Sunday, December 31, 2017

“ቅባት መጠመቅ አለበት” ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን ዳዊት



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
በመጀመሪያ እንኳን ለመልአኩ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም በፍቅር በአንድነት አደረሳችሁ እያልሁ ከዛሬ ሁለት  ዓመታት በፊት የጻፍኋትን ግጥም እነሆ እላለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ያነበበው ሰው ይህንን አልፎ ወደዋናው ርእሰ ጉዳይ መሄድ ይችላል፡፡ መብቱ በሕግ የተፈቀደ ነው ብያለሁ!
                         *********************************
በዱራ ሜዳ ላይ ናቡከደነፆር አምላኩን አቆመው፣
በስድሳ ክንድ ቁመት በስድት ክንድ ወርድ ከወርቅ አቅልጦ ሠራው፡፡
አምላኩን ሊያስመርቅ ያልተመረቀ አምላክ መርቁልኝ ብሎ፣
መኳንንት፣ ሹማምንት፣ አዛዥ፣ አዛውንቱን፣ መጋቢውን ሁሉ ጠራቸው በቶሎ፡፡
የንጉሥ ትዕዛዝ ነው ከታች ባትን ከላይም አንገትን ሊያስቆርጥ የሚችል፣
ታዲያ ማን ይቀራል? ማንስ ይንቀዋል? ማን ያቃልለዋል? READ MORE!
         ****************************************
 (ትንቢተ ዳንኤል ምእራፍ ሦስት በሙሉ ያንብቡ)
ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን ዳዊት በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የስብከት ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ምሥራቅ ጎጃም ላይ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ሲነሣ እርሳቸው ይፈቱታል የሚሉ በርካታ ሰዎች ባይታጡም እርሳቸው ግን በተቃራኒው ሲጓዙ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ እንዲያውም ምእመናን በሊቀ ጳጳሱ ላይ ቅሬታቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ በመሄድ ባሰሙበት ጊዜ ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን በምእመናን ተቃራኒ በመሆን ሊቀ ጳጳሱን ደግፈው አዲስ አበባ እና ባሕርዳር በመመላለስ ይታወቃሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ነሐሴ  ፳፬/፳፻፱ ዓ.ም ገዳመ አስቄጥስ አቡነ ተክለ ሃይማት ገዳም (ደብረ ማርቆስ ውስጥ) አክሊሌን “ተንጠልጥሎ አየሁት” በሚል ርእስ የጻፍሁትን ጽሑፍ ይዘው ሲወቅሱኝም ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ የጻፍሁትን ያነበባችሁ ታስታውሱታላችሁ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህንን አስመልክተው ምን እንዳስተማሩ ዩቲዩብ ላይ በወቅቱ የጫንሁትን አድራሻ እዚህ ላይ ጠቅ አድርጋችሁ ተመልከቱት፡፡
 https://www.youtube.com/watch?v=frZWu8NfM_U ባላዩት ነገር በስማ በለው ብቻ እንደተናገሩም በወቅቱ አንድ ጓደኛየ በጠየቃቸው ጊዜ መመለሳቸውን አስታውሳለሁ፡፡ “ቅባት” የሚለው ስም እንዳይነሣ የቅባቶች ጥምቀት ጉዳይም እንዳይነገር ብዙ ሲሠሩ ነበር፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑን ከማስጨብጨብ ባለፈ ስለተጻፈው የክህደት መጽሐፍ እንኳ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጡም፡፡ የሕዝብ ፊርማ አሰባስበን ለሀገረ ስብከቱ አስገብተናል ሆኖም ግን አንድም ነገር አላሉም ነበር፡፡ መጽሐፉ “ወልደ አብ” ግን በጥቅምቱ ሲኖዶስ ለመወገዝ በቅቷል፡፡ ይህ መጽሐፍ ከተወገዘ በኋላ አይደለም “የክህደት መጽሐፍ ነው” እያሉ ማውራት ድሮ ነበር፡፡
የነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የነ አለቃ አያሌው ታምሩ የነ በላይ ዘለቀ ሀገር ብቸና በተዋሕዶ እምነቱ ላይ ስለተጋረጠው ከፍተኛ ችግር  ኅዳር ፳፯/ ፳፻፲ ዓ.ም ዓ.ም ከፍተኛ ውይይት አድርጓል፡፡ በዚህ ውይይትም ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን ዳዊት ከሀገረ ስብከቱ ተልከው ነበር፡፡ እርሳቸውም ብቸኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገረ ስብከቱ ደረጃ ስላለው ወቅታዊ የሃይማኖት ፈተና በሰፊው ተጠይቀዋል፡፡ እርሳቸውም ጥያቄውን በዘዴ እና በማባል ዓይነት መልሰዋል፡፡ ለጊዜው ሊቀ ሊቃውንት በሰጡት መልስ የተሰበሰበው ሰው ተደስቷል ስቋልም፡፡ ነገር ግን እርሳቸው የተናገሩት የመሰከሩት ነገር በርግጥ ከእውነታቸው ነውን? አይመስለኝም ከሆነ ግን እሰየው፡፡ ብቸና ላይ ሄደው “ቅባት ይጠመቅ” ብለው ፍትሐ ነገሥቱ የሚያዝዘውን መናገራቸው ግድ ስለሆነባቸው ነው፡፡ “አይጠመቅ” ቢሉ ኖሮ ምን ይገጥማቸው እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም የተጠየቁትን ጥያቄ ሁሉ ህዝቡ እንደሚፈልገው አድርገው ለመመለስ ችለዋል፡፡ በእውነት የእውነታቸውን ከሆነ “ቅባት የለም” ሲሉ የነበረው ለምንድን ነው? ያን ያህል ነገር ያለአቅሜ ያለ እውቀቴ ያለችሎታየ ስለቅባት ስጽፍ የነበረውን ጽሑፍ ከንቱ ነው አትከተሉት ሲሉ የነበረውስ ታዲያ ምን ሆነው ነበር? ቅዱስ ሲኖዶስ “ወልደ አብ” በታተመበት አካባቢ ህዝባዊ ውይይት እንዲደረግ ትምህርት በሰፊው እንዲሰጥ ስልጠና እንዲዘጋጅ ብሎ ወስኖ ነበር ታዲያ እርሳቸው የሀገረ ስብከቱ ስብከት ክፍል ኃላፊ እንደመሆናቸው መጠን ምን የሠሩት መሬት የነካ ሥራ አለ? ምንም!
ብዙዎች ሊቀ ሊቃውንት “ቅባቶች ይጠመቁ” ብለው ብቸና ላይ አስተምረዋል ሲባል እንደብርቅ የተመለከቱ አሉ፡፡ ብቸና ሄደው ታዲያ ምን ሊሉ ነበር? ይህን ደግሞ ወደው ሳይሆን ተገደው ነው እውነቱን የመሠከሩት፡፡ የዲማ ሊቃውንት አባ ሣሕሉን ጨምሮ እኮ ስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡ ታዲያ በአባ ሣሕሉ ፊት ፍትሐ ነገሥቱን አጣመው እንዴት ሊናገሩት ይችላሉ? ምንም መውጫ ቀዳዳ የላቸውም እኮ፡፡ የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ አባ ሣሕሉ እዚያው ናቸው፡፡ ደብረ ማርቆስ ከተማ ላይ ይህንን ያሉበት መድረክ እስኪ ፈልጉ በእውት ይገኛል እንዴ? በፍጹም አታገኙም፡፡ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር ሁሉንም ጥያቄዎች ግን እንደ ምእመኑ ፍላጎት ነው የመለሱት፡፡ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም፡፡ “ቅባት ይጠመቃል” ሲሉ ህዝቡ አጨበጨበ “ለምን አጨበጨባችሁ” ብለው ሲጠይቁ “እውነት ስለተነገረ” አሉ፡፡ እውነቱ ይኼው ነው “ቅባት ይጠመቃል” መጽሐፉ ስላለ በቃ፡፡ ዛሬ ማንም ተነሥቶ  ሊሽረው አይችልም፡፡
አሁን በቅርቡ ታሕሳስ ፩/፳፻፲ ዓ.ም ደብረ ገነት ኤልያስ ቤተክርስቲያን ላይ ሊቀ ጳጳሱ “ጎጃምን ተጠመቁ የሚሉ መናፍቃን መጥተዋል” ብለው ቅባቶች መጠመቅ እንደሌለባቸው ሲያስተምሩ እኮ ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን ከአትሮኑሱ ሥር ቁጭ ብለው ነበር እየሳቁ እና እያጨበጨቡ ድጋፋቸውን ሲሰጡ የነበረው ታዲያ ቃሉ ይታበላልን? በቦታ በጊዜ ይለወጣልን? ጎጃም ማለት ቅባት ማለት አይደለም ቅባት ማለትም ጎጃም ማለት አይደለም፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ግን ይህን ደበላልቀው ነው በዘዴ ህዝቡን የሚግቱት፡፡
                                      *****************************************
 ባሳለፍነው  ታሕሳስ ፩/፳፻፲ ዓ.ም በሸበል በረንታ ወረዳ በየዕድውሃ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አንድ ልዩ ጉባዔ  ከቀኑ ፮ ስዓት ጀምሮ ነበር፡፡ ጉባዔው መስረት የደረገው  ቅዱስ ሲኖዶስ በተለያዩ ጊዜያት ያስተላለፈው መመሪያ በተለይም በተሃድሶ መናፍቃን  ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ ጉባዔው ከመካሄዱ በፊት የተወሰኑ የቤተክርስቲያናችን ልጆች ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሲወያዩና በተለያዩ አህጉረ ስብከት የተከናወኑ ስራዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ያገኙትንም ጭምር በሰፊው ሲነጋገሩሩ ከቆዩ በኋላ ስለራሳችን ሃገረ ስብከት አንሥተው ሲወያዩ ምንም የተሠራ ነገር እነደሌለና ከዚያም አልፎ በዚሁ በተሃድሶ መናፍቃን ጉዳይ ላይ ያለመሰልቸት የሚታገሉትን ጠንካራ ጠንካራ ሰንበት ትምህርት  ቤቶችንና ማኅበረ ቅዱሳንን በመክሰስናሥራ እንዳይሠሩ በመከልከል እንዲሁም ከዘህ ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው ያሰቧቸውን የሰበካ ጉባኤ አባላትንና የሀገር ሽማግሌዎቸን ከሥራ ማገዳቸው ከዚህ በተጨማሪም  ውግዘት መፈፀማቸውን ከዚያም ባለፈ ህዝበ ክርስቲያኑ በሃገረ ስብከቱ እየተሠራ ያለውን ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ በደል አቤት ሊሉ አዲስ አበባ ድረስ ከ ፯ ጊዜ በላይ ተመላልሰው ምንም መፍትሔ አለማግኘታቸውን በሰፊው ተነጋግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሀገረ ስብከቱ የተዋቀረው ከአንድ ቤተሰብ ስለሆነ ችግራቸውን ለማንም አቤት ማለት እንዳልቻሉ ሲረዱት ለምን በእኛ ቤተክርስቲያንስ የፀረ ተሃድሶ ጉባኤ አናካሂድም ብለው ወደ ሰበካ ጉባአው ለመሄድ ተገደዋል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም ተፈቀደ (ሰበካ ጉባዔው መጀመሪም ፈቅዶ ነበር ወረዳ ቤተ ክህነት እንጂ) ፡፡ በነገራችን ላይ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ በየአጥቢያ መዋቀር እንዳለበት ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል የጠቅላ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስም በደብዳቤ ለየአህጉረ ስብከቱ አሳውቀዋል፡፡ ይህ ደብዳቤ ሥራ እንዳይሠራ የጠደረገው ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ውስጥ ነው፡፡ በርግጥ የተወሰኑ ሌሎች አህጉረ ስብከቶችም አይታጡም፡፡
በዚህም መሠረት ህዝቡ ተቀሰቀሰ ከጎይ ፣ ከየምጥች ፣ ከገንዳ ኢያሱ፣ ከወረጎ፣ ከመርገጭ እና ከሌሎች የገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር ህዝበ ክርስቲያኑና ለቃውንተ ቤተክርስቲያኑ ከቀኑሰዓት ጀምሮ ተሰበሰቡ በቤተክርሰቲኑ ውስጥ ታላቅ ደንኳን ተጣለ፡፡ ትምህርት በሊቃውንት ተሰጠ ቀጥሎም የተሀድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ገለጻ ተደረገ፡፡ በዚህ ገለጻ ላይ መጀመሪያ የብጹእ አቡነ ቀውስጦስ በእንባ የታጀበ የአደራ ቃል (ልጆቼ ራሳችሁን እንዳታሠርቁ የሚለው) ተሰማ መላ ክርስቲያኑ አብሯቸው አለቀሰ ከዚያም ስለተሐድሶ  መናፍቃን ስለስልቶቻቸው ፣አካሄዳቸው ፣ ግባቸውና ከኛ ምን ይጠበቃል በሚል በድምጽ እና በምሥል ቀረበ፡፡
ገለጻው አልቆ ከምዕመናን  ሃሳብ እንዲሰጥ በተጠየቀ ጊዜ ግን ሌላ ነገር ተፈጠረ ይኸውም አንድ አባት ተነሥተው እንዲህ አሉ ፡- “አሁን ያቀረባችሁልን ነገር እጅግ በጣም ጥሩ ነው አኛም ተኝተን ነበር ቀሰቀሳችሁን አግዚአብሔር ይስጣችሁ ነገር ግን አሁንም የሚቀር ነገር አለ እርሱም የሃገረ ስብከታችን ጉዳይ ነው፡፡ እኔ እድል ገጥሞኝ ቀድሜ ሰምቼ  ስለነበረ  አዲስ አበባ ድረስ ከወንድሞቼ ጋር ሔጄ አቤቱታ አቅርበን ነበር ፡፡ ነገር ግን አቤቱታችንን ሊያጣራ የመጣው ልዑክ ፍርደ ገምድል ሆነብንና ለተከሳሽ ፈርዶ ሄደ፡፡ በጠቅላይ ቤተክህነቱ ተስፋ ቆረጥን (በማዘን እንባ እየተናነቃቸው) ስለዚህ በሀገረስብከቱ  እየተሰራ ያለውን ግፍ እዚህ ይቅረብና እንወያይበት ጠቅላይ ቤተክህነት ቤተክርስቲያናችንን ካልጠበቀ ለራሱ ይብላኝለት እኛ ግን ለራሳችን አናንስምና ይቅረብ እንወያይ በብቸና፣በደጀን ብዙ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡ያልገባን እንዲገባን ይደርግ እንወያይ ይቅረብልን”አሉና ተቀመጡ፡፡ የተሰበሰበው ህዘበ ክርስቲያን በሙሉ ረጅም ደቂቃ የፈጀ የድጋፍ  ጭብጨባ አሰማ፡፡ ገለጻውን የሚያካሂደው ልጅ ግን መርሃግብሩ ይህን አይመለክትም አይሆንም ቢል የተለያዩ የሃገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች እየተነሱ ለምን ትፈራላችሁ ይሄ የሃይማኖት ጉዳይ ነው መሞት ካለብን እንሞታለን አሉ፡፡ ከዚያም መርሃግብሩን ያዘጋጁት ትንሽ ከተወያዩ በኋላ ችግሩ ተመጥኖ እንዲቀርብ ወሰኑ ፡፡
ገለጻውም እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሊቀ ጳጳሱ በሃገረ ስብከቱ እየሰሩት ያለው ችግር በሁለት ተከፍሎ ቀረበ ይኸውም፡-
Ø  የአስተዳደር ችግር
Ø  የሃይማኖት ችግር
በነዚህ ርእሶች መነሻነት  ብዙ ጉዳዮችን ከማስረጃ ጋር አቀረቡ ፡፡ በተለይ “ወልደአብ” የተባለው መጽሐፍ ሲወገዝ የፃፈው ሰውና የአሳተመው ገዳም ዝም መባሉ ምዕመናንን አስቆጣቸው አበሳጫቸውም፡፡ በመጨረሻም ለዚህ ጉባኤ ዝግጅት ተመርጠው የነበሩ ኮሚቴዎችን የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ አድርጎ መርጧል ጉባዔው፡፡ ጉባዔው በአንድ ድምጽም  ከዚህ በኋላ ጉዳዩ ይመለከተናል ሁለቱንም ማለትም የሃገረ ስብከቱም ችግር ሆነ  የተሃድሶ መናፍቃኑ ጉዳይ የሁላችን ተግባር ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ለቅበቶች ከሆኑ የኛ አይደሉም በሃይማኖታችን አንደራደርም፡፡ ጀግኖች አባቶቻችን እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ፣ እነ አለቃ አያሌው ታምሩ ፣ ጀግናው በላይ ዘለቀና ሌሎችም የተጋደሉላት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን አሳልፈን ለማንም አንሰጥም ብለው ሁሉም በቁጭት ሃሳባቸውን አቅርበው፡፡ ጉባዔው በዚህ መልኩ ተፈጽሞ ምእመናን ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡
ይህ ውይይት ከተደረገ ከ፫ ሰምንት በኋላ ሊቀ ጳጳሱ አባ ማርቆስ ይህን ሊያስተባብሉ በሚመጣው እሁድ ታህሳስ ፳፪/፳፻፲ ዓ.ም  የዕድውሃ ላይ በቀድሞው የሸበል በረንታ ወረዳ ቤተ ክህነት ኃላፊውና የአሁኑ ቁጥጥር በሆነው በአባ ክንፈሚካኤል ጫኔ ወንድም ከ መልአከ ኃይል ግብራም ና ከአሁኑ ቤተክህነት ኃላፊ ገብረ  አስተባባሪነት  ጉባኤ አዘጋጂተዋል ተብሏል፡፡ ሸበሎች በቦታው በመገኘት በጨዋና ሃይማኖታዊ ምግባርን በተላበሰ መልኩ እንደብቸኛዎች ጥያቄዎችን በመጠየቅ ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት እንድትሞክሩ እናሳስባለን፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ታህሳስ ፲፰ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment