Thursday, August 4, 2016

“የአንድ ቀን ስህተት እስከሞት”

© መልካሙ በየነ
ሐምሌ 28/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ወንድሞቼ እህቶቼ እንደምን ከረማችሁ፡፡ በሥራ ምክንያት የተወሰኑ ሳምንታትን ጠፍቻለሁ ወደፊትም ልጠፋ እችላለሁ በእርግጥ፡፡ አምላክ ፈቀደልኝና ዛሬ ይችን መልእክት እንድጽፍ ቻልኩ፡፡
እውነት አለ ውሸትም አለ፤ ትክክል አለ ስህተትም እንዲሁ፡፡ ምንም ቢታፈኑ እውነትና ጭስ መውጫ አያጡም ይባላል፡፡ በእርግጥ ስህተትም ቢታፈን ስህተትነቱን እንደ እውነት እንደ ትክክል እስካልተቀበልነው ድረስ መውጫ አያጣም፡፡ ስህተትነቱ ይታወቅ ዘንድ ለሁሉ ይገለጣል ሆኖም ግን ታፍኖ እንዲኖር የእኛ ተጽእኖ ከባድ ነው፡፡ ለዚህም ነው አንድ ቀን በተሳሳትነው ስህተት እድሜ ልካችንን ስህተት እንድንሠራ እድልን የምንሰጠው በርን የምንከፍተው፡፡ የትምህርት ማስረጃዎቻችንን ተመልከቷቸው፡፡ በሆነ ሰው ስህተት ወይም በሆነ አጋጣሚ ስማችን ላይ ያልተገባ ፊደል ተጨምሮ ወይም ከሚገባው ፊደል ጎድሎ የትምህርት ማስረጃ ተሠርቶ ይሰጠናል፡፡ ይህ የትምህርት ማስረጃ ስህተት መሆኑን እያወቅን ማስተካከል ባለመቻላችን ብቻ ወደ ቀጣይ ስህተት እንጓዛለን፡፡ በብዛት እነዚህ አጋጣሚዎች የውጭ ዕድል ባገኙ ሰዎች ዘንድ ጎልተው ይወጣሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ <<ABEBE>> የሚባል ሰው <<ABEBA>> ተብሎ የትምህርት ማስረጃ በስህተት ተሠርቶ ይሰጠዋል፡፡ የውጭ ዕድል አግኝቶ መሄዱ ግድ ከሆነ ይህ ሰው ፓስፖርቱ <<ABEBA>> በሚል ስም ነው የሚሠራለት፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ሰው አንድ ቀን በተሳሳተው ስህተት መታወቂያው፣ የመንጃ ፈቃዱ፣ በቀጣይ የሚማራቸው የትምህርት ማስረጃዎች በሙሉ የሚሠሩለት በ <<ABEBA>> ይሆናል፡፡ የአንድ ቀን ስህተት ዕድሜ ልኩን እንዲሳሳት ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን ስህተቱን ስለሚለምደው እንደ ትክክል ይቆጥረዋልና <<ABEBA>> በሚለው ስም መጠራትን ይለምደዋል፡፡
ይህ ስህተት በሀገራችን በልዩ ልዩ ተቋማት ላይም እንመለከተዋለን፡፡ አንድ ሰው በሆነ ወቅት በሆነ አጋጣሚ መመሪያ ጥሶ ህግ አፍርሶ የሆነ ነገርን በስህተት መሥራት ይለምዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ያ ስህተት አሠራር እንደ ህግ ይሆንና ሁሉም ይሠራበታል፡፡ እርሱ ወርዶ በተራው ሌላ ሰው ቢተካ እንኳ አንዴ ስህተቱ ተሠርቷልና በዚያ ስህተት አሠራር ይቀጥላል፡፡ ይህ የስህተት አሠራር ትክክለኛ አሰራር ሆኖ በህብረተሰቡ ዘንድም እንደ መመሪያ ጸድቋልና ማንም ቅሬታ አያቀርብም፡፡ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ማለት ይህ ነው፡፡ አንድ ጊዜ በስህተት ዝናብ በስብሻለሁና ዳግም ለሚዘንብብኝ የስህተት ዝናብ ዣንጥላ አያስፈልገኝም ምክንያቱም አንዴ በስህተት በስብሻለሁና የሚል አመለካከት ያነገበ ነው፡፡
የህዝብን የጥያቄ ጩኸት በድብደባ ዝም ማስባል ከለመድህ እድሜ ልክህን ያንን ትፈጽመዋለህ፡፡ ምክንያቱም አንተ መደብደብን (ይላላል) ህዝቡም መደብደብን (ይጠብቃል) ልማድ አድርገዋልና እንደ ትክክለኛ አሠራር ይቆጠራል፡፡ የተለያዩ የስህተት ሥራዎቻችን ልማድ ወደ መሆን ይቀየሩና ለስህተታችን ይቅርታ በማለት ፋንታ ስህተታችን ትክክል እንደሆነ ልናስረዳ እንሞክራለን፡፡ መብራት ሲጠፋ፣ ኔት ወርክ ሲቋረጥ፣ ውኃ ስትቀር፣ ስኳር እና ዘይት ሲጠፋ ወዘተ ይቅርታ ብሎ የሚያውቅ ማን አለ? ማንም የለም ምክንያቱም ይህን ማድረጋቸው በራሱ ስህተት እንደሆነ አላወቁማ፡፡ ይቅርታ ለመጠየቅ እኮ በመጀመሪያ ስህተትን ማመን ያስፈልጋል ስህተቱን ያላመነ ሰው ይቅርታን ከወዴት ያውቀዋል፡፡
የወጣቱንም ሱስ እንዲሁ ተመልከቱት አንድ ቀን በሆነ አጋጣሚ በሆነ ሰው ግፊት የጀመራት ሲጋራ ዛሬ ድረስ ጓደኛው አድርጎ ይዟታል፡፡ ጫትና መጠጡ ዝሙትና መዳራቱም እንዲሁ ነው፡፡ በሆነ አጋጣሚ የሆነ ስህተት ስለሠራና ከእነዚህ ሱሶች ጋር ስለተጣበቀ ስህተት ያደረገ አይመስለውም፡፡ ፈጣሪውን የበደለ ራሱንም ያዋረደ አይመስለውም፡፡ ምክንያቱም አንድ ጊዜ ስህተቱን ትክክል ነው ብሎ ራሱን አሳምኖታልና፡፡
አንድ ቀን የተሰራ ስህተት እድሜ ልክን እንደተሳሳትን የሚያደርግ ልማድ ነው፡፡ ስለዚህ ስህተታችን ማየት መቼም ቢሆን የምንሠራውን ነገር ትክክል ስለመሆኑ መመርመር ያስፈልገናል፡፡

No comments:

Post a Comment