Friday, July 8, 2016

የተዋሕዶ መደምደሚያ ቅብአት ነው?

©በመልካሙ በየነ
ሐምሌ 1/2008 .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ፣


የቅብአትን ኑፋቄ ባለፉት በርካታ ጽሑፎቼ መጽሐፋቸውን መነሻ በማድረግ ሳሳውቅ ቆይቻለሁ። አሁን መጽሐፋቸው አደባባይ ላይ እየተሸጠ እያለ እንኳ "ጎጃምን ትልቁን አገር አታሰድብ ቅብአት የሚባል ነገር የለም" የሚሉ አልታጡም። እነዚህ ሰዎች መጀመሪያ ሀገር እና ክፍለ ሀገርም የማያውቁ መሆናቸው ግልጽ ነው። ምክንያቱም ሀገር ብለን ኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር ብለን ጎጃም እንላለን እንጅ "ትልቅ ሀገር ጎጃም" አንልም። ሲቀጥል የሀገር ትልቅነት በምን ይለካል? ለሚለው ጥያቄም በቂ መልስ ማቅረብ አይችሉም። ጎጃም ትልቅ እንደሆነ እናውቃለን ሆኖም ግን ከትልቁ ዝሆን ላይ ትንኝ እንደማትታጣ መረዳት አያዳግተንም። ስለዚህ "ቅብአት የለም" የሚለው የአንዳንድ ሰዎች አስተያየት (አቡነ ማርቆስን ጨምሮ ማለቴ ነው) ተቀባይነት የለውም። ድሮ አቡነ ዘካርያስ ይህንነ ሲሉን ነበር ያን ጊዜ እውነታቸውን ይሆን? ብለን ነበር። ምክንያቱም ከወሬ ያለፈ ተጨባጭ ማስረጃ ስላልነበረን። ዛሬ ግን ሽህ ሰው "ቅብአት የለም" ቢለኝ ሺህ ውሸታም እላቸዋለሁ እንጅ እንደ ድሮው እውነት ይሆን? ብየ አልጠራጠርም። ምክንያቱም የቅብአት እምነት ሊቅ የሚባለው "ገብረ መድኅን" ወይም "ሄኖክ" የጻፈልን "ወልደ አብ" የተባለ መጽሐፍ ማስረጃችን ነውና። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ማንም ጆሮ የለውም። እልፍ ፐርሰንት ያህል እተማመናለሁ ቅብአት አለ ያውም ከቤታችን ከቤተክርስቲያናችን። በዚህ ጉዳይ ይህን ያህል ካልኩ ወደ ዋናው ጉዳየ ልግባ። የቅብአት እምነት ተከታዮች "ለተዋሕዶ መደምደሚያ ቅብአት ነው" ይላሉ። ይህን እስኪ ከራሳቸው መጽሐፍ እንመልከተው።
ወልደ አብ ገጽ 219 ላይ “ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ፡፡ ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ፡፡ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም፡፡ ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪” ይላል። ይህን ጉዳይ "የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች ክፍል 8" ላይ በዝርዝር ተመልክተነዋል። እዚህ ላይ መድገም ያስፈለገው ይህ አገላለጽ "ለተዋሕዶ መደምደሚያ ቅብአት ነው" የሚል አንድምታ ስላለው ነው። ምክንያቱም እርስ በርሱ የሚጋጭ የሚመስል ሃሳብ ይዟል ነገር ግን አይጋጭም ይላሉ የቅብአት እምነት ተከታዮች። ስለዚህ የማይጋጭ ሃሳብ ከሆነ ሊስማማ የሚችለው እንደሚከተለው ይሆናል። መጀመሪያ ሁለት የተዋሕዶ ሂደቶች ይከወናሉ። የመጀመሪው"ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ"የሚለው መለኮት ከሥጋ ጋር ያደረገው ተዋሕዶ ነው። በዚህ ተዋሕዶ ላይ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሐደ እንጅ ሥጋ ከመለኮት ጋር አልተዋሐደም።በዚህ ተዋሕዶ ሥጋ የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጎ በቃል መጠሪያ ተጠራ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ተባለ ማለት ነው። የሚገርማችሁ እስከዚህ ድረስ መለኮት የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አላደረገም በሥጋ ስምም አልተጠራም። ስለዚህ ሙሉ ተዋሕዶ ይደረግ ዘንድ ሥጋ ከመለኮት ጋር መዋሐድ አለበት። ይህኛው ቀጣዩ ተዋሕዶ ነው። ሁለት ነጥላ ተዋሕዶዎች ናቸው እንግዲህ አንድ ሙሉ ተዋሕዶን የሚፈጥሩት። በነገራችን ላይ ይህን የምላችሁ እነርሱ ተዋሐደ እያሉ ስለጻፉት እንጅ እንደ እኔ ይኼ ተዋሕዶ አይባልም። የኅድረት ተዋሕዶ ሊሆን እንደሚችል ብቻ ነው የምገምተው። ስለዚህ ኅድረት ያለበት ተዋሕዶ እንደሆነ እረዳለሁ። ቀጣዩ ተዋሕዶ የሥጋ ከመለኮት ጋር መዋሐድ ነው። "ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ" ይላል ሥጋ ከመለኮት ጋር እንደተዋሐደ ለማጠየቅ። ቅድም ልጅነት አገኘ ቃለአብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ያሉት ሥጋ አሁን ልጅነትን የሚሻ ሆነ ምክንያቱም መለኮት ቢዋሐደው ልጅነት አገኝ እንጅ ሥጋ ከመለኮት ጋር ስላልተዋሐደ የሚቀረው ልጅነት አለ። ስለዚህ ይህን ሙሉ ልጅነት ያገኝ ዘንድ ሥጋ ከመለኮት ጋር መዋሐድ ያስፈልገዋል ማለት ነው። እንግዲህ እነዚህ የተዋሕዶ ሁለት ሂደቶች ከተጠናቀቂ በኋላ ይፈጠራል። ወልደ አብ ገጽ 131 "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል። ለሊሁ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ እምብእሲት እን ቅዱስ ቂርሎስ ሃ አ ስምዓት ክ፪ ቁ፲፱ ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው። መለኮት በሥጋ ርስት ፍጡር ነው። ሥጋ ሲፈጠር መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ አብሮ ተፈጠረ ካላሉ እንደ ንስጥሮስ ፪ አካል ማድረግ ኃደረበብእሲ ማለት ነውና ክህደት ነው" አሁን መለኮት ከሥጋ ጋር ሥጋም ከመለኮት ጋር ተዋሕዶ ተፈጥሯል። ማን ፈጠረው አትሉኝም መቸም ምክንያቱም አምላክ ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጥሯልና። መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ ካላሉ ክህደት ነው ብለዋል እኮ ደግሞ። እንግዲህ ይህ ተዋሕዶ ከተከናወነ በኋላ የተፈጠረው አካል እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ ያዝዝ ይገዛ ዘንድ በቅብአት መክበር ያስፈልገዋል። ይህንንም እንዲህ ያስረዳሉ "ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም" ስለዚህ ከተዋሕዶ በኋላ ቅብአት መደምደሚያ ሆኖ እናገኘዋለን። አንድ ያልተረዱት ነገር አለ እግዚአብሔር በመለካት በመፍጠር አንድ ነው። ይህን ካመኑ ደግሞ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ ማለት ምን ማለት ነው? ወይስ ደግሞ እኛን ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ አጡለት ስለሚሉን ቦታ ለመፈለግ ይሆን? የወልድ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሐደ አንድ ቦታ ለወልድ ተገኘለት። ቀጣይ መለኮት የተዋሐደውን ሥጋ አብ ፈጠረው ለአብ ሌላ ቦታ ተሰጠው ቀጣይ ይህን ከመለኮት ጋር ተዋሕዶ የተፈጠረውን ሥጋ መንፈስ ቅዱስ አከበረው ለመንፈስ ቅዱስም ቦታ ሰጡት።
አምላከ ቅዱሳብ ይቅር ይበለን!!!

No comments:

Post a Comment