Sunday, August 7, 2016

"መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው"


የሀገራችን መሪዎች እና በሥሮቻቸው የሚገኙት ባለሥልጣናት "መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው" የምትለዋን አባባል ከአፋቸው አይለዩአትም በተለይ ደግሞ የምርጫ ሰሙን!
በነገራችን ላይ መንግሥትን እንደ መንግሥት በአንድ ግዛት ላይ ለመመስረት 5 መሠረታዊ ጉዳዮች መኖር እንደአለባቸው ብዙ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው:-
ሉአላዊነት
ህዝብ
ድንበር/ወሰን
መንግሥት
እውቅና ናቸው።
ከዚህ እንደምንረዳው መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት አይደለም። መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ቢሆን ኖሮማ ISIS የተባለው መንግሥትም ሕዝብ ነው በተባለ ነበር። ነገር ግን እውቅና ስላልተሰጠው የራሱ የግዛት ወሰን ወይም ድንበር ስለሌለው እርሱን መንግሥት ነው ልንለው አንችልም። መንግሥት እንደ መንግሥት ለመቀጠል ሕዝብ ያስፈልገዋል ሕዝብ ብቻ ሳይሆንም መንግሥት የሚሆንበትንም ወሰን ማስከበር አለበት። ሱማሊያ መንግሥት አልባ ሐገር ናት እየተባለች ያለችው እኮ ሕዝብ ስለሌላት አይደለም ሉአላዊነቷን ስላላስከበረች ነው እንጅ።
መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው የሚባለው እኮ ሕዝቡ የመሾምና የመሻር ሙሉ ስልጣን የያዘ ሲሆን እና የመምረጥና የመመረጥ መብቱ ያለምንም ገደብ በነጻነት የተፈቀደለት ሲሆን ነው። የአገራችን መንግሥት ይህንን መብት የሰጠ ቢሆንም ወደዚህ ለመግባት ግን በርካታ ደረጃዎች ተቀምጠዋል። እነዚያን ደረጃዎች ለማለፍ ደግሞ በወቅቱ ከሚገኘው መንግሥት ጋር መስማማት ይኖርብሃል። ተስማምተህ መቃወም ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ነቀፌታን ያስከትላል። ይህ የዋህ ሕዝብ ለቅድስናው አብልጦ ይጨነቃል። ለዚህም ነው ውኃ መብራት ኔትወርክ ዘይት ስኳር ወዘተ ሲቋረጥ ሁሉ አሜን ብሎ ሲቀበል የኖረው። ይህን የህዝብ የዋህነት ተመልክቶ እንኳ አጥፍቻለሁ ብሎ መንግሥት ይቅርታ አይጠይቅም ምክንያቱም ሥራው ነውና።
ሕዝብ ማለት ከፖለቲካ አስተሳሰብ በላይ ነው። መንግሥት ደግሞ በፖለቲካ አስተሳሰብ ሥር የተወሽቀ ነው። መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ነው ስንል መንግሥት ከፖለቲካ በላይ ነው እንደማለት ነው። መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ከሆነ ሕዝቡ ውረድልኝ ሲልህ መውረድ ውጣ አስተዳድረኝ ምራኝ ሲልህ ሥልጣን ላይ መውጣት ተግባርህ ይሆን ነበር። ምክንያቱም መንግሥት የሚመሠረተው በሥሩ ላሉ ሰዎችም ሥልጣን የሚሰጣቸው ሕዝቡ ስለፈቀደላቸው ብቻ መሆን አለባቸው። ይህ ሥልጣን እኮ የባሕርያችን አይደለም በጸጋ ያገኘነው ሥልጣን ነው። ጸጋው ደግሞ ከአምላክ ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡም የሚሰጠን ነው። ስለዚህ የሕዝብን ቅሬታ አቤቱታ እና ጩኸት መስማት ያስፈልገናል ምክንያቱም መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው ብለናላ። የሕዝቡ ጩኸት የመንግሥትም ጩኸት መሆን አለበት።
ስለአገራችን ሰላም ጸልዩ። አባቶቻችን ሆይ በጸሎታችሁ አስቡን የሕዝቡ ደም እየፈሰሰ ነውና። እንደ ባሮክ እና አቤሜሌክ የአገራችንን ጥፋት አታሳየን እያልን ፈጠሪያችንን እንለምነው። የወገናችንን እልቂት አታሳየን እንበለው። ትናንትና በድርቅ በረሃብ ስንገርፈው የነበረውን ሕዝብ ዛሬ ደግሞ በጥይት ልንደበድበው እንዴት እንደፍራለን? መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ከሆነማ በአደባባይ የሚፈሰው የሕዝብ ደምም ደማችን በሆነ ነበር።
እኛ የምንበረታው በወንድሞቻችን ላይ ነው። ትናንትና ድንበራችንን ጥሰው የጋምቤላ ተወላጆችን አርደው ንብረታቸውን እና ልጆቻቸውን ዘርፈው ሲወጡ እኮ አንድ ጥይት አላባከንንም ነበር። ምክንያቱም ጉዳዩ ከሌላ አገር ጋር ከሌላ ሕዝብ ጋር ነበርና። እነዚያ ታጥቀው መጥተው ገደሉን ዝም ተባለ ዛሬ ሳይታጠቁ መልካም አስተዳድርን ናፍቀው አደባባይ ላይ ወጡ ጥይት ዘነበባቸው ደማቸው ፈሰሰ። ታዲያ የወገኖቻችንን ደም እንዲህ ደመ ከልብ የምናደርገው መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ሰለሆነ ይሆን?
እንዲህ አይነቱን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ጆሮን መስጠት ከመንግሥት ይጠበቃል። መስቀላቸውን ይዘው እንደ ሰማእተ ጽድቅ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ቆሞ ደም እንዳይፈስ መገላገል ደግሞ ከአባቶቻችን ይጠበቃል። ሆኖም ግን መንግሥት እሥር ቤቶቹ ስለማይሞሉበት ጥይቱም ተተኩሶ ስለማያልቅበት ማሰርና መግደል ሥራውን ካደረገ ግን አገራችን ወደ ከፋ አደጋ መጓዟ አያጠራጥርም። ሰለዚህ በቅርበት የሕዝቡን ጩኸት ብታዳምጡት እድሜያችሁ ይረዝማል እንጅ አያጥርም ነበር። አንሰማችሁም በባዶ ሜዳ ላይ ጩኹ የምትሉን ከሆነ ግን መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው ልትሉን ባልተገባም ነበር።
የትናንቱ ጩኸት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የመቃወም ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የክልል ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የግለሰብ ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የመለያየት ጩኸት ነበር፤ የዛሬው ጩኸት ግን ከዚያም በላይ ነው። የማንነት ጥያቄ ነው፣ የሰብአዊነት ጥያቄ ነው፣ የሀገር ጥያቄ ነው፣ የአንድነት ጥያቄ ነው፣ የሁሉም ጥያቄ ነው፣ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ነው። ሰለዚህ እንደትናንትናው ሁሉ አንሰማችሁም ልንባል አይገባንም። መሰማማት፣ መደማመጥ፣ መረዳዳት፣ መወያየት እና መስማማት  ይገባናል እኮ ምክንያቱም በአገራችን ጉዳይ ላይ ሁላችን እኩል እንደሆንን ስለሚሰማን። እኛ ድንበር ሲወረር ድንበራችንን ለማስከበር ብቻ አይደለም ኢትዮጵያዊ የሆነው በውስጧ ካለው ንብረትም ገንዘብም እኩል ለመሳተፍ ጭምር እንጅ። አንዱ እየተራበ ሌላው የሚጠግብባት፣ አንዱ እየተጠማ ሌላው የሚሰክርባት፣ አንዱ ዘይት አጥቶ በቃሪያ እየተቃጠለ ሌላው በቅቤ የሚመገብባት፣ አንዱ በረንዳ ላይ ወድቆ እያደረ ሌላው ከ5ቤት በላይ የሚሠራባት፣ አንዱ ሥራ አጥቶ ሌላው ሳይማር በዝምድና እና በፖለቲካ ከሥራ ሥራን የሚያማርጥባት አገር ሰትሆን ስናይ እኛም ይቆጨናል እኮ። ይህ የማይቆጨው ሰው ካለ ምናልባትም ሰው አይደለም። መንግሥት ደግሞ ሕዝብ ነኝ ይላልና ይበልጥ ቁጭታችን ሊቆጨው ይገባል። ያ ካልሆነ ግን ሕዝቡ ጠያቂ መንግሥት አጥቂ መሆናችን መቆሚያ አይኖረውም።
ይህን የሕዝብ ጩኸት ኔትወርክ በማጥፋት፣ በጥይት በማስፈራራት፣ መብራት በማጥፋት ማፈንና ማዳፈን ይከብዳል። ለጩኸት ማዳፈኛውና ማፈኛው ማደመጥ ብቻ ነው። አዳምጦ ምላሽ መስጠት ከበሳል መሪ የሚጠበቅ ነው። ምክንያቱም በመግደልና በመደፍለቅ ሕዝብን ለመጨረስማ መንግሥት ባላስፈለገንም ነበር። ምሩን አስተዳድሩን ከእኛ ትሻላላችሁ ብሎ በራሱ ላይ ያሰለጠናችሁ እኮ ሕዝብ ነው። ታዲያ እንዴት መንግሥት ሕዝብ ነው እያልን እያወራን ቃላችንን መጠበቅ ተሳነን?
አምላከ ቅዱሳን ለሀገራችን ሰላምን ለህዝቦቿም አንድነትን ፍቅርን መረዳዳትን አድልልን አሜን። እመ ብርሃን ሆይ በዚህ በያዝነው ሱባኤ ምሕረትን ረድኤትን ጸጋ እና በረከትን አድይን አሜን።

No comments:

Post a Comment