Tuesday, August 23, 2016

“በአግባቡ ያልተጠገነ ስብራት”

ነሐሴ 17/ 2008 ዓ.ም

ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎች ለስብራት ይዳረጋሉ፡፡ በብዛት የሚስተዋለው ስብራት ግን አካላዊ ስብራት ነው፡፡ ይህ አካላዊ ስብራት በእግር፣ በእጅ፣ በአጥንት ላይ በብዛት ይስተዋላል፡፡ በብዛት የሚከሰተውም ከመውደቅ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በተለይ በክረምት ወራት ከላይ ዝናብ ሲዘንብ ምድር ውኃ መቋጠር ትጀምራለች፡፡ በዚህ ጊዜ ሙሉ በጋውን ሲዘልባት የነበረውን ሁሉ ዳዴ እያሰኘች ትነዳዋለች፡፡ አንዳንዱንም እግርህን አልቀበልም ብላ ሰማይ አድርሳ ታፈርጠዋለች፡፡ ያኔ ነው ነገር ተበላሽቶ ስብራት የሚባል ጣጣ የሚፈጠረው፡፡ ከዚያም እንደተሰበሩ አውቆ መጠገን የሚባለውን ፍልስፍና መዘመር ያስፈልጋል፡፡ ስለተሰበርን ብቻ መሰበርን እንደ ውርደት ቆጥረን ስብራታችንን አፍነን መያዝ የለብንም፡፡ ሆኖም ግን መጠገን እንደሚያስፈልገን ራሳችንን ካሳመንን በኋላ ጠጋኝ መፈለግ ግድ ይለናል፡፡ መጠገን እና መጠገን (ጠ ይጠብቃል) ጠጋኝ እና ጠጋኝ ሁሉም አንድ አይደሉም፡፡ አንዳንዱ ጊዜያዊ ጥገና ይሰጣል፣ አንዳንዱም ጥገና የሚመስል ነገር ያደርጋል፣ አንዳንዱ ደግሞ ሙሉ ጥገኛ ይሰጣል፣ አንዳንዱ ደግሞ ከጥገናም በላይ ሌሎችን አስፈላጊ ምክሮችን እና ተሞክሮዎችን ይለግሳል፡፡
ዛሬ እየጻፍኩት ያለው ወጌሻ ስለሆንኩ አይደለም ወይም ደግሞ እግሬ ወይም እጄ ተሰብሮብኝ አይደለም፡፡ አካላዊ ስብራትን ለመተርጎምም ፈልጌ አይደለም ሞራላዊ ስብራትን፣ አገራዊ ስብራትን፣ ህዝባዊ ስብራትን ለመናገር ፈልጌ ነው እንጅ፡፡ በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች ብዙ የማንነት ጥያቄዎች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ግን በወቅቱ እንደ ጥያቄ ተመልክቶ ሊያስተናግዳቸው የቻለ ሰው አልነበረም አሁንም የለም፡፡ በመሆኑም በጥያቄ ላይ ሌላ ጥያቄ ሲደረብ ለነገ እየተባለ ሲገፋ ኖረና ዛሬ ላይ ከባድ ሀገራዊ ስብራትን ፈጠረ፡፡ የህዝቡ አቤቱታ እየጨመረ መጣ፡፡ የአንዱ ስብራት ለሌላውም ስብራት እየሆነ መጣ፡፡ በእርግጥ እስካሁን ድረስም ስብራታችሁ ስብራታችን አይደለም ያሉ አሉ፡፡ ሆኖም ግን ስብራታችን አገራዊ ስብራት ነው፡፡ ይህ ስብራት ደግሞ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ለሁላችን ስብራት የሚሆንበት አንድ ቀን ይመጣል፡፡ ህዝቡ ለምን መቃወም አስፈለገው? የመቃወም አባዜ ተጠናውቶት ይሆን? አይደለም እናውቀዋለን ኢትዮጵያውያን ከመጠን በላይ ያለፈ ትእግስት ያላቸው ህዝቦች ናቸው ነንም፡፡ ከትእግስት መስመር አልፎበት የማንነት ስብራት ሲደርስበትና ስብራት ሲገጥመው ግን ወጌሻ ሆነን መጠገን ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ግብር ከፋዩ ህዝብ ነው፣ መሠረተ ልማቱ የህዝብ ነው፣ በመንግሥት የአመራር ቦታዎች ላይ ያሉትም የህዝብ ናቸው ከህዝብ ናቸው፡፡ ሁሉም አንድ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆን አይችልም እንጅ እኮ እኛም ጠቅላይ ሚኒስቴር ለመሆን የሚጎድለን ነገር የለም ነበር፡፡ ግን ስልጣኑን ለሌላ አሳልፈን ሰጥተነዋል ምክንያቱም ሊመራን ወይም ሊያስተዳድረን ይችላል ያልነው አንድ ሰው ብቻ ስለሆነ፡፡ ዛሬ የሚገድለው እና የሚገደለው ህዝብ እንደ አንድ አገር ዜጋ እኩል ድርሻ ያላቸው ናቸው ለኢትዮጵያ፡፡ የሚገድለው ለአገሬ አስብላታለሁ ከሚለው በላይ እየሞተ ያለው ዜጋ ያስብላታል፡፡ ሆኖም ግን እንደ ባቢሎናውያን ለመሰማማት እና ለመደማመጥ አልቻልንምና የህዝቡ ጥያቄ በጥይት ሲመለስ ተመለከትነው፡፡ ይህ መልስ ምናልባትም ለሕዝቡ የማንነት ስብራት ጊዜያዊ መፍትሔ ሰጥቶ ህዝቡን እንዳይቃወም ልናደርግበት እንችል ይሆናል ዘላቂ መፍትሔ ግን አይሆንም፡፡ በረሃብ ተጎድቶ ዛሬ እንዳይጮኸብን ያለውን ህጻን ተቆጥተንም ሆነ አስፈራርተን እንዳይጮኽ ልናደርገው እንችላለን፡፡ ይህ ማለት ግን ልጁ መጮኹን ያቆመው ረሀቡ ስለጠፋለት አይደለም ስለፈራ እንጅ፡፡ ምናልባትም በዚህ ከቀጠልንበት አንድ ቀን ከሞት ሰይፍ ይሻላል እንዲሉ አበው ሰይፍ ሊመዝብን ይችላል፡፡ ህጻን መሆኑን አንመልከተው እርሱ ዘንድም ብሶት ታፍኗልና፡፡
“መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው” የሚባለው በእውነት የህዝብን ደም ሲያፈስ ነው ወይስ ደግሞ ጥያቄያችሁ ተገቢ ነው ወደ ፊት እናስተካክላለን እናንተ የምትሉትን ነገር እኮ እኛም ቀድመን ተረድተነዋል በማለት በሰላም ህዝቡን የሚያነጋግር ሲሆን ነው፡፡ የኃይል ጥቃት ጊዜያዊ ጥገና ነው፡፡ ምክንያቱም የህዝቡ ስብራት በአግባቡ እስኪጠገን ድረስ ስብራቱ በየጊዜው ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ መንግሥት ጥሩ ወጌሻ መሆን ካልቻለ ከባድ ችግር ይፈጠራል፡፡ በአገራችን ላይስ ከህዝቡ በሚበልጡ ፖሊሶች እያስፈራራን እንደ ህጻን ልጅ ዝም እናስብላቸው ትናንትና ብራዚል ላይ የህዝቡን ስብራት በዓለም አደባባይ ሲያጋልጥ ምን አደረግን? ምንም ልናደርግ አንችልም የእኛን ሚዲያ ቀጥታ ስርጭት ልናቋርጠው እንችላለን የአትሌቱ ተቃውሞ ግን አልተቋረጠም ነበር፡፡ ሌሎች ታላለቅ ሚዲያዎች ቀጥታ ሽፋን ሰጥተውት ነበር እኮ፡፡ ታዲያ የህዝባችንን ጩኸት በእንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች የሚገልጹ ዜጎች ካሉ የሀገራችንን ህዝብ ብናስፈራራው ምን ዋጋ አለው? እኛ እኮ ዝም  ካልን ቆየን በጣም ብዙ ጊዜ አለፈን፡፡ ህገ መንግሥቱ የመናገር መብት ስለሰጠ እንናገራለን ነገር ግን የማሰር ስልጣንን ስለሰጠ ደግሞ እንታሰራለን፡፡ እንደዚህ እየሆነ እስከመቼ? እዚህ ያለውን አስፈራርተን ዝም ብናስብለውም ስብራቱን ማከም የሚችልበትን አጋጣሚ ባገኘ ቁጥር ባለም አደባባይ ቅሬታውን ይገልጻል፡፡
ስለዚህ የጋራ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልገናል፡፡ ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም ጥያቄውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ የህዝቡ ደም እንዳይፈስ መንግሥት ያሰማራቸውን ደም አፍሳሾች መሰብሰብ አለበት፡፡ በእውነት መንግሥት ላይ አንዳችም ጥፋት ባይኖርበት ኖሮ መቶ ፐርሰንት መረጠን ያልነው ህዝብ በየወረዳው እና በየቀበሌው ለምን ይቃወመናል? አንዳንዴ እኮ ራስንም ዞር ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዝንጀሮ በሌላው መላጣ የምትስቀው እኮ የራሷን መላጣ ዞራ ስለማታየው ብቻ ነው፡፡ የራሷን መላጣ ብታይ ግን በሌላው መላጣ የምትስቅበት አፍ እና አንደበት አይኖራትም ነበር፡፡ ስለዚህ የስብራቱ ጥገና ፍቱን መሆን አለበት፡፡ ጀምሮ ነካክቶ ስብራቱን አባብሶ ዞር ማለት ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ እስከዛሬ ድረስ እኮ ተመልክታችሁታል፡፡ ምን ላይ ችግር እንዳለ፣ ምን ላይ ህዝቡ ቅር እንደተሰኘ መመርመር አለባችሁ፡፡ ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ሲቀረጹ ከመቀረጻቸው በፊት ህዝቡን ማወያየት ያስፈልጋል፡፡ ፕሮጀክቱ ብዙ ገንዘብ ከፈሰሰበት በኋላ ወደ ህዝቡ መጥቶ ህዝቡ ድንበራችንን ይጋፋል፣ ታሪካችንን ያደበዝዛል፣ ማንነታችንን ያሳጣል ወዘተ ብሎ ቅሬታ ሲያቀርብ ወደ ድብድብ እና ግድያ ከማምራቱ በፊት እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አልታደል ብለን ነው እንጅ ቅሬታ ያቀረበ ሰው በእውነት ይደበደብ ነበር? ይታሠር ይገደል  ነበር? ለወደፊት እቅዳችን እኮ ግብአት ነው፡፡ የሕዝቡ ቅሬታ ለሚያስተውል መሪ በጣም ሲበዛ ጠቃሚ ነው፡፡ መልካም እየሰራን እንደሆነ የሚነግረን ሰው ምንም አይጠቅመንም ምክንያቱም እየሠራነው ያለው ነገር ስለሆነ፡፡ ጉድለታችንን የሚመለከት ዓይን ግን ተገቢ ነው እኛ መስሎን ከሠራነው በተጨማሪ ሌላ መንገድ ያሳየናልና፡፡
እኔ ይህንን ስጽፍ የሚሰማኝ ሰው ላይኖር ይችላል ምክንያቱም በማንም ዘንድ ቦታ ስለሌለኝ፡፡ ግን አንድ ቀን ታሪክ ሆኖ እንደማገኘው አልጠራጠርም፡፡ ይህ ትንቢት አይደለም አሁን እያየነው ያለ ነገር ነው፡፡ ስብራቱን በደንብ አላከሙትም፡፡ ህዝቡ ተሰብሮ እንደወጣ ሌላ ስብራት ተጨምሮበት እየገባ ነው ያለው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች መልካቸውን እየቀያየሩ ተቃውሞዎች እየመጡ ናቸው፡፡ እስካሁን ግን ህዝቡን ሰብስቦ ምንድን በደልናችሁ? ያለ አካል የለም፡፡ በደሉን አጠገቡ ሆነን ካልሰማነው ምን የኅሊና እርካታ ሊሰጠን ይችላል፡፡ እየጠገንነው ያለው ስብራት ነገም መሰበሩ አይቀርም ምክንያቱም በአግባቡ አልጠገንነውምና፡፡ ወይም ከስብራቱ ውጭ ያለውን አካሉን ነውና የጠገንለት፡፡ ስለዚህ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ እኛ ማድረግ የምንችለውን ነገር እናድርግ፡፡ ህዝቡን ከሞት አገሩን ከመቅሰፍት እንዲጠብቅልን ወደ አምላካችን መጮኽ ብቸኛው አማራጫችን ነው ለእኛ ለሚገደልብን እና ወደፊትም ለምንገደል ሰዎች፡፡ በዚህ ጩኸት በየቤተ እምነታችን በርትተን አምላክን እንለምን እርሱ ምሕረት በእጁ አለችው፡፡ እርሱ ነገርን ይቀይራል አትጠራጠሩ ሁሉም ከስብራቱ ይጠገናል!!!!

አበዛሁ ይብቃኝ!

No comments:

Post a Comment