Friday, July 22, 2016

“የንስጥሮስ ክህደት ዛሬ በቅብአት እምነት ውስጥ ሲደገም”


© መልካሙ በየነ
ሐምሌ 15/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ንስጥሮስ ሁለት መሠረታዊ ክህደቶች አሉበት፡፡ እነዚህም፡-
v  ከተዋሕዶ በኋላ መለያየት እንዳለ ያምን የነበረውን ዲያድርስ የሚባለውን መናፍቅ አስተምህሮ ያምን ነበር፡፡ የዚህ መሠረታዊው ክህደት ሁለት ባሕርይ የሚል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከተዋሕዶ በኋላ አንዱን ወልደ ዳዊት አንዱን ደግሞ ወልደ እግዚአብሔር ነው በማለት ያምን ነበር፡፡
v  ሁለት ባሕርይ የሚል እምነት ስለነበረው ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም የተወለደው ደግሞ ወልደ ዳዊት ነው ብሎ ያምን ስለነበር እመቤታችን ክብር ይግባትና የወለደችልን እሩቅ ብእሲ ሰውን ነው እንጅ አምላክን አይደለም ይል ነበር፡፡ በዚህም ድንግል ማርያምን “ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክህደቱን ጀምሯል፡፡
 ወልደ አብ ገጽ 127
እነዚህን ክህደቶቹን በአደባባይ በማስተማር እርሱን መሰሎችን መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ለዚህ ክህደቱም ይደግፋል ብሎ ይጠቅስ የነበረው “ቃል ሥጋ ሆነ” ዮሐ1÷14 የሚለውን ቃል ነበር፡፡ ይህንን ቃል ለራሱ እንዲመች አድርጎ መለወጥ አለበት በማለት ኑፋቄውን ቀጥሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፊል 2÷5-6 ላይ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ ዐሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኹን እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም” የሚለውን ቃል ይዞ በራሱ ለራሱ እንዲመች አድርጎ በመተርጎም ቃል በሥጋ አደረ ብሎ ኅድረትን ደግፎ ያስተምር ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ንስጥሮስ በውስጡ ብዙ ምንፍቅናዎችን የያዘ ትምህርት በዐደባባይ ያስተምር ነበር፡፡ ይህንን የክህደት ትምህርቱን የሰሙ ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜያት ተገቢውን መልስ እየሰጡ ይመክሩት ነበር፡፡ ለዚህ ለንስጥሮስ ክህደት ተገቢውን ምላሽ  ከሰጡት አባቶች መካከል በእስክንድርያ 24ኛ ፓትርያርክ የተሾመው ቅዱስ ቄርሎስ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይህ ታላቅ አባት የቃልና የሥጋን ተዋሕዶ በሚገባ ከምሳሌ ጋር በማስረዳት ውላጤ እና ኅድረት የሚሉትን የንስጥሮስ ክህደቶች በሚገባ አጋልጧል፡፡  የጌታን አምላክነት የድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት ነቅፎ ያስተምር የነበረው ንስጥሮስ በቅዱስ ቄርሎስ አፈጉባኤነት በተመራው ጉባኤ ኤፌሶን በ200 ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ተወግዞ ተለይቷል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ታላቁ አባት ቅዱስ ቄርሎስ ምሥጢረ ተዋሕዶን በጋለ ብረት መስሎ በሚገባ አስረድቷል፡፡ ብረት የሚስማማው ባህርይ እሳት ከሚስማማው ባህርይ ጋር ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ ብረት እና እሳት ሁለት የተለያዩ አካላት የተለያዩ ባሕርያት ናቸው፡፡ እሳት አንድ አካል ነው አንድ ባሕርይ ነው ብረትም እንዲሁ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፡፡ እሳትና ብረት የየራሳቸው የሆነ አካልና ባሕርይ አላቸው፡፡ በጊዜ ግለት ግን እሳት የብረትን ብረትም የእሳትን ባሕርይ ገንዘባቸው ያደርጋሉ፡፡ በጊዜ ግለት ጥቁር የነበረው ብረት የእሳትን ቀይነት፣ሙቀት፣ መልክእ ገንዘቡ አድርጎ ቀይ፣ሞቃት እንደሚሆን ሁሉ ጎንና ዳር የሌለው የማይጨበጠው ረቂቅ እሳትም ግዙፍ የሆነውን የብረት ቅርጽና ግዘፍነት ገንዘቡ አድርጎ የብረቱን ቅርጽ የብረቱን ግዘፍነት ይዞ ይገኛል፡፡ በዚህም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ይሆናል፡፡ የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶም እንደዚሁ ያለ ነው፡፡ መለኮት ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ መለኮት የሥጋን፣ ሥጋም የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ በማድረግ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ በማለት ለንስጥሮስ በዚህ ምሳሌ አስረድቷል፡፡ የንስጥሮስንም ምንፍቅና ለሁሉ አጋልጧል፡፡ በዚህም መሠረት የንስጥሮስ ክህደት ተወግዞ ተለይቷል፡፡ በዚህ ጉባኤም አባቶቻችን የጨመሩልን አንቀጸ ሃይማኖት “በአማን ወላዲተ አምላክ፤ በእውነት አምላክን የወለደች” የሚል ነው፡፡ ንስጥሮስ “ሕስወኬ ትሰመይ ቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ ወአማነ ትሰመይ  ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክዶ ነበርና ሊቃውንቱ እርሱን አውግዘው “በአማን ወላዲተ አምላክ፤ በእውነት አምላክን የወለደች” ናት በማለት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብለው አንቀጸ ሃይማኖት ጽፈውልናል፡፡ የዛሬ ቅብአት እምነትን የሚከተሉ ሰዎችም ከዚህ ከንስጥሮስ ምንፍቅና ጋር ኅብረት አላቸው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ለምትሉ ከመጽሐፋቸው ላይ ልውሰዳችሁ፡፡ ወልደ አብ ገጽ 127 ላይ  “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው” ብለው ያምናሉ፡፡ ስለዚህ መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ ከተፈጠረ በኋላ ድንግል ማርያም ወለደችው ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ድንግል ማርያም የወለደችው ፈጣሪን ሳይሆን ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ የተፈጠረን ሰው እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ ይቅር ይበለንና እንደዚህ ያለውን ክህደት ሲጽፉ እና ሲያስተምሩ ግን እንደ ንስጥሮስ በጉባኤ ስላልተለዩ ምናልባትም ትክክል ነን ከንስጥሮስ ክህደት እንለያለን ይሉን ይሆናል፡፡ ግን ማታለያ ካልሆነ በቀር ንስጥሮሳውያን እንደሆኑ በዚህ እንረዳለን፡፡ ንስጥሮስ በክህደቱ ተወግዞ ከተለየ በኋላ ላዕላይ ግብጽ ይኖር ነበር፡፡ በዚህ ኑፋቄውም ጸንቶ ስለነበር ቅዱስ ቄርሎስ ዝም ብሎ አልተወውም ነበር፡፡ ንስጥሮስ ካለበት ዘንድ ሄዶ ወንደሜ ጌታን አምላክ ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብለህ እመን አለው፡፡ ንስጥሮስ ግን እኔስ አንተ እንደምትለው አልልም ጌታን እሩቅ ብእሲ ድንግል ማርያምን ወላዲተ ሰብእ እላለሁ እንጅ በማለት አሻፈረኝ አለ፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም እመቤቴን ላዋርድ ብለህ እንዲህ እንዳልክና እኔንም አልታዘዝም እንዳልክ ላንተም አንደበትህ አይታዘዝልህ ብሎ ረገመው፡፡ በዚህም የተነሣ ምላሱ ተጎልጉሎ ከደረቱ ተንጠልጥሎ  ደምና መግል እየተፋ በከፋ አሟሟት ሞቷል፡፡ አሁንም በዚህ የምንፍቅና ባሕር ውስጥ በመዋኘት ላይ ያላችሁ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች ከዚህ ክህደታችሁ ተመልሳችሁ በጎላ የተረዳች የአባቶቻችንን እምነት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን እንድትይዙ መልእክት አስተላልፋለሁ፡፡ አሁንም ለዚህ መልእክቴ ስድብ እንደምትመልሱልኝ አውቃለሁ ግን ቄርሎስን እስክንመስለው ድረስ አላቆምም፡፡ ንስጥሮስ በከፋ አሟሟት ሲሞት ተመልክቻለሁና እናንተም እንደዛ ባለ ሁኔታ ስትሞቱ መመልከት አልፈልግምና ከእናንተ ሞት ይልቅ የእኔ መሰደብ እጅግ ይሻላልና፡፡


Friday, July 15, 2016

“ብራና እና ጥንታዊነት”


© መልካሙ በየነ
ሐምሌ 08/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በመጀመሪያ ሰላምታየን ላደርሳችሁ እወዳለሁ፡፡ አገራችን ማኅበራዊ መገናኛዎች ለፍርድ ቀርበው እስራት ተወስኖባቸው እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ሐምሌ 7 ቀን ከሰዓት በኋላ በተደረገው ችሎት የማኅበራዊ መገናኛዎች ጠበቃ እጅጉን በመከራከር ከእስራቱ በዋስ እንዳስፈታቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን ወደፊት እንደአስፈላጊነቱ ሊታሠሩ እንደሚችሉ ጠበቃቸው አልሸሸገም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ከእስራት ተፈተዋል ከዘመዶቻችን ከወዳጆቻችን ጋር ለማገናኘት አብቅተውናል የተለመደ ሥራቸውንም በይፋ ጀምረዋል፡፡ እኛም ሥራችንን ጀመርንባቸው፡፡


እንግዲህ ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡ ዛሬ የምንመለከተው “ብራና እና ጥንታዊነት” የሚል ነው፡፡ አሁን ከዚህ ከወረቀት ዘመን ራቅ ላድርግና ወደ ጥንቱ የብራና ዘመን ልውሰዳችሁ፡፡ አባቶቻችን ይችን ጥንታዊ እምነታችንን ያቆዩልን ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምጸ አራዊቱን ግርማ ሌሊቱን ጸብአ አጋንንቱን ታግሰው በማስተማር እና ብራና ዳምጠው፣ ብርዕ ቀርጸው፣ ቀለም በጥብጠው ወዘተ መጻሕፍትን በመጻፍ ነው፡፡ በወቅቱ የወረቀት ፋብሪካ የለም የቀለም ማምረቻም መሣሪያ የለም ይህ ቢሆንም መጻሕፍትን ከመጻፍ አልቦዘኑም ነበር፡፡ ቀለም ሲያልቅባቸው ደማቸውን እንደቀለም እየተጠቀሙ ብራናውን አዘጋጅተው በዚያ ላይ ይጽፉ ነበር፡፡ ለዚህም ምስክር ይሆኑ ዘንድ በርካታ የብራና መጻሕፍት በተለያዩ ቦታዎች እናገኛለን፡፡ ዛሬ ቴክኖሎጅው ሲሻሻል ያንን በብራና ላይ ጽፈውት የነበረውን ትምህርት በወረቀት ላይ አሰፈሩት፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባው ወረቀቱ የተቀዳው ከብራናው መሆኑን ነው፡፡ ብራናው ሌላ ወረቀቱ ሌላ የሚናገሩ ከሆነ ግን ሌላ ችግር ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ ይህን ርእስ ለምን አነሣው እንዳትሉኝ የቅብአት እምነት ተከታዮች ሃይማኖተ አበው እዚህ ክፍል እዚህ ምእራፍ እዚህ ቁጥር ላይ እንዲህ ይላል ስንላቸው የብራናው እንዲህ ነው የሚል እያሉ ሰውን ለማደናገር ይፈልጋሉ እና ይህን ርእስ ማንሣት አስፈለገኝ፡፡ እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ወረቀቱ የያዘው ብራናው የያዘውን ነው፡፡ ምክንያቱም ከብራናው ወደ ወረቀቱ ተገለበጠ እንጅ አልተቀነሰም አልተጨመረም፡፡ ልብ በሉ የብራናው ጽሑፍ ጥንታዊነቱን ሊያሳይ የሚችል አይደለም፡፡ የወረቀት መጻሕፍትን ጥንታውያን አይደሉም ልንላቸው አንችልም ምክንያቱም ወረቀቱ ጥንታዊ አይደለም እንጅ የያዘው ትምህርት ጥንታዊ ነውና፡፡ የብራና መጻሕፍት በሙሉ ጥንታውያን ናቸው ማለት አይቻልም ምክንያቱም በብራና መጻፍ ጥንት ተጀመረ እንጅ የሚይዙት ቃል በሙሉ ጥንታዊ ትምህርተ እምነት ነው ሊባል አይችልምና፡፡ መግባባት የሚገባን ጉዳይ አለ እርሱም ብራና እንዴት ይዘጋጃል ከምን ይዘጋጃል የሚለው ነጥብ ላይ ነው፡፡ የብራና አዘገጃጀት በብራና ላይ መጻፍ (የቁም ጽሕፈት የምንለው) ዛሬም ድረስ እንዳለ እናውቃለን፡፡ ፍየሎች እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገጽ እስካልጠፉ ድረስ ብራና ዝግጅት ይኖራል በዚያ ላይም መጻፍ እንደዚያው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጥንት የነበሩት ፍየሎች ዛሬም አሉ ከነቆዳቸው ከነሥጋቸው ማለት ነው፡፡ ድሮ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ብራናው ይዘጋጃል ቀለሙ ይበጠበጣል ብርዑ ይቀረጻል ከዚያም በተዘጋጀው ብራና ላይ የምንፈልገውን ነገር እንጽፍበታለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብራና ስለሆነ ብቻ ጥንታዊ ነው ልንለው የምንችልበት ምንም ምክንያት የለንም፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ እነርሱ የሚጠቅሱት የብራና መጽሐፍ የሚገኘው ደብረወርቅ እና ጎንቻ ሲሶ እነሴ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ የደብረ ወርቅ ሰው ቆዳን እንዴት እንደሚሠሩት እንዴት ለአገልግሎት እንደሚያበቁት ብታዩ ብራና ማውጣት ቀላላቸው እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፡፡ የወንዙን ስም ባላውቀውም ከከተማው ወጥታችሁ ወደ ሞጣ መስመር ስትጓዙ አንድ ድልድይ ታገኛላችሁ፡፡ ያንን ወንዝ ተከትላችሁ ብትሄዱ ሜዳው በሙሉ ቆዳ ተወጥሮበት ታገኛላችሁ ይህ የበሬ እና የላም ቆዳ ነው፡፡ ይህን በውኃ የተነከረ ቆዳ አልፍተው ወጥረው በጸሐይ አድርቀው ፍቀው ጉሎ ቀብተው ለአገልግሎት ያበቁታል፡፡ ያንን በዓይናችሁ ትመለከታላችሁ ያ ካልተሳካላችሁ ደግሞ ከደብረ ወርቅ መናሀሪያ የሚወጡትን መኪኖች ተመልከቱ ጭነው የሚወጡት ብፌ አይደለም ወይም ሶፋ አይደለም ቆዳ ነው፡፡ ታዲያ ይህን እንዲህ አድርገው አሳምረው የሚሰሩ ደብረወርቆች ትንሿን የፍየል ቆዳ ብራና ማድረግ እንዴት ይሳናቸዋል? ስለዚህ ዛሬም ድረስ በብራና ላይ ይጽፋሉ ይደጉሳሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ብራና ላይ የተጻፈ ጽሑፍ ሁሉ ጥንታዊ ነው ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል፡፡ ትክክለኛ የብራና መጻሕፍት እኮ በየገዳማቱና በየአድባራቱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የቅብአት መናፍቃኑ የሚጠቅሱት ግን ደብረወርቅና ጎንቻ ብቻ የሚገኙ መሆናቸው መጻሕፍቱ ችግር እንዳለባቸው ያመላክታል፡፡ በወረቀት የጻፉትን “ወልደ አብ” የተሰኘ የምንፍቅና መጽሐፋቸውን በብራና መጻፍ አይችሉምን? በጣም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ብራና የምትሉትን ነገር ቆም ብላችሁ ብታስቡት ይሻላል፡፡ የብራና መጻሕፍትን ይነቅፋል እንደሚሉኝ አልጠራጠርም፡፡ እኔ ግን ወረቀትም ሆነ ብራና የያዘው ትምህርት የተዋሕዶን ነገር የማያስረዳ ከሆነ እነቅፈዋለሁ ምክንያቱም ትምህርቱ እንጅ ቆዳው ወይም ወረቀቱ አይደለምና የሚነቀፈው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሊቀሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ ቃለ ጽድቁ ለአብ የሚለውን መጽሐፍ በማዘጋጀታቸውና ኑፋቄያቸውን በማጋለጣቸው አንድ ማንም የማያውቀውን እነርሱ ብቻ የሚያውቁትን የብራና መጽሐፍ ጠቅሰዋል ምእራፍና ቁጥር የሚባል ነገር የለም ብራናው እንዲህ እንዲል ብቻ ነው የሚሉት፡፡ ፎቶውን ተመልከቱት ይህ የቄርሎስ ድርሳን የሚሉት ከየት የተገኘ እንደሆነ ከእነርሱ ውጭ ማንም አያውቀውም፡፡

Friday, July 8, 2016

የተዋሕዶ መደምደሚያ ቅብአት ነው?

©በመልካሙ በየነ
ሐምሌ 1/2008 .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ፣


የቅብአትን ኑፋቄ ባለፉት በርካታ ጽሑፎቼ መጽሐፋቸውን መነሻ በማድረግ ሳሳውቅ ቆይቻለሁ። አሁን መጽሐፋቸው አደባባይ ላይ እየተሸጠ እያለ እንኳ "ጎጃምን ትልቁን አገር አታሰድብ ቅብአት የሚባል ነገር የለም" የሚሉ አልታጡም። እነዚህ ሰዎች መጀመሪያ ሀገር እና ክፍለ ሀገርም የማያውቁ መሆናቸው ግልጽ ነው። ምክንያቱም ሀገር ብለን ኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር ብለን ጎጃም እንላለን እንጅ "ትልቅ ሀገር ጎጃም" አንልም። ሲቀጥል የሀገር ትልቅነት በምን ይለካል? ለሚለው ጥያቄም በቂ መልስ ማቅረብ አይችሉም። ጎጃም ትልቅ እንደሆነ እናውቃለን ሆኖም ግን ከትልቁ ዝሆን ላይ ትንኝ እንደማትታጣ መረዳት አያዳግተንም። ስለዚህ "ቅብአት የለም" የሚለው የአንዳንድ ሰዎች አስተያየት (አቡነ ማርቆስን ጨምሮ ማለቴ ነው) ተቀባይነት የለውም። ድሮ አቡነ ዘካርያስ ይህንነ ሲሉን ነበር ያን ጊዜ እውነታቸውን ይሆን? ብለን ነበር። ምክንያቱም ከወሬ ያለፈ ተጨባጭ ማስረጃ ስላልነበረን። ዛሬ ግን ሽህ ሰው "ቅብአት የለም" ቢለኝ ሺህ ውሸታም እላቸዋለሁ እንጅ እንደ ድሮው እውነት ይሆን? ብየ አልጠራጠርም። ምክንያቱም የቅብአት እምነት ሊቅ የሚባለው "ገብረ መድኅን" ወይም "ሄኖክ" የጻፈልን "ወልደ አብ" የተባለ መጽሐፍ ማስረጃችን ነውና። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ማንም ጆሮ የለውም። እልፍ ፐርሰንት ያህል እተማመናለሁ ቅብአት አለ ያውም ከቤታችን ከቤተክርስቲያናችን። በዚህ ጉዳይ ይህን ያህል ካልኩ ወደ ዋናው ጉዳየ ልግባ። የቅብአት እምነት ተከታዮች "ለተዋሕዶ መደምደሚያ ቅብአት ነው" ይላሉ። ይህን እስኪ ከራሳቸው መጽሐፍ እንመልከተው።
ወልደ አብ ገጽ 219 ላይ “ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ፡፡ ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ፡፡ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም፡፡ ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪” ይላል። ይህን ጉዳይ "የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች ክፍል 8" ላይ በዝርዝር ተመልክተነዋል። እዚህ ላይ መድገም ያስፈለገው ይህ አገላለጽ "ለተዋሕዶ መደምደሚያ ቅብአት ነው" የሚል አንድምታ ስላለው ነው። ምክንያቱም እርስ በርሱ የሚጋጭ የሚመስል ሃሳብ ይዟል ነገር ግን አይጋጭም ይላሉ የቅብአት እምነት ተከታዮች። ስለዚህ የማይጋጭ ሃሳብ ከሆነ ሊስማማ የሚችለው እንደሚከተለው ይሆናል። መጀመሪያ ሁለት የተዋሕዶ ሂደቶች ይከወናሉ። የመጀመሪው"ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ"የሚለው መለኮት ከሥጋ ጋር ያደረገው ተዋሕዶ ነው። በዚህ ተዋሕዶ ላይ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሐደ እንጅ ሥጋ ከመለኮት ጋር አልተዋሐደም።በዚህ ተዋሕዶ ሥጋ የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጎ በቃል መጠሪያ ተጠራ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ተባለ ማለት ነው። የሚገርማችሁ እስከዚህ ድረስ መለኮት የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አላደረገም በሥጋ ስምም አልተጠራም። ስለዚህ ሙሉ ተዋሕዶ ይደረግ ዘንድ ሥጋ ከመለኮት ጋር መዋሐድ አለበት። ይህኛው ቀጣዩ ተዋሕዶ ነው። ሁለት ነጥላ ተዋሕዶዎች ናቸው እንግዲህ አንድ ሙሉ ተዋሕዶን የሚፈጥሩት። በነገራችን ላይ ይህን የምላችሁ እነርሱ ተዋሐደ እያሉ ስለጻፉት እንጅ እንደ እኔ ይኼ ተዋሕዶ አይባልም። የኅድረት ተዋሕዶ ሊሆን እንደሚችል ብቻ ነው የምገምተው። ስለዚህ ኅድረት ያለበት ተዋሕዶ እንደሆነ እረዳለሁ። ቀጣዩ ተዋሕዶ የሥጋ ከመለኮት ጋር መዋሐድ ነው። "ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ" ይላል ሥጋ ከመለኮት ጋር እንደተዋሐደ ለማጠየቅ። ቅድም ልጅነት አገኘ ቃለአብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ያሉት ሥጋ አሁን ልጅነትን የሚሻ ሆነ ምክንያቱም መለኮት ቢዋሐደው ልጅነት አገኝ እንጅ ሥጋ ከመለኮት ጋር ስላልተዋሐደ የሚቀረው ልጅነት አለ። ስለዚህ ይህን ሙሉ ልጅነት ያገኝ ዘንድ ሥጋ ከመለኮት ጋር መዋሐድ ያስፈልገዋል ማለት ነው። እንግዲህ እነዚህ የተዋሕዶ ሁለት ሂደቶች ከተጠናቀቂ በኋላ ይፈጠራል። ወልደ አብ ገጽ 131 "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል። ለሊሁ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ እምብእሲት እን ቅዱስ ቂርሎስ ሃ አ ስምዓት ክ፪ ቁ፲፱ ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው። መለኮት በሥጋ ርስት ፍጡር ነው። ሥጋ ሲፈጠር መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ አብሮ ተፈጠረ ካላሉ እንደ ንስጥሮስ ፪ አካል ማድረግ ኃደረበብእሲ ማለት ነውና ክህደት ነው" አሁን መለኮት ከሥጋ ጋር ሥጋም ከመለኮት ጋር ተዋሕዶ ተፈጥሯል። ማን ፈጠረው አትሉኝም መቸም ምክንያቱም አምላክ ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጥሯልና። መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ ካላሉ ክህደት ነው ብለዋል እኮ ደግሞ። እንግዲህ ይህ ተዋሕዶ ከተከናወነ በኋላ የተፈጠረው አካል እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ ያዝዝ ይገዛ ዘንድ በቅብአት መክበር ያስፈልገዋል። ይህንንም እንዲህ ያስረዳሉ "ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም" ስለዚህ ከተዋሕዶ በኋላ ቅብአት መደምደሚያ ሆኖ እናገኘዋለን። አንድ ያልተረዱት ነገር አለ እግዚአብሔር በመለካት በመፍጠር አንድ ነው። ይህን ካመኑ ደግሞ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ ማለት ምን ማለት ነው? ወይስ ደግሞ እኛን ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ አጡለት ስለሚሉን ቦታ ለመፈለግ ይሆን? የወልድ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሐደ አንድ ቦታ ለወልድ ተገኘለት። ቀጣይ መለኮት የተዋሐደውን ሥጋ አብ ፈጠረው ለአብ ሌላ ቦታ ተሰጠው ቀጣይ ይህን ከመለኮት ጋር ተዋሕዶ የተፈጠረውን ሥጋ መንፈስ ቅዱስ አከበረው ለመንፈስ ቅዱስም ቦታ ሰጡት።
አምላከ ቅዱሳብ ይቅር ይበለን!!!

"የቅብአት ምንፍቅና በአደባባይ"

©በመልካሙ በየነ
ሰኔ 30/2008 .
ደብረማርቆስ ኢትዮጵያ፤
"የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች" በሚል ርእስ መነሻነት እስከ ክፍል 10 ድረስ እንደተማማርን ታስታውሳላችሁ። ዛሬም በዚህ ክፍል ምንፍቅናቸው ምን ላይ እንደሆነ በግልጽ እንመለከታለን። እዚህ ላይ ግን ልብ ማለት የሚገባን የምጽፈው ነገር ከራሴ አንቅቸ እንዳልሆነ ነው። የምጽፍላችሁ ነገር ራሳቸው ካሳተሙት የክህደት መጽሐፍ ሲሆን የሚጠቅሱትንም ጥቅስ ትክክለኛውን እና ሙሉውን በግእዝም በአማርኛም እጽፍላችኋለሁ።
ወልደ አብ ገጽ 131 "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል። ለሊሁ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ እምብእሲት እን ቅዱስ ቂርሎስ ሃ አ ስምዓት ክ፪ ቁ፲፱ ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው። መለኮት በሥጋ ርስት ፍጡር ነው። ሥጋ ሲፈጠር መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ አብሮ ተፈጠረ ካላሉ እንደ ንስጥሮስ ፪ አካል ማድረግ ኃደረበብእሲ ማለት ነውና ክህደት ነው" ይላል።
አሁን ይህን ድፍረትና ክህደት አንድ በአንድ እንመልከተው። "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል" ይላሉ ሲጀምሩ። በመጀመሪያ "ወልድ" የሚለው ስም ሥጋን ሲለብስ የጠራንበት ሳይሆን ጥንት ከሌለው ዘመን ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል በጥበበ እግዚአብሔር ከአብ ያለእናት በተወለደ ጊዜ ነው። ሰለዚህ ይህ የመወለድ ግብር ያለው "ወልድ" ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አይበልጥም አያንስምም እኩል ነው እንጅ። ይህ ከሥላሴ አንድነት ለቅጽበት ያህል እንኳ ያልተለየው "ወልድ" ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋንከነፍሳ ነፍስን ነሥቶ በተዋሕዶ የተወለደው ከአምላክነት ክብሩ ዝቅ ለማለት አይደለም። መለኮት ከሥጋ ጋር ሥጋም ከመለኮት ጋር በተዋሐደ ጊዜ ሥጋ አምላክ ሆነ አምላክም ሰው ሆነ። አሁን ከተዋሕዶ በኋላ ሥጋንና መለኮትን መከፋፈል አንችልም ምክንያቱም "አምላክ ወሰብእ" የሚባል ነውና። ቅብዓቶች እዚህ ላይ የሠሩት ስህተት ከተዋሕዶ በኋላ መለኮትን ከሥጋ ከፍለው "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል" ይላሉ። ቅዱስ ቄርሎስ የመሰለውን የጋለ ብረት አስታውሱት ብረቱ ከጋለ በኋላ እሳት ይባላልን? ወይስ ደግሞ ብረት ብቻ ይባላል? አይባልም። ትክክለኛ ስሙ "የጋለ ብረት" የሚለው ነው። ብረት ወይም እሳት ልንለው የሚገባ ከመጋሉ በፊት ነው እንጅ ከጋለ በኋላስ "የጋለ ብረት" እንለዋለን እንጅ "ብረት" ወይም "እሳት" ብቻ ብለን እንደማንጠራው የታወቀ ነው። የመለኮት እና የሥጋም እንዲሁ ነው። ከተዋሕዶ በፊት "ወልድን ፈጣሪ" ብቻ እንለዋለን "ሥጋንም ፍጡር ብቻ" እንለዋለን። ከተዋሕዶ በኋላ ግን የቃልን ገንዘብ ሥጋ የሥጋንም ገንዘብ ቃል ገንዘቡ ስላደረገ የብቻ መጠሪያ አይኖራቸውም። ስለዚህም "ክርስቶስ" እንለዋለን ከሁለት አካላት እንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ያለው "አምላክ ወሰብእ" ነውና። ልብ በሉ "ክርስቶስ" የሚለው ሥም ከተዋሕዶ በኋላ የተጠራበት ነው። ይህም ማለት "ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው" ነው ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ ተዋሕዶ ከፍለን ሥጋን ለብቻው መለኮትንም ለብቻው ልናደርገው እንዴት እንደፍራለን።
"ለሊሁ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ እምብእሲት እን ቅዱስ ቂርሎስ ሃ አ ስምዓት ክ፪ ቁ፲፱ ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው" ይላሉ። ሁልጊዜ የሚገርሙኝ ማስረጃ ብለው የሚጠቅሱት ነገር ከሚናገሩት ጽንሰ ሃሳብ ጋር በምንም የሚገናኝ አይደለም። በመጀመሪያ ግን የፊደል ግድፈትን እንኳ ማጣራት ይገባቸው እንደ ነበር እረዳለው። "ቄርሎስ" ን "ቂርሎስ" ብለው የጻፉት ምናልባትም ሃይማኖተ አበውን ገልጠን ስንመለከት እንዳናገኘው ፈልገው ይሆናል። ከየት ቆርጠው እንደወሰዱት ልብ ብላችሁ ተመልከቱት የጠቀሱትን የቄርሎስ ስምዓት ሙሉውን ግዕዝም በአማርኛም አንብበት ከዚህ በታች ቀርቦላችኋል።
ቄርሎስ ሃ አ ስምዓት ክ፪ ቁ፲፱ "ወካዕበ ይቤ ተሰምየ ገብረ ወውእቱ እግዘኣ ኩሉ ከመ አምላክ ለሊሁ በግዕ ወለሊሁ ካህን ዓዲ ኅቡረ እስመ ውእቱ ሦዐ ርእሶ ባህቲቱ በከመ ንቤ ቅድመ አዕረገ ሥጋሁ ባህቲቱ በፈቃዱ መሥዋእተ ውኩፈ ወዕጣነ ምዑዘ ለእግዚአብሔር አቡሁ በእንቲአነ ለሊሁ ፍጡር ወለሊሁ ፈጣሪ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ በሥጋ እምብእሲት ወካዕበ ይቤ ዝንቱ ዓምደ ሃይማኖት በእንቲአሁ ትብልኑ እስመ ዘተፀንሰ ካልእ ውእቱ ዘምስለ ፈጣሪ በከመ በውስተ መለኮት ወትስብእት ወፈጣሪ ወፍጡር ፍልጣን ሐሰ ለነ እምዝንቱ ንባብ ሙሱን ወርኩስ"
አማርኛውንም እነሆ ሳልጨምር ሳልቀንስ:
"ዳግመኛም አገለገለ ተባለ ግን እሱ አምላክ እንደመሆኑ ሁሉን ፈጥሮ የሚገዛ ነው እሱ መሥዋእት ነው። ወዲህም ከመሥዋእቱ የማይለይ ካህን ነው እሱ ብቻ ሥጋውን በፈቃዱ የተወደደ መሥዋእት የተወደደ ዕጣን አድርጎ ስለእኛ ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር አቀረበ ብለን አስቀድመን እንደተናገርን እሱ ራሱን ብቻ ሠውቶአልና እሱ ሰው ነው እሱ አምላክ ነው አምላክ እግዚአብሔር ሰለሆነ ፈጣሪ እንለዋለን ወዲህም ከድንግል በሥጋ ስለተወለደ ሰው እንለዋለን ዳግመኛ ይህ ዓምደ ሃይማኖት ቅዱስ ቄርሎስ ስለ እሱ ስትናገሩ በመለኮትና በትስብእት በፈጣሪና በፍጡር መካከል መከፋፈል እንዳለ አድርጋችሁ የተፀነሰው ከፈጣሪ ጋር ያለ ሌላ ነው ትላላችሁን ሌላ አይደለም እኛ ግን እንዲህ ያለ የተጠላ የተነቀፈ አነጋገር ልንናገር አይገባንም አለ" ብሎ ትምህርታቸውን ያወግዛል። ከተዋሕዶ በኋላ በሥጋና በመለኮት መካከል መከፋፈል እንደሌለ ሰው ሲሆን አምላክ አምላክ ሲሆን ሰው ነው ብሎ ትምህርተ ተዋሕዶን በጎላ በተረዳ ነገር ነገረን እንጅ ቅብአቶች እንደሚሉት "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል" አላለንም። ይህ ደግሞ ግልጽና ግልጽ አነጋገር ነው እንዲያውም እንዲህ የሚሉትን አወገዛቸው እኮ። ከተዋሕዶ በኋላ ሥጋና መለኮትን ይከፍሉና አሁንም "ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው" ብለው ይደመድማሉ። ከዚህ ቀጥለው የሚጽፉት ደግሞ በክርስትናዋ ዓለምን ከምታስደንቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖር ሰው የማይጠበቅ ከባድ ክህደት ነው። ይህም እንዲህ ይላል "መለኮት በሥጋ ርስት ፍጡር ነው። ሥጋ ሲፈጠር መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ አብሮ ተፈጠረ ካላሉ እንደ ንስጥሮስ ፪ አካል ማድረግ ኃደረበብእሲ ማለት ነውና ክህደት ነው" ብለው ለክህደታቸው ሌላ ክህደትን ይሹለታል። መጀመሪያ "ኃደረበብእሲ" የሚለውን ጸሐፊዋን "ኃደረ በብእሲ" ብላ እንድታስተካክለው አሳስቧት። ይህን ክህደት ሳይ ዛሬስ ምነው ንስጥሮስ ባየ ኖሮ አልኩ ለራሴ። ተመልከቱት የምንፍቅናቸውን ሂደት መጀመሪያ መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሐደ እዚህ ውህደት ላይ ሁለት ትልልቅ ሂደቶች አሉ። እነርሱን በሌላ ጊዜ እናያቸዋለን። ከዚያ ሂደት በኋላ ሙሉ ተዋሕዶ ይደረጋል። ከዚያ ያ ከመለኮት ጋር የተዋሐደውን ሥጋ ይፈጥረዋል። ማን እንደሚፈጥረው ግን እንጃ። ምክንያቱም መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ ሊፈጠር ነውና ሌላ ፈጣሪን ይሻል ማለት ነው። ከዚያ ማን እንደሚፈጥረው ባይታወቅም መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዳ ይፈጠራል አሉ። ከዚህ በኋላ ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ፍጡር የሆነ መለኮት አገኙ ማለት ነው። ይህ ፍጡር የሆነ መለኮት ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ እኩል እንዲገዛ እኩል እንዲስተካከል ቅብአት አስፈለገው። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ቅብአት የሚያስፈልገው። አያችሁ የክህደታቸውን ሰንሰለት። ስለ እውነት እንዲህ ያለውን ምንፍቅና ምን ሲሉ ጀመሩት ይሆን ግን። ንስጥሮስ ፪ ግብር ያለ መለኮት ከሥጋ ጋር ሳይዋሐድ ተፈጠረ ስላለ ነው እንዴ? ምነው ንስጥሮስን ሆናችሁ የንስጥሮስ ክህደት ጠፋችሁ። በእርግጥ የእናንተ ደግሞ ከንስጥሮስም ከአርዮስም የተጨመቀ ክህደት ነው ያፈለቃችሁት። በእውነት የትኛው ሊቅ የትኛው መጽሐፍ ነው "መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ ተፈጠረ" የሚል? መቸም አሁንም ያላነበባችሁትን መጽሐፍ ትጠቅሱት ይሆናል። የምትጠቅሱትን መጽሐፍ ቢያንስ ማወቅ ያስፈልጋችኋል። ለክህደታችሁ ግን እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ ወላዲተ አምላክ እመ ብርሃን ድንግል ማርያም በምልጃዋ ትጠብቃችሁ።

Wednesday, July 6, 2016

“ጵጵስና ሹሙኝ”

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 29/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በቤተክርስቲያኛችን የማዕረግ ደረጃ ጵጵስና ትልቁ ነው፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ወይም እረኞቻችን ምን ዓይነት ምግባር እና ሃይማኖት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጽፈውልናል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሥልጣን ሹመት የለም ምክንያቱም እረኛ ጠባቂ ልንሆን እንጅ ልንገዛቸው አልተመረጥንምና እያሉ ራሳቸውን በትህትና ይገዙ ነበር፡፡ ቀደምቱማ ለቀሚሳቸው ኪስ የለውም ነበር፤ ቀደምቱማ በእጃቸው ከመስቀል ውጭ አይጨብጡም ነበር፤ ቀደምቱማ ለእግራቸው ጫማ አይሉም ነበር፤ ቀደምቱማ ለጉዟቸው አውሮፕላን መኪና እና ባቡር አይሉም ነበር ሲያሻቸው ደመና ጠቅሰው ሲያሻቸው ደግሞ እግዚአብሔር በፈጠረላቸው እግራቸው ይሄዳሉና፤ ቀደምቱማ ለእግዚአብሔር ብቻ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ነበሩ፤ ቀደምቱማ ብህትውናን ገንዘባቸው ያደረጉ ነበሩ፤ ቀድምቱማ አስኬማቸውን አክሊለ ሶክ ነው ይሉ ነበር፤ ቀደምቱማ ለሐገር ለወገን ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ይሰጡ ነበር፤ ቀደምቱማ ይመክሩ ያስተምሩ ነበር፤ ቀደምቱማ ለእምነታቸው በመጋዝ ይሰነጠቁ ነበር፤ ቀደምቱማ ለማዕረጉ ብቁ አይደለሁም ይሉ ነበር፤ ቀደምቱማ በመመረጣቸው ያለቅሱ ያነቡ ነበር፤ ቀደምቱማ መልካም እረኛ የምሆነው እንዴት ነው ብለው ይጨነቁ ነበር ቀ…ደ…ም…ቱ…ማ…!...!...!
ዛሬ ታሪኩ ሁሉ ተለውጧል፡፡ የቀደምት አባቶቻችን ለዛቸው ጣዕማቸው ፍቅራቸው ሊገባንና ልንቀምሰው አልቻልንም፡፡ የዛሬዎቹ ደግሞ እጅግ ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ የዛሬዎቹማ ለቀሚሳቸው ሠላሳ ኪስ ያላቸው ናቸው፡፡ ኪሶቻቸው ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ጭምር ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት በማይጠረቃ ኪሳቸው ለማጠራቀም ጵጵስና ካልተሾምሁ አለቀላችሁ እያሉ የሚደነፉ ናቸው፡፡ የዛሬዎቹማ በእጃቸው መስቀል አይጨብጡም የሚጨብጡት ሌላ ነገር አላቸው፡፡ ሲፈልጉ የመንግሥትን እጅ ይጨብጣሉ፣ ሲፈልጉ የመናፍቃኑን እጅ ይጨብጣሉ፣ ሲፈልጉም የዘራፊዎችን እጅ ይጨብጣሉ፡፡ ዛሬ የሰማነው ነገር እሱ ነው መንግሥት እገሌ ጵጵስና ካልተሾመ ሌላ ሾማችሁ ብትልኩልን አንቀበለውም ብሎ ደብዳቤ እያዘነበ ነው፡፡ ታዲያ የዚች ቤተክርስቲያን መሪዎቿ የመንግሥት አካላት ሲሆኑ ዝም ልንል ይገባናልን፡፡ የዛሬዎቹማ ለእግራቸው ጫማ ብቻ ሳይሆን የወርቅ ጫማም ቢሆን ይመርጣሉ ምክንያቱም ገንዘብ አላቸዋ፡፡ እነርሱ የመዘበሩት የቤተክርስቲያን ገንዘብ እንኳን ለእነርሱ እግር ብቻ ለዘመዶቻቸውም ሁሉ የወርቅ ጫማ ይገዛ አይደል እንዴ፡፡ የዛሬዎቹማ ለጉዟቸው አውሮፕላን መኪና እና ባቡር ካልሆነ በእግራቸው አይሞክሯትም ደመና ጠቅሰው እንዳይሄዱ ደግሞ በየትኛው ቅድስና ደመና ይታዘዛል፡፡ በእግራቸውም እንዳይሞክሩት የምታውቁት ነው ዝሆን እስኪያካክሉ ድረስ በቤተ ክርስቲያኗ ገንዘብ ደልበዋል፡፡ እንግዲህ ከዚህ የበለጠ ለመድለብ ነው ጵጵስና ሹሙን እያሉ ራሳቸውን ለዚህ ማዕረግ ብቁ ያደረጉ የሚመስሉት፡፡ የዛሬዎቹማ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለገንዘብ እና ለቅምጦቻቸው ነው፡፡ የማይገባኝ ነገር አለ ሰው የፍትወቱን ጾር መታገስ ካልቻለ ለምን ህጋዊ ሆኖ አግብቶ ልጅ ወልዶ ልጆቹን እየሳመ አይኖርም፡፡ ምንኩስና እኮ ዝም ብሎ ተዘሎ የሚገባበት ባህር አይደለም፡፡ የምንኩስናውን ቆብ ከጫኑ በኋላ አግብተው በግልጽ መኖር ስለሚከብዳቸው ቤት ተከራይተው ያው ኃጢአቱን ይሠሩታል፡፡ በዚህ ግብራቸው ህጋዊ ባለትዳሮችን ሁሉ ትዳር የሚያፈርሱ በዝተዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ናቸው ዛሬ ጵጵስና ካልሾማችሁን እያሉ በገንዘብም በመንግሥትም በማስፈራራትም ተመዝግበው የምናገኛቸው፡፡ የዛሬዎቹማ ብህትውናን ገንዘባቸው ማድረግ ሳይሆን ብህትውና ምን እንደሆነም ትርጉሙ አይገባቸውም፡፡ መቼም አስኬማው ብቻ አያመነኩስም መነኩሴ ያስመስለን እንደሆነ እንጅ፡፡ ራሳችንን ማመንኮስ ካልቻልን ምን ዋጋ አለው “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ይሆንብናል ነገሩ፡፡ ለቅምጦቻቸው ያስቡ ወይስ ለእግዚአብሔር ቤት ያስቡ፣ በድብቅ ለወለዷቸው ልጆች ያስቡ ወይስ ለእኛ ያስቡ፡፡ አስቸጋሪ ነው ይህንን ጉድ ይዘው ዛሬ ጵጵስና ቢሾሙ “ጳጳሱ እንዲህ አደረጉ” እየተባለ ቤተክርስቲያናችን ባለቤት አልባ ስትሆን ምንኛ እንደሚጎዳን አስቡት፡፡ የዛሬዎቹማ አስኬማቸው አክሊለ ሶክ ሳይሆን አክሊለ ብር ሆኖላቸዋል፡፡ ጃንጥላ ዘቅዝቀው ብር ሲሰበስቡ ጃንጥላው ከሞላባቸው ቀጣይ ዘቅዝቀው የሚለምኑበት አስኬማቸው ነው፡፡ የእንጦንስና የመቃርስ አስኬማ የብር መለመኛ ሲሆን ምንኛ ያስለቅሳል፡፡ እነዚህ አስኬማ ዘቅዝቀው የሚለምኑት ሰዎች ዛሬ ጵጵስና ካልሾማችሁን አለቀላችሁ እያሉ እየዛቱ ነው፡፡ የዛሬዎቹማ ለሐገር ለወገን ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው የሚሰጡ ሳይሆኑ አንተን ለሞት አሳልፈው የሚሰጡ ጨካኞች ናቸው፡፡ ለጠላት አውጥተው የሚወረውሩ እረኛ ነን የሚሉ ግን እረኛ መሆን የማይችሉ ተኩላዎች ናቸው፡፡ እነዚህ በጥቂቱ ያልታመኑት ዛሬ በብዙው ላይ እንዴት ይታመናሉ ተብሎ ወደ ጵጵስና ይመጣሉ፡፡ የዛሬዎቹማ እንዳይመክሩ ራሳቸውንም መምከር የማይችሉ ናቸው እንዳያስተምሩም የተማሩት ነገር የላቸውም፡፡ ከማስተማር ይልቅ ብጥብጥና ንትርክ በመፍጠር ህዝቡን መከፋፈል የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ይሆናል፡፡ ሌሎች እንዳያስተምሩም መድረኩን አይሰጡም፡፡ የዛሬዎቹማ ለእምነታቸው በመጋዝ እስከመሰንጠቅ የሚያደርስ ጥንካሬ የላቸውም፡፡ እንዲያውም እነርሱ ራሳቸው በመጋዝ ይሰነጥቁ እንደሆነ እንጅ ለእምነታቸው ዋጋ የሚከፍሉ አይደሉም፡፡ ከመንግሥት ጎን ተለጥፈው የመንግሥትን ፖሊሲ አስፈጻሚዎች እስኪመስሉ ድረስ እንደዚያ ናቸው፡፡ እነዚህ ታዲያ ጵጵስና ቢመረጡ የመንግሥትን ወይስ የቤተክርስቲያንን ሥራ ነው የሚሠሩ፡፡ የዛሬዎቹማ ለማዕረጉ ብቁ ነን ምረጡን እያሉ እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ጀምረዋል፡፡ የራሳቸውን ደጋፊና አቀንቃኝም አደራጅተዋል፡፡ ከተመረጡ በኋላ ጵጵስናውን ከተሾሙ በኋላ እነዚህን ደጋፊዎች የየደብሩ አስተዳዳሪዎች ያደርጓቸው ይሆን? አምላክ ይወቀው ሁሉንም፡፡ የዛሬዎቹማ ባለመመረጣቸው ያለቅሱ ያነቡ እንደሆነ እንጅ በመመረጣቸው አያለቅሱም አያነቡም፡፡ በእውነት በኅሊና ላለ ሰው ራስን መምራት ራስን ማስተዳደር ራስን ለእግዚአብሔር መስጠት አስቸጋሪ በሆነበት በዚህ ዘመን ለሌሎች እረኛ መሆን አይከብድምን? በጣም ከባድ እኮ ነው፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ጥቂት የጥንት አባቶቻችንን ትህትና የተላበሱት ዛሬም ሲመረጡ እኔ ለእረኝነት ብቁ አይደለሁም የሚሉት፡፡ የዛሬዎቹማ መልካም እረኛ ለመሆን ሳይሆን ጥሩ አሳዳጅ ለመሆን ራሳቸውን ያዘጋጁ ናቸው፡፡ እነዚህን ይመስላሉ ጵጵስና ምረጡኝ እያሉ ቅስቀሳቸውን ያጠናከሩት፡፡ የ…ዛ…ሬ…ዎ…ቹ…ማ…!...!...!
እኔ በጣም የሚገርመኝ አንድ አሠራር አለ፡፡ መንግሥት በተለይ በጣም የሚጠቀምበት ነው፡፡ ቀበሌ ላይ ምዝበራ ፈጽሟል ተብሎ አቤቱታ የቀረበበት ሰው ለበለጠ ማዕረግ ታጭቶ የወረዳ አስተዳዳሪ አድርገው ከቀበሌው ያስወግዱታል፡፡ ወረዳ ላይም እንዲህ ያደረገውን ለዞን፤ዞን ላይ ያደረገውን ክልል ላይ፤ ክልል ላይም እንዲህ ያደረገውን ፌዴራል ላይ መሾም የተለመደ አሠራር ነው፡፡ አሁን አሁን በቤተክርስቲያናችንም ያሉ መሪዎች ይህንን አሠራር የያዙት ይመስላል፡፡ በዲቁና ያልታመነውን ለቅስና ያበቁታል፡፡ ለቅስና ያልበቃውን ሰው ለቁምስና ይሾሙታል፡፡ ለቁምስናም ብቁ ያልሆነን ሰው ለጵጵስና ያጩታል፡፡ ይህ አሠራር ለቤተ ክርስቲያናችን ከባድ አደጋ ነው ስለዚህ ሁላችንም ልንታገለው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እስኪ እነዚህን ለቤተክርስቲያናችን ለጵጵስና ማዕረግ ይበቃሉ ተብለው እጩ ሆነው የቀረቡትን ስም ዝርዝር ተመልክታችሁ ለሚመለከተው አካል እውነተኛውን መረጃ እንድታደርሱ ይሁን፡፡ ይህ ጉዳይ ለሁላችን ነውና፡፡ እዚህ ላይ ግን ይህን የጻፍኩት ዛሬ እውነተኛ እና ለሁሉ መካሪ አስተማሪ የሚሆን ለጵጵስና የሚበቃ የለም ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ አሉ እዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት መካከል ሊቃውንት አሉ፡፡ ግን የታወቁ አሉ ዓላማቸው ጵጵስናውን ተንተርሰው ቤተክርስቲያናችንን ለመናፍቃን አሳልፈው ለመስጠት ፈርመው የመጡ፡፡ ስለዚህ እነዚህን እጩዎች ተመልክተን ሁላችን አጥርተን እውነተኛውን መረጃ ለሚመለከተው አካል እንድናሳውቅ የበኩላችንን የቤተክርስቲያን ልጅነታችንንም እንድናስመሰክር ይህንን ጻፍኩት፡፡ የዕጩዎቹን ዝርዝር ከ “ሐራ ዘ ተዋሕዶ” ወስጀዋለሁ፡፡ አነሆ!!!
እስከ አኹን ድረስ በተለያዩ መንገዶች የተጠቆሙና በአብዛኛውም አስመራጭ ኮሚቴው ከብፁዓን አባቶች እንደተቀበላቸው የተገለጹ ቆሞሳትና መነኰሳት ስም ዝርዝር፤
1.  አባ ዘውዱ በየነ/የደብረ ብርሃን ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
2.  አባ ኃይለ ማርያም አረጋ/የደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ/
3.  አባ ያሬድ ምስጋናው/የእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት መጻሕፍትና ድጓ መምህር/
4.  አባ ገብረ ሥላሴ ጠባይ/የጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል አስተዳዳሪ/
5.  አባ ዘርዓ ዳዊት ኃይለ ሥላሴ/የመርካቶ ቅዱስ ራጉኤል አስተዳዳሪ/
6.  አባ ፍቅረ ማርያም ተስፋ ማርያም/የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አስተዳዳሪ/
7.  አባ ኃይለ ጊዮርጊስ/ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
8.  አባ ገብረ ጻድቅ ደበብ
9.  አባ ሣህለ ማርያም ገብረ አብ/አሜሪካ ‐ ቨርጂንያ)
10.         አባ ኃይለ ሚካኤል ወልደ ሐዋርያት/የደብረ ሊባኖስ ገዳም መጽሐፍ መምህር/
11.         ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለ ሃይማኖት/የናዝሬት ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ/
12.         አባ ኃይለ ሥላሴ ገብረ እግዚአብሔር/አሜሪካ ‐ ሎስ አንጀለስ/*
13.         አባ ፊልጶስ ከበደ /አሜሪካ ‐ቨርጂንያ/
14.         አባ ጽጌ ገነት ወልደ ኪዳን/አሜሪካ ‐ቨርጂንያ/
15.         ጸባቴ አባ የማነ ብርሃን(አዳሙ) ዓሥራት/አሜሪካ ‐ ቨርጂንያ/
16.         አባ ለይኩን ግፋ ወሰን/ደብረ ሊባኖስ ገዳም/
17.         አባ ፍቅረ ማርያም/ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም አስተዳዳሪ/
18.         ዬኔታ ጳውሎስ/ደብረ ሊባኖስ ገዳም/
19.         አባ ልሳነ ወርቅ ደለለኝ/ደብረ ጽጌ ገዳም/
20.         አባ መሐሪ ሀብቴ/አኵስም/
21.         አባ መርሐ ጥበብ ተሾመ/የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ገበዝ/
22.         አባ ኢሳይያስ/የዝቋላ ገዳም አበምኔት/
23.         አባ ማቴዎስ ከፍያለው/እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት/
24.         አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሓ/ጀርመን ‐ ሙኒክ/
25.         አባ ገብረ ሐና ታደሰ/ዱባይ/
26.         አባ ገብረ መድኅን ወልደ ሳሙኤል(ኳታር)*
27.         ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ/የጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ/
28.         አባ ኪዳነ ማርያም ደስታ/የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ቀሲስ/
29.         አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል/የጠቅላይ ጽ/ቤት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ዋና ሓላፊ/
30.         አባ ሞገስ ኃይለ ማርያም/የመናገሻ ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ/
31.         አባ ዘድንግል ኑርበገን/ፈረንሳይ/
32.         አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ/መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የገዳማት መምሪያ ዋና ሓላፊ/
33.         አባ ገብረ ጻድቅ ዐረፈ ዓይኔ/የአኵስም ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
34.         አባ መንግሥተ ኣብ ገብረ ሥላሴ/የቦሌ መድኃኔዓለም ካቴድራል አስተዳዳሪ/
35.         አባ ገብረ አድኃኔ ወልደ ማርያም/የደብረ መንከል ገዳም አስተዳዳሪ/
36.         አባ ጥዑመ ልሳን/ማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም አስተዳዳሪ/
37.         አባ ወልደ መድኅን ተክለ ብርሃን/እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት/
38.         አባ ዘተክለ ሃይማኖት/የደብረ ገሊላ ዐማኑኤል ካቴድራል ሰባኬ ወንጌል/
39.         አባ ወልደ ገብርኤል አማረ/ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የትርጓሜ መምህር/
40.         አባ ኢሳይያስ/ድሬዳዋ ቅድስት ሥላሴ
41.         ንቡረ እድ አባ ገብረ ሕይወት/ድሬዳዋ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ/
42.         ሊቀ ሊቃውንት አባ ዕዝራ ሐዲስ/ጎንደር መጻሕፍት መምህር/
43.         ሊቀ ጉባኤ አባ ገብረ ማርያም ገብረ መስቀል/ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም/
44.         አባ ኪዳነ ማርያም ሞላልኝ/ባሕር ዳር/
45.         አባ ብርሃነ መስቀል ደርበው/አዘዞ/
46.         አባ ቴዎድሮስ መስፍን/የሊቃውንት ጉባኤ አባል/
47.         አባ ወልደ ጊዮርጊስ ጸጋው/ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም መምህር/
48.         አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎሬዎስ/ጎፋ ጥበብ እድ ሥራ አስኪያጅ/
49.         አባ ኃይለ ማርያም/ሐዋሳ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
50.         አባ ተክለ ማርያም አምኜ/አስኮ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ/
51.         አባ ገብረ ሥላሴ ጎበና/ካርቱም ሀገረ ስብከት/
52.         አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ/ጀርመን ‐ በርሊን/
53.         አባ ኄኖክ ተክለ ጊዮርጊስ/መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል አለቃ/
54.         አባ ብንያም ከበደ/የሆሳዕና ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
55.         አባ ገብርኤል ወልደ ዮሐንስ
56.         አባ ሰይፈ ገብርኤል ኦብሰን/አሜሪካ ‐ ሲያትል/*
57.         አባ ሚካኤል ገብረ ማርያም/የዱራሜ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
58.         አባ ስብሐት ለአብ/ጀርመን/
59.         አባ ኢያሱ ገብረ አልፋ/የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ቅኔና መጻሕፍት መምህር/
60.         አባ ኃይለ ሚካኤል/መቐለ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ/
61.         አባ ኃይለ ሚካኤል ወልደ ሚካኤል/የደብረ ሊባኖስ ገዳም መምህር/
62.         አባ ፍቅረ ዮሐንስ ገብረ ሕይወት/ሐይቅ እስጢፋኖስ አበምኔት/
63.         አባ ኤልያስ ታደሰ/የደሴ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ/
64.         መልአከ ሰላም አባ ገብረ ኪዳን/አሜሪካ ‐ ቬጋስ/
65.         አባ ተክለ ሃይማኖት/ዋሽግንተን ዲሲ/
66.         አባ ፍቅረ ማርያም/ዋሽንግተን ዲሲ/
67.         አባ ገሪማ አያልቅበት/ዱባይ/
68.         አባ ብርሃነ መስቀል ዕንቁ
69.         አባ ወልደ ትንሣኤ አባተ/የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ/
70.         አባ ጌዴዎን/አሜሪካ ‐ ፍሎሪዳ/
71.         አባ ገብረ ኪዳን እጅጉ/
72.         አባ ቀለመ ወርቅ/ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም/
73.         አባ ወልደ ሐና ጸጋው/የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ/
74.         ሊቀ ጉባኤ አባ ሳሙኤል/ኢጣልያ/
75.         አባ ገብረ ማርያም/ዱባይ/
76.         አባ ገብረ ሥላሴ/ኢየሩሳሌም ገዳም/
77.         አባ ኃይለ ኢየሱስ ተመስገን/የሽሮ ሜዳ ቅድስት ሥላሴ አስተዳዳሪ/
78.         አባ ዮሐንስ ገብረ ሥላሴ/የወላይታ ሶዶ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
79.         አባ ሀብተ ማርያም ገብረ መስቀል/ሲዳማ ጌዴኦ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
80.         አባ ተክለ ማርያም ስሜ/ሐዋሳ/
81.         አባ ኃይለ መለኰት ተስፋ ማርያም/ጀርመን/
82.         አባ ኃይለ ሚካኤል/ኢየሩሳሌም ገዳም/
83.         አባ ኃይለ ጊዮርጊስ/ሲውዘርላንድ/
84.         አባ ላእከ ማርያም ገብረ ጊዮርጊስ/ዓዲ ግራት/
85.         አባ ገብረ ኪዳን/ማይጨው/
86.         አባ ዮሐንስ ከበደ/አየር ላንድ/
87.         አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን /እንጦጦ ቅድስት ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ/
88.         አባ ገብረ መድኅን/ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም መምህር/
89.         አባ ሳሙኤል ገላነው/የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ መምህር/*
90.         አባ ፈቃደ ሥላሴ/ዋሽንግተን ዲሲ/
91.         አባ ወልደ ማርያም አድማሱ/የደብረ ገዳም ጸባቴ/
92.         አባ ገብረ ሥላሴ በላይ/የደሴ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
93.         አባ ጽጌ ሥላሴ መዝገቡ/የደሴ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ/
94.         አባ ናትናኤል/የአየር ጤና ኪዳነ ምሕረት አስተዳዳሪ/
95.         አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ/የጠቅላይ ጽ/ቤት ውጭ ጉዳይ መምሪያ ሓላፊ/
96.         አባ መልአኩ/ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ/
97.         አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ/የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
98.         አባ ወልደ ዐማኑኤል/አሜሪካ/
99.         አባ ገብረ ጻድቅ/ምዕራብ ሸዋ/
100.       አባ ክንፈ ሚካኤል ልሳኑ/መንበረ ፓትርያርክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር/
101.       አባ ገብረ ማርያም/ደቡብ አፍሪካ/
102.       ዬኔታ ይባቤ በላይ/ምዕራብ ጎጃም የሐዲሳትና የቅኔ መምህር/
103.       ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ/መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል/
104.       አባ ዘርዓ ዳዊት/አሜሪካ ‐ ሚኒሶታ/
105.       አባ ወልደ ሰማያት/አሜሪካ ‐ ሲያትል/
106.       አባ እስጢፋኖስ/ዋሽንግተን ዲሲ/
107.       አባ ዘሚካኤል ደሬሳ/ዴንማርክ/
108.       አባ ዕንቁ ሥላሴ ተረፈ/መዝገበ ምሕረት ካራ ቆሬ ፋኑኤል አስተዳዳሪ/

የመመልመያው መሥፈርት የሚከተለው ነው፡፡
1.  በሥርዓተ ምንኵስና በታወቀ ገዳም በድንግልና መንኵሶ በክህነት ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግልና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዕጩ ኾኖ የተመረጠ፤
2.  ከመነኰሰበት ገዳም ስለ ምንኵስና ሕይወቱና ስለ ክህነቱ በቂ ማስረጃ ማቅረብ የሚችልና በመነኰሰበት ገዳም በቅንነትና በታማኝነት ቢያንስ ለአምስት ዓመት ያገለገለ መኾኑ የተረጋገጠለት፤
3.  ለሀገር ውስጥ አገልግሎት ወይም ኢትዮጵያውያን ለሚኖሩበት የውጭ ሀገረ ስብከት የሚሾም ከኾነ ዜግነቱና ትውልዱ ኢትዮጵያዊ የኾነ፤
4.  በውጭ ሀገር ለሚገኙና የውጭ ሀገር ዜጎች ከራሳቸው መካከል አባት መሾም እንዲቻል በቅድሚያ ከመካከላቸው ወደ አገር ቤት መጥተው አስፈላጊውን ትምህርት እንዲያገኙ፤ ሥርዓተ ገዳምና ሥርዓተ ምንኵስናን እንዲያውቁ ይደረጋል፤
5.  ኢትዮጵያውያን ያልኾኑ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሚኖሩበት የውጭ ሀገረ ስብከት የሚሾም ከኾነ፤ ዜግነቱ/ትውልዱ ኢትዮጵያዊ የኾነ ወይም ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገን የኾነ ወይም ኢትዮጵያዊ ኾኖ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት ተቀብሎ በሥርዓተ ክህነት መቀደስና ማስተማር የሚችል፤ እስከ ቆሞስነት ደረጃ የደረሰ በሚሾምበት ሥፍራ ለማገልገል የትምህርት ዝግጅትና የቋንቋ ችሎታና ብቃት ያለው፤
6.  የብሔረሰቡ ተወላጅ የኾነና በብሔረሰቡ ቋንቋ የማስተማር ችሎታ ያለው ወይም ተወላጅነቱ ሌላ ብሔረሰብ ኾኖ በተሠየመበት ሀገረ ስብከት በብሔረሰቡ ቋንቋ ማስተማር የሚችል፤ እንዲኹም በብሔረሰቡ ቋንቋ የሚናገር ከሌለ ቅዱስ ሲኖዶስ መንፈሳዊ ሕይወቱ የታመነበት አባት ይመድባል፡፡
7.  ለአንድ ቦታ አምስት ተጠቋሚዎች ለግምገማ የሚቀርቡ ሲኾን፤ ለምርጫ ቀርበው የሚወዳደሩት ግን ኹለት ናቸው፤
8.  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት/ነገረ መለኰት/ በቂ ዕውቀትና የማስተማር ችሎታ ያለው፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓተ ቀኖና ጠንቅቆ ያወቀ ለመኾኑ የተረጋገጠ ማስረጃ ያለው፤ ከቤተ ክርስቲያን የአብነት ት/ቤቶች ቢያንስ በአንድ ጉባኤ የተመረቀ፣ ወንበር ዘርግቶ ያስተማረ ቢኾን፤ ቢቻል ኹለገብ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ዘመናዊ ትምህርት ያለው ኾኖ ከመንፈሳዊው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቢያንስ ዲፕሎማ ያለው፤
9.  በመንፈሳዊ ሕይወቱና በግብረ ገብነቱ በአስተዳደር የሥራ ልምዱና በሥራ አመራር ችሎታና ብቃቱ በነበረበት አካባቢ/የሥራ ቦታ/ በሚገኙ ሊቀ ጳጳስ ሰብሳቢነት በካህናትና በምእመናን የተመሰከረለት ስለመኾኑ የተረጋገጠለት፤
10.         የምእመናንንና የካህናትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ችግር የመረዳትና የችግር አፈታት ልምድና ችሎታ ያለው፤
11.         የቤተ ክርስቲያኒቱ ቋንቋ የኾነውን ግእዝ በሚገባ የሚያውቅ ኾኖ ቢቻል ከዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አንዱን የሚያውቅ፤
12.         በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጽኑዕ የኾነ፤
13.         ሙሉ አካል ያለውና ጤንነቱ የተሟላ፤
14.         ዕድሜው ከ45 እስከ 60 ዓመት የኾነ፤
15.         ቢቻል የተሾመበትን ሀገረ ስብከት ቋንቋ የሚያውቅ፤
16.         አዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም እንደ ሌሎች አህጉረ ስብከት ጥቆማ የመስጠት ድርሻው የተጠበቀ ነው፤

17.         በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ለኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾሙ የተመረጡት ቆሞሳት፣ ከመሾማቸው በፊት ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንና የሥራ አመራር በአባቶች፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በምሁራን የሦስት ወራት ሥልጠና እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡