፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፵፪ ጀምረን ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን
ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
ካሳሁን ምናሉ በዚህ ገጽ ላይ ምእራፍ ዘጠኝን ይጀምራል፡፡ ምእራፉም
ስለጌታችን የልደት በዓል ነው የሚናገረው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከዚህ በፊት ጥቂት ነገሮችን የተመለከትን ቢሆንም እዚህ ክፍል ላይም
በጥልቀት እንመለከታለን፡፡
****************************
ሊቃውንቱ በዚህ ጉዳይ በጥሩ ሁኔታ ያብራሩበት የቪዲዮ ትምህርት አለ
ይህንን ሊንክ ጠቅ አድርጉና ተከታተሉት፡፡ ሙሉውን ተከታተሉት እንዳያመልጣችሁ ለሚጠይቋችሁ መልስ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ ተብለናል
ይህ ደግሞ አንዱ ዝግጅታችን ነው፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=sbriV-ou5NU&feature=youtu.be
***************************
የጌታችን ልደት አንድ
ጊዜ ነው፡፡ በዓሉ አከባበር ላይ
ግን በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ ፳፰ ይከበራል፡፡ ይህ የበዓል አከባበር በአባቶቻችን በሲኖዶስ የተወሰነ ነው፡፡ ይህንን አልቀበልም
ማለት መብት ነው ያ ማለትም መንፈስ ቅዱስ የሚመራውን ቅዱስ ሲኖዶስ አልቀበልም ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት እና የሊቃነ ጳጳሳት ጉባዔ ሆኖ ለቤተክርስቲያናችን
የበላይ ወሳኝ አካል ነው፡፡ ይህንን ጉባዔ አልቀበልም ማለት ከኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ውጭ መሆን ነው፡፡ ስለዚህ ነው ካሳሁን ምናሉም ራሱን ከቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ውጭ አድርጎ ሲከራከር እና ሲነታረክ የምናየው፡፡
በመሠረቱ የበዓላት አከባበር ሊያጣላ የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ሲኖዶሱ
በዚህ ጊዜ አክብሩ ብሎ ሲያዝዝ የሚፈጸም ጉዳይ ነው፡፡ ለልደቱ መጽሐፍ ቅዱስ መቸም አንጠቅስም፡፡ ካሳሁን እኮ መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅስ
ነው የሞከረው “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” ብሏልና ጌታ ልደቱ ከ፳፱ አይወጣም ብሎ እርፍ ይላል፡፡ ካስሽ እስኪ
አንድ ነገር መልስልኝ የጌታ ልደት ታህሳስ ፳፱ ቀን ነው የሚል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አምጣልኝ፡፡ ብዙ መጻሕፍትን ጠቅሰሃል ታህሳስ ፳፱ ቀን ነው የሚል ማስረጃ እንዲሆንህ
ልክ ነህ፡፡ የጌታ ልደት እኮ ታህሳስ ፳፱ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በ፳፱ ጌታችን የተወለደበት ነው ተብሎ ባለቤትነቱን ለጌታ
ሰጥተን በ፳፷ ጌታችንን የወለደችበት ነው ብለን ባለቤትነቱን ለእመቤታችን ሰጥተን እናከብራለን፡፡ በዓሉ ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ ፳፷ ይከበራል
ይህ ማለት እኮ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታህሳስ ፳፷ ተወለደ ማለታችን አይደለም የወለደችበት ቀን ነው ብለን እናከብረዋለን እንጅ፡፡
ታህሳስ ፳፷
ጌታችንን የወለደችበት ቀን ነው ብለን የምናከብረው ስለሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡፡
፩ኛ. የዘመነ
ሉቃስ ጳጉሜን ከሌሎች ዓመታት በተለየ ፮ ቀን ትሆናለች፡፡ ይህች ጳጉሜን ስድስት በመሆኗ ምክንያት ታህሳስ ፳፱ ይከበር የነበረውን አንድ ቀን
ወደፊት ታመጣዋለች፡፡ ይህ ከሆነ ጥምቀት ግዝረትስ ለምን ካላችሁ እንመልሳለን፡፡ እግዚአብሔር የአዳምን ንስሐ ተቀብሎ ተስፋ የሰጠው “በኃሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ” ከአምስት
ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ ለአዳም መዳን የጌታችን መሰቀል ግድ ነው ለመሰቀል ደግሞ
መወለድ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ነው “ከልጅ ልጅህ ተወልጀ” ያለው፡፡ ስለዚህ የጌታ በዓለ በኩረ በዓላት ነው ማለት ነው፡፡ አዳም
ተስፋ ያደርግ የነበረውም የጌታን መወለድ ነበር፡፡ ጌታችን ለእኛ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን ግን አላደረገም አንልም፡፡ ለምሳሌ
በስምንተኛው ቀን ተገዝሯል በሠላሳ ዓመቱ ተጠምቋል፡፡ እነዚህ ሥራዎቹ ለእኛ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው እንጅ አዳም ለድኅነቱ
ተስፋ ያደረጋቸው አይደሉም፡፡ ስለዚህ ተስፋ የተደረገበትን በዓል ሱባዔ የተቆጠረለትን በኩለ በዓላት የሆነውን ልደት ብቻ ነው አንድ
ቀን አስቀድመን ልናከብረው አባቶቻችን የወሰኑልን፡፡ ምሥጢር የጠነቀቁ መጻሕፍትን ያወቁ እኮ ናቸው ይህንን የወሰኑልን፡፡ ከልጅ
ልጅህ ተወልጀ በመስቀል ተሰቅየ ሞቼ ተነስቼ አድንሃለሁ አለው እንጅ ተገዝሬ ተጠምቄ አድንሃለሁ አላለውም፡፡ ግዝረቱም ጥምቀቱም
ለአርአያ ነው ልደቱ ሞቱ ትንሳዔው ግን ለድኅነታችን ነው፡፡ ስለዚህ ለድኅነታችን የተፈጸመውን ልደት እንጅ ጥምቀት እና ግዝረቱን
ወደፊት አምጥተን አናከብረውም፡፡
፪ኛ. ወንድ
ልጅ የተጸነሰ እንደሆነ ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀን ይቆያል፡፡ የጌታ ጽንሰት መጋቢት ፳፱ ቀን ነው፡፡ ልደቱም ታህሳስ ፳፱ ቀን ነው ይህን ስንቆጥር ፱ ወር ከ፭ ይሆናል፡፡
በዘመነ ሉቃስ የምትፈጸመዋ ስድስቷ ጳጉሜን ልደቱን ታሕሳስ ፳፰ እንድናከብር ታስገድደናለች ማለት ነው፡፡ በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ
፳፱ እናክብር ካልን ጌታ በማኅጸነ ማርያም የቆየው ፱ ወር ከ፭ መሆኑ ይቀርና ፱ ወር ከ፮ ቀን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ
ፈጽሞ የማይሆን ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የቀን አቆጣጠራችን ያመጣው ጉዳይ እንጅ ከሃድያን ያመጡት ፍልስፍና አይደለም ምሥጢር
ያለበት ጉዳይ እንጅ፡፡ ካሳሁን ይህን ያመጡት መናፍቃን ናቸው ብሎ ስማቸውን ይዘረዝራል ይህ ሁሉ የካሳሁን የመሰለኝ ፍልስፍና ነው፡፡
፫ኛ. የልደት በዓል
ዕለት ምርያ በዋለችበት ዕለት በታህሳስ መጨረሻ እንዲከበር አባቶቻችን አዝዘውናል፡፡ ዕለተ ምርያ የምትባለዋም ጳጉሜን ፭ ናት፡፡
ይችን ዕለት ይዛችሁ ታህሳስ ፳፰ ወይም ታህሳስ ፳፱ ላይ ልደትን ታገኙታላችሁ፡፡ ለምሳሌ በዘመነ ማቴዎስ ዕለት ምርያ (ጳጉሜን
፭) ማክሰኞ ዋለች እንበል፡፡ መስከረም ፩ ረቡዕ ይውላል ማለት ነው፡፡
ታህሳስ ወር ትሄዱና ማክሰኞ የሚውሉ የወሩ የመጨረሻ ቀናትን ታወጣላችሁ
ማለት ነው፡፡ መስከረም ፳፰ ማክሰኞ ይውላል፡፡ የጥቅምት ፳፮ አሁንም ማክሰኞ ይውላል፡፡ የኅዳር ፳፬ ማክሰኞ ይውላል፡፡ የታህሳስ
፳፪ ማክሰኞ ይውላሉ፡፡ ከማክሰኞ እስከ ማክሰኞ ድረስ አስልተን የታህሳስን የመጨረሻ ማክሰኞ የሚውለውን ቀን እናገኛለን ይህ ቀንም
ታህሳስ ፳፱ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ገና በዘመነ ማርቆስ ታህሳስ ፳፱ ይውላል ማት ነው፡፡ ዕለተ ምርያን አልለቀቀም፡፡ የሦስቱንም
ዘመናት (ዘመነ ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ) በዚህ መልኩ አስሉት ታህሳስ ፳፱ ይውላል፡፡ ወደ ዘመነ ዮሐንስ ደግሞ እንምጣ እስኪ፡፡
በዘመነ ሉቃስ ጳጉሜን ፭ ዕለተ ምርያ ረቡዕ ዋለች እንበል፡፡ ሐሙስ ጳጉሜን ፮ ዓርብ መስከረም
፩ ይውላሉ ማለት ነው፡፡ መስከረም ፩ በዋለበት መስከረም ፳፱ ይውላል፡፡ በዚሁ መሠረት ጥቅምት ፳፯፣ ኅዳር ፳፭፣ ታህሳስ ፳፫
ዓርብ ይውላሉ ማለት ነው፡፡ የታህሳስ ዕለተ ምርያ በዋለችበት ረቡዕ የሚውለውን የወሩ መጨረሻ ቀን ፈልጉ እስኪ፡፡ ታህሳስ ፳፫
ዓርብ ውሏል የዚህ ሳምንት ታህሳስ ፴ ይሆናል፡፡ ከዚያ ረቡዕ የሚውለውን ቀን ተመልሳችሁ አስሉት፡፡ ሐሙስ ታህሳስ ፳፱ ይሆናል
ዕለተ ምርያ የዋለችበት ረቡዕ ታህሳስ ፳፰ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዘመነ ዮሐንስ ልደቱ በ፳፰ ይውላል ይከበራል ማለት ነው፡፡
፬ኛ. በዓሉ
በቀኖና የሚከበር እንደመሆኑ መጠን አክብሩት በተባልንበት ዕለት ልናከብረው ግዴታ ነው፡፡ ከጥንተ ጀምራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆና የቆየች ስለሆነች የመንግሥት
መሥሪያ ቤቶች እንኳን በዘመነ ዮሐንስ የሚዘጉት ታህሳስ ፳፰ ነው፡፡ ይህ እንደ ማስረጃ ሊጠቀስ ባይገባውም ማለት ነው፡፡
ጠቅለል ስናደርገው የበዓላት አከባበር ላይ ለመነጋገር በመጀመሪያ የተወለደውን
ክርስቶስን በተዋሕዶ ከበረ ብለን ልንቀበለው ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት የጻፍሁትን እዚህ ላይ መድገም እፈልጋለሁ፡፡
ካሳሁን ምናሉ በዚህ የክህደት መጽሀፉ ላይ በዚህ ገጽ በዋናነት እያነሣ
ያለው ልደት ታህሳስ ፳፰ መከበር የለበትም የሚለውን ነጥብ ነው፡፡ ልደት በ፳፱ እንዲከበር ዲድስቅልያው ፍትሐነገሥቱ አዝዟል ይላል፡፡
ዲድስቅልያውም ፍትሐ ነገሥቱም እንደዚህ ይላሉ ልክ ነው፡፡ መጻሕፍተን ጠቃቅሰው ሰውን ለማሳት ከተነሡ እስኪ እነዚህን ጉዳዮች እንመልከታቸው፡፡
፩ኛ. መሠረተ እምነቱን ደብቀን በቀኖና በበዓላት አከባበር ላይ በሥርዓተ
ቤተክርቲያን ላይ መከራከር አለብን ወይ? አንድ ሰው መከራከር ያለበት እኮ የእምነቱን መሠረታዊ አስተምህሮ በሚገባ ከተረዳ በኋላ
ነው፡፡ አንድ ሙዚቀኛ በትዝታ ቅኝት አምባሰልን እጫወታለሁ ቢል አይችልም፤ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ተጫዋቾች ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ተጫዋቾች አሰላለፍ ማውራት አይችልም ምክንያቱም አይመለከተውማ፡፡ ከሆነለት የራሱን አሰላለፍ ነው ማሳመር ያለበት፡፡ ምን ለማለት
ፈልጌ ነው ልደት ታህሳስ ፳፰ ወይም ታህሳስ ፳፱ ይከበር አይከበር ብሎ ለመናገር በመጀመሪያ ስለጌታ ልደት ማወቅ አለብን፡፡ የጌታን
ልደት ከማክበራችን አስቀድሞ ጌታ የተወለደው እንዴት ነው? ቃል ሥጋ የሆነበት ምሥጢር ምንድን ነው? እንዴት የሰውን ሥጋ ለበሠ?
አካላዊ ቃል እንዴት በሥጋ ማርያም ተገለጠ? ምሥጢሩ እንዴት ነው? ወዘተ የሚለውን ነገር መጀመሪያ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ እንዴት
በሥጋ ማርያም እንደተገለጠ ሳንስማማ ልደት ታህሳስ ፳፰ ወይም ታህሳስ ፳፱ ነው እያልን ልንጨቃጨቅ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ይህ
መሠረታዊ ጉዳይ አይደለምና፡፡ የልደት በዓል ሳይከበርም ሊቀር ይችል ነበር እኮ ሥርዓት ቀኖና ባይሠራለት ኖሮ፡፡ አሁን ግን አባቶቻችን
እንዳዘዙን እናከብራለን፡፡ ልደት ታህሳስ ፳፰ ወይም ታህሳስ ፳፱ ተከበረ ማለት እኮ ጌታችን በየዓመቱ ይወለዳል ማለታችን አይደለም፡፡
ታዲያ በዐራት ዓመት አንድ ጊዜ ስለምትከበረው አንዲት ቀን ምን አከራከረን፡፡
፪ኛ. ዲድስቅልያው ላይ የተጻፈውን ሁሉ ተቀብላችኋል ወይ አሁን ተግባራዊ
እየተደረገ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ የዲድስቅልያውን ሃሳብ ፍትሐ ነገሥቱም ስለሚተባበርበት አንዳንድ ነጥቦችን
ማንሣት እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌ ስለኤጲስቆጶሳት በሚናገርበት አንቀጹ ላይ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት ቀጥታ መዝግቦት እናገኛለን፡፡
“ማንም ሰው ኤጲስ ቆጶስነትን ሊሾም ቢወድ እነሆ መልካም ሥራን ወደደ፡፡ ነውር የሌለበት ሰው ኤጲስ ቆጶስ ይሆን ዘንድ ይገባል፡፡
አንዲት ሴት ያገባ፣ በሃሳቡ ንቁ የሆነ… ቤተሰቡን የሚያስተዳድርና ልጆቹን በሚገባ የሚያሳድግ” ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፭ ቁጥር
፹፫ ተመልከቱ፡፡ ይህ ራሱ ሳይቀየር ዲድስቅልያው ላይም አለ ስለኤጲስቆጶሳት የሚናገረውን አንቀጽ ተመልከቱ፡፡ እዚህ ላይ ለማሳየት
የፈለግሁት ምንድን ነው፡፡ የጌታ ልደትን ዲድስቅልያ በ፳፱ አክብሩ እያለ “በተዋሕዶ ከበረ” የሚሉ የተዋሕዶ አማኞች ልደትን ከዐራት
ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ ፳፰ ያከብራሉ ብሎ እንደነውር ስላመጣ ዲድስቅልያውን በሙሉ ከተቀበላችሁትማ ስለኤጲስ ቆጶሳትም
ሲናገር “አንዲት ሴት ያገባ፣ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርና ልጆቹን በሚገባ የሚያሳድግ” ይላልና ያገባ ኤጲስ ቆጶስ መሾም የለበትም
ስንል ዲድስቅልያውን አልተቀበሉትም ልትሉን ነው ለማለት ነው፡፡ ታዲያ ዲድስቅልያውን ስታከብር “ኤጲስ ቆጶስም ያገባ እና ቤተሰቡን
የሚያስተዳድር እንዲሁም ልጆቹን በሚገባ የሚያሳድግ” መሆን አለበት በማለት ያገቡ ጳጳሳትን እንድታደርግ ቤተክርስቲያንንም እየተገዳደርህ
ነው ማለት እኮ ነው፡፡ ስለዚህ ልደት መቼ ጀምሮ ነው ታህሳስ ፳፰ መከበር የጀመረው እና ምሥጢሩስ ምንድን ነው ብለህ ብትመረምር
ይበጅሃል እልሃለሁ፡፡
፫ኛ. ልደትን ታህሳስ ፳፰ እንዲከበር ያደረጉ መናፍቃን ናቸው ብሎ ካሳሁን
የሚተርተው ተረት ምንም ማስረጃ እና መሳመኛ የሌለው ግምታዊ ጽሑፍ ነው፡፡ ካሳሁን በጠቀሰው ዘመን የተነሡ መናፍቃን እኮ ምንፍቅናቸው በጉባዔ ተጋልጦ
ለእያንዳንዱ መልስ ተሰጥቶበታል፡፡ ታዲያ ልደትን በታህሳስ ፳፰ እናክብር ስላሉ መናፍቃን ተብሎ አንቀጽ ያልገባ ለምንድን ነው?
“ንስጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ህጹጽ” ብሏል ብለህ ያላለውን አለ እንዳልከው ሁሉ የፈጠራ ስራ ነው እየሠራህ ያለህ እና ልብ ይስጥህ፡፡
፬ኛ. ልደት ከ፳፱ መውጣት የለበትም በሚለው ከጸናችሁ እስኪ እነዚህን
በዓላት ለምን እንደዚህ እንዲቀያየሩ ተደረገ የሚለውን መልሱልን፡፡ ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት የሚውሉበትን ቀን ቀን አስቡት፡፡
ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት ፳፯ ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት ፳፱ ጥንተ ዕርገቱ ግንቦት ፰ ነው እኛ ግን ስቅለቱን በየዓመቱ ግን እነዚህን
በዓላት የምናከብረው ቀኑን እየቀያየርን ዕለቱን ሳንቀያይር ነው፡፡ ለምን እንዲህ አደረግን ታዲያ ይህም ስህተት ሰርተን ነው ማለት
ነው? ቀኖና ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ወደኋላ መለስ ብላችሁ በየዓመቱ እነዚህን በዓላት መቼ መቼ እንዳከበርናቸው ተመልከቱ፡፡ በየዓመቱ
ይለያያሉ ዕለታቸው አይቀየርም እንጅ ቀናቸው ይቀያየራል፡፡ ይህን ዝም ብለን የተቀበልን ሰዎች በጌታ ልደት ላይ ምን አከራከረን?
ልደትን እንደእነዚህ ሁሉ ቀያይረን እንድናከብር ብንታዘዝ ኖሮ እኮ አይደለም በምሥጢር ፳፰ እንዲከበር የታዘዝነውን ቀርቶ መስከረም፣
ጥቅምት፣ ህዳር፣ ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት፣ ሚያዝያ፣ ሰኔ፣ ሐምሌ፣ ነሐሴ ወይም ጳጉሜን ከሚውሉ በአንዱ ቀን አክብሩ ቢሉን ኖሮ ልናከብረውም እንችል ነበር፡፡
በዓሉ በመከበሩ ባለመከበሩ ዶግማችንን አይለውጠውምና፡፡ መከራከር ያለብን በመጀመሪያ መሠረተ እምነቱ ላይ ነው፡፡ “በተዋሕዶ ከበር”
እና “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” በሚለው ሰፊ ልዩነት ላይ መታረቅ አለብን መጀመሪያ፡፡ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” እያልህ
ልደት ፳፰ ተከበረ ፳፱ ተከበረ ምን ቤት ሆነህ ይመለከትሃል? ወልድን ፍጡር ብለህ እያመንህ እኛ ስለምናከብረው ልደት ምን ያገባሃል?
፭ኛ.
በዓላት አከባበር ላይ ተንተርሰን አንዱን መናፍቅ አንዱን አማኒ ልንለው አንችልም፡፡ መናፍቅ አማኒ የሚያሰኘን መሠረተ እምነታችን
ነው፡፡ እርሱ ደግሞ የሰማይ እና የምድር ያህል ሰፊ ልዩነት ያለን ሰዎች ነን በእኛ እና በእናንተ መካከል፡፡ እኛ “ወልደ አብ
ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ” እንላለን እነርሱ ደግሞ “ወልደ አብ ወልደ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ይላሉ፡፡ ይህ
ልዩነት ነው አማኒ መናፍቅ የሚያስብለን እንጅ ልደት ፳፰ ወይም ፳፱ ስላከበርን አይደለም፡፡ ልደቱን ከማክበርህ በፊት ልደቱ ስለሚከበርለት
ጌታ ምሥጢረ ሥጋዌ ተማር፡፡ ይህ ግድ ነው ዝም ብሎ ልደት ማክበር እኮ አይደለም ልደቱ ደግሞ እንደምድራውያን ሰዎች አይደለም፡፡
ስለዚህ በመጀመሪያ መሠረተ እምነቱ ላይ መተማመን ይገባናል እንጅ የበዓላት
አከባበር ላይ ዘው ብለን ገብተን ልናወናብድ አይገባውም፡፡ ይህንን መጠየቅ ያለበት የሚመለከተው ሰው ብቻ ነው የማይመለከተው ሰው
አይመለከተውም፡፡ ቤተክርቲያናችን አስቀድመን ከላይ በገለጽነው ምክንያት ልደቱን ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ
፳፰ ስታከብር ኖራለች አሁን እያከበረች ትገኛለች ወደፊትም እንዲሁ ስታከብር ትኖራለች፡፡
በዚህ
ጉዳይ የቀረበውን ድንቅ ትምህርት ከዚህ ሊንክ ላይ ተጭናችሁ ተከታተሉት፡፡ ምርጥ የሆነ ማብራሪያ እና ገለጻ የተደረገበት የቤተክርቲያናችን
ሊቃውንት የሚስማሙበት ሃሳብ ነው፡፡ አደራ ሙሉውን ተከታተሉት፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=sbriV-ou5NU&feature=youtu.be
#ይቀጥላል
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፳፱
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment