ዐቢይ ጾም (ክፍል 1)
© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 2/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ይህ ጾም ዐቢይነቱ
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው በመሆኑ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ
ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ ወደ ገዳም ሄደ ገዳሙ ገዳመ ቆርንቶስ ነው፡፡ ይህን ማድረጉ ወደዚህ ምድር በሥጋ የተገለጠ ለአርአያ ነውና
እናንተም እንደተጠመቃችሁ ሳትውሉ ሳታድሩ ወደ ገዳም ሂዱ ሲል ነው፡፡ አንድም ከዚህ ጾም በኋላ የሚያስተምር ነውና እናንተም ጾምን
የሥራችሁ ሁሉ መጀመሪያ አድርጉ ሲል ነው፡፡ ወደዚህ ገዳም የወሰደው ፈቃዱ ነው መንፈስ ወሰደው የሚልም አለ፡፡ ነገር ግን መንፈስ
ወሰደው ብንል ሰማዕታትን ወደ ደም ጻድቃንን ወደ ገዳም አስጨክኖ እንደሚወስዳቸው ያለ መንፈስ አይደለም በፈቃድ ከመንፈስ ቅዱስ
ጋር አንድ መሆናቸውን መናገር ነው እንጅ፡፡ የወልድ ፈቃድ የመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ነውና በፈቃዱ በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ
ገዳም ሄደ፡፡ ወደዚህ መምጣቱ ለመፈተን አስቦ አይደለም እፈተናለሁ ብሎ አስቦ ሄዶ ቢሆንስ እዳ በሆነበት ነበር ነገር ከሄደ ዘንድ
ሰይጣን ሊፈትነው ይቀርባል እርሱም ጾሩን እየቀለበ ይሰብርበታል፡፡ ዲያብሎስም በሦስት ዐበይት ኃጣውእ ይፈትነዋል እርሱም ድል ይነሣዋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስም በጾር መፈተኑ እማርበታለሁ ብሎ አይደለም፡፡ መከራውንና ፈተናውንም ሽቶ አላመጣውም፡፡ እነዚህ የኃጢአት ሁሉ
የበላይ ናቸው እነዚህን ያሸነፈ ሰው በሌሎች አይሸነፍምና ትልልቅ ኃጢአቶች ተብለዋል፡፡ እነዚህም ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ
ናቸው፡፡ እነዚህን በሌላ ክፍል እንመለከታቸዋልን፡፡ አዳም ከዚህ ዓለም አፍአ በምትሆን ገነት ድል ተነሥቶ ነበርና እርሱም ከዚህ
ዓለም አፍአ በምትሆን ገዳም እነዚህን ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል ነሳቸው፡፡ ድል መንሳቱም በሥጋው ነው እንጅ በመለኮቱ አይደለም
በመለኮቱ ድል ነስቶ ቢሆን ኖሮስ ባልተደነቀም ነበር፡፡ በመለኮቱማ ዲያብሎስስ ሊቀርበው እንዴት ይቻለው ነበር?
ወደ ገዳም የሄደበት
ሌላም ምክንያት አለው፡፡ ለወጣንያን (ለጀማሪዎች) ወደ ገዳም መሄድ ፈተና ይቀላልና ለወጣንያን አብነት ለመሆን አንድም ለፍጹማን
ለበቁት ጾር ይጸናልና ለእነርሱ አብነት ለመሆን ይሄዳል፡፡ ይህ ጾም የተለያዩ መጠሪያዎች አሉት፡፡
1. ዐቢይ ጾም፡- ስያሜው ትልቅ ጾም እንደ ማለት ነው፡፡ አምላካችን
ጾሞ ጹሙ ብሎ ያሳየን ነውና ትልቅ እንለዋለን፡፡ አንድም ሦስቱ ዐበይት (አርእስተ) ኃጣውእ ድል የተነሡበት ነውና፡፡ አንድም አምላክ
የሥራው ሁሉ መጀመሪያ አድርጎታልና ዐቢይ (ትልቅ) እንለዋለን፡፡
2. ጾመ ኢየሱስ፡- ሌሎችን ጾሞች በጾሟቸው ሰዎች መሠረት አድርገን
ጾሞ ነቢያት፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ነነዌ እያልን እንደምንጠራቸው ሁሉ ይህንንም ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ከዘረጋ ሳያጥፍ
ከቆመ ሳይቀመጥ እረፍትን ሳይሻ ጾሞታልና ጾመ ኢየሱስ እንለዋለን፡፡
3. ጾመ ሁዳዴ፡- ሁዳድ ማለት ሰፊ የመንግሥት እርሻ ቦታ ማለት
ነው በዚህ እርሻ ቦታ ላይ ልጅ አዋቂ፣ ሴት ወንድ፣ ወጣት አዛውንት፣ ደካማ ብርቱ ሳይለይ ሁሉም በሥራ ይሳተፍበታል፡፡ እንደዚሁም
ሁሉ በዚህ ጾም ሁሉ ይሳተፋል ለሁሉ ነውና ጾመ ሁዳዴ ተብሎ ይጠራል፡፡
4. ጾመ አርባ፡- ይህ ስያሜ በጾመው የቀን ብዛት የተሰጠ ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት የጾመው ጾም በመሆኑ ጾመ አርባ ይባላል፡፡
5. ጾመ ሙሴ ፡- ይህ ደግሞ ቅዱስ ያሬድ በዘወረደ ሰኞ ዕዝል ከመዝ
ይቤ ሙሴ . . . ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት . . . እያለ በጾመ ድጓው ስለ ዘመረ ጾመ ሙሴ ይባላል ፡፡
6.
በዓተ ጾም ፡- ይህም ማለት የጾም መግቢያ፣ መባቻ ወይም ጾሙ የሚሰፍርበት በዓት
ማለት ነው፡፡
እኛ ይህንን ጾም
እንዴት እንጹመው የሚለውን ከፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ላይ እንመልከተው፡፡
ቁጥር 602፡ ዐቢይ ጾም ስምንት ሱባዔ እንደሆነ በነገሥታት መጽሐፍ ተጻፈ፡፡
መጀመሪያው የክረምት መጨረሻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክረምት እንዳይደለ ይታወቃል መጨረሻው የበጋ መጀመሪያ ነው በየሳምንቱ አምስት ቀን
መጾም ይገባል፡፡
ቁጥር 575፡ ጾመ አርባ በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን መጀመሪያውም ከሰንበቶቹ
ሁለተኛ የሆነው ሰኞ ነው፡፡ መጨረሻውም ከፍሥህ አስቀድሞ ባለው በዕለተ ዓርብ ነው፡፡ ይህም ከፍሥህ ሱባዔ በኋላ ያለ ሱባዔ እንደሆነ
ያስረዳል፡፡ ከዐቢይ ጾም በኋላ የከበረ ሰሙነ ሕማማትን ትፈጽሙ ዘንድ ትጉ፡፡
ቁጥር 596፡ ክብርት በምትሆን በአርባ ጾም በመጀመሪያው ሱባዔ ፀሐይ እስኪገባ
ድረስ ይጹሙ፡፡ የመጀመሪያው ሱባዔ ካለፈ በኋላ እስከ 11 ሰዓት ድረስ ይጹሙ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ግን ኮከብ እስኪወጣ ድረስ ይጹሙ፡፡
በእነዚህም ወራቶች አያጊጡ፡፡
ቁጥር 578፡ በሊህ በስድስቱ ቀኖች (በሰሙነ ሕማማት) ከቂጣ ከጨው ከውኃ
ብቻ በቀር አይብሉባቸው፡፡ በሊህ ቀኖች ከወይን ከሥጋ ተለዩ የኀዘን ቀኖች ናቸውና የደስታ ቀኖች አይደሉም፡፡ዓርብንና ቅዳሜን ግን
ሁለቱንም በአንድነት ጹሟቸው፡፡ የሚችል እስከ ሌሊቱ ዶሮ ጩኸት ጊዜ ድረስ ምንም ምን አይቅመስባቸው ሰውየውም ሁለቱን ቀኖች በአንድነት
መጾም ባይቻለው ግን የቅዳሜን ጾም ይጹም፡፡
ቁጥር 589፡ ዐቢይ ጾምንና ዓርብን ረቡዕን የማይጾም የታወቀ ደዌ ያለበት
ካልሆነ በቀር ካህን ከሆነ ይሻር ሕዝባዊ ቢሆንም ይለይ፡፡
ቁጥር 590፡ ካህን ሰሙነ ሕማማትን ቀንና ሌሊቱን ሳያስተካክል አስቀድሞ
ቢያውል ይሻር፡፡ ከሕማማት ቀጥላ ከምትሆን ከቅዳሜ ስዑር በቀር እሑድንና ቅዳሜን የጾመ ካህን ቢኖር ይሻር፡፡
ቁጥር 591፡ በዐቢይ ጾም የሰማዕታትን በዓል ልናከብር አይገባንም፡፡ የሰማዕታት
መታሰቢያ በእሁድ በቅዳሜ ይሁን እንጅ፡፡
ቁጥር 592፡ በአርባ ጾም ሠርግ ማድረግ አይገባም ሴትም በወለደች ጊዜ ሰውን
ወደ መጠጥ ቤት መጥራት አይገባም፡፡
ቁጥር፡ 593፡ ከካህናት ወገን ማንም ቢሆን በአርባ ጾም በዓርብና በረቡዕም
ጾም ወይን መጠጣት አይገባውም ወደ መዋት (ውሽባ ቤት) አይግባ፡፡ በዐቢይ ጾም ወራት ሰው ከሚስቱ ጋር አይተኛ፡፡
ቁጥር 597፡ ሴቶችም ጌጣቸውን ይተው፡፡ ሁሉም ለእያንዳንዱ በአርባ ጾምና
በሰሙነ ሕማማት መጠበቅ ይገባዋል ድኅነታችንና የኃጢአታችን ሥርየት በእነርሱ ነውና፡፡ ይኸውም ሥራ አንዱስ እንኳ በአርባ ጾም ወራት
በምንጣፍ ፈጽሞ እንዳይገናኝ ከጋብቻ ሕግ የወጣ ነው፡፡ ክብርት በምትሆን በሕማማት ወራት ይህችን ኃጢአት የሚሠራት ሰው ወዮለት፡፡
በአርባ ጾም በተድላ በደስታ ፈቃዳችንን ካደረግን ትንሣኤውን ባየን ጊዜ ተድላ ደስታችን ወዴት አለ?
ቁጥር 599፡ በተባሕትዎ በትሕትና አርባ ቀን ጾምን ይጹሙ፡፡ ከጥሉላት መከልከል
ይገባል፡፡ አያግቡም፡፡
ቁጥር 600፡ በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሣት ክህነት መስጠት ለሞቱ ሰዎች
መጸለይ አይገባም፡፡ በእነዚህም ቀኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ ማገልገል ይገባል እንጅ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ስለሚሞቱት ሰዎች
የሙታን ግንዘትና የሐዋርያት ሥራ ወንጌላት የሙታን ፍትሐት በሆሣዕና በዓል ቀን ይነበብ እንጅ፡፡
ቁጥር 601፡ በጸሎተ ሐሙስ ጸሎተ ተአምኆ እግዚአ ሕያዋን የቡራኬ ጸሎት
አይባልም (አይጸለይም)፡፡ ቅዳሜ ግን እግዚአ ሕያዋን ይባላል ፍትሐት ይፈታል፡፡ ከመሳለም በቀር ጸሎተ ዕጣንም ይጸለያል፡፡ በዕለተ
እሑድ ግንዘት ማድረግ በፋሲካ ቀንም ማልቀስ አይገባም፡፡ ዳግመኛም በውስጧ በአርባ ጾም ከተድላ ከደስታ ወገን ምንም ማድረግ አይገባም፡፡
መጋባት ክህነት መስጠት ክርስትና ማንሣት ከሹመትም ወገን ስለሚሞቱት ከመጸለይ በቀር ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ ይሞታል ተብሎ ለሚያስፈራው
ግን ጥምቀተ ክርስትና ይደረግለታል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ
ለምን አርባ ቀንና አርባ ሌሊትን ጾመ? በቀጣይ ክፍል ይጠብቁን!...
No comments:
Post a Comment