© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 05/2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ኤልሳዕ መምህሩ ኤልያስን ሸኝቶ ሲመለስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ኢያሪኮ ደረሰ፡፡ ከዚያም ከከተማው ገባና “ሠናይት
ንብረታ ለዛቲ ሐገር” አለ፡፡ ኤልሳዕ እየተመለከታት ያለችው ሀገር መልካም ናት፡፡ ከውጭ ሲመለከቷት መልካም ናት፣ ያማረች ናት፣
ያጌጠች ናት ለዚህም ነው ኤልሳዕ መልካምነቷን የሚመሠክርላት፡፡ ሆኖም ግን የሀገሪቱን መልካም መሆን አለመሆን የሚያውቁ በውስጧ
የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች የሚመለከቱት ህንጻውን ነው፣ ሌሎች የሚመለከቱት መንገዱን ነው፣ ሌሎች የሚመለከቱት የቤተ መንግሥቱን
ልምላሜ ነው፣ ሌሎች የሚመለከቱት 24 ሰዓት ያለአገልግሎት የሚፈሰውን ፋውንቴን ነው እውነቱ ያለው ግን በኗሪዎች እጅ ብቻ ነው፡፡
ለዚህም ነው ኤልሳዕ ሐገሪቱ መልካም ናት እያለ ስለሐገሪቱ መልካምነት ሲናገር ከታይታ መልካምነቷ ያልተጠቀመው ህዝብ “ወማየ ብሔራሰ እኩይ ውእቱ፣ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕ ሆይ! ውኃው ግን
ወላድ ቢጠጣው ያመክናል፣ መካን ብትጠጣውም አንጀቷን ቆርጦ ሆዷን በጥብጦ ይገድላታል” ማለቱ፡፡
የአገራችን መልካምነት፣ ታይታነት፣ ዕድገትና ልማት፣ ብልጽግና ሰላም ወዘተ እንዲህ ነው፡፡ አሜሪካ ብትመሰክር፣
እስራኤል ብትመርቅ፣ ቻይና ብታሞግስ፣ ኮሪያ ብትሸልም፣ ጃፓን ብታደንቅ አይገርምም ምክንያቱም እነርሱ ያዩት ፎቁን እንጅ ከፎቁ
ሥር የወደቁትን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦውን እንጅ ውኃውን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት
አስፋልቱን እንጅ በአስፋልቱ ላይ ተኝቶ የሚያድረውን መጠለያ አልባ ወገኖቻችንን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የቤተ መንግሥቱን
የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት እንጅ የእኛን በኩራዝና በሻማ ማደራችንን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የቴሌቪዥኗን ኢትዮጵያ
ነው እንጅ እኛ የምንኖርባትን እውነተኛዋን ኢትዮጵያ አይደለምና፡፡ ስለዚህም አንፈርድባቸውም፡፡ ደግሞም እኮ እኛ ተደራጅተን ለመኖሪያ
እንኳ 200 ካሬ ሜትር ያላገኘነውን የአገራችንን መሬት በገፍ የሚያፍሱ ስለሆነ ቢያወድሱን አይገርምም፡፡ አለቃ ገብረ ሃናን ልጃቸው
“አባቴ ሰው ሁሉ ድንቼ ድንቼ ይለኛል” አለቻቸው አሉ፡፡ እርሳቸውም ሲመልሱ “ልጄ እንዳይልጡሽ ተጠንቀቂ” አሏት ይባላል፡፡ ስለዚህ
ነው እንግዲህ መጠንቀቅ የሚያሻን፡፡ ድንቼ ድንቼ የሚለንን የውጭ ሙገሳ አንሻም በሉልን ምክንያቱም ሊልጡን የተዘጋጁ ናቸውና፡፡
ኤልሳዕ የዚችን ሐገር እውነተኛ ማንነት ተረዳ፡፡ የሃይማኖት አባቶቻችን ሆይ ኤልሳዕን እንስማው እባካችሁ፡፡
ዝም ብለን ይህች አገር መልካም ናት ባንል መልካም ነው፡፡ ኤልሳዕ ውጯን ስለተመለከተ ነው እናንተ ግን ውስጧን ትመለከታላችሁና
የመልካምነቷ ተካፋዮች ስለመሆናችሁ ማረጋገጥ አለባችሁ፡፡ አሁን ኤልሳዕ መልካም አገር እንደሆነች ተረድቷል ነገር ግን መልካምነቷን
የሚለውጥ አንድ ችግር እንዳለ ከነዋሪዎች ሰምቷል፡፡ ታዲያ ሐገሪቱ መልካም ናትና እንዲህ ያለውን የማይገባ ስም አትለጥፉባት ነው
እንዴ ያለው? ወይስ አንዴ መልካም ናት ብያለሁ ብያለሁ ዝም ብላችሁ መልካምነቷን ተቀበሉ ነው ያለው? አንዳንዴ እኮ እየኖርንበት
ስላለው ሁኔታ ከጠፋን ራሱ የሚኖሩትን ማየት እና መጠየቅም ያስፈልገናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እየኖርን ራሱ እየኖርን ስላለበት ሁኔታ
የምናውቀው ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ የኤልሳዕን ድንቅ ተግባር ለህዝባችን ማሳየት ይጠበቅባችኋል ማለት ነው፡፡
ኤልሳዕም አገሪቱስ መልካም ነበረች ዳሩ ግን ውኃው መርዝ ነው፡፡ ወላድን ያመክናል፤ መካንንም ይገድላል
እንጅ ያሉትን ወገኖች ሰምቶ መፍትሔ ፈለገላቸው፡፡ ምክንያቱም ኤልሳዕ
ንብረቱን ትቶ ለድኃ አብልቶ መምህሩ ኤልያስን የተከተለው ራሱን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ነውና የህዝቡን ሞት አይፈልግም፡፡
ስለዚህህዝቡ በውኃው መርዝነት አንጀቱ ሲቆረጥ ሆዱ ሲበጠበጥ መመልከት አላስቻለውምና “አዲስ ሸክላ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” አለ፡፡
ከአንድ አባት የሚጠበቀው መልካም ነገር ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ የዛሬ አባቶቻችንም የሰላም ጨው፣ የፍቅር ጨው፣ የአንድነት ጨው፣ የመረዳዳት
ጨው፣ የመተባበር ጨው፣ የመተሳሰብ ጨው፣ የመቻቻል ጨው፣ የመዋደድ ጨው በአዲስ ማሰሮ ጨምራችሁ እመጡልኝ አንጀታችሁን የሚቆርጠውን
ሆዳችሁን የሚበጠብጠውን መርዝ ላስወግድላችሁ ማለት ያስፈልጋችኋል፡፡ ከዚህ በፊት ግን እንደ ኤልሳዕ ጥፋቱ ማን ላይ እንደሆነ በግልጽ
መለየት ተገቢ ነው፡፡ ውኃው ላይ ነው ወይስ ውኃውን ከሚጠጡት ሰዎች ላይ ነው ችግሩ ያለው? የሚለውን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
መንግሥት ላይ ነው ወይስ ሕዝቡ ላይ ነው ጥፋቱ? የሚለውን እንደ አባትነታቸው የማወቅና የመረዳት ግዴታ አለባቸው ምክንያቱም ያለሕዝብ
የሕዝብ አባት መሆን አይቻልምና፡፡ አባቶች ከመንግሥት ጋር ወግነው ህዝቡ ሲታሰር፣ ሲደበደብ፣ ሲገደል እየተመለከቱ ዝም ማለት ግን
የኢሳይያስን ለምጽ የሚያከናንብ ፍርሐትና አድርባይነት ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ደም ሲፈስ እየተመለከትን ለጸሎት ለሱባኤ ለምሕላ ያወጅነው
የአባትነት ዐዋጅ የት አለ? የሙስሊሙም፣ የክርስቲያኑም የሃይማኖት አባቶች ለዚህ ለፈሰሰው ደም ምንም ዓይነት ከሃይማኖቱ የሚጠበቅ
ተግባር አላሳዩም፡፡ ይልቁንም መንግሥት የተናገራቸውን ቃላት ሳንቀይር “እንደ በቀቀን” ብናስተጋባ ግን ታሪክ አንድ ቀን ይወቅሰናል፡፡
ዕድሜያችን አጭር ናት፣ ዛሬ ናት አልያም ነገ ብቻ ናት ያለችን ጊዜ በዚች ጊዜ ውስጥ ግን የሰላም ማሰሮንአምጡልኝ ማለት ይጠበቅብናል፡፡
ኤልሳዕ በአዲስ ሸክላ ጨው ጨምረው እንዲያመጡለት ጠየቀ ህዝቡም አመጡለት፡፡ ኤልሳዕ እውነተኛ አባት መሆኑን
ተረድተዋል፣ የኤልያስ ደቀመዝሙር እንደሆነ አውቀዋል፣ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆነ ተረድተዋል ስለዚህም ታዘዙት በአዲስ
ሸክላ ጨው ጨምረው አመጡለት፡፡ ከዚያም ምንጩን አሳዩኝ አላቸው ምንጩን አሳዩት፡፡በቃ ይህ ነው ዋናው መፍትሔ ምንጩን መለየት ያሻል፡፡
ዝም ብሎ ከሚፈሰው ውኃ ጋር መፍሰስ አይደለም ምንጩ ላይ መሄድ ነው እንጅ፡፡ የደም መፍሰሱ ምንጭ ምነድን ነው? የመገዳደላችን
ምንጩ ምንድን ነው? ንብረታችን የመውደሙ ምንጭ ምነድን ነው? የህዝባችን መቆጣት ምንጩ የት ነው? ማለት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ነው
ኤልሳዕ ምንጩን አሳዩኝ ማለቱ፡፡ ህዝቡም ምንጩን አሳዩት፡፡ እርሱም
እንደአባትነቱ “እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል ፈወስክዎ ለዝንቱ ማይ ከመ አልቦ ዘይመክን እምኔሁ ወዘይመውት” ብሎ ጨው ያለበትን
አዲሱን ሸክላ ከምንጩ ላይ አድርጎ ጸልዮበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ውኃው ተፈውሶ ወላድ ብትጠጣው የማያመክን መካን ብትጠጣውም የማይገድል
ሆኗል፡፡ ከሞት የከፋ ነገር የለም ኤልሳዕ ከዚህ ሞት የታደጋቸው የአባትነቱን አደራ የተወጣው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬም
አባቶቻችን ሆይ የኤልሳዕን ሥራ ትሠሩ ዘንድ እንማልዳችኋለን፡፡ አገራችን መልካም ናት፣ አገራችን የሃብታሞች ሃብታም ናት፣ አገራችን
ትልቅ አገር ናት ነገር ግን ወላድን የሚያመክን መካንን የሚገድል ውኃ አለባት፡፡ ይህንን ውኃ መፈወስ የአባቶችቻን ትልቅ ኃላፊነት
ነው፡፡
ሁሉም የሚጠቀምበትን ሰላም ፍቅር አንድነት ለህዝቦቻችን ያድልልን ዘንድ የፈጣሪያችን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment