Friday, December 1, 2017

መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? ክፍል ፲፪



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፳፯ ጀምረን  ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
ቅዳሜ እና እሁድን ቀስ ብላችሁ አንብቡት በዛ ብላችሁ እንዳትሰለቹ!
ካሳሁን ምናሉ ገጽ ፳፯ ላይ ምዕራፍ ሰባት ብሎ በሚጀምረው የገጹ መጨረሻ ላይ እንዲህ ይላል “መንፈስ ቅዱስን ትቶ ወልድን ብቻ በተዋሕዶ ከበረ ማት እንደንስጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ህፀፅ እንደማለት ይቆጠራል ምክንያቱም የባሕርይ አባቱን አብን የባሕርይ ሕይወቱን መንፈስ ቅዱስን ትቶ ወልድን በተዋሕዶ ከበረ ማለት ስተት ነው፡፡ ወልድ በማኅጸነ ማርያም ሲፀነስ በመንፈስ ቅዱስ ሲወለድም በመንፈስ ቅዱስ ቀስ በቀስ ሲያድግም በመንፈስ ቅዱስ ነውና ወልደ አብ ወልደ ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለት ይገባል” ይላል፡፡ እስካሁን ድረስ ካሳሁን ምናሉ ከመምህራን እግር ስር ቁጭ ብሎ የተማረ ሰው ይመስለኝ ነበር ለካ የኔቢጤ ነው በተባራሪ የሰማውን ብቻ ነው የጻፈው፡፡ በፊደል ግድፈቱም ስንወቅሰው የነበረ በስህተት ነው ለካ፡፡ ምን ይፈረድበታል ነገሩን አላወቀውማ አያያዙ አልገባውማ፡፡ 



“መንፈስ ቅዱስን ትቶ ወልድን ብቻ በተዋሕዶ ከበረ ማት እንደንስጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ህፀፅ እንደማለት ይቆጠራል” የምትለዋን ተመልከቱልኝማ፡፡ የንስጥሮስ ክህደት “መንፈስ ቅዱስ ህፁፅ” ማለት ነውን? የንስጥሮስ ክህደት  ይህ ነው፡፡
v  ከተዋሕዶ በኋላ መለያየት እንዳለ ያምን የነበረውን ዲያድርስ የሚባለውን መናፍቅ አስተምህሮ ያምን ነበር፡፡ የዚህ መሠረታዊው ክህደት ሁለት ባሕርይ የሚል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከተዋሕዶ በኋላ አንዱን ወልደ ዳዊት አንዱን ደግሞ ወልደ እግዚአብሔር ነው በማለት ያምን ነበር፡፡
v  ሁለት ባሕርይ የሚል እምነት ስለነበረው ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም የተወለደው ደግሞ ወልደ ዳዊት ነው ብሎ ያምን ስለነበር እመቤታችን ክብር ይግባትና የወለደችልን እሩቅ ብእሲ ሰውን ነው እንጅ አምላክን አይደለም ይል ነበር፡፡ በዚህም ድንግል ማርያምን “ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክህደቱን ጀምሯል፡፡
ታዲያ ንስጥሮስ “መንፈስ ቅዱስ ህፁፅ” ብሏል ብሎ መጻፍ ምን የሚሉት ቅዠት ነው? ንስጥሮስ ቢሰማ ኖሮ ካሳሁን ምናሉን ፍርድቤት ነበር የሚያቆመው እንኳንም አልሰማህ፡፡ “መንፈስ ቅዱስ ህፁፅ” ብሎ የተነሣው መቅዶንዮስ ነው፡፡  ከጉባዔ ኒቅያ እስከ ጉባዔ ቍስጥንጥንያ ሃምሳ አምስት ዓመት ነው በዚህ ጊዜ መቅዶንዮስ ለአብ መንበር እንዳለው “እግዚአብሔርሰ ይነብር ዲበ መንበሩ ቅዱስ” ተብሎ ተነግሯል ለወልድ መንበር እንዳለው “መንበርከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም” ተብሎ ተነግሯል ለመንፈስ ቅዱስ ግን መንበር እንዳለው የተነገረበት ቦታ የለምና “ሕፁፅ ነው” ብሎ ተነሣ ንጉሡ ዘየዓቢ ቴዎዶስዮስ ነው በቍስጥንጥንያ  ጉባዔ ይሁን ብሎ አዋጅ ነገረ በዚህ ምክንያት መቶ ሃምሳ ሊቃውንት ተሰብስበዋል አፈ ጉባዔው ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት ነው ኢይቤ ሠናየ ይቤ አብ ኢይቤ ሠናየ ይቤ ወልድ አላ ይቤ፤ ይቤ ሰናየ መንፈስ ቅዱስ በአፈ ኢሳይያስ ነቢይ በዓመተ ሞተ ዖዝያን ንጉሥ ርኢክዎ ለእግዚአብሔር እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ነዋኅ ወብሩህ ያለውን ይህን ባለመንበር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ  መንፈስ ቅዱስ ብሎ ተርጉሞብሃል ብሎ ረትቶበታል በዚህ ጊዜ እሱን ተከራክረው ረትተው አውግዘው ለይተው “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ” ብለው ሠልስቱ ምዕት ጸሎተ ሃይማኖት ላይ ጨምረውበታል፡፡
ካሰሁን ምናሉ ግን የመቅዶንዮስን ለንስጥሮስ ሰጥቶ ይናገራል፡፡

ካሳሁን ይቀጥልና “ምክንያቱም የባሕርይ አባቱን አብን የባሕርይ ሕይወቱን መንፈስ ቅዱስን ትቶ ወልድን በተዋሕዶ ከበረ ማለት ስተት ነው፡፡ ወልድ በማኅጸነ ማርያም ሲፀነስ በመንፈስ ቅዱስ ሲወለድም በመንፈስ ቅዱስ ቀስ በቀስ ሲያድግም በመንፈስ ቅዱስ ነውና ወልደ አብ ወልደ ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለት ይገባል” የሚገርማችሁ ነገር “በተዋሕዶ ከበረ” ማለት ስህተቱ ምኑ ላይ እንደሆነ መጽሐፍ ጠቅሶ አላስረዳም በጭፍኑ ነው እየጻፈ ያለ፡፡ እኛ ግን ማስረጃ እናቀርባለን፡፡ መጽሐፍ ነው ሊዳኘን የሚገባው፡፡ በነገራችን ላይ ካሳሁን ምናሉ  “ወልድ ብቻ በተዋሕዶ ከበረ ማለት ስህተት ነው” ሲል አብም መንፈስ ቅዱስም ሥጋን ተዋሕደዋል እያለን ነው፡፡ እኛ ደግሞ አባቶች እንዳስተማሩን መጻሕፍት እንደሚናገሩት ለተዋሕዶ የመጣው አካላዊ ቃል እንጅ አብና መንፈስ ቅዱስ ለልብሰተ ሥጋ አልመጡም እንላለን፡፡ ሦስቱ አካላት በድንግል ማርያም ማደራቸው ለልብሰተ ሥጋ አይደለም፡፡  ማደራቸውም አብ ለአጽንዖ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ነው እንጅ ሦስቱ ኹሉ ለለቢሰ ሥጋ ያደሩ አይደለም፡፡ በዚህ ጊዜ መለኮት ርቀቱን ለቆ ሳይገዝፍ ሳይለወጥ ትስብእትም ግዘፍነቱን ለቆ ሳይረቅ ሳይለወጥ እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾነ፡፡ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ማለት ይህ ነው አብ ለአጽንዖ ማለትም ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ መለኮትን እመቤታችን በጠባብ ማኅጸን እንድትችለው አጸናት ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ማለትም ትስብእትን ከአዳም መርገም አንጽቶ ቀድሶ ለተዋሕዶተ መለኮት የበቃ አደረገው ማለት ነው፡፡
ሁላችን እንደምናውቀው በከዊን አብን “ልብ” ወልድን “ቃል” መንፈስ ቅዱስን “እስትንፋስ” እንላለን፡፡ የአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” ከመንፈስ ቅዱስም ሕይወትነት (እስትንፋስነት) አይቀድምም አይከተልምም፡፡ በተመሳሳይ የወልድ “ቃልነት” ከአብ “ልብነት” እና ከመንፈስ ቅዱስ “እስትንፋስነት” አይይቀድምም አይከተልምም፡፡ የመንፈስ ቅዱስም “ሕይወትነት” (እስትንፋስነት) ከአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ለአብ እና ለወልድ እስትንፋሳቸው ነው ማለት የባሕርይ ሕይወታቸው ነው ማለት ነው፡፡ በቅብአት እምነት ውስጥ ግን “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ”  ይላሉ፡፡ እንግዲህ “ወልድ” ማለት ልጅ ማለት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ልጅነቱም ከአብ የባሕርይ ልጅነት ነው፡፡ ይህ “ወልድ” የሚለው ስም አብ “አብ” ከተባለበት መንፈስ ቅዱስም “መንፈስ ቅዱስ” ከተባለበት ስሙ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ “ወልድ” የሚለው ስም የተገባው የሆነ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ አይደለም፡፡ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜስ “አማኑኤል” “ኢየሱስ” ተባለ እንጅ ወልድ የተባለውስ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ “ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል” ከአብ በተወለደ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ “ወልድ” የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ያገኘው ዛሬ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ሳይሆን ጥንት ከአብ ተወልዶ “ወልድ” ተብሎ በተጠራበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ”  ቢባል ክህደት ነው አንጅ እምነት አይባልም፡፡ ምክንያቱም “አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ህልው ነውና” እንዳሉ የቀደሙ አባቶቻችን በሃይማኖተ አበው ዘዲዮናስዮስ ምእ ፻፩ ቁጥር ፲ ላይ፡፡
ካሳሁን “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለት ይገባል” ብሎ ይደመድማል፡፡ “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” ብለን እንዳንቀበልማ ሊቃውንት አውግዘውታል፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው፤ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፤ በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል የሚለው፤ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው፤ የአምላክነትንም ሥራ እርሱ ራሱ ይሠራል የማይል ቢኖር ውጉዝ ይሁን” ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ፸፫÷፵፱ ይላል፡፡ ታዲያ ይህንን ውግዘት ምን ብለን እንተርጉመው?
ካሳሁን ምናሉ “መንፈስ ቅዱስ በማኅፀነ ማርያም አምስት ነገር ሠርቷል፡፡ መፍጠር፣ መክፈል፣ ማንጻት፣ ማዋሐድ፣ ቅብዕ መሆን” ይላል፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ” ካላችሁ መንፈስ ቅዱስ ይህንን ሁሉ ሥራ አልሠራም ትላላችሁና ስም ሰጥታችሁ ግብር ነስታችኋል ይለናል፡፡  በመጀመሪያ “በተዋሕዶ ከበረ” ብለህ ስለማታምን ምሥጢረ ተዋሕዶ አልገባህም፡፡ ምሥጢረ ተዋሕዶ የተሰወረብህ ደግሞ ምሥጢረ ሥላሴ እና ምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ችግር ስላለብህ ነው፡፡ በሥላሴ ዘንድ ያለውን መገናዘብ እና አንዱ በአንዱ ህልው ሆኖ መኖር አልገባህም፡፡ በዚህ ጉዳይ ከዚህ በፊት ስላብራራሁ ጊዜ አልውሰድ፡፡
ካሳሁን ዝቅ ይልና “በአምስቱ አእማደ ምሥጢር ላይ እንደተጻፈ ከሆነ ወልድ ቅብዕ ለሊሁ ቀባዒ ወለሊሁ ተቀባዒ ይላል፡፡ ይህ ጥቅስ ከየት እንደተገኘ የተዋሕዶ ሊቃውንት ብጠይቅ የቄርሎስ መጽሐፍ ነው አሉኝ፡፡ በሐይማኖተ አበው በብራናው የቄርሎስ ብፈልግ ባስፈልግ አንድም ነገር የለም፡፡ ከተለያዩት ሊቃውነት እንደተረዳሁት ከሆነ በመሳፍንት ዘመን የኢትዮጵያ ስድስተኛው ጳጳስ መናፍቁ ቄርሎስ ነው ይችን ቃል የጻፋት የሚል መረጃ በሰፊው አገኘሁ” ይላል፡፡ እዚህ ላይ የሚያስቅ ንግግር ነው የተናገርህ፡፡ የብራና የምትለው እኮ ቆጋ ያለውን የክህደት ጽሑፍ የያዘውን መጽሐፍ ነው፡፡ እስኪ የት ጠይቀህ ነው ያጣኸው? እስኪ ጥንታውያን አድባራት እና ገዳማት ላይ ሂደህ ጠይቅ፡፡ ቄርሎስማ እንዲህ ይልልሃል ቄርሎስ  ስምዐት ፻፳፬÷፴፬ “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ …ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ..”፡፡ ይህ ቃል “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” ባዮችን ሲቀጠቅጥ የሚኖር ቃል ነው፡፡ ካሳሁን ምናሉም በአምስቱ አእማደ ምሥጢር መጽሐፍ ላይ ቁጭ ብሎ ያገኘው ቃል ይኼው ነው፡፡ ያኔ ደነገጠና የቅባት ሊቃውንት ላይ ሲሄድ አይዞህ ተረጋጋ “ለሊሁ ቀባዒ” ብሎ ለወልድ አይቀጸልም አሉት፡፡ ቄርሎስ  “ለሊሁ ቀባዒ” ይላ እኮ ሲላቸው ተወው እሱን ይህን የጨመረው መናፍቁ ቄርሎስ ነው ብለውት እርፍ፡፡ ሃይማኖተ አበውን አንቀበልም አንድ ነገር ነው ነገር ግን ለእናንተ አስተምህሮ የማይስማማ ሆኖ የተገኘን ቃል ሁሉ የመናፍቁ ነው ብላችሁ አትገፉትም፡፡ ይህማ ከሆነ ቀጥላችሁ እኮ ወንጌላዊው ዮሐንስንም እንደዚሁ ልትሉት ነው ፡፡ በተዋሕዶ ከበረ ማለት ኑፋቄ ከሆነማ እስኪ እነዚህን ተርጉሙልና፡፡
፩. “ዘአንገሦ ለሥጋ አዳም በመንፈስ ቅዱስ ወረሰዮ ቅዱሰ ወማሕየዌ፤ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት የአዳምን ባህርይ ያከበረዉ የባሕርይ አምላክ ያደረገዉ እርሱ ነው” ሃይማኖተ አበው ዘአልመስጦአግአያ ም ፪ ቁ ፭
፪. ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ላይ እንዲህ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ስምዐት ፻፳፬÷፴፬ “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ ውእቱ ወዐርገ ኀበ ሥልጣነ መለኮቱ እንዘ ሰብእ ውእቱ ወለሊሁ እግዚአብሔር አምላክ ተብህለ በእንቲአሁ ከመ ውእቱ ተለዐለ ፈድፋደ በእንተ ትህትና ወሕጸጽ እንተ ዘትስብእት ወንዴት ወለሊሁ ጸገዎ ስመ ዘላዕለ ኩሉ ዝንቱ ዘኮነ በህላዌ ከመ አምላክ ከመ ያልዕለነ ለነሂ ዓዲ ኀበ ሀሎ ዝኩ፤ ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው ሥጋ ትሁት ሕጹጽ ነዳይ ስለሆነ ተለዐለ ተብሎ ተነገረለት ከሁሉ በላይ የሆነ ስምንም እሱ ራሱ ሰጠው ተባለ ይህም የሆነ በባህርይ ተዋሕዶ ነው አምላክ እንደሆነ እኛንም እሱ ወደ አለበት ያቀርበን ዘንድ”
፫. “ወከመዝ ነአምሮ ለሊሁ ተቀብዐ ከመ ሥርዓተ ትስብእት ወዳእሙ ውእቱ ዘይቀብዕ ርእሶ በመንፈሱ ባሕቲቱ፤ በተዋሕዶ እንደከበረ እናውቃለን ግን በገዛ ሥልጣኑ ራሱን የሚያከብር እሱ ነው” ሃይማኖተ አበው ስምዓት ምእራፍ ፻፳፬ ክፍል ፪ ቁጥር ፲፬ ላይ፡፡
፬. “መኑ ውእቱ ዝንቱ ዘሐደሶ ለሥጋ እምነ ኀጉል ወተወክፎ እሙስና፤ ሥጋን ከብልየቱ ያደሰው ከመለወጥ አድኖ የተዋሐደው ይህ ማነው” ሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ም ፬ ቁ ፲፩
፭. “አነ እቄድስ ርእስየ፤ እኔ ራሴን አከብራለሁ” ዮሐ ፲፯÷፲፱
፮. “በቃል ክብር መክበር ለሥጋ ተገባዉርሳነ ቄርሎስ ፸፮÷
፯. “ከአብ የተገኘ ቃል ከተዋሐዳት ካከበራት ከሥጋ ጋር አንድ እንደሆነ መጠንርሳነ ቄርሎስ ፶፮÷፲፭
፰. “ሰዉ መሆንን ከወደደ ሰዉ አለመሆንን ከጠላ ሰዉ መሆንን ስለወደደ ከአብ በሚገኝ ክብር ከበረ ተባለ ከአብ የተገኘ ክብርም አካለ ቃል ነዉ ክብርነቱ ለተዋሐደዉ ሥጋ ነዉ፡፡ርሳነ ቄርሎስ ፶፮÷፫- ፬
፱. “በመንፈስ ቀዱስ አዋሐጅነት ከአብ በተገኘ ክብር ከብሯልና ከአብ የተገኘ ክብርም አካለ ቃል ነውከሌላ ክብር አይሻም ቃልን ከበረ የሚል አንቀጽ የለምና መሢህ የሚለዉ ክብር ነዉ ክብር ማለትም ከተዋሕዶ በፊት ክብር ያልነበረዉ ሥጋ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ከቃል ጋር ሲዋሐድ የባህርይ ክብርን በተዋሕዶ ገንዘብ ማድረጉን መናገር ነዉርሳነ ቄርሎስ ፵፯÷፱-፲፡፡
፲.  “ይህ ክብር በጸጋ በኅድረት እንዳልተሰጠው በዚህ ይታወቃል፤ በአንድ የመለኮት ባሕርይ ተዋሕዶ ነው አንጅ ለወልድ የአባቱ ልዑል ጌትነት ገንዘቡ ነውና” ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ም ፴፫ ቁ ፳፱
፲፩. “ዳግመኛ በዚህ ድርሳን እግዚአብሔር ሊዋሐደው ሥጋን እንደ ፈጠረ ተናገረ የመላእክት ፈጣሪ ሥጋ ያልነበረው እውነተኛ ፀሐይ ከንጹሕ ሥጋ ተወለደ ነቅፎ አልተወውም ንፁህ አድርጎ ፈጥሮ ፍጹም አምላክ አደረገው እንጅ” ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ ም ፷፰ ክ ፳፱ ቁ ፵፬
፲፪.  “በሥጋ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ከአብርሃም ከዳዊት ከተገኘ ባህርይዋም ኃጢአት የሌለበት በነፍስ በሥጋ ፍጹም የሚሆን አካልን ሊዋሐደው ፈጠረ ከማርያም የነሣውን ሥጋ ከኃጢአት ከዘር የራቀ አደረገው ከማኅጸን ጀምሮ በማይመረመር ግብር በአንድ ባሕርየ መለኮት ከእርሱ ጋር አንድ አደረገው” ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ም ፸ ቁ ፳
 በሉ ይብቃችሁ!
#ይቀጥላል

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፳፪ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment