያዘዙን እነርሱ ሳይጾሙ አይደለም ጾመው ነው እንጅ ለዚህም  ቁጥር ፭፻፹፭ ላይ “ዳግመኛም ከተሰበሰቡት ወገን ቁጥራቸው ኸያ የሚሆኑት ጹመውታልና ከእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከዚህ ቁጥር ቁጥራቸው እስከበዙት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በዚህ ሳምንት እነሆ ይህን ጾም ጾምን፡፡ የማኅበሩን ትእዛዝ ብንተላለፍ ይህን ማኅበር እንዲነቀፍ ብናደርግ ደግ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሕጋችንን ትሩፋት በተቃወመ ጊዜ፡፡ ይኸውም ስለመብል ስስትን በመግለጽ የሚደረግ ክፋት ነው” ብለዋል። ሰለዚህ ከአባቶቻችን አንበልጥምና በእነርሱ መንገድ እንጓዝ ዘንድ ይገባል። ይህን ሁሉ ብለው አልሰማ ላላቸው ግን ሁሉን ሊጠቀልል የሚችል ትእዛዝ እነሆ ሰጡን። ቁጥር ፭፻፹፬ ላይ “ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል፡፡ ከመብላት በጣም ይሻላል” ብለው አዘዙን። በጾም ወቅት ክርክር ከተፈጠረ ጹሙ ምክንያቱም ከመብላት በጣም ይሻላልና ብለው በአንድ አረፍተ ነገር አሠሩልን። ከዚህ ወዴት እንሸሻለን? እንብላበት እና እንጹምበት የሚሉ ሰዎች ቢከራከሩ እንጹምበት ያለው እንዲረታ እወቁ። ስለዚህ የጾመ ሐዋርያት መግቢያ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት ነው እንጅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ሌላ አንድ ሳምንት ከበላን በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት አይደለም።
ሌላው ነጥብ ስለ ጥምቂት አንዲትነት ነው፡፡ ሠለስቱ ምእት “መነአምን በአሐቲ ጥምቀት፤ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” ብለዋል፡፡ ኤፌ ፬፥፬ ላይም ቅዱስ ጳውሎስ “አንዲት ጥምቀት” ብሏል፡፡ ካሳሁን ምናሉም የጠቃቀሳቸው ሊቃውንት እንዲሁ አንዲት ጥምቀት ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ግን እስላም ያተመቀውን፣ ፕሮቴስታንት ያጠመቀውን፣ አርዮስ ያጠመቀውን፣ ንስጥሮስ ያጠመቀውን፣ ካቶሊክ ያጠመቀውን፣ ቅባት ያጠመቀውን፣ ጸጋ ያጠመቀውን አይደለም፡፡ እነዚህ ያጠመቁት ሰው አማኒ እንደማይሆን ፍትሐነገሥት ተናግሯል፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፫ ቁጥር ፳፬ ላይ “ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኒ አይደለም” ከመናፍቃን ያላቸው ከላይ የጠቀስኋቸውንና ያልጠቀስኋቸውን ከተዋሕዶ ሃይማኖት ውጭ የሆኑትን እምነቶች ሁሉ ነው፡፡ ከ፲፪ ቱ ሐዋርያት የሲኖዶስ ቃል ስንመለከት ዘግንገራ ትእዛዝ ፮ በእንተ እለ ይበውኡ ውስተ ሕግነ እምሰብአ አላውያን አዘዙ ጉባኤ ቅዱሳን ከመ ይወስኑ ሎሙ በኩሉ እመቦ ዘኮነ
አሐዱ እመናፍቃን ዘውእቶሙ ሰብአ ጳውሎስ ሳምሳጢ እመቦ
ዘቦአ እምኔሆሙ ውስተ ሕግነ
ይጠመቅ ዳግመ እስመ ጥምቀቱ
ከመ ወኢምንት ወአኮ ርቱዕ ወዘኮነ ካህነ እምኔሆሙ ጊዜ
ግብዓቶሙ ኀቤነ (ኀበአ/ተዋሕዶ) አኮ ክህነቱ ክህነት ውእቱ እስመ ግብሮሙ ግብር እኩይ ውእቱ ወኢኮነ ርቱዓ ወኢይደሉ ንንግር እምነግብሮሙ ምንተኒ ወዘኮነ እምኔሆሙ ሠናየ ምግባር ወትሑተ እምድኅረ ተወክፈ ጥምቀተ እምኔነ ይትወከፍ ካዕበ ክህነተ እምኤጲስ ቆጶስ በቤተ ክርስቲያኑ ለወልደ እግዚአብሔር ሕያው” ብሎ ያሳርፈናል፡፡ ከመናፍቃን የተጠመቀ አማኒ አይደለም አማኒ እንዲሆን ምን ያስፈልገዋል ከተባለ በተዋሕዶ እምነት ሥርዓት እና ደንብ ቀኖና እና መመሪያ መሠረት ይስተናገዳል ማለት ነው፡፡
ቅባቶች በመጽሐፎቻቸው ላይ “በተዋህዶ ከበረ” ማለት ምንፍቅና ነው ይላሉ፡፡ ታዲያ ክህነት የሚቀበሉት “በተዋሕዶ ከበረ” ከሚል ጳጳስ አይደለም እንዴ? ቅባት በእኛ አስተምህሮ መሠረት ምንፍቅና ነው፡፡ ተዋህዶ በቅባቶች አስተምህሮ መሠረት ደግሞ ምንፍቅና ነው ብለውታል፡፡ ስለዚህ አንገናኝም አንድነት የለንም ማለት ነው፡፡ ከተዋህዶ ውጭ የሆነ ጳጳስ ካላቸው አስተምረው ሲመልሱ አጥምቀው ቅባት እንደሚያደርጉ ሁሉ ቅባቶችንም አስተምረን ስንመልሳቸው ይጠመቃሉ ግድ ነው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በዘንድሮው የጥቅምት ስብሰባው ላይ ወልደ አብ የተባለውን መጽሐፍ ሲያወግዝ “የቅባት እና የጸጋ አስተምህሮ የሚያስፋፋ…” ብሎ መግለጹ ቅብአት ምንፍቅና እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ ምንፍቅና ከሆነ ደግሞ ወደ ተዋሕዶ ሲመለስ ይጠመቃል፡፡ ጥምቀቱም የልጅነት እንጅ የቄድር አይደለም፡፡ የቄድር ጥምቀት የሚያስፈልገው ልጅነት አግኝቶ የነበረ ሰው ክዶ ቆይቶ ሲመነለስ ነው ይህ ግን በመጀመሪያም ክህነት በሌለው ልጅነትን በማያሰጥ መናፍቅ ነውና የተጠመቁ በተዋህዶ ካህናት መጠመቅ ግዴታ ነው ማለት ነው፡፡ ይህን የምለው እኔ አይደለሁም መጽሐፉ እንጅ፡፡
አባ ማርቆስን ጨምሮ “ጎጃም ዳግም ተጠመቅ ተብለሃል” የሚሉት ቅባቶችን ከለላ ለመስጠት ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ መጠመቅ የሚፈልግ ሰው የተዋሕዶ እምነትን አምኖ ይጠመቃል ይህ ማለት እኮ ግዴታ ተጠመቅ ማለት አይደለም፡፡ አንዲት ጥምቀት ያለው ቅዱስ ጳውሎስ እኮ አንዲት ሃይማኖትም ብሏል፡፡ ታዲያ አንዲት ጥምቀት ብለን ሁለት ሃይማኖት ልንል እንዴት እንችላለን፡፡ በአንድ ጥምቀት አንድ ሃይማኖት ብቻ ነው ያለው፡፡ በአንድ ጥምቀት ሁለት ሃይማኖት የለም፡፡ ቅባት የለም ቅባት ምስጢር ነው ቅባት ባህለ ትምህርት ነው ምናምን ምናምን የሚለው የነበጋሻው ዓይነቱ ፍልስፍና ቦታ የለውም፡፡ “ወልድ ፍጡር” የሚል ምሥጢርም ሆነ ባህለ ትምህርት የለንም አናውቅምም፡፡ እነ በጋሻው ለዚህ ደረጃ የደረሱት ተሐድሶ የለም እያሉ በማደራገር ነበር ዛሬም ቅባቶች በማደናገር ላይ ናቸው፡፡ አቡነ ዘካርያስም ለሚመሩት ሀገረ ስብከት እና ለቅዱስ ሲኖዶስ ይህንኑ በማያሻማ መልኩ ነው የጻፉት፡፡ እንዲህ በማለት፡-
*****************************************
                                                ቁጥር፡-1603/2010
                                                ቀን፡- 04/03/2010
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ውስጥ የምትገኙ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መምህራን ሰባኪያነ ወንጌል ካህናትና ዲያቆናት ምእመናን ወምእመናት ወወራዙት (ወጣቶች) ወመሐዛት (ታዳጊዎች) በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡ የቅድስት ድንግል እመቤታችን ረድኤት አይለያችሁ አሜን፡፡
እጽሕፍ ለክሙ ደቂቅየ ልጆቼ ሆይ እጽፍላችኋለሁ ይኸውም “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የሚል በግዕዛዊ አነጋገሩ በሃይማኖታዊ ምሥጢሩ እጅግ በጣም ስህተት ኑፋቄ ክህደት የሞላበት ስለሆነ ከወልደ አብ መጽሐፍ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ይኸውም የተወገዘ እና የተከለከለ ስለሆነ እንዳትቀበሉት እያሳሰብኩ ብታገኙትም በሽፋኑ እና በውስጡም ያሉ ስዕሎችን እያነሣችሁ በእሳት ማቃጠል ትችላላችሁ፡፡ የተዋሕዶ ሃይማኖታችን ጠላት ነውና የቅባቶች የፀጎች የካቶሊኮች መጽሐፍ ነውና ከዚህም ሌላ ስለጥምቀት ከሊቃውንቱ አንዳንዶቻችሁ ጥያቄ አቅርባችኋል፡፡ ጥምቀት የተዋሕዶ ሃይማኖት አንዲት ናት፡፡ እርሷም አትለወጥም አትከለስም አትታደስም ዘላለማዊት አንዲት ጥምቀት ናት፡፡ በተዋሕዶ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት የተጠመቁ ክርስቲያኖች ሌላ ጥምቀት የላቸውም፡፡ ዘላለማዊት አሐቲ ጥምቀት ናትና ነገር ግን ክርስቶስ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ወልድ ተፈጠረ መለኮት ተፈጠረ የሚሉ ቅባቶች ፀጎች ያጠመቋቸው ሰዎች ጥምቀት አይባልም፡፡ ፀጎች ቅባቶች ምንም እንኳ ከተዋሕዶ አባች ጳጰሳት ክህነቱን ቢቀበሉትም ራሳቸው ወልድ ፍጡር የሚሉ አርዮሳውያን ስለሆኑ ክህነታቸው ልጅነት አያሰጥም፡፡ ለምሳሌ ወልደ አብ የተባለውን መጽሐፍ የጻፈው የቆጋው መነኮስ ገብረ መድኅን የዲቁናውን የቅስናውን ክህነት የተቀበለው ከብጹእ አቡነ ማርቆስ ቀዳማዊ ሊቀ ጳጳስ ዘጎጃም ነው፡፡ እርሱም የተዋሕዶ ልጅ ነኝ ብሎ ምሎ ተገዝቶ ነበር የተቀበለው አሁን ግን በመጽሐፉ እንደገለጸው ክርስቶስ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ወልድ ተፈጠረ መለኮት ተፈጠረ ብሎ የሚያምን ስለሆነ በርሱና ርሱን በመሰሉ ካህናት ነን በሚሉ የተጠመቁ ሁሉ ሃይማኖትም ልጅነትም ስለሌላቸው በተዋሕዶ ሃይማኖት ጥምቀት መጠመቁ ግድ ነው፡፡ የሚጠመቁትም በሊቀ ጳጳስ በኤጲስ ቆጶስ በካህን ነው፡፡
ለዘተወልደ እምጻውቲኒ ዳግመ ያጥምቅዎ የተባለውም ስለዚህ ስለሆነ ትርጉሙም በሳምሳጢ ጳውሎስ በአርዮስ ወገኖች የተጠመቀ ቢኖር ርትዕት በሆነችው ተዋሕዶ ሃይማኖት ይጠመቅ “ዲድስቅልያ” ባቀረባችሁት ጥያቄ መሠረት መልሴ ይህ ነው፡፡
                                  እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን
                       የቅድስት ድንግል ቡርክት ማርያም ረድኤት አይለየን አሜን፡፡
                                      አባ ዘካርያስ
                  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ምሥራቅ፣     ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ፊርማ
ግልባጭ//
     - ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
     - ለብጹእ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
     - ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
                         **************************************
ጥምቀት አንድ ተብሎ የሚቆጠረው አማኝ በሆነ እውነተኛ የተዋሕዶ ካህን የጠጠመቀ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ሌላው ከተዋሕዶ ካህን ውጭ የሆነ መናፍቅ በውኃ የጠበውን ሁሉ ተጠመቀ ብለን አንቀበለውም፡፡
በመጨረሻም የምንመለከተው  ስለጌታ ልደት ነው፡፡ ጌታችን የተወለደው እና እኛ የተዋህዶ ልጆች የምናምነው ሁለት ልደታትን ነው፡፡ እነርሱም ቅድመዓለም ያለእናት በመለኮት ከአብ የተወለደውን እና ድኅረ ዓለም ያለአባት ከድንግል ማርያም በሥጋ የተወለደውን ልደት ነው፡፡ ካሳሁን እና ዘመዶቹ ግን ይህንን ለማምታታት ይሞክራሉ፡፡ በዓሉ የሚከበርበትን ቀን ከጌታ ልደት ጋር አመሳስለው ሊያወናብዱ ይሞክራሉ፡፡ ከአብ በመለኮት የተወለደው ታህሳስ ፳፰ የተወለደው ታህሳስ ፳፱ የተወለደው በማለት ድኅረዓለም ከእመቤታችን የተወለደውን ለሁለት ከፍለው አቅርበውታል፡፡ ይህ በእውት በጣም የሚያስቅ ነገር ነው አለመማሩንም ማሳያ ነው፡፡ አሁን እኛ ልደታችንን ስናከብር በየዓመቱ ተወልደናል እያልን ነው እንዴ? የጌታን ስቅለት ለምሳሌ በየዓመቱ በተለያየ ቀን ነው የምናከብረው ታዲያ መጋቢት ፳፯ የተሰቀለው አንድ ጌታ ሚያዝያ ፯ ቀን ስቅለትን ስናከብር ደግሞ ሚያዝያ   የተሰቀለው ሌላኛው ጌታ እያልን ነው እንዴ? ይህ በጣም የሚያስገርም ነገር ነው፡፡ ቅባቶች ግን ሦስት ልደታትን ምንም በማያሻማ መልኩ የተገለጡትን ያከብራሉ፡፡ እኛ ሁለት ልደት ባዮች ስንሆን እነርሱ ቅባቶች  ግን ሦስት ልደት ባዮች ናቸው፡፡ ይህንን የምላችሁ ከምድር ተነስቼ አይደለም ራሳቸው የጻፉትን መሠረት አድርጌ እንጅ፡፡
ወልደአብ የተሰኘው የክህደት መጽሐፋቸው ገጽ ፪፻፲፮-፪፻፲፯ ስናነብ እንዲህ ይላል። “ጌታችን ልደቱ ስንት ነው ቢሉ ፪ ነው። እንዴት ፪ ነው እምቅድመዓለም በመለኮቱ ተወለደ ብለናል ኋላም በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ እንላለን ዳግም ከእመቤታችን በስጋ በጎል ተወለደ እንላለን ይህማ ፫ አይደለምን እንደምን ፪ ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የተወለደው ልደትና ዛሬ በማኅጸን በሥጋ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት አንድ ልደት ይባላል እንጅ ፪ አይባልም። ፪ ጊዜ ቆጥረነው አንድ ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ ፪ ልደት አይባልም።ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ምሳሌ እንዴት ያስረዳል ቢሉ እነሆ ዛሬ ሰው አዲስ ሸማ ለብሶ ያነን በከረጢት ከቶ ዳግመኛ አውጥቶ ቢለብሰው አንዱን ሸማ ፪ጊዜ ለበሰው ተብሎ አንድ ሸማ ይባላል እንጅ 2 አይባልም።ዳግመኛ በአንድ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ፪ ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ፪ ዘውድ አይባልም” ይላል። 
እዚህ ላይ በግልጥ የምንመለከተው ሦስት ልደትን ማመናቸውን ነው፡፡ መጻሕፍት “ሁለት ልደታትን እናምናለን” ብለው ስላጠሩባቸው ለመንፈራገጥ አልመች ቢላቸው ሦስት ጊዜ ቆጥሮ ሁለት ማለት ይገባል ብለው ተናገሩ፡፡ እነርሱ የሚጠቅሷቸው በግልጥ የተቀመጡት የጌታ ልደቶች እነዚህ ናቸው፡፡
፩ኛ. እምቅድመ ዓለም በመለኮቱ የተወለደው ልደት፤
፪ኛ. በማኅጸን በሥጋ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት፤
፫ኛ. ከእመቤታችን በስጋ በጎል ተወለደ በማለት ሦስት ልደታትን አስቀምጠውልናል፡፡
እነዚህ ልደታት መካከል ፪ኛው ልደት በየትኛውም መጽሐፍ ተጽፎ እንደማይገኝ ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች በማስረጃ በማስደገፍ ጽፈናል፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ፩ኛ እና ፪ኛ ላይ የተገለጡት ልደቶች አንድ ተብለው ይቆጠራሉ እንጅ ሁለት አይባሉም ይላሉ፡፡ ለምን ለሚለው መልስ ሲመልሱ “ኹለት ጊዜ ቆጥረነው አንድ ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት ልደት አይባልም” ይላሉ፡፡ በእውነት ምንም የማይመስል የማይገናኝ ከንቱ ነገር ነው፡፡ “እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም” ማለት ምን ማለት ነው? እዚች ላይ ያዝ አድርጓት እስኪ፡፡ የቀደመ ልደቱ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ሳይቀድም ሳይከተል ያለእናት በመለኮት በረቂቅ ምሥጢር የተደረገ ነው፡፡ የዛሬው ልደቱ ደግሞ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ በመለኮት አይደለም ምክንያቱም አብ የወለደው በሥጋ ነው ብለውናላ፡፡ በመለኮት ነው ካሉ ወልድ በመለኮቱ ስንት ጊዜ ተወለደ ብለን እንጠይቃቸዋለን፡፡ በሥጋ ነው የወለደው ካሉን ደግሞ መለኮታዊ አካል ሥጋዊ አካልን መለኮታዊ ባሕርይም ሥጋዊ ባሕርይን ይወልድ ዘንድ ይቻላልን ብለን እንጠይቃቸዋለን፡፡ አዎን ሊወልድ ይቻለዋል ካሉን የቀደመው ልደቱ ከአብ በመለኮት ነው የዛሬው ልደቱ ደግሞ ከአብ በሥጋ ነውና ሁለት ብለን እንቆጥረዋለን እንጅ አንድ ልደት አንለውም ብለን በዚህ እንረታቸዋለን፡፡ ነገር ግን እነርሱ መረታትን ስለማይሹ “ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስ ቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት ልደት አይባልም” ብለው መከራከራቸው አይቀርም፡፡ ነገር ግን ወላዲው አብ ይሁን ተወላዲውም ወልድ ይሁን አይቀየር አይለወጥ እንጅ ልደቱ ግን ለየቅል ነው እንላቸዋለን፡፡ ምክንያቱም “የቀደመው ልደት በመለኮት የዛሬው ልደት በሥጋ” ነውና ልደቱ በጣም ይለያያል እንላቸዋለን፡፡ አብ በመለኮት ቅድመ ዓለም የወለደው ልደት እና ዛሬ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የወለደው ልደት እጅግ የተለያየ እንደሆነ ልብ ማለት ተስኗቸዋል፡፡ ለዚህም እኮ ነው ይች “ዛሬ አብ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ወለደው” የምትለዋ ተጨማሪ የፍልስፍና ልደት ትቅር መጽሐፍ አይደግፋትም የምንለው፡፡ የጻፉትን ነገር ስትመለከቱት ፈራሽ ነገር ነው፡፡ ቀጥለው ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ይሉናል፡፡ ልብ በሉ! ሦስት ልደት ቆጥረው ሁለት ልደት ነው ብለው ሙልጭ ብለው ለጠፉበት ክህደት የተሰጠ ምሳሌ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ይላል ምሳሌው “ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ምሳሌ እንዴት ያስረዳል ቢሉ እነሆ ዛሬ ሰው አዲስ ሸማ ለብሶ ያነን በከረጢት ከቶ ዳግመኛ አውጥቶ ቢለብሰው አንዱን ሸማ ኹለት ጊዜ ለበሰው ተብሎ አንድ ሸማ ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም። ዳግመኛ በአንድ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ኹለት ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ኹለት ዘውድ አይባልም”፡፡ እነዚህን ምሳሌዎች ዘርዘር አድርገን ፍትፍት ብትንትን አድርገን እንመልከታቸውማ!
፩ኛ. የአዲሱ ሸማ ጉዳይ ከልደቱ ጋር እስኪ ይዛመድ፡፡
ምሳሌነቱ፡- ሸማው ወልድ ነው፡፡ ለባሹ አብ ነው፡፡ ስለዚህ ለበሰ ለሚለው ቃል አቻው ወለደ የሚለው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከረጢቱ የድንግል ማርያም ማኅጸን ምሳሌ መሆኑ ነው፡፡ ልብ በሉ አስተውሉ ወገኖቼ!!! የጌታ ልደት እንደዚህ በከረጢት ገብቶ እንደመውጣት ያለ ተራ ነገር አድርገው ማሰባቸው ኅሊና ቢስ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ሸማው ወልድ መጀመሪያ በለባሹ (አብ) ተለበሰ (ተወለደ) ቀጥሎ በከረጢት በተመሰለው የድንግል ማርያም ማኅጸን አደረ (ተዋሐደ) ከዚያ ከዚህ ከረጢት ለባሹ (አብ) አውጥቶ ለበሰው (ወለደው) ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ለባሹም ልብሱም አልተቀየረም አልተለወጠም ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ስንት ጊዜ ለበሰው ብለን ብንጠይቅ ለባሹ እና ልብሱ ስላልተለወጡ ስላልተቀየሩ አንድ ጊዜ ለበሰው ሊባል ይችላል እንዴ? በእውነት ግን አንድ ልብስ የሚያረጀው ብዙ ጊዜ ስለተለበሰ አይደለምን ታዲያ በከረጢት አስገብተው እያወጡ ሲለብሱት ያው አንድ ጊዜ ብቻ እንደተለበሰ ይቆጠራል ከተባለማ በጣም ጥሩ የኑሮ በዘዴ መምህር ሆነዋል ማለት ነው፡፡ ይች ግን ጥሩ ፍልስፍና ሳትሆን አትቀርም፡፡ በእውነት ልብስ በከረጢት እያስገቡ ከዚያ እያወጡ ሲለብሱት ለባሹም ልብሱም ስላልተቀየረ አንድ ተለበሰ ነው የሚባል ብለው አረፉት፡፡ ሁለት ጊዜ ስለተለበሰ ሁለት ሸማ ሳይሆን አንድ ሸማ ይባላል የሚለው ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን በሸማው የተመሰለው ወልድ አይለወጥ አይቀየር እንጅ ሁለት ጊዜ ተወልዷል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ይህ ምሳሌ “እምቅድመዓለም ከአብ የተወለደውንና በማኅጸነ ማርያም ከአብ የተወለደውን ሁለት ልደት ሁለት ብለን እንድንቆጥር እንጅ አንድ ብለን እንድንቆጥር አያደርግም እና የወልድ ልደቶች ሦስት ናቸው እንደሚሉ ጥሩ ምሳሌ ነው” የምንለው፡፡
፪ኛ. የዘውዱ ጉዳይ ከልደቱ ጋር ያለው ምሳሌነት ሲዛመድ፡፡
“ዳግመኛ በአንድ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ኹለት ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ኹለት ዘውድ አይባልም”
ምሳሌነቱ፡- ዘውዱ አብ ነው፡፡ ነጋሹ ወልድ ነው፡፡ ንግሥናው የልደት ምሳሌ ነው፡፡ እዚህ ላይ በአንዱ ዘውድ (በአብ) ብዙ ነገሥታት (ልጆች) ይነግሡበታል (ይወለዱበታል) ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይኼ ምኑ ነው ሦስት ልደት ብለው የቆጠሩትን ሁለት እንድንል የሚያሳምነን? ምናልባት እዚህ ላይ “ዘውዱ” እንደ ልደት ተቆጥሮ ከሆነ ነጋሹ ወልድ አንጋሹ አብ ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአንዱ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት እንደሚነግሡበት ሁሉ በአንዱ ልደትም ሁለት ሦስት ልጆችን ወለደ ያሰኝባቸዋልና ይህም የተዋረደ ከንቱ ምሳሌ እንደሆነ በዚህ እንረዳለን፡፡
ስለዚህ በመጽሐፍ ያልተጻፈ በሊቃውንት በመምህራን ያልተነገረ እንግዳ የሆነ ትምህርትን ዝም ብላችሁ መቀበል እንደማይገባችሁ ለሁሉም የቅብዓት እምነት ተከታዮች ሁሉ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ መሰዳደቡን መጨቃጨቁን ትተን እውነትን ወደ መመርመር እንግባ፡፡ እኛ ከተሳሳትን መጽሐፍ ጠቅሳችሁ ሊቃውንቱን አብነት አድርጋችሁ እውነቱን አሳዩን እናንተ ከተሳሳታችሁ ግን እኛን ምሰሉን!!!
የጌታ ልደታት ሁለት ናቸው እነዚህም ቅድመዓለም ከአብ እንበለ እም ድኅረዓለም ከእመቤታችን እንበለ አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ይህንንም ሊቃውንቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየደጋገሙ አስረድተዋል በመጻሕፍታቸውም ላይ አስፍረዋል፡፡ ይህንንም ከብዙ በጥቂቱ እነዚህን ለማስረጃነት ያህል እንመለከታለን፡፡ “አብ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ወልድን ወለደው” የሚለው የቅብዓቶች ሦስተኛ ልደት ግን በየትም ቦታ ተጽፎ አናገኘውም፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ይህንን ትምህርት ውድቅ የሚያደርጉ የሊቃውንቱን ትክክለኛ እና እውነተኛ ትምህርት እንጽፋለን በመቀጠልም ሁለት ልደታት እነማን እንደሆኑ በቅደም ተከተል እንጽፋለን፡፡
ለሰማያዊ ልደቱ እናት እንደሌለችው ሁሉ ለምድራዊ ልደቱም አባት የሌለው እንደሆነ ሊቃውንቱ እንዲህ ያስተምራሉ፡፡ እዚህ ላይ ለቀዳማዊ ልደቱ መለኮታዊት እናትም ሆነች ሥጋዊት እናት የለችውም ማለት ነው፡፡ ለምድራዊ ልደቱም እንደዚሁ መለኮታዊም ሆነ ሥጋዊ አባት የለውም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት የአብ አባትነት ቀድሞ ዘመን ሳይቆጠር የነበረ  አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር ነው ማለት ነው፡፡ አባትነት እንደ ቀበሌ መታወቂያ በየዘመኑ የሚታደስ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለምድራዊ ልደቱ አብ በድጋሜ አባቱ ሆነ ዳግም በማኅጸነ ማርያም ወለደው አይባልም ቢባልም ክህደት እና ጥፋት ነው፡፡ ይህንንም የምንለው በማስረጃ አስደግፈን ነውና ማስረጃውን እናስቀምጣለን፡፡

፩ኛ ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ም ፷ቁ ፳ ላይ “ዛሬ ግን ከድንግል ብቻ ተወለደ ድንግልናዋንም ባለመለወጥ አጸና ድንቅ የሚሆን መጽነስዋ የታመነ ይሆን ዘንድ ቅድመዓለም ከአብ እንደተወለደም ለማመን መሪ ይሆን ዘንድ” በማለት ድኅረዓለም ከድንግል ማርያም ብቻ እንደተወለደ ከአብ እንዳልተወለደ ይናገራል፡፡

፪ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ም ፴፭ ቁ ፲፯ “በምድራዊ ልደቱ አባት አለው አትበሉ በሰማያዊ ልደቱም እናት አለችው አትበሉ እርሱ በምድር አባት የሌለው ነው በሰማይም እናት የሌለችው ነው”
፫ኛ. “ዘአልቦቱ እም በሰማያት ወአብ በዲበ ምድር ፤ በሰማይ እናት በምድርም አባት የለውም” አንቀጸ ብርሃን ዘቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ፡፡
፬ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘሄሬኔዎስ ም ፯ ክ ፪ ቁ ፳ “ከንጽሕት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን እንደተወለደ እንደሚነግሩን ቀድሞም ከአብ እንደተወለደ እንዲሁ ከአባት ያለእናት ከእናት ያለአባት ለመወለድ መጀመሪያ እርሱ እንደሆነ ለፍጥረት ሁሉ ይነግሩናል”

፭ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ም ፸፫ ቁ ፬-፭ “ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይመረመር ተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነውና ቀዳማዊ ሲሆን ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ ነው ዳግመኛም ከድንግል በሥጋ የተወለደ ነው ተብሎ ስለርሱ እንዲህ ይነገራል፡፡ የመለኮቱ መገኘት ከድንግል አይደለም፤ ከአብ ከተወለደ በኋላ ጥንታዊ (ቀዳማዊ) ልደትን ሊወለድ አልወደደም ከአብ ጋር ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ የነበረ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ስለሚሆን ስለእርሱ ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ጥንታዊ ልደትን ሁለተኛ እንደሻ ይነገር ዘንድ ይህ ሐሰት ክህደትም ነው፤ ዳግመኛ በሥጋ እንደተወለደ ስለእርሱ እንዲህ ይነገራል እንደሰው ሁሉ አስቀድሞ ቅርጽ የተፈጸመለት ሰው ተገኝቶ ከዚህ በኋላ ቃል ያደረበት አይደለም በእመቤታችን ማሕጸን እርሱ ብቻ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ እንጅ በሥጋም ይወለድ ዘንድ ወደደ በሥጋ መወለድንም ለእርሱ ብቻ ገንዘብ አደረገ” …..እዚህ ላይም በማስተዋል አንብቡት “ከአብ ከተወለደ በኋላ ጥንታዊ (ቀዳማዊ) ልደትን ሊወለድ አልወደደም ከአብ ጋር ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ የነበረ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ስለሚሆን ስለእርሱ ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ጥንታዊ ልደትን ሁለተኛ እንደሻ ይነገር ዘንድ ይህ ሐሰት ክህደትም ነው” ይላል ሊቁ ቄርሎስ፡፡ ስለዚህ አብ በማኅጸነ ማርያም ወልድን ወልዶታል ማለት ሐስት ክህደትም ነው ቄርሎስ እንደተናገረው፡፡

፮ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ ም ፶፬ ቁ ፲፩ “አብ ጥንት ፍጻሜ የሌለው ቃልን ዓለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ወለደው በኋላ ዘመንም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ንጽሕት ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወለደ”… ይህንን አጻጻፍ ልበ ብላችሁ አስተውሉት፡፡ አብ በማኅጸን ወልዶት ቢሆን ኖሮ “በኋላ ዘመንም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ወለደው” ለማለት የቀና የተመቸ አጻጻፍ ነበር ነገር ግን አብ በማኅጸነ ማርያም ከአብ አልተወለደምና “ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወለደ” ብሎ ሊቁ ኤጲፋንዮስ ከላይ ባለው መልኩ ጻፈልን፡፡

፯ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ ም ፹፬ ቁ ፰ “ሁለት ልደት እንዳለው በእግዚአብሔር ቃል እንዲሁ ልናምን ይገባናል አንዱ ቅድመዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው የማይመረመር ልደት ነው፡፡ ሁለተኛውም በኋላ ዘመን ከንጽሕት ድንግል ማርያም ያለአባት የተወለደው የማይመረመር የማይነገር ልደት ነው፡፡ ነገር ግን ቃል ሥጋ እንደሆነ ባሕርያችንንም ባሕርይ እንደአደረገ በዓይናችን እንዳየነው በእጃችንም እንደዳሰስነው ይህን ብቻ እናውቃለን”

እነዚህ ሰባት ማስረጃዎች በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ነጥብ የያዙ ናቸው፡፡
፩ኛ. ለሰማያዊ ልደቱ እናት ለምድራዊ ልደቱ ደግሞ አባት እንደሌለው የሚገልጹ መሆናቸው፡፡
፪ኛ. የጌታ ልደታት ሁለት መሆናቸውን እነርሱም ቅድመዓለም ከአብ በመለኮት ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን በሥጋ የተወለዳቸው ልደታት ብቻ መሆናቸውን፡፡ እዚህ ላይ “አብ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ወለደው” የሚለው የቅብዓቶች ሦስተኛ ልደት ደጋፊ የሌለው ከንቱ ፍልስፍና መሆኑን ተረድተንበታል፡፡

፰ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ ም ፳፫ ክ ፩ ቁ ፪ “ለመወለዱ ጥንት በሌለው አስቀድሞ ዓለም ሳይፈጠር በመለኮቱ ከአብ በተወለደ ዳግመኛም እኛን ለማዳን በኋላ ዘመን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በእግዚአብሔር ልጅ እናምናለን የቀኑ ቀጠሮ ሲደርስ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከድንግልም ተወለደ ያለ ብጹዕ ሐዋርያ እንዳስተማረን”
፱ኛ. ሃይማኖተ አበው ባስልዮስ ም ፴፬ ቁ ፮ “ዳግመኛ ለወልደ እግዚአብሔር ሁለት ልደታት እንዳሉት እናምን ዘንድ ይገባናል፤ አንዱ ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፤ ሁለተኛውም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን የተወለደው ልደት ነው”
፲ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘአቡሊዲስ ም ፵፩ ክ ፯ ቁ ፲ “እግዚአብሔር ቃል ሰው እንደሆነ በአንደበቱ የሚያምን በልቡ ግን እንደእኛ አምላክነት የሌለው ዕሩው ብእሲ ከድንግል ተገኘ ብሎ የሚያምን የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ከድንግል እንደተወለደ የማያምን ሰው የምእመናን ባላጋራቸው የመናፍቃን ተባባሪያቸው ነው”
፲፩ኛ ሃይማኖተ አበው ዘናጣሊስ ም ፵፮ ክ ፩ ቁ ፫ “ከእግዚአብሔር አብ በተወለደው በቀዳማዊ ልደቱ የእግዚአብሔር አብ ልጅ ነው፤ ከድንግል በተወለደው በደኃራዊ ልደቱ የሰው ልጅ ሆነ”
፲፪ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘኤፍሬም ም ፵፯ ክ ፭ ቁ ፴ “ዳግመኛ በዚህ አንቀጽ እንዲህ አለ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመዓለም ከአብ ተወለደ ዳግመኛም ከቅድስት ድንግል ተወለደ”
፲፫ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘኤራቅሊስ ም ፵፱ ቁ ፴፮ “ቀድሞ የተወለደው ልደት ለርሱ ብቻ በርሱ ያለ ነው ኋላ ሰው የሆነበት ልደት ግን ስለእኛ ተደረገ አምላክ አምላክ እንደመሆኑ ታምራትን አደረገ ሰውም እንደመሆኑ ካባሕርዩ ሳይለወጥ ወዶ ሕማምን ገንዘብ አደረገ ከባሕርዩ ሳይለወጥ ሰው ሆኗልና”
፲፬ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘሳዊርያኖስ ም ፶ ቁ ፪-፫ “በማይመረመር ልደት ከአብ እንደተወለደ በአካላዊ ቃል እናምናለን ዓለም ሳይፈጠር የነበረ ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም የሚኖር ቀዳማዊ ደኃራዊ እርሱ ነው፡፡ ዳግመኛ ከአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ በምድር ላይ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እርሱ በሥጋ ተወለደ በዚህ ዓለም የተወለደ ሰው ሁሉ ከዳግማዊ አዳም ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ይኸውም እግዚአብሔር ቃል ነው”
፲፭ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘአፍሮስዮስ ም ፶፩ ቁ ፬ “ከአብ የተወለደውን ልደት ሊናገር የሚችል የለም ከአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከእርሱ ጋር አንድ በአደረገው በሥጋ ከድንግል የተወለደው እርሱ ነው”
፲፮ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ም ፶፫ ቁ ፲፮ “ወልድ ዋሕድ ከአብ መወለዱ እንዴት እንደሆነ ከቅድስት ድንግልም መወለዱ እንዴት እንደሆነ አትጠይቀኝ እርሱ በባሕርዩ ከአብ ተወልዷልና ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው”
፲፯ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ም ፸፫ ክ ፲፬ ቁ ፳፬ “ቅድመዓለም በመለኮቱ ከአብ ተወለደ በኋላ ዘመንም ዳግመኛ እኛን ለማዳን ከድንግል ማርያም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኖ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮቱ ትክክል ነው ይህ አንዱ ሰው በመሆኑ ከእኛ ጋር አንድ ነው ሁለቱ ባሕርያት በተዋሕዶ አንድ ሆኑ”
፲፰ኛ. ሃይማኖተ አበው ቴዎዶስዮስ ም ፺፪ ቁ ፲፩ “ዘመን ሳይቀድመው ሳይወሰን ከእግዚአብሔር አብ የተወለደ እርሱ ነው፡፡ በማይመረመር ምሥጢር ከድንግል ኹለተኛ ልደትን  በሥጋ የተወለደ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም የወለደችው ንጽሕት ድንግል በእውነት በድንግልና ጸንታ ኖረች እርስዋም እግዚአብሔር ቃልን የወለደች እንደሆነች እናምናለን ወላዲተ አምላክ እንደሆነች እንዲህ በጎላ በተረዳ ነገር እናውቃታለን”
፲፱ኛ. ሃይማኖተ አበው ዲዮናስዮስ ም ፺፫ ቁ ፩ “የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ወደ እስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ አባ ሚካኤል በላከው መልእክቱ ሁሉን በፈጠረ በአንድ አብ እናምናለን ዓለም ሳይፈጠር ከአብ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእምባህርይ በተወለደ፤ በኋላ ዘመንም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም ነፍስን ሥጋን ነሥቶ ሰው በሆነ በአንድ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን ከአብ ከወልድ ጋር ቀዳማዊ ማሕየዊ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን”
፳ኛ. ሃይማኖተ አበው አባ ገብርኤል ም ፺፬ ቁ ፲-፲፩ “ዳግመኛ በቅድምና የነበረ ቃል ጥንት ሳይኖረው ዘመን ሳይቀድመው ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ ወልድ ዋሕድ ዓለምን የፈጠረ የሁሉ መኖር በእርሱ የሆነ በይቅርታው ብዛት የአዳምን ልጆች ይቅር ባለ ጊዜ ከምላቱ ሳይወሰን ከአብ ባሕርይ ሳይለይ ልዑል ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ባሕርያችንን እንደተዋሐደ አምናለሁ፡፡ ሁልጊዜ ንጽሕት ድንግል በምትሆን በድንግል ማኅጸን እንደ አደረ  ከአብርሃም ከተገኘ በድንግልና ከጸና ባሕርይዋ የምታውቅ የምትናገር ነፍስ ያለችው የእኛን የሚመስል የአዳምን ሥጋ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ሊዋሐደው እንደፈጠረ አምናለሁ እንዲህ ቃል ሥጋ ሆነ በባሕርይ በአካል ተዋሕዶ ከሥጋችን ሥጋን ከነፍሳችን ነፍስን ነሥቶ ስለእኛ ሰው ሆነ ያለመለወጥ ያለመጠፋፋትም እኛን መምሰልን ገንዘብ አድርጎ ያለመለወጥ ያለመቀላቀል በባሕርዩ ጸንቶ ኖረ”
፳፩ኛ. ሃይማኖተ አበው ባስልዮስ ም ፺፮ ቁ ፲፪ “እኛስ የቀናች የጸናች የተረዳች የከበረች ምሥጢረ ሥላሴን በማመናችን ላይ የሚሰገድለት ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ቃል ወልድ ዋሕድ ሰው የመሆኑን ነገር እንናገራለን በልብ እንደምናምን በአነጋገር በቃልም እንዲህ እናምናለን፡፡ መቀዳደም ሳይኖር አጋዥ ሳይሻ ተድኅሮ ተፈልጦ ሳይኖርበት እሱ ከአብ እንደተወለደ በኋላ ዘመንም እኛን ስለማዳን ባሕርያችንን ስለማደስ እኛን ወደቀድሞ ርስታችን ስለመመለስ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ነፍስን ሥጋን ነሥቶ ሰው እንደሆነ እናምናለን”
ስለዚህ የጌታ ልደቶቹ ሁለት ብቻ ናቸው በሊቃውንቱ ተሰፍረው ቆጥረው በዚህ መልኩ የተገለጹ፡፡ ቅባቶች ዋና ምንፍቅናቸውን በውስጣቸው ደብቀው በጾም ቀናት ነው ክርክር የሚያነሡት፡፡ የቅባቶች መገለጫዎች፡-
-የአጽዋማት መግቢያ እና መውጫ ላይ
-የልደት በዓል አከባበር ላይ
-በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ
-የጌታ ልደታት ሦስት ናቸው
-ዳግም ጥምቀት አያስፈልግም
-እምነቴ ኦርቶዶክስ ብቻ ነው
-ቅባት ምሥጢር ነው ባህለ ትምህርት ነው
ወዘተ የሚሉ ናቸውና ጠንቀቅ እንበል፡፡

#ተፈጸመ፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ታህሳስ ፪ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment