Monday, July 4, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 10

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 27/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በፌስ ቡክ ስጽፍ የመጀመሪያውን ረዥም ጽሑፍ የጻፍኩት በዚህ ርእስ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ጉዳዩ አሳሳቢ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እናንተንም ላለማሰልቸት በዚህ ክፍል ይህን ርእስ ለመቋጨት እገደዳለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ ክፍል በዋናነት የምንመለከተው እስካሁን ያየናቸውን ማጠቃለያ ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ማጠቃለያዎችም ለእነርሱ የምንፍቅና ምንጭ በሆኑ ነጥቦች ላይ ነው፡፡
መጀመሪያ ክርስቶስ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ለምንፍቅናቸው ተጠቅመውበታል፡፡ ክርስቶስ ማለት በዐረቡ መሢሕ በግዕዙ ቅብእ በአማርኛው የከበረ ንጉሥ ማለት ነው፡፡ /ቃለ ጽድቁ ለአብ ገጽ 104/ እንግዲህ ቅብአቶች የተጠቀሙት ቅቡእ የሚለውን ቃል ነው፡፡ ክርስቶስ የሚለው ስም ከተዋሕዶ በኋላ ያወቅነው ስም ነው እንጅ ከተዋሕዶ በፊት በዚህ ስም ጠርተነው አናውቅም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ማለት የከበረ ንጉሥ ማለት ነው፡፡ ነገሥታት ሲነግሡ እንደሚቀቡ ሁሉ መለኮትም ተቀብቷል ማለት ግን አይደለም፡፡ ልብ ማለት እዚህ ላይ ነው እነዚህ የጸጋ ነገሥታት ናቸው እርሱ የባሕርይ ንጉሥ ነው፡፡ ዳዊት በመዝሙር 73 ላይ “እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም” ይለዋል ስለዚህ ኢየሱስ የከበረ ንጉሥ ነው፡፡ ይህም ማለት ራሱን በራሱ ያከበረ ሿሚ ሻሪ የሌለው ንጉሥ ማለት ነው፡፡ ልዩነታችን እነርሱ ሌላ አክባሪ ያስፈልገዋል ነው የሚሉት እኛ ደግሞ ራሱን በራሱ ያከብራል ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ስንል በባሕርይው ህልው ሆኖ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ራሱን በራሱ ያከበረ ንጉሥ ማለታችን ነው፡፡ ክርስቶስ ማለት ፈጣሪና ፍጠር አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆነ ማለት ነው እንዲል ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ም35 ክ1 ቁ2 ላይ።
ተዋሕዶ እና በተዋሕዶ ከበረ ልዩነታቸው ምንድን ነው? በሚለው ጥያቄ ጊዜ የሚያቃጥሉ የቅብአት መናፍቃን በዝተዋል፡፡ ምናልባት  “ቅብአት እና በቅብአት ከበረ” የሚሉት ቃላት እንደሚለያዩ ስለሚያውቁ ተዋሕዶ እና በተዋሕዶ ከበረ የሚለውም የሚለያይ መስሏቸው ይሆናል፡፡ ተዋሕዶ ማለት ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሆነበትና የሥጋ ገንዘብ ለቃል የቃልም ገንዘብ ለሥጋ የሆነበት ምሥጢር ነው፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ” ማለትም ህልው ሆኖ በሚኖረው  በባሕርይ ህይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ወልድ ሥጋን አምላክ አደረገው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ተዋሕዶ በተዋሕዶ ከበረ የሚለው ትርጉሙ ጊዜ የሚወስድ አይደለም፡፡ እነርሱ ላይ ግን ልዩነት አለው እነርሱ የሚሉት “ተዋሕዶ” ሁለትንትን አጥፍቶ አንድነትን የሚያጸና እንጅ ሥጋን ማክበር አይችልም፡፡ ስለዚህ ሥጋን አምላክ ለማድረግ ወልድ የባሕርይ ህይወቱ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ ገንዘቡ ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡ ሥጋን አምላክ ለማድረግ ደግሞ ቅብአት ያስፈልጋል የሚል ድምዳሜ ላይ የሚደርሱት ስለዚህ ነው፡፡
ቀኖና እና ዶግማ ላይ ክርክር አለ፡፡ ዶግማ ማንም የማይሽረው ማንም የማያሻሽለው ማንም የማይለውጠው ማንም የማይቀንሰው ማንም የማይጨምረው ነው፡፡ ቀኖና ግን እንደሁኔታው የሚደረግ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ማንም ደስ እንዳለው ያደርጋል ማለት አይደለም፡፡ በዓላት አከባበር ላይ አጽዋማት መግቢያና መውጫ ላይ አባቶቻችን አንድ ጊዜ ሥርዓት ሠርተውልናል በዚያ ሥርዓት መሠረት እንመራለን፡፡ ስለዚህ ገና በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ 28 በሌሎች ዘመናት ታህሳስ 29 እንዲከበር በወሰኑልን መሠረት እናከብራል፡፡ በክፍል 1 ላማሳየት የሞከርኩት ቀኖናው መከራከሪያ መሆን የለበትም ዶግማው አስተምህሮው ላይ ነው ለማለት ነው እንጅ ወደፊት ታህሳስ 29 ብቻ ይከበራል ብለን እንደ ቅብአት እምነት አራማጆች ምሥጢሩ ሳይገባን አንደመድምም፡፡ ቀኖና ላይ አንድ ምሣሌ ልስጣችሁ ጥምቀት ላይ ወንዶች በተወለዱ በ40 ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀናቸው ይጠመቃሉ ይላል ነገር ግን ህጻኑ(ኗ) ሳይጠመቁ ለሞት የሚያበቃ በሽታ ቢይዛቸውስ? የግድ 40 እና 80 ቀን ይጠብቃልን? አይጠብቅም በሞግዚት ገብተው ይጠመቃሉ፡፡ ፍትሐ ነገሥቱን ተመልከቱት፡፡ ሌላም ልጨምራችሁ የጌታችን ጥንተ ስቅለት መጋቢት 27 ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት 29 ነው፡፡ በየዓመቱ ስትመለከቱ ግን ድሜጥሮስ በተገለጸለት ባሕረ ሃሳብ ተሰልቶ ስቅለት አርብን ትንሣኤ እሁድን ዕርገት ሐሙስን እንዳይለቅ ሆኖ ይከበራል እንጅ ሁልጊዜ መጋቢት 27 ስቅለትን መጋቢት 29 ትንሣኤውን አክብረን አናውቅም፡፡ በየዓመቱ በተለያየ ቀን እናከብረዋለን ለምን ብትሉ ቀኖና ስለሆነ ነው መልሳችን፡፡
ቅብአት ማለት መንፈስ ቅዱስ ነው የሚሉት ፈሊጥ አለ፡፡ በእውነት መንፈስ ቅዱስን የት ቦታ የትኛው ሊቅ ነው ቅብአት ነው ብሎ ያስተማረው የጻፈው? እኛ የምናውቀው ቅብአት ቀጥተኛ ትርጉሙ ክብር ማለት እንደሆነ ነው እንጅ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ አይደለም፡፡
አብ በሰውነቱ በማኅጸነ ማርያም ወልዶታል የሚለው ሦስተኛው የልደት ዓይነት በቤተክርስቲያናችን የትኛውም መጽሐፍ ላይ አልተጻፈም፡፡ እነርሱ የሚጠቅሱት መጽሐፍ አለ ያ መጽሐፍ ግን የራሳቸው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ መጻሕፍትን አብነት ማድረግ ይገባናል፡፡ ጥንታዊ ለማስመሰልም የብራና እያሉ የሚጠቃቅሱት አለ፡፡ ይኼ ውሸት ነው ምክንያቱም ሰይጣን እንኳን ይህን ሌላም ያስደርጋልና አሁን የጻፏቸው የብራና መጽሐፍ እንዳለ እረዳለሁ፡፡ የእኛ መጻሕፍት ግን ሦስተኛውን ልደት አውግዘውታል። ኢትዮጵያዊው ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን ላይ "ዘአልቦቱ እም በሰማያት ወአብ በዲበ ምድር ፤ በሰማይ እናት በምድርም አባት የለውም" ይለናል። ሃይማኖተ አበውም ለምድራዊ ልደቱ አባት ለሰማያዊ ልደቱም እናት አትሹለት ይለናል። ስለዚህ በምድራዊ ልደቱ አባት አለው አንልምና አብ በማኅጸነ ማርያም ወለደው የሚለውን የሰይጣን ትምህርት አንቀበልም።
“ማቅ” እና “ካራ” የሚሏቸው ፈሊጦች፡፡ ቅብአቶች ማኅበረ ቅዱሳንን “ማቅ” የተዋሕዶ አማኞችን “ካራ” እያሉ ካራ በሆነ አፋቸው ይሳደባሉ፡፡ እኔ ስጽፍ እስከ ክፍል 10 ድረስ ሁሉንም ማየት ትችላላችሁ አንድም ቦታ ላይ ስለ “ማኅበረ ቅዱሳን” አላነሣሁም፡፡ እነርሱ ግን ጥያቄ ሲጠየቁ እና ዋናው የክህደት መነሻቸው ሲነገር “ማቅ” ወይም “ካራ” ይላሉ ምን ለማለት እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ብዙዎች የተዋሕዶ ልጆች እንዲህ ወደ ስድብ ሲገቡ “አሙካ” ብለው ለቅብአቶች ይመልሱላቸዋል፡፡ እነርሱም “አሙካ” ያልከው እኮ መንፈስ ቅዱስን ነው ምክንያቱም “ቅብአት” መንፈስ ቅዱስ ነውና ይላሉ፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችሁ በእውነት ቅብአት መንፈስ ቅዱስ የሚሆነው በምን ተሰልቶ ነው? እኛ ትንሽ ተማርን የምንል ሰዎች  ይህንን መለየት የሚከብድ አይመስለኝም ምክንያቱም ቅዱስ ቅብአት የምንለው እንዳለ ሁሉ ቅዱስ ያልሆነ ቅብአትም አለና፡፡ ስለዚህ ቅብአት ማለት መንፈስ ቅዱስ ነው ካልን ቅዱስ ያልሆነው ቅብአትም መንፈስ ቅዱስ ነው ልንል ነው ማለት ነው፡፡ ገበያ ወጥታችሁ ቅብአት ስትገዙ መንፈስ ቅዱስን ገዛችሁ ማለት ነው በእናንተ ቤት፡፡ ራሳችሁን ፊታችሁን ቅብአት ስትቀቡ መንፈስ ቅዱስን ተቀባችሁ ማለት ነው በእናንተ ቤት፡፡ ይኼ ከንቱ ትርጓሜ ነው እነርሱው የፈጠሩት የመንደር ትርጉም!
“በማኅጸነ ማርያም ከመንፈስ ቅዱስ በአብ ባይወለድ ኖሮ ወልድ እንደ አብ አይገዛም ነበር” የሚለው ክህደታቸው ውላጤን ሚጠትን ትድምርትን ህድረትን የያዘ ነው፡፡
አብ ባለበት ወልድና መንፈስ ቅዱስ፣ ወልድ ባለበት አብና መንፈስ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስ ባለበት አብና ወልድ እንዳሉ አለመረዳታቸው፡፡ ወልድ ሥጋን ለበሰ ሲባል ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ሥጋን የለበሰ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ቢለብስም ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ግን አልተለየም፡፡
ምሥጢራት ላይ ክፍተት እንዳለባቸው ያሳያል፡፡ “ወልደ አብ” የሚለው የክህደት መጽሐፋቸው አእማደ ምሥጢራትንና ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንን የሚያፋልስ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሃሳብ ያጠራቀመ የዐቃቤ ድግስ ነው፡፡ እሱን መጽሐፍ አንብቡት ኑፋቄያቸውን በሚገባ ትረዳላችሁ የሚጠቅሱትን ጥቅስ አንድ በአንድ በሚገባ ተመልከቷቸው ሃይማኖተ አበውንም ተመልከቱት ከዚያ የትኛው ትክክል እንደሆነ መርምሩ፡፡
በቅብአት ካህን የተጠመቀ ሰው ዳግመኛ መጠመቅ ይገባል አይገባም ለሚለው ጥያቄ መልሱ በደንብ ሆኖ ይገባል የሚል ነው፡፡ ጥምቀት አንዲት ናት አትደገምም አትሰለስም አትከለስም፡፡ ነገር ግን ፍትሐነገሥቱም ሃይማተ አበውም እንደሚለው ከመናፍቅ የተጠመቀ ቢኖር ዳግመኛ ይጠመቅ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱ ከመናፍቅ የተጠመቀ አማኒ አይደለም ይላል ስለዚህ አማኒ ለመሆን ምን ያስፈልጋል ስንል ጥምቀት ነው መልሱ፡፡ ስለዚህ ከቅብአት ካህን የተጠመቀ ሰው ዳግም መጠመቅ አለበት፡፡ ከዚህ በላይ ክህደት ምን አለ ወልድን ፍጡር እንለዋለን እያሉ እየመሰከሩ እየተከራከሩ! ከተዋሕዶ በኋላ መለኮትንና ሥጋን እየከፋፈሉ፡፡ ሎቱ ስብሐት!!!
በመጨረሻ መልእክት አለኝ›››››› “ወልደ አብ” የተሰኘው የኑፋቄ መጽሐፍ የታተመው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥር ባለች ቆጋ ኪዳነምሕረት ገዳም አሳታሚነት በ “መምህር” ገብረመድኅን እንዳለው አዘጋጅነት ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችሁም በምትችሉት አቅም ሁሉ ይህ ለምን እንደተደረገ በያላችሁበት አካባቢ ላሉ አባቶች በተለይ ለጳጳሳትና ለሊቃውንት ጉባኤ አባላት እንድታሳውቁና መፍትሔ በጋራ እንድንፈልግ አሳስባለሁ፡፡ ስለሁሉም ነገር ግን ጸሎት ያስፈልጋልና ሁላችሁም በጸሎት ቤተክርስቲያናችንን አስቧት፡፡ እኔም በሰው ኅሊና ከማይደረስበት መለኮት ጥቂት ነገሮችን ስጽፍ ስጨልፍ ባለማወቅ አጥፍቸ ተሳስቸ ከሆነ ወንድሞቸ አባቶቸ መምህሮቸ በመልካም ትምህርታችሁ አቅኑኝ።
ተፈጸመ፡፡

No comments:

Post a Comment