Sunday, July 3, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 9

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 25/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በክፍል 8 “ወልደ አብ” በተሰኘው የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች ገጽ 219 ላይ ያለውን የክህደት አስተምህሮ ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 182 ላይ ያለውን ክህደት መነሻ በማድረግ እንጽፋለን፡፡
“መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ ተሰጠ ማለት ማለት ነውን ቢሉ እንዲህስ አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት ሆነው ማለት ነው፡፡ በእንተዝ ይትበሃል ከመ ነሥአ መንፈሰ ዚአሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ቀብዓኒ በእንተዝ ሰበከ እንዘ ይብል እስመ መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ በእንተ ዝንቱ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሢሐ እንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ እን ሳዊሮስ ዘአንጾ ሃ አ ክ ፱ ቁ፲፯”  ይላል ሙሉ ንባቡ፡፡ እንግዲህ እንደተለመደው ቃል በቃል ለማየት እንሞክር፡፡
“መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ ተሰጠ ማለት ማለት ነውን ቢሉ እንዲህስ አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት ሆነው ማለት ነው” በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ “መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ” የሚል ትምህርት የለም፡፡ በቤተክርስቲያናችን ካሉት ምሥጢራት መካከል አንዱ “ሜሮን” ነው፡፡ በዚህ ሜሮን በሚባል ቅዱስ ቅብአት ላይ መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል መንፈስ ቅዱስ ያከብረዋል እንላለን እንጅ “መንፈስ ቅዱስ ቅብአ ሜሮን ነው” ብለን አልተማርንም፡፡ በሐዋ ሥራ 2 ላይ እንደምንመለከተው መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ አደረባቸው እንላለን እንጅ “ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ሆኑ” አንልም ምክንያቱም የሚያድርባቸው በጸጋ ነውና፡፡ ስለዚህ ይህ አስተምህሮ የእኛ አይደለምና በአንዲት ገዳማችን ስም እንዲህ ዓይነቱን ኑፋቄ ማውጣት ድፍረት ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ለዚህም የጠቀሱት ማስረጃ ያው እንደተለመደው አንዱን ካንዱ ጋር በማቀላቀል የሚያስቀምጡት የተቆረጠ የመጽሐፍ ክፍልን ነው፡፡ “በእንተዝ ይትበሃል ከመ ነሥአ መንፈሰ ዚአሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ቀብዓኒ በእንተዝ ሰበከ እንዘ ይብል እስመ መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኃደረ ላዕሌየ በእንተ ዝንቱ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሢሐ እንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ እን ሳዊሮስ ዘአንጾ ሃ አ ክ ፱ ቁ፲፯”  ይላሉ፡፡ የጠቀሱት የሃይማኖተ አበው ክፍል ምን እንደሚል በግእዝም በአማርኛም እንመልከተው እስኪ፡፡ በመጀመሪያ እነርሱ እዚህ ላይ ቁጥር 17 ያሉት የቁጥር 16ን የተወሰነ ክፍል እና የቁጥር 17ን የተወሰነ ክፍል ቆራርጠው ነው፡፡ እንዲህ ይላል ሃይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ ክፍል 9 ቁጥር 16 ግእዝ “ወሃሎ መንፈስ ቅዱስ ይጼልል መልዕልተ ማይ እምቅድመ ዝንቱ ግብር ዘተፈጸመ በእንቲአነ በጥበብ ወሥርዓት ዘከመ ወጠነ ዳግመ ልሂኮተነ ወበእንተ ዝንቱ ይደሉ ይትበሃል ከመ ውእቱ ነሥአ መንፈሰ ዚአሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ በእንተ ዝንቱ ቀብዓኒ” አማርኛ ትርጉም “እኛን ማደስን እንደጀመረ በጥበብ በሥርዓት ስለእኛ ከተፈጸመው ከዚህ ሥራ (ከጥምቀት)  አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ ይሰፍ ነበረ ስለዚህም የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ሕልው ነው ስለዚህ ነገር አዋሐደኝ ሲል በኢሳይያስ የተነገረለትን የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን እርሱ ገንዘቡ እንደአደረገ ሊነገር ይገባዋል” የሚል ነው፡፡ በወልድ ህልው ሆኖ የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስ ሥጋ ገንዘቡ አደረገ ሲል እንዲህ አለ እንጅ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ ተቀብሎ  አብ ከድንግል ማርያም በሥጋ ወለደው አላለንም፡፡ ቁጥር 17 ግእዝ “በእንተዝ ሰበከ እንዘ ይብል እስመ መንፈስ ዘዚአየ ዘህላዌየ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሢሐ ዘእንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ ዝንቱ ውእቱ መድኃኒትነ ዝንቱ ውእቱ ፈውሰነ ዝንቱ ውእቱ ሐዋጺነ” ይላል አማርኛ ትርጉሙም “ስለዚህ በባሕሬዬ ገንዘቤ የሚሆን መንፈስ ቅዱስ በህልውናየ ጸና ብሎ አስተማረ ሰው ብሆን ነው እንጅ ያለዚያ ለምን ክርስቶስ ተባልኩ? የምንድንበት ይህ ነው፡፡ የሚፈውሰን ይህ ነው የጎበኘን ይህ ነው” ይላል፡፡ እንግዲህ ሁላችሁ እንደምታዩት ቆራርጠው በጠቀሱት ጥቅስ መንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ የባሕርይ ሕይወት ሆነው የሚል ትርጉም አንድም ቦታ ተጽፎ አላገኘንም፡፡ “በባሕሬዬ ገንዘቤ የሚሆን መንፈስ ቅዱስ በህልውናየ ጸና ብሎ አስተማረ” ይላል እንጅ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቤ ሆነ አላለንም፡፡ ሰው ስለሆነ ይህንን ተናገረ ክርስቶስ የተባለው ሥጋና መለኮት ከተዋሐዱ በኋላ ነው እና፡፡ ከተዋሕዶ በፊት ክርስቶስ አልተባለም ነበርና አሁን ግን ሲዋሐድ ክርስቶስ ተባለ፡፡ ስለዚህም ሰው በመሆኑ “በእኔ ህልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ በህልውናየ ጸና ለሥጋየ ገንዘቡ ሆነ” አለን እንጅ እነርሱ እንደሚሉት ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቤ ሆነ አላለንም፡፡ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ገንዘቡ አደረገ የሚሉት ግን በወልድ ህልው ሆኖ የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ወዴት ሄዶ ነው ዛሬ በሥጋ ርስት ዳግመኛ ሕይወት የሚሆነው? እዚህ ጋር ማስተዋል ያስፈልገናል ዋናው የክህደታቸው ምንጭ ይህ ስለሆነ፡፡ እኛ የምንለው መንፈስ ቅዱስ ለአብ እና ለወልድ የባሕርይ ሕይወታቸው ነው ይህም ጥንት ከሌለው ዘመን ጀምሮ በሰው ህሊና በማይመረመር አምላካዊ ጥበብ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወልድ ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ ይህ በወልድ ሕልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ሥጋን የባሕርይ አምላክ አደረገው ነው፡፡ እነርሱ የሚሉት ደግሞ ወልድ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ሕይወቱ አደረገ ነው፡፡ እኛ የምንጠይቀው ያ በቃል ህልው ሆኖ ይኖር የነበረው መንፈስ ቅዱስ የት ሄዶ ነው ዳግመኛ አከበረው የሚባለው? ወይስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ያልቃል ልትሉን ነው? ወይስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ አርጅቶበት ማደስ ያስፈልገዋል ልትሉን ነው? እኛ ግን አባቶቻችን እንዳስተማሩን እንመራለን፡፡ ኢሳ 61÷1 ላይ ያለውን ቃል ሉቃ 4÷17 ላይ ይተረጉሙታል፡፡ ሳዊሮስም ሃይማኖተ አበው ላይ እሱን ይተረጉማል ሳዊሮስ ክ 9 ቁ 18 እንዲህ ይላል “ስለዚህ ነገር ከዚህ በኋላ ለድኆች የምሥራች እነግራቸው ዘንድ ያዘኑትን አረጋጋቸው ዘንድ ለተማረኩት ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ ዕውሮች ያዩ ዘንድ ስለዚህ ላከኝ አለ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቡ ሆነ መባሉ ቃል ሰው ስለሆነ ነው ሰውማ ባይሆን ኖሮ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ህልው እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ በባሕርየ መለኮት ገንዘቡ ነውና እንደምን ገንዘቡ ሆነ ይባላል አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ  ህልው መሆኑን እንደተናገረ”፡፡ ሳዊሮስ እዚህ ክፍል ላይ የተረጎመው ኢሳ 61÷1 ላይ ያለውን ቃል ነው፡፡ እንግዲህ ሳዊሮስ በግልጽ እንዳስቀመጠልን መንፈስ ቅዱስ በወልድ ህልው ሆኖ ይኖራል ያ ህልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ወልድ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ለሥጋ ገንዘቡ ሆነ ማለት ነው እንጅ ዳግመኛ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚል ትምህርት አላስተማረም እንዲያውም እዚሁ ክፍል ቁጥር 19 ላይ ሳዊሮስ እንዲህ ይላል “በዚህም ግብር ተዋሕዶ ጠፍቶ ከነቢያት እንደአንዱ አልሆነም መንፈስ ቅዱስ ያደረበት አይደለም” ይላል፡፡ ስለዚህ የት ቦታ ላይ ነው ወልድ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ ተቀብሎ አብ ከማኅጸነ ማርያም ወለደው የሚለው ትምህርት ያለው፡፡ ሉቃ 4÷17 ላይም ወንጌላዊው ሉቃስ ‹‹ኢሳ 61÷1›› ያለውን ወስዶ አስቀምጦታል፡፡ ትርጓሜ ወንጌሉ እንዲህ ይላል፡፡ “ዘይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ” መጽሐፉን ገልጾ ሳለ ማስተማር በእኔ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ያዋሐደኝ እግዚአብሔር አንድም ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ተርጉሞታል መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ ብሎ የባሕርይ ህይወቴ መንፈስ ቅዱስ በእኔ ህልው ነው ወዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ ስለማስተማርም ያዋሐደኝ መንፈስ ቅዱስ ነዳያንን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ስለዚህ እነሱ ለጻፉት ኑፋቄ ይህ ማስረጃ ተብሎ ሊጻፍ አይገባውም ነበር ነገር ግን ሰውን ወደ ጥርጥር ለመክተት ተጠቅመውበታል፡፡ “ቀባ” የሚለው ቃል በርካታ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ተመልክተናል እዚህ ላይ ቀብዓኒ ያለውን ያዋሐደኝ ብለው ነው የተረጎሙት፡፡ ስለዚህ ምናልባት ቅብአቶች የራሳቸው ሃይማኖተ አበው የራሳቸው የትርጓሜ መጻሕፍት ሊኖሯቸው ይችል ይሆናል እንጅ የእኛ መጻሕፍት ግን “መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ ተሰጠ ማለት ማለት ነውን ቢሉ እንዲህስ አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት ሆነው ማለት ነው” ብለው አናገኛቸውም፡፡ ምክንያቱም ኑፋቄ ነውና! አባቶቻችንስ የማይመረመረውን መለኮት መርምሮ በማይደርሰው ኅሊናችን እንመረምር ዘንድ እንደማይገባ አስተማሩን እንጅ በድፍረት የመሰለንን ነገር ለመኮት ስንቀጽል ዘንድ አላስተማሩንም፡፡ ሃ አ ዘቴዎዶጦስ ም 53 ቁ 5 ላይ “ተመርምሮ የማይታወቅ ከሆነስ አለመመርመርን ማወቅ ይገባናል፡፡ ድንቅ ምንድን ነው? የባሕርዩ ሥራ ነው እንጅ ድንቅ እርሱ ከሆነ ድንቅ የሆነ እርሱም ሁልጊዜ ድንቅ በመባል የሚኖር ከሆነ እውቀትን ድንቅ ድንቅ ሥራ በሚሠራ ለፍጥረቱ ሁሉ ገዥ ለእርሱ ተው” ይላል፡፡ ስለዚህ የማይመረመረውን መለኮት እንመረምራለን እያሉ ክህደታቸውን ለሚተፉ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች መልእክታችን ቆም ብላችሁ አስቡ የሚል ነው!
ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment