© መልካሙ በየነ
ሐምሌ 18/2009
ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
የሰው ልጅ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ይበዙበታል፡፡
ደስታ እና ሀዘን፣ ሳቅ እና ለቅሶ፣ ልደት እና ሞት፣ ጥጋብ እና ረሀብ፣ ብልጽግና እና ንድየት፣ ሰላም እና ሽብር፣ ጸጥታ እና
ሁካታ፣ ቅድስና እና ርኩሰት፣ ንስሐ እና ኃጢአት፣ ምረቃ እና እርግማን
ብቻ ጥንድ ጥንድ ነገሮችን በጉያው የታቀፈ ፍጥረት ነው ሰው ማለት፡፡ ወደ ርእሰ ጉዳየ ስገባ ደስታ የሚገኘው ከየት
እና እንዴት ነው በሚለው ዙሪያ ጻፍ ጻፍ ሲለኝ ጊዜ ነው ብዕሬን ለማንሣት የተገደድሁት፡፡
ደስታን በደስታነቱ ለማጣጣም ከፈለግህ
ደስታን ራስህ ፍጠረው፡፡ የደስታ ምንጭህ እንዳይደርቅ ደግሞ ከአምላክህ ጋራ በሰላም ኑር፡፡ ከአምላክህ ጋራ በሰላም ከኖርህ ማለትም
ፈጣሪህን በመፍራት ቃሉን በመጠበቅ ከኖርህ የደስታ ምንጮችህ ብዙ ይሆናሉ፡፡ የደስታ ምንጮችህ ብዙ ይሆናሉ ማለት ግን ሀዘን ችግር
መከራ ሰቆቃ ፈጽመው አይደርሱብህም ማለት አይደለም፡፡ አስቀድሜ እንደነገርኩህ ደስታ ካለህ ሀዘን መከራ እንደሚኖርብህም ማዎቅ ይኖርብሃል፡፡
ከፈጣሪ ጋራ ስትሆን ልዩ የሚሆነው ነገር ምን መሰለህ ሀዘን መከራ ስቃዩ በራሱ ደስታ የሚሰጥህ መሆኑ ነው፡፡ ሰማዕታት የዚህን
ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ስለመንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ አይደል ያለው ሊቁ አባ
ኤፍሬም፡፡ ሰማዕታት ደስታ የሚፈጥርላቸው በዚህ ዓለም መኖራቸው አይደለም ስለእግዚአብሔር መከራ ሀዘንን መቀበላቸው እንጅ፡፡ ለሰማእታት
ደስታቸው ስለመንግስተ ሰማያት መራራ ሞትን መታገስ መቻላቸው ነው፡፡ የሰማዕታት ደስታቸው ስጋቸውን ለእሳት ደረታቸውን ለጦር ለጠጠር
አንገታቸውን ለስለት አሳልፈው መስጠት መቻላቸው ነው፡፡ ደስታን ደስታየ ነው የምትለው ከእግዚአብሔር ጋር እንድትኖር ካስቻለህ ብቻ
ነው፡፡
አንድ ጥሩ አባባል አለ የማን እንደሆነ
ግን አላውቀውም፡፡ በእንግሊዝኛ የተጻፈ ነው እኔ ግን በገባኝ መጠን እንዲህ እተረጉመዋለሁ “ጽጌረዳ አበባን ለመቁረጥ በእሾኽ መወጋት ግድ ነው” የሚል መንፈስ ያለበት
ነው፡፡ የደስታን ጽጌረዳ ለመቁረጥ በሐዘን በመከራ በስቃይ እሾኽ መወጋት ግድ ይልሃል፡፡ ጽጌረዳን ቆርጠህ ጥሩ መዓዛውን በአፍንጫህ
ለማጣጣም ከፈለግህ የግድ በእሾኽ ተወግተህ አበባውን መቁረጥ ይኖርብሃል፡፡ እንዲህ በመከራ ተፈትነህ የቆረጥከው አበባ መዓዛውም
ልዩ ይሆንልሃል ያኔ መጠን የሌለው ደስታ በልብህ ይመላል፡፡ ሰዎች ነገር ይሰሩብሃል በሀሰትም ይከስሱሃል ሊደበድቡህና ሊገድሉህም
ይችላሉ በዚህ ሁሉ ግን ከፈጣሪህ ጋር አብረህ ሁን፡፡ ስንክሳሩን ስታነበው “በሰላም ዐረፉ” የሚባልላቸው ቅዱሳን በጣም ጥቂቶቹ
ናቸው፡፡ አብዛኞቹ በእሳት የተፈተኑ በፈላ ውኃ የተጣሉ፤ ወደ ገደል የተወረወሩ ለአውሬ የተሰጡ፣ በሰይፍ የተቀሉ በስለት የታረዱ
ናቸው፡፡ ይህን እያነበብህ የቅዱሳኑን የደስታ ምንጭ ማዎቅ ካልቻልህ ለራስህ ደስታን መፍጠር አትችልም፡፡
መከራህ እንደዓባይ በረሃ የተጥመዘመዘ
አላልቅ ብሎ ትዕግስትህን የሚፈታተን ሊሆንብህ ይችላል፡፡ ነገር ግን እፎይ የምትልበትን ቦታ ማግኘትህ አይቀርም፡፡ ምንም እንኳ
ችግርህ ከደጀን አፋፍ ጀምሮ ሙሉ የዓባይን በረሃ ሁሉ የሚያንከራትትህ ቢሆንም ቅሉ ጎሐጽዮን ላይ ደርሰህ ነፋሻማውን አየር እያጣጣምህ
እፎይ ልትል ጊዜ አለህ፡፡ በዚህ የችግር በረሃ መካከል ላይ ሆነህ ተስፋ አትቁረጥ እንዲያውም የመንገድህን ጠመዝማዛነት እና ፈታኝነት
እየተመለከትህ ደስታን ለራስህ ፍጠርለት፡፡ በተቃራኒው ከጎሐ ጽዮን ተነሥተህ በችግር በረሃው በዓባይ በረሃ ውስጥ በሙቀቱ በሐሩሩ
ብትፈተንም ደጀን አፋፍ ላይ ደርሰህ እፎይ ልትል አምላክህ ጊዜ ሰጥቶሃል፡፡ በችግር በመከራ ውስጥ በወደቅህ ጊዜ ከፊትህ የደስታ
ሰላም እንዳለ አትዘንጋ፡፡ ህዝበ እስራኤላውያን ወደ ምድረ ርስት ለመግባት ሲንቀሳቀሱ ከፊታቸው የኤርትራ ባሕርን እያሰቡ ነው፡፡
የኤርትራ ባሕር በሙሴ አማካኝነት ባይከፈልላቸው ኖሮ ከኋላቸው የሚከተላቸው የፈርዖን ጦር ደስታቸውን በነፈጋቸው ነበር፡፡ ነገር
ግን አምላክ ደስታቸውን በውስጣቸው ጨመረላቸው እና በሙሴ በትር ተአምር ተደረገ ድንቅ ሥራ ተሠራ፡፡ አየህ ይኼኔ “ስቡሐ ዘተሰብሐ”
ብለህ በደስታ ከበሮህን ይዘህ በፈጣሪህ ፊት ትዘምራለህ፡፡
ሰዎች ደስታህን ሊነጥቁህ ሲያስቡ እነርሱ
ባደረጉብህ ነገር ደስታን ለራስህ ፍጠር፡፡ እነዚህ ሰዎች ከኮርኒስ ላይ ልጇን እንደምታጫውት ዓይጥ አንተ በአልጋህ ላይ መተኛትህን
የማያውቁ እረፍትን ነሽዎች ናቸውና ኮርኒስህን በመደብደብ ልታባርራቸው አትሞክር፡፡ ምክንያቱም እነርሱም ቢሆኑ እንቅልፍ የላቸውምና፡፡
እነዚህ የኮርኒስ ላይ ዓይጦች ደስታህን እንዲነጥቁህ ዕድሉን አትስጣቸው በፍጹም! አንተ በደስታ አልጋህ ላይ ተኝተህ እነርሱ ግን
እንቅልፍ ስለሌላቸው ኮርኒስህ ላይ እየተሯሯጡ ሊናድዱህ እና እረፍትህን ሊቀሙህ ይሞክራሉ፡፡ ያልሰማህ መስለህ ዝም በላቸው ያኔ
ራሳቸው ደክመው ዝም ይላሉ፡፡ በፍጹም ልታባርራቸው አትሞክር እንዲያውም እሰይ በርቱ እያልህ አጨብጭብላቸው ያኔ ደስታን ላንተ የፈጠሩ
ስለሚመስላቸው ዝም ይላሉ፡፡ በአንተ ላይ ክፉ ይሥሩብህ መዓት ያውርዱብህ አንተ ግን ከፈጣሪህ ጋር ሆነህ ለቅዱሳኑ የሰጣቸውን ደስታ
አንተም በመጠን ተቀብለህ ኑር::
No comments:
Post a Comment