Monday, April 18, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል ስምንት

© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 10/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት ክፍሎች ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ 19 ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ጋር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ያለመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መናፍቃንን እንዴት ማቆም እንደምንችል እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  20ኛ ነጥብ፡- ያለመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንዴት ማቆም ይቻላል የሚለውን በተመለከተ፡፡
·         ኢየሱስ ያድናል! ኢየሱስ ጌታ ነው! እያሉ ለሚፎክሩ፡- መናፍቃን ኢየሱስ ክርስቶስን ያከበሩ መስሏቸው “ኢየሱስ ያድናል! ኢየሱስ ጌታ ነው!” የሚል መፈክር አነግበው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በእነርሱ ቤት ኦርቶዶክሳውያኑ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት እና ጌትነት ያልተረዳ ነው፡፡ ታዲያ “ኢየሱስ ያድናል! ኢየሱስ ጌታ ነው! ሃሌ ሉያ!” እያሉ ለሚመጡባችሁ መናፍቃን “የኢየሱስን አዳኝነት እና ጌትነት ገና ዛሬ ነውን ያወቃችሁት” በሉት፡፡ “እኔ ግን ኢየሱስ እንደሚያድን እና ጌታ እንደሆነም ካወቅሁት በጣም ብዙ ዘመን ሆኖኛል ለዚያም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምለው” በሏቸው፡፡
·         ለእያንዳንዷ ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አሳዩን ለሚሉ፡- ድንግል ማርያም ታማልዳለች ስንል ጥቅስ ይላሉ፣ ቅዱሳን ያማልዳሉ ስንል ጥቅስ ይላሉ፤ ጸበል ያድናል ይፈውሳል ስንል ጥቅስ አምጡ ይላሉ… በርካታ ጥቅሶችን ስትሰጧቸው ደግሞ ይህ እኮ እንዲህ ለማለት ነው እያሉ በራሳቸው ፍላጎት እየተረጎሙ ቅዱሳንን እስከመሳደብ ይደርሳሉ፡፡ ስለዚህ ቅዱሳንን ላለማሰደብ ቀላል ዘዴ አለው፡፡ ገና ወይም ጥምቀት መቼ ይውላሉ በሏቸው፡፡ ገና ታህሳስ 29 ወይም 28 ጥምቀት ደግሞ ጥር 11 ይውላል ብለው ይመልሱላችኋል፡፡ ያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አሳዩን ብላችሁ ጠይቋቸው፡፡
·         መስቀልን ለሚንቁ፡- መናፍቃን መስቀልን አባት እንደተገደለበት ሽጉጥ እንደሚቆጥሩ ባለፈው ዓይተናል ዛሬ ደግሞ ካለጥቅስ ያንኑ ጥያቄ እንዴት መመለስ እንችላለን የሚለውን እንይ፡፡ መናፍቃኑ መስቀል ጠላታችን ነው ምክንያቱም አባታችን ኢየሱስ የተሰቀለበት ስለሆነ ስለዚህም በአንገት ማሰር ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ ታዲያ የእናንተ መልስ ምን መሆን አለበት መሰላችሁ “ኢየሱስ እንደተሰቀለበት ደሙንም እንዳፈሰሰበት በደሙም እንደቀደሰው አውቃለሁ፡፡ ስለዚህም ጠላቴ አይደለም የዳንኩበት መድኃኒቴ ነው እንጅ፡፡ ነገር ግን ጠላቴ እንኳ ቢሆን ኢየሱስ ጠላትህን ውደድ ብሎ ስላስተማረኝ እወደዋለሁ በአንገቴም አሥረዋለሁ” በሏቸው፡፡
·         ጽላትን ለሚንቁ፡- በተለይ በጥምቀት በዓል ጊዜ ታቦታት ከየመንበራቸው ይወጣሉ ያን ጊዜ እኛም ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት እንደዘለለ እኛም እንዲሁ እያመሰገንን ታቦታትን ከየማረፊቸው እናደርሳለን፡፡ ያን ጊዜ መናፍቃኑ ለምንድነው እንዲህ የምታመሰግኑት ታቦት እኮ ጣዖት ነው ይሉናል፡፡ ጥቅስ ጠቅሳችሁ ታቦት ጣዖት እንዳልሆነ ብታስረዷቸውም በፍጹም አይገባቸውምና ታዲያ ታቦት ምንድን ነው እያሉ አብዝተው ይጠይቁናል፡፡ ያኔ ቁርጥ ያለችዋ መልስ “ባዶ አዳራሽ ያደገ አያውቀውም” ብላችሁ ትታችሁ መሄድ ብቻ ነው፡፡
·         ቅዱሳንን ለሚንቁ፡- መናፍቃን “ኢየሱስ መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ብሏል ዮሐ14፥6 ላይ ስለዚህ ቅዱሳን ምንም አያስፈልጉም ምክንያቱም ኢየሱስ በእኔ በቀር ብሏልና” ብለው የቅዱሳንን ምልጃ ይንቃሉ፡፡ ያን ጊዜ መልሳችሁ ምን መሆን አለበት መሰላችሁ “ኢየሱስ መንገድ ከሆነስ ቅዱሳኑ ደግሞ መንገዱን ይመሩናል” የሚል ነው፡፡
·         ኢየሱስን አማላጅ ለሚሉ፡- መቼም መናፍቃን የሚታወቁት ሮሜ 8÷34ን ብቻ በማነብነብ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ጥቅስ ጠቅሰው ኢየሱስ አማላጅ ነው ከሏችሁ መልሳችሁ “እኛስ ቅዱሳን ስለሚያማልዱን ኢየሱስ ክርስቶስን አማልደን አንለውም” የሚል መሆን አለበት፡፡
·         በ40 በ80 መጠመቅን ለሚንቁ፡- መናፍቃን ኢየሱስ በ30 ዓመቱ ስለተጠመቀ እኛም በ30 ዘመናችን እንጠመቃለን ይላሉ፡፡ እኛ በ40 በ80 መጠመቃችንንም ያንቋሽሻሉ ያንጊዜ መልሳችሁ “አንተ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እኩል ሆነህ ከሆነስ አርባ ሌሊትና አርባ ቀን እንደጾመ አንተም እንዲሁ ጹም” ብላችሁ ትታችኋቸው ሂዱ፡፡
ተፈጸመ፡፡


No comments:

Post a Comment