Monday, April 18, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል ሰባት

© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 9/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት ክፍሎች ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ 18 ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ጋር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
·         19ኛ ነጥብ፡- የዜማ መሣሪያዎችን በተመለከተ፡፡
·         በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ማመስገን አለብን ለሚሉ፡- የእምነት ሥርዓት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን አለበት፡፡ ሃይማኖት ደግሞ ሰማያዊ ነገርን የምናስብበት እጅ ምድራዊ ነገርን የምናስብበት መሆን አይገባውም፡፡ ሰማያዊን ምሥጢር የሚያሳዩንን የዜማ መሣሪያዎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሰፍሮ እና ቆጥሮ ሰጥቶናል፡፡ እነዚያን ከመጠቀም አልፈን ግን ለጭፈራና ለዳንስ ከተሠሩ መሣሪያዎች ጋር የምንቆራኝበት ምንም ምክንያት የለንም፡፡ እያንዳንዳቸው እኛ የምንጠቀምባቸው የዜማ መሣሪያዎች የራሳቸው የሆነ ትርጉም እና የራሳቸው የሆነም ምሳሌነት አላቸው። አሁን እንድንጠቀምባቸው የሚወተውቱን መሣሪያዎች ግን ምንም ትርጉም ምንም ዓይነት ምሳሌነት የሌላቸው መጽሐፍ ቅዱስም የማያውቃቸው ናቸው፡፡ የእኛ የሆኑት እነማን ናቸው መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይላል ትርጉማቸውስ ምንድን ነው እንመልከታቸው፡፡
·         ከዜማ ማሪያዎች መካከል ከበሮ፣ በገና፣ ዋሽንት፣ ጸናጽል፣ መቋሚያ እና መሰንቆ ይጠቀሱበታል፡፡ እነዚህ መሣሪያዎች የራሳቸው ትርጉም ያላቸው እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ መዝ 150 ተመልከቱ፡፡
·         ከበሮ፡- የጌታችን ምሳሌ ሲሆን ትርጉሙም፡- ሰፊው አፍ እግዚአብሔር አምላክ ምሉዕ በኩለሄ /በሁሉ የሚገኝ/ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ጠባቡ አፍ ደግሞ ምሉዕ በኩለሄ የሆነው አምላክ ስለሰው ፍቅር በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት መወሰኑን ይገልጣል፡፡ በከበሮው ላይ የሚታዩት ሁለቱ አፎች የተያያዙበት ጠፍር አይሁድ ጌታችንን በገረፉት ወቅት በሰውነቱ ላይ የወጣውን ሰንበር አጥንቱ መቆጠሩን ሥጋው ማለቁን ያስታውሳል፡፡ በአንገታችን አነግተን መያዛችን ጌታችንን በአንገቱ ገመድ አስገብተው ያንገላቱትን ያጠይቃል፡፡
·         መሠንቆ፡- የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያምመሰንቆሁ ለዳዊትይላታል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ መሠንቆ ያልኳት ሰማዕታት የለበሷት ቀናተኛ ሃይማኖት ናት ይላታል፡፡ መሠንቆ ክሩ አንድ መሆኑ የአንዲት ሃይማኖት ምሳሌ፡፡ መሰንቆ ድምጽ የሚሰጠው በዕጣን ሲታሽ ነው፡፡ ዕጣኑ የክርስቶስ ድምጹ የምስጋናዋ ምሳሌ ነው፡፡ መከርከሪያው የኖኅ ቃል ኪዳንን ያጠይቃል፡፡ ቋሚና አግዳሚ ተዋቅረው የሚሠሩት መስቀል ነገረ መስቀሉን እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡
·         በገና፡- ሁለት ቋሚዎች አሉት ምሳሌነታቸውም ለብሉይ ኪዳንና ለሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ አሥር አውታሮች አሉት እነዚህም የዐሠርቱ ትዕዛዛት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱ ኪዳናት /ማለትም በሐዲስና በብሉይ/ ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር ዐሠርቱ ትእዛዛት እንደሚፈጸሙ ጌታ ያስተማረውን ያጠይቃል፡፡
·         ዋሽንት፡- የወንጌል ምሳሌ ነው፡፡ አራቱ ቀዳዳዎች የአራቱ ወንጌላውያን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ /አራቱ ወንጌላውያን የሚባሉት ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ሉቃስ፣ ቅዱስ ማርቆስና ቅዱስ ዮሐንስ ናቸው፡፡/ ዋሽንት ደስ የሚያሰኝ ድምጽን አውጥቶ ኅሊናን እንደሚያነቃቃ ወንጌልም ወልደ እግዚአብሔር ተወለደ ዲያብሎስ ተሻረ የሚልን የምስራች ትናገራለችና፡፡
·         ጸናጽል፡- ሁለት ቋሚዎች ሁለት አግዳሚዎች አሉት፡፡ ሁለቱ ቋሚዎች የያዕቆብ መሰላል ምሰሶ፣ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ሲሆን አግዳሚዎቹ ደግሞ የያዕቆብ መሰላል መውጫና መውረጃ፣ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌ፡፡ በአግዳሚዎቹ ላይ ያሉት ሻሻታዎች በያዕቆብ መሰላል ላይ ሲወጡና ሲወርዱ የነበሩት መላእክት ምሣሌ፣ 5 ቢሆኑ የአምስቱ አእማደ ምስጢራት፣ 7 ቢሆኑ የሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ምሳሌ፡፡ ሁለቱን ቋሚዎች የሚያገናኘው ደጋን በያዕቆብ መሰላል እግዚአብሔርን ያየበት ዙፋን፣ የኖኅ ቀስተ ደመና፣ የቀራንዮ ተራራ ምሳሌ፡፡ ከደጋኑ ላይ ያለው መስቀል በዙፋኑ ላይ ያለው እግዚአብሔር፣ ቀራንዮ ላይ የተተከለው እውነተኛ መስቀል፣ የተሰቀለው የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ የጸናጽሉ መያዣ የሕገእግዚአብሔር የፍቅር ምሳሌ ነው፡፡
·         መቋሚያ፡- ነገረ መስቀሉን የምናስታውስበት ለጸሎትና ለማኅሌት የምንጠቀምበት መሣሪያ ነው፡፡ 
ከእነዚህና መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ቦታ ከጠቀሳቸው የዜማ መሳሪያዎች ውጭ መጠቀም መጽሐፍ ቅዱሳዊነት ከመሆኑም በላይ ለዝሙት ለጭፈራና ለዳንስ የሥጋ ፍላጎትን ለመቀስቀስ መነሣሣት ነው፡፡ ኦርጋን፣ ፒያኖ፣ ሳክስፎን፣ ጊታር ወዘተ የሚባሉት የሙዚቃ መሣሪያዎች በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔርን እንድናመሰግንባቸው አልተጠቀሱም፡፡ ከዚህም ባለፈ ምንም ትርጉም እና ምሳሌነት የላቸውም፡፡ መናፍቃን ግን መዝ 150÷6 ላይ ያለውንእስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግንይላልና ማንኛውንም የትንፋሽ መሣሪያ መጠቀም መጽሐፍ ቅዱሳዊነት ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን ዳዊትእስትንፋስ ያለውአለ እንጅ በትንፋሽ የሚሠራ መሣሪያ አላለም፡፡ እስትንፋሱ እኮ የመሣሪያ ተጫዋች ከሆነው ሰው የሚወጣ እንጅ ከመሣሪያው የሚወጣ ወይም የሚገኝ አይደለም፡፡ ቢሆንማ መሣሪያው ብቻውን ማመስገን ነበረበት በሏቸው፡፡እስትንፋስ ያለው ሁሉሲል ፍጥረታት ሁሉ ለማለት እንጅ የትንፋሽ መሣሪያዎችን ሁሉ ተጠቀሙ ማለቱ አይደለም፡፡ 
ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻል ነበር ነገር ግን ለዛሬው ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ ይዤላችሁ እመጣለሁ። አምላክ እንዲረዳኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ “ወልደ ማርያም” ነኝ፡፡
ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment