Friday, July 15, 2016

“ብራና እና ጥንታዊነት”


© መልካሙ በየነ
ሐምሌ 08/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በመጀመሪያ ሰላምታየን ላደርሳችሁ እወዳለሁ፡፡ አገራችን ማኅበራዊ መገናኛዎች ለፍርድ ቀርበው እስራት ተወስኖባቸው እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ሐምሌ 7 ቀን ከሰዓት በኋላ በተደረገው ችሎት የማኅበራዊ መገናኛዎች ጠበቃ እጅጉን በመከራከር ከእስራቱ በዋስ እንዳስፈታቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን ወደፊት እንደአስፈላጊነቱ ሊታሠሩ እንደሚችሉ ጠበቃቸው አልሸሸገም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ከእስራት ተፈተዋል ከዘመዶቻችን ከወዳጆቻችን ጋር ለማገናኘት አብቅተውናል የተለመደ ሥራቸውንም በይፋ ጀምረዋል፡፡ እኛም ሥራችንን ጀመርንባቸው፡፡


እንግዲህ ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡ ዛሬ የምንመለከተው “ብራና እና ጥንታዊነት” የሚል ነው፡፡ አሁን ከዚህ ከወረቀት ዘመን ራቅ ላድርግና ወደ ጥንቱ የብራና ዘመን ልውሰዳችሁ፡፡ አባቶቻችን ይችን ጥንታዊ እምነታችንን ያቆዩልን ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምጸ አራዊቱን ግርማ ሌሊቱን ጸብአ አጋንንቱን ታግሰው በማስተማር እና ብራና ዳምጠው፣ ብርዕ ቀርጸው፣ ቀለም በጥብጠው ወዘተ መጻሕፍትን በመጻፍ ነው፡፡ በወቅቱ የወረቀት ፋብሪካ የለም የቀለም ማምረቻም መሣሪያ የለም ይህ ቢሆንም መጻሕፍትን ከመጻፍ አልቦዘኑም ነበር፡፡ ቀለም ሲያልቅባቸው ደማቸውን እንደቀለም እየተጠቀሙ ብራናውን አዘጋጅተው በዚያ ላይ ይጽፉ ነበር፡፡ ለዚህም ምስክር ይሆኑ ዘንድ በርካታ የብራና መጻሕፍት በተለያዩ ቦታዎች እናገኛለን፡፡ ዛሬ ቴክኖሎጅው ሲሻሻል ያንን በብራና ላይ ጽፈውት የነበረውን ትምህርት በወረቀት ላይ አሰፈሩት፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባው ወረቀቱ የተቀዳው ከብራናው መሆኑን ነው፡፡ ብራናው ሌላ ወረቀቱ ሌላ የሚናገሩ ከሆነ ግን ሌላ ችግር ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ ይህን ርእስ ለምን አነሣው እንዳትሉኝ የቅብአት እምነት ተከታዮች ሃይማኖተ አበው እዚህ ክፍል እዚህ ምእራፍ እዚህ ቁጥር ላይ እንዲህ ይላል ስንላቸው የብራናው እንዲህ ነው የሚል እያሉ ሰውን ለማደናገር ይፈልጋሉ እና ይህን ርእስ ማንሣት አስፈለገኝ፡፡ እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ወረቀቱ የያዘው ብራናው የያዘውን ነው፡፡ ምክንያቱም ከብራናው ወደ ወረቀቱ ተገለበጠ እንጅ አልተቀነሰም አልተጨመረም፡፡ ልብ በሉ የብራናው ጽሑፍ ጥንታዊነቱን ሊያሳይ የሚችል አይደለም፡፡ የወረቀት መጻሕፍትን ጥንታውያን አይደሉም ልንላቸው አንችልም ምክንያቱም ወረቀቱ ጥንታዊ አይደለም እንጅ የያዘው ትምህርት ጥንታዊ ነውና፡፡ የብራና መጻሕፍት በሙሉ ጥንታውያን ናቸው ማለት አይቻልም ምክንያቱም በብራና መጻፍ ጥንት ተጀመረ እንጅ የሚይዙት ቃል በሙሉ ጥንታዊ ትምህርተ እምነት ነው ሊባል አይችልምና፡፡ መግባባት የሚገባን ጉዳይ አለ እርሱም ብራና እንዴት ይዘጋጃል ከምን ይዘጋጃል የሚለው ነጥብ ላይ ነው፡፡ የብራና አዘገጃጀት በብራና ላይ መጻፍ (የቁም ጽሕፈት የምንለው) ዛሬም ድረስ እንዳለ እናውቃለን፡፡ ፍየሎች እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገጽ እስካልጠፉ ድረስ ብራና ዝግጅት ይኖራል በዚያ ላይም መጻፍ እንደዚያው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጥንት የነበሩት ፍየሎች ዛሬም አሉ ከነቆዳቸው ከነሥጋቸው ማለት ነው፡፡ ድሮ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ብራናው ይዘጋጃል ቀለሙ ይበጠበጣል ብርዑ ይቀረጻል ከዚያም በተዘጋጀው ብራና ላይ የምንፈልገውን ነገር እንጽፍበታለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብራና ስለሆነ ብቻ ጥንታዊ ነው ልንለው የምንችልበት ምንም ምክንያት የለንም፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ እነርሱ የሚጠቅሱት የብራና መጽሐፍ የሚገኘው ደብረወርቅ እና ጎንቻ ሲሶ እነሴ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ የደብረ ወርቅ ሰው ቆዳን እንዴት እንደሚሠሩት እንዴት ለአገልግሎት እንደሚያበቁት ብታዩ ብራና ማውጣት ቀላላቸው እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፡፡ የወንዙን ስም ባላውቀውም ከከተማው ወጥታችሁ ወደ ሞጣ መስመር ስትጓዙ አንድ ድልድይ ታገኛላችሁ፡፡ ያንን ወንዝ ተከትላችሁ ብትሄዱ ሜዳው በሙሉ ቆዳ ተወጥሮበት ታገኛላችሁ ይህ የበሬ እና የላም ቆዳ ነው፡፡ ይህን በውኃ የተነከረ ቆዳ አልፍተው ወጥረው በጸሐይ አድርቀው ፍቀው ጉሎ ቀብተው ለአገልግሎት ያበቁታል፡፡ ያንን በዓይናችሁ ትመለከታላችሁ ያ ካልተሳካላችሁ ደግሞ ከደብረ ወርቅ መናሀሪያ የሚወጡትን መኪኖች ተመልከቱ ጭነው የሚወጡት ብፌ አይደለም ወይም ሶፋ አይደለም ቆዳ ነው፡፡ ታዲያ ይህን እንዲህ አድርገው አሳምረው የሚሰሩ ደብረወርቆች ትንሿን የፍየል ቆዳ ብራና ማድረግ እንዴት ይሳናቸዋል? ስለዚህ ዛሬም ድረስ በብራና ላይ ይጽፋሉ ይደጉሳሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ብራና ላይ የተጻፈ ጽሑፍ ሁሉ ጥንታዊ ነው ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል፡፡ ትክክለኛ የብራና መጻሕፍት እኮ በየገዳማቱና በየአድባራቱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የቅብአት መናፍቃኑ የሚጠቅሱት ግን ደብረወርቅና ጎንቻ ብቻ የሚገኙ መሆናቸው መጻሕፍቱ ችግር እንዳለባቸው ያመላክታል፡፡ በወረቀት የጻፉትን “ወልደ አብ” የተሰኘ የምንፍቅና መጽሐፋቸውን በብራና መጻፍ አይችሉምን? በጣም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ብራና የምትሉትን ነገር ቆም ብላችሁ ብታስቡት ይሻላል፡፡ የብራና መጻሕፍትን ይነቅፋል እንደሚሉኝ አልጠራጠርም፡፡ እኔ ግን ወረቀትም ሆነ ብራና የያዘው ትምህርት የተዋሕዶን ነገር የማያስረዳ ከሆነ እነቅፈዋለሁ ምክንያቱም ትምህርቱ እንጅ ቆዳው ወይም ወረቀቱ አይደለምና የሚነቀፈው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሊቀሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ ቃለ ጽድቁ ለአብ የሚለውን መጽሐፍ በማዘጋጀታቸውና ኑፋቄያቸውን በማጋለጣቸው አንድ ማንም የማያውቀውን እነርሱ ብቻ የሚያውቁትን የብራና መጽሐፍ ጠቅሰዋል ምእራፍና ቁጥር የሚባል ነገር የለም ብራናው እንዲህ እንዲል ብቻ ነው የሚሉት፡፡ ፎቶውን ተመልከቱት ይህ የቄርሎስ ድርሳን የሚሉት ከየት የተገኘ እንደሆነ ከእነርሱ ውጭ ማንም አያውቀውም፡፡

No comments:

Post a Comment