Tuesday, March 15, 2016

ለምን በምንፍቅና ውስጥ ተደበቁ?



© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 6/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እምነት ውስጥ ማመን እና መታመን የሚሉ ዐበይት ነገሮች አሉበት፡፡ ማመን ማለት ያላየነውን ያልጨበጥነውን ያልዳሰስነውን ነገር እንዳየነው እንደጨበጥነው እንደዳሰስነው አድርገን መቀበል ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር አምላክ ነው ስንል ሳናየው፣ ሳንጨብጠው ሳንዳስሰው እንዳየነው እንደጨበጥነው እንደዳሰስነው አድርገን ተቀብለን ነው፡፡ ሌሎችንም እንዲሁ ሳናይ ሳንዳስስ ሳንጨብጥ ነው አሉ ብለን የተቀበልናቸው፡፡ ገነት መንግሥተ ሰማያት ሲዖል ገሐነመ እሳት መላእክት አሉ ስንል በተመሳሳይ ሳናይ ሳንዳስስ ሳንጨብጥ ነው፡፡ መታመን ስንል ደግሞ ለማመናችን ተግባራዊ ምላሽ የምንሰጥበት ነው፡፡ እግዚአብሔር አለ ስንል ህልውናውን የምናምንበት ትእዛዙን በመጠበቅ ነው፡፡ አድርጉ ያለንን በማድረግ አታድርጉ ያለንንም ባለማድረግ ተግባራዊ ምላሽ ከሰጠን እሱ መታመናችንን ገልጸናል ማለት ነው፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት እነዚህ ሁሉ የመታመን ተግባራት ናቸው፡፡ ምግባራችን ወይም መታመናችን ግን ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ የበረታ አለ የደከመም አለ፡፡ ድካምህ ግን ከደካማነትህ ባለፈ ወደ እምነት ሕጸጽ ሊወስድህ አይገባህም፡፡ ብዙዎች ወደ ምንፍቅና የሚሄዱበት ነገር ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በመሆኑም ብዙዎች ለምን በምንፍቅና ውስጥ ተደበቁ? የሚለውን ትልቅ ጥያቄ መመለስ ተገቢ በመሆኑ ወደእሱ እናምራ መልካም ንባብ!
ብዙዎች ለምን በምንፍቅና ውስጥ ተደበቁ? ለሚለው ዐቢይ ጥያቄ በርካታ መልሶችን መስጠት እንችላለን፡፡ ዋናዋና የሚባሉት ግን የሚከተሉት ናቸው፡-
1.  መታመን አለመቻል
2.  ገንዘብን መውደድ
3.  ዓለምን መናፈቅ
4.  አቋራጭ ጽድቅን መሻት ናቸው፡፡ እነዚህን አራት ነጥቦች በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡
v  መታመን አለመቻል፡- በእምነታችን ውስጥ መታመን መንፈሳዊ ግዴታችን ነው፡፡ በተዋሕዶ እምነት ውስጥ አባል የሆነ ሰው ሁሉም ሰው ሊጾማቸው የሚገባቸውን ጾሞች እስከታዘዘው ሰዓት ድረስ መጾም የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ለምሳሌ አርብና ረቡዕን እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጹሙ ይላል፡፡ ዐቢይ ጾምን ደግሞ የመጀመሪያውን ሳምንት እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ከሕማማት አስቀድሞ ያለውን እስከ አሥራ አንድ ሰዓት የሕማማትን ሳምንት ደግሞ እስከ አንድ ሰዓት እንድንጾም ታዝዘናል ይህን መፈጸም የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ ስግደትም ምጽዋትም ጸሎትም ይጨመርበታል፡፡ ጠዋት ተነሥቶ መብላት ሆዱ አምላኩ የሆነበት ሰው ግን ይህን ማድረግ ይከብደዋል፡፡ ነገር ግን ካልቻልን ማለትም የታወቀ ደዌ ካለብን አምላክ አያስገድደንም፡፡ እኛ የምንጾመው እኮ በዚያች ጾማችን ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን ብለን አይደለም መታመናችንን ለማሳየት መገዛታችንን ለማረጋገጥ ነው እንጅ፡፡  ስለዚህ የቻልነውን ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል ብዙዎች ግን ጾም ጸሎት ስግደት ምጽዋት ወደሚቀልበት እንዲያውም ጭራሽ ስሙም ወደማይነሣበት ምንፍቅና ራሳቸውን ይወስዳሉ፡፡ መጾም አለመቻል፣ መስገድ አለመቻል፣ መጸለይ አለመቻል በአጠቃላይ መታመን አለመቻል እምነትህን እንድትለውጥ ሊያደርግህ አይገባም፡፡ ራስህን ከኅሊና ወቀሳ ነጻ ለማድረግ ብለህ እምነትህን ለመለወጥ አትሻ፡፡ ከዚያስ የቻልከውን ያህል እየሠራህ “አንተ ተአምር ድካሞ ለሰብእ” የሰውን ድካም አንተ ታውቃለህ እያልህ ብትጸልይ ይሻልሃል፡፡ አምላከ ቅዱሳን የእኛን ድካም ያውቃል የእኛን ድካም ይረዳል ስለሆነም እርሱን አላመልክህም ብሎ ከመኮብለል ይልቅ ድካሜን አይተህ ማረኝ ይቅር በለኝ ብንለው የተሻለ ነው፡፡ በብዛት ለሰዎች የምንፍቅና መሠረታቸው ጾም ነው፡፡ ታዲያ ጾሞ ጹሙ ያለንን አምላክ በመጾም ካልመሰልነው መታመናችን እርሱን ማምለካችን እርሱን መውደዳችን በምን ይታወቃል? በሕክምና ጊዜ ለሥጋዊ ፈውስ ብለን ይህን ይህን አትብሉ ተብለን ስንከለከል እናደርገው የለም እንዴ? ታዲያ ለዘላለማዊ የነፍስ ድኅነት ጹሙ ስንባል ለምን እንሰቀቃለን? እውነት ነው የምላችሁ አንድ ቀን ሞክሩት አይደለም እስከዘጠኝ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ እንኳ እንድትቆዩ አምላክ ብርታቱን ይሰጣችኋል፡፡  አምላክን አበርታኝ እንበለው እርሱ ያበረታናል፡፡ ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ምንም ይፈጠር ምን መጾም ባለመቻላችን፣ መስገድ መጸለይ ባለመቻላችን እምነታችንን ልንለውጥ አይገባንም፡፡ ከዚያስ እምነታችንን ይዘን አለመጾም አለመጸለይ አለመስገድ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ቀን አምላክ ብርታቱን ጽናቱን ሰጥቶ ለንሥሐ ያበቃናልና ፡፡
v  ገንዘብን መውደድ፡- ከሦስቱ አርስተ ኃጣውእ መካከል አንዱ ፍቅረ ንዋይ ገንዘብን መውደድ ነው፡፡ ጌታ በወንጌል እንዳስተማረን ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻላችሁም ያለን ገንዘብን ነው፡፡ እንግዲህ ገንዘብ እንደ አንድ ጌታ ነው የተቆጠረው፡፡ ከውጭ እርዳታ እየለቃቀመ ገንዘብ በሚያከፋፍለው እምነት ውስጥ ብዙዎች ራሳቸውን ደብቀዋል፡፡ “”ገንዘቡን ላግኝ እንጅ እኔ ምን ቸገረኝ” በሚል የከሰረ አስተሳሰብ ብዙዎች ለገንዘብ ሲሉ ዕንቁ የሆነች ተዋሕዶ እምነታቸውን ትተው ኮብልለዋል፡፡ ገንዘብ ያው ገንዘብ ነው ስታገኝም ስታጣም እኩል የሚያስጨንቅ ነው፡፡ ሠርተህ መለወጥ ሠርተህ ማግኘት አልቻል ሲልህ እምነትህን ሸጠህ ገንዘብ ልታጠራቅም አይገባህም፡፡ ከገንዘብ በፊት የሚቀድመው እምነት ነው፡፡ ለድቃቂ ሳንቲም፣ ለእራፊ ጨርቅ ብለህ እምነትህን የምትለውጥ ከሆነ በዓለም ካሉ ከንቱዎች መካከል አንዱ አንተ ነህ፡፡
v  ዓለምን መናፈቅ፡- በተዋሕዶ እምነት ስትኖር ሁሉ ነገርህ ሰማያዊ ነው፡፡ አስተሳሰብህ ሰማያዊ፣ አነጋገርህ ሰማያዊ፣ አለባበስህ ሰማያዊ፣ አኗኗርህ ሰማያዊ፣ ዜማህ ሰማያዊ፣ ጸሎትህ ሰማያዊ ነው፡፡ ብዙዎች ግን ዳንኪራ ይናፍቃቸዋል፣ መዝፈን መጨፈር መብላት መጠጣት መስከር መወላገድን፣ ዝሙት መዳራትን ይሻሉ፡፡ ስለዚህ ይህን በነጻነት ወደምታገኝባቸው እምነትን ሽፋን ወዳደረጉ ተቋማት ለመጓዝ አትቸኩል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጉዳታቸው እንጅ ጥቅማቸው አይመዝንም፡፡ መናፍቃኑ አዳራሽ ላይ ሴቶች ዕርቃናቸውን ስታይ ልብህ ሊደሰት ይችላል፣ አጠገብህ ቁጭ ብላ ደረቷን ገልጣ ጡቶቿን አፍጥጣ ስታሳይህ ልትማረክ ትችል ይሆናል፡፡ ይህን ለመመልከት በዚህ ለመደሰት በዚህ ለመርካት ምንፍቅናን መምረጡ ጅልነት ካልሆነ በቀር ምን ሊባል ይችላል? ይህ እኮ ዓለም ውስጥም አስፓልት ላይ ወጥተህ ስትንቀሳቀስ የምትመለከተው ከንቱነት ነው፡፡ እምነት ማለት እኮ ዘላለማዊ ነው ዓለም ደግሞ ታልፋለች ትጠፋለች ትለወጣለች፡፡ ስለዚህ ሽህ ጊዜ ዓለማዊ ሁን እንጅ እምነትህን ለውጠህ በመናፍቃን አዳራሽ ያለውን ርኩሰት አትሻ፡፡ እነርሱ አዳራሽ ውስጥ እንደገባህ አንድ ፍጹም ዓለማዊ የሆነች ሴት ትመደብልሃለች ወንጌልን የምታስተምርህም ከአንተ ጭን ላይ ቁጭ ብላ ነው፡፡ በፍቅር ልብህን በመስረቅና በማማለል እዛው ስለእሷ ፍቅር ስትል እንድትኖር ይፈልጋሉና የምትመደብልህ ሴት እንዲህ ያለች ናት፡፡ ታዲያ ይኼ ሰማያዊ ነውን? አይደለም፡፡ ስለዚህ ራስህን ከዚህ ዓለማዊ ርኩሰት ልትጠብቅ ያስፈልጋል፡፡ መዝሙር የሚሉትን ዳንኪራ እና ጭፈራ አትናፍቅ፡፡

v  አቋራጭ ጽድቅን መሻት፡- መናፍቃን በተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች ላይ ተመሥርተው በአቋራጭ መጽደቅን ይሻሉ፡፡ “ኢየሱስ ያድናል፣ ኢየሱስ ጌታ ነው፣ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” በማለት ገነት እንገባለን ብለው ያስባሉ፡፡ ተዋሕዶን ሲተቹ ምን ይላሉ መሰላችሁ “አንድ መሪጌታ ነበር… አንድ ቄስ ነበር…. አንድ ዲያቆን ነበር…. አንድ መነኩሴ ነበር…. ነገር ግን ስለመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስጠይቀው ምእራፍና ቁጥር ማዎቅ አልቻለም፡፡ እኛ ግን ምእራፍና ቁጥር እንነግራቸዋለን እነርሱ አያነቡም እኛ ግን ጌታ ይባረክ ምሥጢሩን ገልጾልን ጸጋውን አብዝቶልን ሁሉን እናውቀዋለን” ይላሉ፡፡ በእውነት ማነው ጸጋ የለሹ? አለማዎቅ ጥፋት አይደለም አለማዎቅን አለማዎቅ ግን በጣም ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ መናፍቃኑ ትልቁ ችግራቸው አለማወቃቸውን አለማወቃቸው ነው፡፡ ለመዳን አቋራጭ መንገድ የተጠቀመ ማነው? መናፍቃኑ አይደሉም እንዴ? በእውነት የእነርሱን ያህል ጥቅስ መጥቀስ ያቃተው የትኛው መሪጌታ፣ የትኛው ቄስ፣ የትኛው ዲያቆን፣ የትኛው መነኩሴ ነው? እንዴ 81 መጽሐፍ ቅዱስ በዝቶባቸው ከ66 ውጭ ፍንክች አንልም ያሉ እነማን ናቸው? አዋልድ መጻሕፍትን ገድላትን ድርሳናትን ተአምራት አንቀበለም ያሉት እነማን ናቸው? እነዚህ መጻሕፍትን ለመሸምደድ ስላልቻሉ ይሆንን? የእኛ ሊቃውንትማ አንድ ጥቅስ ሮሜ 8÷34 ን ብቻ እንደ ቴፕ የሚያጠነጥኑ አይደሉም እኮ፡፡ ከመናፍቃኑ 66 መጽሐፍ ቅዱስ ባለፈ 81 መጽሐፍ ቅዱስን ምንባቡን ከነትርጓሜው፤ ቅዳሴውን፣ ድጓውን፣ ጾመ ድጓውን፣ ሰዓታቱን ዜማውን ከነምልክቱ፣ ድርሳናትን እና ገድላትን ተአምራትን ሁሉ በቃላቸው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ወዴት ጠጋ ጠጋ ነው፡፡ አቋራጭ ጽድቅን የሚሻ መናፍቅ በ66 መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ ይከራከራል፡፡ መላእክትን አንቀበልም፣ ድንግል ማርያምን አንቀበልም የሚሉ እነማን ናቸው? በአቋራጭ መዳን የሚፈልጉት አይደሉምን? ቅዱሳንን ስናከብር የማይወዱት እነርሱም ማክበር የማይሹት እኮ የእነርሱን ክብር የተሻሙባቸው ስለሚመስላቸው ነው፡፡ በጣም ክብር ፈላጊዎች ናቸው እነርሱ በጸሎታቸው እንፈውሳለን እናድናለን ይላሉ ቅዱሳኑ ግን ይህን ማድረግ አይችሉም በእነርሱ ቤት፡፡ ያሳዝናል ምን ጅልነት እና አለማስተዋል ነው? አብዛኞቹ አቋራጭ ድኅነት ፈላጊዎች ናቸው፡፡ ልጄ ካንሰር ታምማ ነበር፣ እናቴ የወገብ አጥንት መንሸራተት ነበረባት፣ አባቴ መራመድ አይችልም ነበር ወዘተ ብቻ የሌለ ልቦለዳዊ ገጸባሕርይ ይፈጥራሉ ከዚያሳ ከዚያማ ጸበል ብንወስዳቸው መዳን አልቻሉም ፣ ብናቆርባቸውም፣ መፈወስ አልቻሉም፣ እምነት ብንቀባቸውም አልተሻላቸውም ከዚያም ወደዚህ አመጣናቸውና ፓስተሩ ጸሎት ሲያደርጉላቸው ሙሉ በሙሉ ዳኑ የሚል የፈጠራ ምሥክርነት ይሰጣሉ፡፡ በጣም የሚያስቀኝ የሁልጊዜ ተረታቸው ቢኖር ይህ ብቻ ነው፡፡ ጸበል፣ እምነት፣ ቁርባን ያላዳነውን በሽታ ፓስተሩ ጸልዮ አዳነው አቤት ቀልድ፡፡ እሽ ይዳን መቼም የአምላክ ድንቅ ሥራ ብዙ ነው ጠንቅዋይስ ያድናል እያሉ የሚሰግዱ አሉ አይደል፡፡ እንደጠንቅዋዩ ሁሉ ፓስተሩም ያድናል ይፈውሳል እንበል የሚድነው ግን ከነፍስ በሽታ ነውን? አይደለም፡፡ ሁሉንም ስትሰሟቸው የሚመሰክሩት ሁሉ የሥጋ ደዌ ነው፡፡ ጸበል አያድንምን? ያድናል፤ ቁርባን አያድንምን? ያድናል፤እምነት አያድንምን? ያድናል፡፡ ግን ትእግሥትና ጊዜ እምነትና ጽናት ይጠይቃል፡፡ ግን እኮ ደግሞ የግድ ሁሉም በሽታ መዳን የለበትም፡፡ ምክንያቱም እነ ጳውሎስና ጴጥሮስ በጥላቸው ድውይ እየፈወሱ እነርሱ ግን በሽታ ነበረባቸው፡፡ መድኃኒቶች ራሳቸው በሽታ ነበረባቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትእግሥት ስናጣ አቋራጭ ድኅነትን አቋራጭ ጽድቅን መፈለግ አያስፈልገንም ኢዮብን አትዘንጉ እንጅ ወገኖቼ፡፡ የሰጠኸኝን ውሰድ እንበለው እኛ ምን አገባን አምላክ የፈቀደውን ቢያደርግ፡፡ አብዛኛው የመናፍቃኑ አባላት ሲጠየቁ የሚመልሱት ይህንን ነው እንዲህ ተደርጎልኝ እንዲህ ተፈውሶልኝ ወዘተ የሚል የማይረባ ትርኪ ምርኪ፡፡ ቅዱሳኑንም አማላጅ አንላቸውም የሚሉት ለዚሁ ነው፡፡ እኛው ራሳችን በአቋራጭ ፈጣሪችንን ማናገር ስለምንችል ማንንም አማልዱን አንልም ይላሉ፡፡ በቃ በአቋራጭ ራሳቸውን ጻድቅ አድርገውታል፡፡ መድረክ ላይ ወጥቶ መንፈራፈር፣ መንፈስ ነው እያሉ መውደቅ ጽድቅ ነው ብለው ጽፈውታል፡፡ መውደቅ ጽድቅ ከሆነ ታዲያ ማን ሞኝ አለ በጾም በጸሎት በስግደት በምጽዋት የሚንገላታ? እነዚህ የተቀደሱ ተግባራት መንገላታት ናቸው ብለው ካመኑ ማለት ነው፡፡ እናንተ ግን ወገኖቼ አደራ አደራ አደራ አቋራጭ መንገድን አቋራጭ ጽድቅን ምርጫችሁ አታድርጉ ምክንያቱም ያ መንገድ የጥፋት ነውና!!! 

No comments:

Post a Comment