© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 04/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
“አትናገር፤ ተናገር
ካሉህ ግን እውነቱን ብቻ ተናገር!” የሚለውን ምርጥ ቃል እኔ በዚህ መልኩ ልጻፈው እንጅ የቀደሙ አባቶቻችን የኖሩበት የህይወት
መንገድ ነው፡፡ ይህንን የተናገሩት አባቶቻችን ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ የተናገሩት ቃል የለም የጻፉትም መጽሐፍ የለም ካላችሁኝ ግን
ይህ ቃል ምርጥ ስለሆነ እኔ እንደተናገርኩት አድርጋችሁ ያዙት ምክንያቱም የሚያሳፍር የሚያሸማቅቅ እና የሚያዋርድ አይደለምና፡፡
ተናጋሪ አትሁን፣
አፈ ጮሌ አትሁን፣ ጥራዝ ነጠቅ አትሁን፣ ሳታይ አታውራ አትመስክር፣ ሰውን ያስቀይማልና ወሬ አታብዛ፣ መጥፎ ነገር ተናግረህ ሰው
ታስቀይማለህና አትናገር በዚህ ብቻም ያይደለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደተናገረው “ወአርመምኩ ለሠናይ፤ ለመልካም ነገር ለበጎ ነገር
እንኳ ዝም አልኩ አልተናገርኩም” እንዳለው ለመልካም ነገር እንኳ አትናገር፡፡ የምትናገርበት አፍህ የአንተ ነው፣ የምትናገርበት
ምላስህ የአንተ ነው፣ የምትናገርበት ልሳንህ የአንተ ነው፡፡ ማንም አንተ ልሳን ውስጥ ገብቶ እንድትናገር አያደርግህም፤ ማንም የአንተን
አንደበት ሊቆጣጠረው አይችልም፤ ማንም የአንተን አፍ ሊጠቀምበት አይችልም ምክንያቱም ገንዘብህ ነውና፡፡ የአንተን ገንዘብ ካልመጸወትከው
አልያም ካልተሰረቅህ በቀር የአንተ የራስህ ነው፡፡ ስትመጸውተውና ስትሰረቀው ግን የአንተ መሆኑ ይቀራል ያኔ በገንዘብህ ሌላው ያዝበታል፡፡
አንደበት፣ ልሳን፣ ምላስህ ግን እስካልሞትክ ድረስ የአንተ እና የአንተ ብቻ ናቸው ስትሞት ግን ይለወጣሉ አንተም አንተ አትሆንምና፡፡
በሕይወት ሳለህ እነዚህን ንብረቶች የአንተ ማድረግ ካልቻልክ ግን ሰብአዊነትህ ላይ ጥያቄ ይፈጥራል፡፡
በዚህ በወቅታዊው
የወገኖቻችን እልቂት ላይ መንግሥት በርካታ መግለጫዎችን ሲሰጥ የቆየ መሆኑን እናውቃለን፡፡ የየክልሉ ባለሥልጣናትም እንዲሁ በእነርሱ
ሥር ባሉ የሚዲያ አካላት መግለጫዎቻቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ከዕለት ዕለት እልቂቱ ሲባባስ ሲጨምር እንጅ ሲቀንስ ሲረግብ
አላስተዋልንም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው መግለጫ ማስፈራሪያና ዛቻ የታከለበት ስለሆነ ሌላ ቁጭትን ሲፈጥር ነው የሚስተዋለው፡፡ በተለይ
ከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ቃላትን መምረጥ ያሻቸዋል፡፡ እኛ የፈለግነውን ብንናገር ቃላትን ባንመርጥ ማንም ስለማይሰማን
ለብጥበብጡ መባባስ መንስኤ አንሆንም እነርሱ ግን ዓለም ቁጭ ብሎ በሚመለከተው ሚዲያ ላይ ነው እየተናገሩ ያሉት፡፡ ስለዚህ በማስተዋልና
በረዳት ቢሆን መልካም ነው እላለሁ፡፡ ከቻላችሁ አትናገሩ ምክንያቱም መናገራችሁ ብጥብጥን ፈጠረ፣ እልቂትን አባባሰ፣ ደምን አፋሰሰ፡፡
እንድትናገሩ ከተገደዳችሁ ግን ተናገሩ ያውም እውነቱን ብቻ ምንም ውሸትና ስላቅ ማስፋራራትና መዛት የሌለበትን ትምክህትና ቧልት
ያለተቀላቀለበትን ንጹሑን ኢትዮጵያዊነት የሚገልጽ ንግግር ተናገሩ፡፡
የሃይማኖት አባቶችም
እንዲሁ አትናገሩ፤ ተናገሩ ካሉዋችሁ ግን እውነቱን ብቻ ተናገሩ፡፡ የሃይማት አባቶች የምታስተዳድሩት ህዝብ መንግሥት ከሚያስተዳድረው ሕዝብ በላይ
መሆኑን ተረዱ፡፡ መንግሥት ለዚህች አገር ብቻ ነው የሚጨነቀው፣ መንግሥት ለዚህች ሐገር ሰላም ብቻ ነው የሚያስበው፣ መንግሥት ለዚህች
አገር እድገት ብቻ ነው የሚሠራው እናንተ ግን ለዓለም ነው የምትጸልዩት፤ እናንተ ግን ለዓለም እድገት ነው የምትሠሩት፡፡ ስለዚህ
ከመንግሥት በላይ ናችሁ ከህዝቡም በላይ ናችሁ ይህን ከተረዳችሁ ደግሞ በህዝቡና በመንግሥቱ መካከል ገብታችሁ የማስተረቅ የመሸምገል
ያጠፋውን የማውገዝ ሥልጣን አላችሁ፡፡ የእናንተ አደራ ሰው ሲሞት ፍትሐት አድርሶ መቅበር ብቻ አይደለም እንዳይሞት መጠበቅ ጭምር
ነው እንጅ፡፡ መንግሥት የሚነግረንን ነገር ብትነግሩን ግን ምንም አይፈይድልንም ምክንያቱም የሚገድለንን ደግፋችኋልና፡፡ የሃይማኖት
አባቶች ወገንተኞች መሆን አይገባችሁም ክልላዊ ዝቅ ብሎም ጎጣዊ የሆነ አስተሳሰብን ከእናንተ አንሻም፡፡ ሰማእተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ
አቡነ ጴጥሮስን ከልባችሁ ጽላት ጻፏቸው እስኪ፡፡ ይህች አገር እኮ የታላላቅ ታሪክ ሰሪዎች አገር ናት፡፡ ታዲያ ለውጭ ጠላት አንንበረከክም
ብሎ የአንድነት ታሪክን በጀግንነት የሠራ ህዝብን በአገሩ ልጆች በመከፋፈል ሲገደል ደሙ መሬት ሲፈስ እንዴት መስቀላችንን እንደብቀዋለን፡፡
ዋናው መልእክቴ
አባቶቼ ሆይ አትናገሩ፤ ተናገሩ ካሉዋችሁ ግን እውነቱን ብቻ ተናገሩ የሚል ነው፡፡ አባታችን ቅዱስ ፓትርያርኩ ትናንትና መግለጫ
ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ እኔ ለራሴ መግለጫውን አንድ የመንግሥት አካል ከሚሰጠው መግለጫ የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ አንድ የተቀየረ
ቃል ቢኖር “መንግስታችን” የሚለው ቃል “ቤተክርስቲያናችን” በሚል መተካቱ ብቻ ነው፡፡ ይህ የአባታችን ንግግር ምእመናንን ያስቀይማል፣
ህዝቡን ላልተፈለገ ዓላማ ያነሳሳል ስለዚህ ነው ባንናገር መልካም የሚሆነው፡፡ የግድ ከሆነ ግን የአቡነ ጴጥሮስን አንደበት ለደቂቃዎች
እንኳ መዋስ ያስፈልጋል፡፡ “ልጆቻችን” በማለት ፈንታ “ዜጎቻችን” ሲባል ቅር ያሰኛል፡፡ በእውነት አባት የለንምን ያስብላል፡፡
ንግግራችን ካላማረ ንግግሬ አያምርም ብሎ ዝም ማለት ይሻላል፡፡ ተናግሮ ከማስቀየም አለመናገር ይሻላል፡፡ መናገር ግድ ከሆነብን
ግን ህዝቡን ጥፋተኛ መንግሥትን ትክክለኛ አድርገን ያለምንም መረጃ ወደአንዱ በማዘንበል መናገር ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሁለቱም
መካከል ገብተው የቱ ነው ያጠፋ በማለት መመርመር ከንግግራቸው በፊት የሚቀድም ተግባር ነበር፡፡ አባቶቻችን ያቆዩን በጸሎት ማሰብ
እንኳ መጀመሪያ ላሉበት ቦታ ነው ይላሉ ምክንያቱም ዐሥራቱን ቀዳማያቱን ትመገባለህና ይላሉ፡፡ ይህ እየሞተ ያለው ህዝብ እኮ ዐሥራት
በኩራቱን እየከፈለ ሞገስ የሆነን ህዝብ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ህዝብ ሲሞት ወገኔ አይደለህም ልንለው እንችላለንን?
ለሀገራችን ሰላም
እንማልዳለን!!!
No comments:
Post a Comment