Tuesday, November 28, 2017

መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? ክፍል ፲፩



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፳፭ ጀምረን  ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡


ለእመቤታችን ዓመታዊ በዓል እንኳን አደረሳችሁ!




ካሳሁን ምናሉ በዚህ በክህደት መጽሐፉ ገጽ ፳፭ እና ፳፮ ላይ የጻፈውን ነገር ሁላችሁ ተመልከቱት፡፡ አንብቡት እኔ ከዚህ በፊት “ወልደ አብ” ላይ ይህንኑ ራሱን መልስ ስለሰጠሁበት ባለፈው የሰጠሁትን መልስ ለዚህ በሚመጥን መልኩ አቀርብላችኋለሁ፡፡ 

የተዋሕዶ ልጆች እኛ አብን ወላዲ አስራጺ፣ ወልድን ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስን ሰራጺ ብለን እናምናለን፡፡ እነርሱ ቅባቶች ደግሞ ከዚህ በተጨማሪ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ይላሉ፡፡ በስም በግብር በአካል በገጽ ስንመለከት አብ አብን እንጅ ወልድን እና መንፈስ ቅዱስን አይሆንም፡፡ ወልድም ወልድን እንጅ አብን እና መንፈስ ቅዱስን አይሆንም፡፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስን እንጅ አብን እና ወልድን አይሆንም፡፡ (አብ) አብ የተባለበት ጥንት የሌለው ጊዜ፤ (ወልድ) ወልድ ከተባለበት (መንፈስ ቅዱስም) መንፈስ ቅዱስ ከተባለበት ጥንት ከሌለው ጊዜ አይቀድምም አይከተልምም፡፡  (ወልድ) ወልድ የተባለበት ጥንት የሌለው ጊዜ፤ (አብ) አብ ከተባለበት (መንፈስ ቅዱስም) መንፈስ ቅዱስ ከተባለበት ጥንት ከሌለው ጊዜ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ (መንፈስ ቅዱስ) መንፈስ ቅዱስ  የተባለበት ጥንት የሌለው ጊዜ፤ (አብ) አብ ከተባለበት (ወልድም) ወልድ ከተባለበት ጥንት ከሌለው ጊዜ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ይህ ሦስትነት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የአካል  መጠሪያ ስም ነው፡፡ አብ የራሱ የሆነ የተለየ አካል አለው ወልድም እንዲሁ መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ፡፡ የአካል መቀላቀል የአካል አንድ መሆን የአካል ተዋሕዶ የላቸውም “ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት” እንዲል፡፡ ስለዚህ በአብ ስም ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም፡፡ በወልድ ስምም አብ እና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ስምም አብ እና ወልድ አይጠሩበትም፡፡ ምክንያቱም አካላቸው ለየራሳቸው ነውና አንድም በባሕርይ እንጅ በአካል አንድነት የላቸውምና አንዱ በሌላኛው ስም አይጠሩበትም፡፡
ሌላው የአካል የግብር ሦስትነት ነው፡፡ ሥላሴ በአካል ግብር ሦስትነት የየራሳቸው የሆነ ስም አላቸው፡፡ ይህም ወላዲ፤ ተወላዲ፤ ሰራጺ ነው፡፡  አብ ወላዲ ቢባል እንጅ እንደ ወልድ ተወላዲ እንደመንፈስ ቅዱስ ሰራጺ አይባልም፡፡ ወልድም ተወላዲ ቢባል እንጅ እንደ አብ ወላዲ እንደመንፈስ ቅዱስ ሰራጺ አይባልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ሰራጺ ቢባል እንጅ እንደ አብ ወላዲ እንደ ወልድ ተወላዲ አይባልም፡፡ የአካል ግብር ስም አንዱ ለአንዱ አይሰጥም አንዱ በአንዱ አይጠራም፡፡ አብም ወላዲ ሲባል ይኖራል ወልድም ተወላዲ ሲባል ይኖራል መንፈስ ቅዱስም ሰራጺ ሲባል ይኖራል እንጅ አንዱ ለአንዱ መጠሪያ አይሆንም፡፡ በአካል ግብር ስም መቀላቀል እና መፋለስ የለባቸውም፡፡ ምንም እንኳ ሥላሴ በባሕርይ በአገዛዝ በሕልውና በመፍጠር በማሳለፍ አንድ ይሁኑ እንጅ በወላዲነት በተወላዲነት በሰራጺነት ግን አንድ አይደሉም፡፡ በመለኮት በባሕርይ አንድ ናቸው ብለን አብ ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ ፤ ወልድ ወላዲ  ተወላዲ ሰራጺ፤ መንፈስ ቅዱስ ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ አንልም፡፡



በቅብዓት አስተምህሮ ውስጥ ግን እኛ የማንቀበለው “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚል የአካላት የግብር ስም አላቸው፡፡ ይህም የአካላት የግብር ስም አንዱ ለአንዱ መሆን ይችላል፡፡ መፋለስ እና መቀላቀልም አለበት፡፡ በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ይህ የሥላሴ የግብር ስም ተፋልሶ አለበት፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን የካሳሁን ምናሉ የክህደት መጽሐፍ ነው፡፡ ገጽ ፳፭ ላይ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ናቸው” ይልና ዝቅ ብሎ ደግሞ በመለኮታቸው ሁሉም ቀባዒ ናቸው ብሎ ይደመድማል፡፡ ይህ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው እንዴት በሉኝና እናብራራው እስኪ፡፡
የሚገርማችሁ በመጀመሪያ አካባቢ ከቅባቶች ጋር ስንነጋገር “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ብቻ ነበር ያሉን፡፡ ከዚያ መጽሐፋችሁ እንዲህ ይላል እኮ ደግሞስ ቄርሎስ  ስምዐት ፻፳፬÷፴፬ “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ …ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ..” ይላልሳ፡፡ “ለሊሁ ቀባዒ” የተባለ ማንን ነው ስንላቸው ወልድን ነው አሉን፡፡ ታዲያ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ለምን ትላላችሁ አልናቸው፡፡ እነርሱ ግን በባሕርይማ አንድ ናቸውና ሁሉም ቀባዒ ናቸው “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የምንል በሥጋ ርስት ብቻ ነው አሉ፡፡ ስለዚህ “አብ ቀባዒ ወልድ ቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቀባዒ” ናቸው ይላሉ ብለን ደመደምን፡፡ ይህንን ድምዳሜያችንንም በመጽሐፋቸው ላይ አገኘነው፡፡ “አብ ቀባዒ ወልድ ቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቀባዒ” የሚሉት በመለኮት አንድ ስለሆኑ ነው በሥጋ ደግሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ እንደምረዳው ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት አንድ አይደለም እያሉ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ደግሞ “ወልድ ፍጡር” ያለውን አርዮስን ያደርጋቸዋል ማለት ነው፡፡ አስቡት ለሥላሴ አካል የግብር ስማቸው አንድነት አለው ማለት ነው በቅባቶች አስተምህሮ፡፡ ይህ ማለት “አብ ቀባዒ መለኮት ወልድ ተቀባዒ መለኮት መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ መለኮት” በማለት የመለኮትን አንድነት ወደ ሦስትነት የሚከፍል አስተምህሮ ነው ያላቸው፡፡ ምክንያቱም “ቀባዒ ተቀባዒ ቅብዕ” የሚለው የባሕርይ ግብራቸው አይደለምና፡፡ የባሕርይ ግብር ከሆነ በሥጋ ርስት በመለኮት ርስት በምንም ዓይነት ርስት ውሰዱት አንድ ነው አይለወጥም አይቀየርምም፡፡ እነርሱ ግን በመለኮት ርስት ሁሉም “ቀባዒ” ናቸው በሥጋ ርስት ድግሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ናቸው ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ!!! ቀባዒ መለኮት አብ በሥጋ ርስት ቀባዒ ሆነ፤ ቀባዒ መለኮት ወልድ በሥጋ ርስት ተቀባዒ ሆነ፣ ቀባዒ መለኮት መንፈስ ቅዱስ በሥጋ ርስት ቅብዕ ሆነ ማለታቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሐሰት ክህደትም ነው፡፡ “ቅብዕ” ማለት ቀጥተኛ ትርጉሙ “ክብር” ማለት ነውና፡፡ አብ ቀባዒ ሲሉ አብ አክባሪ ወልድ ተቀባዒ ሲሉ ወልድ ተከባሪ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሲሉ መንፈስ ቅዱስ ክብር ሆኑ ማለት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚለው ስም የአካል ስም ነው፡፡ ታዲያ በአካል አንዱ አክባሪ አንዱ ከባሪ አንዱ ክብር ይሆን ዘንድ ይህን ክህደት ማን አስተማራችሁ ብለን እንጠይቃቸው እስኪ፡፡
ከዚህ ስህተታቸው የምንረዳው ነገር የሚከተለውን ነው፡፡
፩. የአካላት ግብር ስም ሁለት ጊዜ እንደተሰጣቸው ነው፡፡ ዘመን ሳይቆጠር ቀድሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቀባዒ” ነበር ማለት ነው፡፡
፪. ድኅረ ዓለም ወልድ በሥጋ ማርያም በተገለጠ ጊዜ ደግሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ሆኑ ማለት ነው፡፡
፫. ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ምእራፍ ፪ ቁጥር ፻፶፬ ላይ “ለአጽንዖተ ክልዔሆሙ፤ አብን መንፈስ ቅዱስን በጥንተ ስማቸው ለማስጠራት በጥንተ ግብራቸው ለማጽናት” የሚለው ትምህርት ተቀባይነትን አላገኘም ማለት ነው፡፡
፬. አብ ከቀባዒነት ወደ ቀባዒነት፤ ወልድ ከቀባዒነት ወደ ተቀባዒነት፤ መንፈስ ቅዱስ ከቀባዒነት ወደ ቅብዕነት እንደተለወጡ የሚያሳይ መሆኑ፡፡
ስለዚህ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚለው የግብር ስም በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ተቀባይነት የሌለው ከንቱ ፍልስፍና ነው፡፡ ስለዚህ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” ብለን አባቶቻችን እንዳስተማሩን እንዲህ እናምናለን፡፡ እንዲህም እንታመናለን፡፡

#ይቀጥላል

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፳ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment