© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 25/2009
ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እናንተ አንባቢዎች ሆይ! ከዚህ ጽሑፍ ጋራ የተያያዘውን ቪዲዮ ተመልከቱና
እውነቱን ፍረዱ፡፡ በሁለቱም ቦታዎች ላይ ሁለቱም ሰባኪዎች ያነሷቸው ጉዳዮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ከታች ያስቀመጥሁላችሁንም ሊንክ
ተጭናችሁ የእኔን ጽሑፍ ሙሉውን አንብቡት፡፡
1ኛ. አብማ ማርያም አትቁረቡ ክርስትና አታስነሡ ብሏል፡፡ የአብማ ማርያም
አገልጋይ ካህናትም በሙሉ ክህነት የላቸውም ሁሉም ቅባቶች ናቸው በሏል የሚል ነው፡፡
2ኛ. ከምሥራቅ ጎጃም ሊቀጳጳስ መሾም መመረጥ የለበትም ብሏል የሚሉ
ናቸው፡፡
3ኛ. ሊቃውንቱን የእምነት ህጸጽ አለባቸው ብሏል የሚሉ ናቸው፡፡
እኔ ግን ይህንን አላልኩም ወደፊትም አልልም፡፡ ምክንያቱም አብማ ማርያም
እኮ ቤተክርስቲያናችን ናት፡፡ ቤተክርስቲያናችን ደግሞ ቅባት አይደለችም ተዋሕዶ እንጅ ግለሰቦች ላይ ነው ይህ ችግር የሚገኘው፡፡
አንዳንድ ካህናት በዚህ በቅባት እምነት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ደግሞ ከእኔ ይበልጥ ራሳችሁ አሳምራችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ ቅባት
የሆነ ቢያንስ አንድ ካህን አለ አልኩ እንጅ አብማ ማርያም ቅባት ናት አላልኩም ወዴት ጠጋ ጠጋ ነው፡፡ እኔ አብማ ማርያምን ያነሣሁት
ከዚህ ጋራ በተያያዘ ጉዳይ አልነበረም በርግጥ እነርሱ በተረዱበት መጠን ልናገር ብየ እንጅ፡፡
ከምሥራቅ ጎጃም ሊቀጳጳስ መሾም መመረጥ የለበትም አላልኩም አልልምም፡፡
እኔ ምን አገባኝና ማንስ ሆኘ ነው በእግዚአብሔር አሠራር ውስጥ ገብቼ ልፈተፍት የምችለው፡፡ እኔ ያልሁት ምሥራቅ ጎጃም አካባቢ
የተወለዱት ጳጳሳት እዚህ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ላይ በሊቀጳጳስነት አይመደቡ ነው፡፡ ይህን የምልበት ምክንያት ደግሞ ከዚሁ
ከእምነቱ ጋራ አያይዠ ስላየሁት ነው፡፡ አባ ማርቆስ ዝዋይ በቆሞስነት ሳሉ እኮ ይሠሩት የነበረውን ሥራ አሁን እዚህ በሊቀጳጳስነት
ሆነው አልሠሩትም፡፡ እዚህ የአገር ልጅ የወንዝ ልጅ የሚል አጉል ኮተት ይከተላል ሌላ ቦታ ቢሆኑ ግን በሚገባ ያስተምራሉ ይሠራሉ፡፡
እዚሁ ተወላጅ የሆነ ከሆነ ግን ምን ተምረሃል ሳይሆን የት ወረዳ ነህ መባባል ይመጣል፡፡ ከዚህ አንጻር ይህንን አልኩ እንጅ መሾምማ
እንዴት አይሾሙም ታላላቅ ሊቃውንት የወጡበት አገር ጎጃም እኮ ነው፡፡ ስረሳ ብውል አቡነ ቴዎፍሎስን እንዴት እረሳቸዋለሁ ሊቃውንቱንስ
ቢሆን እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን እነ አለቃ አያሌው ታምሩን እንዴት ከኅሊናየ ላጠፋቸው እችላለሁ አልችልም፡፡
እውነተኞቹን ሊቃውንቱ የእምነት ህጸጽ አለባቸው ያልኩበት ቦታ የለም
አልልምም፡፡ ነገር ግን በካባ ብቻ ሊቅ ናቸው ማለት ይከብደኛል፡፡ በነገራችን ላይ ሊቅነት እና እምነት አንድ አይደሉም አዋቂነት
እና እምነት አንድ የሚሆኑለት ሰው እርሱ ብጹእ ነው፡፡ ግን አርዮስን ያህል ሊቅ የለም ነበር ግን ምን አለ “ወልድ ፍጡር በመለኮቱ”
ሎቱ ስብሐት፡፡ አዚህ የምናያቸው “ወልደ አብ” ን ያሳተሙት ገብረ መድኅን እንዳለው እኮ ሊቅ ናቸው፡፡ ግን ሊቅነታቸው እንደ አርዮስ
ነው፡፡ ስለዚህ እውቀትን ወይም ሊቅነትን ከሃይማኖት ቀጥተኛነት ጋራ አታያይዙት፡፡ እነዚያማ እነ አለቃ አያሌው እነ መልአከ ብርሃን
አድማሱ ናቸው፡፡
አብማ ላይ መግለጫ የሰጡትን በአካል አላውቃቸውም በርግጥ እምነታቸውም
ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ቅባት የሚባል አላውቅም ብለው ስለካዱ ግን እጠራጠራቸዋለሁ፡፡ ቅባት ከሌለ “ወልደ አብ” እና “ሚሥጢረ
ሃይማኖት” የሚሉ መጻሕፍት ማን አሳተማቸው በሉ መልሱልኝ፡፡ በስም የጠቃቀሷቸውን መምህራንን እና ሊቃውንትን እኔ በምንም ጉዳይ
አላነሣኋቸውም እርስዎ ነዎት ያነሷቸው፡፡ አሁንም እኮ “ተዋሕዶ” ብለው ሲጠሩ ድምጽዎትን በጣም ቀንሰው ነው ለምን ቀነሡት ግን፡፡
ይህንን የሚጽፈው ሰው ቅባት ይሆናል ብለው ለማጠራጠር ሞክረዋል ቅባትማ ቅባት የለም ብሎ የሚክድ ሰው ነው፡፡ ቅባት ለመኖሩ እኮ
ሁለቱን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት የታተሙትን መጥቀስ በቂ ነው፡፡
ገዳመ አስቄጥስ ላይ የተናገሩትን ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡
ተዋሕዶን አስተምረው ምእመናንን በተዋሕዶ እምነት ያጸናሉ ብለን ተስፋ ያደረግንባቸው መምህር ነበሩ አሁን ግን የታዘዝኩትን ነው
የምሠራ በሚል ምን እንደተጻፈ እንኳ ሳያነቡ መድረክ ላይ በስማ በለው ብቻ ሲያወሩ ሳይ አዘንሁላቸው፡፡ ሊቀ ሊቃውንት በእውነት
ለእምነትዎ የሚጨነቁስ ከሆነ “ወልደ አብ” የተባለውን ቅባቶች ያሳተሙትን መጽሐፍ እንደሰጠንዎ በሚገባ አንብበው መልስ በሰጡበት
ነበር ግን ምን ይሆናል፡፡ ለማንኛውም የጀመሩትን መንጃ ፈቃድ ያውጡና እዛው በሹፌርነት መኖሩ ይሻላል፡፡
ሁለቱም የቅባት መጻሕፍት የታተሙበትን ቦታ የቅዱሳን መገኛ ነው እያሉ
ብዙ ጊዜ ደጋግመው ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ አባታችን ይህን ቦታ የቅዱሳን መገኛ ነው ካሉ ታዲያ ምን እንጠብቃለን ቅባት ናቸው ብንል
እኮ ፍርድ የለብንም፡፡ ይህንንም ከዚሁ ጋራ አያይዠላችኋለሁ ተመልከቱት፡፡
እኔ የጻፍሁትን ጽሑፍ ሙሉውን ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ተጭናችሁ አንብቡ እና አመዛዝኑት፡፡