© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 20/ 2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በጉልበቱ እና
በኃይሉ የሚመካ ፍልስጥኤማዊ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም ያልተገዘረ ሲሆን በእግዚአብሔር ህዝብ በእስራኤላውያን ላይ እጁን ጫነባቸው፡፡
እነርሱንም ለመግደል ይዝት እና ያስፈራራ ነበር፡፡ ንጉሡ ሣዖልም እነዚህን ፍልስጥኤማውያንን ድል ለሚያደርግለት ሽልማትን አዘጋጀ፡፡
ነገር ግን ይህን ግዙፉን በጉልበቱ እና በኃይሉ እንዲሁም በታጠቀው መሣሪያ የሚመካውን ጎልያድ ማንም እስራኤላዊ ሊያሸንፈው አልቻለም
ነበር፡፡ ጎልያድ ላይ ዛቻ አለ፣ ጎልያድ ላይ ሰይፍ አለ፣ ጎልያድ
ላይ ኃይል አለ፣ ጎልያድ ላይ ጉልበት አለ፣ ጎልያድ ላይ ማስፈራራት አለ፣ ጎልያድ ላይ የጦር መሣሪያ አለ፡፡ ለዚህም ነው ፍልስጥኤማውያን
በዚህ ሰው ተመክተው በእስራኤላውያን ላይ የተገዳደሩ፡፡
አምላክ ይሁን
ካላለ በቀር አንዲት ነገር አትደረግም፡፡ ጎልያድ የእግዚአብሔር ሰው አይደለም፡፡ የህዝበ እስራኤላውያንን ደም ለማፍሰስ የሚፈጥን
እጅ የያዘ ግፈኛ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የህዝቡን ደም ከእጁ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ የጎልያድ ዛቻ፣ የጦር መሣሪያ፣ ማስፈራራት፣
ኃይልና ጉልበት ሁሉ በእስራኤላውያን ዘንድ ቦታ የለውም፡፡ ምክንያቱም እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸውና፡፡ እነርሱ ዘንድ
እምነት አለ፣ እነርሱ ዘንድ እግዚአብሔር አለ፣ እነርሱ ዘንድ ድል መንሳት አለ፣ እነርሱ ዘንድ ማሸነፍ አለ፣ እነርሱ ዘንድ ሞገስ
አለ፡፡ ለጊዜው ጎልያዳውያኑ ደም ሊያፈሱ ይችላሉ፣ ለጊዜው ፍልስጥኤማውያኑ ሊገድሉ ይችላሉ፣ ለጊዜው ጎልያዳውያኑ ያሸነፉ ይመስላቸዋል፣
ለጊዜው ፍልስጤማውያኑ ኃይላቸው ከእነርሱ ጋር ይቆይ ይመስላቸዋል፣ግን አምላክ ከማን ጋር እንዳለ አያውቁም፡፡
ጎልያዳውያኑ!
ዛሬ ግደሉን እንሞታለን፣ ዛሬ ደማችንን አፍስሱት፣ ዛሬ አስፈራሩን ዝም እንላለን፣ ዛሬ ተዋጉን ድል እንደረጋለን፣ ዛሬ ሥጋችንን
አቃጥሉት እንቃጠላለን፣ ዛሬ በሰይፍ ቁረጡን አንገታችንን እናመቻቻለን፣ ዛሬ በጥይት ደብድቡን ደረታችንን እንሰጣለን፣ ዛሬ እሰሩን
እጅ እንሰጣለን፣ ዛሬ አሸማቁን እንሸማቀቃለን፣ ዛሬ በኃይላችሁ ተመኩ፣ ዛሬ በጉልበታችሁ ተመኩ፣ ዛሬ በመሣሪያችሁ ተመኩ፣ ዛሬ
በሚሆነው ሁሉ ነገር ስልጣን ይኑራችሁ፡፡ ግን አይቀጥልም፡፡ ምክንያቱም ጎልያዳዊነት የሚዝተው፣ ጎልያዳዊነት የሚያሸንፈው፣ ጎልያዳዊነት
የሚገዳደረው የዳዊት ጠጠር እስኪለቀም ድረስ ብቻ ነው፡፡ ዳዊት ጠጠሩን ይሰበስባል፡፡ ከሁሉ የሚያንሰው ዳዊት ከሁሉ የሚበልጠውን
ጎልያድ አሸንፈዋለሁ ብሎ ሊገጥመው ነው፡፡ ጎልያድ መገዳደር፣ መዛት፣ በጉልበቱ መመካት ልማዱ ነውና ወንጭፉን ይዞ ጠጠሩን ለቅሞ የተጠጋውን ዳዊትን ውሻ የምትገድል መሰለህን ወንጭፍ
ይዘህ የመጣህ አለው፡፡ ዳዊት ከጠጠሩ ጋር አብሮት ያለውን አምላክ ያውቃል፡፡ ለጎልያድ መለሰለት ውሻስ ጌታውን ያውቃል አንተ ግን
ጌታህን የማታውቅ አህዛብ ነህ አለው፡፡ ዳዊት ዘንድ ፍርሐት የለም፡፡ ከጎልያዳዊ ሰይፍ ይልቅ ዳዊታዊ ጠጠር እንዲልቅ በውስጡ ያውቃልና፡፡
ዳዊት ጠጠሩን
ከወንጭፉ ላይ አኖረ፡፡ ጎልያድ በዳዊት ድርጊት ሳቀ፣ ተደነቀ፣ ከእጀ የሚያስጥልህንም አየዋለሁ ብሎ ዛተ በራሱም ተመካ፡፡ ጎልያድ
እስከዛሬ ድረስ ደም ያፈሰሰ፣ ደሀ የበደለ፣ ፍርድ ያጓደለ፣ በባርነት አገዛዝ ቀንበር ስር ህዝቡን ያስጨነቀ ዳዊት ስላልተነሣ ብቻ
ነው፡፡ ዳዊት ሲነሣ ግን ጎልያድ ጎልያድነቱ ያከትምለታል፡፡ ዳዊት ጠጠሩን በወንጭፉ ላይ አስቀመጠና ወደ ጎልያድ ወረወረው፡፡ ጎልያድን
ለተመለከተው ሰው እንኳን በጠጠር በጦርም የሚሸነፍ ሰው አይደለም፡፡ ጎልያድ በዚያ ዘመን በነበረ ማንኛውም መሣሪያ የሚሞት ሰው
አይመስልም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ትልቅነቱን እንድንረሳ በትንሽ ጠጠር ወደቀ፡፡ ዳዊት ጎልያድን በጠጠር ግንባሩ ላይ መትቶ ጣለው፡፡
ፍልስጥኤማውያን ወደቁ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጭነው ዝም አሉ፡፡ እስራኤላውያንም የድል ዝማሬን ዘመሩ፡፡ ዳዊት በጠጠር ከጣለው
ጎልያድ ላይ ሰይፉን መዘዘና ቸብቸቦውን ቆረጠው፡፡ ከእስራኤላውያን ዘንድም ስድብን አራቀ፡፡ ዳዊታዊ ጠጠር እንዲህ ያለ ኃይል አለው፡፡
ዛሬ በሐገራችን
ጎልያዳዊ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሰዎች በዝተዋል፡፡ በመሣሪያቸው ተመክተው ያስፈራራሉ፣ ያስራሉ፣ ያንገላታሉ፣ ይገድላሉ፡፡ ምድርን
በህዝቦቿ ደም አረከሷት፡፡ የህዝቡን ጩኸት በመሣሪያ በዛቻና በማስፈራራት ለማፈን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን
ላይም ይህን ማስፈራሪያ አብዝተው ያስተጋባሉ፡፡ ግን ዕለት ዕለት ቁጣው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዳዊታዊ ቁጣ መጥፎ ነው፣ ዳዊታዊ አስተሳሰብ
ከባድ ነው፣ ዳዊታዊ ጠጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ስናርደው ዝም ያለን ዳዊታዊ ጠጠርን እየፈለገ ስለነበረ ነው፡፡
እባካችሁ እርስ
በርሳችን እንሰማማ፡፡ እኛው ገዳዮች እኛው ተገዳዮች፣ እኛው አስጨናቂዎች እኛው ተጨናቂዎች፣ እኛው አሳዳጆች እኛው ተሳዳጆች፣ እኛው
አቃጣዮች እኛው ተቃጣዮች ሆነን እስከመቼ እንቀጥላለን፡፡ ጎልያዊ ዛቻ፣ ጎልያዳዊ ማስፈራሪያ የዳዊትን ቁጣ ያስነሣል፡፡ ከሁሉ ታናሽ
የሆነውን ብላቴና ያስቆጣል፡፡ ዳዊት እኮ ከእርሱ የሚበልጥ ስንት ሚሊዮን ህዝብ እያለ ነው ገና በ12 ዓመቱ ጎልያዳዊ ዛቻ የቀሰቀሰው፡፡
ስለዚህ ሌሎችን ብላቴኖችን የሚቀሰቅስ ጎልያዳዊ ማስፈራሪያችንን እና ትምክህታችንን እናስወግድና እንነጋገር፡፡ ትናንት የገነባናቸውን
ዛሬ ካፈረስናቸው፣ ትናንት አደግን ተመነደግን ያልንባቸውን ዛሬ ከናድናቸው ብልጽግናችን ከቶ ወዴት አለ፡፡ እየሞተ ያለው የእኛው
ወገን ነው እየገደለ ያለም የእኛው ወገን ነው፡፡ አልሸባብ አልመጣብን፣ አይሲስ አልደረሰብን፣ ቦኮ ሐራም አልተቃወመን ታዲያ ማንን
ማን ይገድላል? የእግዚአብሔርን ህንጻ እያፈረስን እንደሆነ አይገባንም እንዴ? እኛ በምናፈርሰው የእግዚአብሔር ህንጻ እግዚአብሔር
ተቆጥቶ ራሱ በራሱ ሥልጣን እኛን እንዲያፈርሰን እወቁ፡፡ አትጠራጠሩ ዳዊትን አስነስቶ ቸብቸቧችንን ያስቆርጠናል፡፡ እኛ ለገነባነው
እና እኛ ለሠራነው ህንጻ መፍረስ ተጨንቀን አይደል እንዴ መሠረተ ልማቶች ፈረሱ በሚል ሰበብ ሰሪዎቹን እየገደልናቸው ያለን፡፡ ታዲያ
እግዚአብሔርስ ገንባን ሳንለው የገነባንን የራሱ ንብረቶች የሆንነውን ህንጻዎች ስታፈርሱን ዝም ይል ይመስላችኋል፡፡ በፍጹም ዝም
አይልም፡፡ ቃየን ይቅበዘበዛል ያገኘው ሁሉ ይገድለዋል፡፡ ጎልያድ ይዝታል ዳዊታዊ ጠጠር ግን ኃይልን ታደርጋለች፡፡
“ንኡስ አነ እምአኃውየ፣
እኔ ከወንድሞቼ ታናሽ ነኝ” ያለው ዳዊት “ወአሰሰልኩ ጽእለተ እምደቂቀ እስራኤል፤ ከእስራኤላውያን ልጆች ዘንድ ስድብን አጠፋሁ”
በማለት የደስታ ዝማሬን ዘመረ፡፡ ዳዊት ሲዘምር ጎልያድ ወዴት ነበር? በጠጠር ወድቆ ሞቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ከጎልያድ ሰይፍ የሚልቅ
የዳዊት ጠጠር በህዝቡ ዘንድ እንዳለ አውቀን ህዝባችንን ለሚበልጥ ቁጣ ባናነሣሣው የሚል ምክር ለሚሰማኝ ሁሉ እመክራለሁ፡፡ አልሰማም
ለሚል ግን ዳዊታዊ ጠጠር ተነሥቶ ጎልያዳዊ አስተሳሰብ ወድቆ “ወአሰሰልኩ ጽእለተ እምደቂቀ ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያውያን ልጆች ዘንድ
ስድብን አጠፋሁ” የሚለውን የድል ዝማሬ ሊዘምሩበት ጊዜው ቅርብ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደ ኋላ ዞራችሁ ያለፈውን መንግሥት ታሪክ
መርምሩ፡፡ “ምክር ሰናዪት ለኩሉ ዘይገብራ፣ ለሚያደርጋት ለሚፈጽማት ሁሉ ምክር መልካም ናት”
አበቃሁ
No comments:
Post a Comment