Monday, December 4, 2017

መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? ክፍል ፲፫



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፳፰ ጀምረን  ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መድሎተ አሚን ላይ በቅባተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ብለዋል የሚለውን ውሸት መድሎተ አሚንን በፎቶ አስቀምጫለሁ፡፡ ፍትሐ ነገሥቱንም እንዲሁ ለማጣቀሻነት እንድትመለከቱት በፎቶ አያይዠላችኋለሁ፡፡

ካሳሁን ምናሉ በዚህ የክህደት መጽሀፉ ላይ በዚህ ገጽ በዋናነት እያነሣ ያለው ልደት ታህሳስ ፳፰ መከበር የለበትም የሚለውን ነጥብ ነው፡፡ ልደት በ፳፱ እንዲከበር ዲድስቅልያው አዝዟል ይላል፡፡ ዲድስቅልያው እንደዚህ ይላል ልክ ነው፡፡ አሁን ዲድስቅልያው የተናገረውን በሙሉ መቀበል አለብን፡፡ ግን ማንሣት የሚገባን ጉዳይ ይኖራል፡፡
፩ኛ. መሠረተ እምነቱን ደብቀን በቀኖና በበዓላት አከባበር ላይ በሥርዓተ ቤተክርቲያን ላይ መከራከር አለብን ወይ? አንድ ሰው መከራከር ያለበት እኮ የእምነቱን መሠረታዊ አስተምህሮ በሚገባ ከተረዳ በኋላ ነው፡፡ አንድ ሙዚቀኛ በትዝታ ቅኝት አምባሰልን እጫወታለሁ ቢል አይችልም፤ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ተጫዋቾች ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች አሰላለፍ ማውራት አይችልም ምክንያቱም አይመለከተውማ፡፡ ከሆነለት የራሱን አሰላለፍ ነው ማሳመር ያለበት፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው ልደት ታህሳስ ፳፰ ወይም ታህሳስ ፳፱ ይከበር አይከበር ብሎ ለመናገር በመጀመሪያ ስለጌታ ልደት ማወቅ አለብን፡፡ የጌታን ልደት ከማክበራችን አስቀድሞ ጌታ የተወለደው እንዴት ነው? ቃል ሥጋ የሆነበት ምሥጢር ምንድን ነው? እንዴት የሰውን ሥጋ ለበሠ? አካላዊ ቃል እንዴት በሥጋ ማርያም ተገለጠ? ምሥጢሩ እንዴት ነው? ወዘተ የሚለውን ነገር መጀመሪያ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ እንዴት በሥጋ ማርያም እንደተገለጠ ሳንስማማ ልደት ታህሳስ ፳፰ ወይም ታህሳስ ፳፱ ነው እያልን ልንጨቃጨቅ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ይህ መሠረታዊ ጉዳይ አይደለምና፡፡ የልደት በዓል ሳይከበርም ሊቀር ይችል ነበር እኮ ሥርዓት ቀኖና ባይሠራለት ኖሮ፡፡ አሁን ግን አባቶቻችን እንዳዘዙን እናከብራለን፡፡ ልደት ታህሳስ ፳፰ ወይም ታህሳስ ፳፱ ተከበረ ማለት እኮ ጌታችን በየዓመቱ ይወለዳል ማለታችን አይደለም፡፡ ታዲያ በዐራት ዓመት አንድ ጊዜ ስለምትከበረው አንዲት ቀን ምን አከራከረን፡፡
፪ኛ. ዲድስቅልያው ላይ የተጻፈውን ሁሉ ተቀብላችኋል ወይ አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ የዲድስቅልያውን ሃሳብ ፍትሐ ነገሥቱም ስለሚተባበርበት አንዳንድ ነጥቦችን ማንሣት እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳ ስለኤጲስቆጶሳት በሚናገርበት አንቀጹ ላይ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት ቀጥታ መዝግቦት እናገኛለን፡፡ “ማንም ሰው ኤጲስ ቆጶስነትን ሊሾም ቢወድ እነሆ መልካም ሥራን ወደደ፡፡ ነውር የሌለበት ሰው ኤጲስ ቆጶስ ይሆን ዘንድ ይገባል፡፡ አንዲት ሴት ያገባ፣ በሃሳቡ ንቁ የሆነ… ቤተሰቡን የሚያስተዳድርና ልጆቹን በሚገባ የሚያሳድግ” ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፭ ቁጥር ፹፫ ተመልከቱ፡፡ ይህ ራሱ ሳይቀየር ዲድስቅልያው ላይም አለ ስለኤጲስቆጶሳት የሚናገረውን አንቀጽ ተመልከቱ፡፡ እዚህ ላይ ለማሳየት የፈለግሁት ምንድን ነው፡፡ የጌታ ልደትን ዲድስቅልያ በ፳፱ አክብሩ እያለ “በተዋሕዶ ከበረ” የሚሉ የተዋሕዶ አማኞች ልደትን ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ ፳፰ ያከብራሉ ብሎ እንደነውር ስላመጣ ዲድስቅልያውን በሙሉ ከተቀበላችሁትማ ስለኤጲስ ቆጶሳትም ሲናገር “አንዲት ሴት ያገባ፣ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርና ልጆቹን በሚገባ የሚያሳድግ” ይላልና ያገባ ኤጲስ ቆጶስ መሾም የለበትም ስንል ዲድስቅልያውን አልተቀበሉትም ልትሉን ነው ለማለት ነው፡፡ ታዲያ ዲድስቅልያውን ስታከብር “ኤጲስ ቆጶስም ያገባ እና ቤተሰቡን የሚያስተዳድር እንዲሁም ልጆቹን በሚገባ የሚያሳድግ” መሆን አለበት በማለት ያገቡ ጳጳሳትን እንድታደርግ ቤተክርስቲያንንም እየተገዳደርህ ነው ማለት እኮ ነው፡፡ ስለዚህ ልደት መቼ ጀምሮ ነው ታህሳስ ፳፰ መከበር የጀመረው እና ምሥጢሩስ ምንድን ነው ብለህ ብትመረምር ይበጅሃል እልሃለሁ፡፡

፫ኛ. ልደትን ታህሳስ ፳፰ እንዲከበርያደረጉ መናፍቃን ናቸው ብሎ ካሳሁን የሚተርተው ተረት ምንም ማስረጃ እና መሳመኛ የሌለው ግምታዊ ጽሑፍ ነው፡፡ በተለይ ስለ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የሰነዘረው ጽርፈት አጽማቸው እሾኽ ሆኖ ይወጋዋል ባይ ነኝ፡፡ ካሳሁን በጠቀሰው ዘመን የተነሡ መናፍቃን እኮ ምንፍቅናቸው በጉባዔ ተጋልጦ ለእያንዳንዱ መልስ ተሰጥቶበታል፡፡ ታዲያ ልደትን በታህሳስ ፳፰ እናክብር ስላሉ መናፍቃን ተብሎ አንቀጽ ያልገባ ለምንድን ነው? “ንስጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ህጹጽ” ብሏል ብለህ ያላለውን አለ እንዳልከው ሁሉ የፈጠራ ስራ ነው እየሠራህ ያለህ እና ልብ ይስጥህ፡፡
፬ኛ. ልደት ከ፳፱ መውጣት የለበትም በሚለው ከጸናችሁ እስኪ እነዚህን በዓላት ለምን እንደዚህ እንዲቀያየሩ ተደረገ የሚለውን መልሱልን፡፡ ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት የሚውሉበትን ቀን ቀን አስቡት፡፡ ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት ፳፯ ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት ፳፱ ጥንተ ዕርገቱ ግንቦት ፰ ነው እኛ ግን ስቅለቱን በየዓመቱ ግን እነዚህን በዓላት የምናከብረው ቀኑን እየቀያየርን ዕለቱን ሳንቀያይር ነው፡፡ ለምን እንዲህ አደረግን ታዲያ ይህም ስህተት ሰርተን ነው ማለት ነው? ቀኖና ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ወደኋላ መለስ ብላችሁ በየዓመቱ እነዚህን በዓላት መቼ መቼ እንዳከበርናቸው ተመልከቱ፡፡ በየዓመቱ ይለያያሉ ዕለታቸው አይቀየርም እንጅ ቀናቸው ይቀያየራል፡፡ ይህን ዝም ብለን የተቀበልን ሰዎች በጌታ ልደት ላይ ምን አከራከረን? ልደትን እንደእነዚህ ሁሉ ቀያይረን እንድናከብር ብንታዘዝ ኖሮ እኮ አይደለም በምሥጢር ፳፰ እንዲከበር የታዘዝነውን ቀርቶ መስከረም፣ ጥቅምት፣ ህዳር፣ ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት፣ ሚያዝያ፣ ሰኔ፣ ሐምሌ፣ ነሐሴ ወይም  ጳጉሜን ከሚውሉ በአንዱ ቀን አክብሩ ቢሉን ኖሮ ልናከብረውም እንችል ነበር፡፡ በዓሉ በመከበሩ ባለመከበሩ ዶግማችንን አይለውጠውምና፡፡ መከራከር ያለብን በመጀመሪያ መሠረተ እምነቱ ላይ ነው፡፡ “በተዋሕዶ ከበር” እና “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” በሚለው ሰፊ ልዩነት ላይ መታረቅ አለብን መጀመሪያ፡፡ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” እያልህ ልደት ፳፰ ተከበረ ፳፱ ተከበረ ምን ቤት ሆነህ ይመለከትሃል? ወልድን ፍጡር ብለህ እያመንህ እኛ ስለምናከብረው ልደት ምን ያገባሃል?

፭ኛ. በዓላት አከባበር ላይ ተንተርሰን አንዱን መናፍቅ አንዱን አማኒ ልንለው አንችልም፡፡ መናፍቅ አማኒ የሚያሰኘን መሠረተ እምነታችን ነው፡፡ እርሱ ደግሞ የሰማይ እና የምድር ያህል ሰፊ ልዩነት ያለን ሰዎች ነን፡፡ እኛ “ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ” እንላለን እነርሱ ደግሞ “ወልደ አብ ወልደ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ይላሉ፡፡ ይህ ልዩነት ነው አማኒ መናፍቅ የሚያስብለን እንጅ ልደት ፳፰ ወይም ፳፱ ስላከበርን አይደለም፡፡ ልደቱን ከማክበርህ በፊት ልደቱ ስለሚከበርለት ጌታ ምሥጢረ ሥጋዌ ተማር፡፡ ይህ ግድ ነው ዝም ብሎ ልደት ማክበር እኮ አይደለም ልደቱ ደግሞ እንደምድራውያን ሰዎች አይደለም፡፡
፮ኛ. ልደትን በ፳፱ ብቻ ማክበርን ጠንቅቀን በመያዛችን እውነተኞች ነን ስለሚለው የቅባቶች መታጀር ስናይ እንደነቃለን፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕንም በማንሳት ለመሳደብ የሞከረው ደፋሩ ካሰሁን በብራና መጻሕፍት ሁሉ የተጻፈው በ፳፱ አክብሩ ነው የሚል ብሎ “ዝክሪ እና ጳውሊ” ጽፈውታል የሚለውን መጽሐፍ ይጠቅሳል፡፡ ይህ መጽሐፍ ቆጋ የሚገኝ ብቻ ነው እንግዲህ፡፡ በነገራችን ላይ ብራና መጽሐፉ ከቆዳ መዘጋጀቱን ያመለክታል እንጅ ጥንታዊነቱን እና እውነተኛነቱን አያስረዳም፡፡ ድሮ ወረቀት ስላልነበረ የወረቀት መጻሕፍትን ጥንታውያን ናቸው ብንል ስህተት ነው፡፡ ዛሬ ብራና ስላለም ሁሉም የብራና መጻሕፍት ጥንታውያን ናቸው ብንል ስህተት ነው፡፡ የአንድ መጽሐፍ እውነተኛነቱ የሚረጋገጠው ደግሞ ራሱ በያዘው ብቻ ሳይሆን በሌሎች መጻሕፍትም ሚዛንነት ተመዝኖ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነጥቦች ማስተዋል አለብን፡፡
፯ኛ. የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን ስም በማንሣትህ አፈርሁብህ፡፡ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ በመድሎተ አሚን መጽሐፋቸው ላይ ደግመው ደጋግመው መንፈስ ቅዱስ በማሕጸን አድሮ የባሕርይ አምላክ ሆነ ብለው ተናግረዋል ይላል፡፡ በዚህም መሠረት እውነተኛዋ እምነት “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ነው ይላል፡፡ በጣም የምናዝነው “ወልደ አብ” እና ይህ “መሠረተ ሐይማኖት” መልአከ ብርሃንን በስማቸው ሲነግዱባቸው ስናይ ነው፡፡ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ባለውለታ የዲማ ሊቅ በሃይማኖታቸውም የሚመሠከርላቸው የሞተ ልጃቸውን ያስነሡ የበቁ ሊቅ ናቸው፡፡ ታዲያ እርሳቸው እነካሳሁን በጠቀሱት መድሎተ አሚን መጽሐፋቸው ላይ እንኳን በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ሊሉ ቀርቶ እንዲህ ያሉትንም አሳፍረው ነው መልስ የጻፉላቸው፡፡ መድሎተ አሚን የተዘጋጀችው እኮ ለእንደዚህ ላለው ምንፍቅና ነው፡፡ ታዲያመልአከ ብርሃን አድማሱ ለጃንሆይ ስለጻፉት መጽሐፍ በጻፉላቸው መልእክት ላይ  ምን ይላሉ መሰላችሁ “ከአባቶችዎ ከአብርሃ ወአጽብሃ ጀምሮ ሳይቋረጥ ተያይዞ የወረደው አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሁለት ልደት በተዋሕዶ ከበረ የሚል ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት  ጸንቶ እንዲኖር…” እያሉ ይቀጥላሉ፡፡ መልአከ ብርሃንስ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ አሉ ካላችሁ እናንተ ዝም ብላችሁ በግምት እንደምትነዱ ያሳያል፡፡ በታዋቂ ሊቃውንት ስም ስትነግዱም አለማፈራችሁ፡፡ አንዴ ዝክሪ እና ጳውሊ ትላላችሁ አንዴ መልአከ ብርሃን ትላላችሁ፡፡ ተግባብተናል ዲማ እውነተኛ የሃይማኖት ሀገር ናትና በዲማ ሊቃውንት ስም የእናንተንም ኑፋቄ ድጋፍ ልታሰባስቡበት ፈልጋችሁ ነው ግን አይሆንም፡፡ በነገራችን ላይ ያላሉትን አሉ ብሎ ለዚያውም ሁለት መጻሕፍትን ጠቅሶ ትክክለኛዋ ሃይማኖት እንዲህ ናት ማለት ይቻላል እንዴ?
፰ኛ. የደብረ ጽሙና ሊቃውንት ዝክሪ እና ጳውሊ እንዲህ ብለዋል የሚለው ያልተባለ ተረት አምና በሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ ተጽፏል፡፡ ይህንን መጽሐፍም በብራና የተጻፈው እያለ ይተርታል፡፡ ዝክሪ እና ጳው ይህንን ነገር አልተናገሩም ከዚህ በፊት ስለእነ ዝክሪ እና ጳውሊ በሰፊው ከመድሎተ አሚን ያለውን ሳልጨምር ሳልቀንስ አስፍሬላችኋለሁ፡፡ ቅባቶች ግን የጨመሩት የቀነሱት ያደባለቁት ያጨማለቁት ነገር አለ፡፡ ዋና ዓላማቸው በሊቃውንቱ ስም መነገድ ስለሆነ ነው፡፡ ዝክሪ እና ጳውሊ የተናገሩትን የተጠየቁትን ለተጠየቁት የመለሱትን በታሪክ አገኘሁት ብለው ከዛሬ ሃምሳ ስድስት ዓመት በፊት በ፲፱፻፶፬ ዓ.ም ከጻፉት ከመድሎተ አሚን መጽሐፋቸው ላይ ሙሉውን እነሆ አንብቡት፡፡

ኢትዮጵያን ግራኝ መሀመድ በወረራት ጊዜ ዐፄ ልብነ ድንግል ከፖርቹጊዝ መንግሥት እርዳታ ጠይቀው እርሳቸው ከሞቱ በኋላ በፖርቹጊዞች እርዳታ ግራኝ ድል ሆኖ ኢትዮጵያ ሙሉ ነጻነቷን አግኝታ መንግሥቷን በትክክል ማቋቋሟ የታወቀ ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ከኢትዮጵያ ተልኮ ፖርቹጊዞችን ለእርዳታ ያመጣው ቤርሙዲዝ ከኢትዮጵያ ግዛት ገሚሱ ለፖርቹጊዝ መንግሥት ይሰጥ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም ከእንግዲህ ወዲያ አቡን ከእስክንድርያ መምጣቱ ቀርቶ ከሮም ይምጣ እኔም ለኢትዮጵያ አንደኛ መጀመሪያ ሮማዊ ጳጳስ ልሁን ብሎ ዐፄ ገላውዴዎስን ጠየቀ፡፡ ዐፄ ገላውዴዎስም ሊቃውንቱን ሰብስበው ምን እናድርግ ብለው ጠየቁ፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንትም ፍርድ በቃ ይስጡን እንከራከርና ሮማውያን ቢረቱን እንልቀቅላቸው ብንረታቸው ይልቀቁልን አሏቸው፡፡ ንጉሡም ፈቅደው ጉባዔ ተደረገ ለኢትዮጵያ ሊቃውንት አፈ ጉባኤ ዝክሪና ጳውሊ ኾኑ፡፡

ዝክሪና ጳውሊም በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ አጠገብ የሚገኝ የደብረ ጽሙና ገዳም ሊቃውንት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሮማውያንን ሀገራችሁ ወዴት ነው ሃይማኖታችሁ ምንድን ነው ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ሮማውያን ሲመልሱ ሀገራችን ሮም ነው፤ ሃይማኖታችንም ኹለት ባሕርይ ኹለት ጠባይዕ አንዱ የመለኮቱ አንዱ የትስብእቱ እንላለን፡፡ ኹለተኛም ወልድ ከአብ ያንሳል መንፈስ ቅዱስም ከወልድ ያንሳል እንላለን አሏቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሲመልሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ የሚል ምን አለ እስኪ አስረዱን አሏቸው፡፡

ሮማውያን ሲመልሱ እርሱው ራሱ ወልድ ደቀመዛሙርቱ ሕልፈተ ዓለም የሚሆነው መቼ ነው ብለው ቢጠይቁት መላእክትም ቢሆኑ ወልድም ቢሆን ከአብ በቀር ያችን ዕለት ያችን ሰዓት የሚያውቃት የለም ብሏል፡፡ ስለዚህ አብ መለኮት ስለሆነ ያውቃል ወልድ መንፈስ ቅዱስ ግን መለኮት ስላልሆኑ አያውቁም እንላለን እናንተ ይህን ነገር ምን ትሉታላችሁ አሉ፡፡

አባ ዝክሪ ሲመልስ ሦስቱን አካላት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን አንድ አምላክ የምንላቸው አብን ልብ ወልድን ቃል መንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ ብለን በአብ ልብነት ያስባሉ ያውቃሉ፤ በወልድ ቃልነት ይናገራሉ፤ በመንፈስ ቅዱስ እስትንስነት ሕያዋን ሆነው ይኖራሉ ለየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ የላቸውም በማለት ነው፡፡ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ያለው አንድ ሰው በልቡ አስቦት አውቆት ለመናገር ጊዜው ባለመድረሱ ሰዓት እየጠበቀለት ሰውሮ የያዘውን ነገር ጊዜው ባለመድረሱ ምክንያት በቃሉ ሳይናገረው ቢቆይ ቢጠየቅም ዛሬ አልናገረውም ቢል አያውቅም እንደማይባል ወልድም ያችን ዕለት ያችን ሰዓት የምትገለጽበት ጊዜው እስኪደርስ በልቤ በአብ ሰውሬ አቆያታለሁ እንጅ ዛሬ በቃልነቴ አውጥቼ አልናገራትም ማለቱ ነው እንጅ የማያውቃት ሆኖ አይደለም፡፡ እንዲህስ ባይሆን የከዊን ስማቸውና ግብራቸው ተፋልሶ አብ ቃል፤ ወልድ ልብ በተባሉ ነበረ አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ሮማውያን መልስ አጥተው ዝም አሉ፡፡

ኹለተኛ ጥያቄ፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሮማዊ ተነሥቶ መለኮት ሥጋ አልሆነም ሥጋም መለኮት አልሆነም ሥጋ ለመለኮት እንደ ብረት ልብስ እንደ ጥሩር ኾነው መለኮትና ሥጋ እንደ ኀዳሪና ማኅደር ኾነው መለኮት የመለኮትን ሥራ ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ሲሰሩ ኖረው በዕርገቱ ጊዜ የለበሰውን ሥጋ አውልቆ በሦስተኛው ሰማይ አኑሮት በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ተቀመጠ፡፡ የዚህም ምሳሌው አንድ ንጉሥ ለጦርነት ወደ ሰልፍ ሲገባ የጦርነት ልብስ ይለብሳል፡፡ ሲዋጋ ውሎ ድል ካደረገ በኋላ የለበሰውን የጦር ልብስ አውልቆ ከግምጃ ቤት ሰቅሎ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ እንደሚቀመጠው ያለ ነው እንጅ ትስብእቱን ከመለኮቱ ጋራ በአባቱ ቀኝ አያስቀምጠውም አለ፡፡

አባ ዝክሪ ሲመልስ ነፍስ ርቀቷን ሳትለቅ ሥጋ ግዙፍ ውሱን መኾኑን ሳይለቅ ተዋሕደው አንድ ሰው እንዲኾኑ መለኮት ምልዐቱን ስፍሐቱን ርቀቱን ሳይለቅ ትስብእትም ግዙፍነቱን ውሱንነቱን ሳይለቅ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾኗል እንጅ እንደ ልብስና እንደ ገላ አይደለም አለ፡፡

ሮማዊ መለኮት ከደረሰበት ኹሉ ይህ መዋቲ ትስብእት ደረሰ ትላለህን አለ፡፡

አባ ዝክሪ ሲመልስ እኔስ መለኮት እና ትስብእት በተዋህዶ አንድ ስለሆኑ መለኮት በሥጋ ውሱን ግዙፍ ኾነ፤ ትስብእትም በመለኮት ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ ኾነ እላለሁ፡፡ ትስብእት ከመለኮት ተለይቶ በሦስተኛው ሰማይ እንዳልቀረ  በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ እንደተቀመጠም ሲያስረዳ አሜሃ ትሬእይዎ ለወልደ እጓለ እመሕያው እንዘ ይነብር በየማነ እግዚአብሔር ብሏል፡፡ በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት ዳግም እንዲመጣ ሲያስረዳም ወአመ ይመጽእ ወልደ እጓለ እመሕያው በስብሐተ አቡሁ ወኲሎሙ መላእክቲሁ ምስሌሁ ብሏል፡፡ ይህ ንባብ በቅዱስ ወንጌል መጻፉን ታምናለህ ትክዳለህ? አለው፡፡ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
ሦስተኛ ጥያቄ፡፡
ሮማዊ እኔ ክርስቶስን ፍጡር እለዋለሁ አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ ክርስቶስን ፍጡር የሚል ንባብ ከምን ታገኛለህ አለው፡፡

ሮማዊ አምላክ ከኾነ ከሣምራዊት ውኃ እስኪለምን ድረስ ለምን ተጠማ ከላይ ያለው ሐኖስ ከታች ያለው ውቅያኖስ በመኃል እጁ ሲሆን አምላክ ይጠማልን አለ፡፡

አባ ጳውሊ ሲመልስ ፍጡር ከኾነ የእግዚአብሔርንስ ስጦታ አውቀሽ ቢኾን ይህ ውኃ አጠጭኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደሆነ ተገንዝበሽ አንች የሕይወት ውኃን አጠጣኝ ብለሽ በለመንሺው ነበረ እርሱም በሰጠሸ ነበረ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ኹሉ ዳግመኛ ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ዳግመኛ ይህ እኔ የምሰጠው ውኃ ለዘላለም ሕይወት ሊኾነው ከውስጡ ሲመነጭ ይኖራል እንጅ ዳግመኛ አይጠማም ለምን አላት አለው፡፡

ዐራተኛ ጥያቄ፡፡
ሮማዊ አምላክ ከኾነ አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት ብሎ ለምን ጠየቀ የተቀበረበትን ባላወቀውም ነበረን፡፡ ኹለቱ ዕውራንስ የዳዊት ልጅ ይቅር በለን ባሉት ጊዜ ምን ትሻላችሁ ብሎ ለምን ጠየቃቸው የሚሹትን ባላወቀውም ነበረን አለ፡፡


አባ ጳውሊ ሲመልስ እግዚአብሔር አዳምን አይቴ ሀሎከ  ብሎ ጠየቀው ይላል ዘፍ ፫÷፱፡፡ ሙሴንም ምንት ውስተ እዴከ ብሎ ጠየቀው ይላል፡፡ ዘፀ ፬÷፪፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መጠየቁ አዳም ያለበትን ቦታ አጥቶት፤ ሙሴም በእጁ ምን እንደያዘ አላውቀው ብሎ ይኾን አይደለም፡፡ ይህም ይህን የመሰለ ጥያቄ ነው፡፡ በዚያውስ ላይ ፍጡር ከኾነ አልዓዛር አልዓዛር ነዓ ፃዕ አፍአ እመቃብር ብሎ ሊያስነሣው እንደምን ቻለ፡፡ በደረቅ ግንባርስ ላይ ዐይን ሊፈጥር እንደምን ቻለ አለው፡፡

ሮማዊ ይህን የመሳሰለስ ቅዱሳንም ልዩ ልዩ የኾኑ ብዙ ተአምራት ያደርጋሉ አለ፡፡

አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱሳን ልዩ ልዩ ተአምራት ቢያደርጉ የርሱን ስም ጠርተው በስሙ ለኢየሱስ ናዝራዊ ተንሥእ ወሑር እያሉ ነው፡፡ ግብ ሐዋ ፫÷፮ ፤፱÷፴፬፤ ፲፮÷፲፰ እርሱ ግን እኤዝዘከ ፃዕ እምኔሁ እያለ በገዛ ሥልጣኑ ነውና ቅዱሳን ከሚያደርጉት ተአምራት ጋራ ሊነጻጸር አይገባውም አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
ዐምስተኛ ጥያቄ፡፡
ስሙን ልዮን የሚሉት አንድ ሮማዊ ተነሥቶ ወልደ አብ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሥጋ ማርያምን በለበሰ ጊዜ ሰይፍ በሰገባው እንዲከተትና እንዲቀመጥ አደረበት እንጅ አልተዋሐደውም በሰላሳ ዘመኑ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በራሱ ላይ ሲቀመጥ መለኮቱ ከትስብእቱ ተዋሐዶ የጸጋ አምላክ ኾነ መዋቲ ትስብእትም የማይሞት ኾነ ከሰላሳ ዘመን በፊት የጸጋ አምላክ ስላልኾነ አምላካዊ ሥራ አልሠራም ከተጠመቀ በኋላ ግን የጸጋ አምላክ ስለኾነ ውኃውን ወይን አደረገ ብዙ የአምላክነት ሥራ ሠራ አለ፡፡

እንደዚኸውም በንግድ ምልክት መጥቶ እስክንድርያዊ መስሎ በኢትዮጵያ የሚኖር አንድ ሰው ተነሥቶ እንዲህ ሲል ተናገረ እናንተ ኢትዮጵያውያን ቃል ሥጋ በለበሰ ጊዜ በማኅጸነ ማርያም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ የባሕርይ አምላክ ኾነ ትላላችሁ በማኅጸን መንፈስ ቅዱስን ሲቀበል ያየው የለም፡፡ ሮማውያን ግን እስከ ሰላሳ ዘመን በሰብአዊ ግብር ኖሮ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ ሰው ሁሉ እያየው በራሱ ላይ ስለተቀመጠበት የጸጋ አምላክ ኾኖ የአምላክነት ሥራ ሠራ ይላሉና ከእስክንድርያ ሃይማኖት የሮማ ሃይማኖት ትሻላለች አለ፡፡

አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ሲያበሥራት መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል የአብም ኃይሉ ይጋርድሻል ካንች የሚወለደውም ቅዱስ ነው የልዑል የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ብሎ ሦስቱም አካላት በማኅጸነ ማርያም እንደ አደሩ ተናግሯል፡፡ ማደራቸውም አብ ለአጽንዖ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ነው እንጅ ሦስቱ ኹሉ ለለቢሰ ሥጋ ያደሩ አይምሰልህ፡፡
በዚህ ጊዜ መለኮት ርቀቱን ለቆ ሳይገዝፍ ሳይለወጥ ትስብእትም ግዘፍነቱን ለቆ ሳይረቅ ሳይለወጥ እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾነ፡፡ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ማለት ይህ ነው አብ ለአጽንዖ ማለትም ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ መለኮትን እመቤታችን በጠባብ ማኅጸን እንድትችለው አጸናት ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ማለትም ትስብእትን ከአዳም መርገም አንጽቶ ቀድሶ ለተዋሕዶተ መለኮት የበቃ አደረገው ማለት ነው፡፡ ይህን በማኅጸን በረቂቅ ምሥጢር የሠሩትን አምላካዊ ሥራ በዮርዳኖስ ወልድ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሲጠመቅ በመታየት አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ የሚል ድምጽ በማሰማት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጦ አብ ልጀ ይህ ነው ብሎ የመሰከረለት ወልድ ይህ ነው ብሎ በጣት ጠቅሶ እንደ ማሳየት በመመስከሩ ገልጸውለታል እንጅ እስከዚያ ድረስ ሰላሳ ዘመን መንፈስ ቅዱስ ተለይቶት ኖሮ በዮርዳኖስ አደረበት ማለት አይደለም አለ፡፡ ያ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ገላውዴዎስ አባ ዝክሪንና አባ ጳውሊን እኔ የክርስቶስ ባሪያ ሃይማኖቴ እንደ ሃይማኖታችሁ ኦርቶዶክስ እስክንድርያዊ ነው ይህነንም እናንተ ታውቁልኛላችሁ ነገር ግን እኛ የሕክምናና የተግባረ እድ ትምህርት የለንም ሮማውያን ብዙ ጥበብ ያውቃሉና ይህን ጥበባቸውን እስኪያስተምሩን ድረስ በሀገራችን እንዲቆዩ ፈቃዳችሁ ይኹን ሲል ለመናቸው፡፡
አባ ዝክሪ የተባለው መነኲሴ ተነሥቶ እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች እሊህ ሮማውያን በሀገራችን ይቀመጡ ካላችሁ ወደፊት በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስባትን ነገር ልንገራችሁ እኒህ ሰዎች ከእህቶቻችን ከልጆቻችን ይወልዳሉ እኒያ ልጆች በድብቅ ያባቶቻቸውን የካቶሊካውያንን ትምህርት ይማራሉ እኛ ወገኖቻችን መስለውን ቅስና ዲቁና ስንሾማቸው የመምህርነት ማዕርግ ስንሰጣቸው ውስጥ ውስጡን የኹለት ባሕርይን ባህል እያስተማሩ ሃይማኖታችንን ይለውጧታል ይህም የተናገርኩት ነገር አይቀርም አምስት ነገሥታት ካለፉ በኋላ ስድስተኛ ንጉሥ ከወደ ዐረማውያን ሀገር መጥቶ ይነግሣል በርሱ ጊዜ ይፈጸማል ሲል ትንቢት ተናገረ፡፡ ከዚህ በኋላ ከዐፄ ገላውዴዎስ ዐፄ ፋሲል፤ ከዐፄ ፋሲል ዐፄ ሚናስ፤ ከዐፄ ሚናስ ዐፄ ሠርጸ ድንግል፤ ከዐፄ ሠርጸ ድንግል ዐፄ ያዕቆብ፤ ከዐፄ ያዕቆብ ዐፄ ሱስንዮስ  ዐፄ ሱስንዮስ ከዐረማውያን ሀገር መጥተው ነገሡ፡፡ በስድስተኛው ንጉሥ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ የአባ ዝክሪ ትንቢት ተፈጸመ፡፡

በአጠቃላይ ስላነሣው ሁኔታ በእነዚህ ጉዳዮች እንዝጋውና በዋናነት በሚነሣበት ርእስ ላይ በሰፊው እያየን እንሄዳለን፡፡
#ይቀጥላል

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፳፭ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment