Friday, August 26, 2016

“ከጎልያድ ሰይፍ የሚልቅ የዳዊት ጠጠር”


© መልካሙ በየነ

ነሐሴ 20/ 2008 ዓ.ም

ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በጉልበቱ እና በኃይሉ የሚመካ ፍልስጥኤማዊ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም ያልተገዘረ ሲሆን በእግዚአብሔር ህዝብ በእስራኤላውያን ላይ እጁን ጫነባቸው፡፡ እነርሱንም ለመግደል ይዝት እና ያስፈራራ ነበር፡፡ ንጉሡ ሣዖልም እነዚህን ፍልስጥኤማውያንን ድል ለሚያደርግለት ሽልማትን አዘጋጀ፡፡ ነገር ግን ይህን ግዙፉን በጉልበቱ እና በኃይሉ እንዲሁም በታጠቀው መሣሪያ የሚመካውን ጎልያድ ማንም እስራኤላዊ ሊያሸንፈው አልቻለም ነበር፡፡ ጎልያድ ላይ ዛቻ አለ፣ ጎልያድ ላይ ሰይፍ አለ፣  ጎልያድ ላይ ኃይል አለ፣ ጎልያድ ላይ ጉልበት አለ፣ ጎልያድ ላይ ማስፈራራት አለ፣ ጎልያድ ላይ የጦር መሣሪያ አለ፡፡ ለዚህም ነው ፍልስጥኤማውያን በዚህ ሰው ተመክተው በእስራኤላውያን ላይ የተገዳደሩ፡፡
አምላክ ይሁን ካላለ በቀር አንዲት ነገር አትደረግም፡፡ ጎልያድ የእግዚአብሔር ሰው አይደለም፡፡ የህዝበ እስራኤላውያንን ደም ለማፍሰስ የሚፈጥን እጅ የያዘ ግፈኛ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የህዝቡን ደም ከእጁ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ የጎልያድ ዛቻ፣ የጦር መሣሪያ፣ ማስፈራራት፣ ኃይልና ጉልበት ሁሉ በእስራኤላውያን ዘንድ ቦታ የለውም፡፡ ምክንያቱም እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸውና፡፡ እነርሱ ዘንድ እምነት አለ፣ እነርሱ ዘንድ እግዚአብሔር አለ፣ እነርሱ ዘንድ ድል መንሳት አለ፣ እነርሱ ዘንድ ማሸነፍ አለ፣ እነርሱ ዘንድ ሞገስ አለ፡፡ ለጊዜው ጎልያዳውያኑ ደም ሊያፈሱ ይችላሉ፣ ለጊዜው ፍልስጥኤማውያኑ ሊገድሉ ይችላሉ፣ ለጊዜው ጎልያዳውያኑ ያሸነፉ ይመስላቸዋል፣ ለጊዜው ፍልስጤማውያኑ ኃይላቸው ከእነርሱ ጋር ይቆይ ይመስላቸዋል፣ግን አምላክ ከማን ጋር እንዳለ አያውቁም፡፡
ጎልያዳውያኑ! ዛሬ ግደሉን እንሞታለን፣ ዛሬ ደማችንን አፍስሱት፣ ዛሬ አስፈራሩን ዝም እንላለን፣ ዛሬ ተዋጉን ድል እንደረጋለን፣ ዛሬ ሥጋችንን አቃጥሉት እንቃጠላለን፣ ዛሬ በሰይፍ ቁረጡን አንገታችንን እናመቻቻለን፣ ዛሬ በጥይት ደብድቡን ደረታችንን እንሰጣለን፣ ዛሬ እሰሩን እጅ እንሰጣለን፣ ዛሬ አሸማቁን እንሸማቀቃለን፣ ዛሬ በኃይላችሁ ተመኩ፣ ዛሬ በጉልበታችሁ ተመኩ፣ ዛሬ በመሣሪያችሁ ተመኩ፣ ዛሬ በሚሆነው ሁሉ ነገር ስልጣን ይኑራችሁ፡፡ ግን አይቀጥልም፡፡ ምክንያቱም ጎልያዳዊነት የሚዝተው፣ ጎልያዳዊነት የሚያሸንፈው፣ ጎልያዳዊነት የሚገዳደረው የዳዊት ጠጠር እስኪለቀም ድረስ ብቻ ነው፡፡ ዳዊት ጠጠሩን ይሰበስባል፡፡ ከሁሉ የሚያንሰው ዳዊት ከሁሉ የሚበልጠውን ጎልያድ አሸንፈዋለሁ ብሎ ሊገጥመው ነው፡፡ ጎልያድ መገዳደር፣ መዛት፣ በጉልበቱ መመካት ልማዱ ነውና  ወንጭፉን ይዞ ጠጠሩን ለቅሞ የተጠጋውን ዳዊትን ውሻ የምትገድል መሰለህን ወንጭፍ ይዘህ የመጣህ አለው፡፡ ዳዊት ከጠጠሩ ጋር አብሮት ያለውን አምላክ ያውቃል፡፡ ለጎልያድ መለሰለት ውሻስ ጌታውን ያውቃል አንተ ግን ጌታህን የማታውቅ አህዛብ ነህ አለው፡፡ ዳዊት ዘንድ ፍርሐት የለም፡፡ ከጎልያዳዊ ሰይፍ ይልቅ ዳዊታዊ ጠጠር እንዲልቅ በውስጡ ያውቃልና፡፡
ዳዊት ጠጠሩን ከወንጭፉ ላይ አኖረ፡፡ ጎልያድ በዳዊት ድርጊት ሳቀ፣ ተደነቀ፣ ከእጀ የሚያስጥልህንም አየዋለሁ ብሎ ዛተ በራሱም ተመካ፡፡ ጎልያድ እስከዛሬ ድረስ ደም ያፈሰሰ፣ ደሀ የበደለ፣ ፍርድ ያጓደለ፣ በባርነት አገዛዝ ቀንበር ስር ህዝቡን ያስጨነቀ ዳዊት ስላልተነሣ ብቻ ነው፡፡ ዳዊት ሲነሣ ግን ጎልያድ ጎልያድነቱ ያከትምለታል፡፡ ዳዊት ጠጠሩን በወንጭፉ ላይ አስቀመጠና ወደ ጎልያድ ወረወረው፡፡ ጎልያድን ለተመለከተው ሰው እንኳን በጠጠር በጦርም የሚሸነፍ ሰው አይደለም፡፡ ጎልያድ በዚያ ዘመን በነበረ ማንኛውም መሣሪያ የሚሞት ሰው አይመስልም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ትልቅነቱን እንድንረሳ በትንሽ ጠጠር ወደቀ፡፡ ዳዊት ጎልያድን በጠጠር ግንባሩ ላይ መትቶ ጣለው፡፡ ፍልስጥኤማውያን ወደቁ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጭነው ዝም አሉ፡፡ እስራኤላውያንም የድል ዝማሬን ዘመሩ፡፡ ዳዊት በጠጠር ከጣለው ጎልያድ ላይ ሰይፉን መዘዘና ቸብቸቦውን ቆረጠው፡፡ ከእስራኤላውያን ዘንድም ስድብን አራቀ፡፡ ዳዊታዊ ጠጠር እንዲህ ያለ ኃይል አለው፡፡
ዛሬ በሐገራችን ጎልያዳዊ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሰዎች በዝተዋል፡፡ በመሣሪያቸው ተመክተው ያስፈራራሉ፣ ያስራሉ፣ ያንገላታሉ፣ ይገድላሉ፡፡ ምድርን በህዝቦቿ ደም አረከሷት፡፡ የህዝቡን ጩኸት በመሣሪያ በዛቻና በማስፈራራት ለማፈን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ላይም ይህን ማስፈራሪያ አብዝተው ያስተጋባሉ፡፡ ግን ዕለት ዕለት ቁጣው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዳዊታዊ ቁጣ መጥፎ ነው፣ ዳዊታዊ አስተሳሰብ ከባድ ነው፣ ዳዊታዊ ጠጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ስናርደው ዝም ያለን ዳዊታዊ ጠጠርን እየፈለገ ስለነበረ ነው፡፡
እባካችሁ እርስ በርሳችን እንሰማማ፡፡ እኛው ገዳዮች እኛው ተገዳዮች፣ እኛው አስጨናቂዎች እኛው ተጨናቂዎች፣ እኛው አሳዳጆች እኛው ተሳዳጆች፣ እኛው አቃጣዮች እኛው ተቃጣዮች ሆነን እስከመቼ እንቀጥላለን፡፡ ጎልያዊ ዛቻ፣ ጎልያዳዊ ማስፈራሪያ የዳዊትን ቁጣ ያስነሣል፡፡ ከሁሉ ታናሽ የሆነውን ብላቴና ያስቆጣል፡፡ ዳዊት እኮ ከእርሱ የሚበልጥ ስንት ሚሊዮን ህዝብ እያለ ነው ገና በ12 ዓመቱ ጎልያዳዊ ዛቻ የቀሰቀሰው፡፡ ስለዚህ ሌሎችን ብላቴኖችን የሚቀሰቅስ ጎልያዳዊ ማስፈራሪያችንን እና ትምክህታችንን እናስወግድና እንነጋገር፡፡ ትናንት የገነባናቸውን ዛሬ ካፈረስናቸው፣ ትናንት አደግን ተመነደግን ያልንባቸውን ዛሬ ከናድናቸው ብልጽግናችን ከቶ ወዴት አለ፡፡ እየሞተ ያለው የእኛው ወገን ነው እየገደለ ያለም የእኛው ወገን ነው፡፡ አልሸባብ አልመጣብን፣ አይሲስ አልደረሰብን፣ ቦኮ ሐራም አልተቃወመን ታዲያ ማንን ማን ይገድላል? የእግዚአብሔርን ህንጻ እያፈረስን እንደሆነ አይገባንም እንዴ? እኛ በምናፈርሰው የእግዚአብሔር ህንጻ እግዚአብሔር ተቆጥቶ ራሱ በራሱ ሥልጣን እኛን እንዲያፈርሰን እወቁ፡፡ አትጠራጠሩ ዳዊትን አስነስቶ ቸብቸቧችንን ያስቆርጠናል፡፡ እኛ ለገነባነው እና እኛ ለሠራነው ህንጻ መፍረስ ተጨንቀን አይደል እንዴ መሠረተ ልማቶች ፈረሱ በሚል ሰበብ ሰሪዎቹን እየገደልናቸው ያለን፡፡ ታዲያ እግዚአብሔርስ ገንባን ሳንለው የገነባንን የራሱ ንብረቶች የሆንነውን ህንጻዎች ስታፈርሱን ዝም ይል ይመስላችኋል፡፡ በፍጹም ዝም አይልም፡፡ ቃየን ይቅበዘበዛል ያገኘው ሁሉ ይገድለዋል፡፡ ጎልያድ ይዝታል ዳዊታዊ ጠጠር ግን ኃይልን ታደርጋለች፡፡
“ንኡስ አነ እምአኃውየ፣ እኔ ከወንድሞቼ ታናሽ ነኝ” ያለው ዳዊት “ወአሰሰልኩ ጽእለተ እምደቂቀ እስራኤል፤ ከእስራኤላውያን ልጆች ዘንድ ስድብን አጠፋሁ” በማለት የደስታ ዝማሬን ዘመረ፡፡ ዳዊት ሲዘምር ጎልያድ ወዴት ነበር? በጠጠር ወድቆ ሞቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ከጎልያድ ሰይፍ የሚልቅ የዳዊት ጠጠር በህዝቡ ዘንድ እንዳለ አውቀን ህዝባችንን ለሚበልጥ ቁጣ ባናነሣሣው የሚል ምክር ለሚሰማኝ ሁሉ እመክራለሁ፡፡ አልሰማም ለሚል ግን ዳዊታዊ ጠጠር ተነሥቶ ጎልያዳዊ አስተሳሰብ ወድቆ “ወአሰሰልኩ ጽእለተ እምደቂቀ ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያውያን ልጆች ዘንድ ስድብን አጠፋሁ” የሚለውን የድል ዝማሬ ሊዘምሩበት ጊዜው ቅርብ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደ ኋላ ዞራችሁ ያለፈውን መንግሥት ታሪክ መርምሩ፡፡ “ምክር ሰናዪት ለኩሉ ዘይገብራ፣ ለሚያደርጋት ለሚፈጽማት ሁሉ ምክር መልካም ናት”
አበቃሁ

Tuesday, August 23, 2016

“በአግባቡ ያልተጠገነ ስብራት”

ነሐሴ 17/ 2008 ዓ.ም

ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎች ለስብራት ይዳረጋሉ፡፡ በብዛት የሚስተዋለው ስብራት ግን አካላዊ ስብራት ነው፡፡ ይህ አካላዊ ስብራት በእግር፣ በእጅ፣ በአጥንት ላይ በብዛት ይስተዋላል፡፡ በብዛት የሚከሰተውም ከመውደቅ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በተለይ በክረምት ወራት ከላይ ዝናብ ሲዘንብ ምድር ውኃ መቋጠር ትጀምራለች፡፡ በዚህ ጊዜ ሙሉ በጋውን ሲዘልባት የነበረውን ሁሉ ዳዴ እያሰኘች ትነዳዋለች፡፡ አንዳንዱንም እግርህን አልቀበልም ብላ ሰማይ አድርሳ ታፈርጠዋለች፡፡ ያኔ ነው ነገር ተበላሽቶ ስብራት የሚባል ጣጣ የሚፈጠረው፡፡ ከዚያም እንደተሰበሩ አውቆ መጠገን የሚባለውን ፍልስፍና መዘመር ያስፈልጋል፡፡ ስለተሰበርን ብቻ መሰበርን እንደ ውርደት ቆጥረን ስብራታችንን አፍነን መያዝ የለብንም፡፡ ሆኖም ግን መጠገን እንደሚያስፈልገን ራሳችንን ካሳመንን በኋላ ጠጋኝ መፈለግ ግድ ይለናል፡፡ መጠገን እና መጠገን (ጠ ይጠብቃል) ጠጋኝ እና ጠጋኝ ሁሉም አንድ አይደሉም፡፡ አንዳንዱ ጊዜያዊ ጥገና ይሰጣል፣ አንዳንዱም ጥገና የሚመስል ነገር ያደርጋል፣ አንዳንዱ ደግሞ ሙሉ ጥገኛ ይሰጣል፣ አንዳንዱ ደግሞ ከጥገናም በላይ ሌሎችን አስፈላጊ ምክሮችን እና ተሞክሮዎችን ይለግሳል፡፡
ዛሬ እየጻፍኩት ያለው ወጌሻ ስለሆንኩ አይደለም ወይም ደግሞ እግሬ ወይም እጄ ተሰብሮብኝ አይደለም፡፡ አካላዊ ስብራትን ለመተርጎምም ፈልጌ አይደለም ሞራላዊ ስብራትን፣ አገራዊ ስብራትን፣ ህዝባዊ ስብራትን ለመናገር ፈልጌ ነው እንጅ፡፡ በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች ብዙ የማንነት ጥያቄዎች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ግን በወቅቱ እንደ ጥያቄ ተመልክቶ ሊያስተናግዳቸው የቻለ ሰው አልነበረም አሁንም የለም፡፡ በመሆኑም በጥያቄ ላይ ሌላ ጥያቄ ሲደረብ ለነገ እየተባለ ሲገፋ ኖረና ዛሬ ላይ ከባድ ሀገራዊ ስብራትን ፈጠረ፡፡ የህዝቡ አቤቱታ እየጨመረ መጣ፡፡ የአንዱ ስብራት ለሌላውም ስብራት እየሆነ መጣ፡፡ በእርግጥ እስካሁን ድረስም ስብራታችሁ ስብራታችን አይደለም ያሉ አሉ፡፡ ሆኖም ግን ስብራታችን አገራዊ ስብራት ነው፡፡ ይህ ስብራት ደግሞ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ለሁላችን ስብራት የሚሆንበት አንድ ቀን ይመጣል፡፡ ህዝቡ ለምን መቃወም አስፈለገው? የመቃወም አባዜ ተጠናውቶት ይሆን? አይደለም እናውቀዋለን ኢትዮጵያውያን ከመጠን በላይ ያለፈ ትእግስት ያላቸው ህዝቦች ናቸው ነንም፡፡ ከትእግስት መስመር አልፎበት የማንነት ስብራት ሲደርስበትና ስብራት ሲገጥመው ግን ወጌሻ ሆነን መጠገን ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ግብር ከፋዩ ህዝብ ነው፣ መሠረተ ልማቱ የህዝብ ነው፣ በመንግሥት የአመራር ቦታዎች ላይ ያሉትም የህዝብ ናቸው ከህዝብ ናቸው፡፡ ሁሉም አንድ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆን አይችልም እንጅ እኮ እኛም ጠቅላይ ሚኒስቴር ለመሆን የሚጎድለን ነገር የለም ነበር፡፡ ግን ስልጣኑን ለሌላ አሳልፈን ሰጥተነዋል ምክንያቱም ሊመራን ወይም ሊያስተዳድረን ይችላል ያልነው አንድ ሰው ብቻ ስለሆነ፡፡ ዛሬ የሚገድለው እና የሚገደለው ህዝብ እንደ አንድ አገር ዜጋ እኩል ድርሻ ያላቸው ናቸው ለኢትዮጵያ፡፡ የሚገድለው ለአገሬ አስብላታለሁ ከሚለው በላይ እየሞተ ያለው ዜጋ ያስብላታል፡፡ ሆኖም ግን እንደ ባቢሎናውያን ለመሰማማት እና ለመደማመጥ አልቻልንምና የህዝቡ ጥያቄ በጥይት ሲመለስ ተመለከትነው፡፡ ይህ መልስ ምናልባትም ለሕዝቡ የማንነት ስብራት ጊዜያዊ መፍትሔ ሰጥቶ ህዝቡን እንዳይቃወም ልናደርግበት እንችል ይሆናል ዘላቂ መፍትሔ ግን አይሆንም፡፡ በረሃብ ተጎድቶ ዛሬ እንዳይጮኸብን ያለውን ህጻን ተቆጥተንም ሆነ አስፈራርተን እንዳይጮኽ ልናደርገው እንችላለን፡፡ ይህ ማለት ግን ልጁ መጮኹን ያቆመው ረሀቡ ስለጠፋለት አይደለም ስለፈራ እንጅ፡፡ ምናልባትም በዚህ ከቀጠልንበት አንድ ቀን ከሞት ሰይፍ ይሻላል እንዲሉ አበው ሰይፍ ሊመዝብን ይችላል፡፡ ህጻን መሆኑን አንመልከተው እርሱ ዘንድም ብሶት ታፍኗልና፡፡
“መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው” የሚባለው በእውነት የህዝብን ደም ሲያፈስ ነው ወይስ ደግሞ ጥያቄያችሁ ተገቢ ነው ወደ ፊት እናስተካክላለን እናንተ የምትሉትን ነገር እኮ እኛም ቀድመን ተረድተነዋል በማለት በሰላም ህዝቡን የሚያነጋግር ሲሆን ነው፡፡ የኃይል ጥቃት ጊዜያዊ ጥገና ነው፡፡ ምክንያቱም የህዝቡ ስብራት በአግባቡ እስኪጠገን ድረስ ስብራቱ በየጊዜው ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ መንግሥት ጥሩ ወጌሻ መሆን ካልቻለ ከባድ ችግር ይፈጠራል፡፡ በአገራችን ላይስ ከህዝቡ በሚበልጡ ፖሊሶች እያስፈራራን እንደ ህጻን ልጅ ዝም እናስብላቸው ትናንትና ብራዚል ላይ የህዝቡን ስብራት በዓለም አደባባይ ሲያጋልጥ ምን አደረግን? ምንም ልናደርግ አንችልም የእኛን ሚዲያ ቀጥታ ስርጭት ልናቋርጠው እንችላለን የአትሌቱ ተቃውሞ ግን አልተቋረጠም ነበር፡፡ ሌሎች ታላለቅ ሚዲያዎች ቀጥታ ሽፋን ሰጥተውት ነበር እኮ፡፡ ታዲያ የህዝባችንን ጩኸት በእንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች የሚገልጹ ዜጎች ካሉ የሀገራችንን ህዝብ ብናስፈራራው ምን ዋጋ አለው? እኛ እኮ ዝም  ካልን ቆየን በጣም ብዙ ጊዜ አለፈን፡፡ ህገ መንግሥቱ የመናገር መብት ስለሰጠ እንናገራለን ነገር ግን የማሰር ስልጣንን ስለሰጠ ደግሞ እንታሰራለን፡፡ እንደዚህ እየሆነ እስከመቼ? እዚህ ያለውን አስፈራርተን ዝም ብናስብለውም ስብራቱን ማከም የሚችልበትን አጋጣሚ ባገኘ ቁጥር ባለም አደባባይ ቅሬታውን ይገልጻል፡፡
ስለዚህ የጋራ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልገናል፡፡ ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም ጥያቄውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ የህዝቡ ደም እንዳይፈስ መንግሥት ያሰማራቸውን ደም አፍሳሾች መሰብሰብ አለበት፡፡ በእውነት መንግሥት ላይ አንዳችም ጥፋት ባይኖርበት ኖሮ መቶ ፐርሰንት መረጠን ያልነው ህዝብ በየወረዳው እና በየቀበሌው ለምን ይቃወመናል? አንዳንዴ እኮ ራስንም ዞር ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዝንጀሮ በሌላው መላጣ የምትስቀው እኮ የራሷን መላጣ ዞራ ስለማታየው ብቻ ነው፡፡ የራሷን መላጣ ብታይ ግን በሌላው መላጣ የምትስቅበት አፍ እና አንደበት አይኖራትም ነበር፡፡ ስለዚህ የስብራቱ ጥገና ፍቱን መሆን አለበት፡፡ ጀምሮ ነካክቶ ስብራቱን አባብሶ ዞር ማለት ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ እስከዛሬ ድረስ እኮ ተመልክታችሁታል፡፡ ምን ላይ ችግር እንዳለ፣ ምን ላይ ህዝቡ ቅር እንደተሰኘ መመርመር አለባችሁ፡፡ ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ሲቀረጹ ከመቀረጻቸው በፊት ህዝቡን ማወያየት ያስፈልጋል፡፡ ፕሮጀክቱ ብዙ ገንዘብ ከፈሰሰበት በኋላ ወደ ህዝቡ መጥቶ ህዝቡ ድንበራችንን ይጋፋል፣ ታሪካችንን ያደበዝዛል፣ ማንነታችንን ያሳጣል ወዘተ ብሎ ቅሬታ ሲያቀርብ ወደ ድብድብ እና ግድያ ከማምራቱ በፊት እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አልታደል ብለን ነው እንጅ ቅሬታ ያቀረበ ሰው በእውነት ይደበደብ ነበር? ይታሠር ይገደል  ነበር? ለወደፊት እቅዳችን እኮ ግብአት ነው፡፡ የሕዝቡ ቅሬታ ለሚያስተውል መሪ በጣም ሲበዛ ጠቃሚ ነው፡፡ መልካም እየሰራን እንደሆነ የሚነግረን ሰው ምንም አይጠቅመንም ምክንያቱም እየሠራነው ያለው ነገር ስለሆነ፡፡ ጉድለታችንን የሚመለከት ዓይን ግን ተገቢ ነው እኛ መስሎን ከሠራነው በተጨማሪ ሌላ መንገድ ያሳየናልና፡፡
እኔ ይህንን ስጽፍ የሚሰማኝ ሰው ላይኖር ይችላል ምክንያቱም በማንም ዘንድ ቦታ ስለሌለኝ፡፡ ግን አንድ ቀን ታሪክ ሆኖ እንደማገኘው አልጠራጠርም፡፡ ይህ ትንቢት አይደለም አሁን እያየነው ያለ ነገር ነው፡፡ ስብራቱን በደንብ አላከሙትም፡፡ ህዝቡ ተሰብሮ እንደወጣ ሌላ ስብራት ተጨምሮበት እየገባ ነው ያለው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች መልካቸውን እየቀያየሩ ተቃውሞዎች እየመጡ ናቸው፡፡ እስካሁን ግን ህዝቡን ሰብስቦ ምንድን በደልናችሁ? ያለ አካል የለም፡፡ በደሉን አጠገቡ ሆነን ካልሰማነው ምን የኅሊና እርካታ ሊሰጠን ይችላል፡፡ እየጠገንነው ያለው ስብራት ነገም መሰበሩ አይቀርም ምክንያቱም በአግባቡ አልጠገንነውምና፡፡ ወይም ከስብራቱ ውጭ ያለውን አካሉን ነውና የጠገንለት፡፡ ስለዚህ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ እኛ ማድረግ የምንችለውን ነገር እናድርግ፡፡ ህዝቡን ከሞት አገሩን ከመቅሰፍት እንዲጠብቅልን ወደ አምላካችን መጮኽ ብቸኛው አማራጫችን ነው ለእኛ ለሚገደልብን እና ወደፊትም ለምንገደል ሰዎች፡፡ በዚህ ጩኸት በየቤተ እምነታችን በርትተን አምላክን እንለምን እርሱ ምሕረት በእጁ አለችው፡፡ እርሱ ነገርን ይቀይራል አትጠራጠሩ ሁሉም ከስብራቱ ይጠገናል!!!!

አበዛሁ ይብቃኝ!

Thursday, August 11, 2016

“ወማየ ብሔራሰ እኩይ ውእቱ”

© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 05/2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ኤልሳዕ መምህሩ ኤልያስን ሸኝቶ ሲመለስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ኢያሪኮ ደረሰ፡፡ ከዚያም ከከተማው ገባና “ሠናይት ንብረታ ለዛቲ ሐገር” አለ፡፡ ኤልሳዕ እየተመለከታት ያለችው ሀገር መልካም ናት፡፡ ከውጭ ሲመለከቷት መልካም ናት፣ ያማረች ናት፣ ያጌጠች ናት ለዚህም ነው ኤልሳዕ መልካምነቷን የሚመሠክርላት፡፡ ሆኖም ግን የሀገሪቱን መልካም መሆን አለመሆን የሚያውቁ በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች የሚመለከቱት ህንጻውን ነው፣ ሌሎች የሚመለከቱት መንገዱን ነው፣ ሌሎች የሚመለከቱት የቤተ መንግሥቱን ልምላሜ ነው፣ ሌሎች የሚመለከቱት 24 ሰዓት ያለአገልግሎት የሚፈሰውን ፋውንቴን ነው እውነቱ ያለው ግን በኗሪዎች እጅ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኤልሳዕ ሐገሪቱ መልካም ናት እያለ ስለሐገሪቱ መልካምነት ሲናገር ከታይታ መልካምነቷ ያልተጠቀመው ህዝብ  “ወማየ ብሔራሰ እኩይ ውእቱ፣ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕ ሆይ! ውኃው ግን ወላድ ቢጠጣው ያመክናል፣ መካን ብትጠጣውም አንጀቷን ቆርጦ ሆዷን በጥብጦ ይገድላታል” ማለቱ፡፡
የአገራችን መልካምነት፣ ታይታነት፣ ዕድገትና ልማት፣ ብልጽግና ሰላም ወዘተ እንዲህ ነው፡፡ አሜሪካ ብትመሰክር፣ እስራኤል ብትመርቅ፣ ቻይና ብታሞግስ፣ ኮሪያ ብትሸልም፣ ጃፓን ብታደንቅ አይገርምም ምክንያቱም እነርሱ ያዩት ፎቁን እንጅ ከፎቁ ሥር የወደቁትን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦውን እንጅ ውኃውን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት አስፋልቱን እንጅ በአስፋልቱ ላይ ተኝቶ የሚያድረውን መጠለያ አልባ ወገኖቻችንን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የቤተ መንግሥቱን የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት እንጅ የእኛን በኩራዝና በሻማ ማደራችንን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የቴሌቪዥኗን ኢትዮጵያ ነው እንጅ እኛ የምንኖርባትን እውነተኛዋን ኢትዮጵያ አይደለምና፡፡ ስለዚህም አንፈርድባቸውም፡፡ ደግሞም እኮ እኛ ተደራጅተን ለመኖሪያ እንኳ 200 ካሬ ሜትር ያላገኘነውን የአገራችንን መሬት በገፍ የሚያፍሱ ስለሆነ ቢያወድሱን አይገርምም፡፡ አለቃ ገብረ ሃናን ልጃቸው “አባቴ ሰው ሁሉ ድንቼ ድንቼ ይለኛል” አለቻቸው አሉ፡፡ እርሳቸውም ሲመልሱ “ልጄ እንዳይልጡሽ ተጠንቀቂ” አሏት ይባላል፡፡ ስለዚህ ነው እንግዲህ መጠንቀቅ የሚያሻን፡፡ ድንቼ ድንቼ የሚለንን የውጭ ሙገሳ አንሻም በሉልን ምክንያቱም ሊልጡን የተዘጋጁ ናቸውና፡፡
ኤልሳዕ የዚችን ሐገር እውነተኛ ማንነት ተረዳ፡፡ የሃይማኖት አባቶቻችን ሆይ ኤልሳዕን እንስማው እባካችሁ፡፡ ዝም ብለን ይህች አገር መልካም ናት ባንል መልካም ነው፡፡ ኤልሳዕ ውጯን ስለተመለከተ ነው እናንተ ግን ውስጧን ትመለከታላችሁና የመልካምነቷ ተካፋዮች ስለመሆናችሁ ማረጋገጥ አለባችሁ፡፡ አሁን ኤልሳዕ መልካም አገር እንደሆነች ተረድቷል ነገር ግን መልካምነቷን የሚለውጥ አንድ ችግር እንዳለ ከነዋሪዎች ሰምቷል፡፡ ታዲያ ሐገሪቱ መልካም ናትና እንዲህ ያለውን የማይገባ ስም አትለጥፉባት ነው እንዴ ያለው? ወይስ አንዴ መልካም ናት ብያለሁ ብያለሁ ዝም ብላችሁ መልካምነቷን ተቀበሉ ነው ያለው? አንዳንዴ እኮ እየኖርንበት ስላለው ሁኔታ ከጠፋን ራሱ የሚኖሩትን ማየት እና መጠየቅም ያስፈልገናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እየኖርን ራሱ እየኖርን ስላለበት ሁኔታ የምናውቀው ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ የኤልሳዕን ድንቅ ተግባር ለህዝባችን ማሳየት ይጠበቅባችኋል ማለት ነው፡፡
ኤልሳዕም አገሪቱስ መልካም ነበረች ዳሩ ግን ውኃው መርዝ ነው፡፡ ወላድን ያመክናል፤ መካንንም ይገድላል እንጅ ያሉትን ወገኖች ሰምቶ መፍትሔ ፈለገላቸው፡፡ ምክንያቱም ኤልሳዕ  ንብረቱን ትቶ ለድኃ አብልቶ መምህሩ ኤልያስን የተከተለው ራሱን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ነውና የህዝቡን ሞት አይፈልግም፡፡ ስለዚህህዝቡ በውኃው መርዝነት አንጀቱ ሲቆረጥ ሆዱ ሲበጠበጥ መመልከት አላስቻለውምና “አዲስ ሸክላ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” አለ፡፡ ከአንድ አባት የሚጠበቀው መልካም ነገር ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ የዛሬ አባቶቻችንም የሰላም ጨው፣ የፍቅር ጨው፣ የአንድነት ጨው፣ የመረዳዳት ጨው፣ የመተባበር ጨው፣ የመተሳሰብ ጨው፣ የመቻቻል ጨው፣ የመዋደድ ጨው በአዲስ ማሰሮ ጨምራችሁ እመጡልኝ አንጀታችሁን የሚቆርጠውን ሆዳችሁን የሚበጠብጠውን መርዝ ላስወግድላችሁ ማለት ያስፈልጋችኋል፡፡ ከዚህ በፊት ግን እንደ ኤልሳዕ ጥፋቱ ማን ላይ እንደሆነ በግልጽ መለየት ተገቢ ነው፡፡ ውኃው ላይ ነው ወይስ ውኃውን ከሚጠጡት ሰዎች ላይ ነው ችግሩ ያለው? የሚለውን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ላይ ነው ወይስ ሕዝቡ ላይ ነው ጥፋቱ? የሚለውን እንደ አባትነታቸው የማወቅና የመረዳት ግዴታ አለባቸው ምክንያቱም ያለሕዝብ የሕዝብ አባት መሆን አይቻልምና፡፡ አባቶች ከመንግሥት ጋር ወግነው ህዝቡ ሲታሰር፣ ሲደበደብ፣ ሲገደል እየተመለከቱ ዝም ማለት ግን የኢሳይያስን ለምጽ የሚያከናንብ ፍርሐትና አድርባይነት ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ደም ሲፈስ እየተመለከትን ለጸሎት ለሱባኤ ለምሕላ ያወጅነው የአባትነት ዐዋጅ የት አለ? የሙስሊሙም፣ የክርስቲያኑም የሃይማኖት አባቶች ለዚህ ለፈሰሰው ደም ምንም ዓይነት ከሃይማኖቱ የሚጠበቅ ተግባር አላሳዩም፡፡ ይልቁንም መንግሥት የተናገራቸውን ቃላት ሳንቀይር “እንደ በቀቀን” ብናስተጋባ ግን ታሪክ አንድ ቀን ይወቅሰናል፡፡ ዕድሜያችን አጭር ናት፣ ዛሬ ናት አልያም ነገ ብቻ ናት ያለችን ጊዜ በዚች ጊዜ ውስጥ ግን የሰላም ማሰሮንአምጡልኝ ማለት ይጠበቅብናል፡፡
ኤልሳዕ በአዲስ ሸክላ ጨው ጨምረው እንዲያመጡለት ጠየቀ ህዝቡም አመጡለት፡፡ ኤልሳዕ እውነተኛ አባት መሆኑን ተረድተዋል፣ የኤልያስ ደቀመዝሙር እንደሆነ አውቀዋል፣ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆነ ተረድተዋል ስለዚህም ታዘዙት በአዲስ ሸክላ ጨው ጨምረው አመጡለት፡፡ ከዚያም ምንጩን አሳዩኝ አላቸው ምንጩን አሳዩት፡፡በቃ ይህ ነው ዋናው መፍትሔ ምንጩን መለየት ያሻል፡፡ ዝም ብሎ ከሚፈሰው ውኃ ጋር መፍሰስ አይደለም ምንጩ ላይ መሄድ ነው እንጅ፡፡ የደም መፍሰሱ ምንጭ ምነድን ነው? የመገዳደላችን ምንጩ ምንድን ነው? ንብረታችን የመውደሙ ምንጭ ምነድን ነው? የህዝባችን መቆጣት ምንጩ የት ነው? ማለት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ነው ኤልሳዕ ምንጩን አሳዩኝ ማለቱ፡፡ ህዝቡም ምንጩን አሳዩት፡፡  እርሱም እንደአባትነቱ “እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል ፈወስክዎ ለዝንቱ ማይ ከመ አልቦ ዘይመክን እምኔሁ ወዘይመውት” ብሎ ጨው ያለበትን አዲሱን ሸክላ ከምንጩ ላይ አድርጎ ጸልዮበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ውኃው ተፈውሶ ወላድ ብትጠጣው የማያመክን መካን ብትጠጣውም የማይገድል ሆኗል፡፡ ከሞት የከፋ ነገር የለም ኤልሳዕ ከዚህ ሞት የታደጋቸው የአባትነቱን አደራ የተወጣው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬም አባቶቻችን ሆይ የኤልሳዕን ሥራ ትሠሩ ዘንድ እንማልዳችኋለን፡፡ አገራችን መልካም ናት፣ አገራችን የሃብታሞች ሃብታም ናት፣ አገራችን ትልቅ አገር ናት ነገር ግን ወላድን የሚያመክን መካንን የሚገድል ውኃ አለባት፡፡ ይህንን ውኃ መፈወስ የአባቶችቻን ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡

ሁሉም የሚጠቀምበትን ሰላም ፍቅር አንድነት ለህዝቦቻችን ያድልልን ዘንድ የፈጣሪያችን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡

Wednesday, August 10, 2016

“ወሥሉጥ ስምኪ በኀበ እግዚአብሔር”


© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 04/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
የአባ ሕርያቆስ ረድኤት በረከት ይደርብንና እመቤታችንን ባመሰገነበት ቅዳሴው እንዲህ አለ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም እንዲህ ብለው ተረጎሙልን፡፡ የቃሉ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን አሜን፡፡
ወሥሉጥ ስምኪ በኀበ እግዚአብሔር፡፡ ስምሽም በእግዚአብሔር ዘንድ በማማለድ ሥሉጥ ነው፡፡ ይህም በአንድ ሰው ታውቋል፡፡ ታሪክ እጅግ ገንዘቡ የበዛ የተረፈው አንድ ባለጸጋ ነበረ ላዝማሪ ለዘዋሪ እየሰጠ አለቀበት፡፡ አንድም የዚህ ዓለም ገንዘብ ሲሰበሰብ እንጅ ሲጠፋ አይታወቅምና፡፡ ኅልፈቱ ቅድመ አስተርእዮቱ እንዲል፡፡ ከዚህ በኋላ ከብሬ በኖርሁበት አገር ተዋርጄ ሰጥቼ በኖርሁበት አገር ለምኜ  አልኖርም ብሎ አገር ጥሎ ቁርበት ጠቅሎ ሲሄድ ሰይጣን የጨዋ ልጅ መስሎ ከጎዳና ቆይቶ ወዴት ትሄዳለህ አለው ከብሬ በኖርሁበት አገር ተዋርጄ ሰጥቼ በኖርሁበት አገር ለምኜ  አልኖርም ብየ አገር ጥየ ቁርበት ጠቅልየ መሄዴ ነው አለው፡፡ ያዘነ መስሎ ደንጊያውን በምትሐት ወርቅ አስመስሎ ይህን ብሰጥህ አትመለስምን አለው፡፡ ይህንንማ ካገኘሁ ስንኳን ለእኔ ለልጅ ልጄ አይበቃም አለው ከዚህ በኋላ ሰጠው አንተም ፈቃዴን ፈጽምልኝ አለው፡፡ ምን ላድርግልህ አለው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ካድልኝ መላእክት ጻድቃን ሰማዕታትን አያማልዱም በል አለው፡፡ ካደ አያማልዱም አለ፡፡ ከተለያዩ በኋላ ነገር ረስቼ ቆየኝ አለው፡፡ ምእመናን አፍረው አክብረው ስሟን የሚጠሯት ማርያም የምትባል አለች ወላዲተ አምላክ መሆኗን ካድልኝ አለው፡፡ የለማኝ ምኩዜን ምን ይዞ ይሄዷል ጉዞ እንዲሉ እርሷንስ አይሆንም አለው፡፡ እንኪያስ አምጣ ብሎ ወርቅ አስመስሎ የሰጠውን ደንጊያ ተቀብሎ ልብ ራሱን ብሎ ገደለው፡፡ መላእክተ ጽልመት ነፍሱን ከሥጋው ለይተው እጅ አድርገዋታል፡፡ መላእክተ ብርሃንም የጌታን ቁርጽ ፍርድ ሳያዩ አይለዩምና ከእመቤታችን ዘንድ ሂደው ምነው ዝም አልሽ ይህች ነፍስ ከሥጋው የተለየች ባንቺ ምክንያ አይደለምን አታማልጅም አሏት፡፡ እርሷም መሐር ሊተ ወልድየ ዛተ ነፍሰ አለችው፡፡ ከልብኑ ይትመሐር  አባቴን እኔን የባሕርይ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስን የወዳጆቼ የመላእክትን የጻድቃን የሰማዕታት አማላጅነታቸውን የካደ ይማራልን አላት፡፡ ዘጸውዐ ስምኪ ወዘገብረ ተዝካረኪ እምሕር ለኪ ያልኸው ቃልህ ይታበላልን አለችው፡፡ ያውስ ቢሆን የሕጸጸ ምግባር ነው እንጅ የሕጸጸ ሃይማት ነውንነገር ግን ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቼ ሰው መሆኔ ፈቃድሽን ላልፈጽምልሽ ነውን ምሬልሻለሁ አላት፡፡ እንኪያስ ከማርህልኝ ነፍሱን ከሥጋው አዋሕደህ አስነሣልኝ  አለችው፡፡ ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሕዶ አስነሣላት  ለምን ካድህ አለችው፡፡ ባጣ አላት ያጣ ይለምናል እንጅ ይክዳልን  አሁንም ከልጄ አማልጄህ እንዲህ ካለ ቦታ ምግብህን አዞልሃልና ሂድ አለችው፡፡ በዚያች ቦታ አንድ ባለጸጋ ነበር፡፡ አንዲት መልከ መልካም ልጅ ነበረችው፡፡ ባለጸጋ መጥቶ ልጅህን ስጠኝ ያለው እንደሆነ ልጄን በመልክ አትተካከላትም ይለዋል፡፡ መልከ መልካም መጥቶ ስጠኝ ያለው እንደሆነ ልጄን በገንዘብ አትተካከላትም ይለዋል፡፡ እንዲህ አድርጎ ከፍቅሩ ጽናት የተነሣ ያኖራት ነበረ፡፡ በዚያች ቀን እመቤታችን ከቤተ ክርስቲያን እንዲሄድ አድርገዋለች፡፡ የባለጸጋ ጸሎት አጭር ነውና የሰጠኸኝን አትንሣኝ ይህችን አንዲት ቅንጣት ልጄን ባርክልኝ ብሎ ተቀመጠ፡፡ ወዲያው ተደሞ መጣበት፡፡ ያም ሰው ጠፈር ጠፈሩን እያየ ሲዞር ከሱ አጠገብ ደረሶ ቆመ፡፡ ልጅህንም ከብትህንም ለዚህ ሰው ስጠው አለችው፡፡ ቀና ቢል አየው፡፡ ከዚህ በኋላ ወስዶ ልጁንም ከብቱንም ሰጥቶት ወዲያው ዐረፈ፡፡ እርሱም ቆርቦ የእመቤታችንን ስሟን ሲጸራ ዝክሯን ሲዘክር የሚኖር ሁኗል፡፡ ከሞተም በኋላ በዚህ ጊዜ ያልፋልየማይባል መንግሥተ ሰማያትን አውርሰዋለችና እንዲህ አለ፡፡
፩ዱ ነዳይ ዘክሕደ ሃይማኖቶ ኪያኪ ክሕደ ሶበ አበየ በቅድመ ሰይጣን ዘአስሐቶ
አሚነ ዚአኪ ድንግል ለአድኅኖ ነፍሱ በቍዐቶ
እንዘ ይሴባሕ ተአምርኪ ወለጽጌኪ ምሕረቶ
ተንሥአ እምንዋሙ ወአተወ ቤቶ እንዳለ ደራሲ፡፡
(ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጉም ገጽ 30 እና 31)
ይቆየን……

“አትናገር፤ ተናገር ካሉህ ግን እውነቱን ብቻ ተናገር!”

© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 04/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

“አትናገር፤ ተናገር ካሉህ ግን እውነቱን ብቻ ተናገር!” የሚለውን ምርጥ ቃል እኔ በዚህ መልኩ ልጻፈው እንጅ የቀደሙ አባቶቻችን የኖሩበት የህይወት መንገድ ነው፡፡ ይህንን የተናገሩት አባቶቻችን ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ የተናገሩት ቃል የለም የጻፉትም መጽሐፍ የለም ካላችሁኝ ግን ይህ ቃል ምርጥ ስለሆነ እኔ እንደተናገርኩት አድርጋችሁ ያዙት ምክንያቱም የሚያሳፍር የሚያሸማቅቅ እና የሚያዋርድ አይደለምና፡፡
ተናጋሪ አትሁን፣ አፈ ጮሌ አትሁን፣ ጥራዝ ነጠቅ አትሁን፣ ሳታይ አታውራ አትመስክር፣ ሰውን ያስቀይማልና ወሬ አታብዛ፣ መጥፎ ነገር ተናግረህ ሰው ታስቀይማለህና አትናገር በዚህ ብቻም ያይደለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደተናገረው “ወአርመምኩ ለሠናይ፤ ለመልካም ነገር ለበጎ ነገር እንኳ ዝም አልኩ አልተናገርኩም” እንዳለው ለመልካም ነገር እንኳ አትናገር፡፡ የምትናገርበት አፍህ የአንተ ነው፣ የምትናገርበት ምላስህ የአንተ ነው፣ የምትናገርበት ልሳንህ የአንተ ነው፡፡ ማንም አንተ ልሳን ውስጥ ገብቶ እንድትናገር አያደርግህም፤ ማንም የአንተን አንደበት ሊቆጣጠረው አይችልም፤ ማንም የአንተን አፍ ሊጠቀምበት አይችልም ምክንያቱም ገንዘብህ ነውና፡፡ የአንተን ገንዘብ ካልመጸወትከው አልያም ካልተሰረቅህ በቀር የአንተ የራስህ ነው፡፡ ስትመጸውተውና ስትሰረቀው ግን የአንተ መሆኑ ይቀራል ያኔ በገንዘብህ ሌላው ያዝበታል፡፡ አንደበት፣ ልሳን፣ ምላስህ ግን እስካልሞትክ ድረስ የአንተ እና የአንተ ብቻ ናቸው ስትሞት ግን ይለወጣሉ አንተም አንተ አትሆንምና፡፡ በሕይወት ሳለህ እነዚህን ንብረቶች የአንተ ማድረግ ካልቻልክ ግን ሰብአዊነትህ ላይ ጥያቄ ይፈጥራል፡፡
በዚህ በወቅታዊው የወገኖቻችን እልቂት ላይ መንግሥት በርካታ መግለጫዎችን ሲሰጥ የቆየ መሆኑን እናውቃለን፡፡ የየክልሉ ባለሥልጣናትም እንዲሁ በእነርሱ ሥር ባሉ የሚዲያ አካላት መግለጫዎቻቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ከዕለት ዕለት እልቂቱ ሲባባስ ሲጨምር እንጅ ሲቀንስ ሲረግብ አላስተዋልንም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው መግለጫ ማስፈራሪያና ዛቻ የታከለበት ስለሆነ ሌላ ቁጭትን ሲፈጥር ነው የሚስተዋለው፡፡ በተለይ ከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ቃላትን መምረጥ ያሻቸዋል፡፡ እኛ የፈለግነውን ብንናገር ቃላትን ባንመርጥ ማንም ስለማይሰማን ለብጥበብጡ መባባስ መንስኤ አንሆንም እነርሱ ግን ዓለም ቁጭ ብሎ በሚመለከተው ሚዲያ ላይ ነው እየተናገሩ ያሉት፡፡ ስለዚህ በማስተዋልና በረዳት ቢሆን መልካም ነው እላለሁ፡፡ ከቻላችሁ አትናገሩ ምክንያቱም መናገራችሁ ብጥብጥን ፈጠረ፣ እልቂትን አባባሰ፣ ደምን አፋሰሰ፡፡ እንድትናገሩ ከተገደዳችሁ ግን ተናገሩ ያውም እውነቱን ብቻ ምንም ውሸትና ስላቅ ማስፋራራትና መዛት የሌለበትን ትምክህትና ቧልት ያለተቀላቀለበትን ንጹሑን ኢትዮጵያዊነት የሚገልጽ ንግግር ተናገሩ፡፡
የሃይማኖት አባቶችም እንዲሁ አትናገሩ፤ ተናገሩ ካሉዋችሁ ግን እውነቱን ብቻ ተናገሩ፡፡  የሃይማት አባቶች የምታስተዳድሩት ህዝብ መንግሥት ከሚያስተዳድረው ሕዝብ በላይ መሆኑን ተረዱ፡፡ መንግሥት ለዚህች አገር ብቻ ነው የሚጨነቀው፣ መንግሥት ለዚህች ሐገር ሰላም ብቻ ነው የሚያስበው፣ መንግሥት ለዚህች አገር እድገት ብቻ ነው የሚሠራው እናንተ ግን ለዓለም ነው የምትጸልዩት፤ እናንተ ግን ለዓለም እድገት ነው የምትሠሩት፡፡ ስለዚህ ከመንግሥት በላይ ናችሁ ከህዝቡም በላይ ናችሁ ይህን ከተረዳችሁ ደግሞ በህዝቡና በመንግሥቱ መካከል ገብታችሁ የማስተረቅ የመሸምገል ያጠፋውን የማውገዝ ሥልጣን አላችሁ፡፡ የእናንተ አደራ ሰው ሲሞት ፍትሐት አድርሶ መቅበር ብቻ አይደለም እንዳይሞት መጠበቅ ጭምር ነው እንጅ፡፡ መንግሥት የሚነግረንን ነገር ብትነግሩን ግን ምንም አይፈይድልንም ምክንያቱም የሚገድለንን ደግፋችኋልና፡፡ የሃይማኖት አባቶች ወገንተኞች መሆን አይገባችሁም ክልላዊ ዝቅ ብሎም ጎጣዊ የሆነ አስተሳሰብን ከእናንተ አንሻም፡፡ ሰማእተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ አቡነ ጴጥሮስን ከልባችሁ ጽላት ጻፏቸው እስኪ፡፡ ይህች አገር እኮ የታላላቅ ታሪክ ሰሪዎች አገር ናት፡፡ ታዲያ ለውጭ ጠላት አንንበረከክም ብሎ የአንድነት ታሪክን በጀግንነት የሠራ ህዝብን በአገሩ ልጆች በመከፋፈል ሲገደል ደሙ መሬት ሲፈስ እንዴት መስቀላችንን እንደብቀዋለን፡፡
ዋናው መልእክቴ አባቶቼ ሆይ አትናገሩ፤ ተናገሩ ካሉዋችሁ ግን እውነቱን ብቻ ተናገሩ የሚል ነው፡፡ አባታችን ቅዱስ ፓትርያርኩ ትናንትና መግለጫ ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ እኔ ለራሴ መግለጫውን አንድ የመንግሥት አካል ከሚሰጠው መግለጫ የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ አንድ የተቀየረ ቃል ቢኖር “መንግስታችን” የሚለው ቃል “ቤተክርስቲያናችን” በሚል መተካቱ ብቻ ነው፡፡ ይህ የአባታችን ንግግር ምእመናንን ያስቀይማል፣ ህዝቡን ላልተፈለገ ዓላማ ያነሳሳል ስለዚህ ነው ባንናገር መልካም የሚሆነው፡፡ የግድ ከሆነ ግን የአቡነ ጴጥሮስን አንደበት ለደቂቃዎች እንኳ መዋስ ያስፈልጋል፡፡ “ልጆቻችን” በማለት ፈንታ “ዜጎቻችን” ሲባል ቅር ያሰኛል፡፡ በእውነት አባት የለንምን ያስብላል፡፡ ንግግራችን ካላማረ ንግግሬ አያምርም ብሎ ዝም ማለት ይሻላል፡፡ ተናግሮ ከማስቀየም አለመናገር ይሻላል፡፡ መናገር ግድ ከሆነብን ግን ህዝቡን ጥፋተኛ መንግሥትን ትክክለኛ አድርገን ያለምንም መረጃ ወደአንዱ በማዘንበል መናገር ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሁለቱም መካከል ገብተው የቱ ነው ያጠፋ በማለት መመርመር ከንግግራቸው በፊት የሚቀድም ተግባር ነበር፡፡ አባቶቻችን ያቆዩን በጸሎት ማሰብ እንኳ መጀመሪያ ላሉበት ቦታ ነው ይላሉ ምክንያቱም ዐሥራቱን ቀዳማያቱን ትመገባለህና ይላሉ፡፡ ይህ እየሞተ ያለው ህዝብ እኮ ዐሥራት በኩራቱን እየከፈለ ሞገስ የሆነን ህዝብ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ህዝብ ሲሞት ወገኔ አይደለህም ልንለው እንችላለንን?

ለሀገራችን ሰላም እንማልዳለን!!!

Monday, August 8, 2016

"ውዳሴ ዘሠሉስ ውዳሴ በሠሉስ... አክለለ ምክሕነ"

©መልካሙ በየነ
ነሐሴ 3/2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ ኢትዮጵያ
ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ሠሉስ፡፡
ለምስጋና ሁለተኛ ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፡፡ ከዚያ ላይ ሁና ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም ትለዋለች እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ወድሰኒ ትለዋለች በዕለተ ሰኑይ ክርክር አልቋልና ባርክኒ ይላታል፡፡ በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ ይኅድር በላእሌከ ትለዋለች፡፡ ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል፡፡
ውዳሴ ዘሠሉስ ውዳሴ በሠሉስ ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ሠሉስ ይላል ቃለ ጸሐፊ ነው እርሱ ግን አክሊለ ምክሕነ ብሎ  ይጀምራል፡፡
አክሊለ ምክሕነ…. አክሊል የወዲህኛው ምክሕ የወዲያኛው
ወቀዳሚተ መድኃኒትነ…. ቀዳሚት የወዲህኛው መድኃኒት የወዲያኛው
ወመሠረተ ንጽሕነ…. መሠረት የወዲህኛው ንጽሕ የወዲያኛው
ኮነ በማርያም ድንግል… በማርያም ድንግል ሆነልን አለ፡፡ ማርያም ናት ሲል ነው፡፡ አንድም በዚህ ቀን ከነገሥታት ዳዊትን፣ ከመሣፍንት ኢያሱን፣ ከደናግል ኤልያስን አስከትላ መጥታለች፡፡ ዳዊት ምንም ንጉሠ ነገሥት ብትባል የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለህም፡፡ ኢያሱም መድኃኒት ብትባል የደኅንነታችን መጀመሪያ መሆን አልተቻለህም፡፡ ኤልያስም ንጹሕ ድንግል ብትባል የንጽሕናችን መሠረት መሆን አልተቻለህም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ የደኅንነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት ድንግል ማርያም ናት ሲል ነው፡፡ አንድም አክሊሎሙ ለሰማዕት እንዲለው አክሊለ ሰማዕት የሚባል ጌታ፤ ጥንተ ሕይወቶሙ እንዲለው ጥንተ ሕይወት የሚባል ጌታ አኃዜ ዓለም በእራኁ ኩሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ መሠረተ ዓለም ይጸውር ድደ ወይነብር ጠፈረ እንዲል፡፡ መሠረተ ዓለም የሚባል ጌታ በድንግል ማርያም   ተገኘልን፡፡
ትላንት ስሟን አላነሣም ዛሬ ስሟን አነሣ በእንግዳ ልማድ እንግዳን ዕለቱን ስሙን አይጠሩትም ከዋለ ካደረ በኋላ ስሙን ይጠሩታል በዚያ ልማድ ማርያም ማለት ፍጽምት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው መልክ ከደም ግባት አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ ፍጻሜው ግን ንጽሐ ሥጋ ከንጽሐ ነፍስ ድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ አንድም ጸጋ ወሐብት ማለት ነው ለጊዜው ለእናት ለአባቷ ጸጋ ሆና ተሰጥታለች ፍጻሜው ግን ለሰው ሁሉ ጸጋ ሁና ተሰጥታለችና፡፡ አንድም መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው ምእመናንን መርታ ገነት መንግሥተ ሰማያት አግብታለችና፡፡ አንድም ልዕልት ማለት ነው፡፡ ሮም አርያም ማለት ልዑል ማለት እንደሆነ፡፡ እርሷንም መትህተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን ይላታልና፡፡ አንድም ማኅበረ መሐይምናን ወሕዝብ ተለአኪተ እግዚአብሔር ወሰብእ ተፈሥሒ ቤተ እስራኤል ወተሐሰዪ ቤተ ይሁዳ ማለት ነው፡፡ አንድም ማርያም ማለት እግዝእተ ብዙኃን ማለት ነው ያንንማ ዘዕብራይስጢ እንጅ አይለውም ብሎ ማሪሃም ማለት ቅሉ እግዝእተ ብዙኃን ማለት ነው፡፡ አብርሃም ማለት አበ ብዙኃን ማለት እንደሆነ፡፡
እንተ ወለደት ለነ ዘእግዚአብሔር ቃለ… መመኪያነቷን በቅጽል አመጣው አካላዊ ቃልን በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን፡፡
ዘኮነ ሰብአ በእንተ መድኃኒትነ… እኛን ስለማዳን ሰው የሆነ
እምድኅረ ኮነ ሰብአ ጥዩቀ አምላክ ፍጹም ውእቱ… ሰውም ከሆነ በኋላ ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ሐራ ጥቃ ቃል ሥጋ ሆነ ያለውን ይዘው ወደ ታች ተለወጠ ይላሉና ሰውም ከሆነ በኋላ ፍጹም አምላክ ነው አለባቸው፡፡
ወበእንተዝ ወለደቶ እንዘ ድንግል ይእቲ… ስለዚህ ነገር ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ወለደችው
መንክር ኃይለ ወሊዶታ ዘኢይትነገር… ድንቅ የሚሆነው የመውለዷ ሥራ የማይመረመር ነው፡፡ የማይመረመር የመውለዷ ሥራ ድንቅ ነው፡፡
ሰአሊ ለነ ቅድስት… በማይመረመር ግብር ከወለድሽው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ ሐተታ እንደ ሰኞ ።

Sunday, August 7, 2016

"መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው"


የሀገራችን መሪዎች እና በሥሮቻቸው የሚገኙት ባለሥልጣናት "መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው" የምትለዋን አባባል ከአፋቸው አይለዩአትም በተለይ ደግሞ የምርጫ ሰሙን!
በነገራችን ላይ መንግሥትን እንደ መንግሥት በአንድ ግዛት ላይ ለመመስረት 5 መሠረታዊ ጉዳዮች መኖር እንደአለባቸው ብዙ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው:-
ሉአላዊነት
ህዝብ
ድንበር/ወሰን
መንግሥት
እውቅና ናቸው።
ከዚህ እንደምንረዳው መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት አይደለም። መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ቢሆን ኖሮማ ISIS የተባለው መንግሥትም ሕዝብ ነው በተባለ ነበር። ነገር ግን እውቅና ስላልተሰጠው የራሱ የግዛት ወሰን ወይም ድንበር ስለሌለው እርሱን መንግሥት ነው ልንለው አንችልም። መንግሥት እንደ መንግሥት ለመቀጠል ሕዝብ ያስፈልገዋል ሕዝብ ብቻ ሳይሆንም መንግሥት የሚሆንበትንም ወሰን ማስከበር አለበት። ሱማሊያ መንግሥት አልባ ሐገር ናት እየተባለች ያለችው እኮ ሕዝብ ስለሌላት አይደለም ሉአላዊነቷን ስላላስከበረች ነው እንጅ።
መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው የሚባለው እኮ ሕዝቡ የመሾምና የመሻር ሙሉ ስልጣን የያዘ ሲሆን እና የመምረጥና የመመረጥ መብቱ ያለምንም ገደብ በነጻነት የተፈቀደለት ሲሆን ነው። የአገራችን መንግሥት ይህንን መብት የሰጠ ቢሆንም ወደዚህ ለመግባት ግን በርካታ ደረጃዎች ተቀምጠዋል። እነዚያን ደረጃዎች ለማለፍ ደግሞ በወቅቱ ከሚገኘው መንግሥት ጋር መስማማት ይኖርብሃል። ተስማምተህ መቃወም ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ነቀፌታን ያስከትላል። ይህ የዋህ ሕዝብ ለቅድስናው አብልጦ ይጨነቃል። ለዚህም ነው ውኃ መብራት ኔትወርክ ዘይት ስኳር ወዘተ ሲቋረጥ ሁሉ አሜን ብሎ ሲቀበል የኖረው። ይህን የህዝብ የዋህነት ተመልክቶ እንኳ አጥፍቻለሁ ብሎ መንግሥት ይቅርታ አይጠይቅም ምክንያቱም ሥራው ነውና።
ሕዝብ ማለት ከፖለቲካ አስተሳሰብ በላይ ነው። መንግሥት ደግሞ በፖለቲካ አስተሳሰብ ሥር የተወሽቀ ነው። መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ነው ስንል መንግሥት ከፖለቲካ በላይ ነው እንደማለት ነው። መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ከሆነ ሕዝቡ ውረድልኝ ሲልህ መውረድ ውጣ አስተዳድረኝ ምራኝ ሲልህ ሥልጣን ላይ መውጣት ተግባርህ ይሆን ነበር። ምክንያቱም መንግሥት የሚመሠረተው በሥሩ ላሉ ሰዎችም ሥልጣን የሚሰጣቸው ሕዝቡ ስለፈቀደላቸው ብቻ መሆን አለባቸው። ይህ ሥልጣን እኮ የባሕርያችን አይደለም በጸጋ ያገኘነው ሥልጣን ነው። ጸጋው ደግሞ ከአምላክ ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡም የሚሰጠን ነው። ስለዚህ የሕዝብን ቅሬታ አቤቱታ እና ጩኸት መስማት ያስፈልገናል ምክንያቱም መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው ብለናላ። የሕዝቡ ጩኸት የመንግሥትም ጩኸት መሆን አለበት።
ስለአገራችን ሰላም ጸልዩ። አባቶቻችን ሆይ በጸሎታችሁ አስቡን የሕዝቡ ደም እየፈሰሰ ነውና። እንደ ባሮክ እና አቤሜሌክ የአገራችንን ጥፋት አታሳየን እያልን ፈጠሪያችንን እንለምነው። የወገናችንን እልቂት አታሳየን እንበለው። ትናንትና በድርቅ በረሃብ ስንገርፈው የነበረውን ሕዝብ ዛሬ ደግሞ በጥይት ልንደበድበው እንዴት እንደፍራለን? መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ከሆነማ በአደባባይ የሚፈሰው የሕዝብ ደምም ደማችን በሆነ ነበር።
እኛ የምንበረታው በወንድሞቻችን ላይ ነው። ትናንትና ድንበራችንን ጥሰው የጋምቤላ ተወላጆችን አርደው ንብረታቸውን እና ልጆቻቸውን ዘርፈው ሲወጡ እኮ አንድ ጥይት አላባከንንም ነበር። ምክንያቱም ጉዳዩ ከሌላ አገር ጋር ከሌላ ሕዝብ ጋር ነበርና። እነዚያ ታጥቀው መጥተው ገደሉን ዝም ተባለ ዛሬ ሳይታጠቁ መልካም አስተዳድርን ናፍቀው አደባባይ ላይ ወጡ ጥይት ዘነበባቸው ደማቸው ፈሰሰ። ታዲያ የወገኖቻችንን ደም እንዲህ ደመ ከልብ የምናደርገው መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ሰለሆነ ይሆን?
እንዲህ አይነቱን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ጆሮን መስጠት ከመንግሥት ይጠበቃል። መስቀላቸውን ይዘው እንደ ሰማእተ ጽድቅ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ቆሞ ደም እንዳይፈስ መገላገል ደግሞ ከአባቶቻችን ይጠበቃል። ሆኖም ግን መንግሥት እሥር ቤቶቹ ስለማይሞሉበት ጥይቱም ተተኩሶ ስለማያልቅበት ማሰርና መግደል ሥራውን ካደረገ ግን አገራችን ወደ ከፋ አደጋ መጓዟ አያጠራጥርም። ሰለዚህ በቅርበት የሕዝቡን ጩኸት ብታዳምጡት እድሜያችሁ ይረዝማል እንጅ አያጥርም ነበር። አንሰማችሁም በባዶ ሜዳ ላይ ጩኹ የምትሉን ከሆነ ግን መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው ልትሉን ባልተገባም ነበር።
የትናንቱ ጩኸት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የመቃወም ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የክልል ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የግለሰብ ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የመለያየት ጩኸት ነበር፤ የዛሬው ጩኸት ግን ከዚያም በላይ ነው። የማንነት ጥያቄ ነው፣ የሰብአዊነት ጥያቄ ነው፣ የሀገር ጥያቄ ነው፣ የአንድነት ጥያቄ ነው፣ የሁሉም ጥያቄ ነው፣ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ነው። ሰለዚህ እንደትናንትናው ሁሉ አንሰማችሁም ልንባል አይገባንም። መሰማማት፣ መደማመጥ፣ መረዳዳት፣ መወያየት እና መስማማት  ይገባናል እኮ ምክንያቱም በአገራችን ጉዳይ ላይ ሁላችን እኩል እንደሆንን ስለሚሰማን። እኛ ድንበር ሲወረር ድንበራችንን ለማስከበር ብቻ አይደለም ኢትዮጵያዊ የሆነው በውስጧ ካለው ንብረትም ገንዘብም እኩል ለመሳተፍ ጭምር እንጅ። አንዱ እየተራበ ሌላው የሚጠግብባት፣ አንዱ እየተጠማ ሌላው የሚሰክርባት፣ አንዱ ዘይት አጥቶ በቃሪያ እየተቃጠለ ሌላው በቅቤ የሚመገብባት፣ አንዱ በረንዳ ላይ ወድቆ እያደረ ሌላው ከ5ቤት በላይ የሚሠራባት፣ አንዱ ሥራ አጥቶ ሌላው ሳይማር በዝምድና እና በፖለቲካ ከሥራ ሥራን የሚያማርጥባት አገር ሰትሆን ስናይ እኛም ይቆጨናል እኮ። ይህ የማይቆጨው ሰው ካለ ምናልባትም ሰው አይደለም። መንግሥት ደግሞ ሕዝብ ነኝ ይላልና ይበልጥ ቁጭታችን ሊቆጨው ይገባል። ያ ካልሆነ ግን ሕዝቡ ጠያቂ መንግሥት አጥቂ መሆናችን መቆሚያ አይኖረውም።
ይህን የሕዝብ ጩኸት ኔትወርክ በማጥፋት፣ በጥይት በማስፈራራት፣ መብራት በማጥፋት ማፈንና ማዳፈን ይከብዳል። ለጩኸት ማዳፈኛውና ማፈኛው ማደመጥ ብቻ ነው። አዳምጦ ምላሽ መስጠት ከበሳል መሪ የሚጠበቅ ነው። ምክንያቱም በመግደልና በመደፍለቅ ሕዝብን ለመጨረስማ መንግሥት ባላስፈለገንም ነበር። ምሩን አስተዳድሩን ከእኛ ትሻላላችሁ ብሎ በራሱ ላይ ያሰለጠናችሁ እኮ ሕዝብ ነው። ታዲያ እንዴት መንግሥት ሕዝብ ነው እያልን እያወራን ቃላችንን መጠበቅ ተሳነን?
አምላከ ቅዱሳን ለሀገራችን ሰላምን ለህዝቦቿም አንድነትን ፍቅርን መረዳዳትን አድልልን አሜን። እመ ብርሃን ሆይ በዚህ በያዝነው ሱባኤ ምሕረትን ረድኤትን ጸጋ እና በረከትን አድይን አሜን።

Friday, August 5, 2016

“ቃና የለሹ ቃና”

© መልካሙ በየነ
ሐምሌ 29/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ዓላማ አድርጎ የተነሣው ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ውስጣችን እንድናደርገው ነው፡፡ ውስጣችን ስናደርገው ደግሞ ባሕል፣ ወግ፣ እሴት፣ እምነት እና ፍቅር ከእያንዳንዳችን ይርቃሉ፡፡ ላይ ላዩን ስንመለከተው በመዝናናት የሚጀምር ይሁን እንጅ ውስጡ እና ፍጻሜው ግን  ሃይማኖታዊ ሳይሆን አይቀርም የቃና የለሹ ቃና!
አንድ የኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ባለሥልጣን በእነዚህ የግል ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ተጠይቆ በገሪቱ ቴሌቪዥን ማሰራጫ በኢ.ቢ.ሲ ሲመልስ “የእኛ ባለሥልጣን ለማንኛውም የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ እውቅና አልሰጠንም፡፡ ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ ከተከፈቱት የቴሌቪዥን ጣቢያ ፕሮግራሞች የአገራችንን ባህል፣ ወግ እና እሴት የሚጻረሩ አይደሉም” ብሏል፡፡ በእውነት የእኛ ባሕል ቀኑን ሙሉ ከቴሌቪዥን ስክሪን ላይ አፍጥጦ መዋል ነው እንዴ? የእኛ ባሕል እና እሴት እኮ መረዳዳት፣ መከባበር፣ መፈቃቀር፣ እንግዳን መቀበል፣ ፈጣሪን ማመስገን፣ሥራን አብዝቶ መሥራት፣ ጀግንነት ወዘተ ነው፡፡ ባሕልና እሴት ፖለቲካ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካ ደጋፊም አለው ተቃዋሚም አለው ህላችን ግን ለሁላችን ነው ለተቀዋሚውም ለደጋፊውም፡፡ በእውነት እነዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሀገራችንን መንግሥት ደካማ ጎኖች የሚገልጹ ቢሆኑ ኖሮ ይህን ያህል ዕድሜ ይኖራቸው ነበር? የኢሳትን እድል ይገጥማቸው ነበር፡፡ እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገጽ ይጠፋ ነበር፡፡
የእኛ ባህል፣ ወግ እና እሴት በቃና የለሹ ቃና እንደሚቀርበው ዛራ እና ቻንድራ የተንዛረረ እና የተቸናደረ፣ እንደ ኩዚና ጉኒ የተንኳዘዘ እና የተንጓነነ፣ እንደ ጥቁር ፍቅር ውስጡ የጠቆረ፣ እንደ ውበት እስረኞች በውበት የታሠረ፣ እንደ መንታ ገጽ ልቡ በመንታ መንገድ የሚጓዝ አይደለም፡፡ እነዚህ ፊልም ተብየዎቹ የሚቀርቡባቸውን ሰዓታት ተመልከቱት፡፡ ተያይዘው ለ24 ሰዓታት ለ7 ቀናት የሚዘልቁ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ ወጣቶቹን ከሥራ አግቶ ተቀምጠው እንዲውሉ እና የቴሌቪዥናቸውን የስክሪን መጠን  ወይኔ 21 ቢሆን ኖሮ! ወይኔ 41 ኢንች ቢሆን ኖሮ! ወይኔ ፍላት ቢሆን ኖሮ!ወይኔ እንዲህ ሆኖልኝ ኖሮ! ወዘተ ብቻ እንዲሉ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሃይማታዊም፣ ባህላዊም እሴት የለውም፡፡ ዓላማው ከሃይማኖት፣ ከሐገር ፍቅር፣ ከፖለቲካ፣ ከማንኛውም ማኅበራዊ ግንኙነት ግዴለሾች ማድረግ ብቻ ነው፡፡
ዓላማው ሃይማታዊ ግዴለሾች ለማድረግ ነው የምለው ዝም ብየ አይደለም፡፡ የሚተላለፉበት ሠዓት ግን ከብዙ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች የሚያርቅ ነው፡፡ በዛራና ቻንድራ ስንንዛረርና ስንንቸናደር የሰርክ መርሀ ግብር ያልፈናል፡፡ ችግር የለውም አንዴ ደርሼ እመጣለሁ እያልን ስንጠብቅ እነ ኩዚና ጉኒ መጥተው ያንጓንኑናል ያንኳዝዙናል፡፡ በቃ ቀረ ነገ እሄዳለሁ እንል እና ራሳችንን እንጽናናለን ከዚያም ነገ እንደዛው ይኼው ተመሳሳይ ሂደት ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ዓላማው ሃይማታዊ ነው የምላችሁ ለዚህ ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ተጽእኖዎች ምናልባትም የፕሮቴስታንቱ ሊሆኑ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ መብራትና ውኃን ተመልከቷቸው መቸ መቸ እንደሚመጡና መቸ መቸ እንደሚሄዱ አስተውሉ፡፡ ውኃ እሁድና ቅዳሜ ስትፈስ ትውልና ሰኞ ጀምራ ትደርቃለች፡፡ ሰንበትን ውኃ ከቤቴ አላስገባም የሚለው የአገራችን አማኝ ሳይወድ በግዱ እንዲያስገባ ይገደዳል ማለት ነው፡፡ መብራትንም እንዲሁ ተመልከቱት፡፡ ገጠር ላይ እና ከተማ ላይ የሚጠፋበት ቀን ይለያያል፡፡ ገጠር ላይ በዓላትን እየጠበቁ ማብራት ሥራን እየጠበቁ ማጥፋት ልማድ ሆኗል፡፡ ከበረሃው ከደጋው ወደ ወፈጮ ቤቶች እህላቸውን ጭነው ይተምማሉ፡፡ በዚያም ወፍጮ ቤት ይከትሙና መብራት መጣ መብራት ሄደ ሲሉ ይከርማሉ፡፡ በጣም ታላላቅ በሚባሉ በዓላት ዕለት መብራት ይመጣል፡፡ መብራትን በመጠበቅ ከቤቱ ሳምንት ያህል ርቆ የሰነበተ ህዝብም በዓሉን ከምንም ሳይቆጥር አስፈጭቶ ይኼዳል፡፡  ከተማ ላይ ስትሄዱ ግን መብራት የሚጠፋው በታላቅ በዓላት ቀን ነው፡፡ በእነዚህ ታላለቅ በዓላት አብያተ ክርስቲያናት የማኅሌት ሥርዓቱን ለህዝቡ ለማሰማት በድምጽ ማጉያ ተጠቅመው ስለሚቆሙ ይህንን ህዝቡ እንዳይሰማ መብራት ይቋረጣል፡፡ በእርግጥ ይህ እንደሚደረግ የታወቀ ስለሆነ አብዛኞቹ በከተማ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው የሆነ ጀነሬተር ገዝተው በመገልገል ላይ ናቸው፡፡
ቃና የለሹ ቃናም ከእነዚህ የፕሮቴስታንት ዓላማ ካነገቡ ሰዎች እጅ የገባ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ በተለይ ወጣቱ ሱስ እንዳይሆንባችሁ ቃና የሚለውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም በመጠን እና በልክ እንጠቀምበት፡፡ ብንችል ከቻናል ሊስቱ ላይ እናጥፋው ባንችል የምንመለከትበትን ሰዓት ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን በማይጋፋ መልኩ እናመቻች፡፡ ቃና ውስጤ ነው የሚለው መፈክራቸው ቀላል እንዳይመስለን፡፡ ውስጣችን እየሆነ መጥቷል ውስጣችን ደግሞ ደማችን ነው ደማችን ደግሞ ድንግል ማርያም ያለችበት ደም ነው፡፡ ታዲያ ውስጣችን ነው ሲሉን እኮ ደማችን ውስጥ ያለችውን ድንግል ማርምያን አስወግደው በእነርሱ ቃናነት ሊለውጡት ነው፡፡

በእርግጥ 2008 ለቃና መፈጠር ብቻ አልነበረም ዘመን የሆነው፡፡ ሌሎችም እንደ አሸን የፈሉ ጣቢያዎች ተፈልፍለዋል፡፡ ባህላችንን፣ ወጋችንን፣ እሴታችንን፣ ሃይማኖታችንን የሚጋፋ ቃና የለሹ ቃና ስለሆነ ብቻ ነው እንጅ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የቴሌቪዥን ሥርጭት ጀምሯል ታላቅ ፓትርያርክ የነበሩትን የጸሎት እና የትህትና አባት የነበሩትን 3ኛው ፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማትን ከዘመናቸው ዘመን ባይገጥመንም እንኳ ትምህርታቸው እየተላለፈ ነውና እንስማው እስኪ፡፡ በቃና የለሹ ቃና ውስጣችንን ከምናጣ ውስጣችን ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤትክርስቲያንን የቴሌቪዥን ሥርጭት እንከታተል እላለሁ፡፡ ይህን የምላችሁ ግን እንደ ምክር ነው እንጅ ለማስተዋወቅ ወይም ጥላቻን ለመፍጠር አይደለም፡፡ እንደምትሩኝ ግን ተስፋ አደርጋለሁ!!!

Thursday, August 4, 2016

“የአንድ ቀን ስህተት እስከሞት”

© መልካሙ በየነ
ሐምሌ 28/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ወንድሞቼ እህቶቼ እንደምን ከረማችሁ፡፡ በሥራ ምክንያት የተወሰኑ ሳምንታትን ጠፍቻለሁ ወደፊትም ልጠፋ እችላለሁ በእርግጥ፡፡ አምላክ ፈቀደልኝና ዛሬ ይችን መልእክት እንድጽፍ ቻልኩ፡፡
እውነት አለ ውሸትም አለ፤ ትክክል አለ ስህተትም እንዲሁ፡፡ ምንም ቢታፈኑ እውነትና ጭስ መውጫ አያጡም ይባላል፡፡ በእርግጥ ስህተትም ቢታፈን ስህተትነቱን እንደ እውነት እንደ ትክክል እስካልተቀበልነው ድረስ መውጫ አያጣም፡፡ ስህተትነቱ ይታወቅ ዘንድ ለሁሉ ይገለጣል ሆኖም ግን ታፍኖ እንዲኖር የእኛ ተጽእኖ ከባድ ነው፡፡ ለዚህም ነው አንድ ቀን በተሳሳትነው ስህተት እድሜ ልካችንን ስህተት እንድንሠራ እድልን የምንሰጠው በርን የምንከፍተው፡፡ የትምህርት ማስረጃዎቻችንን ተመልከቷቸው፡፡ በሆነ ሰው ስህተት ወይም በሆነ አጋጣሚ ስማችን ላይ ያልተገባ ፊደል ተጨምሮ ወይም ከሚገባው ፊደል ጎድሎ የትምህርት ማስረጃ ተሠርቶ ይሰጠናል፡፡ ይህ የትምህርት ማስረጃ ስህተት መሆኑን እያወቅን ማስተካከል ባለመቻላችን ብቻ ወደ ቀጣይ ስህተት እንጓዛለን፡፡ በብዛት እነዚህ አጋጣሚዎች የውጭ ዕድል ባገኙ ሰዎች ዘንድ ጎልተው ይወጣሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ <<ABEBE>> የሚባል ሰው <<ABEBA>> ተብሎ የትምህርት ማስረጃ በስህተት ተሠርቶ ይሰጠዋል፡፡ የውጭ ዕድል አግኝቶ መሄዱ ግድ ከሆነ ይህ ሰው ፓስፖርቱ <<ABEBA>> በሚል ስም ነው የሚሠራለት፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ሰው አንድ ቀን በተሳሳተው ስህተት መታወቂያው፣ የመንጃ ፈቃዱ፣ በቀጣይ የሚማራቸው የትምህርት ማስረጃዎች በሙሉ የሚሠሩለት በ <<ABEBA>> ይሆናል፡፡ የአንድ ቀን ስህተት ዕድሜ ልኩን እንዲሳሳት ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን ስህተቱን ስለሚለምደው እንደ ትክክል ይቆጥረዋልና <<ABEBA>> በሚለው ስም መጠራትን ይለምደዋል፡፡
ይህ ስህተት በሀገራችን በልዩ ልዩ ተቋማት ላይም እንመለከተዋለን፡፡ አንድ ሰው በሆነ ወቅት በሆነ አጋጣሚ መመሪያ ጥሶ ህግ አፍርሶ የሆነ ነገርን በስህተት መሥራት ይለምዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ያ ስህተት አሠራር እንደ ህግ ይሆንና ሁሉም ይሠራበታል፡፡ እርሱ ወርዶ በተራው ሌላ ሰው ቢተካ እንኳ አንዴ ስህተቱ ተሠርቷልና በዚያ ስህተት አሠራር ይቀጥላል፡፡ ይህ የስህተት አሠራር ትክክለኛ አሰራር ሆኖ በህብረተሰቡ ዘንድም እንደ መመሪያ ጸድቋልና ማንም ቅሬታ አያቀርብም፡፡ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ማለት ይህ ነው፡፡ አንድ ጊዜ በስህተት ዝናብ በስብሻለሁና ዳግም ለሚዘንብብኝ የስህተት ዝናብ ዣንጥላ አያስፈልገኝም ምክንያቱም አንዴ በስህተት በስብሻለሁና የሚል አመለካከት ያነገበ ነው፡፡
የህዝብን የጥያቄ ጩኸት በድብደባ ዝም ማስባል ከለመድህ እድሜ ልክህን ያንን ትፈጽመዋለህ፡፡ ምክንያቱም አንተ መደብደብን (ይላላል) ህዝቡም መደብደብን (ይጠብቃል) ልማድ አድርገዋልና እንደ ትክክለኛ አሠራር ይቆጠራል፡፡ የተለያዩ የስህተት ሥራዎቻችን ልማድ ወደ መሆን ይቀየሩና ለስህተታችን ይቅርታ በማለት ፋንታ ስህተታችን ትክክል እንደሆነ ልናስረዳ እንሞክራለን፡፡ መብራት ሲጠፋ፣ ኔት ወርክ ሲቋረጥ፣ ውኃ ስትቀር፣ ስኳር እና ዘይት ሲጠፋ ወዘተ ይቅርታ ብሎ የሚያውቅ ማን አለ? ማንም የለም ምክንያቱም ይህን ማድረጋቸው በራሱ ስህተት እንደሆነ አላወቁማ፡፡ ይቅርታ ለመጠየቅ እኮ በመጀመሪያ ስህተትን ማመን ያስፈልጋል ስህተቱን ያላመነ ሰው ይቅርታን ከወዴት ያውቀዋል፡፡
የወጣቱንም ሱስ እንዲሁ ተመልከቱት አንድ ቀን በሆነ አጋጣሚ በሆነ ሰው ግፊት የጀመራት ሲጋራ ዛሬ ድረስ ጓደኛው አድርጎ ይዟታል፡፡ ጫትና መጠጡ ዝሙትና መዳራቱም እንዲሁ ነው፡፡ በሆነ አጋጣሚ የሆነ ስህተት ስለሠራና ከእነዚህ ሱሶች ጋር ስለተጣበቀ ስህተት ያደረገ አይመስለውም፡፡ ፈጣሪውን የበደለ ራሱንም ያዋረደ አይመስለውም፡፡ ምክንያቱም አንድ ጊዜ ስህተቱን ትክክል ነው ብሎ ራሱን አሳምኖታልና፡፡
አንድ ቀን የተሰራ ስህተት እድሜ ልክን እንደተሳሳትን የሚያደርግ ልማድ ነው፡፡ ስለዚህ ስህተታችን ማየት መቼም ቢሆን የምንሠራውን ነገር ትክክል ስለመሆኑ መመርመር ያስፈልገናል፡፡