Wednesday, March 30, 2016

ውለታዋን የዘነጋ መንጋ

© መልካሙ በየነ
መጋቢት 21/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  ገና ዳዴ ሳልል ለመጀመሪያ ጊዜ ከተወለድኩበት ቤት ወጥቼ የተመለከትኳት ዳግም ከአብራከ መንፍስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ የተወለድኩባት የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ የበላሁባት ደሙንም የጠጣሁባት በልቤ ውስጥ ገና በጨቅላ ዕድሜየ የታተመች የፍቅር ቤት ናት፡፡ የዚህችን ቤት ፍቅሯን የቀመስኩት ጣዕሟንም ያጣጣምኩት ገና በ40 ቀኔ ነው፡፡ ከፍ ስልም ወተት እና የማር ወለላ ከዚያም በላይ ምሳሌ የሌለውን ትምህርቷን ሳትሰስት ሳትነፍግ መግባኛለችና ከእቅፏ መውጣት አልሻም፡፡ የቤተክርስቲያን እቅፏ ይሞቃል፣ የቤተክርስቲያን እናትነቷ ይለያል፣ የቤተክርስቲያን ሰላሟ ያሳርፋል፣ የቤተክርስቲያን ፍቅሯ ያጠግባል፡፡ ስለዚህም አልሸሻትም አልርቃትምም ዕለት ዕለት አስባታለሁ እርሷም ወልደ ማርያም ልጄ ና! እያለች ታስበኛለች ትስበኛለችም፡፡ እናቴ ናትና መቼም ቢሆን ጥፋቷን አልመኝም፡፡ ከቻልኩም እንደ አቤሜሌክ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየኝ ብሎ ስድሳ ስድስት ዘመን በእንቅልፍ እንዳሳለፈ እኔም እንዲሁ የእናቴን ጥፋት አታሳየኝ ብየ እለምናለሁ፡፡ እናቴ ስትጠፋ ማየት አልሻምና፡፡

ዛሬ ብዙዎች የዚችን እናት ጡት ነክሰዋል፡፡ ዛሬ ብዙዎች የዚችን እናት ጣት ቆርጥመዋል፡፡ እናቴ ቤተክርስቲያን  ሆይ! እኔ ልጅሽ ነኝ እነርሱም ልጆችሽ እንደሆኑ ያወራሉ እኔ ጥፋትሽ አልታየኝም እነርሱ ግን ጥፋትሽ ጎልቶ ታያቸው፡፡ ለእኔ ያልታየኝ ጥፋትሽ ለእነርሱ እንዴት ጎልቶ ታየ? እናቴ ሆይ! ንገሪኝ በእርግጥ እናት ነሽና ገመናቸውን እንደምትሸሽጊላቸው አውቃለሁ ግን እኮ እኔም ልጅሽ ነኝ ፡፡ ከፊደል ጀምረሽ ያስተማርሻቸው፣ ዳዊት ያስደገምሻቸው፣ ቅኔውን ያስቆጠርሻቸው፣መጽሐፍትን  የመገብሻቸው ወተት ፍቅርሽን ያጠባሻቸው ናቸው አኮ ዛሬ አጥርሽን ለማፍረስ ላይ ታች የሚሉት፡፡ በእውነት እናቴ ሆይ ግልጹን ንገሪኝ ምንሽ ነው የጎሰቆለው? ምንሽስ ነው ያረጀው? ምንሽስ ነው እንቅፋት የሆነው? ምንሽስ ነው ለድኅነት ጉዞ መሰናክል የሆነው? እነርሱ እናድሳት እያሉ ነው፡፡ እኔ ደግሞ አንች ሁሌም አዲስ መሆንሽን ነው የማውቀው የምመሰክረው፡፡ የአንች እርጅና ለእነርሱ ብቻ ነው እንዴ የሚታየው? የአንች ጉስቁልና ለእነርሱ ብቻ ነው እንዴ የተገለጠው? ወይስ ደግሞ ዓይናችን አንድ አይደለም? ታሪክሽ ታሪኬ ነው፤ ፍቅርሽ ፍቅሬ ነው፣ ትምህርትሽ ትምህርቴ ነው፣ ሰላምሽ ሰላሜ ነው፣ ድካምሽ ድካሜ ነው፣ ብርታትሽ ብርታቴ ነው፣ ጉዳትሽም ጉዳቴ ነው፣ ጠላትሽም ጠላቴ ነው፡፡ ስለዚህ በአንች ለሚመጣብኝ ሁሉ ቅድሚያ ተሰላፊ እንደምሆንልሽ አስባለሁ፡፡

ግን እኮ የአገራችን ሁሉም ታሪክ አንችው ነሽ፡፡ ግን እኮ የአገራችን ሁሉም ነገር አንችው ነሽ፡፡ ግን እኮ የአገራችን ሰላምና ፍቅር አንችው ነሽ፡፡ ግን ብዙዎች ውለታሽን ዘንግተዋል፡፡ ላሊበላን ያነጸው ልጅሽ ነው፡፡ ላሊበላን የሚጎበኝ ከዓለም ዳርቻ የሚጎርፈው ሕዝብ አብዛኛውን ክፍያ የሚከፍለው ለመንግሥት ነው፡፡ የጥምቀት በዓል የመስቀል በዓል የአንች ንብረት የአንች ሃብት ነው፡፡ ይህንን አስገራሚ ድንቅ የሆነውን የበዓል አከባበርሽን ለማየት ከዓለም ዳርቻ የሚጎርፈው ህዝብ አብዛኛውን ነገር አሁንም ለመንግሥት ነው የሚከፍለው ግን ውለታሽን አላወቀም፡፡ ዩኔስኮ ከመዘገባቸው የሚዳሰሱም ሆኑ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ከእምነት ተቋማት መካከል ብቸኛዋ አንችው የእኛ ቤተክርስቲያን ነሽ፡፡ ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፈው እኮ ላሊበላን ለመጎብኘት ነው፡፡ ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፈው እኮ የጥምቀትን በዓል አከባበር ለመመልከት ነው፡፡ ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፈው እኮ የመስቀልን (የደመራን) በዓል አከባበር ለመመልከት ነው፡፡ ዓለም እኮ አረፋ እና መውሊድን ለመጎብኘት ኢትዮጵያ መጥቶ አያውቅም፡፡ ዓለም እኮ የፕሮቴስታንቱን ጭፈራ ለመመልከት ኢትዮጵያ መጥቶ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያን ለዓለም ከጥንት ጀምራ እስከአሁን ድረስ እያስተዋወቀች ያለችው ብቸኛዋ እምነት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት፡፡ በዚህ እውነት ላይ ማንም ተቃውሞ ሊያነሣ አይችልም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ውለታዋ የሚሰጣት ምላሽ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ተሐድሶ መናፍቃኑ ይህን ሁሉ ባህሏን፣ ታሪኳን፣ ትምህርቷን፣ ዶግማዋን እና ቀኖናዋን ካላደስናት እያሉ ሌሊት ከቀን መሠሪ ተግባራቸውን እያከናወኑ ናቸው፡፡ በእውነት የመስቀል (የደመራ) በዓል እና የጥምቀት በዓል ባይከበር አገሪቱስ አሁን እያገኘች ያለውን የውጭ ምንዛሬ ልታገኝ ትችላለችን? የተሐድሶዎቹ ዓላማ እኮ ሃይማኖታዊ ብቻም አይደለም አገራዊ ችግርም ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን ትኩረት ሰጥቶ ሊፈትሻቸው ሊያጠናቸውም ይገባል፡፡ የቤተክርስቲያን ውለታ ለእኛ ለልጆቿ ብቻ አይደለም ለማንኛውም ዜጋ ሁሉ ነው፡፡ ይህን ውለታዋን ግን ላይረዱ ይችላሉ ይህን ውለታዋን ግን ላይገነዘቡ ይችላሉ እኛ ግን ልጆቿ ነንና እንረዳለን እንገነዘባለንም፡፡ እኛ ግን እናታችን ናትና ውለታዋን አንዘነጋም ውለታዋን እንከፍላለን እንጅ፡፡

ተሐድሶ መናፍቃኑ ከውስጥ ፕሮቴስታንቱ፣ ሙስሊሙ፣ መንግሥት ሳይቀር ከወጭ ጦራቸው የተሰበቀው ወደዚች እናታችን ነው፡፡ ግን ለምን? ለእኔ ይህ የሁልጊዜ ጥያቄየ ነው፡፡ መልሴ ደግሞ አንድ ብቻ ነው እርሱም “ውለታዋን የዘነጋ መንጋ ስለተፈጠረ ነው” እላለሁ፡፡ ማንም እኮ የመሰለውን እምነት ሊከተል ሕገመንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን አምላካዊም መብት ነው፡፡ አንዱ በሌላው እየገባ ማማሰል ግን ሕገመንግሥታዊም አምላካዊም አይመስለኝም፡፡ ግን ብዙዎች በማይመለከታቸው እየገቡ ሲያማስሉ ዝም ተብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያናችን ማሻሻል የሚገባት ነገር ካለ ለእናታችን ለመንገር የምንቀርበው እኛው ልጆቿ ሳለን መናፍቃኑ ትሻሻልልን ትታደስልን እያሉ የሚጮኹት ጩኸታቸው የት ሊያደርሰን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ትሻሻል ትታደስ ማለት ምን ማለት ነው? ብዙ አሠራሮች አሉ መሻሻል መታደስ የሚገባቸው፡፡ ለምሳሌ የቤተክርስቲያናችን የሂሳብ አሠራር፣ የቤተክርስቲናችን የሙዳዬ ምጽዋእት አቀማመጥ ደኀንነት፣ የቤተ ክርስቲያናችን የአሥራት እና የበኩራት ክፍያ አሰባሰብ፣ የቤተክርስቲያናችን የመባእ አሰባሰብ ዘዴ ላይ ሊሻሻል  ሊስተካከል የሚገባው አሰራር አለ፡፡ ይህንን እኮ ማሻሻል ያለብን እኛው ልጆቿ እኛው አማኞቿ ነን፡፡ ሌላው ከውጭ ያለ  ምንም አይመለከተውም ምክንያቱም እናትነቷን አምኖ አልተቀበለምና፡፡  ግን በእውነት የሚፈልጉት እንዲህ ያለውን ለውጥና መሻሻል ነውን? አይደለም፡፡ እነርሱ የተነሡትና የዘመቱት ዶግማዋ እና ቀኖናዋ ላይ ነው፡፡ ዶግማዋ ደግሞ በማንም ጩኸት ሊሻሻል አይችልም ምክንያቱም የእምነታችን መሠረት ነውና፡፡ ዶግማችን የሆነውን በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ማመንን ካሻሻልነው፣ አምላክ ሰው ሆነ ሰውም አምላክ ሆነ በሥጋ ማርያም ተገለጠ የሚለውን የሥጋዌን ምሥጢር ከለወጥነው፣ ሰው ዳግም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ካልተወለደ በቀር መንግሥተ ሰማያትን አይወርስም የሚለውን ምሥጢረ ጥምቀት ከቀየርነው፣ ሥጋዬን ያልበላ ደሜንም ያልጠጣ የዘላለም ሕይወትን አያገኝም የሚለውን ምሥጢረ ቁርባንን ካሻሻልነው፣ የሰው ልጅ ከሞት በኋላ ትንሣኤ ዘለክብር ወይም ትንሣኤ ዘለሐሳር ይነሣል የሚለውን ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ከሰረዝነው ወይም ካሻሻልነው እምነታችን መሠረቱ ምን ሊሆን ነው? ይህን ሁሉ ካሻሻልን በኋላስ እምነታችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊባል ይችላልን? በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ ዶግማችን ትንሽም ብትሆን ከተዛባች ከተሻሻለች ከተበረዘች እምነታችንም አብሮ ተለወጠ ማለት ነው፡፡ ሙስሊሞች እኮ ሙስሊም የሚባሉት፣ ፕሮቴስታንቶችም ፕሮቴስታንት የሚባሉት ዶግማቸው ከእኛ ዶግማ ጋር አንድ ስላልሆነ ነው፡፡ እነርሱ የራሳቸው የሆነ ዶግማ አላቸው እኛም እንዲሁ የራሳችን የሆነ ዶግማ አለን፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሆኖ ለመጽናት ከዚህ ዶግማ ውጭ ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝም መመልከት አይቻልም፡፡


ምንም እንኳ ውለታዋን የዘነጋ መንጋ ቢፈጠርም ቤተክርስቲያን ግን የገሐነም ደጆችም የማይችሏት ሰማያዊት ናት፡፡ ስለዚህ እናድሳት እያሉ ሥርዓቷን ጥሰው ለማስጣስ፣ ዶግማዋንም አፍርሰው ላማስፈረስ የሚጥሩ ሰዎችን በጥንቃቄ ልንታገላቸው ይገባል፡፡ አሁን እየመጡብን ያሉት በዓይናችን ብሌን በሆነችው እናታችን ቤተክርስቲያን ነው፡፡ በዚች እናታችን ደግሞ ከጥንትም ጀምረን ቀልደን አናውቅም አባቶቻችን በሰይፍ የተቀሉላት በመጋዝ የተሰነጠቁላት እንደ ሽንኩርት የተከተፉላት ናት፡፡ እባካችሁ ወገኖቼ ዘመኑ ክፉ ዘመን ነውና ለእናታችን እንቁምላት፡፡ መላእክት ሌሊት ከቀን በሚጠብቋት ቅድስት እናታችን ውስጥ የተሐድሶ መንፈስ ያደረባቸው ሰዎች እንዳያስተምሩ፣ እንዳይሰብኩና እንዳይዘምሩ እንከላከል፡፡ እናታችን እናታቸው ስላልሆነች ሊመርዟት ቆርጠዋልና፡፡

No comments:

Post a Comment