Friday, July 8, 2016

"የቅብአት ምንፍቅና በአደባባይ"

©በመልካሙ በየነ
ሰኔ 30/2008 .
ደብረማርቆስ ኢትዮጵያ፤
"የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች" በሚል ርእስ መነሻነት እስከ ክፍል 10 ድረስ እንደተማማርን ታስታውሳላችሁ። ዛሬም በዚህ ክፍል ምንፍቅናቸው ምን ላይ እንደሆነ በግልጽ እንመለከታለን። እዚህ ላይ ግን ልብ ማለት የሚገባን የምጽፈው ነገር ከራሴ አንቅቸ እንዳልሆነ ነው። የምጽፍላችሁ ነገር ራሳቸው ካሳተሙት የክህደት መጽሐፍ ሲሆን የሚጠቅሱትንም ጥቅስ ትክክለኛውን እና ሙሉውን በግእዝም በአማርኛም እጽፍላችኋለሁ።
ወልደ አብ ገጽ 131 "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል። ለሊሁ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ እምብእሲት እን ቅዱስ ቂርሎስ ሃ አ ስምዓት ክ፪ ቁ፲፱ ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው። መለኮት በሥጋ ርስት ፍጡር ነው። ሥጋ ሲፈጠር መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ አብሮ ተፈጠረ ካላሉ እንደ ንስጥሮስ ፪ አካል ማድረግ ኃደረበብእሲ ማለት ነውና ክህደት ነው" ይላል።
አሁን ይህን ድፍረትና ክህደት አንድ በአንድ እንመልከተው። "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል" ይላሉ ሲጀምሩ። በመጀመሪያ "ወልድ" የሚለው ስም ሥጋን ሲለብስ የጠራንበት ሳይሆን ጥንት ከሌለው ዘመን ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል በጥበበ እግዚአብሔር ከአብ ያለእናት በተወለደ ጊዜ ነው። ሰለዚህ ይህ የመወለድ ግብር ያለው "ወልድ" ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አይበልጥም አያንስምም እኩል ነው እንጅ። ይህ ከሥላሴ አንድነት ለቅጽበት ያህል እንኳ ያልተለየው "ወልድ" ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋንከነፍሳ ነፍስን ነሥቶ በተዋሕዶ የተወለደው ከአምላክነት ክብሩ ዝቅ ለማለት አይደለም። መለኮት ከሥጋ ጋር ሥጋም ከመለኮት ጋር በተዋሐደ ጊዜ ሥጋ አምላክ ሆነ አምላክም ሰው ሆነ። አሁን ከተዋሕዶ በኋላ ሥጋንና መለኮትን መከፋፈል አንችልም ምክንያቱም "አምላክ ወሰብእ" የሚባል ነውና። ቅብዓቶች እዚህ ላይ የሠሩት ስህተት ከተዋሕዶ በኋላ መለኮትን ከሥጋ ከፍለው "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል" ይላሉ። ቅዱስ ቄርሎስ የመሰለውን የጋለ ብረት አስታውሱት ብረቱ ከጋለ በኋላ እሳት ይባላልን? ወይስ ደግሞ ብረት ብቻ ይባላል? አይባልም። ትክክለኛ ስሙ "የጋለ ብረት" የሚለው ነው። ብረት ወይም እሳት ልንለው የሚገባ ከመጋሉ በፊት ነው እንጅ ከጋለ በኋላስ "የጋለ ብረት" እንለዋለን እንጅ "ብረት" ወይም "እሳት" ብቻ ብለን እንደማንጠራው የታወቀ ነው። የመለኮት እና የሥጋም እንዲሁ ነው። ከተዋሕዶ በፊት "ወልድን ፈጣሪ" ብቻ እንለዋለን "ሥጋንም ፍጡር ብቻ" እንለዋለን። ከተዋሕዶ በኋላ ግን የቃልን ገንዘብ ሥጋ የሥጋንም ገንዘብ ቃል ገንዘቡ ስላደረገ የብቻ መጠሪያ አይኖራቸውም። ስለዚህም "ክርስቶስ" እንለዋለን ከሁለት አካላት እንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ያለው "አምላክ ወሰብእ" ነውና። ልብ በሉ "ክርስቶስ" የሚለው ሥም ከተዋሕዶ በኋላ የተጠራበት ነው። ይህም ማለት "ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው" ነው ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ ተዋሕዶ ከፍለን ሥጋን ለብቻው መለኮትንም ለብቻው ልናደርገው እንዴት እንደፍራለን።
"ለሊሁ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ እምብእሲት እን ቅዱስ ቂርሎስ ሃ አ ስምዓት ክ፪ ቁ፲፱ ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው" ይላሉ። ሁልጊዜ የሚገርሙኝ ማስረጃ ብለው የሚጠቅሱት ነገር ከሚናገሩት ጽንሰ ሃሳብ ጋር በምንም የሚገናኝ አይደለም። በመጀመሪያ ግን የፊደል ግድፈትን እንኳ ማጣራት ይገባቸው እንደ ነበር እረዳለው። "ቄርሎስ" ን "ቂርሎስ" ብለው የጻፉት ምናልባትም ሃይማኖተ አበውን ገልጠን ስንመለከት እንዳናገኘው ፈልገው ይሆናል። ከየት ቆርጠው እንደወሰዱት ልብ ብላችሁ ተመልከቱት የጠቀሱትን የቄርሎስ ስምዓት ሙሉውን ግዕዝም በአማርኛም አንብበት ከዚህ በታች ቀርቦላችኋል።
ቄርሎስ ሃ አ ስምዓት ክ፪ ቁ፲፱ "ወካዕበ ይቤ ተሰምየ ገብረ ወውእቱ እግዘኣ ኩሉ ከመ አምላክ ለሊሁ በግዕ ወለሊሁ ካህን ዓዲ ኅቡረ እስመ ውእቱ ሦዐ ርእሶ ባህቲቱ በከመ ንቤ ቅድመ አዕረገ ሥጋሁ ባህቲቱ በፈቃዱ መሥዋእተ ውኩፈ ወዕጣነ ምዑዘ ለእግዚአብሔር አቡሁ በእንቲአነ ለሊሁ ፍጡር ወለሊሁ ፈጣሪ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ በሥጋ እምብእሲት ወካዕበ ይቤ ዝንቱ ዓምደ ሃይማኖት በእንቲአሁ ትብልኑ እስመ ዘተፀንሰ ካልእ ውእቱ ዘምስለ ፈጣሪ በከመ በውስተ መለኮት ወትስብእት ወፈጣሪ ወፍጡር ፍልጣን ሐሰ ለነ እምዝንቱ ንባብ ሙሱን ወርኩስ"
አማርኛውንም እነሆ ሳልጨምር ሳልቀንስ:
"ዳግመኛም አገለገለ ተባለ ግን እሱ አምላክ እንደመሆኑ ሁሉን ፈጥሮ የሚገዛ ነው እሱ መሥዋእት ነው። ወዲህም ከመሥዋእቱ የማይለይ ካህን ነው እሱ ብቻ ሥጋውን በፈቃዱ የተወደደ መሥዋእት የተወደደ ዕጣን አድርጎ ስለእኛ ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር አቀረበ ብለን አስቀድመን እንደተናገርን እሱ ራሱን ብቻ ሠውቶአልና እሱ ሰው ነው እሱ አምላክ ነው አምላክ እግዚአብሔር ሰለሆነ ፈጣሪ እንለዋለን ወዲህም ከድንግል በሥጋ ስለተወለደ ሰው እንለዋለን ዳግመኛ ይህ ዓምደ ሃይማኖት ቅዱስ ቄርሎስ ስለ እሱ ስትናገሩ በመለኮትና በትስብእት በፈጣሪና በፍጡር መካከል መከፋፈል እንዳለ አድርጋችሁ የተፀነሰው ከፈጣሪ ጋር ያለ ሌላ ነው ትላላችሁን ሌላ አይደለም እኛ ግን እንዲህ ያለ የተጠላ የተነቀፈ አነጋገር ልንናገር አይገባንም አለ" ብሎ ትምህርታቸውን ያወግዛል። ከተዋሕዶ በኋላ በሥጋና በመለኮት መካከል መከፋፈል እንደሌለ ሰው ሲሆን አምላክ አምላክ ሲሆን ሰው ነው ብሎ ትምህርተ ተዋሕዶን በጎላ በተረዳ ነገር ነገረን እንጅ ቅብአቶች እንደሚሉት "ወልድንም በሰውነቱ ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል" አላለንም። ይህ ደግሞ ግልጽና ግልጽ አነጋገር ነው እንዲያውም እንዲህ የሚሉትን አወገዛቸው እኮ። ከተዋሕዶ በኋላ ሥጋና መለኮትን ይከፍሉና አሁንም "ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው" ብለው ይደመድማሉ። ከዚህ ቀጥለው የሚጽፉት ደግሞ በክርስትናዋ ዓለምን ከምታስደንቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖር ሰው የማይጠበቅ ከባድ ክህደት ነው። ይህም እንዲህ ይላል "መለኮት በሥጋ ርስት ፍጡር ነው። ሥጋ ሲፈጠር መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ አብሮ ተፈጠረ ካላሉ እንደ ንስጥሮስ ፪ አካል ማድረግ ኃደረበብእሲ ማለት ነውና ክህደት ነው" ብለው ለክህደታቸው ሌላ ክህደትን ይሹለታል። መጀመሪያ "ኃደረበብእሲ" የሚለውን ጸሐፊዋን "ኃደረ በብእሲ" ብላ እንድታስተካክለው አሳስቧት። ይህን ክህደት ሳይ ዛሬስ ምነው ንስጥሮስ ባየ ኖሮ አልኩ ለራሴ። ተመልከቱት የምንፍቅናቸውን ሂደት መጀመሪያ መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሐደ እዚህ ውህደት ላይ ሁለት ትልልቅ ሂደቶች አሉ። እነርሱን በሌላ ጊዜ እናያቸዋለን። ከዚያ ሂደት በኋላ ሙሉ ተዋሕዶ ይደረጋል። ከዚያ ያ ከመለኮት ጋር የተዋሐደውን ሥጋ ይፈጥረዋል። ማን እንደሚፈጥረው ግን እንጃ። ምክንያቱም መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ ሊፈጠር ነውና ሌላ ፈጣሪን ይሻል ማለት ነው። ከዚያ ማን እንደሚፈጥረው ባይታወቅም መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዳ ይፈጠራል አሉ። ከዚህ በኋላ ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ፍጡር የሆነ መለኮት አገኙ ማለት ነው። ይህ ፍጡር የሆነ መለኮት ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ እኩል እንዲገዛ እኩል እንዲስተካከል ቅብአት አስፈለገው። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ቅብአት የሚያስፈልገው። አያችሁ የክህደታቸውን ሰንሰለት። ስለ እውነት እንዲህ ያለውን ምንፍቅና ምን ሲሉ ጀመሩት ይሆን ግን። ንስጥሮስ ፪ ግብር ያለ መለኮት ከሥጋ ጋር ሳይዋሐድ ተፈጠረ ስላለ ነው እንዴ? ምነው ንስጥሮስን ሆናችሁ የንስጥሮስ ክህደት ጠፋችሁ። በእርግጥ የእናንተ ደግሞ ከንስጥሮስም ከአርዮስም የተጨመቀ ክህደት ነው ያፈለቃችሁት። በእውነት የትኛው ሊቅ የትኛው መጽሐፍ ነው "መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ ተፈጠረ" የሚል? መቸም አሁንም ያላነበባችሁትን መጽሐፍ ትጠቅሱት ይሆናል። የምትጠቅሱትን መጽሐፍ ቢያንስ ማወቅ ያስፈልጋችኋል። ለክህደታችሁ ግን እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ ወላዲተ አምላክ እመ ብርሃን ድንግል ማርያም በምልጃዋ ትጠብቃችሁ።

No comments:

Post a Comment