፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
የቅባቶቹ መጽሐፍ መሠረተ ሐይማኖት
|
ዛሬ ከገጽ ፴፪ ጀምረን ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን
ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
#ረዝሟል_አሳጥረው_እንዳትሉኝ_አደራ_አልቻልሁም፡፡ ምስጢር ከምሥጢር
ጋር ሲያያዝ ነውና የሚያምረው ቆራርጨ ማቅረብ አልቻልሁም፡፡ ከዚህ በፊት ቆራርጨ ለወልደ አብ መጽሐፍ ክህደቶች መልስ ስጽፍ አቅርቤው
ነበር ሆኖም ግን ምሥጢሩ ከምሥጢሩ ጋር አልተያያዘልንም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሁሉንም በአንድ ማቅረብ ችያለሁ፡፡ “የበረታ ቆሞ የደከመ
ተቀምጦ” ብላለች ተአምረ ማርያም እና የበረታ ያንብብ የደከመ #SHARE ያድርግና ጊዜ ሲኖረው ያንብበው፡፡ አንድ ጊዜ ማንበብ
ሊደክም ይችላልና፡፡
ወንጌል አንድምታ
|
ወንጌል አንድምታ
|
ካሳሁን ምናሉ የእኛ የተዋሕዶ ሊቃውንት በጻፉት የአንድምታ ትርጓሜ ውስጥ
ገብቶ የራሱን ክህደት ሊያስደግፍ ይሞክራል፡፡ ለዚህም የጠቀሰው የማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ ፩ ቁጥር ፲፮ ላይ የተጠቀሰውን የአንድምታ
ትርጓሜ ለራሱ ወስዶታል፡፡ አንድምታውን ስትመለከቱ ብዙ ማብራሪያ ይሰጥና በመጨረሻ “ሲቀባም ሲዋሐድም አንድ ጊዜ ነው” ይላል፡፡
ይህ የሊቃውንቱ ገለጻ ትክክለኛ ነው፡፡ መለያየት የመጣውም እኮ ሊቃውንቱ የተናገሩትን ከእነርሱ አስተምህሮ በወጣ መልኩ እየተተረጎመ
መቅረቡ ነው፡፡ በቃ “ሲቀባም ሲዋሐድም አንድ ጊዜ ነው” ይህ እኮ ነው በተዋሕዶ ከበረ ማለትም፡፡ አካላዊ ቃል ከድንግል ማርያም
ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ተዋሕዶ ፍጡር የነበረውን ሥጋ አምላክ አደረገው፡፡ “ሲቀባ ሲዋሐድ አንድ ጊዜ ነው” ማለትም ይኼው
ነው፡፡ ሲዋሐድ ሲከብር አንድ ጊዜ ነው ማለት ነው፡፡ ቅባት ማት ክብር ማለት ነውና፡፡ የእኛ እምነትም እኮ ይኼው ነው “ወልደ
አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ”፡፡ ሲቀባ ሲዋሐድ አንድ ጊዜ ነው ማለትም በተዋሕዶ ከበረ ማለት ነው፡፡ የቅባቶች ግን እንዲህ
አይደለም “ሲቀባ” የምትል ቃል ስላገኙ ለማደናገር ያመጡት ነው እንጅ፡፡ የእነርሱ አስተምህሮ ወልደ አብ ላይ በደንብ ነው ተብራርቶ
የተቀመጠው፡፡ ወልደ አብ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፻፳፮ ላይ “… ተዋሕዶ ተፈጠረ ሳይዋሐድ አልተፈጠረም፡፡ ተዋሕዶ ሳይፈጠር አልቆየም፡፡
ሲዋሐድ ሲፈጠር አንድ ጊዜ ነው፡፡ ከተፈጥሮ ተዋሕዶ ቀደመ ባሉ ጊዜ ከቅብዓትም ተዋሕዶ ቀደመ ማለት ይሆናል” በማለት ነው “መቀባት”
ማት መፈጠር ማለት እንደሆነ የሚጽፉት፡፡ እኛ የተዋሕዶ አማኞች ግን “ሲቀባ ሲዋሐድ አንድ ጊዜ ነው” እንላለን እንጅ “ሲዋሐድ
ሲፈጠር አንድ ጊዜ ነው” አንልም፡፡ “ቀባ” አዋሐደ፣ አዘጋጀ፣ አከበረ ወዘተ የሚል ትርጉም አለው፡፡ የማቴዎስ ወንጌልን አንድምታ
በፎቶ አብሬ አያይዝላችኋለሁና ተመልከቱት እንዲያውም “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ባዮችን የሚቃወም እንጅ የሚደግፍ አይደለም፡፡
ሌላው ካሳሁን ቀባ የሚል ቃል ስላገኘ ብቻ እንደፈለገው የተረጎማቸው
ጥቅሶች እንመለከታለን፡፡ ሊቃውንቱ ምን ብለው እንደተረጎሙት ሳልቀንስ ሳልጨምር አስቀምጥላችኋለሁ፡፡ በዚህ የአንድምታ ትርጓሜ መሠረት
የካሳሁንን የክህደት ትምህርት እያነበባችሁ በሊቃውንቱ ሚዛን መዝኑት እስኪ፡፡ በመጀመሪያ ግን ቅብዓት ምን እንደሆነ ትርጉሙን አስፈላጊነቱን
እንመለከታለን፡፡
የቅብዓት ትርጉም
የቅባቶቹ መጽሐፍ መሠረተ ሐይማኖት
|
በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፺፬ ላይ ያለውን ቅብዓት (ቅባት) ከልዩ ልዩ እንጨቶች ተቀምሞና ተነጥሮ የሚወጣ ፈሳሽ ዓይነት ዘጸ ፴÷፳፪-፴፪፡፡
የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡ ፩ኛ ዮሐ፪÷፳፡፳፯፡፡ ከዚያም ሲጨርስ “ቀባ” ን ተመልከት ይላል ስለዚህ የ “ቀባ”ንም ትርጉም መመልከት
ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ “ቀባ” መቀባት በመጽሐፍ ቅዱስ ለ፫ ዓይነት ነገር ያገለግላል፡፡ ፩ኛ. ለአገልግሎት፡- ሰዎችና ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ሥራ ሲለዩ ይቀቡ ነበር፡፡ በብሉይ
ኪዳን ዘመን የመገናኛው ድንኳንና ዕቃው ተቀብቷል፡፡ ዘጸ ፴÷ ፳፪-፳፱፤ ዘጸ ፴÷፴፤ ፩ኛ ሳሙ ፱÷፲፮፤ ፩ኛ ሳሙ ፲÷፩ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል (በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ ሐዋ ፲÷፴፰)፤
፪ኛ ቆሮ፩÷፳፩-፳፪፤ ፩ኛ ዮሐ፪÷፳፡፳፯ ላይም ተገልጿል፡፡ በማለት
ይገልጻል፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው መጽሐፈ ግስ ወሰዋስው መርኆ መጻሕፍት
በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፻፺፱ ላይ ቀብዐ ቀባ ካሉ በኋላ ማስረጃ ይሰጣሉ፡፡ በዘተሰብአ ተቀብዐ ፤ ተዋሐደ ተቀብዐ ተዋሐደ ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ከመዝ ይትቀብዑ እምቅዱስ ቅብዕ በኀበ ምቅባዕ እን ቆስጠ ፴፱
ወፈነወ ኢየሱስሀ ወአቅደመ ቀቢዖቶ አዘጋጀ ብለው ቀብዐ ያለውን
ግስ አዘጋጀ ብለው ይተረጉሙታል፡፡ በዚህ ግስ እርባታ ላይ
ቀብዐ የሚለው ግስ ቀባ ከሚለው የአማርኛ ትርጉም በተጨማሪ አዘጋጀ አዋሐደ ተብሎ እንደሚተረጎም ማስረጃዎችን አስቀምጠዋል፡፡ ሌላው
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ
በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ ፯፻፸፱ እና ገጽ ፯፻፹ ላይ በዝርዝር ያስቀመጡትን እንመልከት፡፡ ቀቢዕ፤ ዖት፤ (ቀብዐ፡ ይቀብዕ፡ ይቅባዕ፡፡ ዕብ፡ ቃባዕ፡ ሐገገ፡ ዐደመ ፡ መልአ ፡ ሤመ) ብለው፤ ሲተረጉሙ መቅባት፣
መቀባት፣ መላላክ፣ መለቅለቅ፣ ለመሾም፣ ለማክበር፣ ለማሳመር ለመፈወስ ይላሉ፡፡
ይህን ቃል በተለያዩ መዝገበ ቃላት እንዲሁም በሰዋስውና በግስ መጻሕፍት
ላይ ምን ተብሎ እንደተተረጎመ እንመልከት፡፡ በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፺፬ ላይ ያለውን እንመልከት፡፡ ቅብዓት (ቅባት)
ከልዩ ልዩ እንጨቶች ተቀምሞና ተነጥሮ የሚወጣ
ፈሳሽ ዓይነት ዘጸ ፴÷፳፪-፴፪፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡ ፩ኛ ዮሐ ፪÷፳፡፳፯ ብሎ ‹‹ቀባ›› ን ይመልከቱ ይላል፡፡ በመጀመሪያ
በዚህ የተጠቀሱትን ጥቅሶች እንመልከት፡፡ ዘጸ ፴÷፳፪-፴፪ ላይ “ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፡፡ አንተም ክቡሩን
ሽቱ ውሰድ የተመረጠ ከርቤ ዐምስት መቶ ሰቅል ግማሽም ጣፋጭ ቀረፋ ሁለት መቶ ዐምሳ ሰቅል የጠጅ ሣርም እንዲሁ ሁለት መቶ ዐምሳ
ሰቅል ብርጉድም ዐምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መሥፈሪያ ትወስዳለህ፡፡ በቀማሚም ብልኀት
እንደተሠራ ቅመም የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ታደርገዋለህ፡፡ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሆናል፡፡ የመገናኛውንም ድንኳን የምስክሩንም
ታቦት ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ መቅረዙንም ዕቃውንም የዕጣን መሠዊያውንም ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋእት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም
ሁሉ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ፡፡ ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፡፡
በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው ቀድሳቸውም፡፡ አንተም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር ይህ ለልጅ
ልጃችሁ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሁንልኝ፡፡ በሰው ሥጋ ላይ አይፍሰስ እንደ እርሱም የተሠራ ሌላ ቅብዐት አታድርጉ ቅዱስ ነው
ለእናንተም ቅዱስ ይሁን” ይላል፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እግዚአብሔር ለሙሴ ቅብዐት እንዴት እንደሚዘጋጅ እና ለምን
አገልግሎት ሊውል እንደሚገባ ነግሮታል፡፡ ሙሴም በዚሁ መልኩ እያዘጋጀ ለተባለው አገልግሎት ያውል ነበር፡፡ ከዚህ ቀጥለን ደግሞ
ቅብዐት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ እንደሆነ የሚያስረዳውን ጥቅስ እንመለከታለን፡፡
፩ኛ ዮሐ ፪÷፳ ላይ “እናንተም ከቅዱሱ ቅብዐት ተቀብታችኋል ሁሉንም
ታውቃላችሁ” ይላል ዳግመኛም ፩ኛ ዮሐ ፪÷፳፯ ላይ “እናንተስ ከርሱ የተቀበላችሁት ቅብዓት በእናንተ ይኖራል፡፡ ማንም ሊያስተምራችሁ
አያስፈልጋችሁም ነገር ግን የእርሱ ቅብዓት ስለሁሉ እንደሚያስተምራችሁ እውነተኛም እንደሆነ ውሸትም እንዳልሆነ እናንተም እንዳስተማራችሁ
በርሱ ኑሩ” ይላል፡፡ እነዚህ ሁለት ጥቅሶች ላይ ቅባት ተብሎ የተገለጸው ምሳሌነቱ ለመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ
ቀጥለን ቀባ ወደሚለው ቃል ትርጉም እንመለስ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፺ ላይ እናገኘዋለን፡፡ ቀባ መቀባት በመጽሐፍ ቅዱስ #ለሦስት ዓይነት ነገር ያገለግላል፡፡ ይልና
ይዘረዝራቸዋል ማስረጃ ጥቅሶችንም ይሰጣል፡፡
የቅባቶቹ መጽሐፍ መሠረተ ሐይማኖት
|
፩ኛ. ለአገልግሎት፡- ሰዎችና ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ሥራ ሲለዩ ይቀቡ ነበር፡፡ በብሉይ
ኪዳን ዘመን የመገናኛው ድንኳንና ዕቃው ተቀብቷል፡፡ ዘጸ ፴÷ ፳፪-፳፱ ከላይ የተጻፈውን ተመለከት፡፡ ካህናት፣ ነቢያትና ነገሥታት
ተቀብተዋል፡፡ ይህን ለተጠሩበት ሥራ በእግዚአብሔር መለየታቸውንና ለሥራቸው የሚያበቃቸው በዘይቱ የተመሰለው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን
ያሳያል፡፡ ዘጸ ፴÷፴ ላይ “በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው ቀድሳቸውም” ብሎ ሙሴን አዝዞታልና፡፡ ፩ኛ ሳሙ
፱÷፲፮ ላይ “ነገ በዚች ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እሰድልሃለሁ ልቅሷቸው ወደእኔ የደረሰ ህዝቤን ተመልክቻለሁና ለህዝቤ
ለእስራኤል አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ህዝቤን ያድናል” ብሎ እግዚአብሔር ለሳሙኤል ነገረው፡፡ ፩ኛ ሳሙ
፲÷፩ ላይ “ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው ሳመውም እንዲህም አለው በርስቱ ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር
ቀብቶሃል የእግዚአብሔርንም ህዝብ ትገዛለህ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ” ይላል፡፡ ከዚያም ይቀጥልና ክርስቶስ በመንፈስ
ቅዱስ ተቀብቷል (በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ ሐዋ ፲÷፴፰) ይላል፡፡ ጥቅሱን እንመልከተው ሐዋ ፲÷፴፰ ላይ “እግዚአብሔር የናዝሬቱን
ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ እግዚአብሔር ከእርሱ
ጋር ነበረና” ይላል፡፡ የዚህን ጥቅስ ትርጉም በስፋት የምንመለከትበት ክፍል ስለሚኖረን እዚህ ላይ ማብራሪያ አንሰጥም፡፡ ከዚህ
ቀጥሎ ምእመናን በመንፈስ ቅዱስ ይቀባሉ ይላል፡፡ ፪ኛ ቆሮ፩÷፳፩-፳፪ ላይ “በክርስቶስም ከእናንተ ጋራ የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር
ነው፡፡ ደግሞም ያተመን የመንፈሱም መያዣ በልባችን የሰጠን ርሱ ነው” ይላል፡፡ ከላይ የተመለከትነው ጥቅስ ፩ኛ ዮሐ፪÷፳፡፳፯ ላይም
ተገልጿል ሙሉ ንባን ከላይ ጽፈናል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ‹‹መሢሕ›› በዕብራይስጥ ‹‹ክርስቶስ›› በግሪክ ቋንቋዎች የተቀባ ማለት ነው
ብሎ መቀባት ለአገልግሎት አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ሐዋ ፲÷፴፰ ላይ ኢየሱስ መቀባቱ ለአገልግሎት እንደሆነ በሚገባ ተነግሯል፡፡
መቀባቱ ለአክብሮት አይደለም ስለዚህም ይህንን ጥቅስ ይዘን “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” ልንል አንችልም “አገልግሎት ጀመረ ለድኆች
ወንጌልን ሰበከ” እንላለን እንጅ፡፡
የቅባቶቹ መጽሐፍ መሠረተ ሐይማኖት
|
፪ኛ. ለአክብሮት፡- ተጋባዦች ለአክብሮት ይቀቡ ነበር፡፡ ሉቃ ፯÷፵፮ ላይ “አንተ ራሴን
ዘይት አልቀባኸኝም ርሷ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች” በማለት ክርስቶስ ለማርያም እንተ እፍረት ሲመሰክርላት እንመለከታለን፡፡ የሰዎች
ሬሳ ሳይቀበር ሽቱ ይቀባ ነበር፡፡ ማር ፲፬÷፰ ላይ “የተቻላትን አደረገች አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋየን ቀባችው” ይላል ማር ፲፮÷፩
ላይም እንዲሁ “ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ” ይላል፡፡
ስለዚህ ለአክብሮት ሽቱ ይቀቡ እንደነበርና ሬሳንም እንዲሁ ይቀቡ እንደነበር ያስረዳል፡፡
፫ኛ. ለሕክምና፡- ቁስለኞችና ሌላም በሽታ ያለባቸው በዘይት ይቀቡ ነበር፡፡ ማር ፮÷፲፫ላይ “ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ
ፈወሷቸው” ይላል፡፡ ሉቃ ፲÷፴፬ላይም “ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍሶ አሰራቸው …” ይላል፡፡ ያዕ ፭÷፲፬
ላይም “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎችን ወደርሱ ይጥራ በጌታም ሥም ርሱን ዘይት
ቀብተው ይጸልዩለት” ይላል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ‹‹ዘይት›› ይመልከቱ ብሎ ይጨርሳል እኛ ግን የዘይትን ትርጉምም እንመለከተው ዘንድ
መጽሐፋችንን (መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት) ገጽ ፪፻፲፫ ላይ ገለጥን እና ዘይት የሚለውን ቃል ትርጉም እንዲህ ወሰድነው፡፡ ዘይት ከወይራ ፍሬ ይጨመቃል፡፡ ሰዎች ይህን ዓይነት ዘይት ለምግብ፣ ለልዩ
ልዩ ቅባት፣ ለጠጉር ለመድኃኒት፣ ለመብራት፣ ሰዎችንና ዕቃዎችን ለእግዚአብሔር አገልግሎት ለመለየት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ፩ኛ ሳሙ
፲÷፩፣ ፩ኛነገ ፲፯÷፪-፲፮፣ ሉቃ ፲÷፴፬፣ ያዕ ፭÷፲፬ ‹‹ቀባ›› ይመልከቱ ብሎ ይደመድማል፡፡ እኛ ግን ‹‹ቀባ›› የሚለውን
ቃል አስቀድመን ስለተመለከትነው ድጋሜ አንመለስበትም፡፡ ከእነዚህ ከተቀመጡት ጥቅሶች መካከል ያልተመለከትነው ፩ኛነገ ፲፯÷፪-፲፮
ያለውን ታሪክ ነው፡፡ ሌሎችን ጥቅሶች አስቀድመን ተመልክተናቸዋልና አንደግማቸውም፡፡ ይህንን ጥቅስ ሙሉውን አንብቡት ዋናው መልእክት
ዘይትን ሰዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚጠቀሙበት ለማሳየት ነውና ያንን እንጽፋለን ቁጥር ፲፬-፲፮ “…ዘይቱም ከማሰሮው አይጎድልም፡፡
እርሷም ሄዳ እንደ ኤልያስ ቃል አደረገች እርሷና እርሱ ቤቷም ብዙ ቀን በሉ፡፡ በኤልያስም እጅ እንደተናገረው እንደእግዚአብሔር
ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም” ይላል፡፡
እስካሁን ቅብዐት የሚለው
ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዴት እንደተተረጎመ ተመልክተናል፡፡ ቀጥለን በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎችን መዝገበ ቃላት፣ ሰዋስውና
ግስ መጻሕፍትንም በማገላበጥ የቃሉን ግስ አገባብ አፈታት አተረጓጎም እንመለከታለን፡፡
የቅባቶቹ መጽሐፍ መሠረተ ሐይማኖት
|
፩ኛ. ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ
ሽፈራው መጽሐፈ ግስ ወሰዋስው መርኆ መጻሕፍት በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፻፺፱ ላይ ቀብዐ
ቀባ
የሁሉ
ካሉ በኋላ ግሱን ማርባት ይጀምራሉ፡፡ ቅቡዕ ውስጠዘ ቅቡዓን (በብዙ) ቅብዕት (ለሴት) አብ መቅብዕ (ባዕድ ቅጽል) ቀባዕት (መድበል) ቆብዕ ቅብዕ (ዘመድ ዘር) ቀዋብዕ ቅብዓት(በብዙ) ቅብዐት (ሳቢ ዘር) ---ማስረጃ በዘተሰብአ ተቀብዐ
፤ ተዋሐደ (ቆብዕ ቆብ ማለት ነው) ምቅባዕ ባዕድ ዘር ከመዝ ይትቀብዑ እምቅዱስ ቅብዕ በኀበ ምቅባዕ እን ቆስጠ ፴፱ ወፈነወ ኢየሱስሀ ወአቅደመ ቀቢዖቶ
አዘጋጀ ብለው ቀብዐ ያለውን ግስ ይፈጽማሉ፡፡ በዚህ ግስ እርባታ
ላይ ቀብዐ የሚለው ግስ ቀባ ከሚለው የአማርኛ ትርጉም በተጨማሪ አዘጋጀ አዋሐደ ተብሎ እንደሚተረጎም ማስረጃዎችን አስቀምጠዋል፡፡
በዘተሰብአ ተቀብዐ ባለው ላይ ተቀብዐ ያለውን ቃል ተዋሐደ ተብሎ ተተርጉሞ እናገኛለን፡፡ ወፈነወ ኢየሱስሀ ወአቅደመ ቀቢዖቶ ሲል
ደግሞ ቀብዐ የሚለው ቃል አዘጋጀ በሚለው አማርኛ ተተርጉሞ እናገኘዋለን፡፡
፪ኛ. አለቃ ኪዳነ ወልድ
ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ ፯፻፸፱ እና ገጽ ፯፻፹ ላይ በዝርዝር ያስቀመጡትን እንመልከት፡፡ ቀቢዕ፤ ዖት፤ (ቀብዐ፡ ይቀብዕ፡ ይቅባዕ፡፡ ዕብ፡ ቃባዕ፡ ሐገገ፡ ዐደመ ፡ መልአ ፡ ሤመ) ይልና፤ ሲተረጉም መቅባት፣
መቀባት፣ መላላክ፣ መለቅለቅ፣ ለመሾም፣ ለማክበር፣ ለማሳመር ለመፈወስ ይላል፡፡ ቀብዖ በሕጉሬ፡፡ ቀብዖ ወርቀ ንጹሐ፡፡ ኢትቅብዖ
ዕፍረተ፡፡ ገብረ ጽቡረ በምራቁ በቀብዖ አዕይንቲሁ (ሢራ ፵፭÷፲፭፤ ጥበ ፲፫÷፲፬ ፤፫ኛ ነገ ፲÷፲፰ ፤ፍት ነገ ፶፩፡፡ ዮሐ ፱÷፳)፡፡
ልብስና ቀለም ሽቱና ተቀቢው ልዩ ልዮች ስለሆኑ መጋጠማቸው ለተዋሕዶ ምሳሌ እየሆነ ይነገራል፡፡ ከመ ፀምር ውስተ ሠርዮ ከማሁ ተቀቢዖ
ትስብእተ በመለኮተ፡፡ ዕፍረትሰ ሥጋ ዚአኪ ወተቀባዒሁ ቃል ውእቱ (ኤጲ አክሲ፡፡ አርጋ)፡፡ እንዲህ ያለው ንባብ ግስ ሠም ለበስ
ይባላል ካሮች ግን ሠሙን ወርቅ ምሣሌውን ጽድቅ አድርገው ቀብዐን አዋሐደ
ተቀብዐን ተዋሐደ እያሉ አለቋንቋው አለንባቡ አለስልቱ አላገባቡ አላንጻሩ አለምሥጢሩ ይፈቱታል፡፡ የተቀባዐ ፍች ተዋሐደ
ማለት ከሆነ ቄርሎስ አፈወርቅ ኢይጽሕቅ ቅብዐተ በህላዌሁ፡፡ ወመለኮቱሰ ኢይትቀባዕ ይላሉና ይህ ንባብ ሳይወዱ በግድ በባሕርዩ ተዋሕዶ
አይሻም፡፡ መለኮቱ አይዋሐድም ያሰኝባቸዋል፡፡ ተማሪ ሳይሆኑ መምህር መሆን እውነቱን ሐሰት ሐሰቱንም እውነት እያሰኘ እንዲህ ፈራሽ
ነገር ያናግራል፡፡ የተሰብአንና የተቀብዐን ምሥጢር ስንኳን ልቡን ዠርባውን አላገኙትም ቅባቶችም እንዲሁ ናቸው ይላሉ፡፡
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “ካሮች”
እና “ቅብአቶች” የተሰብአንና የተቀብዐን ትርጉም (ምሥጢር) እንኳን ልቡን ዠርባውንም አላገኙትም ብለዋል፡፡ እኛ ስለካሮች እና
ስለ ቅብአቶች ባይመለከትንም እኛ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” የምንል ኦርቶዶክሳውያን ግን የምንለው ነገር ይኖረናል፡፡ ይህን
መዝገበ ቃላት ወጥተው ወርደው ደክመው በማዘጋጀታቸው የግእዝ ችሎታቸውን እንዳሳዩበት እንረዳለን፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከዚህ
ቃል ጋር በተያያዘ ግን ጉድለት እንዳለባቸው እንገነዘባለን፡፡ እሳቸው ያዩበት ዓይናቸው እንዴት እንደሆነ ባናውቅም እኛ ግን ሊቅነታቸው
መራቀቃቸው እንደጎዳቸው እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም አንድ ቃል በተለያዩ አገባቦች የተለያየ ትርጉም እንደሚኖረው አልተገነዘቡትም፡፡
በእርግጥ ይህን ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም ምክንያቱም እርሳቸው የሚያምኑት ምንታዌነት ተጋፍቷቸው እንደሚሆን እንረዳለንና፡፡
አንድ ቃል በተለያዩ አገባቦች ላይ የተለያዩ ትርጉሞችን እንደሚይዝ መጽሐፍ ቅዱስን አብነት አድርገን አንድ ቀላል የሆነ ምሳሌ እንመልከት
እስኪ፡፡
የቅባቶቹ መጽሐፍ መሠረተ ሐይማኖት
|
“አዳምም ሚስቱን ሔዋንን
ዐወቀ ጸነሰችም ቃየንንም ወለደች” ይላል ዘፍ ፬÷፩
ላይ፡፡ ይህንን “ዐወቀ” የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ምን ብለው ይተረጉሙት ነበር፡፡ “ዐወቀ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ
ተረዳ፣ ተገነዘበ፣ ልብ አለ፣ አስታወሰ፣ እውቀትን አገኘ ወዘተ ማለት ነው፡፡ በዚህ ትርጉም ብንሄድ ይህ የመጽሐፍ ክፍል ትርጉም
አይኖረውም ምክንያቱም አዳም ሚስቱን ተረዳ፣ ተገነዘበ፣ ልብ አለ፣ አስታወሰ፣ እውቀትን አገኘ ወዘተ ተብሎ ሊነገር አይችልምና፡፡
ምክንያቱም አዳም ከግራ ጎኑ የተፈጠረችለትን አጋዡን አስታወሳት ቢባል አያስማማም ምክንያቱም ሚስቱ እንዴት ትጠፋዋለች በዚያ ላይ
በዓለም ያሉ ሰዎች እኮ ሁለት ብቻ ናቸው አዳም እና ሔዋን ታዲያ አዳም የትናዋ ሴት በመልክ ከሔዋን ጋር ተመሳስላበት ሊረሳት ይችላል፡፡
እሽ ይሁን ብለን እንኳ ብንቀበለው ቀጥሎ ከሚመጣው ቃል ጋር መስማማት አንችልም፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ቃል መጽነስና መውለድን የሚገልጽ
ነው፡፡ አዳም የረሳት ሚስቱን በማስታወሱና በማወቁ ብቻ ሔዋን ልትጸንስና ልትወልድ አትችልም፡፡ ስለዚህ “ዐወቀ” የሚለው ቃል በዚህ
አገባቡ ቀድሞ የምናውቀውን ትርጉም ይዞ ሊገኝ አይችልም፡፡ በመሆኑም “ዐወቀ” የሚለው ቃል በዚህ አገባብ “በግብረ ሥጋ ተገናኘ”
ተብሎ የሚተረጎም እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ሆኖም ግን ዐወቀ የሚለው ቃል ሁልጊዜ ይህንን ትርጉም ይዞ ይገኛል ማለት ደግሞ አይቻልም፡፡
በሌላ አገባብ በሌላ ቦታ ላይ ድሮ ከምናውቀው ትርጉም ጋር አንድ ሆኖ ገጥሞ የምናገኝበት ጊዜ አለ፡፡ ዮሀ ፳÷፲፫ ላይ “…ጌታየን
ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው”
የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ አላውቅም የሚለውን ቃል ከላይ በተረጎምንበት አገባብ ብንተረጉመው ምን መልእክት ሊኖረው ይችላል፡፡
ይህን ቃል ግን ከላይ በተረጎምንበት አገባብ ተርጉመን “በግብረ ሥጋ አልተገናኘሁም” ብንለው ትርጉሙ ምን እንደሚሆን ለመረዳት ይከብዳል፡፡
ስለዚህ በዚህ አገባብ ላይ ይህ ቃል ድሮ በምናውቀው ትርጉም ልንተረጉመው ይገባል ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት አላውቅም ስትል
አልተረዳሁም አልተገነዘብኩም ልብ አላልኩም አላስታወስኩም ወዘተ ብለን ብንፈታው ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ “ቀብዐ” የሚለው ቃል
ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ትርጉም ብቻ ነው ያለው የሚለው የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ አባባል ችግር እንዳለበት እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም
አገባቡንም ልንመለከተው ያስፈልጋልና፡፡ “ተማሪ ሳይሆኑ መምህር መሆን እውነቱን ሐሰት ሐሰቱንም እውነት እያሰኘ እንዲህ ፈራሽ ነገር
ያናግራል፡፡ የተሰብአንና የተቀብዐን ምሥጢር ስንኳን ልቡን ዠርባውን አላገኙትም” በማለት መተርጉማኑን የነቀፉበት አገላለጻቸው ደግሞ
ከቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት የሚጠበቅ ንግግር እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም እኔ ትል ነኝ፣ እኔ አፈር ትቢያ ነኝ፣ እኔ
ጭንጋፍ ነኝ፣ እኔ አላዋቂ ነኝ ወዘተ የሚሉ የትህትና አባቶች በህይወት ኖረው ያስተማሩባት ቤተክርስቲያን ናትና እኔ ሊቅ ነኝ ሌላው
የሚለው ሁሉ ድንቁርና ነው አይባልም፡፡
የቅባቶቹ መጽሐፍ መሠረተ ሐይማኖት
|
ስለዚህ “ቀብዐ” የሚለው
ቃል ቀባ ከሚለው አማርኛም በተጨማሪ እንደአገባቡ ሌሎች ትርጉሞችን እንደሚይዝ እንገነዘባለን፡፡ ኢሳ ፷፩÷፩1 “መንፈሰ እግዚአብሔር
ዘላእሌየ ዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ…” የሚለውን ሊቃውንቱ ሲተረጉሙ “በህልውናየ ያለ መንፈስ ቅዱስ ስለከዊነ ትስብእት ያዋሐደኝ…” ብለው
ነው የተረጎሙት፡፡ ከዚህ የምንረዳው “ቀብዐ” የሚለው ቃል “ቀባ” ከሚለው አማርኛ በተጨማሪም አዋሐደ ተብሎ እንደሚተረጎም እንደሚፈታ
ነው፡፡ ሌላው “ዘተቀባእከ ሥጋሃ ለማርያም” የሚለውን “የማርያምን ሥጋ የተዋሐድህ” በማለት ተርጉመውታል መጽሐፈ አርጋኖን ዘአባ
ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፡፡ “ወከመዝ ነአምሮ ለሊሁ ተቀብዐ ከመ ሥርዓተ ትስብእት ወዳእሙ ውእቱ ዘይቀብዕ ርእሶ በመንፈሱ ባሕቲቱ” የሚለውንም
“በተዋሕዶ እንደከበረ እናውቃለን ግን በገዛ ሥልጣኑ ራሱን የሚያከብር እሱ ነው” በማለት ተርጉመውታል ሃይማኖተ አበው ስምዓት ምእራፍ
፻፳፬ ክፍል ፪ ቁጥር ፲፬ ላይ፡፡ ስለዚህ ቀብዐ የሚለው ቃል አዋሐደ በሚለው ቃል ተተርጉሞ እንደምናገኘው መገንዘብ ያሻል፡፡
በቅብዓት እምነት
ተከታዮች ዘንድ የሚጠቀሱ በካሳሁን መጽሐፍም የተቀመጡ ብርቅ ጥቅሶች አሉ፡፡ እነዚህን ጥቅሶች በጥሬው በማንበብ ወደ ክህደት ሲያመሩ
ስንመለከት በጣም እናዝናለን፡፡ “ቃል ይገድላል ትርጓሜ ያድናል” እንዲሉ እነዚህን በጥሬው የተቀመጡ ቃላትን ከሊቃውንቱ ትምህርት
ጋር በማስማማት መተርጎም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ማንኛውም ትርጓሜ ትምህርተ መለኮትን የማያፋልስ መሆን አለበት፡፡ እነርሱ ግን ጥሬውን
እንቆረጥማለን እያሉ ቃሉ የብረት ቆሎ ሆኖባቸው ጥርሳቸው ሲሰበር ስንመለከት አብዝተን እናዝናለን፡፡ የሚመለሱት እንዲመለሱ በጥርጥር
ላይ ያሉ ወገኖቻችንም እውነታውን እንዲረዱ እነርሱ የሚያነሷቸውን ጥቅሶች በሊቃውንቱ ትርጓሜ እንዴት ተተረጎሙ የሚለውን እንመለከታለን፡፡
እዚህ ላይ ግን ልብ በሉ! እኔ ምንም አልጨምርም አልቀንስም ያለውን የተተረጎመውን ነው የምጽፈው፡፡ መልካም ንባብ! የሊቃውንቱ አንድምታ ትርጓሜ፡፡
፩ኛ. መዝ ፪÷፪ “ላእለ እግዚአብሔር ወላእለ መሢሁ”
በእግዚአብሔር አብ በእኔ በእግዚአብሔር ወልድ፡፡ በእግዚአብሔር
ወልድስ ይሁን ሰቅለው ገድለውታል በእግዚአብሔር አብ ምን ብለው ተነሡ ቢሉ ወልድ ቢነክ አብ ይነክ እንዲሉ ወልድን መስቀል መግደል
አብን መስቀል መግደል ሆኖባቸዋልና ባያገኙት ቀርቶባቸዋል እንጂ፡፡ አንድም አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብሎ የመሰከረለት ወልድን እሩቅ
ብእሲ ማለት አብን ዕሩቅ ብእሲ ማለት ነውና፡፡
፪ኛ መዝ ፪÷፯ “እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ”
“ እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ” አሁን አንተን አይሻም (ቃል ይቤ በል) ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል
፣ ባህርይ ዘእም ባህርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡
“ወአነ ዮም ወለድኩከ” አሁንም “አነ” ን አይሻም ዛሬም በተዋሕዶ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡
ተውህቦ ለእግዚአብሔር
ቃል ስም በሥጋ ዘበህላዌሁ ይሰመይ እንዲል ስለ
ሥጋ እንግድነት አንድም “ይቤ ሥጋ” አንተ ሥጋ ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ
ልጄ ነህ አለኝ፡፡ አንተ ልጄ ነህ ዛሬም በተዋሕዶ ወለድኩህ ማለት በቃል ርስት፡፡ አንድም አሁንም አንተን እና አነን
አይሻም (ሥግው ቃል ይቤ) ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ ፡፡ ዛሬም
አውጻእኩከ
አንሣእኩከ ሲል ነው፡፡ በትንሣኤ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ አሁን ኹለተኛ የሚወልደው ሆኖ አይደለም በምሳሌ ተናገረው
እንጅ፡፡ ሰው ዘምቶ ያረጃል፤ በልቶ ያፈጃል፡፡ ሕዝብን ሰብስቦ ልጁን አስጠርቶ ልጄ “ዘምቶ ያረጀ በልቶ ያፈጀ ይሉሃል እኔ ነኝ፤
በርስቴ ውጣበት ውረድበት” ብሎ ይሰጠዋል፡፡ እሱም ወጣሁ ልጅ ነኝ ፈላሁ ጠጅ ነኝ ብሎ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ይዘምታል፡፡
በርስቱ ርስት በጉልቱ ጉልት ጨምሮበት ይመጣል፡፡ አባቴ በሰጠኸኝ ርስት ጉልት ጨምሬበት መጣሁ ይለዋል፡፡ እርሱም
ቀድሞም ልጄ ዛሬም ልጄ ይልቅስ የዛሬው ይብለጥ ይለዋል፡፡ ጌታም ከአቤል ጀምሮ እስከ ዕለተ ዓርብ ያሉትን ነፍሳት “እለ ውስተ
ሲዖል ፃዑ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከሰቱ ወርእዩ ብርሃነ ዐቢየ” በገነት አድርጎ ባረገ ጊዜ ልጄ ነህ አለው እንጅ፡፡
፫ኛ መዝ ፵፬÷፯ “አፍቀርከ
ጽድቀ ወአመጻ ጸላዕከ በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዓ ትፍሥሕት እምእለ ከማከ”
“አፍቀርከ ጽድቀ ወአመጻ ጸላዕከ በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ”
እውነትን ወደድህ ሐሰትን ጠላህ ማለት ትንቢተ ነቢያትን
መፈጸምን ወደድህ አለመፈጸምን ጠላህ አንድም ሰው መሆንን ወደድህ አለመሆንን ጠላህ፡፡ ሰው እሆናለሁ ብሎ በነቢያት አናግሮ መቅረት
መጥላት የነቢያትን ነገር ሐሰት ማድረግ ነውና፤ አንድም ቀጠሮ መፈጸምን ወደድህ አለመፈጸምን ጠላህ፡፡ አንድም ጻድቅ አምላክ ወልደ
አምላክ የሚልህን ወደድህ፤ ወአማፄ ሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ የሚልህን ጠላህ፡፡
“በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ”
ሰው መሆንን ስለወደድህ አለመሆንን ስለጠላህ የባሕርይ
አባትህ እግዚአብሔር አብ አዋሐደህ፡፡ አንድም አግዚአብሔርነትህ አምላክነትህ አዋሐደህ፡፡
“ቅብዓ ትፍሥሕት እምእለ ከማከ”
እምእለ ከማከ እንዳንተ ያሉ ነቢያት ካህናት ከተቀቡት
ልዩ የሚሆን ቅብዓ ትፍሥሕትን ማለት ተዋሕዶን ተዋሐድህ፡፡ አንድም ነቢያት ካህናት ከተቀበሉት ልዩ የሚሆን ቅብዓ ትፍሥሕትን ማለት
ልዩ ተዋሕዶን ተዋሐድህ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ዘይኄይስ ያለውን ዮሐንስ አፈወርቅ በዘይተ ፍሥሐ ብሎ ወስዶታል፡፡ ዘይኄይስ ማለቱ የሱ
የማይነሳ ሕጸጽ የሌለበት የባህርይ የነሱ የሚነሳ ሕጸጽ ያለበት የጸጋ የሱ ከራሱ የነርሱ ግን ከርሱ ነውና፡፡
፬ኛ ኢሳ ፵፪÷፩-፪
ናሁ ቁልዔየ ዘአኀዝክዎ
እነሆ በስልጣኔ የያዝኩት ዘሩባቤል፡፡ ወእስራኤልኒ ኅሩይየ፤
የመረጥኩት ዘሩባቤል፡፡ ዘተወክፈቶ ነፍስየ፤ ልቡናየ የወደደችው ዘሩባቤል፡፡
ወወሀብኩ መንፈስየ ዲቤሁ፤ መንፈሰ ረድኤትን ያሳደርሁበት ዘሩባቤል፡፡ ወናሁ ያመጽእ ፍትሐ ለአሕዛብ፤ እነሆ ለአሕዛብ ኦሪትን ያስተምራል፡፡
ኢይኬልሕ ወኢይጠርእ፤ አይጮኽም፤ አይገነታም (በጥርአ ቃል እንዲል፤ ጥበብ ፲፯÷፲፰)፡፡ ወኢይሰምዕዎ ቃሎ በአፍአ፤ በአፍአ ያሉ
ሰዎች ቃሉን አይሰሙትም፡፡ የቃሉን መለዘብ መናገር ነው፡፡ አንድም ናሁ ቁልዔየ ዘአኀዝክዎ፤ በስልጣን አንድ የምንሆን ልጄ ክርስቶስ፡፡
ወእሥራኤልኒ ኅሩይየ፤ የመረጥኩት ልጄ ክርስቶስ፣ ልብነቴ የወደደችው ልጄ ክርስቶስ፣ መንፈስ ቅዱስን በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ
ያስቀመጥሁበት ልጄ ክርስቶስ፣ ለአሕዛብ ወንጌልን ያስተምራል፡፡ አይጮኽም አይገነታም በአፍአ ያሉ ሰዎች ቃሉን አይሰሙትም ማለት
የቃሉን መለዘብ መናገር ነው፡፡ ከዚህ እንዲህ አለ፤ ከዚያ ወአልዐለ ቃሎ በምኩራብ ይላል ዮሀ ፯÷፳፰ አይጣላም ቢሉ አይጣላም፡፡
ከዚህ እንዲህ ማለቱ በሥጋዊ ነገር አይከራከርም ሲል ነው፡፡ ከዚያ ወአልዐለ ቃሎ ማለቱ መንፈሳዊውን አሰምቶ ያስተምራል ሲል ነው፡፡
፭ኛ. ኢሳ ፷፩1÷፩ “መንፈሰ
እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ አስተፍሥሆሙ ለነዳያን ፈነወኒ”
“መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ ወአስተፍስሆሙ
ለነዳያን ፈነወኒ”
ስለሱ ነዳያን ትሩፋንን ደስ አሰኛቸው ዘንድ በኔ ያደረ
መንፈሰ ረድኤት ላከኝ ይላል ኢሳይያስ ወእፈውሶሙ ለቁስላነ ልብ፣ በቁስለ መከራ የተያዙትን አድናቸው ዘንድ፤ ወእስብክ ሎሙ ግዕዛነ
ለፂውዋን፣ ለተማረኩት ነጻነትን አስተምራቸው ዘንድ ማለት ሚጠትን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ፡፡ ወይርአዩ እውራን፤ እውራነ ልቡና
እስራኤል ያዩ ዘንድ ላከኝ፡፡ ወእስምዮ ለዓመተ እግዚአብሔር ኅሩየ፤ ዕለተ ሚጠትን የተመረጠ እለው ዘንድ ወለዕለተ ፍዳ ኅሪተ፤
ዕለተ ፍዳም ያላት ዕለተ ሚጠት ናት የባቢሎን ሰዎች ፍዳን ስለተቀበሉባት ዕለተ ፍዳ አላት፡፡ ወአስተፍሥሆሙ ለልህዋን፤ ሰባ ዘመን
ያዘኑትን ደስ አሰኛቸው ዘንድ፡፡ ወአሀቦሙ ክብረ ለእለ ይላህውዋ ለጽዮን፣ ኢየሩሳሌምን አጥተው ላዘኑ ሰዎች ክብረ ሥጋን እሰጣቸው
ዘንድ፡፡
ወህየንተ ሐመድ እፍረተ ትፍሥሕት ለእለ ይላህው፣ ትቢያ
ይበንባቸው ስለነበረ ፈንታ ላዘኑ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ ሽቱን እሰጣቸው ዘንድ፤ ወልብሰ ክብር ህየንተ መንፈስ ትኩዝ፣ ሰባ ዘመን
ስለአዘነ ልብ ፈንታ ደስ አሰኘው ዘንድ ፈነወኒ፣ ላከኝ፣ አንድም መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ አስተፍሥሆሙ
ለነዳያን ፈነወኒ፣ ያዋሐደኝ በህልውናዬ ያለ የእግዚአብሔር የባሕርይ ህይወቱ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድም ሳይናበብ መንፈሰ እግዚአብሔር
ላዕሌየ፤ በእኔ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ያዋሀደኝ እግዚአብሔር አብ ምእመናንን አስተምር ዘንድ ላከኝ፣ አንድም መንፈስ ዘዚአየ
በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላእሌየ ብሎ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ተረጉሞታልና ብሎ የእግዚአብሔር አብ የባህርይ ህይወቱ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌየ
በእኔ ህልው ነው፣ ወዘበእንቲአሁ ቀብዐኒ፣ ስለማስተማርም ያዋሐደኝ መንፈስ ቅዱስ ምእመናንን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ፡፡
፮ኛ. ዳን ፱÷፳፬
“ወይትቀባዕ ቅዱሰ ቅዱሳን፣ ቅዱሰ ቅዱሳን ጌታ ይከብራል፣
የባህርይ ክብሩን ገንዘብ ያደርጋል፤ አእምር ወለቡ እምፀአተ ቃሉ ዘታወሥእ፣ ንገረው የሚለኝ ቃሉ ከመውጣቱ የተነሳ የምትመልሰውን
እወቅ፤ አንድም እምጸአተ ቃል ዘአወስአከ ንገረው የሚለኝ ቃል ከመውጣቱ የተነሳ የምመልስልህን እወቅ፡፡ አንድም እምፀአተ ቃሉ ዘታወሥእ
ንገረው የሚለኝ አካላዊ ቃሉ ከመምጣቱ የተነሳ የምትመልሰውን እወቅ፤ አንድም እምጸአተ ቃል ዘአወሥአከ አካላዊ ቃል ከመምጣቱ የተነሣ
የምመልስልህን እወቅ ወትትሐነፅ ኢየሩሳሌም እስከ ክርስቶስ ንጉሥ፣ ኢየሩሳሌም ጌታ እስቲወለድ ድረስ በመፍረስ በመታነፅ ቤተ መቅደስ
በመሆን ቆይታ ቤተክርስቲያን በመሆን ትታነፃለች ሰብአተ ሰንበታተ ስሳ ወክልዔተ ሰንበታተ ሰባት ሱባኤ ስድሳ ሁለት ሱባኤ ቆይታ፡፡
፯ኛ. ሐዋ ፲÷፴፰ “ዘቀብኦ
እግዚአብሔር መንፈሰ ቅዱሰ ወኃይለ”
“ዘቀብኦ እግዚአብሔር መንፈሰ ቅዱሰ ወኃይለ”
እግዚአብሔርነቱ ኃይሉ ሕይወቱ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ
የመረጠው የሾመው፡፡ ውእቱ መጽአ ከገሊላ ወደ ይሁዳ በመምህርነት መጥቶ ወረድኦሙ ለእለ ይተዔገሎሙ ሰይጣን፤ ሰይጣን ድል አድርጓቸው
የነበሩትን እንዳዳነ ታውቃላችሁ እስመ በዘአመከርዎ ክህለ ረድኤቶሙ ለሕሙማን ወረድነ በከመ ምክረ ፈቃዱ እንዲል፡፡ እስመ እግዚአብሔር
ምስሌሁ እግዚአብሔር በህልውናው ነውና፡፡
፰ኛ. ሮሜ ፩÷፪-፬ “በእንተ ወልዱ ዘተወልደ ወመጽአ እም ዘርአ ዳዊት በሥጋ ሰብእ ወአርአየ ከመ ወልደ
እግዚአብሔር ውእቱ በኃይሉ ወበመንፈሱ ቅዱስ”
“ዘአቅደመ ነጊረ በአፈ ነቢያቲሁ ወበመጻሕፍቲሁ ቅዱሳት በእንተ ወልዱ
ዘተወልደ”
አካል ዘእም
አካል፣ ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ የልጁን ነገር ፤ ስለ ተወለደ ስለ ልጁ፤ በዳዊት “ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ” መዝ
፪÷፯፤ በነገሥት “አነ እከውኖ አባሁ ወውእቱ ይከውነኒ ወልድየ” ፪ኛ ነገ ፯÷፲፬፤ በሰሎሞን “እምቅድመ አድባር ወአውግር ወለደኒ”
ምሳሌ ፰÷፳፭፤ በነቢያት በመጻሕፍት ያናገረ የአብን ነገር ከማስተምር
ከእኔ ከጳውሎስ የተገኘች ክታብ (መልእክት) ሐተታ መጻሕፍት፣ ነቢያት የሚላቸው ልዩ ናቸውን ቢሉ ነቢያት ያላቸው ሳሉ የተናገሩት፡፡
መጻሕፍት የሚላቸው ከሞቱ በኋላ የተጻፉት ናቸው፡፡ ይህማ ሳሉ የተናገሩት ከሞቱ በኋላ ቢጻፍ ልዩ ነውን ብሎ ነቢያት የሚላቸው አድሮ
ያናገራቸው፡፡ መጻሕፍት የሚላቸው በዘፈቀደ ታይቶ ያጻፋቸው ናቸው፡፡ ቅዱሳት ንጹሐት ክቡራት ሲል ነው፡፡ ርኩሳት መጻሕፍተ ጥንቆላ
አሉና ከዚያ ሲለይ ንጹሐት አለ፡፡ ምኑናት መጻሕፍተ ደብዳቤ አሉና ከዚያ ሲለይ ክቡራት አለ፡፡
“ወመጽአ እም ዘርዐ ዳዊት በሥጋ ሰብእ”
በሥጋ ከዘርዐ
ዳዊት ስለተወለደ ስለ ልጁ፤ የተወለደ የልጁን ነገር በኢሳይያስ “ትወጽእ በትር እምሥርዎ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ
እምጉንዱ” “ወይቀውም ሥርዎ እሴይ ወዘተወልደ እምኔሁ ይከውን ንጉሠ ለአሕዛብ“ ኢሳ ፲፩÷፩ እና ፲፤ በዳዊት “ እስመ እምፍሬ
ከርስከ አነብር ዲበ መንበርከ” መዝ ፻፴፪÷፩ ብሎ በነቢያት በመጻሕፍት ያናገረ የአብን ህግ ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ ሐተታ ሥጋ እንስሳ አለና ከዚያ ሲለይ ሥጋ ሰብእ አለ፡፡ ምነው ዘርዐ ዳዊት
ያለው አይበቃምን ቢሉ ነፍስን እንደነሣ ለማጠየቅ ፤ ያውስ ቢሆን “ዘርዐ አብርሐም አልዐለ” እንዲል (ዮሐንስ አፈወርቅ) ዘርዐ
ዳዊት ያለው አይበቃምን ቢሉ በከዊን ሲል ነው፡፡
“ወአርአየ ከመ ወልደ እግዚአብሔር በኃይሉ ወበመንፈሱ ቅዱስ”
“ዘተወልደ
ወዘአርአየ” ብሎ ለወልድ ይቀጽላል፡፡ ኃይሉ ሕይወቱ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ከዘርዐ ዳዊት በመወለዱ ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ
ስላሳየ ፣ ስለ ልጁ ያሳየ፣ የልጁን ሕግ ወንጌልን ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ ሐተታ፡፡ አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም
ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን ያስረዳልና፡፡ “ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በደኃራዊ ልደት” እንዲል (ሃይማኖተ አበው ዘሱኑትዩ) አንድም በኃይሉ በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና በመወለዱ ፡፡
“ወበመንፈሱ
ቅዱስ”
መንፈስ ቅዱስን
በዮርዳኖስ በርግብ አምሳል በእራሱ ላይ በማኖሩ፡፡ “አሜሃ ስምዐ ኮነ መንፈስ በዮርዳኖስ ከመ ወልድ ዘበአማን ወአምላክ ዘበአማን”
እንዲል ቄርሎስ አንድም በኃይሉ ሦስት አመት ሦስት ወር ባደረገው ተአምራት፡፡
ወበመንፈሱ
ቅዱስ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን በመስደዱ፡፡ አንድም፡ “ዘአቅደመ ወዘአርአየ” ብሎ ለአብ ይቀጽላል፡፡ “በኃይሉ
ከመ ወልደ እግዚአብሔር አርአየ በመንፈስ ቅዱስ” በባሕርዩ ወልደ
እግዚአብሔር እንደሆነ መንፈስ ቅዱስን በእራሱ ላይ በማኖሩ ያሳየ የልጁን ነገር፡፡ አንድም “በመንፈስ ቅዱስ ከመ ወልደ እግዚአብሔር
አርአየ በኃይሉ” በግብረ መንፈስ ቅዱስ በመወለዱ ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ በግብሩ፣ በነገሩ አሳየ አለ፡፡ በነገሩ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ” ብሎ፡፡ በግብሩ መንፈስ ቅዱስን በርግብ አምሳል
በእራሱ ላይ በማኖሩ ያሳየ የልጁን ነገር በኢሳይያስ “ቁልዔየ ፍቁርየ ዘሰምረቶ ነፍስየ ወአነብር መንፈስየ ላዕሌሁ ወየአርር መንፈሰ
እግዚአብሔር ዘላዕሌየ ዘበእንቲሁ ቀብዓኒ” ብሎ ያናገረ የአብን ሕግ ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ የተላከች ክታብ፡፡
፱ኛ. ፩ኛ ዮሐ ፪÷፳፪
“ወመኑ ውእቱ ሐሳዊ ዘእንበለ ዘይክህድ ወይብል እስመ
ኢየሱስ ኢኮነ መሢሐ” ኢየሱስ መሢሕ አይደለም ከሚል ሰው በቀር የሚል ሰው ነው እንጅ ያለሱ ሐሰተኛ ማን ነው፡፡ አንድም ኅድረት
ከሚል ከንስጥሮስ በቀር ሐሰተኛ ማነው የለም፡፡ ሐተታ ምነው ሥጋ አምላክ አይደለም ብሏል እንጅ፡፡ ቃል መሲሕ አይደለም ብሏልና
እንዲህ አለ ቢሉ ቃልንስ መሢሕ ቢሆን ሥጋን አምላክ ባለ ነበር ቀንጃ ተዋሕዶን አለ፡፡
፲ኛ. ፩ኛ ዮሐ ፭÷፩
“ኩሉ ዘየአምን ከመ ኢየሱስ ውእቱ መሢሕ እምነ እግዚአብሔር
ተወልደ” ኢየሱስ መሢሕ እንደሆነ አለ ሥጋን እንደ ተዋሐደ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማረ፡፡ አንድም የተወለደ ነው፡፡ “ወኩሉ
ዘያፈቅሮ ለወላዲ ያፈቅር ዘኒ ተወልደ እምኔሁ” ወላዲውን አብን የሚወደው ተወላዲውን ወልድን ይወደዋል፡፡ አንድም ወላዲውን ወልድን
የሚወድ ተወላዲውን ምእመንን ይወዳል፡፡
ከላይ በዚህ መልኩ ሊቃውንቱ በአንድምታ በሐተታ አብራርተው ግልጥልጥ አድርገው የጻፉትን ካሳሁን እና መሰሎቹ
ግን እየቆነጸሉ እና በራሳቸው ፈቃድ እየተረጎሙ ምእመናንን ሲያደናግሩ ይታያሉ፡፡ ቤተክርስቲያናችን የምትጠቅሰው ይህንን መጽሐፍ
ነው እነካሳሁን ግን ይህንን የቤተክርስቲያናችንን መጽሐፍ ሲነቅፉ ይታያሉ፡፡ የካሳሁን ምናሉ መሰረተ ሐይማኖት ምእራፍ ስምንት በዚህ
ይፈጸማል ምእራፍ ዘጠኝን እንቀጥልበታለን፡፡
#ይቀጥላል
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፳፰
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment