Friday, December 30, 2016

“እርሷ እናቴ ናት!”


© መልካሙ በየነ
ታህሳስ 21/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
የሰማያዊው ንጉሥ የመድኅን ክርስቶስ እናቱ የሆነች ድንግል በክልኤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥም አጠራሯ ከፍ ከፍ ይበልና እናቴ መመኪያ ዘውዴ የመወደድ ግርማ ሞገሴ እርሷ ናት፡፡ በብርሃን መውጫ ምሥራቅ የተመሰለች እውነተኛ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ከሩቅ እንደ ፋና የምታበራ ለእውራን ብርሃናቸው ለኃንካሳዎችም ምርኩዛቸው ለተራቡትም ምግባቸው ለተጠሙትም መጠጣቸው እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ሰባ ስምንት ሰዎችን የበላውን የበላኤ ሰብእን ነፍስ አማልዳ ገነትን እንድትወርስ ያደረገች የበላኤ ሰብእ እመቤት እርሷ እናቴ  ናት፡፡ የሌሊቱ ጨለማ የተገፈፈባት እውነተኛ ብርሃን ያየንባት የእርቅ ምልክታችን የመግባቢያ ሰነዳችን እርሷ እናቴ  ናት፡፡ የአዳም ፍዳ እንደ ደንጊያ ከላያችን ላይ ተጭኖ የቅድስና ሰማይን ቀና ብለን እንዳናይ ሲያደርገን ፈጥና ደርሳ ከላያችን ላይ የወረወረችልን እርሷ እናቴ  ናት፡፡ በሄዋን ምክንያት የተድላ የደስታ ቦታችን ገነት ተዘግቶብን ለ5500 ዘመናት ያህል በእግረ አጋንንት ስንረገጥ እና ስንጠቀጠቅ ብንኖርም ዘመኑ ሲደርስ ገነትን ከፍታ ግቡ ያለችን ደግ እመቤት እርሷ እናቴ ናት፡፡ ስሄድ አብራኝ የምትሄድ ስጓዝ አብራኝ የምትጓዝ መንገዴን ቀድማ የምታስተካክልልኝ ከፊቴ ሆና የምትመራኝ እርሷ እናቴ ናት፡፡ በማድርበት የምታድር በእንግድነቴም የምታረጋጋኝ እና የምታጽናናኝ እርሷ እናቴ ናት፡፡ ማንነቴ የተመሠረተባት እኔነቴን ያወቅሁባት እርሷ እናቴ  ናት፡፡

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ፈርቶ እና አክብሮ “ትጸንሻለሽ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ” ብሎ ያበሠራት እርሷ እናቴ  ናት፡፡ የዓለም መድኃኒት አምላክን በበረት የወለደችው በጨርቅ የጠቀለለችው እርሷ እናቴ ናት፡፡ የሥላሴን አንድነት እና ሦስትነት በሚገባ ያስተማረችን ረቂቅ ምሥጢርን ያሳየችን እርሷ እናቴ ናት፡፡ እሳትን በማኅጸኗ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የተሸከመች እርሷ እናቴ ናት፡፡ እሳተ መለኮትን የታቀፈች ኀሊበ ድንግልናዋን ያጠባች እርሷ እናቴ ናት፡፡ ከሔሮድስ ሸሽታ የተወደደ ልጇን ይዛ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በግብጽ በረሃ የተሰደደችው የተንከራተተችው እግሯ በእሾህ እና በስለት ድንጋይ ደም ያጎረፈው እርሷ እናቴ ናት፡፡ የተወደደ ልጇ በማእከለ ምድር በቀራንዮ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በእንጨት መስቀል ላይ በአደባባይ ተሰቅሎ ባየችው ጊዜ መሪር እንባን ያነባችው ከመስቀሉ ሥር የተገኘቸው እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮሐንስ እነኋት እናትህ ብሎ የሰጠው እርሷንም አነሆ ልጅሽ ብሎ የሰጣት አዛኝቷ እመቤት እርሷ እናቴ ናት፡፡ እውነተኛ መብልን እና እውነተኛ መጠጥን ያስገኘችልን ቤተ ልሄም እርሷ እናቴ  ናት፡፡ በኃጢአት ስወድቅ በንስሐ የተነሣሁባት ምርኩዝ ድጋፌ እርሷ እናቴ ናት፡፡ ለተጠማ ውሻ በወርቅ ጫማዋ ውኃ ቀድታ የምትሰጥ ርኅርኅተ ልብ እመቤቴ እርሷ እናቴ ናት፡፡ ለኃጥአን የምትራራ አማልዳ ገነት መንግሥተ ሰማያት የምታገባ እመቤቴ እርሷ እናቴ ናት፡፡ መርኅ ለመንግሥተ ሰማያት የተባለች ገነት መንግሥተ ሰማያት እየመራች የምታገባ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ለጠፋው በግ አዳም መገኘት ምክንያት የሆነችው ንጽህት ዘር እርሷ እናቴ ናት፡፡ የአዳም መርገም ያላገኛት ከፍጡራን ሁሉ በላይ የሆነች ልዩ ዘር እርሷ እናቴ ናት፡፡ ስሟ ከማር ከወተት ይልቅ የሚጥመው እርሷ እናቴ ናት፡፡ ምግበ ሥጋ እና ምግበ ነፍስን ያገኘንባት የወርቅ መሶብ እርሷ እናቴ ናት፡፡ መላእክት የሰውን ልመና ወደ አምላክ ለማድረስ የሚወጡባት እና የአምላክን ምሕረት ቸርነት ረድኤት ለሰዎች ለማድረስ የሚወርዱባት የወርቅ መሰላል የመገናኛ ድልድይ እናታችን እርሷ ናት፡፡

መናፍቃን እና አጋንንት የሚርዱላት የሚንቀጠቀጡላት የመፈራት ግርማ ሞገስን የተጎናጸፈች እርሷ እናቴ ናት፡፡ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች የተባለላት የንጉሡ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርም እርሷ እናቴ ናት፡፡ ሙሴ በነደ እሳት ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ባያት ዕጽ የምትመሰል የመለኮት እናት ድንግል ማርያም እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ሳይተክሏት እና ውኃ ሳያጠጧት ለምልማ አፍርታ በተገኘችው በትረ አሮን የምትመሰለው እመቤቴ እርሷ እናቴ ናት፡፡ እውነተኛ ዝናም ያገኘንባት እውነተኛ ደመናችን ድንግል ማርያም እርሷ እናቴ ናት፡፡ ስለምናት ከዓይን ጥቅሻ ፈጥና የምትደርስልኝ የችግሬ ደራሽ እመቤቴ እርሷ እናቴ ናት፡፡

ፍቅሯ ያልገባችሁ መናፍቃን እና አጋንንት የምትሉትን በሉ እንጅ የእናቴ ስሟ በደሜ ውስጥ ይዘዋወራል ፍቅሯም በልቤ ጽላት ታትሞ ለዘላለም ይኖራል፡፡ ምክንያቱም በአርባ ቀኔ የበላሁት ሥጋ እና የጠጣሁት ደም ከእርሷ የተገኘውን ነውና፡፡ ደሟ ደሜ ሥጋዋም ሥጋየ ሆኗል፡፡ ስለዚህም እርሷ እናቴ ናት!!!!

Tuesday, December 20, 2016

“ድንቅ ነገር የተደረገብሽ ድንግል ሆይ!”

© መልካሙ በየነ

ታህሳስ 11/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ቅዱሳን ስለእናታችን ስለቅድስት ድንግል ማርያም አመስግነው እና አስተምረው፣ ሰብከው እና አመስጥረው፣ አርቅቀውና አጉልተው ተናግረው በዚህም አገልግሎታቸው ረክተው እና ጠግበው አያውቁም፡፡ ሌሊት በሰዓታቱ ንዒ እያሉ ተአምሯን እና ድንቅ ሥራዋን ሲያሰሙን እናታችንን ሲያመሰግኗት ያድራሉ፡፡ ጠዋት በኪዳኑም “ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል” ብለው እናታችንን ያነሧታል፡፡ በሰርክ በቅዳሴውም እናታችን ድንግል ማርያምን ያመሰግኗታል፡፡ እንግዲህ ካህናቱ እንዲህ ለ24 ሰዓታት ያህል አመስገነው ስሟን አንሥተው አይጠግቡም አይረኩምም፡፡ ምስጋናዋ የበዛላቸው እነ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴዋ እነ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴዋ እነ አባ ጊዮርጊስ በሰዓታቷ እነ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ እነ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ምስጋናቸው በብዙ አምሳል በብዙ መልክእ አመስግነዋታል፡፡ ሆኖም ግን አልጠገቡም አልረኩምም፡፡ ለምን ምስጋናዋን አልጠገቡም ቢሉ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ድንቅ ነገር ስለተደረገባት ነው፡፡ በእርሷ ድንቅ ነገር ተደርጓል ረቂቅ ምሥጢር ተፈጽሟል፡፡

ድንግል ሆይ ይህን ባንች የተደረገውን ድንቅ ምሥጢር ግለጭልኝ! ይህን ባንች የተደረገውን ረቂቅ ምሥጢር አጉልተሸ አሳይኝ! ድንግል ሆይ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እሳተ መለኮትን ከወዴት አስቀመጥሽው ብሎ ጠይቆሽ ነበር፡፡ ሁሉ የእርሱ ሁሉ በእርሱ የሆነን አምላክ እንዴት ወለድሽው ይህ ድንቅ ነገር እጹብ እጹብ ሲባል ይኖራል እንጅ በሥጋ ዓይን ረቂቅ ምሥጢር ነው፡፡ እናቴ ሆይ! ከሃና እና ከኢያቄም በዘር በሩካቤ እንድትወለጅ የፈጠረሽን አምላክ እንዴት ወለድሽው፡፡ ድንግል ሆይ! በምጥ በልብ ጋር ከሃና ማኅጸን የተወለድሽ ስትሆኝ ያለምጥ ያለልብ ጋር ፈጣሪን እንዴት አስገኘሽልን፡፡ ድንግል ሆይ! ከአባት እና ከእናት ስትወለጅ ቀድሞ ያለእናት ከአብ የተወለደውን ዛሬ ያለ አባት እንዴት ወለድሽው፡፡ ድንግል ሆይ! ሴቶች ሁሉ ድንግል ሆነው መውለድ የማይቻላቸው ሆኖ ሳለ አንች ግን በፍጹም ድንግልና አምላክን ለመውለድ በቃሽ ይህ ድንቅ ነገር እንዴት ተፈጸመልሽ፡፡ ድንግል ሆይ! ሰማይ መንበሩ ምድርም የእግሩ መረገጫ የሆነው አምላክ ማኅጸንሽ እንዴት ሊወስነው ቻለ፡፡ ድንግል ሆይ! ልብሱ እሳት ክዳኑ እሳት እየተባለ የሚመሰገነውን አምላክ በማኅጸንሽ ስትሸከሚው እሳተ መለኮቱ እንዴት አላቃጠለሽም፡፡ ድንግል ሆይ! ኪሩቤልና ሱራፌል ፈርተውና አፍረው ብርሃነ መለኮትህን ማየት አይቻለንም፤ እሳተ መለኮትህም ያቃጥለናል ሲሉ  ፊታቸውን በመስቀል ምልክት አመሳቅለው የሚያመሰግኑትን አምላክ ማኅጸንሽ እንዴት ተሸከመው፣ ያለበሽው ጨርቅስ እንዴት ልብስ ሆነው፡፡

ድንግል ሆይ! ባንች የተፈጸመው ድንቅ ነገር ለማንም ያልተደረገ ለማንም የማይደረግ ረቂቅ ነገር ነው፡፡ ኅብስተ ሕይወት ጌታን ያስገኘሽልን ድንግል ሆይ እናመሰግንሻለን ከፍ ከፍም እናደርግሻለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋየን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘላለም ሕይወትን ይወርሳል በማለት ያስተማረን ካንች የነሣውን ሥጋና ደም እንበላ እና እንጠጣ ዘንድ ነው፡፡ በሄዋን ምክንያት የተዘጋ ገነት የተከፈተብሽ ድንግል ሆይ ባንች ድንቅ ነገር ረቂቅ ምሥጢር ተደረገልን፡፡ ካንች የተዋሐደውን ሥጋ እና ደም ተቀብለን  ገነት መንግሥተ ሰማያትን የምንወርስብሽ ድንግል ሆይ እናመሰግንሻለን፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ሳለን ብርሃን የተመለከትንብሽ የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም ሆይ እናመሰግንሻለን፡፡ በማኅጸን የፈጠረሽን አምላክ በማኅጸንሽ የተሸከምሽ ቅድስት ሆይ እናከብርሻለን፡፡ በዘር በሩካቤ ተፈጥረሽ ያለዘር ያለሩካቤ አምላክን ያስገኘሽልን ድንግል ሆይ እናገንሻለን፡፡ ድንግልናዋን ከአጣች እናት ተወልደሽ በድንግልና አምላክን በመውለድሽ ከፍከፍ እናደርግሻለን፡፡


Tuesday, November 29, 2016

“እናቱ ስትባይ ለእኔም እናቴ ነሽ”

© መልካሙ በየነ

ኅዳር 21/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
በመጀመሪያ  በሰላም በፍቅር በአንድነት ጠብቆ ለዚህ ለተቀደሰው ዕለት ያደረሰንን የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን አምላካችንን አመሰግነዋለሁ፡፡ ይህች ዕለት የተከበረች እና የተቀደሰች ከፍ ከፍም ያለች ናት፡፡ ካህኑ ዘካርያስ በቤተመቅደስ እንደ ፋና ስታበራ እመቤታችንን ተመልክቶባታል፡፡ ምንኛ የታደለ ካህን ነው? ቤተመቅደሳችንን አረከሰችብን ብለው ከቤተመቅደስ ለማባረር ነገር የሚሸርቡ ካህናት በነበሩበት በዚያ ወቅት የእግዚአብሔር አገልጋይ ቅዱሱ ካህን አምላክን ያጠመቀውን ትልቅ ነቢይ የወለደ ዘካርያስ እመቤታችንን ያከብራት እና ይገዛላት ይታዘዛትም ነበር፡፡ ይህ ካህን ከሴቶች ሁሉ የተለየ ድንቅ ነገር በእርሷ እንደሚደረግ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለታል፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌ በእርሷ እንደሚከናወን ተረድቷል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእውራን ብርሃናቸው፣ ለኃንካሳዎች ምርኩዛቸው፣ ለማይሰሙትም የመስሚያ ጆሯቸው፣ ለማይናገሩትም ልሳናቸው መግባቢያቸው፣ ለተራቡት ምግባቸው፣ ለታመሙት መድኃኒታቸው፣ ለተቸገሩት ደራሻቸው፣ ለተጨነቁት አረጋጊያቸው፣ ለተሠበሩት ጠጋኛቸው ናት፡፡ በእውነት ማንም የማይመስላት ማንም የማይተካከላት ማንም የማይደርስባት በማንም የማትመረመር ድንቅ እና ልዩ ፍጥረት ናት፡፡ በእግረ ኅሊናችን የዓለምን ዳርቻ ሁሉ ብናዳርስ፣ በክንፈ ኅሊናችን ሰማየ ሰማያት ብንመጥቅ፣ ወደ ጥልቁ እመቀ እመቃት ብንወርድ አንደርስባትም፡፡

ድንግል ማርያም እናት ናት፡፡ እናትነቷ ግን በዘር በሩካቤ ለተወለደ ህጻን አይደለም፤ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ያለ ዘር ያለ ሩካቤ በማይመረመር ምሥጢር ለወለደችው አምላክ ነው እንጅ፡፡ እርሷ ልጅ ተብላለች፡፡ ወለተ ዳዊት ወለተ ኢያቄም (የዳዊት የኢያቄም ልጅ) ብለናታል፡፡ እርሷስ በዘር በሩካቤ ከሃና እና ከኢያቄም የተገኘች ናት፡፡ እርሷስ ልጅ ስትባል ብትቆይም እናት ለመባል በቅታለች፡፡ ድንግል ወእም (ድንግል እና እናት) ብለናታል፡፡ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ ቅዱሳን፣ ሊቃውንት ድንግል ማርያምን በልዩ ልዩ ምሳሌዎች እየመሰሉ አስረድተውናል፤ በተለያዩ ቃላት አመስግነዋታል፡፡ ከምስጋናቸውም በላይ ስትሆንባቸው፤ የተደረገላትን ድንቅ ምሥጢርም ሲመረምሩ “ናርምም፤ ዝም እንበል” ይላሉ፡፡ አባ ሕርያቆስ እመቤታችንን የሚመስልበት ምሣሌ ቢያጣ “በመኑ ወበአምሳለ መኑ ናስተማስለኪ፣  በምን እና በምን ምሳሌ እንመስልሻለን” አለ፡፡ ይህ ቅዱስ አባት ምሳሌ አጣላት፡፡ ከፍ ብሎ በሰማይ ዝቅ ብሎ በምድር እንዳይመስላት የሰማይ እና የምድርን ፈጣሪ ዘጠኝ ወር በማኅጸኗ ተሸክማዋለች፡፡ ፈጣሬ ኩሉ (የሁሉ ፈጣሪ እና አስገኝ) ጌታን በጭኗ ታቅፈዋለችና፡፡ በእውነት በምን እንመስላታል?

ድንግል ማርያም እናት ተባለች፡፡ እናትነቷ ለዘለዓለም ልጅ ሲባል ለሚኖረው አምላክ ነው፡፡ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነስቶ በተዋሕዶ ተወልዷል፡፡ እርሱ በዘመን ብዛት አባት አይባልም፡፡ እኛ ልጅ ስንባል ብንኖር አባት ወይም እናት የምንባልበት ዘመን ይመጣል፡፡ እኛ ከእናት እና ከአባቶቻችን ብንወለድ እና ልጆች ብንባልም ባል ወይም ሚስት አግብተን ትዳር መስርተን ልጆችን ወልደን ልጅ ከመባል አባት ወይም እናት ወደመባል እንሸጋገራለን፡፡ አምላካችን ፈጣሪያችን ግን ለዘላለም ወልድ ሲባል ይኖራል፡፡ አስቀድሞ በማይመረመር ምሥጢር ከአብ ያለ እናት አሁን ደግሞ ከድንግል ማርያም ያለ አባት እንበለ ዘርእ ተወለደ፡፡ በፊትም ከአብ ሲወለድ ወልድ (ልጅ) ነው ዛሬም ከእመቤታችን ሲወለድ ወልድ (ልጅ) ነው፡፡ ዘመን ሲበዛ ወልድ (ልጅ) ወልድነቱ (ልጅነቱ) ተለውጦ አብ (አባት) አይሆንም፡፡ እመቤታችን ከሃና እና ከኢያቄም ተወልዳ ልጅ ስትባል ብትቆይም በኋላ ግን እናት ተብላለች፡፡ አምላክ ግን በፊትም አሁንም ያው ወልድ ነው፡፡ በፊትም አሁንም ወልድ (ልጅ) ለሚባል አምላክ ወልድ (ልጅ) ከመባል እናት ወደ መባል ለተሸጋገረችበት ምሥጢር ኅሊናችን እጹብ ድንቅ ይላል፡፡

ድንግል ማርያምስ እናት መባሏ ለአምላክ ብቻ አይደለም፡፡ ለእርሱ እናቱ ስትባል ለእኛም እናታችን ትባላለች፡፡ ይህንንም የሰጠን አምላካችን ነው፡፡ በዮሐ 19÷27 ላይ በወንጌላዊው ዮሐንስ በኩል ለሁላችን እናት ልትሆን አምላክ ሰጥቶናል፡፡ እናቱን እነኋት እናታችሁ ብሎ አስረክቦናል፡፡ ስሟን ጠርተን ዝክሯን ዘክረን እናታችን ብለን ውዳሴዋን ቅዳሴዋን አድርሰን የሞት ዜና ከማይነገርበት መንግሥተ ሰማያት እንገባ ዘንድ እንማጸናታለን፡፡ 

Wednesday, November 23, 2016

“ጾመ ነቢያት”

© መልካሙ በየነ

ኅዳር 14/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ይህ ጾም የገና ጾም በመባልም ይጠራል፡፡ ነቢያት እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠውን ተስፋ እየጠበቁ አምላክ ይወርዳል ይወለዳል ብለው የጾሙት ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም በሦስቱ ዘመናት ማለትም በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ እና በዘመነ ሉቃስ ኅዳር 16 ይጀምርና ታህሳስ 29 ይፈሰካል፤ በዘመነ ዮሐንስ ግን ኅዳር 15 ቀን ጀምሮ ታህሳስ 28 ቀን ይፈሰካል፡፡ እንደዚህ ሲሆን በአራቱም ዓመታት የጾሙ ቀናት 43 ይሆናል ማት ነው፡፡ ነገር ግን ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ኅዳር 15 የሚገባው ጾም ስለሚረሳ ሁልጊዜ ኅዳር 15 ቀን ጾሙ ይጀምራል፡፡ በዚህም የተነሣ በሦስቱ ዘመናት 44 ቀናት ይሆናል በዘመነ ዮሐንስ ግን 43 ቀናት ይጾማል፡፡ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የጾሙ ቀናት በ 1 ቀን ይቀንሳል፤ በሦስቱ ዘመናት 44 ቀናትን የምንጾመው ለጾም ማድላት ተገቢ ስለሆነ ነው፡፡
ስለዚህ ነቢያቱን አርአያ አብነት አድርገን እግዚአብሔር በተስፋ በበረከት ያኖረን ዘንድ፣ በጎውን የልቦናችንንም መሻት ሁሉ ይፈጽምልን ዘንድ፣ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን በቃሉ እንኖር ዘንድ እንጾመዋለን፡፡ ይህ ጾም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 568 ላይ “ከእነርሱም የሚያንስ እንደ ረቡዕና እንደ ዓርብ የሚሆን አለ፡፡ ይኸውም ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው፡፡ መጀመሪያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የገና በዓል ነው” በማለት መዝግቦት እናገኘዋለን፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ ወገኖች የጾሙን መግቢያ እና መውጫ ሲከራከሩበት እናያለን፡፡ ነገር ግን ይህ ቀኖና ቤተክርስቲያን እንጅ ዶግማ ባለመሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ ሊሆን አይገባውም፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔርን በማሰብ ወደ ፍቅር ተመልሰን ለጾም በማድላትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በማሰብ በፍቅር እንድናደርገው አባቶች ይመክሩናል፡፡ ስለዚህ በተሠራልን ሥርዓት እንመራ ዘንድ እመክራለሁ፡፡
በዚህ ጾም የሚነሣው መሠረታዊ ጉዳይ ነቢያቱ ዐርባ ቀናትን ብቻ ነው የጾሙት ይህ በትርፍነት የተጨመረው ዐራት ወይም ሦስት ቀን ከየት መጣ የሚል ነው፡፡ ነቢያቱ አርባ ቀናትን ጾሙ ስንል ኅዳር 19 ቀን ጀምረው ታህሳስ 29 ላይ ጾሙን ፈጸሙ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አኛ ኅዳር 15 ቀን ጾሙ ይጀምራል እንላለን ይህ አይጣላምን ቢሉ አይጣላም፡፡ ለዚህ ማስረጃችን፡-
1ኛ. ከላይ እንዳየነው ፍትሐ ነገሥቱ የዚህን ጾም መግቢያ ሲገልጽ የኅዳር እኩሌታ ስላለ ነው፡፡ የህዳር እኩሌታ ደግሞ ህዳር 15 እንጅ ህዳር 19 አይደለም፡፡ 2ኛ. ስንክሳሩ ኅዳር 15 “ወበዛቲ ዕለት ጥንተ ጾመ ስብከተ ጌና ዘውእቱ ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት ዘሠርዕዎ ክርስቲያን ያዕቆባውያን ዘግብጽ ሣህሉ ወምሕረቱ የሃሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን፤ በዚችም ቀን የስብከተ ጌና ጾም መጀመሪያ ነው፡፡ ይህም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተወለደበት በግብጽ የሚኖሩ ያዕቆባውያን የሠሩት ነው፡፡ ይቅርታው ቸርነቱ ከእኛ ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን” በማለቱ የህዳር እኩሌታ የሚለውን ኅዳር 15 ነው እንላለን፡፡
3ኛ. ሐዋርያው ፊልጶስ ኅዳር 16 በሰማእትነት ካሳረፉት በኋላ ሥጋውን ሊያቃጥሉ ሲነሡ መልአከ እግዚአብሔር ሥጋውን ሰወረባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ከዕለቱ ጀምረው 3 ቀናትን እንደጾሙ  በኅዳር 18 ሥጋውን ሰጣቸውና ቀበሩት፡፡ ስለዚህም ሦስቱ ጾም ጾመ ፊልጶስ ተብሎ ተጨመረ፡፡

4ኛ. በዓለ ልደት ረቡዕና ዓርብ ቢውል ይበላበታልና ለዚያ ማካካሻ ወይም ምትክ የምትሆን ጾም የገሐድ ጾም አንድ ቀን ከጾመ ፊልጶስ በፊት ተጨመረችና ኅዳር 15 ቀን እንዲጾም አዘዙን፡፡ ጌታ የጾመው ጾም ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ሆኖ ሳለ 55 ቀናትን እንደምንጾመው ያለ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል የመጨረሻውን ሳምንት ደግሞ የሕማማት ሳምንት በማለት እንደምንጾመው ሁሉ ይህንንም እንዲሁ አደረግን፡፡ ይህም የአባቶቻችን ትእዛዝ የአባቶቻችን ሥርዓት ነውና እኛም ተቀበልነው፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው በጾም ምክንያት ክርክር ቢነሣ መጾም ከመብላት እጅግ ይሻላል እንዳሉን እንጾመው ዘንድ ይገባናል፡፡

Friday, November 11, 2016

“ሁለቱ የሰይጣን ቀስቶች”

© መልካሙ በየነ

ኅዳር 2/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ዲያብሎስ ጥንተ ጠላታችን ነው፡፡ በአዳምና በሔዋን ላይ መርዙን ረጭቶ ከተድላ ቦታቸው ከገነት አስወጥቷቸዋል፡፡ ይህ ጠላት ዛሬ ድረስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቀስቱን ይወረውርብናል፡፡ ከቀስቱ ማምለጥና አለማምለጥ ግን በራሳችን ብርታትና ድክመት የተወሰነ ነው፡፡ ሰይጣን በዋናነት ሁለት ቀስቶችን ይወረውርብናል፡፡ የሚገርመው ነገር አንዱን ቀስት ስታመልጡ የውጊያ ስልቱን ቀይሮ በሌላ ቀስት መጠቀም እና ማጥቃት መቻሉ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ሰይጣንን እንደ ቁራ ጥቁር፣ ጥርሱ የገጠጠ፣ ዓይኑ የፈጠጠ፣ ጥፍሩ የዘረዘረ ወዘተ ስለሚመስለን ጸአዳ ሆኖ በውበት አምሮና ደምቆ ሲመጣ እንታለላለን፡፡  ለመሆኑ ሰይጣን የሚጠቀማቸው ቀስቶች ምንድን ናቸው?

እኛን ለማጥቃት እና ለመማረክ ሰይጣን በዋናነት ሁለት ቀስቶችን ይጠቀማል፡፡ እነዚህንም እንደሚከተለው እንዘረዝራለን፡፡
1.   ጽድቅ እንዳትሠራ ማድረግ፤ ሰይጣን የጽድቅ ሥራ ሁሉ ጠላት ነው፡፡ ምክንያቱም ጽድቅ አይስማማውምና ነው፡፡ ሰይጣን የሚችለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ ከጽድቅ ሥራ ያርቅሃል፡፡ አንተ በነፍስህ ተገድደህ ጽድቅ ልትሠራ ስትሞክር እርሱ ሥጋህን ተጠቅሞ ወደ ኃጢአት ይመራሃል፡፡ ስለዚህም ሰይጣን እንዳትጾም፣ እንዳትጸልይ፣ እንዳትሰግድ፣ እንዳትመጸውት፣ እንዳትራራ፣ ህግጋተ እግዚአብሔርን እንዳትጠብቅ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዳታነብ፣ ቅዱሳት መካናትን እንዳትሳለም፣ ንስሐ እንዳትገባ፣ ሥጋ ወደሙን እንዳትቀበል፣ እንዳታስቀድስ፣ እንዳትዘምር፣ ድሆችን እንዳትረዳ፣ የተራቡትን እንዳትመግብ፣ የታሠሩትን እንዳትጠይቅ፣ የታመሙትን እንዳትጎበኝ፣ ወንጌልን እንዳትማር እና እንዳታስተምር፣ ቅዱሳንን አማላጆቼ እንዳትል፤ በእግዚአብሔር ህልውና እንድትጠራጠር፣ ጉቦ እንድትቀበል፣ በአራጣ እንድታበድር፣ በሃሰት እንድትመሰክር ወዘተ ያደርግሃል፡፡ የቅድስና ሥራ የሚባል ነገር እንዳትሠራ ሰይጣን ቀስቱን ይወረውርብሃል፡፡ አንተም ቀስቱን መመከት ካልቻልክ ዕድሜ ልክህን የጽድቅ ሥራ ሳትሠራ ትኖራለህ፡፡ ነገር ግን ቀስቱን የመመከት አቅም ኖሮህ ሰይጣንን ማሳፈር ከቻልክ ወደ ጽድቅ መንገድ እንደገባህ ታውቃለህ፡፡ ሆኖም ግን ከሰይጣን ቀስት አሁንም ቢሆን አታመልጥም፡፡ ጽድቅ እንዳትሠራ ከሚያደርግህ ጠላት ጋር ተዋግተህ ማሸነፍ ከቻልክ ሰይጣን ቀስቱን ይቀይራል፡፡ ምክንያቱም ጽድቅን ለመሥራት ቆርጠሃልና፡፡ ጽድቅን ለመሥረት ከቆረጥክ ያን ጊዜ ሰይጣን በሌላ ቀስት ይዘጋጅና ይመጣሃል፡፡ እርሱም ሁለተኛው ቀስት ሲሆን በውስጡ ሁለት የውጊያ ስልቶችን የያዘ ነው፡፡
2.  ዋጋ እንዳታገኝበት ማድረግ፤ ጽድቅን እንዳትሠራ ታግሎህ አንተ ግን አልሸነፍም ብለህ የሰይጣንን ምክር አልሰማም ካልክ ሰይጣን በዚህኛው ቀስት ሊያጠቃህ ይሞክራል፡፡ አሁን ሰይጣን ጽድቅ እንዳትሠራ ማድረግ ላይ ተስፋ ቆርጧል፡፡ ስለዚህ በምትሰራው የጽድቅ ሥራ ዋጋ እንዳታገኝ ማድረግ ይጀምራል፡፡ ይህንንም ቀስት የሚወረውርባቸው ሁለት ስልቶች አሉት፡፡ እነዚህም፡-
v  ባለህ ማስቀጠል፤  ሰይጣን በምትሠራው ሥራ ዋጋ እንዳታገኝበት እና ተስፋ የምታደርጋትን ቦታ እንዳትወርስ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ያለው ምርጫ የጀመርካትን ነገር ሳታሳድግ ሳታጎለምስ በዚያው እንድትቀጥል ማድረግ ነው፡፡ ጾም፣ጸሎት፣ስግደት፣ ምጽዋት ወዘተ ማድረግን በትንሹ እና በጥቂቱ ጀምረሃል፡፡ ነገር ግን በዚሁ በጥቂቱ በጀመርከው የጽድቅ ሥራ ብቻ እንድትቀጥል ያድርግሃል፡፡ ለምሳሌ ጾም ስትጀምር እስከ 6 ሰዓት ድረስ ብቻ ከሆነ የምትጾም ሕጉ እስከ 9 እና ከዚያም በላይ እንደሆነ እያወቅህ ከዚህ ሰዓት በላይ ማለፍ እንዳትችል ያደርግሃል፡፡ እዚህ ላይ የጀመርካቸውን የጽድቅ ሥራዎች ሕጉ ከሚለው በታች እንድትሠራ በማድረግ ነው የሚፈትንህ፡፡ ንስሐ ለመግባት ቆርጠሃል በቃ በዚህ እንደማይፈትንህ አርግጠኛ ሆነሃል፡፡ ነገር ግን ንስሐ ስትገባ ወይ ከባድ ኃጢአት የምትለውን እንዳትናዘዝ ያደርግሃል አለበለዚያም ንስሐህን በቁርባን እንዳትደመድም ያደርግሃል፡፡ ጸሎት ላይም እንዲሁ ስትጀምር ውዳሴ ማርያምን በመጸለይ ከጀመርህ በቃ ከዚህ ሌላ ጸሎት እንደሌለ አድርጎ በዚሁ ጸሎት ብቻ ያስቀጥልሃል፡፡ ያውም በተመስጦ በተሰበሰበ ኅሊና ያይደለ ቃሉን በማነብነብ ብቻ እንድትጸልይ ያደርግሃል፡፡ በአጠቃላይ እዚህ ላይ ቅድስናን በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ በትንሹ ከህጉ በታች በሆነ መልኩ ከተሰማራህ በኋላ በዚያው ከህጉ በታች እንድትቀጥል በማድረግ ዋጋ ማሳጣት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ብዙ ዘመናትን ካቆየህ በኋላ አንተው ተሰላችተህ ከዚህ ሥራህ እንትሸሽ ያደርግሃል፡፡ ዋናውም ዓላማ ከጽድቅ ሥራ ማራቅ ነውና፡፡
v  ከንቱ ውዳሴን መጨመር፡- ሰይጣን ጽድቅን እንዳትሠራ ከታገለህ በኋላ በዚያ ከተሸነፈ በጀመርካት ትንሽየ ነገር በዚያው እንድትቀጥል ያደርግሃል፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ እንድትተዋት ያደርግሃል፡፡ ነገር ግን አልተወውም ብለህ የጽድቅ ሥራህን እያበዛህ ስትሄድ ከንቱ ውዳሴ የተባለውን አረም ይዘራብሃል፡፡ ከዚያም ሳትሠራ ሁሉ ሠራሁ ማለትን ያስጀምርሃል፡፡ ከእኔ በላይ ጿሚ፤ ከእኔ በላይ ሰጋጅ፤ ከእኔ በላይ ቆራቢ፤ ከእኔ በላይ መጽዋች፤ ከእኔ በላይ ሰባኪ፤ ከእኔ በላይ ዘማሪ፣ ከእኔ በላይ ንስሐ ገቢ፣ ከእኔ በላይ አገልጋይ ወዘተ ማለት ያስጀምረናል፡፡ ከዚያ በኋላ የቅዱሳኑን ገድል ሳይቀር መናቅ ትጀምራለህ፡፡ ከዚሁ ጋር ትእቢት ይይዝሃል፡፡ በቃ ሁሉን ነገር ከእኔ በላይ ለኃሳር ነው ማለት ትጀምራለህ፡፡ ከዚህ በኋላ የመናገር ሱስ ይይዝሃል፡፡ የሰራኸውንም ያልሰራኸውንም እየቀጣጠልህ እየጨማመርህ ማውራትን ትለምዳለህ፡፡ ለታይታ እና ለማስመሰል መባከን ትጀምራለህ፡፡ መለከት በፊቴ ካልተነፋልኝ ከበሮ ካልተደለቀልኝ ማለትን ትጀምራለህ፡፡ መድረኩን ይዘህ ማይኩን ጨብተህ ቅዱሳን እንዲህ ተጋደሉ ማለቱን ትዘነጋውና እኔ እንዲህ አድርጌ እንዲህ ፈጥሬ ወዘተ ማለት ትጀምራለህ ፡፡ አገልግሎትህ በሙሉ ራስህን በማስተዋወቅ ላይ የተጠመደ ይሆናል፡፡

ሰይጣን ጽድቅን እንዳትሠራ ማድረግ አልችል ካለ ያለው ምርጫ ወይ ባለህበት ማስቆም ነው አልያም ከንቱ ውዳሴን ማምጣት ነው፡፡ ስለዚህ ሰይጣንን ድል ነስቸዋለሁ ብለን ልንናገር የምንችልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም ማለት ነው፡፡ ሰይጣንን ድል መንሳታችንን ማረጋገጥ ያለብን በጌታ ፍርድ ቆመን “ኑ የአባቴ ቡሩካን…” የሚለውን አጥንት አለምላሚ ቃል ከሰማን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በየትኛው አቅማችን በየትኛው ቅድስናችን አፋችንን ሞልተን ሰይጣንን ድል እንደነሳነው እንናገራለን፡፡ ስለዚህ ከሰይጣን ፈተና ማምለጥ አይቻልምና የትግል ስልታችንን እንደአመጣጡ መቀያየር ተገቢ ነው፡፡ 

Wednesday, November 9, 2016

“አውሎግሶን”

© መልካሙ በየነ

ኅዳር 1/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================

“አውሎግሶን” ማለት “አቤቱ ክፈትልኝ፤ አቤቱ ግለጥልኝ” ማለት ነው፡፡ (ድርሳነ ሚካኤል ዘኅዳር)
ይህ ልመና እንደ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ያለ ልመና ነው፡፡ ዳዊት “አቤቱ ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ፡፡ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስመዝ 50 እንዳለው ያለ ማለት ነው፡፡
የልባችን ክፋት ሲያይልብን፣ ማሥተዋል ሲጎድለን፣ መረዳት ሲሳነን፣ ተስፋችን ሲሟጠጥ፣ ኅሊናችን ሲታወክ ወዘተ አውሎግሶን ማለት ይገባናል፡፡ የደነቆረ ልቡናችን፣ ማየት የቸገረው ዓይናችን፣ ማሰብ የተሳነው ልቡናችን፣ ለፈጣሪ የተገዛ እንዲሆንልን ቅዱሳንን አማላጆቼ እንዲልልን አሁንም አውሎግሶን እንበል፡፡ በዘመናችን ተገቢ ልመና ከፈጣሪ መታረቂያ ጸሎት አውሎግሶን ነው፡፡ የተዘጋው ሲከፈት የተሰወረው ሲገለጥ ሰይጣን የኃፍረት ካባ ሲጎናጸፍ ነፍሳችን ሥጋችንን ገዝታ በነፍስ ጎዳና ትመራታለች፡፡ የሥጋ ገበያ ይቀዘቅዛል የነፍስ በረከት ምድሪቱን ይሸፍናታል፡፡ የመላእክቱ ጠባቂነት ይበዛልናል ስለዚህ ትናንት አበው አውሎግሶን እንዳሉ ዛሬ እኛም እንዲሁ ብለን ለነገው ትውልድ የሚድንበትን መንገድ እንዲከፈት የተሠወረው እንዲገለጥ አውሎግሶን በሉ ብለን እናስተምር፡፡

ዳዊት “አቤቱ ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ፡፡ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስመዝ 50 ብሏል፡፡ ይህን የዳዊት ልመና እንደእኔ ዓይነቱ ሞኝ ዳዊት ድሮ የነበረውን ወይም ቀድሞ የተፈጠረለትን ልብ ፈጣሪ በጥበቡ እንዲቀይርለት (እንዲለውጥለት) የለመነ ይመስለዋል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ልቡናው በኃጢአት ረክሷል፣ ልቡናው ሰው በመግደል አድፏል፣ ልቡናው የቀናውን መንፈስ ለማሰብ ተስኖታል፣ ልቡናው ጽድቅን እንዳያስብ ተዘግቷል፤ ልቡናው የሰውን ሚስት በማስነወር ቆሽሿል፣ ልቡናው ያልተፈቀደለትን የካህናትን ምግብ በመመገብ ኃጢአት ሠርቷል፡፡ ስለዚህ ነው ይህንን በኃጢአት የሚባዝነውን ልቡናየን ንጹሕ አድርግልኝ ማለቱ፡፡ ያለኝን ቀድሞ የፈጠርክልኝን ልብ በንስሐ ሳሙና ንጹህ አድርግልኝ ማለቱ ነው፡፡ ንስሐ እንድገባ በንስሐ እንድመላለስ በቅድስና እንድጓዝ አድርገኝ ሲል ነው፡፡ የእኛም ልመና ይኼ ነው መሆን ያለበት፡፡ እኛን ከፍጥረታት ሁሉ አልቆ አብልጦ ፈጥሮናል ነገር ግን በማይገባ የኃጢአት ሥራ እየባዘንን እንሳሳትን እንመስላለን፡፡ በርግጥ ሰው እንስሳዊ ባሕርይ አለው፡፡ እንስሳዊ ባሕርይውን ግን መቆጣጠር እንዲችል ሆኖ የተፈጠረ ድንቅ ፍጥረት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች በሬ ሲያዩ በሬ ባደረገኝ፣ ወፍ ሲያዩ ወፍ ባደረገኝ፣ አንበሳ ሲያዩ አንበሳ ባደረገኝ፣ ነብር ሲያዩ ነብር ባደረገኝ ወዘተ ይላሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ዳዊት ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ ማለቱን አለማስተዋላችን ነው፡፡ ዳዊት ያለኝን የቆሸሸ ልቤን ንጹሕ አድርግልኝ አለ እንጅ የእንስሳትን ልብ ስጠኝ አላለም፡፡ እኛም የሚያስፈልገን ይኼ ልመና ነው፡፡ ያለንን ነገር ቀድስልን ባርክልን ንጹሕ አድርግልን ማለት ያስፈልገናል፡፡ የሌለንን ነገር ምኑን እንዲባርክልን እንለምነዋን? አውሎግሶን በሉ እባካችሁ፡፡ ሁሉም ከተዘጋብን ሁሉም ከተሠወረብን ከዚህ የልመና ቃል ውጭ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ልመናችንን እንድናስተካክል የተሠወረው እንዲገለጥልን የተዘጋው እንዲከፈትልን አውሎግሶን እንበል፡፡ ልቡናችን በኃጢአት ቁልፍ ተዘግቷል፤ የጽድቅ ጎዳና በዲያብሎስ ተንኮል ታጥሮብናል ተዘግቶብናል፤ የንስሐ ሳሙና ተደብቆብናል ስለዚህ የተዘጋው እንዲከፈት የተሠወረው እንዲገለጥ አውሎግሶን እንበል፡፡


ጸሎት ለመጀመር በጣም የከበደ እንዲሆን አድርጎ ሰይጣን በልባችን ገብቶ መጥፎ አረም ይዘራብናል፡፡ ለዚያም ነው ትንሿ ጸሎት ዳገት ሆና ለመጀመር የምትከብደን፡፡ አውሎግሶን ብለን ጸሎት ስንጀምር ግን ዳገቱ ሁሉ የተስተካከለ ሜዳ ይሆንና ውዳሴዋን ስንጨርስ አንቀጸ ብርሃኗን፤ አንቀጸ ብርሃኗን ስንጨርስ ይዌድስዋ መላእክትን፤ ያን ስንጨርስ አቡነ ዘበሰማያትን እርሱንም ስንጨርስ ቅዳሴዋን፣ መልክአዋን ሌሎችንም ለመጸለይ ልባችን ተከፍቶ በተመስጦ እንድንጸልይ ብርታት እናገኛለን፡፡ ማንም ማረጋገጥ የሚችለው እውነት ነው፡፡  ትንሽ ጸሎት ብንጀምር ትልቁን ጸሎት እንድንጀምር ሰይጣን የመቃወም ኃይሉ ይቀንሳል፡፡ አማትበን አቡነ ዘበሰማያትን ስንጀምር ሰይጣን መሸሽ ይጀምራል፡፡ በዚያ ላይ ስግደት ስንጨምርበት በኖ ይጠፋል፡፡ አውሎግሶን!!!

Friday, November 4, 2016

“ለምንት አንገለጉ አሕዛብ፤ አሕዛብ ለምን ያጉረመርማሉ” መዝ 2÷1

© መልካሙ በየነ
ጥቅምት 25/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================

ቃሉን የምናገኘው በመዝ 2÷1 ላይ ነው፡፡ አሕዛብ የሚባሉት በታቦት ፈንታ ጣዖት በግዝረት ፈንታ ቁልፈትን የሥራቸው መሠረት ያደረጉ ለሕገ እግዚአብሔር የማይገዙ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለእግዚአብሔር አይገዙም፤ አለመገዛትም ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር በሚገዙ ህዝቦች ላይ የሚነሣሡ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በተለያዩ ጉዳዮች በእግዚአብሔርና በማደሪያው ላይ የሚያጉረመርሙት፡፡ ማጉረምረም የቅድስና ሥራ አይደለም፤ ቅድስናውን በመናቅ የሚደረግ ነው እንጅ፡፡ ታዲያ አሐዛብ ለምን እና በምን ያጉረመርማሉ? የሚለውን ጥያቄ በጥቂቱ እንመልከት፡፡
v  በመንፈሳዊ ሥራዎች ላይ
አሕዛብ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ሥራን አይሠሩም አያሠሩምም፡፡ አይጾሙም አይጸልዩም አይሰግዱም አይመጸውቱም ንስሐ አይገቡም ወዘተ፡፡ ነገር ግን  አያጾሙም አያጸልዩም አያሰግዱም አያስመጸውቱም ንስሐ አያስገቡም ወዘተ፡፡ እነዚህ ሰዎች “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል” ያለችውን የእኛን አገር እንስሳ በግብር ይመስሏታል፡፡  እነርሱ አይጾሙም ነገር ግን ሌሎች ለሚጾሙት ጾም እነርሱ ጾሙ ይቀነስልን ብለው ያጉረመርማሉ፡፡ እነርሱ አይጸልዩም ነገር ግን ሌላው ለሚጸልየው ጸሎት በዛብን ብለው ያጉረመርማሉ፡፡ እነርሱ አይሰግዱም ነገር ግን ሌላው ለሚሰግደው ስግደት እነርሱ ስግደት አያስፈልግም እያሉ ያጉረመርማሉ፡፡ እነርሱ አይመጸውቱም ነገር ግን ሌላው ለሚመጸውተው ምጽዋት ጥቅም የለውም በማለት አብዝተው ያጉረመርማሉ፡፡ እነርሱ ንስሐ አይገቡም ነገር ግን ንስሐ የሚገቡትን ይኮንናሉ፡፡ ለምን በቀጥታ ለአምለካክህ አትነግረውም ከካህኑ ዘንድ ምን ያመላልስሃል ብለው ያጉረመርማሉ፡፡ በአጠቃላይ ለድኅነት ሥራዎች ሁሉ ፀር ናቸው፡፡ ለዚያም ነው አሕዛብ የሚያጉረመርሙት፡፡
v   ሥርዓት ይሻሻልልን
እነርሱ በቤቱ ሳይኖሩ በቤቱ እንዳሉ መስለው በማይመሩበት በማይተዳደሩበት ሥርዓት ላይ ያጉረመርማሉ፡፡ በማያገባቸው ነገር ሲጨቃጭቁ የሚያገባቸውን ነገር ይረሳሉ፡፡ ሥርዓቱን ማሻሻል እንደማይችሉ እያወቁ ውዥንብር ለመፍጠርና አማኙን ክርስቲያን ለመከፋፈል ደፋ ቀና የሚሉ ናቸው፡፡ ሥርዓቱ ይሻሻልልን እያሉ በሥርዓቱ ላይ ያጉረመርማሉ፡፡ ሲያሻቸውም የየራሳቸውን ሥርዓት ሰርተው በዚያ ሲመሩ ይታያሉ፡፡ ለምን እንዲህ አደረጋችሁ ሲባሉም ሥርዓቱ እንደዚህ ስለሆነ ነዋ በማለት በማያውቁት ሥርዓት ላይ በድፍረት ሲመሰክሩ ይሰማሉ፡፡ የሚገርመው ነገር አይጾሙም አይጸልዩም አይሰግዱም ንስሐ አይገቡም ነገር ግን የእነዚህን ሁሉ ሥርዓት ይነቅፋሉ ይሻሻልልን ብለውም ያጉረመርማሉ፡፡ በእውነት ለማይኖሩበት ለማይመሩበት ሥርዓት ምኑ ነው የሚሻሻልላቸው፡፡ በርግጥ ዓላማቸው እነርሱን የመሰሉ በርካት አህዛብን ማፍራት ነውው፡ ለዚህም ነው ሥርዓት ይሻሻልልን ብለው የሚያጉረመርሙት፡፡
v  ቤተክርስቲያን ትታደስ
የዚህ ጽንሰ ሃሳብ አራማጆች የቤተክርስቲያንን እውቅ መለያ ሀብቶች በማጥፋት ቅርስ አልባ በማድረግ የመናፍቃን መናኸሪያ እና ባዶ አዳራሽ ማድረግ ነው፡፡ የብራና መጽሐፍ እስከ 20 ሺ ብር ድረስ ተሸጠ ሲባል ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ስትሉ የቤተክርስቲያኒቷ ጥንታዊ መረጃዎች የተጻፉት በብራና ስለሆነ ህዝቡ መጻሕፍትን ከአብያተ ክርስቲያናት እየዘረፉ እንዲሸጡላቸው ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ መጻሕፍትን ሰብስበው ያቃጥሏቸዋል፡፡ ዋናው ዓላማቸው ይህ ስለሆነ ማት ነው፡፡ መዝሙራት ስብከቶች ዓለማዊነትን እንዲላበሱ ሆነው መዘጋጀት አለባቸው ብለው ዘፈን መሳይ መዝሙራትን የስድብ ውርጅብኝ የወረደበት የስብከት ካሴቶችን ይለቅቃሉ፡፡ ያሬድን ሳያውቁ ያሬዳዊ ዜማ በማለት ለመሸጥ በሞንታርቮ በየከተማው እየዞሩ የሚጮሁ ብዙዎች እየሆኑ ነው፡፡ አሕዛብ ቤተክርስቲያንን የራሳቸው መፈንጫ ለማድረግ እነርሱን የሚመች ህግ እንዲወጣ እና በአዲስ መልኩ እንዲሰራበት ይወተውታሉ፡፡


Tuesday, November 1, 2016

“ገነስትስ መቼ አማረብን?”

© መልካሙ በየነ

ጥቅምት 22/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
የምበላው የምጠጣው የለኝም ለዚህም ነው አምላኬን የማላመሰግነው፡፡ አንዳንዱን በጥጋብ ብዛት  እያዘለለ እኔን በረሃብ አለንጋ ይገርፈኛል ለዚህም ነው “ተመስገን” የማልለው፡፡ እኔ የምኖርበት ጎጆ የለኝም፡፡ የቀን ፀሐይ የሌሊት ቁር ይፈራረቅብኛል ውሎ እና አዳሬ መንገድ ዳር ነው፡፡ ያዘነ ይሰጠኛል ያላዘነም ይሰድበኛል በዚህ መልኩ ነው የምኖረው፡፡ መንገድ ዳር አላፊ እና አግዳሚውን ስለምን የምውል ችግረኛ ነኝ ለዚህም ነው አምላኬን “ተመስገን” የማልለው፡፡ እኔ የምለብሰው የሌለኝ የፀሐዩ ሙቀት ያቃጠለኝ የሌሊቱ ቁር ያኮማተረኝ የታረዝኩ ችግረኛ ነኝ፡፡ ሌላው ሦስት አራት ልብስ እየቀያየረ ባለበት ጊዜ፤ ጠዋት የለበሰውን ማታ ቀይሮ በሚወጣበት ጊዜ እኔ ግን እርቃኔን እንደ ድንጋይ ብርድና ሙቀት ይፈራረቅብኛል ለዚህም ነው አምላኬን የማላመሰግነው፡፡ እኔ በየሰው ቤት እየዞርኩ ጭቃ የማቦካ እንጨት የምፈልጥ ድንጋይ የምሰብር ቁፋሮ የምቆፍር የቀን ሰራተኛ ነኝ፡፡ እጀ እስኪያብጥ ድረስ አሠራለሁ ጉልበቴ እስኪዝል ድረስ እሸከማለሁ ነገር ግን ኑሮየን ሊቀይር የሚችል ገንዘብ አላገኝም፡፡ ጠዋት በሠራሁበት ምሳ ከሠዓት በኋላ በሠራሁበት እራት እመገብበታለሁ፤ ኑሮየ ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ አንድ ቀን ሥራ ባቆም ማንም አያበላኝም፡፡ የማድርበት ቤት ደግሞ የለኝም በረንዳ ላይ ነው ወድቄ የማድረው፡፡ ለዚህም ነው አምላኬን “ተመስገን” የማልለው፡፡

እኔ ጤና አጥቸ እንቅልፍ ተነሥቼ የምኖር በሽተኛ ነኝ፡፡ በየህክምና ቦታው ተመላለስኩ መፍትሔ የለውም፤ በየፀበል ቦታዎች ሁሉ ተንከራተትኩ ምንም መፍትሔ አላገኘሁም፡፡ በባሕላዊ መንገድ ይፈውሳሉ ፍቱን መድኃኒት አላቸው ከሚባሉ ባለመድኃኒተኞችም ዘንድ ተመላልሻለሁ፡፡ ነገር ግን ገንዘቤን ከመበተን ውጭ ምንም ትርፍ ነገር አላገኘሁበትም፡፡ ከአልጋ ጋር እንደ ትኋን ተጣብቄ መኖር ከጀመርኩ ረዥም ዘመን ሆኗል፡፡ አንድ ቀን ብሎ የፈጣሪየ እርዳታ አልመጣልኝም አንድ ቀን እንኳ ከበሽታየ እንዳገግም ፈጣሪየ አላደረገም ለዚህም ነው የማላመሰግነው፡፡

እኔ በባእድ አገር ኑሮ አልሳካልኝ ብሎ የምኖር ስደተኛ ነኝ፡፡ ቋንቋቸውን አልችለውም ባሕላቸውን አልተላመድኩትም ምግባቸውን አልወደድኩትም፡፡ ነገር ግን የእንጀራ ጉዳይ ነውና በግድ እኖራለሁ፡፡ ገንዘቡ አልጠራቀምልህ ብሎኛል፤ ቤተሰቦቼን አሳልፍላቸዋለሁ ብየ ወጥቼ ራሴን እንኳ ማስተዳደር አልችል አልኩኝ፡፡ ቀን ከሌሊት ያዝዙኛል እንቅልፍ የሚባል ነገር በዓይኔ ከዞረ ከሳምንት በላይ ሆኗል፡፡ አገሬ የምመለስበት ገንዘብ አላጠራቀምኩም ኑሮየ ከእጅ ወደ አፍ ብቻ ነው፡፡ ሁሉ ነገር ለእኔ ባእዳ ነው፡፡ አገሬ መልሰኝ ብየ ፈጣየን ተማጸንኩት እርሱ ግን ይባስ ብሎ ለክፉ አሠሪዎች አሳልፎ ሰጠኝ ለዚህም ነው አላመሰግንህም የምለው፡፡ በስደት አገር የተወኝ ለችግር የጣለኝ እርሱ ነው ታዲያ እንዴት አመሰግነዋለሁ?

ብዙ ችግር፣ ብዙ መከራ፣ ብዙ ፈተና አለብን፡፡ ፈጣሪ የፈጠረው ፍጥረት ሁሉ አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ አንዱን ድሃ ሌላውን ሃብታም፣ አንዱን ቀይ ሌላውን ጥቁር፣ አንዱን የተማረ ሌላውን ያልተማረ፣ አንዱን ረዥም ሌላውን አጭር፣ አንዱን ጌታ ሌላውን ባሪያ፣ አንዱን መልካም ሌላውን መጥፎ ወዘተ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ፈጣሪ ሲፈጥረን በተለያየ መልኩ አድርጎ ነው፡፡ አላውቅ ብየ እንጅ ለዚህ ነበር ምስጋና የሚገባው፡፡ እኔ ድሃ ካልሆንኩ ሌላው ሃብታም ሊባል አይችልም በመካከላችን ያለውን ልዩነት እያየሁ ራሴን በተስፋ እንዳኖር ይረዳኛል፡፡ በበጎ ባስበው ኖሮ አምላክን ማመስገን የሚገባኝ እኔን ተመጽዋች ሌላውን መጽዋች ስላደረገው ነበር፡፡ እምነት ካለኝ ብታመም ያድነኛል ምናልባት ዋጋ የሚያሰጠኝ ህመም ከሆነ ግን ተመስገን ብለው ሲዖልን እንዳላይ ያደርገኛል፡፡ ኢዮብን ዘመዴ አደርገዋለሁ ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ስለሌለኝ ፈጣሪየን አላመሰግነውም የምለው ለምንድን ነው? ገንዘብን መውደድ የይሁዳን ልብ አውሮ ፈጣሪውን በ30 ብር እንዲሸጥ ያደረገው እኮ ነው፡፡ ገንዘብ ቢኖረኝ ምናልባት ፈጣሪየን አሳዝንበት ይሆናል እንጅ እንደ አብርሃም ፈጣሪየን አላስደስትበትም፡፡ የምበላው የምጠጣው አጣሁ ብየ ፈጣሪየን አላመሰግንም ካልኩኝ ስበላ እና ስጠጣ ስጠግብ እንደምረሳው አውቃለሁ፡፡ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ መና ከደመና እየወረደላቸው ተመግበው ውኃ ከጭንጫ አለት ላይ እየፈለቀ ጠጥተው ሲጠግቡ ፈጣሪያቸውን ረስተው ጣዖት አሠርተው ለጣዖት ተንበርክከዋል፡፡ ጥጋብ እንዲህ ፈጣሪን ያስረሳል፡፡

ለነገሩማ አልገባህ ብሎኝ እንጅ ተድላ ደስታ በበዛባት ገነት እየኖሩ የሚበሉት ሳያጡ የሚጠጡት ሳይጎድልባቸው የሚለብሱት ሳያስፈልጋቸው አዳምና ሄዋን ትእዛዝ አፍረሰው አይደል እንዴ፡፡ ሰው ነኝ ለካ! አወ ሰው እኮ ነኝ፡፡ ታዲያ ሰው ፍላጎቱ ይረካል እንዴ? ሰው እኮ በቃኝን የማያውቅ ፍጥረት ነው፡፡ አንድ ሲኖረው ሁለትን ይመኛል፤ ሁለት ሲኖረው ሦስትን ይመኛል፤ ሦስት ሲኖረው ደግሞ አራትን ይመኛል ብቻ ተቆጥሮ የማያልቅ ፍላጎት ነው ያለው፡፡ ታዲያ ገንዘብ ቢኖረው ባይኖረው፣ ቢለብስ ባይለብስ፣ ድሃ ቢሆን ሃብታም፣ ቀይ ቢሆን ጥቁር፣ የቀን ሠራተኛ ሆነ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ምንም ሆነ ምን ሰው ፈጣሪውን ላለማመስገን ምክንያት ያስቀምጣል፡፡ እንኳን የቅጣት ቦታችን መሬት ላይ ቀርቶ የተድላ ቦታችን ገነት ላይም ኖረን አላማረብንም፡፡ ምንም ምክንያት አያስፈልገንም የገነት ኑሮ ያላማረብን ሰዎች እስር ቤት ወርደን ያምርብናል ብለን አናስብ፡፡ ባለህ ነገር ፈጣሪህን አመስግን፣ ባለህ ነገር አቅድ፣ ባለህ ነገር ብቻ ኑር፣ ባለህ ነገር ደስ ይበልህ፣ ባለህ ነገር ተስፋህን አለምልም፡፡ የሌለህን ነገር ስትመኝ ያለህን ነገር ሳትጠቀምበት ትሰናበታለህ፡፡ እስኪ በቃኝ ማለትን እንልመድ፡፡ ገንዘቡ በቃኝ፣ መብላት መጠጣቱ በቃኝ፣ መልበስ ማጌጡ በቃኝ፣ ኃጢአትን መስራቱ በቃኝ፣ መቀማቱ በቃኝ፣ ሰውን ማሳዘኑ በቃኝ፣ ሰውን መግደሉ በቃኝ እንበል እስኪ፡፡ ሰው በወርቅ አልጋ ላይ የወርቅ ምንጣፍ አንጥፎ ቢተኛ አይረካም፡፡ ሰው የወርቅ ጫማ ተጫምቶ በወርቅ ልብስ አሸብርቆ ቢወጣ አይረካም፡፡ ሰው ጮማ ቢያወራርድ ጠጅ ቢያንቆረቁር አይረካም፡፡ ሰው መኖሪያ ቤቱን በዕንቍ ቢሽቆጠቁጠው በወርቅ መጋረጃ ቢከልለው ምንም አይረካም፡፡ ታዲያ ገነት ያላማረበትን መሬት ላይ እንዴት ይመርበት፡፡ የመሬት ላይ ኑሮ አላምርልህ ቢል አትደነቅ አትገረም ገነት መኖርም አላማረብህምና!!!

Monday, October 31, 2016

“እመ አምላክ ድንግል ማርያም”

© መልካሙ በየነ

ጥቅምት 21/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
እመ አምላክ (የአምላክ እናት) ድንግል ማርያም፡፡ ይህ አገላለጽ ከእናታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ውጭ ለማንም ለማን የማይነገር ብቸኛ አገላለጽ ነው፡፡ እናትነትን ከድንግልና ጋራ አስተባብራ የምትገኝ ሴት ከድንግል ማርያም ውጭ በየትኛውም ዓለም ውስጥ አትገኝም፡፡ እም ወድንግል ቢሉ የአዳም ተስፋ ምክንያተ ድኅነታችን የገነት በር የተከፈተባት እናታችን ብቻ ናት፡፡ ይህ ነገር ከሰው ኅሊና በላይ ነው፡፡ አእምሯችን ምጡቅ ሥራችን ረቂቅ ነው የሚሉ ጠቢባን ሁሉ ይህንን ነገር ሊረዱት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እናት እና ድንግል ሲባል መስማት ለጆሮም እንግዳ ነውና፡፡ ሌሎች ሴቶች ድንግል ከተባሉ እናት፤ እናት ከተባሉም ድንግል መባል አይችሉም፡፡ በምንም ተአምር ይህንን ማስተባበር አይችሉም፡፡ ከዓለም መፈጠር በፊት በአምላክ ኅሊና ተስላ የነበረች ንጽሕት ዘር እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ይህንን አስተባብራ ከፍጥረታት ሁሉ ልቃ ተገኘች፡፡ አስቡት ይህንን ድንቅ ምሥጢር! ይህ ነገር እኮ ከእኛ ኅሊና በላይ ወደ ላይ ብንወጣ የማናገኘው፣ ወደ ታች እመቀ እመቃት ወደ ጥልቁ ብንወርድ የማንረዳው፣ ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ ብንበርር የማንገነዘበው  ምጡቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የእናታችን ምስጋና የበዛለት አባ ኤፍሬም “ኦ ዝ ነገር” በማለት በአንክሮ የሚናገረው፡፡ እውነት ነው ነገሩ ይረቃል፣ ነገሩ ይደንቃል፣ ነገሩ ይከብዳል፣ ነገሩ ለመረዳት ያስቸግራል፣ ነገሩ እጹብ እጹብ ብቻ የሚባል ነው፡፡

ሴቶች ልጅ በመጽነሳቸው ደስ ይላቸዋል በመውለዳቸው ደግሞ አብልጠው ደስ ይላቸዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ደግሞ ወንድ ይወለድላችኋል ሲባሉ ደስ ይላቸዋል፡፡ አያችሁት የእናታችንን ደስታ! በመልአኩ ብሥራት ትጸንሻለሽ መባል ምንኛ ያስደስታል!!! ይህንንማ ሌሎች ሴቶችስ የሚያገኙት አይደለምን ቢሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ነቢይ ነው በዚያ ይደሰታሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ሐዋርያ ነው በዚያ ይደሰታሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ቅዱስ አባት ቅድስት እናትን ነው በዚያ ይደሰታሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ጳጳስ ሊቀጳጳስ ካህንን ነው በዚያ አብዝተው ይደሰታሉ፡፡ እናታችን ግን ትወልጃለሽ ብትባል የሰማይ እና የምድር ጌታን እርሷንም የፈጠራትን አምላክ ነው፡፡ ይህ ያስደስታል! በዚህም ላይ ድንግልናን ከእናትነት ጋራ ማስተባበር ምንኛ ያስደስት፡፡ ይህ ድንቅ ነገር የተደረገው ለእናታችን ለድንግል ማርያም ብቻ ነው፡፡ ፈጣሪን ጸንሶ መውለድ ምንኛ ረቂቅ ምሥጢር ነው? ይህ ረቂቅ ምሥጢር በድንግል ማርያም ሲደረግ ስናይ እናታችንን አብዝተን ወደድናት አብዝተንም አደነቅናት አብዝተንም ተስፋችን አልናት፡፡ አብዝተን ስንደነቅ አብዝተን ስንወዳት አብዝተን ተስፋችን ነሽ ስንላት ግን ቅንጣት ታህል የምንጨምርላት ነገር ኖሮ አይደለም ነገሩ ቢረቅብን ነው እንጅ፡፡ በእውነት በእናታችን ፍቅር ተነድፈን አፋችን ለዘለዓለም ድንግል እናቴ ድንግል እናቴ አማልጅኝ ሲል ቢኖር ምንኛ በታደልን! ከእናታችን ፍቅር ርቀው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ፍቅሯ ጣዕሟ ባይገባቸው ነው፡፡ ቢገባቸውማ እናቴ ለማለት ቅጽበት ባልወሰደባቸውም ነበር፡፡ አምላካችን ፈጣሪያችን ከእናቱ ከእናታችን ከድንግል ማርያም ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡


Friday, October 28, 2016

“ሳይሆኑ እንዲሆኑ መምከር”

© መልካሙ በየነ

ጥቅምት 18/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================

“መሆን ደስ ይላል መምሰል ግን ያስጠላል” ይሉኝ ነበር አንድ አባት፡፡ ለጊዜው ነገራቸው አልገባኝም ነበር እየቆየ በሕይወቴ ውስጥ ሳየው ግን ገባኝ፡፡ ብዙዎች ያውቁኛል፤ ምን ማወቅ ብቻ ያደንቁኛልም እንጅ፡፡ ያወቁኝ እና ያደነቁኝ ግን በማወቄ ሳይሆን በመታወቄ ነበር፡፡ ለመታወቅ ደግሞ መሆን ላያስፈልግ ይችላል፡፡ አረ ልክ ነው መምሰል ለመታወቅ በቂ ነው፡፡ አሁን ገና አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ለመታወቅማ መምሰልም ላያስፈልግ ይችላል አሉ፡፡ አወ ልክ ነው፡፡ በዚያ ቀደምለት አንዱ ለመታወቅ ሲል ታዋቂዎችን ሲገርፍ ነበር አሉ፡፡ በታዋቂ ሰዎች ትክሻ ላይ ተንጠልጥለህ ታዋቂነትህን ለመጎናጸፍ በቻልከው መጠን በስድብ መወረፍ ነው አሉ፡፡ ታዋቂዎችን ካልተሳደብክ አትታወቅም፡፡ ብታመሰግናቸው ማንም አያውቅህም ምክንያቱም እልፍ ህዝብ ያመሰግናቸዋልና፡፡ ስለዚህ በቻልከው መጠን ብዙ ተከታይ ያላቸውን ሰዎች በስድብ ናዳ ትቀጠቅጣቸዋለህ ለጊዜው እብድ ሊሉህ ቢችሉም ከጊዜ በኋላ ግን ታዋቂ ትሆናለህ፡፡ ይሁዳ እንዲህ ስመ ገናና ሆኖ ዓለም ሁሉ ሲጠራው የሚውለው እኮ ጽድቅ ስለሰራ አይደለም ጌታውን ስለሸጠ እንጅ፡፡ በእርሱ ምትክ የተተካውን ሐዋርያ ማትያስን ማን ይጠራዋል? በዓለም ዘንድ የይሁዳን ያህል እውቅና ያገኘ አይመስለኝም፡፡ መንገድ ዳር ሄደህ ይሁዳ ማነው ብትል ጌታውን በ30 ብር የሸጠ ሰው ነው ይሉሃል፡፡ ማትያስ ማነው ብትል ግን ማንም አይመልስልህም፡፡ ይሁዳ ሁሉን አዋቂ በሆነው በሁሉም ዘንድ ስሙ በደረሰው አምላክ ላይ ስለተነሣሣ ነው ታዋቂ የሆነው፡፡ ዛሬም ይህንን ፈለግ ይዘው ሆነው ሳይሆን መስለው የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ታዋቂነት ለመጨመር ብቻ ያልተደረገውን ተደረገ እያሉ ያለማስረጃ አደባባይ ላይ በስድብ የሚቀጠቅጡ ሰዎች አሉ፡፡

እኔ አስመሳይ የለመለመ ዛፍ ነኝ፡፡ ቅጠል አለኝ ፍሬ ግን የለኝም፡፡ ለተራበ አጓጓለሁ ነገር ግን ከእኔ ፍሬን አያገኝብኝም፡፡ ምናልባት ለጥላነት ሊጠቀምብኝ ይችል ይሆናል፡፡ ብዙ ዛፎች የቅጠሌን ማማር ተመልክተው እንደአንተ እንድናምር ምን እናድርግ ይሉኛል፡፡ እኔም ፍሬ ያለኝ መስየ እንደ እኔ ቅጠላቸው እንዲያምር እመክራቸዋለሁ፡፡ ከዚህም በበለጠ እኔ ማፍራት ያልቻልኩትን ፍሬ እንዴት እንደሚያፈሩ ሁሉ እመክራቸዋለሁ፡፡ ያልሆንኩትን ሁኑ እያልኩ ስመክር ውስጤ ይረበሻል፡፡ አዋቂ አይደለሁም በዚህ መካሪነቴ ግን ብዙዎች ያውቁኛል፡፡ አልጾምም ሰዎች እንዲጾሙ ግን እመክራለሁ፡፡ አልሰግድም ሌሎች እዲሰግዱ ግን እመክራለሁ፡፡ አልጸልይም ሌሎች እንዲጸልዩ ግን አስተምራለሁ፡፡ አልመጸውትም ሌሎች እንዲመጸውቱ ግን እወተውታለሁ፡፡ አልቆርብም ሌሎች እንዲቆርቡ ግን አስተምራለሁ፡፡ ንስሐ ገብቼ አላውቅም ሌሎች እንዲገቡ ግን ሥርዓት አስተምራቸዋለሁ፡፡ እኔ እቅማለሁ አጨሳለሁ ሌሎች እንዳይቅሙ እንዳያጨሱ ግን አስተምራለሁ፡፡ እኔ ከመጠን በላይ እጠጣለሁ እሰክራለሁም ነገር ግን ሌሎች እንዳይሰክሩ አስተምራለሁ፡፡ አያችሁኝ ሳላችሁኝ! እኔ ማለት ነጠላየ በጣም የነጣ ልቡናየ በኃጢአት ብዛት የገረጣ ሰው ነኝ፡፡ የማስበው ኃጢአትን ነው፡፡ አፌ ይሰብካል ነጠላየ ይመሰክራል ውስጤ ማንነቴ ግን የሲዖልን ደጅ የሚያንኳኳ ነው፡፡ በአፌ እመርቃለሁ በልቤ እረግማለሁ፡፡ የእኔ ክርስትና ከነጠላ የዘለለ አይደለም፡፡ በልቤ የሸፈትኩ ወንበዴ ነኝ፡፡ በዝሙት አልጋ ውስጥ ተደብቄ እኖራለሁ፡፡ በዋዘኞች ወንበር ላይ ተቀምጨ አንቀላፋለሁ፡፡ ፍርዴ ደሃን ያስለቅሳል፤ እጀ ደምን ያፈሳል፡፡ እግሬ ለስርቆት ይገሰግሳል፤ ልቤ ኃጢአትን ያመላልሳል፡፡ በሰዎች ሃብትና ንብረት ዓይኔ ይቀላል፤ በወንድሜ ላይ እቀናለሁ በእህቴ ላይ አመነዝራለሁ፡፡ እናቴን እደበድባለሁ አባቴን እገድላለሁ፡፡ እንደዚህ ባደርግም ግን ስለ ጽድቅ እመክራለሁ፡፡ ምክንያቱም ታዋቂነትን ስለምሻ፡፡

ባልሆንኩበት ጠባይ ሌሎች እንዲሆኑ እመክራለሁ፡፡ እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ስለጽድቅ እመክራለሁ፤ እኔ አልጾምም ጹሙ ብየ ግን እመክራለሁ፡፡ በጣም የሚገርሙኝ ግን እኔን ምከረን የሚሉኝ ሰዎች ናቸው፡፡ እኔ ለራሴ መቸ ሆንኩና ነው መካሪ የምሆነው? በእርግጥ የእኔን ድፍረት ተመልክተው እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ እኔ ከፈጣሪየ ጋር ሳልታረቅ ሰዎችን ታረቁ የምል ከንቱ ፍጥረት ነኝ፡፡ እናንተ ቅጠሌን አትመልከቱ ፍሬ አልባ ነኝና፡፡ እናንተ የምትሹ ፍሬ ማፍራትን ነው እኔ ግን ቅጠል ብቻ ነኝ፡፡ ታዲያ እኔ ያላፈራሁትን ፍሬ ታፈሩ ዘንድ እንዴት ልመክራችሁ እችላለሁ?


  

Friday, October 21, 2016

“አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1

© መልካሙ በየነ

ጥቅምት 10/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
በመጀመሪያ ይህንን እንደ ርእስነት እንድጠቀምበት በውስጥ መስመር ለላከልኝ ፀገየ ባዩ አመሰግናለሁ፡፡
“አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1 ይህንን ቃል የተናገረው አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ቃሉ የተነገረው በዘመኑ ለነበሩት የሕዝብ መሪዎች ለሆኑ ነቢያት እና ካህናት ቢሆንም ፍጻሜው ግን በዘመናችን ላሉ የሃይማኖት አባቶች ሁሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ በዋናነት ሁለት ነገሮችን ማንሣት ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ የመጀመሪያው እግዚአብሔር ሕዝቤ የሚላቸው እነማንን ነው የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማጽናናት ምንድን ነው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ከፍጥረት ሁሉ አክብሮ እና አብልጦ ሲፈጥረን የመንግሥቱ ወራሾች የሥሙ ቀዳሾች እንድንሆን እንጅ በከንቱ እንድንጠፋበት አይደለም፡፡
የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚባለው በእግዚአብሔር አምላክነት የሚያምንና በእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚመራ ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃችን እግዚአብሔር ሙሴን አሥነስቶ  እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ ሊወጣቸው በወደደ ጊዜ የግብጹን ፈርዖን “ህዝቤን ልቀቅ” ብሎታል፡፡ እነዚህ በግብጽ ባርነት ውስጥ አገዛዝ የከበዳቸው እስራኤላውያን በእግዚአብሔር አምላክነት የሚያምኑ እና በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሥርዓት የሚመሩ ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር “ህዝቤ” የሚላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የነጻነት ጉዞውን በሙሴ መሪነት ጀመሩ፡፡ የኤርትራን ባህር ከፍሎ አሻገራቸው፡፡ አሁን ሲና ተራራ ላይ ደርሰዋል ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ለቃል ሊነጋገር ወደ ተራራው ወጥቷል፡፡ ሙሴ በጣም እንደዘገየባቸው ሲረዱ ሕዝበ እስራኤላውያን “ሙሴ አመሌ አመሌ ሲል እሳት አቃጥሎት ሞቶ እንደሆነ አናውቅማና አምላክ ሥራልን” ብለው ወንድሙ አሮንን አስቸገሩት፡፡ አሁን ህዝበ እስራኤላውያን አምላካቸው እግዚአብሔር እንደሆነ ዘንግተዋል፡፡ የሚገርመው ነገር “አምላክ ሥራልን” ማለታቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ባህረ ኤርትራን ከፍሎ አሻግሮ፣ መና ከደመና እያወረደ መግቦ ውኃ ከጭንጫ እያፈለቀ አጠጥቶ፣ ዋዕየ ፀሐይን በደመና ከልሎ እየመራቸው ለዚህ ደርሰዋል እነርሱ ግን ይህንን ሁሉ ውለታ ዘነጉ፡፡ አሮንም ከግብጽ ስትወጡ ይዛችሁት የመጣችሁትን  ንብረታችሁን ሰብስቡ አላቸው፡፡ ለገንዘባቸው ቀናዒ ናቸውና አንሰጥህም ይሉኛል ጊዜ አገኛለሁ እስከዚያ ድረስም ወንድሜ ይመጣልኛል አርፋቸዋለሁ ብሎ ነበር፡፡ እነርሱ ግን ወዲያውኑ ገንዘባቸውን ሰብስበው “አምላክ ሥራልን” አሉት፡፡ አርሱም ጉድጓድ አስምሶ እሳት አስነድዶ ወርቅ ብራቸውን ከዚያ ላይ ጣለው የጥጃ ምስል ሆኖ ወጣላቸው፡፡ አምላካችን ይኼ ነው ብለው ዘፈኑለት ሰገዱለት መስዋእት ሰውለት፡፡ በዚህ ጊዜ  እግዚአብሔር “ሙሴ ህዝብህ በደለኝ” አለው፡፡  ቅድም “ህዝቤ” ያላቸውን አሁን “ህዝብህ” አለው ጠብ ተጀመረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብነት ዝም ብሎ የሚኖር የባሕርያችን አይደለም ማለት ነው፡፡ ጠቅለል ሲል ህዝብ ማለት በእግዚአብሔር የሚያምን፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጠብቅ፣ በእግዚአብሔር ሥርዓት የሚኖር ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ “ማጽናናት” የሚለው ነው፡፡ ይህ ህዝብ ያዝናል፣ ይተክዛል፣ ይራባል፣ ይጠማል፣ ይሰደዳል፣ ይገደላል፣ ሃብት ንብረቱ ይዘረፋል፣ በበሽታ ይሰቃያል፣ ይታሰራል፣ ይንገላታል ወዘተ፡፡ በዚህ ጊዜ እንባውን አባሽ፣ መካሪ፣ አይዞህ ባይ ይሻል፡፡ ማጽናናት ሃዘንን ማስረሳት ነው፡፡ ማጽናናት ችግሩን መፍታት ነው፡፡ ማጽናናት አይዞህ አለንልህ ብቻህን አይደለህም ብሎ ከጎኑ መቆም ነው፡፡ ማጽናናት ሲራብ ማብላት ሲጠማ ማጠጣት ሲታረዝ ማልበስ ነው፡፡ ማጽናናት የጠፋበትን ሃብትና ንብረት መተካት ነው፡፡ ማጽናናት ማለት የሚያድርበትን የሚያርፍበትን ጎጆ መቀለስ ነው፡፡ ማጽናናት ማለት ከኃጢአት ባርነት መመለስ ነው፡፡ ማጽናናት ማለት ንስሐን ማስተማር ነው፡፡ ማጽናናት ማለት የተስፋ ቆራጭነትን ስሜት ማጥፋት ነው፡፡ ማጽናናት ማለት ተስፋን ማለምለም ነው፡፡

እግዚአብሔር “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1 ሲል ከላይ በተመለከትነው መልኩ ነው፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር ህዝቦች በሥጋቸውም በነፍሳቸውም እግዚአብሔርን ሲያመልኩ እንዲኖሩ፣ በፍቅር በደስታ ምድርን እንዲሞሏት፣ መከራ ጭንቀታቸውን እንዲረሱ፣ ኃጢአታቸውን ትተው ወደ ጽድቅ እንዲመለሱ አድርጉ ማለቱ ነው፡፡


አባቶቻችን ዛሬም እኛ ከሃዘናችን፣ ከመከራችን፣ ከስቃያችን ሁሉ እንድንጽናና ምክራችሁ ትምህርታችሁ ያስፈልገናል፡፡ ማጽናናት እንደማስለቀስ እንደማሳዘን ቀላል አይደለም፡፡ ልቡ የተሰበረን ህዝብ አጽናኑ፣ የእኛ ተስፋ ነገ ብቻ ነው፡፡ ነገ አዲስ ቀን ነው ነገ ይችን ምድር ተሰናብተን ለዘለዓለም የምንሄድበት ቀን ነው፡፡ ነገ እንደ ሥራችን ገነት ወይም ሲዖል የምንገባበት ነው፡፡ ዕድሜ ዘመናችንን በምድር ላይ አናሳልፍም፡፡ እርስ በርሳችን አንጠላላ፣ እርስ በርሳችን አንገዳደል፣ አርስ በርሳችን አንወቃቀስ፣ እርስ በርሳችን ቂም በቀል አንያዝ ሁላችንም ነገ ከመቃብር በታች ነን፡፡ ይች ምድር አትጥበበን ነገ ጥለናት የምንሄድ ሰዎች ነን፡፡ ሁላችን በፍቅር እንተያይ፡፡ አባቶቻችን ካህናት፣ ጳጳሳት ሆይ “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሃዘናችንን አስረሱን፣ ኃጢአት በደላችንን በንሥሐ እጠቡት፣ ፍቅር ማጣታችንን በፍቅር ግዙት፣ መገዳደላችንን ደም መፋሰሳችንን በመስቀላችሁ ሰላም አቁሙት፣ እናንተ የመጽናናት መንገድን ምሩን እኛም እስከ ገነት ድረስ እንከተላችሁ፡፡ ያለእናንተ እኛ ምንድን ነን? ያለእናንተ ማን ሊያጽናናን ይችላል? ያለ እናንተ ማን ሊደርስልን ይችላል? ለሞቱት እረፍትን እና ምሕረትን ላሉት ፍቅር አንድነትን ከፈጣሪ ዘንድ ለምኑልን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘለዓለም እንድንኖር እርዱን፡፡ ይህን ካላደረጋችሁ ግን በኃጢአት ወድቀን  “ህዝቤ” ያለንን “ህዝብህ” ብሎ ለጠላት አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ለጠላት “ህዝብህ” ከመባላችን በፊት እናንተ ከፈጣሪያችን ጋር አገናኙን አጽናኑን፡፡ አጽናኙ መንፈስ እስኪመጣልንም ድረስ በኢየሩሳሌም እንጠብቃለን፡፡ “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1

Saturday, October 15, 2016

“ሁለት ክብደት በአንድ ሚዛን”

© መልካሙ በየነ

ጥቅምት 5/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ሰውየው መዛኝ ነው፡፡ የሚገርመኝ ግን እርሱ ራሱ የተመዘነ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ በእኛ አገር እንዲህ ዓይነቱ አሠራር የተለመደ ብቻ ሳይሆን የተዋሐደ ነው፡፡ ሳትመዘን መመዘን ትችላለህ ያ ማለት እኮ ሳትማር ማስተማር ትችላለህ፣ ሳትሰለጥን ታሰለጥናለህ ማለት ነው፡፡ ሳይመዘን የሚመዝነው  ሰውየ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ይጮኸል፡፡ ይህን ጩኸቱን የሰማ ሰው ዳግም በዚያ በኩል የሚያልፍ አይመስለኝም፡፡ ሰውየው ከሚጮኸው በላይ የምትጮኽ መሣሪያ ከሚዛኑ አጠገብ አለች፡፡ እርሷ ታዲያ መጮኋን አታቋርም ትላዝናለች፡፡
መዛኙ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ይጮኸል፡፡ አንድ ኩንታል ሊሞላው ጥቂት ኪሎዎች የሚቀረው ሰውየ ራሱን ሊመዝን ተጠጋ፡፡ ባለሚዛኑ 50ዋ እንዳትቀርበት እንጅ ሰውየውን መመዘን አልፈለገም፡፡ ሚዛኑን የሚሰብርበት ነው የመሰለው፡፡ ሆኖም ግን መዛኝ ነውና የውስጡን ስሜት ዋጥ አድርጎ የሰማይ ስባሪ የሚያህለውን ሰውየ ወደ ሚዛኑ እንዲወጣ ጠቆመው፡፡ መዛኙ አሁንም “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ይጮኸል፡፡ አንድ ቀጫጫ ሰው የመዛኙን ጩኸት ሰምቶ ሊመዘን ቀረበ፡፡ የሰማይ ስባሪ የሚያህለው ሰውየ ሚዛኗ ላይ እንደቆመ ነው፡፡ ጎንበስ ብሎ ማነበብ ስላልቻለ “ስንት ኪሎ ነኝ” ብሎ መዛኙን ጠየቀው፡፡ መዛኙም “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” ነህ አለው፡፡ ሰውየው ተናደደ፡፡ እኔ ግን በመዛኙ አልፈረድኩበትም ምክንያቱም አፉ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” ከማለት ውጭ ሌላ አልለመደለትምና ነው፡፡ ልማድ ክፉ ነው በጣም ክፉ በሽታ ነው፡፡ እንዲያውም ሰው ተጣልቶ ሲሳደብም “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” የሚል ነው የሚመስለኝ፡፡ ልማድ በሽታ ነው ሲባል ብዙ ነገር ትዝ ይለኛል፡፡ ሲጋራ ማጨስ ልማድ የሆነባቸው ሰዎች ሲጋራ ካላገኙ ያዛጋሉ፡፡ የሚገርመው ነገር የሲጋራ ጢስ ሆድ የሚሞላ አለመሆኑ ነው፡፡ ሰው ጢስ ቀረብኝ ብሎ ሲያዛጋ ስታዩ “አይ ልማድ” ማለታችሁ አይቀርም፡፡ ጫት የሚቆረጥሙትንም እንዲሁ ነው የምታዘባቸው፡፡ ፍየሎቻችን የናቁትን ቅጠል ሰዎች ሲያመነዥኩ ሳይ “አይ ልማድ፤ ልማድ እኮ ክፉ በሽታ ነው” እላለሁ፡፡ ወደ ነገሬ ልመለስና ሰውየው 96 ኪሎ ነው፡፡ ሚዛኗ ሰውየውን የፈራችው ትመስላለች 96ን ጽፋ ትርገበገባለች፡፡ መዛኙ 96 ኪሎ ነህ አለው፡፡ ተመዛኙ ሰውየም ከሚዛኗ ከመቅጽበት ወርዶ 50 ሳንቲሙን ወርውሮለት ሄደ፡፡
ቀጭኑ ተመዛኝ ወደሚዛኑ ወጣ፡፡ መዛኙ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50”  እያለ ደጋግሞ ይጮኸል፡፡ ቀጫጫው ሚዛኗ ላይ የወጣው በአንድ እግሩ ነው፡፡ ቀጫጫው በአንድ እግሩ እንደቆመ “መዛኝ ስንት ኪሎ ነኝ” አለው፡፡ መዛኙም 45 ኪሎ ነህ አለው፡፡ ከሚዛኗ ወረደ እና 15 ሳንቲም ወረወረለት፡፡ መዛኙ ግራ ገባው “ምንድን ነው ይኼ” አለው ተመዛኙን፡፡ ተመዛኙም “የቅድሙ ትልቁ ሰውየ 96 ኪሎውን በ50 ሳንቲም ተመዝኖ እኔ 45 ኪሎውን ለዚያውም በ1 እግሬ ቆሜ ተመዝኘ 15 ሳንቲም አነሰህ” አለ፡፡ መዛኙ በጣም ተበሳጨና “ቀጫጫ በል 354 ሳንቲም ጨምር” አለው፡፡ ተመዛኙም ያልሰማ መስሎ ትቶት ሊሄድ ሲል መዛኙ አንቆ ያዘው፡፡ ተመዛኙ “በአንድ እግሬ ቆሜ 45 ኪሎ ለተለካሁት እና በ2 እግሩ ቆሞ 96 ኪሎ ለተለካ ሰው እኩል ታስከፍላለህ እንዴ” አለው፡፡ መዛኙም “ስትፈልግ ተኝተህም መመዘን ትችል ነበር እርሱ ያንተ ሂሳብ ነው የእኔ ሂሳብ ደግሞ 50 ሳንቲም ነው” አለው፡፡ ተመዛኙም ነገሩ ስለከረረበት ተጨማሪውን 35 ሳንቲም ወርውሮለት ሄደ፡፡
በአንድ ሚዛን ሁለት ክብደት ሲመዘን ሳይ ገረመኝ፡፡ እንዳትስቁብኝ ግን ሚዛን እንኳን ይህን ሌላስ ይመዝን አይደል እንዴ ምን ያስገርምሃል እንዳትሉኝ፡፡ በሁለት እግሩ ቆሞ የተመዘነ እና በአንድ እግሩ ቆሞ የተመዘነ ሰው እኩል ሂሳብ መክፈላቸው በጣም ያስገርማል እንጅ፡፡ በአንድ ሚዛን ስለተመዘኑ ብቻ እኩል ክፍያ መክፈላቸው ያስገርማል፡፡ በዚህ ህግ መሠረት ሳይሆን ይቀራል ፍርድ የሚፈረደው፡፡ በአንድ ዓይነት ወንጀል ሳይሆን በአንድ ዳኛ ስለተዳኙ ብቻ እኩል መቀጣታቸው አያስገርምም፡፡ በሬ የሰረቀ እና መርፌ የሰረቀ ሰው እኩል ሲፈረድባቸው አይደንቅም፡፡ በእርግጥ ይኼ ሰማያዊ ፍርድ ስላልሆነ ፍትሐዊ ይሆናል ማለት አይቻልም፡፡ በሥራ ቅጥርስ ገጥሟችሁ አያውቅም፡፡ በአንድ ተቋም ስለተማራችሁ ብቻ እኩል የምትቀጠሩበት ጉዳይ አይገርማችሁም፡፡ 5 ዓመት 3 ዓመት ወይም 2 ዓመት የተማረ ሰው በአንድ ተቋም ስለተማሩ ብቻ እኩል ደመወዝ ሲከፈላቸው ይገርመኛል፡፡ ቢያንስ እኮ ያጠናኸው የትምህርት መስክ እና ያስመዘገብከው ውጤት ግምት ውስጥ መግባት ነበረባቸው፡፡ ግን የለም!

በአንድ ሚዛን ተመዘን እንጅ የግድ እኩል ትከፍላለህ፡፡ በአንድ ዳኛ ተዳኝ እንጅ እኩል ይፈረድብሃል፣ በአንድ ሃኪም ታከም እንጅ አንድ አይነት መድኃኒት ይታዘዝልሃል፣ በአንድ ተቋም ተማር እንጅ እኩል ትቀጠራለህ፣ በአንድ መምህር ተማር እንጅ እኩል ውጤት ታገኛለህ፡፡ ይኼ የተለመደ ሆኗል፡፡  በእርግጥ አንድ ሚዛን ሁለት ክብደት መለካቱን ስመለከት ከዚህም ባለፈ ያየሁት ነገር አለ፡፡ ሁለት ሰዎች በአንድ ህግ እኩል ሳይሆኑ ሲቀሩ ታያለህ፡፡ ለምሳሌ ለእኔ የሚሰራ ህግ ላንተ ላይሰራ ይችላል፡፡ እኔ በተዳኘሁበት ህግ አንተ ላትዳኝ ትችላለህ፡፡ ሰው የገደለ ወንጀለኛ በሙሉ አንድ ዓይነት ፍርድ አይጠብቃቸውም፡፡ አንዳንዱ መግደልን እንደመብትም የተሰጠው ይመስላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ እድሜ ልኩን እስር ቤት ይጣላል አንዳንዱም ከ10 ዓመት በኋላ ይወጣል ብቻ ይለኛኛል፡፡ በአንድ ወንጀል እኩል አለመዳኘት እንደዚህ ነው፡፡ አንድ ሚዛን ሁለት ክብደት እንደለካው ማለት ነው፡፡ ብቻ ብዙ ነገር አለ እናንተም ጨምሩበት!!!!

Wednesday, October 5, 2016

የሚጠት ወይስ የምጽአት ዋዜማ?

© መልካሙ በየነ

መስከረም 25/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
“ሚጠት” መመለስ ነው “ምጽአት” ደግሞ መምጣት ነው፡፡ መከራ፣ ስቃይ፣  እንግልት፣ ረሃብ፣ ጥም፣ እርዛት፣ ሰሚ ማጣት  ያሰድዳል፡፡ መሰደድ ፍርሐት አይደለም፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል  አረጋዊው ዮሴፍን ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን እና  እናቱ ድንግል ማርያምን ይዘህ ወደ ግብጽ ሂድ ብሎታል፡፡ አምላክ ሁሉን ማድረግ ይችላል፤ ንጉሡ ሔሮድስን በተቀመጠበት ዙፋን ላይ ጸጥ ማድረግ ይችላል፤ 14 እልፍ የቤተልሄም ሕጻናት እንዳይሞቱ ማድረግ ይችላል ግን መከራ ሲመጣባችሁ ፈተና ሲገጥማችሁ ክፉ ንጉሥ ሲነሣባችሁ እኔ ያደረግሁትን አድርጉ ለማለት አርአያነቱን ለማሣየት ተሰደደ፡፡ አሁን ወደ ግብጽ እየተሰደዱ ናቸው፡፡ የስደታቸው ምክንያት ደግሞ የክፉው ንጉሥ የሔሮድስ አሰቃቂ ግድያ ነው፡፡ ለዚህ ነው መሰደድ ፍርሐት አይደለም ያልኩት፡፡ ሕጻኑ ያለጊዜው ደሙ አይፈስም ስለዚህ ነው መሰደድን የመረጠው፡፡ ሆኖም ግን ጊዜው በደረሰ ጊዜ ደሙ የሚፈስበት ቀን ሲደርስ ራሱ በፈቃዱ ለገዳዮቹ እጁን ሰጥቷል፡፡ እዚህ ላይ የምንገነዘበው ነገር ለሚገድሉት እጁን ሰጠ እንጅ ልግደላችሁ አላለም፡፡ ለዚህ ነው ክርስትና ውስጥ እንሞታለን እንጅ አንገድልም እንደማለን እንጅ አናደማም እንቆስላለን እንጅ አናቆስልም የምንለው፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና በዚህ በዘመነ ሄሮድስ ሁለት ምርጫዎች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ የመጀመሪያው በንጉሡ እጅ መሞት ሌላኛው ደግሞ መሰደድ ናቸው፡፡ እንግዲህ ሁለተኛው ምርጫ ነው ለአረጋዊው ዮሴፍ የተነገረው እርሱም እንደተነገረው ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡ ከዚያም ምን ቢገዙ፣ ምን ቢነዱ፣ ምን ቢጨክኑ ከሞት እጅ ማምለጥ አይቻልምና ይህ ጨካኝ ንጉሥ ሔሮድስ ሞተ ያን ጊዜ “ተመየጢ ተመየጢ ተመየጢ ሱላማጢስ” ተባለች፡፡ አወ አሁን በቤተልሔም መገደል የለም፣ ያ ጨካኙ ንጉሥ ከመቃብር በታች ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተልሄም መመለስ አለባቸው “ሚጠት” ማለት ይህ ነው፡፡ ሰው የሚሰደደው አገሩን ጠልቶ አይደለም ችግር ሆኖበት እንጅ፤ ስለዚህ ያ ችግር ሲፈታ መመለሱ አይቀርም፡፡ የንጉሡ ሞት ለሚጠት ዋዜማ ነበር፡፡
እስራኤላውያንም በግብጽ የባርነት ታሪክ ውስጥ ብዙ እንደተቸገሩ እናውቃለን፡፡ ዛሬ “የግብጽ ፒራሚድ” እያልን ግብጽን የምናነሣት ያኔ ድሮ እስራኤላውያን ራሳቸውን እንደ እባብ እየተቀጠቀጡ ባቦኩት ጭቃና ሲሚንቶ የተገነባ ነው፡፡ ራሄል የመውለጃዋ ቀን ደረሰ ነገር ግን ማንም ሊያሳርፋት አልቻለም ነበር፡፡ ምጧ ደረሰ ጭቃ እያቦካች ነው፡፡ አሁንም እየተደበደበች ምጧን ዋጥ አድርጋ ጭቃ ታቦካ ጀመረች፡፡ አልቻለችም እዛው ጭቃው ላይ ወለደች፡፡ ከዚያም ልጆችሽን ከጭቃው ጋር እርገጫቸው ደማቸው ጭቃችንን ያጠነክርልናልና ተባለች፡፡ አስቡት ይህን ግፍ፡፡ ይህ ግፍ ለእስራኤላውያን “ሚጠት” ዋዜማ ነበር፡፡ እንባዋን ወደ ሰማየ ሰማያት ረጨች አምላክ እንባዋን ተቀበለ ድንቅ መሪ የሆነውን ሙሴ አዘጋጀ ከዚያም ግብጽን ዳግም ባሪያ ሆነው ላይኖሩባት ተሰናብተው ወደ ርስት ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ ይህ የእስራኤላውያን ሚጠት ነው፡፡
በተመሳሳይ ወደ ፋርስ ባቢሎን በባርነት በተሰደዱ ጊዜ ኤርምያስ ሳይቀር አብሮ ተሰዷል፡፡ በዚህ ወቅት ሀገሪቱ ተፈታለች ሰው የሚባል ፍጡር ጠፍቶባታል፡፡ ይህ የሚሆነው ለ70 ዓመታት ያህል ነበር፡፡ ከዚህ ጥፋት በእግዚአብሔር ጥበብ የተሠወሩት የኤርምያስ ደቀመዛሙርት ባሮክና አቤሜሌክ ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው ህዝብ ግን የአገሩን ጥፋት በዓይኑ ተመልክቷል፤በባርነት ተሰዷል፡፡ አቤሜሌክ ለድውያን የሚቀባ መድኃኒት ሊያመጣ ተላከ ባሮክም መቃብረ ነገሥትን እንዲጠብቅ ተደረገ፡፡ የሚገርመኝ የአቤሜሌክ ጉዳይ ነው፡፡ መድኃኒቷን ቆርጦ ሲመጣ ደከመውና ከጥላ ሥር አረፍ አለ በዚያው 66 ዓመት ተኛ ሲነቃ እንቅልፉ በደንብ አልለቀቀውም ነበር፡፡ ተነሥቶ መንገዱን ሊቀጥል ሲል መንገዱ ሁሉ ጠፋበት አገሪቱ ጠፍታለች ሰው አይኖርባትም በኋላ ግን መልአኩ ከባሮክ ጋር አገናኝቶታል፡፡ ከዚያም መድኃኒቷን ለኤርምያስ በንስር አሞራ ላኩለት፡፡ ያኔ ለሚጠት ዋዜማ ነበር 4 ዓመት ብቻ ነበር የቀራቸው፡፡
አገራችን እንግዳ ተቀባይ፣ በማንም ወራሪ ጠላት ያልተንበረከከች የጀግኖች መፍለቂያ፣ የፍቅር አገር ናት፡፡ ለራበው የሚያበላ፣ ለጠማው የሚያጠጣ፣ ለበረደው የሚያለብስ፣ ለጠላት እጁን የማይሰጥ፣ ለማንም የውጭ ኃይል የማይንበረከክ ጀግና የሚፈልቅባት ቅድስና የማይጠፋባት፣ ጥበብ የሚመነጭባት፣ ጠላት የሚያፍርባት፣ በገንዘብና በብልጭልጭ ነገር የማይታለል ህዝብ ያላት አገር ናት፡፡  ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ የመጣውን የጣሊያን ጦር በቆራጥ የአገር ፍቅር እንዴት እንዳንቀጠቀጠ ህዝባችንን አይተናል፡፡ ዛሬ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ጀግና ተብሎ ማዕርግ እንደሚጨመርለት ያለ ወኔ አይደለም የጥንቱ ጀግንነት፡፡ ዛሬ  እንደ ሔሮድስ፣ እንደ ሂትለር እጃችን በደም ጨቅይቷል፡፡ ወንዞቻችን ደም እያጎረፉ ናቸው፣ ሴቶቻችን ተገዳዮችን እያረገዙ ናቸው፣ የቻሉት ስደትን መርጠው እየተሰደዱ ናቸው ያልቻሉትም በአገራችን መቃብራችንን አድርግልን ብለው ፈጣሪያቸውን እየተማጸኑ ናቸው፡፡ ይህ ዘመን ለሀገራችን ከባድ የሀዘን፣ የዋይታ፣ የለቅሶ፣ የስቃይ ዘመን እየሆነ ነው፡፡ ታዲያ “ሚጠት” ነው ወይስ “ምጽአት” ነው እየቀረበን ያለው፡፡
“ምጽአት” የጌታ ለዘላለም ፍርድ ወደዚህ ዓለም መምጣት ነው፡፡ የምጽአት ዋዜማዎች በርካቶች ናቸው ከእነዚህ ውስጥ ግን በማቴ 24 ላይ “ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ” ይላል፡፡ ዛሬ በእኛ ላይም እንደዚያ እየሆነ ነው፡፡ ጦርን የጦርንም ወሬ በርቀት ሳይሆን በቅርበት እየሰማን ነው፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እየተነሣ ነው፡፡ ለአገራችን አስከፊ የሚሆነው ህዝብ በህዝብ ላይ ከተነሣ ብቻ ነው፡፡ መንግሥት በመንግሥት ላይ፤ መንግሥት በሕዝብ ላይ ቢነሣ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሚያመጣው ተጽእኖ ከባድ አይሆንም ህዝብ የሌለው መንግሥት ምንም ሊያደርግ ስለማይቻለው፡፡ ህዝብ በህዝብ ላይ ከተነሣ ግን ተጽእኖው ከበድ ያለ ይሆናል፡፡ ህዝብ በህዝብ ላይ ከተነሣ ቋንቋ፣ ቀለም፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ጎጥ፣ የደም ዓይነት ሁሉ የጥላቻ ምንጭ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥትንም እንዳይቆም ያደርገዋል ሀገርንም ያፈራርሳል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ” የሚለው ቃል የምጽአት ዋዜማ ነው፡፡ አገራችንን እንደቀደመ ክብሯ ለማስቀጠል ካስፈለገን ህዝብ በህዝብ ላይ መነሣት የለበትም፡፡ በዘር፣ በጎሳ፣ በብሄር፣ በቋንቋ አንከፋፈል አንድ እንሁን፡፡ መከፋፈል ካለብን ወድደን ባመጣነው ነገር ብቻ እንጅ ተፈጥሮ በቸረን ነገር ሊሆን አይገባውም፡፡ ከሆነ ዘር፣ ከሆነ ብሄር፣ ከሆነ እምነት፣ ከሆነ ቋንቋ ተናጋሪ በሆነ ብሔር የተፈጠርነው ፈልገን አይደለም ይህ የፈጣሪ ሥራ ብቻ ነው፡፡ አገራችን ደግሞ በህብረ ብሔሯ ዓለምን የምታስቀና ናት፡፡ ስለዚህ ይህን ህብረ ብሔር አንድ ማድረግ ካልቻልን መለያየታችን ሞታችንን ያፋጥነዋል፡፡

ለዚህ ነው አሁን በአገራችን እየተፈጸመ ባለው ግድያ የእናቶች ለቅሶ ከፍ ብሎ ሲሰማ ሳስተውል ዋዜማነቱ ወደ ቀደመ ክብራችን ወደ ቀደመ ኃያልነታችን ወደ ቀደመ አልደፈርም ባይነታችን ወደ ቀደመ ጀግንነታችን ልንመለስ ይሆን ወይስ ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ” እንዳለው ምጽአት ቀርቦ ይሆን ብየ እንዳስብ የተገደድኩት፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ወይ ለ “ሚጠት” ወይ ለ “ምጽአት” ዋዜማ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አምላከ ቅዱሳን ለአገራችን ሰላምን እንዲሰጥልን ሁላችንም እንጸልይ መፍትሔው ከፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የፈቃድ ጾም ቢሆንም ነገ መስከረም 26 ጀምሮ የጽጌ ጾም ይጀመራል እስኪ ለዚሁ ዓላማ ብለን ዘንድሮ እንጹመው ሱባኤ እንያዝ፡፡ ሌላው እምነትም በራሱ ለዚሁ ብሎ በእምነት ሥርዓቱ የሚገባውን ያድርግ፡፡