Tuesday, March 15, 2016

ለምን በምንፍቅና ውስጥ ተደበቁ?



© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 6/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እምነት ውስጥ ማመን እና መታመን የሚሉ ዐበይት ነገሮች አሉበት፡፡ ማመን ማለት ያላየነውን ያልጨበጥነውን ያልዳሰስነውን ነገር እንዳየነው እንደጨበጥነው እንደዳሰስነው አድርገን መቀበል ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር አምላክ ነው ስንል ሳናየው፣ ሳንጨብጠው ሳንዳስሰው እንዳየነው እንደጨበጥነው እንደዳሰስነው አድርገን ተቀብለን ነው፡፡ ሌሎችንም እንዲሁ ሳናይ ሳንዳስስ ሳንጨብጥ ነው አሉ ብለን የተቀበልናቸው፡፡ ገነት መንግሥተ ሰማያት ሲዖል ገሐነመ እሳት መላእክት አሉ ስንል በተመሳሳይ ሳናይ ሳንዳስስ ሳንጨብጥ ነው፡፡ መታመን ስንል ደግሞ ለማመናችን ተግባራዊ ምላሽ የምንሰጥበት ነው፡፡ እግዚአብሔር አለ ስንል ህልውናውን የምናምንበት ትእዛዙን በመጠበቅ ነው፡፡ አድርጉ ያለንን በማድረግ አታድርጉ ያለንንም ባለማድረግ ተግባራዊ ምላሽ ከሰጠን እሱ መታመናችንን ገልጸናል ማለት ነው፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት እነዚህ ሁሉ የመታመን ተግባራት ናቸው፡፡ ምግባራችን ወይም መታመናችን ግን ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ የበረታ አለ የደከመም አለ፡፡ ድካምህ ግን ከደካማነትህ ባለፈ ወደ እምነት ሕጸጽ ሊወስድህ አይገባህም፡፡ ብዙዎች ወደ ምንፍቅና የሚሄዱበት ነገር ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በመሆኑም ብዙዎች ለምን በምንፍቅና ውስጥ ተደበቁ? የሚለውን ትልቅ ጥያቄ መመለስ ተገቢ በመሆኑ ወደእሱ እናምራ መልካም ንባብ!
ብዙዎች ለምን በምንፍቅና ውስጥ ተደበቁ? ለሚለው ዐቢይ ጥያቄ በርካታ መልሶችን መስጠት እንችላለን፡፡ ዋናዋና የሚባሉት ግን የሚከተሉት ናቸው፡-
1.  መታመን አለመቻል
2.  ገንዘብን መውደድ
3.  ዓለምን መናፈቅ
4.  አቋራጭ ጽድቅን መሻት ናቸው፡፡ እነዚህን አራት ነጥቦች በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡
v  መታመን አለመቻል፡- በእምነታችን ውስጥ መታመን መንፈሳዊ ግዴታችን ነው፡፡ በተዋሕዶ እምነት ውስጥ አባል የሆነ ሰው ሁሉም ሰው ሊጾማቸው የሚገባቸውን ጾሞች እስከታዘዘው ሰዓት ድረስ መጾም የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ለምሳሌ አርብና ረቡዕን እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጹሙ ይላል፡፡ ዐቢይ ጾምን ደግሞ የመጀመሪያውን ሳምንት እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ከሕማማት አስቀድሞ ያለውን እስከ አሥራ አንድ ሰዓት የሕማማትን ሳምንት ደግሞ እስከ አንድ ሰዓት እንድንጾም ታዝዘናል ይህን መፈጸም የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ ስግደትም ምጽዋትም ጸሎትም ይጨመርበታል፡፡ ጠዋት ተነሥቶ መብላት ሆዱ አምላኩ የሆነበት ሰው ግን ይህን ማድረግ ይከብደዋል፡፡ ነገር ግን ካልቻልን ማለትም የታወቀ ደዌ ካለብን አምላክ አያስገድደንም፡፡ እኛ የምንጾመው እኮ በዚያች ጾማችን ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን ብለን አይደለም መታመናችንን ለማሳየት መገዛታችንን ለማረጋገጥ ነው እንጅ፡፡  ስለዚህ የቻልነውን ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል ብዙዎች ግን ጾም ጸሎት ስግደት ምጽዋት ወደሚቀልበት እንዲያውም ጭራሽ ስሙም ወደማይነሣበት ምንፍቅና ራሳቸውን ይወስዳሉ፡፡ መጾም አለመቻል፣ መስገድ አለመቻል፣ መጸለይ አለመቻል በአጠቃላይ መታመን አለመቻል እምነትህን እንድትለውጥ ሊያደርግህ አይገባም፡፡ ራስህን ከኅሊና ወቀሳ ነጻ ለማድረግ ብለህ እምነትህን ለመለወጥ አትሻ፡፡ ከዚያስ የቻልከውን ያህል እየሠራህ “አንተ ተአምር ድካሞ ለሰብእ” የሰውን ድካም አንተ ታውቃለህ እያልህ ብትጸልይ ይሻልሃል፡፡ አምላከ ቅዱሳን የእኛን ድካም ያውቃል የእኛን ድካም ይረዳል ስለሆነም እርሱን አላመልክህም ብሎ ከመኮብለል ይልቅ ድካሜን አይተህ ማረኝ ይቅር በለኝ ብንለው የተሻለ ነው፡፡ በብዛት ለሰዎች የምንፍቅና መሠረታቸው ጾም ነው፡፡ ታዲያ ጾሞ ጹሙ ያለንን አምላክ በመጾም ካልመሰልነው መታመናችን እርሱን ማምለካችን እርሱን መውደዳችን በምን ይታወቃል? በሕክምና ጊዜ ለሥጋዊ ፈውስ ብለን ይህን ይህን አትብሉ ተብለን ስንከለከል እናደርገው የለም እንዴ? ታዲያ ለዘላለማዊ የነፍስ ድኅነት ጹሙ ስንባል ለምን እንሰቀቃለን? እውነት ነው የምላችሁ አንድ ቀን ሞክሩት አይደለም እስከዘጠኝ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ እንኳ እንድትቆዩ አምላክ ብርታቱን ይሰጣችኋል፡፡  አምላክን አበርታኝ እንበለው እርሱ ያበረታናል፡፡ ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ምንም ይፈጠር ምን መጾም ባለመቻላችን፣ መስገድ መጸለይ ባለመቻላችን እምነታችንን ልንለውጥ አይገባንም፡፡ ከዚያስ እምነታችንን ይዘን አለመጾም አለመጸለይ አለመስገድ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ቀን አምላክ ብርታቱን ጽናቱን ሰጥቶ ለንሥሐ ያበቃናልና ፡፡
v  ገንዘብን መውደድ፡- ከሦስቱ አርስተ ኃጣውእ መካከል አንዱ ፍቅረ ንዋይ ገንዘብን መውደድ ነው፡፡ ጌታ በወንጌል እንዳስተማረን ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻላችሁም ያለን ገንዘብን ነው፡፡ እንግዲህ ገንዘብ እንደ አንድ ጌታ ነው የተቆጠረው፡፡ ከውጭ እርዳታ እየለቃቀመ ገንዘብ በሚያከፋፍለው እምነት ውስጥ ብዙዎች ራሳቸውን ደብቀዋል፡፡ “”ገንዘቡን ላግኝ እንጅ እኔ ምን ቸገረኝ” በሚል የከሰረ አስተሳሰብ ብዙዎች ለገንዘብ ሲሉ ዕንቁ የሆነች ተዋሕዶ እምነታቸውን ትተው ኮብልለዋል፡፡ ገንዘብ ያው ገንዘብ ነው ስታገኝም ስታጣም እኩል የሚያስጨንቅ ነው፡፡ ሠርተህ መለወጥ ሠርተህ ማግኘት አልቻል ሲልህ እምነትህን ሸጠህ ገንዘብ ልታጠራቅም አይገባህም፡፡ ከገንዘብ በፊት የሚቀድመው እምነት ነው፡፡ ለድቃቂ ሳንቲም፣ ለእራፊ ጨርቅ ብለህ እምነትህን የምትለውጥ ከሆነ በዓለም ካሉ ከንቱዎች መካከል አንዱ አንተ ነህ፡፡
v  ዓለምን መናፈቅ፡- በተዋሕዶ እምነት ስትኖር ሁሉ ነገርህ ሰማያዊ ነው፡፡ አስተሳሰብህ ሰማያዊ፣ አነጋገርህ ሰማያዊ፣ አለባበስህ ሰማያዊ፣ አኗኗርህ ሰማያዊ፣ ዜማህ ሰማያዊ፣ ጸሎትህ ሰማያዊ ነው፡፡ ብዙዎች ግን ዳንኪራ ይናፍቃቸዋል፣ መዝፈን መጨፈር መብላት መጠጣት መስከር መወላገድን፣ ዝሙት መዳራትን ይሻሉ፡፡ ስለዚህ ይህን በነጻነት ወደምታገኝባቸው እምነትን ሽፋን ወዳደረጉ ተቋማት ለመጓዝ አትቸኩል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጉዳታቸው እንጅ ጥቅማቸው አይመዝንም፡፡ መናፍቃኑ አዳራሽ ላይ ሴቶች ዕርቃናቸውን ስታይ ልብህ ሊደሰት ይችላል፣ አጠገብህ ቁጭ ብላ ደረቷን ገልጣ ጡቶቿን አፍጥጣ ስታሳይህ ልትማረክ ትችል ይሆናል፡፡ ይህን ለመመልከት በዚህ ለመደሰት በዚህ ለመርካት ምንፍቅናን መምረጡ ጅልነት ካልሆነ በቀር ምን ሊባል ይችላል? ይህ እኮ ዓለም ውስጥም አስፓልት ላይ ወጥተህ ስትንቀሳቀስ የምትመለከተው ከንቱነት ነው፡፡ እምነት ማለት እኮ ዘላለማዊ ነው ዓለም ደግሞ ታልፋለች ትጠፋለች ትለወጣለች፡፡ ስለዚህ ሽህ ጊዜ ዓለማዊ ሁን እንጅ እምነትህን ለውጠህ በመናፍቃን አዳራሽ ያለውን ርኩሰት አትሻ፡፡ እነርሱ አዳራሽ ውስጥ እንደገባህ አንድ ፍጹም ዓለማዊ የሆነች ሴት ትመደብልሃለች ወንጌልን የምታስተምርህም ከአንተ ጭን ላይ ቁጭ ብላ ነው፡፡ በፍቅር ልብህን በመስረቅና በማማለል እዛው ስለእሷ ፍቅር ስትል እንድትኖር ይፈልጋሉና የምትመደብልህ ሴት እንዲህ ያለች ናት፡፡ ታዲያ ይኼ ሰማያዊ ነውን? አይደለም፡፡ ስለዚህ ራስህን ከዚህ ዓለማዊ ርኩሰት ልትጠብቅ ያስፈልጋል፡፡ መዝሙር የሚሉትን ዳንኪራ እና ጭፈራ አትናፍቅ፡፡

v  አቋራጭ ጽድቅን መሻት፡- መናፍቃን በተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች ላይ ተመሥርተው በአቋራጭ መጽደቅን ይሻሉ፡፡ “ኢየሱስ ያድናል፣ ኢየሱስ ጌታ ነው፣ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” በማለት ገነት እንገባለን ብለው ያስባሉ፡፡ ተዋሕዶን ሲተቹ ምን ይላሉ መሰላችሁ “አንድ መሪጌታ ነበር… አንድ ቄስ ነበር…. አንድ ዲያቆን ነበር…. አንድ መነኩሴ ነበር…. ነገር ግን ስለመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስጠይቀው ምእራፍና ቁጥር ማዎቅ አልቻለም፡፡ እኛ ግን ምእራፍና ቁጥር እንነግራቸዋለን እነርሱ አያነቡም እኛ ግን ጌታ ይባረክ ምሥጢሩን ገልጾልን ጸጋውን አብዝቶልን ሁሉን እናውቀዋለን” ይላሉ፡፡ በእውነት ማነው ጸጋ የለሹ? አለማዎቅ ጥፋት አይደለም አለማዎቅን አለማዎቅ ግን በጣም ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ መናፍቃኑ ትልቁ ችግራቸው አለማወቃቸውን አለማወቃቸው ነው፡፡ ለመዳን አቋራጭ መንገድ የተጠቀመ ማነው? መናፍቃኑ አይደሉም እንዴ? በእውነት የእነርሱን ያህል ጥቅስ መጥቀስ ያቃተው የትኛው መሪጌታ፣ የትኛው ቄስ፣ የትኛው ዲያቆን፣ የትኛው መነኩሴ ነው? እንዴ 81 መጽሐፍ ቅዱስ በዝቶባቸው ከ66 ውጭ ፍንክች አንልም ያሉ እነማን ናቸው? አዋልድ መጻሕፍትን ገድላትን ድርሳናትን ተአምራት አንቀበለም ያሉት እነማን ናቸው? እነዚህ መጻሕፍትን ለመሸምደድ ስላልቻሉ ይሆንን? የእኛ ሊቃውንትማ አንድ ጥቅስ ሮሜ 8÷34 ን ብቻ እንደ ቴፕ የሚያጠነጥኑ አይደሉም እኮ፡፡ ከመናፍቃኑ 66 መጽሐፍ ቅዱስ ባለፈ 81 መጽሐፍ ቅዱስን ምንባቡን ከነትርጓሜው፤ ቅዳሴውን፣ ድጓውን፣ ጾመ ድጓውን፣ ሰዓታቱን ዜማውን ከነምልክቱ፣ ድርሳናትን እና ገድላትን ተአምራትን ሁሉ በቃላቸው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ወዴት ጠጋ ጠጋ ነው፡፡ አቋራጭ ጽድቅን የሚሻ መናፍቅ በ66 መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ ይከራከራል፡፡ መላእክትን አንቀበልም፣ ድንግል ማርያምን አንቀበልም የሚሉ እነማን ናቸው? በአቋራጭ መዳን የሚፈልጉት አይደሉምን? ቅዱሳንን ስናከብር የማይወዱት እነርሱም ማክበር የማይሹት እኮ የእነርሱን ክብር የተሻሙባቸው ስለሚመስላቸው ነው፡፡ በጣም ክብር ፈላጊዎች ናቸው እነርሱ በጸሎታቸው እንፈውሳለን እናድናለን ይላሉ ቅዱሳኑ ግን ይህን ማድረግ አይችሉም በእነርሱ ቤት፡፡ ያሳዝናል ምን ጅልነት እና አለማስተዋል ነው? አብዛኞቹ አቋራጭ ድኅነት ፈላጊዎች ናቸው፡፡ ልጄ ካንሰር ታምማ ነበር፣ እናቴ የወገብ አጥንት መንሸራተት ነበረባት፣ አባቴ መራመድ አይችልም ነበር ወዘተ ብቻ የሌለ ልቦለዳዊ ገጸባሕርይ ይፈጥራሉ ከዚያሳ ከዚያማ ጸበል ብንወስዳቸው መዳን አልቻሉም ፣ ብናቆርባቸውም፣ መፈወስ አልቻሉም፣ እምነት ብንቀባቸውም አልተሻላቸውም ከዚያም ወደዚህ አመጣናቸውና ፓስተሩ ጸሎት ሲያደርጉላቸው ሙሉ በሙሉ ዳኑ የሚል የፈጠራ ምሥክርነት ይሰጣሉ፡፡ በጣም የሚያስቀኝ የሁልጊዜ ተረታቸው ቢኖር ይህ ብቻ ነው፡፡ ጸበል፣ እምነት፣ ቁርባን ያላዳነውን በሽታ ፓስተሩ ጸልዮ አዳነው አቤት ቀልድ፡፡ እሽ ይዳን መቼም የአምላክ ድንቅ ሥራ ብዙ ነው ጠንቅዋይስ ያድናል እያሉ የሚሰግዱ አሉ አይደል፡፡ እንደጠንቅዋዩ ሁሉ ፓስተሩም ያድናል ይፈውሳል እንበል የሚድነው ግን ከነፍስ በሽታ ነውን? አይደለም፡፡ ሁሉንም ስትሰሟቸው የሚመሰክሩት ሁሉ የሥጋ ደዌ ነው፡፡ ጸበል አያድንምን? ያድናል፤ ቁርባን አያድንምን? ያድናል፤እምነት አያድንምን? ያድናል፡፡ ግን ትእግሥትና ጊዜ እምነትና ጽናት ይጠይቃል፡፡ ግን እኮ ደግሞ የግድ ሁሉም በሽታ መዳን የለበትም፡፡ ምክንያቱም እነ ጳውሎስና ጴጥሮስ በጥላቸው ድውይ እየፈወሱ እነርሱ ግን በሽታ ነበረባቸው፡፡ መድኃኒቶች ራሳቸው በሽታ ነበረባቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትእግሥት ስናጣ አቋራጭ ድኅነትን አቋራጭ ጽድቅን መፈለግ አያስፈልገንም ኢዮብን አትዘንጉ እንጅ ወገኖቼ፡፡ የሰጠኸኝን ውሰድ እንበለው እኛ ምን አገባን አምላክ የፈቀደውን ቢያደርግ፡፡ አብዛኛው የመናፍቃኑ አባላት ሲጠየቁ የሚመልሱት ይህንን ነው እንዲህ ተደርጎልኝ እንዲህ ተፈውሶልኝ ወዘተ የሚል የማይረባ ትርኪ ምርኪ፡፡ ቅዱሳኑንም አማላጅ አንላቸውም የሚሉት ለዚሁ ነው፡፡ እኛው ራሳችን በአቋራጭ ፈጣሪችንን ማናገር ስለምንችል ማንንም አማልዱን አንልም ይላሉ፡፡ በቃ በአቋራጭ ራሳቸውን ጻድቅ አድርገውታል፡፡ መድረክ ላይ ወጥቶ መንፈራፈር፣ መንፈስ ነው እያሉ መውደቅ ጽድቅ ነው ብለው ጽፈውታል፡፡ መውደቅ ጽድቅ ከሆነ ታዲያ ማን ሞኝ አለ በጾም በጸሎት በስግደት በምጽዋት የሚንገላታ? እነዚህ የተቀደሱ ተግባራት መንገላታት ናቸው ብለው ካመኑ ማለት ነው፡፡ እናንተ ግን ወገኖቼ አደራ አደራ አደራ አቋራጭ መንገድን አቋራጭ ጽድቅን ምርጫችሁ አታድርጉ ምክንያቱም ያ መንገድ የጥፋት ነውና!!! 

Monday, March 14, 2016

ዐቢይ ጾም (ክፍል 3)


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 5/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል ሁለት ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ፵ ቀንና ፵ ሌሊት እንደጾመ፣ የፈጸማቸውን አምስት ግብራት እንዲሁም አምስቱን የተገኘባቸውን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ የተፈተነባቸውን ሦስቱን አርእሥተ ኃጣውእ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡ መልካም ንባብ!
ማቴ 4÷3 “ወቀርበ ዘያሜክሮ” የሚፈታተነው ዲያብሎስ ቀረበ፡፡ ዲያብሎስ የቀረበው እንዲሁ አይደለም “ርኅብኩ” ሲል ሰምቶት፣ ፍሬ ዕጽን ሲሻ አይቶት፣ መልኩን አጠውልጎ ታይቶት ነው እንጅ ዲያብሎስም እንዲያው አይቀርበውም በአምሳለ ሰዓሊ በአምሳለ ሐራሲ በቀዳዳ ሽልቻ ትኩስ ዳቦ የያዘ መስሎ ሁለት ደንጊያ ይዞ ይቀርበዋል፡፡ አመጣጡ አንዱን ላንተ አንዱን ለኔ ዳቦ አድርገህ እንብላ ሊለው ደንጊያውን ዳቦ ከማድረግማ የያዝከውን አንበላም ቢለኝ አዳም አባቱን በመብል ምክንያት ድል እንደነሣሁት እሱንም በመብል ምክንያት ድል እነሣዋለሁ ብሎ ነው፡፡ ከዚያም ያሰበውን ተናገረ፡፡ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ አብ በሰማይ የምወደው ልጄ ብሎ ሲመሰክርለት ሰምቶ ነበርና “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እኒህ ደንጊያዎች ኅብስት ይሁኑ ብለህ እዘዝ” አለው፡፡ ለዓላማ ነው ይህን መጠየቁ ቢያደርገው የኔ ታዛዥ ነው ለማለት ባያደርገውም ደካማ ነው ለማለት ነው፡፡ አንድም ቢያደርገው ሌላ ጾር እሻለታለሁ ባያደርገውም ድካሙን አይቼ እቀርበዋለሁ ብሎ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “ሰው የሚድነው በኅብስት ብቻ እንዳይደለ በእግዚአብሔር ቃል ጭምር እንደሆነ ተጽፏል” ይለዋል፡፡ ይህን ማለቱ ሰው ምግብ የሚሆነው ገበሬ የጣረበት ኅብስት ብቻ እንዳይደለ እግዚአብሔር ምግብ ሁን ያለው ምግብ ሆኖለት ይኖራል ለማለት ነው፡፡ አንድም ሰው የሚድነው ገበሬ በጣረበት በጋረበት እንጀራ ብቻ አይደለም በትምህርት በዓቂበ ሕግ (ሕግን በመጠበቅ) ነው እንጅ፡፡ አንድም አንተስ ወልደ እግዚአብሔር ከሆንህ ይህ እንደ ደንጊያ የፈዘዘው ሰውነትህ ኅብስተ ሕይወት ኅብስተ መድኃኒት ይሁን በል ሲለው ነው፡፡ ጌታም ሰው የሚድን በዕሩቅ ብእሲ ሥጋ እንዳይደለ ተጽፏል አካላዊ ቃል በተዋሐደው ሥጋ ነው እንጅ ይለዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በዚህ እንደተሸነፈ የተረዳ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት አገር ወደ ኢየሩሣሌም ይወስደዋል፡፡ ሰይጣን የሚወስደው ሁኖ አይደለም በፈቃዱ ሔደለት እንጅ፡፡ በፈቃዱ የሔደለትም ካህናትን ድል ነሥቸበት በማላውቀው ገዳም ሁኖ ነው እንጅ ካህናትን ድል በምነሣበት ቤተመቅደስ ቢሆንማ ድል እነሣው ነበር ሲል ሰምቶት ነው የዲያብሎስን ውርደት የእርሱንም አምላክነት ለማሳየት ነው፡፡ በዚያም ሌላ ፈተና ይፈትነዋል፡፡ ከዚያም ተድባብ ቢሉ ከዝንቦው ማዕዘንት ቢሉ ከምሕዋሩ ርእስ ቢሉ ከጉልላቱ ላይ ያቆመዋል፡፡ ከዚያም “አንተ በእውነት ወልደእግዚአብሔር ከሆንህ ከዚህ ዘልለህ ከታች ውረድ” ይለዋል፡፡ ቢሰበር ዐርፈዋለሁ ባይሰበር ምትሐት አሰኘዋለሁ ብሎ አንድም ቢያደርገው ሌላ ጾር እሻለታለሁ ባያደርገውም ደካማ አሰኘዋለሁ ብሎ አንድም ቢያደርገው የሰይጣን ታዛዥ እልበታለሁ ባያደርገውም ድካሙን አይቼ እቀርበዋለሁ ብሎ፡፡ ጌታም መልሶ “እግዚአብሔር ፈጣሪህን አትፈታተነው የሚል ጽሑፍ አለ” ይለዋል፡፡ በዚህም ዲያብሎስ ድል ማድረግ አልቻለም በመሆኑም ወደ ረዥም ተራራ ይወስደዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ከረዥም ተራራ አወጣው፡፡ ነገሥታትን ድል በማልነሣበት ቤተመቅደስ ድል ነሣኝ እንጅ ነገሥታትን ድል በምነሣበት በተራራ ቢሆን ኖሮ ድል ባላደረገኝ ነበር ሲል ሰምቶታልና ጌታ በፈቃዱ ወደ ተራራ ይወጣለታል፡፡ ከዚያም ጠጠሩን ወርቅ ብር፣ ቅጠሉን ግምጃ አስመስሎ አሳየው አንድም ግዛቱን ሁሉ አሳየው እንስሳትን አራዊትን ፈረስ በቅሎ ሠራዊት አስመስሎ አሳየው፡፡ ጌታ ግን አያይለትም እሱ ያየለት ስለመሰለው ነው እንጅ፡፡  ከዚያም መቼም ዲያብሎስ ደፋር ነውና የሁሉ አምላክ መሆኑን ዘንግቶ “ብትሰግድልኝ እጅ ብትነሣኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው፡፡ ጌታም “ከእኔ ወግድ ሂድ አንተ ሰይጣን” አለው፡፡ እንዲህ ማለቱ ራስ አይቶ የሚመጣ ጠላት ክፉ ነውና ከኋላየ ወግድ ሲል ነው አንድም ከእኔ በኋላ ከሚነሡ ምእመናንም ወግድላቸው ሲል ነው፡፡ እንዲህ ሲለው እንደ ጢስ ተኖ እንደ ትቢያ በኖ ይጠፋል፡፡ እስካሁን ወግድ ያላለው አሁን ያለው ስለምን ነው ቢሉ በመጀመሪያ ሽሽ በሁለተኛም ሽሽ በሦስተኛው ግን ተጋደል ድል ንሣ የሚል አብነት ስላለ ነው በሦስተኛው ድል ንሡ ለማለት ነው፡፡ አንድም ጎልማሳ በሚስቱ ንጉሥ በመንግሥቱ እንዲቀና ጌታም ለአምልኮቱ ቀናዒ ነውና በአምላክነቱ ሲመጣበት ወግድ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ጌታ “ለፈጣሪህ ለእግዚአብሔር ብቻ ትሰግድ ዘንድ እሱንም ብቻ ታመልክ ዘንድ ተጽፏል” ይለዋል፡፡ ቅድም እንደትቢያ በኖ እንደጢስ ተኖ ጠፋ ብለን ነበር ነገር ግን ሰይጣን እና ውሻ ምልልስ ይወዳሉና ተመልሶ መጥቶ ሲሰማው እንዲህ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ በአይሁድ ሥግው ሁኖ በመስቀል እስኪያሰቅለው ድረስ ዲያብሎስ ተወው አልተመለሰበትም፡፡
እነዚህን አርእስተ ኃጣውእ እንዲህ አድርጎ ለአዳምና ለሔዋን ድል ነሥቶላቸዋል፡፡ ጌታ እንዲህ ማድረጉ የአባቴ የአዳም የእናቴ የሔዋን ደም የማይቀርብኝ ሲል ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል አድርጎላቸዋል፡፡ እነዚህ ሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ ምን ምን ናቸው ቢሉ፡
1.  ስስት፡- ያልሰጡትን መሻት፤
2.  ትዕቢት፡-አምላክ እሆናለሁ ማለት፤
3.  ፍቅረ ንዋይ፡- በቃኝ አለማለት ነው፡፡
ዲያብሎስ ድል የሆነው በዚህ ሁሉ ነው፡፡ ድል መንሣቱ ግን ለአዳምና ለሔዋን ብቻ አይደለም ለሁሉ ነው እንጅ፡፡
·         መነኮሳት በፈለጉ ጊዜ አያገኙምና በትኅርምት ኗሪዎች ናቸውና ጾራቸው ስስት ነው፡፡ ለዚያም ነው በቦታቸው በገዳም በስስት ቢመጣበት በትዕግሥት ድል የነሣላቸው፡፡
·         ካህናት አእምሯችን ረቂቅ ማዕረጋችን ምጡቅ እያሉ ይታበያሉና ጾራቸው ትዕቢት ነው፡፡ ለዚያም ነው በቦታቸው በቤተ መቅደስ በትዕቢት ቢመጣበት በትህትና ድል የነሣላቸው፡፡
·         ነገሥታት ቤታቸውን ከፍ ካለ ቦታ ሠርተው የወጣ የወረደውን ያለፈ ያገደመውን እያዩ የዚህ ሁሉ እንጅ ኑሮው በኛ ነው እያሉ ገንዘብ ይሰበስባሉና ጾራቸው ፍቅረ ንዋይ ነው፡፡  ለዚህም ነው በቦታቸው በተራራ ላይ በፍቅረ ንዋይ ቢመጣበት በጸሊአ ንዋይ ድል የነሣላቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ኃጢአት ከሥሩ እንደተነቀለ ዛፍ ሁናለች፡፡ ከሥሩ የተነቀለ ዛፍ እንዳይለመልም እንዳያብብ እንዳያፈራ ኃጢአትም በፍዳ የማታሲዝ ሁናለች፡፡ አሁን በፍዳ የተያዙ አሉ ቢሉ እነዚህ አዋጅ አፍራሾች ናቸው፡፡ ንጉሥ ይዘምታል ድል ነሥቶ ሲመለስ ከመንገድ የወጣህ ወታደር ብሎ ያውጃል ያንጊዜ በደለኛ ወታደር ከመንደር ገብቶ ሲዘርፍ ቢሞት ንጉሥ ድል አላደረገም አይባልምና እነዚህም በኃጢአት የተያዙት አዋጅ አፍራሾች ናቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ተወው እነሆም መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር፡፡ አርባ ቀን በትኅርምት ኖሯልና መላእክት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋእ ሰማያዊ ይዘው መጡ አንድም ድል ነሥቷልና ለከ ኃይል ለከ ጽንእ እያሉ ቀረቡ፡፡ ድል ከነሣ በኋላ መምጣታቸው ስለምን ነው ቢሉ አስቀድመው መጥተው ቢሆን ኖሮ  መላእክትን ይዞ ድል ነሣኝ ብቻውን ቢሆን ኖሮ መቼ ድል ይነሣኝ ነበር ባለ ነበር፡፡ አንድም እናንተም ድል ብትነሡ ይገለጽላችኋል ለማለት፡፡ አንዱን ባሕታዊ ሰይጣን መጥቶ ንጉሥ ይጠራሃል አለው፡፡ ባህታዊውም አልብየ ንጉሥ ዘእንበለ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አለው፡፡ ሰይጣንም በያዘው በሎታ ቀጥቅጦት ሄዷል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ ዑቃቢው ተገለጸለት ባህታዊውም ማነህ አለው እሱም መልአከ ዑቃቢህ ነኝ አለው፡፡ ታዲያ እስካሁን የት ነበርህ አለው መልአከ ዑቃቢውም አሁንም ድል ስለነሣህ ተገለጽኩልህ እንጅ ድል ባትነሣ አልገለጽልህም ነበር አለው፡፡ ስለዚህ እናንተም ድል ብትነሡ ይገለጽላችኋል ለማለት መላእክት መጡ፡፡

ተፈጸመ፡፡

ዐቢይ ጾም (ክፍል 2)


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 4/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል አንድ ዐቢይ ጾም እንዴት እንደሚጾምና የዐቢይ ጾም የተለያዩ ስያሜዎች ምን እንደሆኑ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን አርባ ቀንና አርባ ሌሊትን ጾመ? የሚለውን ጥያቄ እንመልሳለን፡፡ መልካም ንባብ!
ማቴ4÷2 “፵ መዓልተ ወ፵ ሌሊተ ጾመ” አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ ይላል፡፡ አርባ መጾሙ ሰራዔ ሕግ በመሆኑ ጾምን የሕግ ሁሉ መጀመሪያ አድርጎ ጾመ፡፡ አንድም ጾምን ለሥራው መጀመሪያ አደረገ፡፡ መብላት ለኃጢአት መሠረት እንደሆነ ጾምም ለምግባር ለትሩፋት መሠረት ናት፡፡ ጾምን እንዲህ ይሏታል “እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብእ ወጥንተ ኵሉ ገድል ሰናይት” ጾም ማለት የጸሎት እናት የዝምታ እኅት የእንባ ምንጭ የመልካም ሥራ ሁሉ መጀመሪያ ናት፡፡ ስለዚህ አምላክም መጾሙ ለሥራው መጀመሪያ ለማድረግ ነው፡፡ አርባ (፵) መጾሙ ስለምን ነው ቢሉ ስለብዙ ነገር ፵ ጾሟል፡
1.  ቀድሞ አባቶቹ ነቢያት ፵ ፵ ጹመዋል ከዚያ ቢያተርፍ አተረፈ ብለው ቢያጎድልም አጎደለ ብለው አይሁድ እውነተኛዪቱን ደጊቱን ወንጌል ከመቀበል ወደኋላ ይሉ ነበር፡፡ ወደዚህ ምድር መምጣቱ ለቤዛ ዓለም ነውና ወንጌልን እንዲቀበሉ አባቶቻቸው ያደረጉትን አደረገ፡፡
2.  ሙሴ በ፵ ዘመኑ አንድ ዕብራዊ እና አንድ ግብጻዊ ተጣልተው ደርሶ ወገኑ ነውና ለዕብራዊው ረድቶ ግብጻዊውን ገድሎ በኆጻ ቀብሮታል፡፡ ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር ዕብራዊው የአዳም ግብጻዊው የዲያብሎስ ምሳሌ ነው፡፡
3.  ሙሴ ፵ ጹሞ ሕገ ኦሪትን ሠርቷል ጌታም ፵ ጾሞ ሕገ ወንጌልን ሠርቷል፡፡
4.  ሙሴ  ፵ ዘመን በምድያም ኑሮ እሥራኤላውያንን ከግብጽ አውጥቷቸዋል ጌታም አርባ ጹሞ ነፍሳትን ከሲኦል ባርነት የሚያወጣ ነውና፡፡
5.  የእሥራኤል ጉበኞች በ፵ ቀን ተመልሰዋል እርሱም የመንግሥተ ሰማያት ጉበኛ ነውና አርባ ጾሞ ነፍሳትን ከሲዖል የሚመልስ ነውና፡፡
6.  እሥራኤል በገዳም ፵ ዘመን ኑረው ምድረ ርስት ገብተዋል እናንተም ፵ ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ለማለት፤
7.  ነቢዩ ሕዝቅኤል በጸጋማይ ጎኑ (በግራ ጎኑ) ፵ ቀን ተኝቶ ስድስት መቶ ሙታንን አስነሥቷል እናንተም ፵ ብትጾሙ ትንሣኤ ዘለክብር ትነሣላችሁ ለማለት፡፡
8.  ዕዝራ ፵ ቀን ጹሞ መጻሕፍትን አጽፏል፡፡ ሌሎች ቀን ሲጽፉ ውለው ማታ ይመገቡ ነበር ዕዝራ ግን ቀን ያጻፈውን ማታ ሲያስበው ያድር ነበር፡፡ እናንተም ፵ ብትጾሞ ምሥጢር ይገለጥላችኋል ሲል፤
9.  እባብ አካሉ ሲያረጅ ሲደገድግበት ፵ ቀን ከምግብ ተከልክሎ ይሰነብታል ከዚያም በስቁረተ ዕጽ ወይም በስቁረተ እብን ሲሄድ ተገፎ ይወድቅለታል ይታደሳል፡፡ እናንተም ፵ ብትጾሙ ተሐድሶተ ነፍስ ታገኛላችሁ ሲል፤
10. አዳም በ፵ ቀን ያገኘውን ልጅነት አስወስዶ ነበርና ለአዳም እንደካሰ ለማጠየቅ፤
11. በ፵ ቀን ተስእሎተ መልክእ ለተፈጸመለት ሰው ሁሉ ሊክስ እንደመጣ ለማጠየቅ፣
12. ለአራቱ ባሕርያተ ነፍስ ዐሥር ዐሥሩን ለመካስ እንደመጣ ለማጠየቅ ባሕርየ ነፍስን ጨምሮ አምስት ቢባል ደግሞ ስምንት ስምንቱን ሊክስ እንደመጣ ለማጠየቅ፣
13.  በዚህ ጾም ፵ ሲጾም ተራበ አልሳሳም ተዋጋ ድል አልተነሣም ለአርአያ ነውና ጾሙ ጹሙ፣ ሠርቶ ሥሩ ለማለት ጾመ፡፡ ሌሎች እንደሚያደርጉት ሳይጾም ጹሙ ሳይሠራ ሥሩ አላለንም፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች ፵ ጾሟል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን አምስት ግብራት ፈጽሟል፡፡
1.  ጥምቀት፡- በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ መጠመቁ ነው፡፡
2.  ተአምኖ ኃጣውእ፡- ከተአማንያነ ኃጣውእ አንድ ሆኖ መቆጠር ነው፡፡
3.  ከዊነ ሰማዕት፡- በጲላጦስ ፊት ቆሞ አንሰ በእንተ ዝንቱ ተወለድኩ ወእንበይነ ዝንቱ መጻእኩ ውስተ ዓለም ከመ እኵን ሰማዕተ በጽድቅ ሎ መመስከር ነው፡፡
4.  ተባሕትዎ፡-፵ ቀን ከምግብ ተከልክሎ በገዳም መኖር ነው፡፡
5.  ምንኲስና፡- በድንግልና መኖር ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከረቂቅ የተገኘ ረቂቅ፣ ከማይራብ የተገኘ የማይራብ፣ ከማይዳሰስ የተገኘ የማይዳሰስ፣ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከሕይወት የተገኘ ሕይወት እንደሆነ ሲያጠይቅ፡
1.  ረቂቅ ዘእምረቂቅ (ከረቂቅ የተገኘ ረቂቅ) ሲያጠይቅ፡- በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ፡፡
2.  ዘኢይርኅብ እምዘኢይርኅብ (ከማይራብ የተገኘ የማይራብ) ሲያጠይቅ፡- ፵ ቀንና ፵ ሌሊት ጾመ፡፡
3.  ዘኢይትገሠሥ እምዘኢይትገሠሥ (ከማይዳሰስ የተገኘ የማይዳሰስ) ሲያጠይቅ፡- በባሕር ላይ ተራመደ፡፡
4.  ብርሃን ዘእምብርሃን (ከብርሃን የተገኘ ብርሃን) ሲያጠይቅ፡- ብርሃነ መለኮቱን በደብረታቦር ገለጸ፡፡
5.  ሕይወት ዘእምሕይወት (ከሕይወት የተገኘ ሕይወት) ሲያጠይቅ፡- የአራት ቀን እሬሳ አልዓዛርን አንሥቷል፡፡
“ወእምዝ ርኅበ” ከዚህ በኋላ ተራበ መራቡ ግን በፈቃዱ ነው እንጅ እንደእኛ ያለ ረኀብ አይደለም፡፡  እኛ ብንበላው ቁንጣን ብንተወው ድካም ቅጥነት ስልት ይሆንብናል፡፡ የእርሱ ረኀብ ከዚህ ረኀብ የተለየ የፈቃዱ ነው፡፡ ቅድም ከማይራብ የተገኘ የማይራብ ብለን ነበር አሁን ደግሞ ተራበ አለ አይጋጭምን ቢሉ አይጋጭም፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ እንደሆነ ለማጠየቅ አንድ ጊዜ ርኅበ አንድ ጊዜ ኢርኅበ ይላል፡፡ መራቡም ለአጽድቆተ ትስብእት ለካሳ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የሚፈታተነው ዲያብሎስ ቀረበ፡፡

በምን በምን ፈተነው? በቀጣይ ክፍል ጠብቁን፡፡ ይቀጥላል…

Friday, March 11, 2016

ዐቢይ ጾም (ክፍል 1)

ዐቢይ ጾም (ክፍል 1)
© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 2/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ይህ ጾም ዐቢይነቱ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው በመሆኑ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ ወደ ገዳም ሄደ ገዳሙ ገዳመ ቆርንቶስ ነው፡፡ ይህን ማድረጉ ወደዚህ ምድር በሥጋ የተገለጠ ለአርአያ ነውና እናንተም እንደተጠመቃችሁ ሳትውሉ ሳታድሩ ወደ ገዳም ሂዱ ሲል ነው፡፡ አንድም ከዚህ ጾም በኋላ የሚያስተምር ነውና እናንተም ጾምን የሥራችሁ ሁሉ መጀመሪያ አድርጉ ሲል ነው፡፡ ወደዚህ ገዳም የወሰደው ፈቃዱ ነው መንፈስ ወሰደው የሚልም አለ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ወሰደው ብንል ሰማዕታትን ወደ ደም ጻድቃንን ወደ ገዳም አስጨክኖ እንደሚወስዳቸው ያለ መንፈስ አይደለም በፈቃድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ መሆናቸውን መናገር ነው እንጅ፡፡ የወልድ ፈቃድ የመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ነውና በፈቃዱ በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ገዳም ሄደ፡፡ ወደዚህ መምጣቱ ለመፈተን አስቦ አይደለም እፈተናለሁ ብሎ አስቦ ሄዶ ቢሆንስ እዳ በሆነበት ነበር ነገር ከሄደ ዘንድ ሰይጣን ሊፈትነው ይቀርባል እርሱም ጾሩን እየቀለበ ይሰብርበታል፡፡ ዲያብሎስም በሦስት ዐበይት ኃጣውእ ይፈትነዋል እርሱም ድል ይነሣዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በጾር መፈተኑ እማርበታለሁ ብሎ አይደለም፡፡ መከራውንና ፈተናውንም ሽቶ አላመጣውም፡፡ እነዚህ የኃጢአት ሁሉ የበላይ ናቸው እነዚህን ያሸነፈ ሰው በሌሎች አይሸነፍምና ትልልቅ ኃጢአቶች ተብለዋል፡፡ እነዚህም ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ ናቸው፡፡ እነዚህን በሌላ ክፍል እንመለከታቸዋልን፡፡ አዳም ከዚህ ዓለም አፍአ በምትሆን ገነት ድል ተነሥቶ ነበርና እርሱም ከዚህ ዓለም አፍአ በምትሆን ገዳም እነዚህን ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል ነሳቸው፡፡ ድል መንሳቱም በሥጋው ነው እንጅ በመለኮቱ አይደለም በመለኮቱ ድል ነስቶ ቢሆን ኖሮስ ባልተደነቀም ነበር፡፡ በመለኮቱማ ዲያብሎስስ ሊቀርበው እንዴት ይቻለው ነበር?  
ወደ ገዳም የሄደበት ሌላም ምክንያት አለው፡፡ ለወጣንያን (ለጀማሪዎች) ወደ ገዳም መሄድ ፈተና ይቀላልና ለወጣንያን አብነት ለመሆን አንድም ለፍጹማን ለበቁት ጾር ይጸናልና ለእነርሱ አብነት ለመሆን ይሄዳል፡፡ ይህ ጾም የተለያዩ መጠሪያዎች አሉት፡፡
1.  ዐቢይ ጾም፡- ስያሜው ትልቅ ጾም እንደ ማለት ነው፡፡ አምላካችን ጾሞ ጹሙ ብሎ ያሳየን ነውና ትልቅ እንለዋለን፡፡ አንድም ሦስቱ ዐበይት (አርእስተ) ኃጣውእ ድል የተነሡበት ነውና፡፡ አንድም አምላክ የሥራው ሁሉ መጀመሪያ አድርጎታልና ዐቢይ (ትልቅ) እንለዋለን፡፡
2.  ጾመ ኢየሱስ፡- ሌሎችን ጾሞች በጾሟቸው ሰዎች መሠረት አድርገን ጾሞ ነቢያት፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ነነዌ እያልን እንደምንጠራቸው ሁሉ ይህንንም ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳይቀመጥ እረፍትን ሳይሻ ጾሞታልና ጾመ ኢየሱስ እንለዋለን፡፡
3.  ጾመ ሁዳዴ፡- ሁዳድ ማለት ሰፊ የመንግሥት እርሻ ቦታ ማለት ነው በዚህ እርሻ ቦታ ላይ ልጅ አዋቂ፣ ሴት ወንድ፣ ወጣት አዛውንት፣ ደካማ ብርቱ ሳይለይ ሁሉም በሥራ ይሳተፍበታል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በዚህ ጾም ሁሉ ይሳተፋል ለሁሉ ነውና ጾመ ሁዳዴ ተብሎ ይጠራል፡፡
4.  ጾመ አርባ፡- ይህ ስያሜ በጾመው የቀን ብዛት የተሰጠ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት የጾመው ጾም በመሆኑ ጾመ አርባ ይባላል፡፡
5.   ጾመ ሙሴ ፡- ይህ ደግሞ ቅዱስ ያሬድ በዘወረደ ሰኞ ዕዝል ከመዝ ይቤ ሙሴ . . . ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት . . . እያለ በጾመ ድጓው ስለ ዘመረ ጾመ ሙሴ ይባላል ፡፡
6.  በዓተ ጾም ፡- ይህም ማለት የጾም መግቢያ፣ መባቻ ወይም ጾሙ የሚሰፍርበት በዓት ማለት ነው፡፡
እኛ ይህንን ጾም እንዴት እንጹመው የሚለውን ከፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ላይ እንመልከተው፡፡
ቁጥር 602፡ ዐቢይ ጾም ስምንት ሱባዔ እንደሆነ በነገሥታት መጽሐፍ ተጻፈ፡፡ መጀመሪያው የክረምት መጨረሻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክረምት እንዳይደለ ይታወቃል መጨረሻው የበጋ መጀመሪያ ነው በየሳምንቱ አምስት ቀን መጾም ይገባል፡፡
ቁጥር 575፡ ጾመ አርባ በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን መጀመሪያውም ከሰንበቶቹ ሁለተኛ የሆነው ሰኞ ነው፡፡ መጨረሻውም ከፍሥህ አስቀድሞ ባለው በዕለተ ዓርብ ነው፡፡ ይህም ከፍሥህ ሱባዔ በኋላ ያለ ሱባዔ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከዐቢይ ጾም በኋላ የከበረ ሰሙነ ሕማማትን ትፈጽሙ ዘንድ ትጉ፡፡
ቁጥር 596፡ ክብርት በምትሆን በአርባ ጾም በመጀመሪያው ሱባዔ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ይጹሙ፡፡ የመጀመሪያው ሱባዔ ካለፈ በኋላ እስከ 11 ሰዓት ድረስ ይጹሙ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ግን ኮከብ እስኪወጣ ድረስ ይጹሙ፡፡ በእነዚህም ወራቶች አያጊጡ፡፡

ቁጥር 578፡ በሊህ በስድስቱ ቀኖች (በሰሙነ ሕማማት) ከቂጣ ከጨው ከውኃ ብቻ በቀር አይብሉባቸው፡፡ በሊህ ቀኖች ከወይን ከሥጋ ተለዩ የኀዘን ቀኖች ናቸውና የደስታ ቀኖች አይደሉም፡፡ዓርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱንም በአንድነት ጹሟቸው፡፡ የሚችል እስከ ሌሊቱ ዶሮ ጩኸት ጊዜ ድረስ ምንም ምን አይቅመስባቸው ሰውየውም ሁለቱን ቀኖች በአንድነት መጾም ባይቻለው ግን የቅዳሜን ጾም ይጹም፡፡
ቁጥር 589፡ ዐቢይ ጾምንና ዓርብን ረቡዕን የማይጾም የታወቀ ደዌ ያለበት ካልሆነ በቀር ካህን ከሆነ ይሻር ሕዝባዊ ቢሆንም ይለይ፡፡
ቁጥር 590፡ ካህን ሰሙነ ሕማማትን ቀንና ሌሊቱን ሳያስተካክል አስቀድሞ ቢያውል ይሻር፡፡ ከሕማማት ቀጥላ ከምትሆን ከቅዳሜ ስዑር በቀር እሑድንና ቅዳሜን የጾመ ካህን ቢኖር ይሻር፡፡
ቁጥር 591፡ በዐቢይ ጾም የሰማዕታትን በዓል ልናከብር አይገባንም፡፡ የሰማዕታት መታሰቢያ በእሁድ በቅዳሜ ይሁን እንጅ፡፡
ቁጥር 592፡ በአርባ ጾም ሠርግ ማድረግ አይገባም ሴትም በወለደች ጊዜ ሰውን ወደ መጠጥ ቤት መጥራት አይገባም፡፡
ቁጥር፡ 593፡ ከካህናት ወገን ማንም ቢሆን በአርባ ጾም በዓርብና በረቡዕም ጾም ወይን መጠጣት አይገባውም ወደ መዋት (ውሽባ ቤት) አይግባ፡፡ በዐቢይ ጾም ወራት ሰው ከሚስቱ ጋር አይተኛ፡፡
ቁጥር 597፡ ሴቶችም ጌጣቸውን ይተው፡፡ ሁሉም ለእያንዳንዱ በአርባ ጾምና በሰሙነ ሕማማት መጠበቅ ይገባዋል ድኅነታችንና የኃጢአታችን ሥርየት በእነርሱ ነውና፡፡ ይኸውም ሥራ አንዱስ እንኳ በአርባ ጾም ወራት በምንጣፍ ፈጽሞ እንዳይገናኝ ከጋብቻ ሕግ የወጣ ነው፡፡ ክብርት በምትሆን በሕማማት ወራት ይህችን ኃጢአት የሚሠራት ሰው ወዮለት፡፡ በአርባ ጾም በተድላ በደስታ ፈቃዳችንን ካደረግን ትንሣኤውን ባየን ጊዜ ተድላ ደስታችን ወዴት አለ?
ቁጥር 599፡ በተባሕትዎ በትሕትና አርባ ቀን ጾምን ይጹሙ፡፡ ከጥሉላት መከልከል ይገባል፡፡ አያግቡም፡፡
ቁጥር 600፡ በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሣት ክህነት መስጠት ለሞቱ ሰዎች መጸለይ አይገባም፡፡ በእነዚህም ቀኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ ማገልገል ይገባል እንጅ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ስለሚሞቱት ሰዎች የሙታን ግንዘትና የሐዋርያት ሥራ ወንጌላት የሙታን ፍትሐት በሆሣዕና በዓል ቀን ይነበብ እንጅ፡፡
ቁጥር 601፡ በጸሎተ ሐሙስ ጸሎተ ተአምኆ እግዚአ ሕያዋን የቡራኬ ጸሎት አይባልም (አይጸለይም)፡፡ ቅዳሜ ግን እግዚአ ሕያዋን ይባላል ፍትሐት ይፈታል፡፡ ከመሳለም በቀር ጸሎተ ዕጣንም ይጸለያል፡፡ በዕለተ እሑድ ግንዘት ማድረግ በፋሲካ ቀንም ማልቀስ አይገባም፡፡ ዳግመኛም በውስጧ በአርባ ጾም ከተድላ ከደስታ ወገን ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ መጋባት ክህነት መስጠት ክርስትና ማንሣት ከሹመትም ወገን ስለሚሞቱት ከመጸለይ በቀር ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ ይሞታል ተብሎ ለሚያስፈራው ግን ጥምቀተ ክርስትና ይደረግለታል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን አርባ ቀንና አርባ ሌሊትን ጾመ? በቀጣይ ክፍል ይጠብቁን!...

Wednesday, March 9, 2016

ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚሉት ሁሉ የጌታ ናቸውን?

© በመልካሙ በየነ
የካቲት 30/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በምንፍቅናው ዓለም በጨለማ ውስጥ ሳሉ በብርሃን ነን የሚሉት የእግዚአብሔርን ፍቅር ከአምላክነትና ከአባትነት ደረጃ አውርደው የጓደኛን እንኳ ያህል ክብር ሳይሰጡ “ኢየሱስ ጌታ ነው!” በማለት ብቻ እንድናለን ብለው ራሳቸውን የሚያታልሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በእውነት የኢየሱስን ጌትነት ለእኛ ለተዋሕዶ ልጆች እነርሱ የሚያስረዱን ይመስላቸዋልን? ድፍረትስ አይሆንምን? በኢየሱስ ደም በተመሠረተች ቤተክርስቲያን ውስጥ በ40 በ80 ቀናችን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማየ ዮርዳኖስ የልጅነት ጥምቀት የተጠመቅን የብርሃን ልጆች የኢየሱስን ጌትነት እንዴት አናውቅም? በሚገባ እናውቀዋለን እንጅ ምን ነካችሁ፡፡ በእርግጥ ከተራራ የሚልቅ ልዩነት አለን፡፡ እነርሱ ኢየሱስ የሚሉት እኛ ኢየሱስ የምንለውን ጌታ አይደለም፡፡ እኛ ኢየሱስ የምንለው ቀድሞ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ ያለ እናት የተወለደውን የአብ ልጅ በኋላም ከንጽሕት ዘር ከድንግል ማርያም ያለ አባት በተዋሕዶ የተወለደውን የድንግል ማርያምን ልጅ ነው፡፡ እኛ ኢየሱስ የምንለው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሥጋን ለብሶ ለድኅነተ ዓለም ወደዚህ የመጣውን በመልእልተ መስቀል ተሰቅሎ በደመ ማኅተሙ ሲዖልን የከፈተውን በባርነት የነበረውን አዳም ልጅነቱን የመለሰውን ነው፡፡ ኢየሱስ ለእኛ አምላክ ነው፣ ኢየሱስ ለእኛ ፈራጅ ነው፣ ኢየሱስ ለእኛ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው፣ ኢየሱስ ለእኛ ጌታችን ነው፣ ኢየሱስ ለእኛ መድኃኒታችን ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ያልነው ዛሬ ሳይሆን ድሮ ገና ሉተር ሳይፈጠር ነበር፡፡ እኛ አክብረን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንለዋለን እነርሱ ንቀው ከጓደኛም አሳንሰው “ኢየሱሴ!” ይሉታል ሎቱ ስብሐት፡፡
የመናፍቃን ማታለያ ዘዴዎች በርካታ ናቸው፡፡ እነርሱ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ በደረቁ ሸምድዶ እዚህ ቦታ እንዲህ ይላል እያሉ ሰውን ጥርጣሬ ውስጥ መጨመር ፍላጎታቸው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከመጣን አንድ ቦታ እና አንድ ነጥብ ላይ ብቻ ቆመን መከራከር ከቻልን ችግር የለውም፡፡ በዚያች ባነሷት ነጥብ ላይ ተማምነን ወደሌላ ካለፍን ችግር የለውም እንነጋገር፡፡ ነገር ግን የዚያ ዓይነት ወኔ የላቸውም  ምክንያቱም መሠረት ስለሌላቸው ጸንተው አይቆሙም፡፡ ስለድንግል ማርያም አማላጅነት ጀምረው ስለመስቀል ሲከራከሩ ነው የምታገኟቸው፡፡ እነርሱ ጥርጥርና ኑፋቄን በሰው ልብ ላይ መዝራት እንጅ ማመንና ማሳመን አይችሉም፡፡ ዋናው መከራከሪያቸው “እንዲህ የሚል ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አይገኝም” የሚለው ብሂላቸው ነው፡፡ ትልቁ ስህተታቸው እዚህ ጋር ነው የሚጀምረው እንግዲህ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ታሪክ የያዘ ነው ልንል እንዴት እንደፍራለን? ጌታ ያደረገው፣ እመቤታችን ያደረገችው፣ ሐዋርያት ያደረጉት ሁሉ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ ውስጥ እንዴት ነው ሊጻፍ የሚችለው? እኛ እንኳ ከንቱዎች ከመጽሐፍ ቅዱሱ ገጽ ብዛት ይልቅ የሚበዛ ታሪክ ስለራሳችን እንጽፍ የለም እንዴ? ታዲያ የአንድ ሰው ታሪክ ያን ያህል ከሆነ እንዴት ነው የጌታችን ታሪክ፣ የእመቤታችን ታሪክ፣ የሐዋርያት ታሪክ በዚያ መጽሐፍ ብቻ ሊወሰን  የሚችለው? አለማስተዋል ካልሆነ በቀር በፍጹም ሊወሰን አይችልም፡፡ ሰማይ እና ምድር እንደ ብራና ቢሆኑ ቀላያት በሙሉ የብርዕ ቀለም ቢሆኑ ውሉደ አዳም ጸሐፍት ቢሆኑ በፍጹም ተጽፎ የማያልቅ ታሪክ አላቸው፡፡ ስለዚህ እንደመግቢያ ያህል ትንሹን ነገር ብቻ መሠረታዊ የሆነውን ለእኛ በምንረዳው መጠን ተጻፈልን እንጅ ሁሉንም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አላሰፈሩልንም፡፡ ይህን የምለው ዝም ብየ አይደለም ራሱ መጽሐፉ ስለሚል ነው፡፡ ዮሐ 21፥25 ላይ እንዲህ ይላል “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ ኹሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል”፡፡ ታዲያ እኛ ተአምረ ኢየሱስ ስንል፣ መልክአ ኢየሱስ ስንል ምኑ ነው የማይዋጥላቸው? ስለእመቤታችንም ቢሆን እንዲሁ ነው፡፡ ዮሐንስ ወንጌላዊው እነኋት እናትህ ተብሎ በዮሐ19፥27 ላይ ከተቀበላት በኋላ 15 ዓመት አብሯት አብራው ኖረዋል፡፡ ከዚያ በፊት ያለው መተዋወቃቸው ቀርቶ በዚህ 15 ዓመት ውስጥ ስለእርሷ ያወቀውን በወንጌሉ ማስፈር አቅቶት ነው እንዴ ምንም ያላለው? አይደለም እነርሱ እንደ እኛ ምሥጢር የማይገባቸው አይደሉም ሁሉን ነገር በምሥጢር ነው የሚያነሡት፡፡ በምሥጢር እኮ በወንጌሉ ላይ በምዕራፍ 2 አንሥቷታል፡፡ ያንን በሚገባ ተርጉመን ምሥጢሩን አራቅቀን መማርና ማዎቅ የእኛ ፈንታ እንጅ የዮሐንስ ፈንታ አይደለም፡፡ እርሱ ያስተማረውን ማን ነው የጻፈለት? ቃል በቃል አፍ ለአፍ የተናገራቸውን ትምህርቶች ማን ነው መዝግቦ የያዘለት? 2ኛ ዮሐ 1፥12 ላይ “እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ” ይላል፡፡ 3ኛ ዮሐ1፥13 ላይም “ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወድም” ይላል፡፡ ከእነዚህ ጥቅሶች የምንረዳው ነገር አለ፡፡ እርሱም ከዚህ መልእክት በተጨማሪ አፍ ለአፍ ያናገራቸው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ያ አፍ ለአፍ ያናገራቸው ያስተማራቸው ትምህርት ምንድን ነው? ስለእመቤታችን ድንግል ማርያም ነውን? ስለ መስቀል ነውን? ስለ መላእክት ነውን? ስለኢየሱስ ክርስቶስ ነውን? ስለ ታቦት ነውን? ስለ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ነውን? ታዲያ ስለምንድን ነው? አሁን ይህን ማን ያውቃል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ እስካላገኘነው ድረስ የዮሐንስን ትምህርት አንቀበለውም አንልም ምክንያቱም መልእክቱ ላይ ይህንን ስላስቀመጠልን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ ቢሆንም ዮሐንስ በአፍ ያስተማረውን እኛ እንቀበለዋለን፡፡ እነርሱ አይቀበሉትም ልዩነታችን ይህ ነው እንግዲህ፡፡ መዳን የማይሻ ትውልድ ሁልጊዜ እንደተከራከረ ነው በሚያውቀው አንድ ሳይሰራ በማያውቀው ሺህ ጊዜ ሲከራከር ኅልፈት ይቀድመዋል፡፡
እኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምን አዋልድ መጻሕፍትን ድርሳናትን፣ ገድላትን፣ ተአምራትን፣ መልክአ መልኮችን፣ የሥርዓት መጻሕፍትን፣ ትርጓሜ መጻሕፍትን በሙሉ እንሻለን ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር ሳይሆን በጥቅል የተጻፈ ስለሆነ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መተርጎም መብራራት የሚሻቸው ናቸው፡፡ ከዚያ ውጭ ከሆነ ግን ገደል ይዞን እንደሚገባ አያጠራጥርም፡፡ 2ኛ ጢሞ 3፥16 “…የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ኹሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” ይላል፡፡ ታዲያ መናፍቃኑ ትምህርት አንፈልግም፣ ተግሳጽ አንሻም፣ ልባችን እንዲቀና አንፈልግም፣  ምክር አይጠቅመንም ነው እንዴ የሚሉት? አልገባኝም እኔስ በእውነት ነው የምላችሁ፡፡ መናፍቃኑ እኮ የሚከራከሩት “እንዲህ የሚል ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም” ጥቅስ አሳዩን በሚል ነው፡፡ በእውነት ሲጀመር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን በሙሉ አምነው እየሠሩበት ነውን? ትልቁ ጥያቄ እዚህ ጋር ነው፡፡ ለምሳሌ ኢየሱስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾመ የሚል በወንጌል እናገኛለን ማቴ 4ን ተመልከቱ ግን እነርሱ እየጾሙ ነው? አይደለም፡፡ እንዲያውም “ኢየሱስ ጾሞልኛል እና አልጾምም” ነው የሚሉት፡፡ በዚህም ይሁን እሽ እርሱ ጾሞላቸዋል እና እነርሱ መጾም አያስፈልጋቸውም እንበልና እንስማማ ማቴ 26፥20 ላይ “በመሸም ጊዜ ከ12ቱ ደቀመዛሙርት ጋር በማእድ ተቀመጠ ሲበሉም እውነት እላቸኋለሁ…” ይላል  ስለዚህ እዚህ ክፍል ላይ ስትደርሱ ደግሞ ኢየሱስ በማእድ ተቀምጦልኛና እርሱ ስለበላልኝ እኔ አልበላም ማለት ያስፈልጋችኋል ማለት ነው፡፡ ሲጾም ጾመልን እንዳላችሁ ሁሉ ሲበላም በላልን ማለት አለባችሁ፡፡ ለመከራከር እኮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የማይጾም ሰው ስለጾም ምን አከራከረው? የማይጸልይ ሰው ስለጸሎት ምን አከራከረው? የማያስቀድስ ሰው ስለ ቅዳሴ ምን አከራከረው? የማይሰግድ ሰው ስለ ስግደት ምን አከራከረው? እኛ ለጾምን፣ እኛ ለጸለይን፣ እኛ ላስቀደስን፣ እኛ ለሰገድን እነርሱ ምን ቤት ናቸው የሚለፈልፉት? አንዳንድ ጊዜማ በሰከነ መንፈስ ራስን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማዳመጥ ያስፈልጋል እኮ፡፡ እኛን ብቻ ስሙን ማለት አይገባም እነርሱም እኛን ሊሰሙን ሊያዳምጡን ያስፈልጋል፡፡
ዝም ብሎ የማያውቁትን ጌታ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ማለት የሚያጸድቀን አይደለም፡፡ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ከማለታችን አስቀድሞ ጌታን ማወቅ ያስፈልጋል እንጅ ስሙን የጠራ ሁሉ ይድናል እያሉ ሳያምኑ “ኢየሱስ ጌታ ነው!” ብሎ መፎከር አይደለም፡፡ ማቴ 7፥21 “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጅ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” ይላል መጽሐፉ፡፡ ስለዚህ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ከማለት በፊት የአባቱን ፈቃድ ማዎቅና መፈጸም ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” እያሉ መጨፈር መንግሥቱን የሚያወርስ አይደለም፡፡ በእርግጥ እኛ እንደፈለጋችሁ ብትዘሉ ብትጨፍሩ አይመለከተንም እምነት ብላችሁ የያዛችሁት እስከሆነ ድረስ ነገር ግን የእኛን ልጆች እንዲጠራጠሩ ኑፋቄያችሁን ልትዘሩባቸው አይገባም፡፡ እናንተም ለራሳችሁ ነው እኛም ለራሳችን ነውና! እኛና እናንተን የማያገናኘን ትልቅ ገደል አለ ከዚያ ገደል ልታልፉ አይገባም ካለፋችሁ ግን ያው በሚገባ እናስተምራችኋለን፡፡ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ማለት የጌታ መሆንን የሚያሳይ እንዳይመስላችሁ፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ የጌታ ለመሆን “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ማለት ብቻ ሳይሆን እርሱን መምሰል ጭምር ያስፈልጋል፡፡ እርሱን የምንመስለው ደግሞ በመጾም፣ በመጸለይ፣ በመስገድ፣ በመመጽወት፣ እውነተኛውን መንገድ በመምረጥ፣ እውነተኛውን ትምህርት በመማር በማስተማር ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ማለት ብቻውን የጌታ መሆንን አያሳይም፡፡ ይህንን ኑፋቄያችሁን በተለያዩ መገናኛዎች ለማደናገር የምትሞክሩ መናፍቃንም ልታስተውሉ ያስፈልጋል፡፡

እግዚአብሔር ማስተዋልን ያድለን፡፡

Tuesday, March 8, 2016

ፍትሐ ነገሥት እና ጾም

© በመልካሙ በየነ
የካቲት 28/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አባቶቻችን ለእያንዳንዱ ሥራዎች ሥርዓትን ሠርተውልናል፡፡ ይህንን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ለኛ የሠሩልንን ሕግ ደግሞ ማዎቅና ተግባራዊ ማድረግ ሕይወትን የሚያሰጥ በረከትን ያሚያድል መሆኑ የተረዳ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን በያዝነው ጾም ውስጥ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል የሚለውን ከፍትሐ ነገሥቱ ቃል በቃል እንመልከት፡፡
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 (በእንተ ኵሎሙ አጽዋም፤ ስለጾሞች ሁሉ)
ቁጥር 564፡ ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ፡፡
ቁጥር 565፡ ለክርስቲያን ሁሉ የታዘዘውም ጾም ክብር ምስጋና ይግባውና ክርስቶስ የጾመው ጾመ አርባ ነው፡፡ ፍጻሜዋ ከፍሥህ (የአይሁድ ፋሲካ) በፊት ባለው ዓርብ የሚሆን ነው፡፡ ከዚህም ቀጥሎ የስቅለት ሳምንት ነው፡፡ እነዚህን እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ ይጾማሉ ደም የሚወጣው እንስሳ ከእንስሳትም የሚገኘው አይበላባቸውም፡፡
ቁጥር 566፡ ዳግመኛም በእየሳምንቱ ሁሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው፡፡
ቁጥር 567፡ በዚህ ላይ የተጨመሩ ሌሎች ጾሞች ግን በግብጽ ቤተክርስቲያን ተጽፈዋል፡፡ ከእነርሱም እንደ ዐቢይ ጾም በመጠንቀቅ የሚሆን አለ፡፡ ይህችውም ከዐቢይ ጾም አስቀድማ የምትሆን የሕርቃል ጾም ናት፡፡ የነነዌ ሰዎች ጾም 3 ቀን የልደትና የጥምቀት ዋዜማ ጾም (ገሀድ)፡፡
ቁጥር 568፡ ከእነርሱም የሚያንስ እንደ ረቡዕና እንደ ዓርብ የሚሆን አለ፡፡ ይኸውም ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው፡፡ መጀመሪያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የገና በዓል ነው፡፡
ቁጥር 569፡ ከዚህም ቀጥሎ ከበዓለ ሃምሳ ቀጥሎ ያለ የሐዋርያት ጾም ነው፡፡ ፋሲካው በጴጥሮስና በጳውሎስ በዓል ሐምሌ 5 ቀን ነው፡፡
ቁጥር 570፡ እነዚህን ጾሞች ሕጎቻቸውን ከተቀበሏቸው በኋላ ከጥቂቶቹ ውሳኔዎች ቁጥራቸው ከሚበዙ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከተቆጠሩት ጋር ሕዝቡ እነሆ ጾመዋቸዋል፡፡ ያለሕጸጽም ሊጠብቋቸው ይገባል፡፡
ቁጥር 571፡ ከእነዚህም ሌላ ብዙ ሰዎች ጠብቀው የሚጾሙት አለ፡፡ ይኸውም ጾም ስለእመቤታችን በዓል ነው፡፡ ይልቁንም መናኒዎች መነኮሳት የሚጾሙት መጀመሪያው ነሐሴ አንድ ቀን ፋሲካው የእመቤታችን በዓል ነው፡፡
ቁጥር 572፡ በእነዚህ በታዘዙት ጾሞች ከቀኑ እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሙ ከዓሣ በቀር ሥጋ አይብሉባቸው፡፡ (እዚህ ጋር ግን ዓሣ ይበላል ማለት አይደለም ዓሣም ቢሆን ለማለት ነው)፡፡ ከዚህ ከታዘዘው አብልጦ የጾመ ግን ዋጋው ይበዛለታል ከጥሉላት በቀር እሁድና ቅዳሜ አይጹሙ፡፡
ቁጥር 573፡ ጾምስ የሥጋ ግብር ነው ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ጸሎትን ያሻው ፈቃድ ለልብ የቁጣ ኃይል እንድትታዘዝ እንደሆነ፡፡
ቁጥር 574፡ ጾም ይረባናል ብለን ከመጾማችን የተነሣ መንፈሳውያንን እንመስላለን ከመሰልናቸውም የሚመስሉትን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም ጿሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ለተራቡትና ለሚለምኑት ይራራላቸው፡፡ ዳግመኛም በፅኑዕ ፈቃድ ሁኖ ሊመገበው ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ነው መቀበሉም በሥጋዊና በነፍሳዊ ትጋት ይሁን ዳግመኛም ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ የጾምን ሥርዓት ጠብቆ ከሰው ወገን ደግሞ በጸሎት የተለየ ሁኖ ስለአጽዋም በተሠሩት ሕጎች የፀና ሁኖ በሁለንተናው እግዚአብሔርን ያምልከው፡፡
ቁጥር 575፡ ጾመ አርባ በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን መጀመሪያውም ከሰንበቶቹ ሁለተኛ የሆነው ሰኞ ነው፡፡ መጨረሻውም ከፍሥህ አስቀድሞ ባለው በዕለተ ዓርብ ነው፡፡ ይህም ከፍሥህ ሱባዔ በኋላ ያለ ሱባዔ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከዐቢይ ጾም በኋላ የከበረ ሰሙነ ሕማማትን ትፈጽሙ ዘንድ ትጉ፡፡
ቁጥር 576፡ ከእርሷ በኋላ የፋሲካ ሳምንት የሚሆን ሰሙነ ፍሥህ (የአይሁድ ፋሲካ) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደዚሁም እነዚህን ስድስቱን ቀኖች እንጾም ዘንድ አዘዙን፡፡ በየሳምንቱም ረቡዕንና ዓርብን እንጾም ዘንድ አዘዙን፡፡ ይኸውም ምክር የተፈጸመበት ነውና፡፡ ይኸኛውም መድኃኒታችን ፈቃዱን ስለፈጸመበት ነውና፡፡ በሰባተኛው ቀን ዶሮ በጮኸ ጊዜ ከጾም ይረፉ፡፡
ቁጥር 577፡ ዘወትር በዕለተ ሰንበት መጾም አይገባም እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ አርፎበታልና ቅዳሜ ስዑርን ብቻ ሊጾሙ ይገባል እንጅ፡፡ የፍጥረታቱ ሁሉ ፈጣሪ በመቃብር ውስጥ አድሮበታልና፡፡
ቁጥር 578፡ በሊህ በስድስቱ ቀኖች ከቂጣ ከጨው ከውኃ ብቻ በቀር አይብሉባቸው፡፡ በሊህ ቀኖች ከወይን ከሥጋ ተለዩ የኀዘን ቀኖች ናቸውና የደስታ ቀኖች አይደሉም፡፡ዓርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱንም በአንድነት ጹሟቸው፡፡ የሚችል እስከ ሌሊቱ ዶሮ ጩኸት ጊዜ ድረስ ምንም ምን አይቅመስባቸው ሰውየውም ሁለቱን ቀኖች በአንድነት መጾም ባይቻለው ግን የቅዳሜን ጾም ይጹም፡፡
ቁጥር 579፡ ጌታ ስለ ራሱ እንዲህ አለ “ሙሽራውን ከእነርሱ ለይተው በወሰዱት ጊዜ ያንጊዜ ይጾማሉ” እናንተም በእነዚህ ቀኖች እስከ ሌሊት ድረስ ጹሙ ሙሽራውን ከእኛ ለይተው በወሰዱት ጊዜ እኛ እንደ ጾምን፡፡
ቁጥር 580፡ በዓለ ሃምሳን ከጨረሳችሁ በኋላ ዳግመኛ ሰባት ቀን ሌላ በዓል አድርጉ ከዚህም ቀጥሎ ከአረፋችሁ በኋላ ቱሙ፡፡ ዳግመኛም ረቡዕንና ዓርብን ዘወትር ትጾሙ ዘንድ እናዝዛችኋለን የሚቻላችሁስ ከሆነ ከእህል ከዚህ አብልጣችሁ ጹሙ ለድሆችም ምጽዋት ስጡ፡፡
ቁጥር 581፡ እግዚአብሔር ይቅር ይበለውና ይህን መጽሐፍ ከሰበሰበው ተመረጠ ከሆነው መምህር ቃል የተገኘ ነው፡፡ የዚህ ሳምንት ምልክት ግን ልንበላበት እንደማይገባ እነሆ ረቡዕንና ዓርብን እንድንጾም ያዘዘበት አንቀጽ አለ ዳግመኛም በዓለ ሃምሳ ልደት ጥምቀት ቢውልባቸው አትጹሙ ብሎ ያዘዘበት አንቀጽ አለ፡፡ ስለዚህ ሳምንት ግን አልተናገረም፡፡ ቢበሉባቸው በሚገባ ቀኖች ውስጥ ሊጾሙባቸው የማይገባ ቢሆን ኖሮ እንደነዚያ መልሶ በተናገረ ነበር፡፡
ቁጥር 582፡ ዳግመኛም እንድንጾምባቸው እንድንሰግድባቸው የታዘዝንባቸው ቀኖች እንደ እሁድ እንደ ሰንበት እንደ ጌታ በዓላት ያሉ ቀኖች አሉና ከእነርሱ ጋር ይህን ሳምንት አልተናገረም፡፡ ዳግመኛም የሰሙነ ሕማማትን ሥራ ሳይሠራ ላለፈበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ስለርሷ መጾም መስገድ ይገባ ዘንድ ታዘዘ፡፡ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሚውለው ሳምንት ይህ ቢሆን ኖሮ ከሃምሳ ቀኖች በኋላ ይበሉበት ዘንድ የሚገባ ቢሆን እንደገና ብሉበት በተባለ ነበር፡፡ በዓል አድርጉ ከማለቱ በቀር ብሉበት አላለምና፡፡
ቁጥር 583፡ ይህስ በውስጡ ያሉትን የዓርብንና የረቡዕን ጾም ያስረዳል፡፡ እነርሱንም ይፈጽሟቸው ዘንድ አያስረዳም እነሆ ባስልዮስና አፈወርቅ እንዲህ አሉ፡፡ በዓል ማክበር በመብል አይደለምና ዳግመኛም በጾም በዓል ማክበር እንዲገባ የታወቀ ነው፡፡ ይኸውም ለበዓሉ የሚስማማው እንዲነበብ ነው እንጅ ሊበሉበት አይደለም፡፡ ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ 3 ቀን እንድናከብር እነሆ ቀኖና አዘዘችን፡፡ በጾም ቀን እንኳ ቢሆን በእነዚህ በ3 ቀኖች እንዳንበላ የታወቀ ነው በዓል ማክበር በመብል አይደለም፡፡  
ቁጥር 584፡ ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል፡፡ ከመብላት በጣም ይሻላል፡፡
ቁጥር 585፡ ዳግመኛም ከተሰበሰቡት ወገን ቁጥራቸው ኸያ የሚሆኑት ጹመውታልና ከእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከዚህ ቁጥር ቁጥራቸው እስከበዙት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በዚህ ሳምንት እነሆ ይህን ጾም ጾምን፡፡ የማኅበሩን ትእዛዝ ብንተላለፍ ይህን ማኅበር እንዲነቀፍ ብናደርግ ደግ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሕጋችንን ትሩፋት በተቃወመ ጊዜ፡፡ ይኸውም ስለመብል ስስትን በመግለጽ የሚደረግ ክፋት ነው፡፡
ቁጥር 586፡ ዳግመኛም ስለ ሃምሳኛው ቀን አከባበር ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማር በፊት እንደጾመ ጌታችንም በርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የርሱን ሕግ ለሕዝብ ከማስተማሩ አስቀድሞ እንደዚሁ ጾመ፡፡ ሐዋርያትም በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሕገ ወንጌልን ለሕዝብ ከማስተማራቸው አስቀድሞ እንደዚሁ ጾሙ፡፡ እኛም በዚህ በእነርሱ ተመራን፡፡
ቁጥር 587፡ ልደት በጾም ቀኖች ረቡዕና ዓርብ ቢውል ይጸልዩ፡፡ ሥጋውንና ደሙንም ይቀበሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ጹሙ ብለው አይፍረዱ፡፡
ቁጥር 588፡ አንድ ሰው በባሕር ቢኖር ሰሙነ ሕማማትን ባያውቅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ይጹም፡፡ ይኸውም ሰሙነ ሕማማትን የሚጠብቅ አይደለም፡፡ ምሳሌውን ብቻ ነው እንጅ ስለእርሱ መጾም ይገባዋል፡፡
ቁጥር 589፡ ዐቢይ ጾምንና ዓርብን ረቡዕን የማጾም የታወቀ ደዌ ያለበት ካልሆነ በቀር ካህን ከሆነ ይሻር ሕዝባዊ ቢሆንም ይለይ፡፡
ቁጥር 590፡ ካህን ሰሙነ ሕማማትን ቀንና ሌሊቱን ሳያስተካክል አስቀድሞ ቢያውል ይሻር፡፡ ከሕማማት ቀጥላ ከምትሆን ከቅዳሜ ስዑር በቀር እሑድንና ቅዳሜን የጾመ ካህን ቢኖር ሻር፡፡
ቁጥር 591፡ በዐቢይ ጾም የሰማዕታትን በዓል ልናከብር አይገባንም፡፡ የሰማዕታት መታሰቢያ በእሁድ በቅዳሜ ይሁን እንጅ፡፡
ቁጥር 592፡ በአርባ ጾም ሠርግ ማድረግ አይገባም ሴትም በወለደች ጊዜ ሰውን ወደ መጠጥ ቤት መጥራት አይገባም፡፡
ቁጥር፡ 593፡ ከካህናት ወገን ማንም ቢሆን በአርባ ጾም በዓርብና በረቡዕም ጾም ወይን መጠጣት አይገባውም ወደ መዋት (ውሽባ ቤት) አይግባ፡፡ በዐቢይ ጾም ወራት ሰው ከሚስቱ ጋር አይተኛ፡፡
ቁጥር፡ 594 የሰማዕታት በዓል ከጾም ላይ ቢውል ስለሰማዕታት ሞት ምክንያት ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ቄሱ ለሕዝቡ በመብል በዓል ቢያከብር ይሻር፡፡ እርሱ ለብዙዎች ሰዎች የኃጢአት ምክንያት ሆኗልና እነርሱ በፈቃዳቸው ቢበሉ ግን ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ቄሱ ይለያቸው፡፡ በጾም ወራት ከሆነ በሰማዕታት በዓል ቀን በመብል በመጠጥ ማክበር አይገባቸውምና፡፡ እነዚህ ሰማዕታት እየተራቡ እየተጠሙ በእሳት ተቃጥለው ሞተዋልና፡፡
ቁጥር 595፡ ስለ ልደትና ስለ ጥምቀት ግን በዚያ ዘመን በኒቅያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት ቅዳሴው በሌሊት ይሆን ዘንድ አዘዙ፡፡ ዳግመኛም በበዓለ ሃምሳ እንደዚሁ ነው፡፡
ቁጥር 596፡ ክብርት በምትሆን በአርባ ጾም በመጀመሪያው ሱባዔ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ይጹሙ፡፡ የመጀመሪያው ሱባዔ ካለፈ በኋላ እስከ 11 ሰዓት ድረስ ይጹሙ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ግን ኮከብ እስኪወጣ ድረስ ይጹሙ፡፡ በእነዚህም ወራቶች አያጊጡ፡፡
ቁጥር 597፡ ሴቶችም ጌጣቸውን ይተው፡፡ ሁሉም ለእያንዳንዱ በአርባ ጾምና በሰሙነ ሕማማት መጠበቅ ይገባዋል ድኅነታችንና የኃጢአታችን ሥርየት በእነርሱ ነውና፡፡ ይኸውም ሥራ አንዱስ እንኳ በአርባ ጾም ወራት በምንጣፍ ፈጽሞ እንዳይገናኝ ከጋብቻ ሕግ የወጣ ነው፡፡ ክብርት በምትሆን በሕማማት ወራት ይህችን ኃጢአት የሚሠራት ሰው ወዮለት፡፡ በአርባ ጾም በተድላ በደስታ ፈቃዳችንን ካደረግን ትንሣኤውን ባየን ጊዜ ተድላ ደስታችን ወዴት አለ?
ቁጥር፡ 598 ጾም ከእህል ከውኃ መከልከል አይደለም ከእግዚአብሔር ፊት የሚደርስ ጾምስ የልብ ንጽሕና ነው፡፡ ሥጋ ቢራብ ቢጠማ ነፍስ ግን ፈቃዷን ብትፈጽም ልብም ከጣዕሙ የተነሣ ደስ ቢለው የጾምህ ጥቅሙ ምንድን ነው?
ቁጥር 599፡ በተባሕትዎ በትሕትና አርባ ቀን ጾምን ይጹሙ፡፡ ከጥሉላት መከልከል ይገባል፡፡ አያግቡም፡፡
ቁጥር 600፡ በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሣት ክህነት መስጠት ለሞቱ ሰዎች መጸለይ አይገባም፡፡ በእነዚህም ቀኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ ማገልገል ይገባል እንጅ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ስለሚሞቱት ሰዎች የሙታን ግንዘትና የሐዋርያት ሥራ ወንጌላት የሙታን ፍትሐት በሆሣዕና በዓል ቀን ይነበብ እንጅ፡፡
ቁጥር 601፡ በጸሎተ ሐሙስ ጸሎተ ተአምኆ እግዚአ ሕያዋን የቡራኬ ጸሎት አይባልም (አይጸለይም)፡፡ ቅዳሜ ግን እግዚአ ሕያዋን ይባላል ፍትሐት ይፈታል፡፡ ከመሳለም በቀር ጸሎተ ዕጣንም ይጸለያል፡፡ በዕለተ እሑድ ግንዘት ማድረግ በፋሲካ ቀንም ማልቀስ አይገባም፡፡ ዳግመኛም በውስጧ በአርባ ጾም ከተድላ ከደስታ ወገን ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ መጋባት ክህነት መስጠት ክርስትና ማንሣት ከሹመትም ወገን ስለሚሞቱት ከመጸለይ በቀር ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ ይሞታል ተብሎ ለሚያስፈራው ግን ጥምቀተ ክርስትና ይደረግለታል፡፡
ቁጥር 602፡ ዐቢይ ጾም ስምንት ሱባዔ እንደሆነ በነገሥታት መጽሐፍ ተጻፈ፡፡ መጀመሪያው የክረምት መጨረሻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክረምት እንዳይደለ ይታወቃል መጨረሻው የበጋ መጀመሪያ ነው በየሳምንቱ አምስት ቀን መጾም ይገባል፡፡
ቁጥር 603፡ በብሉይ ሕግ በዓል በቅዳሜ በሐዲስ ሕግ በዓል በእሁድ ይብሉ ቅመማት የበዛበትን አይብሉ፡፡ የዓርብንና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት ከጥምቀት ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ፡፡
ቁጥር 604፡ ከእሁድና ከቅዳሜ በቀር ለእግዚአብሔር የሚታዘዙ ሰዎች ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሐዋርያት ጾም መጾም ይገባቸዋል፡፡

===============================================================

Monday, March 7, 2016

“ለሞት የተዘጋጀ በመድኃኒት አይድንም”

© በመልካሙ በየነ
የካቲት 25/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ሞትና ሕይወት በተቃርኖ የሚኖሩ ጥንዶች ናቸው፡፡ ሞት ካለ ሕይወት የለም፤ ሕይወት ካለም ሞት የለም፡፡ በእርግጥ የዘነጋሁት ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡ ሞት ሦስት ዓይነት እንደሆነ፡፡ የነፍስ ከሥጋ መለየት (የሥጋ ሞት)፣ በቁም ሳሉ የነፍስ ከእግዚአብሔር መለየት በኃጢአት በበደል (የቁም ሞት) እና ከሥጋ ሞት በኋላ የነፍስ ወደ ሲኦል መውረድ (የነፍስ ሞት/ዘላለማዊ ሞት) ናቸው፡፡ አሁን እኔ በርእሰ ጉዳዬ ላይ ያነሣሁት ሁለተኛውን ዓይነት ሞት ነው፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያው የሥጋ ሞት ለማንኛውም እኩል የተሰጠ ስለሆነ አያስጨንቀንም ሦስተኛውም ሞት ሞኞች የሚሞቱት መጀመሪያ ከሥጋ ሞት በፊት በሁለተኛው ሞት በቁም ሞት የሞቱ ከሆነ ብቻ ነው፡፡  በቁሙ ያልሞተ ሰው በነፍሱ አይሞትም፡፡ ስለዚህ መጠንቀቅ የሚገባን ሞት ሁለተኛው ሞት በመሆኑ ነው እንግዲህ ዛሬ እንደ ርእስ ያነሣሁት፡፡ ሕይወት ማለት አለመሞት ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሥጋችን ከነፍሳችን ሳትለይም በቁማችን ሞት ስላለብን ማለት ነው፡፡ አንዳንዶቻችን በሕይወት መኖር ማለት የነፍስና የሥጋችን አለመለያየት ወይም በሥጋ አለመሞት ይመስለናል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮማ ሞትና ሕይወት ተቃራኒ አይሆኑም ነበር፡፡ ከሥጋ ሞት በኋላም ሕይወት ስላለ አለመሞት ማለት ሕይወት ማለት አይደለም፡፡
ስለሞት እና ሕይወት ይህን ያህል ካልን ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስና ለዚህ ለቁም ሞት የተዘጋጀ ነፍሱን ለሞት ያዘጋጀ ምንም ዓይነት መድኃኒት አያድነውም ያልንበትን ምክንያት እንመልከት፡፡ የሰው ልጅ በሥጋው ሳይሞት ብዙ ውጣ ውረዶችን፣ ብዙ ፈተናዎችን፣ ብዙ ችግሮችን፣ ብዙ ክስተቶችን ፣ብዙ መከራዎችን፣ ብዙ ደስታዎችን ያሳልፋል፡፡ የሰው ልጅ ሕይወቱ አንዴ የሞቀ አንዴ የቀዘቀዘ፣ አንዴ የተቀደሰ አንዴ የረከሰ፣ አንዴ የተደላደለ አንዴ የጎራበጠ፣ አንዴ የለሰለሰ አንዴ የሻከረ፣ አንዴ የነጣ አንዴ የገረጣ፣ አንዴ ከፍ ከፍ ያለ አንዴ ዝቅ ዝቅ ያለ፣ አንዴ ደስ የሚሰኝበት አንዴ የሚከፋበት፣ አንዴ የሚስቅበት አንዴ የሚያለቅስበት፣ አንዴ የሚበላበት አንዴ የሚራብበት፣ አንዴ የሚጠጣበት አንዴ የሚጠማበት፣ አንዴ የሚነሣበት አንዴ የሚወድቅበት ነው፡፡ በዚህ መካከልም የሰው ልጅ ጽናቱ አምላክ እንደሰጠው ጻጋ መጠን ይለያያል፡፡ አንዳንዱ “ሁሉ ነገር ለበጎ ነው” የሚለው እንደ ኢዮብ ጻድቅ ከደስታው በፊት በመከራው ወቅት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው በመከራውም በደስታውም ፈጣሪውን የሚያመሰግን ነው፡፡እንዲህ ዓይነቱ  በጊዜውም ያለጊዜውም የሚጸና ሰው ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ “ሁሉ ነገር ለበጎ ነው ለካ” ይላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ደግሞ ሁሉ ነገር ለበጎ መሆኑን የተቀበለው መከራውን አልፎ ደስታ ስላገኘ ብቻ ነው፡፡ ከደስታው በፊት በመከራው ወቅት “ሁሉ ነገር ለበጎ ነው” የሚል አስተሳሰብ አልነበረውም፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በመከራውም ሆነ ከመከራው በኋላ በደስታው ወቅት ፈጣሪውን በማማረር ይጠመዳል፡፡ በመከራው ሰዓት ለእንደዚህ ዓይነቱ መከራ የጣልኸኝ ምን አድርጌህ ነው እያለ መከራው ለበጎ መሆኑን አይረዳም፡፡ በደስታው ሰዓትም ደስታውን ፈጣሪው እንደሰጠው ስለማይረዳ የሌሎችን ደስታ እየናፈቀ በእነርሱ ደስታ እየቀና እንደሌሎች ያለውን ደስታ ያልሰጠኸኝ ለምንድን ነው እያለ ፈጣሪውን ያማርራል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በመከራው ሰዓትም ሆነ በደስታው ሰዓት ፈጣሪውን አያመሰግንም አያማርርምም፡፡ ዝም ብሎ ብቻ የሆነውን ሁሉ የሚቀበል አለ፡፡ ዝናብ ሲወርድበት ዝም! ፀሐይም ሲያቃጥለው ዝም! ሲመቱት ዝም! ሲሰድቡት ዝም! ሲስቁበት ዝም! ሲንቁት ዝም! ሲጠግብ ዝም! ሲራብ ዝም! ሲጠማ ዝም! ሲጠጣ ዝም! ሲታመም ዝም! ሲድንም ዝም! ብቻ ሁልጊዜ ዝምታ! ዝምታው ግን ለምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ምናልባት ፈጣሪውን በውስጡ እያመሰገነ ወይም እያማረረ ይሁን አይሁን ለሌሎች በግልጽ አይታወቅም፡፡ በዚህ ምክንያት ሕይወታችን እና ሞታችን ይለያያል፡፡

እንግዲህ ሰው  በኃጢአት ሲቆሽሽ፣ በበደል ሲረክስ፣ ከፈጣሪው ሲለይ፣ ከአገልግሎት ሲርቅ፣ ከቅዱሳኑ በረከት ሲያጣ፣ ዕጣኑን ማሽተት ሲተው፣ ጸሎት ማድረስ ሲያቆም፣ መስገድ ሲዘነጋ፣ መጾም ሲረሳ፣ ማስቀደስ ሲያቆም፣ ኪዳን ማስደረስ ሲተው፣ ጸበል መጠጣት ሲረሳ ያን ጊዜ ሞተ እንለዋለን፡፡ በዚህ ሞት ያልነቃ ሰው በነፍሱም እንደሚሞት የተረዳ ነው፡፡ በእርግጥ እዚህ ጋርም ሁለት ዓይነት አስተሳሰቦች አሉብን፡፡ አንዳንዱ አውቆ የተደበቀ ነው አንዳንዱም ሳያውቅ የተጋለጠ ነው፡፡ ሳያውቅ ለዚህ ሞት የተጋለጠ ሰው ሲማር ሲሰበክ ሲያውቅ ሲመከር ይሻሻላል፡፡ አድርግ የተባለውን ሲያደርግ አታድርግ የተባለውን ሲተው ያን ጊዜ ቅድስና ይቀርበዋል በረከት ይጎበኘዋል፡፡ ይህ ሰው ሳያውቅ የታመመ ስለሆነ በመድኃኒት ለመታከም አይከብደውም፡፡ የሞተም ሳያውቅ  ስለሆነ ለመነሣት አይቸገርም፡፡ በዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ ኃጢአት የሚሠራው ተሳስቶ ስለሆነ ተፀፅቶ የመመለስ አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ለሞት የተዘጋጀ ስላልሆነ በመድኃኒት ታክሞ ለመዳን ጊዜ አይወስድበትም፡፡ ነገር ግን ለሞት የተዘጋጁ ሰዎች በመድኃኒት የማይድኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚጠፉና የሚያጠፉ አውቀው ነው፡፡ ለበደል ለኃጢአት የሚሮጡት በንስሐ ላለመመለስ ጭምር ወስነው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ከምግባር ሕጸጽነቱ ይልቅ የእምነት ሕጸጽነቱ ያመዝናል፡፡ የምግባር ሕጸጽን በንስሐ መድኃኒት ማከም ይቻላል የእምነት ሕጸጽን ግን የንስሐንም መድኃኒትነት ካለመቀበል ጋር የሚመጣ ስለሆነ ለማከም የሚያስችል መድኃኒት አይገኝለትም፡፡ የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና አማላጅነቷን፣ የመላእክትን ጥበቃ እና ምልጃ፣ የቅዱሳኑን ጸሎትና ልመና ምልጃ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ፈጣሪነት፣ የቤተክርስቲያንን ክብር ልዕልና ቅድስና፣ አእማደ ምሥጢራትን፣ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንን፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ወዘተ በመናቅና በማንቋሽሽ ላይ የተጠመዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሥርዓቷን ንደው እነርሱ እንደሚፈልጉት ለማድረግ የሚታገሉ ናቸው፡፡ ለሞት የተዘጋጁ ስለሆነም ተመክረው ተዘክረው አይመለሱም፡፡ ታክመው ለመዳን ፍላጎትም ዓላማም የላቸውም ምክንያቱም አውቀው የታመሙ ስለሆነ፡፡ በሽታችሁ ይህ ነውና በዚህ መድኃኒት ታከሙ ሲባሉ መድኃኒቱን እንደመድኃኒትነቱ አይቀበሉትም ምክንያቱም በሽታቸው ሌላ እንደሆነ ያውቃሉና፡፡ የምግባር ሕጸጽ ነው ብለን ብንመክራቸውና የዚህን መድኃኒት ብናዝዝላቸው በሽታቸው የእምነት ሕጸጽ እንደሆነ ራሳቸው ስለሚያውቁ መድኃኒቱን አይወስዱትም፡፡ ለምን በኦርጋን አንዘምርም? ለምን በልተን አንቀድስም? ለምን ሴቶች አይቀድሱም? ለምን ከነጫማችን መቅደስ አንገባም? ለምን ተመሳሳይ ጾታ አይጋባም? ለምን ኢየሱስን አማላጅ አንልም? ለምን ድንግል ማርያም አታማልድም አንልም? ቅዳሴው ረዝሟል ለምን አያጥርም? ጾም በዝቷል ለምን አይቀነስም? የሚሉ ጥያቄዎችን የሚጠይቁና የሚያስፈጽሙ የተሐድሶ መንፈስ የተጠናወታቸው ግለሰቦች ለሞት የተዘጋጁ ስለሆነ ለመዳን ቦታ የላቸውም፡፡ በዚህ በሽታ የተለከፉት አውቀው ስለሆነ መድኃኒት አይሹም፡፡ ቢመከሩ ቢዘከሩ አይሰሙም ምክንያቱም “ለሞት የተዘጋጀ በመድኃኒት አይድንም” እና ነው፡፡

Tuesday, March 1, 2016

New Ethiopian Orthodox Tewahedo Mezmur 2016- Mindaye Berhanu- Selam Leki

የሔዋን ቸልተኝነት

© በመልካሙ በየነ
የካቲት 9/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ሔዋንን ብዙ ጊዜ በተለያዩ ርእሶች ላይ አንሥተናታል፡፡ እዚህ ላይ ለማየት የምንሞክረው ቸልተኝነቷንና በቸልተኝነቷ የመጣባትን ርግማን ነው፡፡ ሔዋን በቸልተኝነት ለሌላ ሊነገር የማይገባውን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሕግ ክፉ ባልንጀርነትን ከእባብ ጋር መሠረተችና ምሥጢራቸውን ለእባብ አወጣች፡፡ እባብ ምሥጢራቸውን ከተረዳ በኋላ ዕፀ በለስን ወደ ሔዋን አፍ የሚጨምርበትን ጥበብ መፈለግ ቀጠለ፡፡ ይህ የሔዋን የመጀመሪያው ቸልተኝነት እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ የተባሉትን ዕፅ ለመብላት ሌላ ቸልተኝነትን አመጣባት፡፡ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው ያችን ዕፅ በበሉ ጊዜ የሞት ሞትን እንደሚሞቱ ሔዋን በሚገባ ታውቃለች፡፡ነገር ግን “ያችን ዕፅ በበላችሁ ጊዜእግዚአብሔር መልካምና ክፉውን የምታውቁ ያደርጋችኋል ጥበብንም ይገልጽላችኋል፤ አምላክም ትሆናላችሁ” የሚለውን የእባብ ክፉ ምክር በቸልተኝነት ተቀበለች፡፡ ያ ቀስ በቀስ የጎለበተው የሔዋን ቸልተኝነት አትብሉ የተባሉትን ዕፅ እንዲበሉ አድርጓቸዋል፡፡ የሔዋን ቸልተኝነት የወለደው ክፉ መዘዝከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ለመሸሸግ አበቃቸው፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ማምለጥ አልተቻላቸውም፡፡ ሁሉም ተጠየቁ አዳም በሔዋን ሔዋንም በእባብ አሳበቡ፡፡ ይሁን እንጅ ያ ቸልተኝነት ርግማን ማምጣትን አልተወም፡፡ ሁሉም እንደየድርሻቸው ርግመታቸውን ተቀበሉ፡፡ ርግማኑ ከእባብ ጀመረ“ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፡፡ በሆድህም ትሄዳለህ አፈርንም ሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ፡፡ በአንተና በሴቲቱ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” የሚለውን ርግማን እባብ ተቀበለ፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስተምሩት እባብ መልከ መልካም በአራት እግሩ የሚሄድ ጊደር የሚያህል እንስሳ ነበር ከተረገመ በኋላ ግን በልቡ የሚሳብ ሆኗል፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣ ሲመጣ እንዲህ ነውበአራት እግሩ የሄደውን በሆዱ እየተሳበ እንዲመለስ ያደርጋል፡፡ ቀጣይ የርግማን ሰለባ ሔዋን ናት፡፡ “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ በጭንቅ ትወልጃለሽ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፡፡ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” የሚል ርግማን ለሔዋን ደረሳት፡፡ለዚህ ነው ሴቶች ሲወልዱ በምጥ በልብ ጋር የሚወልዱት ከወለዱም በኋላ ፈቃዳቸው ወደ ባላቸው ይመለሳል፡፡ የመጨረሻው ርግማን ለአዳም እንዲህ ሲል መጣ “የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝኩህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርሷ ትበላለህ እሾህና አሜከላን ታበቅልብሃለች የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ፡፡ ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና” /ዘፍ3÷1-ፍጻ/እንግዲህ የሔዋን ቸልተኝነት ያመጣው ርግማን በጣም ከባድ መሆኑን ልብ ልንል ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቸልተኝነት የሞት ሞትን ወደ ሰው ልጅ ሁሉ ያመጣ ነው፡፡ሰነፎችንም ቸልተኛ መሆን ያጠፋቸዋልና እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን አዳምና ሔዋን በቸልተኝነታቸው ጠፉ፡፡ /ምሳ1÷32/ በገነት ሦስት ዕፅዋት ነበሩ እንዳይበሉት የታዘዙት፣ እንዲበሉት የታዘዙትና ብሉም አትብሉም ያልተባሉት ማለት ነው፡፡ ብሉም አትብሉም ያልተባሉት ዕፅ ዕፀ ሕይወት ይባላል፡፡ አትብሉ የተባሉትን ዕፅ ሳይበሉ ቢጠብቁት ኖሮ ከአንድ ሽህ ዘመን በኋላ ይህን ዕፀ ሕይወት በልተው ታድሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት ይሸጋገሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ዕፀ በለስን ከበሉ በኋላ ያን ዕፀ ሕይወት በልተው መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ እግዚአብሔር ከገነት አባረራቸው፡፡ ወደ ሕይወት የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ፡፡ አዳምና ሔዋን ተድላና ደስታ ከነበረባት ገነት ወጥተው ኀዘንና መከራ ወደበዛባት ምድር ወረዱ፡፡ ከእንስሳት ከአራዊት ጋር ከአጋንንትም ጋር ስትዋጋ ኑር ተብሎ ተፈረደበት፡፡ በገነት ሳለ ያከብሩት ይገዙለትም የነበሩ እንስሳት ሰባን አርደህ ብላን አልበህ ጠጣን ይሉት የነበሩት ሁሉ እንበላሃለን፣ እንወጋሃለን እያሉ ያስጨንቁት ጀመር፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት እንዲህ ነው እንስሳት አራዊቱን ሁሉ በጠላትነት ያስነሣል፡፡ አዳምም በዚህ የተነሣ እጅግ አለቀሰ ከዋሻ ዋሻ ከዱር ዱር ተንከራተተ፡፡ ይህን የተመለከተ የእግዚአብሔር መልአክ ደብር ቅዱስ ወደሚባል ተራራ ወስዶ በዚያ አኖረው፡፡ በዚህ ቦታ ተቀምጠው እጅግ እያለቀሱ እግዚአብሔርን ለመኑ ነገር ግን ልመናቸው ቅድመ እግዚአብሔር አልደርስ አላቸውና ከእህል ከውኃ ተለይተው ለየብቻ ሁነው ባሕር ውስጥ ገብተው ለ40 ቀን ያህል ሱባኤ ገቡ፡፡ ጠላት አሁንም 35ኛውን ቀን ጨርሰው 36ኛውን ሊጀምሩ ሲሉ የእግዚአብሔርን መልአክ መስሎ መጥቶ ጸሎታችሁ ተሰምቷልና ከባሕር ውጡ አላቸው፡፡ ሔዋን አሁንም ሌላ ቸልተኝነት ተፈጠረባት፡፡ አዳም ድሮ የፍጡር ቃል ሰምቼ ተጎድቻለሁና እግዚአብሔር ውጣ ካላለኝ በቀር አልወጣም ብሎ የመጣውን ጠላት ሲያባርር እርሷ ግን እግዚአብሔር እንኳንን ይህን ያህል ቀን ቆይተን ይቅርና በ1 ቀንስ ይቅር ይለን የለምን ብላ የጠላትን ምክር አሁንም ተቀበለች፡፡ በዚህም ምክንያት ሱባኤውን አቋርጠው ወጡከገነት ያስወጣቸውን ያን የቀደመውን ጠላታቸውን ባለማዎቅ ተከተሉት፡፡ ከእግረ ገነት ሲደርሱ ገብርኤል ነኝ ያላቸው እነርሱም መስሏቸው የተከተሉት ዲያብሎስ ከእንግዲህ ወዲያ ተስፋ የላችሁም ብሎ መጥፎ ሽታውን አሸተታቸው ክፉ መልኩንም አሳያቸው፡፡ አዳምም ደንግጦ ወደቀየምይራራ ጠላት ዲያብሎስም ቤት የሚያህል ድንጋይ አንሥቶ ጫነበት፡፡አዳም በሦስተኛው ቀን ቢነሣ ሥጋው ተቆርሶ፣ ደሙ ፈስሶ፣ አጥንቱ ተከስክሶ አገኘው ፍሬ ዕፅም አምጥቶ በደሙ ለውሶ መሥዋዕት አሳረገ፡፡ እግዚአብሔርም ተስፋ ሰጠው “ከሰማየ ሰማያት ወርጄ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀል ተሰቅዬ ሥጋዬን ቆርሴ ደሜን አፍስሼ ሞቼ ተነሥቼ ከሲዖል አወጣሃለሁ ከዲያብሎስም መከራ አድንሃለሁ” አለው፡፡እነርሱም ይህንን ተስፋ ሲጠብቁ ኖሩ፡፡ ከዚህ የምንረዳው የሔዋን ቸልተኝነት የከፋ ርግማንን በሰው ዘር ሁሉ ማምጣቱን ነው፡፡

የዮናስ ቸልተኝነት

© በመልካሙ በየነ
የካቲት 22/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ዮናስ ማለት የዋህ ማለት ነው፡፡ የሰራፕታዋ መበለት ልጅ ነው፡፡ ረሀብ በነበረ ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቤቷን በበረከት የሞላላት ናት፡፡በዚያም ወቅት ልጇ ዮናስ ሞተ ነቢዩ ኤልያስም ከሞት አስነሣው፡፡ ይህ ልጅ ሲያድግ እግዚአብሔር ወደ ታላቂቷ ከተማ ነነዌ በነቢይነት ሄዶ እንዲያስተምር አዘዘው፡፡ ዮናስ ግን ወደ ነነዌ መሄድን ቸል አለ፡፡ ነነዌ ሄጄ ኃጢአታችሁ ወደ እግዚአብሔር ደርሷልና እግዚአብሔር ከተማዋን ሊያጠፋ ነው እያልኩ ብሰብክና ከኃጢአታቸው ቢመለሱ እግዚአብሔር ምሕረቱ የበዛ ነው በዚያ ላይ እኔ ሐሰተኛ ነቢይ ልባል አይደለምን? ብሎ አሰበ አስቦም አልቀረ የነነዌን ጉዞ ቸል አለና ወደ ተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ከፍሎ መርከብ ውስጥ ገባ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አመጣና ታላቅ ማዕበል ሆነ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች፡፡ መርከበኞቹም ፈሩ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ መርከቢቱም እንድትቀልላቸው በውስጧ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በመርከቢቱ የነበረውን ሀብት ንብረታቸውን ሁሉ ወደ ባሕር ሲወረውሩ ያን ያህል የሚያስጨንቅ ፍርሐት ሲመጣባቸው ዮናስ ግን በመርከቢቱ ውስጠኛ ክፍል ተኝቶ ነበር፡፡ የመርከቡ አለቃ ዮናስን ተነሥተህ አምላክህን ጥራ ክፉ ማዕበል አስጨንቆናልና አለው፡፡ ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንደመጣባቸው ለማወቅ ዕጣ ተጣጣሉ ዕጣውም ለዮናስ ወጣ፡፡ ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህን ንገረን? ሥራህ ምንድን ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነሀ? ብለው በዮናስ ላይ የጥያቄ መዓት አወረዱበት፡፡ ዮናስም ሰማይንና ምድርን በፈጠረ እግዚአብሔር የሚያመልክ ዕብራዊ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ሞገዱ የተፈጠረውም በእርሱ ምክንያት እንደሆነና እንዲቆምላቸውም እርሱን ወደ ባሕር እንዲጥሉት ፈቀደላቸው፡፡ እነርሱም ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ ንጹሕም ደም በእጃችን ላይ እንዳታደርግ እንለምንሃለን አሉና ዮናስን ወደ ባሕር ውስጥ ጣሉት ባሕሩም ከመናወጥ ጸጥ አለ፡፡ሰዎቹም እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ መሥዋዕትንም አቀረቡ ስእለትንም ተሳሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን ለዮናስ በባሕሩ ውስጥ ሦስት ቀንና ሶስት ሌሊት ውጦ የሚያቆየውን ዓሣ አንበሪ አዘጋጅቶ ነበርና በዚያ ውስጥ አስገባው፡፡ከሦስት ቀን በኋላ ዓሣ አንበሪው ዮናስን የብስ ላይ ተፋው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል አሁንም ድጋሜ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ የምነግርህንም ስብከት ስበክላቸው” አለው፡፡ ዮናስም ተነሥቶ እንደእግዚአብሔር ቃል ወደ ነነዌ ሄደ ቸልተኝነቱን ተወ፡፡/ትንቢተ ዮናስን በሙሉ ተመለከት/ ዮናስ የየዋህነት ቸልተኝነት ነበረበት ያ ቸልተኝነቱ ደግሞ ወዳልታዘዘው አገር እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ የትም ቢሄዱ ከእግዚአብሔር መሠወር አይቻልምና ዮናስን እግዚአብሔር በጥበቡ መጀመሪያ እንዲሄድ ወዳዘዘው ቦታ ወሰደው፡፡ ነነዌንም አስተማረ እግዚአብሔርም ሊያመጣ የነበረውን መከራ መለሰላቸው፡፡ የሰዎች መዳን ሊያስደስተው ሲገባ ነቢዩ ዮናስ የራሱን ክብር ማለትም ሐሰተኛ ነቢይ እንዳይባል ብቻ ከእግዚአብሔር ሊርቅ መወሰኑ ጥሩ እንዳልነበር እንማራለን፡፡

የተከሰሰ ሁሉ ወንጀለኛ ነውን?

© በመልካሙ በየነ
የካቲት 20/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አንድ ወንድሜ ስለክስና ወንጀል እንዲሁም ስለወንጀለኛና ስለ ፍርድ ውሳኔ አሰጣጥ ያጫወተኝ ጫወታ ዛሬ በጣም ትዝ አለኝ፡፡ እርሱ ጥፋት ሠራም አልሠራም ብቻ በመከሰስ ይታወቃል በዚህም የተነሣ ብዙ ፍርድ ቤቶችን እና ብዙ ዳኞችን የማየት ዕድል አጋጥሞታል፡፡ እኔ ግን ፍርድ ቤት የሚባለውን ነገር እንዳያሳየኝ ነው ፈጣሪየን የምለምነው፡፡ ለምን መሰላችሁ እንዲህ የምለው ተከስሼ ለፍርድ ከቀረብኩ አጠፋሁም አላጠፋሁም የሚቀጣኝ እንጅ በነጻ የሚለቀኝ ዳኛ ያለ ስለማይመስለኝ ነው ግን ይቅርታ!
እኔ የሚመጣብኝ በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 27 ላይ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ የተከሰሰበት ወንጀልና የነሔሮድስና የነጲላጦስ ፍርድ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ከጲላጦስ ወደ ሔሮድስ ከሔሮድስ ወደ ጲላጦስ እርጥብ መስቀልን ተሸክሞ የተንገላታውና በመጨረሻም ለመስቀል ሞት ተላልፎ የተሰጠው ወንጅል ሰርቶ በደል ኖሮበት አልነበረም ዓለም ለቀማኞች፣ ለሐሰተኞች፣ ለወንጀለኞች፣ ስለሆነች እንጅ፡፡ ለዛም ነው ዓለም እውነትን ለመስቀል እውነትን ለመግደል እውነትን ለማሰቃየት ፍቅርን ለመስቀል ጠማማ ፍርዷን ለመፍረድ የተቻኮለች፡፡ የተከሰሰ ሁሉ በደለኛ የተከሰሰ ሁሉ ወንጀለኛ ነው ብላ ይሙት በቃ የምትፈርደዋ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስንም ስቀሉት ስቀሉት ስቀሉት በሚሉ አፎች ተሞልታ ያችን የመከራ ዕለተ አርብን አሳለፈች፡፡ ፍርድን የሚሹ አይሁዳውያን ለፍርድ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አቀረቡት ይህ ባልከፋም ነበር፡፡ ንጉሡ በቅንአት ተነሣሥተው ወደ ፍርድ አደባባዩ እንዳመጡት በሚገባ ያውቅ ስለነበር በርባንን ልፍታላችሁ ወይስ ኢየሱስን አላቸው ሕዝቡ ግን የቀማኞችን አለቃ በርባንን እንዲፈታላቸው አጥብቀው ጮኹበት፡፡ ኢየሱስን ምን ላድርገው ብሎ ንጉሡ ዳግም ጠየቃቸው ለፍርድ ያቀረቡት ሰዎች ራሳቸው ፈራጅ ሆኑና ይሰቀል ብለው በአንድ ድምጽ ተናገሩ፡፡ ንጉሡም ምን ጥፋት አግኝታችሁበት ነው አላቸው እነርሱ ግን አሁንም መልሳቸው ይሰቀል የሚል ብቻ ነው፡፡ ተመልከቱ የዓለምን ጉድ ጥፋቱ ምንድን ነው ለሚል ንጉሥ መልሷ ይሰቀል የሚል ነው ለስቅላት የሚያበቃውን ወንጀል መናገር አልቻለችም ምክንያቱም እውነትን ነውና ልትሰቅል የያዘችው ሐሰትን ከአፉ ማግኘት እንኳ አልቻለችም፡፡ ንጉሡ የኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ተሰቅሎ መሞት አልፈለገም ምክንያም የተከሰሰበት ነገር ለስቅላት ለሞት ሳይሆን ለሹመት ለሽልማት የሚያበቃ ነውና፡፡ ለዚህም ነው ንጉሡ እጁን ታጥቦ ከዚህ ሰው ደም በእውነት ንጹሕ ነኝ ብሎ የመሰከረው፡፡ ነገር ግን ከሳሾቹ ራሳቸው ፈራጆች ሆኑና ደሙ በእኛ ብቻ ሳይሆን ልጆቻችን ላይም ይደር ብለው ንጹሕ ክርስቶስን ለመስቀል ሞት አበቁት፡፡ አይሁድን የምጠይቃቸው ነገር ቢኖር ይኼው ነው፡፡ እናንተው ፈራጆች ከሆናችሁ ለምን መክሰስና በጲላጦስ አደባባይ ማቆም አስፈለጋችሁ? የንጉሡን ውሳኔስ መፈጸም ካለባችሁ ለምን ንጹሕ ክርስቶስን በነጻ አልለቀቃችሁትም? ወይስ ወደ ንጉሡ አቅርባችሁ ክስ መሳይ ነገር ያቀረባችሁት ለይስሙላና እንዲህ አደረጉ ለመባል ብቻ ነበር? እናንተው ከሳሽ እናንተው ወሳኝ እናንተው ገዳይ እናንተው ሁሉን ሰሪ ያደረጋችሁስ ማነው? በእውነት አይሁዳውያን እነዚህን ጥያቄዎችን በመለሱልኝ ኖሮ ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር፡፡
የወንድሜ ክስና ውሳኔም ከአይሁዳውያኑ የተቀዳ ነው፡፡ ወንድሜ አሁን የተከሰሰው ከሳሹና ወሳኙ ራሱ በሆነ አካል ነው፡፡ በማን አለብኝነት ተከሰሰ በማን አለብኝነት ተፈረደበት በማን አለብኝነት ተቀጣ፡፡ ለነገሩ የአገሬ ሰው ጨርሶታል እኮ “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ” ብሎታል፡፡ የቀማኞች ስብስብ ንጹሐንን ወደ ወኅኒ ይወረውራል፡፡ ቆይ ግን ለምን? እኛ ሰዎች እኮ ከእንስሳት የምንለየው በማሰባችን መሰለኝ ታዲያ ማሰቢያችን የት ሔደ? በገንዘብና በማንአለብኝነት ለወጥነው እንዴ? ወይስ የትም አይሔዱም ምንም አያመጡም ተብለን ይሆን? እንጃ አምላከ ሰማይ አምላከ ፀሐይ እያለልን የምንሔድበት የምናጣ ምንም የማናመጣ እንዳይመስላቸው፡፡ ዳኞቹ በከሳሾች ተጽእኖ ይደረግባቸዋል፡፡ ከሳሹ በፈለገው መልኩ ውሳኔ ካልሰጡ ዳግም ጉዳዩ እንዲታይ ያደርጉታል፡፡ ምን ዓይነት ፍርድ ነው ግን? ይህ የሚሆነው ግን አንተ ከሳሽ ስትሆን ሳይሆን ተከሳሽ ስትሆን ብቻ ነው፡፡ አንተማ ምን አቅም አለህና ነውና እንዲህ ብላችሁ ወስኑ ብለህ የምትከሰው፡፡ “ግን እኮ ያለማስተዋል ጉዳይ እንጅ እኔም እኮ የበላይ ሐላፊ ነኝ እነርሱ የሆኑትን ሁሉ መሆን የምችል ነበርኩ ግን ዕድሉን ለእነርሱ አሳልፌ የሰጠኋቸው ራሴው ነኝ፡፡ በታማኝነት በእውነትና በቅንነት ያለምንም አድልዎ ይሠራሉ ብየ ወንበር ላይ ያከበርኳቸው እኮ እኔው ራሴ ነኝ፡፡ አላስተውል ብለው እንጅ እኮ እኔ የምቀጣላቸው ሕግን ለማክበር እንጅ ትክክለኛ ውሳኔን ስለወሰኑብኝ አይደለም፡፡ ሕግ ከሌለ እኮ እሱም ወንበሯን ይለቅቃል እኔም የማደርገውን አደርጋለሁ፡፡” ይለኝ ነበር በፍርድ አሰጣጥ ሂደቱ የተማረረው ወንድሜ እውነት ነው፡፡ ቀበሌ ላይ ከተከሰስክ ወረዳው ቀድሞ እንዲሰማው ይደረጋል፡፡ ወረዳ ላይ አቤቱታ ብታቀርብ ማንም አይሰማህም አጠፋህም አላጠፋህም ጥፋተኛ ነው ተብለህ ወረዳ ድረስ ተናፍሶልሃላ፡፡
የተከሰሰ ሁሉ ወንጀለኛ ነው? አይደለም!!! 100% እርግጠኛ ነኝ አይደለም!!! ግን ይፈረድብሃል፡፡ ያሳዝናል!!! ታዲያ መቼ ይሆን ከከሳሹ ተጽእኖ ነጻ የሆነ ዳኛ ተፈጥሮ የምናየው፡፡ ከሳሹ አቅርቦህ ውሳኔው እንደ ከሳሹ ፍላጎት ካልሆነ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ዳኞች ተብለው ገለል ይደረጋሉ፡፡ ከሳሹ ማን ሲሆን መሰላችሁ ይህ የሚሆነው መ…..
(በሐሰት ተከሶ ከሳሹ ራሱ ለወሰነበት ወንድሜ!!!)