የካቲት 30/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
በምንፍቅናው ዓለም በጨለማ ውስጥ ሳሉ በብርሃን
ነን የሚሉት የእግዚአብሔርን ፍቅር ከአምላክነትና ከአባትነት ደረጃ አውርደው የጓደኛን እንኳ ያህል ክብር ሳይሰጡ “ኢየሱስ ጌታ
ነው!” በማለት ብቻ እንድናለን ብለው ራሳቸውን የሚያታልሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በእውነት የኢየሱስን ጌትነት ለእኛ ለተዋሕዶ ልጆች
እነርሱ የሚያስረዱን ይመስላቸዋልን? ድፍረትስ አይሆንምን? በኢየሱስ ደም በተመሠረተች ቤተክርስቲያን ውስጥ በ40 በ80 ቀናችን
ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማየ ዮርዳኖስ የልጅነት ጥምቀት የተጠመቅን የብርሃን ልጆች የኢየሱስን ጌትነት እንዴት አናውቅም? በሚገባ
እናውቀዋለን እንጅ ምን ነካችሁ፡፡ በእርግጥ ከተራራ የሚልቅ ልዩነት አለን፡፡ እነርሱ ኢየሱስ የሚሉት እኛ ኢየሱስ የምንለውን ጌታ
አይደለም፡፡ እኛ ኢየሱስ የምንለው ቀድሞ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ ያለ እናት የተወለደውን የአብ ልጅ በኋላም ከንጽሕት ዘር ከድንግል
ማርያም ያለ አባት በተዋሕዶ የተወለደውን የድንግል ማርያምን ልጅ ነው፡፡ እኛ ኢየሱስ የምንለው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሥጋን
ለብሶ ለድኅነተ ዓለም ወደዚህ የመጣውን በመልእልተ መስቀል ተሰቅሎ በደመ ማኅተሙ ሲዖልን የከፈተውን በባርነት የነበረውን አዳም
ልጅነቱን የመለሰውን ነው፡፡ ኢየሱስ ለእኛ አምላክ ነው፣ ኢየሱስ ለእኛ ፈራጅ ነው፣ ኢየሱስ ለእኛ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው፣
ኢየሱስ ለእኛ ጌታችን ነው፣ ኢየሱስ ለእኛ መድኃኒታችን ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ያልነው ዛሬ ሳይሆን ድሮ ገና ሉተር ሳይፈጠር ነበር፡፡
እኛ አክብረን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንለዋለን እነርሱ ንቀው ከጓደኛም አሳንሰው “ኢየሱሴ!” ይሉታል ሎቱ ስብሐት፡፡
የመናፍቃን ማታለያ ዘዴዎች በርካታ ናቸው፡፡
እነርሱ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ በደረቁ ሸምድዶ እዚህ ቦታ እንዲህ ይላል እያሉ ሰውን ጥርጣሬ ውስጥ መጨመር ፍላጎታቸው ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከመጣን አንድ ቦታ እና አንድ ነጥብ ላይ ብቻ ቆመን መከራከር ከቻልን ችግር የለውም፡፡ በዚያች ባነሷት ነጥብ
ላይ ተማምነን ወደሌላ ካለፍን ችግር የለውም እንነጋገር፡፡ ነገር ግን የዚያ ዓይነት ወኔ የላቸውም ምክንያቱም መሠረት ስለሌላቸው ጸንተው አይቆሙም፡፡ ስለድንግል ማርያም አማላጅነት
ጀምረው ስለመስቀል ሲከራከሩ ነው የምታገኟቸው፡፡ እነርሱ ጥርጥርና ኑፋቄን በሰው ልብ ላይ መዝራት እንጅ ማመንና ማሳመን አይችሉም፡፡
ዋናው መከራከሪያቸው “እንዲህ የሚል ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አይገኝም” የሚለው ብሂላቸው ነው፡፡ ትልቁ ስህተታቸው እዚህ ጋር
ነው የሚጀምረው እንግዲህ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ታሪክ የያዘ ነው ልንል እንዴት እንደፍራለን? ጌታ ያደረገው፣ እመቤታችን ያደረገችው፣
ሐዋርያት ያደረጉት ሁሉ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ ውስጥ እንዴት ነው ሊጻፍ የሚችለው? እኛ እንኳ ከንቱዎች ከመጽሐፍ ቅዱሱ ገጽ
ብዛት ይልቅ የሚበዛ ታሪክ ስለራሳችን እንጽፍ የለም እንዴ? ታዲያ የአንድ ሰው ታሪክ ያን ያህል ከሆነ እንዴት ነው የጌታችን ታሪክ፣
የእመቤታችን ታሪክ፣ የሐዋርያት ታሪክ በዚያ መጽሐፍ ብቻ ሊወሰን
የሚችለው? አለማስተዋል ካልሆነ በቀር በፍጹም ሊወሰን አይችልም፡፡ ሰማይ እና ምድር እንደ ብራና ቢሆኑ ቀላያት በሙሉ
የብርዕ ቀለም ቢሆኑ ውሉደ አዳም ጸሐፍት ቢሆኑ በፍጹም ተጽፎ የማያልቅ ታሪክ አላቸው፡፡ ስለዚህ እንደመግቢያ ያህል ትንሹን ነገር
ብቻ መሠረታዊ የሆነውን ለእኛ በምንረዳው መጠን ተጻፈልን እንጅ ሁሉንም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አላሰፈሩልንም፡፡ ይህን የምለው ዝም
ብየ አይደለም ራሱ መጽሐፉ ስለሚል ነው፡፡ ዮሐ 21፥25 ላይ እንዲህ ይላል “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ ኹሉ
በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል”፡፡ ታዲያ እኛ ተአምረ ኢየሱስ ስንል፣ መልክአ ኢየሱስ
ስንል ምኑ ነው የማይዋጥላቸው? ስለእመቤታችንም ቢሆን እንዲሁ ነው፡፡ ዮሐንስ ወንጌላዊው እነኋት እናትህ ተብሎ በዮሐ19፥27 ላይ
ከተቀበላት በኋላ 15 ዓመት አብሯት አብራው ኖረዋል፡፡ ከዚያ በፊት ያለው መተዋወቃቸው ቀርቶ በዚህ 15 ዓመት ውስጥ ስለእርሷ
ያወቀውን በወንጌሉ ማስፈር አቅቶት ነው እንዴ ምንም ያላለው? አይደለም እነርሱ እንደ እኛ ምሥጢር የማይገባቸው አይደሉም ሁሉን
ነገር በምሥጢር ነው የሚያነሡት፡፡ በምሥጢር እኮ በወንጌሉ ላይ በምዕራፍ 2 አንሥቷታል፡፡ ያንን በሚገባ ተርጉመን ምሥጢሩን አራቅቀን
መማርና ማዎቅ የእኛ ፈንታ እንጅ የዮሐንስ ፈንታ አይደለም፡፡ እርሱ ያስተማረውን ማን ነው የጻፈለት? ቃል በቃል አፍ ለአፍ የተናገራቸውን
ትምህርቶች ማን ነው መዝግቦ የያዘለት? 2ኛ ዮሐ 1፥12 ላይ “እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው
አልወድም ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ” ይላል፡፡ 3ኛ ዮሐ1፥13
ላይም “ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወድም” ይላል፡፡ ከእነዚህ ጥቅሶች የምንረዳው
ነገር አለ፡፡ እርሱም ከዚህ መልእክት በተጨማሪ አፍ ለአፍ ያናገራቸው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ያ አፍ ለአፍ ያናገራቸው ያስተማራቸው
ትምህርት ምንድን ነው? ስለእመቤታችን ድንግል ማርያም ነውን? ስለ መስቀል ነውን? ስለ መላእክት ነውን? ስለኢየሱስ ክርስቶስ ነውን?
ስለ ታቦት ነውን? ስለ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ነውን? ታዲያ ስለምንድን ነው? አሁን ይህን ማን ያውቃል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ
ተመዝግቦ እስካላገኘነው ድረስ የዮሐንስን ትምህርት አንቀበለውም አንልም ምክንያቱም መልእክቱ ላይ ይህንን ስላስቀመጠልን፡፡ መጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ የሌለ ቢሆንም ዮሐንስ በአፍ ያስተማረውን እኛ እንቀበለዋለን፡፡ እነርሱ አይቀበሉትም ልዩነታችን ይህ ነው እንግዲህ፡፡
መዳን የማይሻ ትውልድ ሁልጊዜ እንደተከራከረ ነው በሚያውቀው አንድ ሳይሰራ በማያውቀው ሺህ ጊዜ ሲከራከር ኅልፈት ይቀድመዋል፡፡
እኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምን አዋልድ መጻሕፍትን
ድርሳናትን፣ ገድላትን፣ ተአምራትን፣ መልክአ መልኮችን፣ የሥርዓት መጻሕፍትን፣ ትርጓሜ መጻሕፍትን በሙሉ እንሻለን ምክንያቱም መጽሐፍ
ቅዱስ በዝርዝር ሳይሆን በጥቅል የተጻፈ ስለሆነ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መተርጎም መብራራት የሚሻቸው ናቸው፡፡ ከዚያ ውጭ ከሆነ
ግን ገደል ይዞን እንደሚገባ አያጠራጥርም፡፡ 2ኛ ጢሞ 3፥16 “…የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ኹሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ
ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” ይላል፡፡ ታዲያ መናፍቃኑ ትምህርት አንፈልግም፣ ተግሳጽ አንሻም፣ ልባችን
እንዲቀና አንፈልግም፣ ምክር አይጠቅመንም ነው እንዴ የሚሉት? አልገባኝም
እኔስ በእውነት ነው የምላችሁ፡፡ መናፍቃኑ እኮ የሚከራከሩት “እንዲህ የሚል ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም” ጥቅስ አሳዩን በሚል
ነው፡፡ በእውነት ሲጀመር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን በሙሉ አምነው እየሠሩበት ነውን? ትልቁ ጥያቄ እዚህ ጋር ነው፡፡ ለምሳሌ
ኢየሱስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾመ የሚል በወንጌል እናገኛለን ማቴ 4ን ተመልከቱ ግን እነርሱ እየጾሙ ነው? አይደለም፡፡ እንዲያውም
“ኢየሱስ ጾሞልኛል እና አልጾምም” ነው የሚሉት፡፡ በዚህም ይሁን እሽ እርሱ ጾሞላቸዋል እና እነርሱ መጾም አያስፈልጋቸውም እንበልና
እንስማማ ማቴ 26፥20 ላይ “በመሸም ጊዜ ከ12ቱ ደቀመዛሙርት ጋር በማእድ ተቀመጠ ሲበሉም እውነት እላቸኋለሁ…” ይላል ስለዚህ እዚህ ክፍል ላይ ስትደርሱ ደግሞ ኢየሱስ በማእድ ተቀምጦልኛና እርሱ
ስለበላልኝ እኔ አልበላም ማለት ያስፈልጋችኋል ማለት ነው፡፡ ሲጾም ጾመልን እንዳላችሁ ሁሉ ሲበላም በላልን ማለት አለባችሁ፡፡ ለመከራከር
እኮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የማይጾም ሰው ስለጾም ምን አከራከረው? የማይጸልይ ሰው ስለጸሎት ምን አከራከረው? የማያስቀድስ ሰው
ስለ ቅዳሴ ምን አከራከረው? የማይሰግድ ሰው ስለ ስግደት ምን አከራከረው? እኛ ለጾምን፣ እኛ ለጸለይን፣ እኛ ላስቀደስን፣ እኛ
ለሰገድን እነርሱ ምን ቤት ናቸው የሚለፈልፉት? አንዳንድ ጊዜማ በሰከነ መንፈስ ራስን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማዳመጥ ያስፈልጋል
እኮ፡፡ እኛን ብቻ ስሙን ማለት አይገባም እነርሱም እኛን ሊሰሙን ሊያዳምጡን ያስፈልጋል፡፡
ዝም ብሎ የማያውቁትን ጌታ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ”
ማለት የሚያጸድቀን አይደለም፡፡ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ከማለታችን አስቀድሞ ጌታን ማወቅ ያስፈልጋል እንጅ ስሙን የጠራ ሁሉ ይድናል
እያሉ ሳያምኑ “ኢየሱስ ጌታ ነው!” ብሎ መፎከር አይደለም፡፡ ማቴ 7፥21 “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጅ
ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” ይላል መጽሐፉ፡፡ ስለዚህ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ከማለት በፊት
የአባቱን ፈቃድ ማዎቅና መፈጸም ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” እያሉ መጨፈር መንግሥቱን የሚያወርስ አይደለም፡፡
በእርግጥ እኛ እንደፈለጋችሁ ብትዘሉ ብትጨፍሩ አይመለከተንም እምነት ብላችሁ የያዛችሁት እስከሆነ ድረስ ነገር ግን የእኛን ልጆች
እንዲጠራጠሩ ኑፋቄያችሁን ልትዘሩባቸው አይገባም፡፡ እናንተም ለራሳችሁ ነው እኛም ለራሳችን ነውና! እኛና እናንተን የማያገናኘን
ትልቅ ገደል አለ ከዚያ ገደል ልታልፉ አይገባም ካለፋችሁ ግን ያው በሚገባ እናስተምራችኋለን፡፡ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ማለት የጌታ
መሆንን የሚያሳይ እንዳይመስላችሁ፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ የጌታ ለመሆን “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ማለት ብቻ ሳይሆን እርሱን መምሰል
ጭምር ያስፈልጋል፡፡ እርሱን የምንመስለው ደግሞ በመጾም፣ በመጸለይ፣ በመስገድ፣ በመመጽወት፣ እውነተኛውን መንገድ በመምረጥ፣ እውነተኛውን
ትምህርት በመማር በማስተማር ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ማለት ብቻውን የጌታ መሆንን አያሳይም፡፡ ይህንን ኑፋቄያችሁን
በተለያዩ መገናኛዎች ለማደናገር የምትሞክሩ መናፍቃንም ልታስተውሉ ያስፈልጋል፡፡
እግዚአብሔር ማስተዋልን ያድለን፡፡
No comments:
Post a Comment