Thursday, June 30, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 8


© መልካሙ በየነ
ሰኔ 23/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 7 “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት” ክህደት እንደሆነ በሚገባ ተመልክተናል በዚህ ክፍልም የዚህን ተከታይ መጽሐፋቸው “ወልደ አብ” ላይ ያለውን መነሻ አድርገን እንመለከታለን፡፡
በመጀመሪያ የመጽሐፉ ርእስ “ወልደ አብ” የተባለበትን ምሥጢር ግን ሁላችን ልንረዳው ይገባል፡፡ “ወልደ አብ” ብለው መሰየማቸው አብ በመለኮትና በሰውነት ሁለት ጊዜ ወልዶታል ብለው ስለሚያስቡ ነው “ወልደ ማርያም” ከሚለው ስሙ ይበልጣል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ ለማንኛውም እምነታቸው የራሳቸው ስለሆነ ባይመለከተንም በአንድ ገዳማችን ስም ስለጻፉት ግን የእኛ አስተምህሮ እንዳልሆነ እንገልጽ ዘንድ እንገደዳለን፡፡ ስለዚህም ዝም አንልም!!!
ወልደ አብ ገጽ 219 ላይ ነኝ ዛሬ “ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ፡፡ ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ፡፡ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም፡፡ ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪” እያለ ክህደት እንደ ጉድ ይጎርፋል፡፡ ቃል በቃል እንመልከት፡፡
“ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ” ሥጋ ከፈጣሪው የጸጋ ልጅነትም የለውም ነበር ማለታቸው አዳም ስለበደለ እና ጸጋ እግዚአብሔር ስለተገፈፈበት ነው፡፡ ሆኖም ግን እምቅድመዓለም የባሕርይ ልጅነት ያለው መለኮት ሲዋሐደው የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አደረገ እና ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነትንም አገኘ ብለው ይደመድማሉ፡፡ በጣም ጥሩ ነው አሁን ላይ መለኮት ሲዋሐደው ሥጋ አምላክ ሆነ ክቡር ሆነ የቃል ገንዘብ ገንዘቡ ሆነ እና ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ቀጥለው ይህንን ይጣረሱታል፡፡ “ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ከላይ “የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ” ብለው ነበር አሁን ደግሞ እንደገና ተመልሰው “በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ብለው የሚጋጭ ሃሳብ አስፍረዋል፡፡ ለዚህ ሃሳባቸውም የሚደግፍ ማስረጃ ብለው ሰውን ለማደናገር ግዕዙን ብቻ ጠቅሰው አማርኛውን ሳያስቀምጡት አለፉ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ግእዝን እንደማይችል ስለሚያውቁ እንዲህ ይላልሳ እያሉ ያወናብዳሉ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ፍችውም “ሃብታም ሲሆን እናንተ በርሱ ድህነት ባለጠጋዎች ትሆኑ ዘንድ ስለእናንተ ደሃ ሆነ” የሚል ነው፡፡ እነርሱ ግን ሙሉውን ሳይጠቅሱ ቆርጠውታል፡፡ ሆኖም ይህ ጥቅስ “ቃል በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ” ለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ ስለዚህም ማስረጃነቱን ለማወናበድ ካልተጠቀሙበት በቀር ምንም ማረጃነት የለውም፡፡ ማስረጃ ሊሆን የማይችለውም ነድየ የሚለው የሚስማማው ለሥጋ ነው እንጅ ለመለኮት አይደለምና ቃል ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ የሥጋ ንድየት በቃል ባዕልነት ተወግዷል፡፡ ስለዚህ የዚህ ማስረጃነት ተቀባይነት የለውም፡፡ ቀጥለውም  “ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም” ይላሉ፡፡ በክፍል 7  ዳግመኛ “ከአብ በማኅጸነ ማርያም ተወለደ” የሚለውን ክህደት ተመልክተናል ስለዚህ እዚህ ላይ አልደግመውም፡፡  በመቀጠልም “ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር” ብለው ወልድን ከአብ ያሳንሳሉ፡፡ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በመግዛት አንድ ናቸው፡፡ ይህ ምሥጢረ ሥላሴ ነው፡፡ ይህ የመግዛት አንድነት ወልድ ሥጋን በለበሰ ጊዜ አልተቋረጠም፡፡ ስለዚህ ወልድ የመግዛት አንድነቱን ይዞ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ሥጋን ቢዋሐድ ሥጋ የመግዛት ሥልጣንን ከወልድ ያገኛል እንጅ ከአብ አያገኝም፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው ወልድ ባለበት አብና መንፈስ ቅዱስ አሉና አብ ለወልድ የመግዛት ስልጣንን የሚሰጠው ወልድም የመግዛት ስልጣንን የሚቀበል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከመግዛት አንድነቱ የጠለየበት ጊዜ ስለሌለ፡፡ ምናልባት በግልጽ አልጻፈላቸው ይሆናል እንጅ ጸሐፊው “ገብረ መድኅን እንዳለው” ወልድ አምላክነቱን ለዓይን ጥቅሻ ታህል አጥቷል ብሎ ያምናል፡፡ ሎቱ ስብሐት!
አሁንም በግእዝ ጠቅሰው ለማወናበድ “ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰” ይላሉ ትርጉሙን እንመልከት፡- “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ፡- ክብሬን ለሌላ ምስጋናየንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” የሚል ነው ቆርጠው ስላስቀሩት ነው እንጅ፡፡ እስኪ አስተውሉ ወገኖቼ! “ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር” ለሚለው “ክብሬን ለሌላ ምስጋናየንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” ማስረጃ ሊሆን የሚችለው በምን ሂሳብ ነው፡፡ ወይስ ደግሞ ግእዝ ስለሆነ የተጠቀሰው ሁሉ ማስረጃ ይሆናል ማለት ነው፡፡ “ገብረ መድኅን እንዳለው” በእውነት የመጽሐፍ ሊቅ አይደለም ማለት ነው እንጅ እንዲህ ባላለም ነበር፡፡ ከመጻሕፍት ሊቃውንት የወሰዳቸው ቃላት “እንዲል” “አንድም” የሚሉትን ብቻ ነው እንጅ እውቀቱን ትምህርቱን አልወሰደም፡፡ በራሱ ደስ እንዳለው የሚጽፍ የልብወለድና የፈጠራ ጸሐፊ ነው፡፡ በመቀጠልም “መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው” ይላሉ፡፡ አብን ሰጭ ወልድን ተቀባይ ልናደርገው እንዴት እንደፍራለን፡፡ ወልድስ ለመግዛት አብን እያስፈቀደ ነው ልንል እንዴት እንደፍራለን፡፡ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ መቀበል ያስፈለገውስ እምቅድመዓለም የባሕርይ ሕይወቱ የሆነው መንፈስ ቅዱስ አልቆበት ነው ልንል ነውን? ወይስ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ሊያድስ ነው ልንል ይሆን? ለዚህም ማስረጃቸው ያው የተለመደው ግእዝ ብቻ ነው፡፡ “አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ትርጉሙም “እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል” የሚል ነው፡፡ አንድምታውን ስትመለከቱ “ከእግዚአብሔር አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ተወልዶ የመጣ እሱን እግዚአብሔርነቱን ያስተምራል፡፡ ሀብተ መንፈስን በልክ የሚሰጥ አይደለምና” ይላል ተመልከቱት ሁላችሁም፡፡ ሌላው የጠቀሱት “ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪” የሚል ነው ትርሙም “ሁሉን ወራሽ ባደረገው” ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ሁለቱም ቦታዎች ላይ ያስቀመጧቸው ጥቅሶች “ወልድ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው” የሚል አይደለም፡፡ ስለዚህ ማስረጃ ተብለው የተቀመጡት ሁሉ ማስረጃነት የሌላቸው የመጽሐፉን ገጽ ብቻ ለመጨመር የተጻፉ እንደሆኑ ልብ ይሏል፡፡

ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment