Monday, March 14, 2016

ዐቢይ ጾም (ክፍል 2)


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 4/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል አንድ ዐቢይ ጾም እንዴት እንደሚጾምና የዐቢይ ጾም የተለያዩ ስያሜዎች ምን እንደሆኑ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን አርባ ቀንና አርባ ሌሊትን ጾመ? የሚለውን ጥያቄ እንመልሳለን፡፡ መልካም ንባብ!
ማቴ4÷2 “፵ መዓልተ ወ፵ ሌሊተ ጾመ” አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ ይላል፡፡ አርባ መጾሙ ሰራዔ ሕግ በመሆኑ ጾምን የሕግ ሁሉ መጀመሪያ አድርጎ ጾመ፡፡ አንድም ጾምን ለሥራው መጀመሪያ አደረገ፡፡ መብላት ለኃጢአት መሠረት እንደሆነ ጾምም ለምግባር ለትሩፋት መሠረት ናት፡፡ ጾምን እንዲህ ይሏታል “እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብእ ወጥንተ ኵሉ ገድል ሰናይት” ጾም ማለት የጸሎት እናት የዝምታ እኅት የእንባ ምንጭ የመልካም ሥራ ሁሉ መጀመሪያ ናት፡፡ ስለዚህ አምላክም መጾሙ ለሥራው መጀመሪያ ለማድረግ ነው፡፡ አርባ (፵) መጾሙ ስለምን ነው ቢሉ ስለብዙ ነገር ፵ ጾሟል፡
1.  ቀድሞ አባቶቹ ነቢያት ፵ ፵ ጹመዋል ከዚያ ቢያተርፍ አተረፈ ብለው ቢያጎድልም አጎደለ ብለው አይሁድ እውነተኛዪቱን ደጊቱን ወንጌል ከመቀበል ወደኋላ ይሉ ነበር፡፡ ወደዚህ ምድር መምጣቱ ለቤዛ ዓለም ነውና ወንጌልን እንዲቀበሉ አባቶቻቸው ያደረጉትን አደረገ፡፡
2.  ሙሴ በ፵ ዘመኑ አንድ ዕብራዊ እና አንድ ግብጻዊ ተጣልተው ደርሶ ወገኑ ነውና ለዕብራዊው ረድቶ ግብጻዊውን ገድሎ በኆጻ ቀብሮታል፡፡ ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር ዕብራዊው የአዳም ግብጻዊው የዲያብሎስ ምሳሌ ነው፡፡
3.  ሙሴ ፵ ጹሞ ሕገ ኦሪትን ሠርቷል ጌታም ፵ ጾሞ ሕገ ወንጌልን ሠርቷል፡፡
4.  ሙሴ  ፵ ዘመን በምድያም ኑሮ እሥራኤላውያንን ከግብጽ አውጥቷቸዋል ጌታም አርባ ጹሞ ነፍሳትን ከሲኦል ባርነት የሚያወጣ ነውና፡፡
5.  የእሥራኤል ጉበኞች በ፵ ቀን ተመልሰዋል እርሱም የመንግሥተ ሰማያት ጉበኛ ነውና አርባ ጾሞ ነፍሳትን ከሲዖል የሚመልስ ነውና፡፡
6.  እሥራኤል በገዳም ፵ ዘመን ኑረው ምድረ ርስት ገብተዋል እናንተም ፵ ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ለማለት፤
7.  ነቢዩ ሕዝቅኤል በጸጋማይ ጎኑ (በግራ ጎኑ) ፵ ቀን ተኝቶ ስድስት መቶ ሙታንን አስነሥቷል እናንተም ፵ ብትጾሙ ትንሣኤ ዘለክብር ትነሣላችሁ ለማለት፡፡
8.  ዕዝራ ፵ ቀን ጹሞ መጻሕፍትን አጽፏል፡፡ ሌሎች ቀን ሲጽፉ ውለው ማታ ይመገቡ ነበር ዕዝራ ግን ቀን ያጻፈውን ማታ ሲያስበው ያድር ነበር፡፡ እናንተም ፵ ብትጾሞ ምሥጢር ይገለጥላችኋል ሲል፤
9.  እባብ አካሉ ሲያረጅ ሲደገድግበት ፵ ቀን ከምግብ ተከልክሎ ይሰነብታል ከዚያም በስቁረተ ዕጽ ወይም በስቁረተ እብን ሲሄድ ተገፎ ይወድቅለታል ይታደሳል፡፡ እናንተም ፵ ብትጾሙ ተሐድሶተ ነፍስ ታገኛላችሁ ሲል፤
10. አዳም በ፵ ቀን ያገኘውን ልጅነት አስወስዶ ነበርና ለአዳም እንደካሰ ለማጠየቅ፤
11. በ፵ ቀን ተስእሎተ መልክእ ለተፈጸመለት ሰው ሁሉ ሊክስ እንደመጣ ለማጠየቅ፣
12. ለአራቱ ባሕርያተ ነፍስ ዐሥር ዐሥሩን ለመካስ እንደመጣ ለማጠየቅ ባሕርየ ነፍስን ጨምሮ አምስት ቢባል ደግሞ ስምንት ስምንቱን ሊክስ እንደመጣ ለማጠየቅ፣
13.  በዚህ ጾም ፵ ሲጾም ተራበ አልሳሳም ተዋጋ ድል አልተነሣም ለአርአያ ነውና ጾሙ ጹሙ፣ ሠርቶ ሥሩ ለማለት ጾመ፡፡ ሌሎች እንደሚያደርጉት ሳይጾም ጹሙ ሳይሠራ ሥሩ አላለንም፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች ፵ ጾሟል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን አምስት ግብራት ፈጽሟል፡፡
1.  ጥምቀት፡- በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ መጠመቁ ነው፡፡
2.  ተአምኖ ኃጣውእ፡- ከተአማንያነ ኃጣውእ አንድ ሆኖ መቆጠር ነው፡፡
3.  ከዊነ ሰማዕት፡- በጲላጦስ ፊት ቆሞ አንሰ በእንተ ዝንቱ ተወለድኩ ወእንበይነ ዝንቱ መጻእኩ ውስተ ዓለም ከመ እኵን ሰማዕተ በጽድቅ ሎ መመስከር ነው፡፡
4.  ተባሕትዎ፡-፵ ቀን ከምግብ ተከልክሎ በገዳም መኖር ነው፡፡
5.  ምንኲስና፡- በድንግልና መኖር ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከረቂቅ የተገኘ ረቂቅ፣ ከማይራብ የተገኘ የማይራብ፣ ከማይዳሰስ የተገኘ የማይዳሰስ፣ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከሕይወት የተገኘ ሕይወት እንደሆነ ሲያጠይቅ፡
1.  ረቂቅ ዘእምረቂቅ (ከረቂቅ የተገኘ ረቂቅ) ሲያጠይቅ፡- በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ፡፡
2.  ዘኢይርኅብ እምዘኢይርኅብ (ከማይራብ የተገኘ የማይራብ) ሲያጠይቅ፡- ፵ ቀንና ፵ ሌሊት ጾመ፡፡
3.  ዘኢይትገሠሥ እምዘኢይትገሠሥ (ከማይዳሰስ የተገኘ የማይዳሰስ) ሲያጠይቅ፡- በባሕር ላይ ተራመደ፡፡
4.  ብርሃን ዘእምብርሃን (ከብርሃን የተገኘ ብርሃን) ሲያጠይቅ፡- ብርሃነ መለኮቱን በደብረታቦር ገለጸ፡፡
5.  ሕይወት ዘእምሕይወት (ከሕይወት የተገኘ ሕይወት) ሲያጠይቅ፡- የአራት ቀን እሬሳ አልዓዛርን አንሥቷል፡፡
“ወእምዝ ርኅበ” ከዚህ በኋላ ተራበ መራቡ ግን በፈቃዱ ነው እንጅ እንደእኛ ያለ ረኀብ አይደለም፡፡  እኛ ብንበላው ቁንጣን ብንተወው ድካም ቅጥነት ስልት ይሆንብናል፡፡ የእርሱ ረኀብ ከዚህ ረኀብ የተለየ የፈቃዱ ነው፡፡ ቅድም ከማይራብ የተገኘ የማይራብ ብለን ነበር አሁን ደግሞ ተራበ አለ አይጋጭምን ቢሉ አይጋጭም፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ እንደሆነ ለማጠየቅ አንድ ጊዜ ርኅበ አንድ ጊዜ ኢርኅበ ይላል፡፡ መራቡም ለአጽድቆተ ትስብእት ለካሳ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የሚፈታተነው ዲያብሎስ ቀረበ፡፡

በምን በምን ፈተነው? በቀጣይ ክፍል ጠብቁን፡፡ ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment