© መልካሙ በየነ
ሐምሌ 15/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ንስጥሮስ ሁለት መሠረታዊ ክህደቶች አሉበት፡፡
እነዚህም፡-
v ከተዋሕዶ
በኋላ መለያየት እንዳለ ያምን የነበረውን ዲያድርስ የሚባለውን መናፍቅ አስተምህሮ ያምን ነበር፡፡ የዚህ መሠረታዊው ክህደት ሁለት
ባሕርይ የሚል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከተዋሕዶ በኋላ አንዱን ወልደ ዳዊት አንዱን ደግሞ ወልደ እግዚአብሔር ነው በማለት ያምን
ነበር፡፡
v ሁለት
ባሕርይ የሚል እምነት ስለነበረው ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም የተወለደው ደግሞ ወልደ ዳዊት
ነው ብሎ ያምን ስለነበር እመቤታችን ክብር ይግባትና የወለደችልን እሩቅ ብእሲ ሰውን ነው እንጅ አምላክን አይደለም ይል ነበር፡፡
በዚህም ድንግል ማርያምን “ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክህደቱን ጀምሯል፡፡
ወልደ አብ ገጽ 127 |
እነዚህን ክህደቶቹን በአደባባይ በማስተማር እርሱን
መሰሎችን መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ለዚህ ክህደቱም ይደግፋል ብሎ ይጠቅስ የነበረው “ቃል ሥጋ ሆነ” ዮሐ1÷14 የሚለውን ቃል ነበር፡፡
ይህንን ቃል ለራሱ እንዲመች አድርጎ መለወጥ አለበት በማለት ኑፋቄውን ቀጥሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፊል 2÷5-6 ላይ “በክርስቶስ
ኢየሱስ የነበረ ይህ ዐሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኹን እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት
እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም” የሚለውን ቃል ይዞ በራሱ ለራሱ እንዲመች አድርጎ በመተርጎም ቃል በሥጋ አደረ ብሎ ኅድረትን ደግፎ
ያስተምር ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ንስጥሮስ በውስጡ ብዙ ምንፍቅናዎችን የያዘ ትምህርት በዐደባባይ ያስተምር ነበር፡፡ ይህንን የክህደት
ትምህርቱን የሰሙ ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜያት ተገቢውን መልስ እየሰጡ ይመክሩት ነበር፡፡ ለዚህ ለንስጥሮስ ክህደት ተገቢውን ምላሽ ከሰጡት አባቶች መካከል በእስክንድርያ 24ኛ ፓትርያርክ የተሾመው ቅዱስ ቄርሎስ
ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይህ ታላቅ አባት የቃልና የሥጋን ተዋሕዶ በሚገባ ከምሳሌ ጋር በማስረዳት ውላጤ እና ኅድረት የሚሉትን የንስጥሮስ
ክህደቶች በሚገባ አጋልጧል፡፡ የጌታን አምላክነት የድንግል ማርያምን
ወላዲተ አምላክነት ነቅፎ ያስተምር የነበረው ንስጥሮስ በቅዱስ ቄርሎስ አፈጉባኤነት በተመራው ጉባኤ ኤፌሶን በ200 ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን
ተወግዞ ተለይቷል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ታላቁ አባት ቅዱስ ቄርሎስ ምሥጢረ ተዋሕዶን በጋለ ብረት መስሎ በሚገባ አስረድቷል፡፡ ብረት
የሚስማማው ባህርይ እሳት ከሚስማማው ባህርይ ጋር ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ ብረት እና እሳት ሁለት የተለያዩ አካላት የተለያዩ ባሕርያት
ናቸው፡፡ እሳት አንድ አካል ነው አንድ ባሕርይ ነው ብረትም እንዲሁ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፡፡ እሳትና ብረት የየራሳቸው
የሆነ አካልና ባሕርይ አላቸው፡፡ በጊዜ ግለት ግን እሳት የብረትን ብረትም የእሳትን ባሕርይ ገንዘባቸው ያደርጋሉ፡፡ በጊዜ ግለት
ጥቁር የነበረው ብረት የእሳትን ቀይነት፣ሙቀት፣ መልክእ ገንዘቡ አድርጎ ቀይ፣ሞቃት እንደሚሆን ሁሉ ጎንና ዳር የሌለው የማይጨበጠው
ረቂቅ እሳትም ግዙፍ የሆነውን የብረት ቅርጽና ግዘፍነት ገንዘቡ አድርጎ የብረቱን ቅርጽ የብረቱን ግዘፍነት ይዞ ይገኛል፡፡ በዚህም
አንድ አካል አንድ ባሕርይ ይሆናል፡፡ የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶም እንደዚሁ ያለ ነው፡፡ መለኮት ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ መለኮት
የሥጋን፣ ሥጋም የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ በማድረግ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ በማለት ለንስጥሮስ በዚህ ምሳሌ አስረድቷል፡፡
የንስጥሮስንም ምንፍቅና ለሁሉ አጋልጧል፡፡ በዚህም መሠረት የንስጥሮስ ክህደት ተወግዞ ተለይቷል፡፡ በዚህ ጉባኤም አባቶቻችን የጨመሩልን
አንቀጸ ሃይማኖት “በአማን ወላዲተ አምላክ፤ በእውነት አምላክን የወለደች” የሚል ነው፡፡ ንስጥሮስ “ሕስወኬ ትሰመይ ቅድስት ድንግል
ወላዲተ አምላክ ወአማነ ትሰመይ ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክዶ ነበርና
ሊቃውንቱ እርሱን አውግዘው “በአማን ወላዲተ አምላክ፤ በእውነት አምላክን የወለደች” ናት በማለት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ
ብለው አንቀጸ ሃይማኖት ጽፈውልናል፡፡ የዛሬ ቅብአት እምነትን የሚከተሉ ሰዎችም ከዚህ ከንስጥሮስ ምንፍቅና ጋር ኅብረት አላቸው፡፡
ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ለምትሉ ከመጽሐፋቸው ላይ ልውሰዳችሁ፡፡ ወልደ አብ ገጽ 127 ላይ “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም
ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው” ብለው ያምናሉ፡፡ ስለዚህ መለኮት ከሥጋ ጋራ
ተዋሕዶ ከተፈጠረ በኋላ ድንግል ማርያም ወለደችው ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ድንግል ማርያም የወለደችው ፈጣሪን ሳይሆን ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ
የተፈጠረን ሰው እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ ይቅር ይበለንና እንደዚህ ያለውን ክህደት ሲጽፉ እና ሲያስተምሩ ግን እንደ ንስጥሮስ በጉባኤ
ስላልተለዩ ምናልባትም ትክክል ነን ከንስጥሮስ ክህደት እንለያለን ይሉን ይሆናል፡፡ ግን ማታለያ ካልሆነ በቀር ንስጥሮሳውያን እንደሆኑ
በዚህ እንረዳለን፡፡ ንስጥሮስ በክህደቱ ተወግዞ ከተለየ በኋላ ላዕላይ ግብጽ ይኖር ነበር፡፡ በዚህ ኑፋቄውም ጸንቶ
ስለነበር ቅዱስ ቄርሎስ ዝም ብሎ አልተወውም ነበር፡፡ ንስጥሮስ ካለበት ዘንድ ሄዶ ወንደሜ ጌታን አምላክ ድንግል ማርያምን ወላዲተ
አምላክ ብለህ እመን አለው፡፡ ንስጥሮስ ግን እኔስ አንተ እንደምትለው አልልም ጌታን እሩቅ ብእሲ ድንግል ማርያምን ወላዲተ ሰብእ
እላለሁ እንጅ በማለት አሻፈረኝ አለ፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም እመቤቴን ላዋርድ ብለህ እንዲህ እንዳልክና እኔንም አልታዘዝም እንዳልክ
ላንተም አንደበትህ አይታዘዝልህ ብሎ ረገመው፡፡ በዚህም የተነሣ ምላሱ ተጎልጉሎ ከደረቱ ተንጠልጥሎ ደምና መግል እየተፋ በከፋ አሟሟት ሞቷል፡፡ አሁንም በዚህ የምንፍቅና ባሕር
ውስጥ በመዋኘት ላይ ያላችሁ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች ከዚህ ክህደታችሁ ተመልሳችሁ በጎላ የተረዳች የአባቶቻችንን እምነት ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶን እንድትይዙ መልእክት አስተላልፋለሁ፡፡ አሁንም ለዚህ መልእክቴ ስድብ እንደምትመልሱልኝ አውቃለሁ ግን ቄርሎስን እስክንመስለው
ድረስ አላቆምም፡፡ ንስጥሮስ በከፋ አሟሟት ሲሞት ተመልክቻለሁና እናንተም እንደዛ ባለ ሁኔታ ስትሞቱ መመልከት አልፈልግምና ከእናንተ
ሞት ይልቅ የእኔ መሰደብ እጅግ ይሻላልና፡፡
No comments:
Post a Comment