የካቲት 25/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ሞትና ሕይወት በተቃርኖ የሚኖሩ ጥንዶች ናቸው፡፡
ሞት ካለ ሕይወት የለም፤ ሕይወት ካለም ሞት የለም፡፡ በእርግጥ የዘነጋሁት ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡ ሞት ሦስት ዓይነት እንደሆነ፡፡
የነፍስ ከሥጋ መለየት (የሥጋ ሞት)፣ በቁም ሳሉ የነፍስ ከእግዚአብሔር መለየት በኃጢአት በበደል (የቁም ሞት) እና ከሥጋ ሞት
በኋላ የነፍስ ወደ ሲኦል መውረድ (የነፍስ ሞት/ዘላለማዊ ሞት) ናቸው፡፡ አሁን እኔ በርእሰ ጉዳዬ ላይ ያነሣሁት ሁለተኛውን ዓይነት
ሞት ነው፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያው የሥጋ ሞት ለማንኛውም እኩል የተሰጠ ስለሆነ አያስጨንቀንም ሦስተኛውም ሞት ሞኞች የሚሞቱት
መጀመሪያ ከሥጋ ሞት በፊት በሁለተኛው ሞት በቁም ሞት የሞቱ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በቁሙ ያልሞተ ሰው በነፍሱ አይሞትም፡፡ ስለዚህ መጠንቀቅ የሚገባን ሞት ሁለተኛው
ሞት በመሆኑ ነው እንግዲህ ዛሬ እንደ ርእስ ያነሣሁት፡፡ ሕይወት ማለት አለመሞት ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሥጋችን ከነፍሳችን
ሳትለይም በቁማችን ሞት ስላለብን ማለት ነው፡፡ አንዳንዶቻችን በሕይወት መኖር ማለት የነፍስና የሥጋችን አለመለያየት ወይም በሥጋ
አለመሞት ይመስለናል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮማ ሞትና ሕይወት ተቃራኒ አይሆኑም ነበር፡፡ ከሥጋ ሞት በኋላም ሕይወት ስላለ
አለመሞት ማለት ሕይወት ማለት አይደለም፡፡
ስለሞት እና ሕይወት ይህን ያህል ካልን ወደ
ጥንተ ነገራችን እንመለስና ለዚህ ለቁም ሞት የተዘጋጀ ነፍሱን ለሞት ያዘጋጀ ምንም ዓይነት መድኃኒት አያድነውም ያልንበትን ምክንያት
እንመልከት፡፡ የሰው ልጅ በሥጋው ሳይሞት ብዙ ውጣ ውረዶችን፣ ብዙ ፈተናዎችን፣ ብዙ ችግሮችን፣ ብዙ ክስተቶችን ፣ብዙ መከራዎችን፣
ብዙ ደስታዎችን ያሳልፋል፡፡ የሰው ልጅ ሕይወቱ አንዴ የሞቀ አንዴ የቀዘቀዘ፣ አንዴ የተቀደሰ አንዴ የረከሰ፣ አንዴ የተደላደለ
አንዴ የጎራበጠ፣ አንዴ የለሰለሰ አንዴ የሻከረ፣ አንዴ የነጣ አንዴ የገረጣ፣ አንዴ ከፍ ከፍ ያለ አንዴ ዝቅ ዝቅ ያለ፣ አንዴ
ደስ የሚሰኝበት አንዴ የሚከፋበት፣ አንዴ የሚስቅበት አንዴ የሚያለቅስበት፣ አንዴ የሚበላበት አንዴ የሚራብበት፣ አንዴ የሚጠጣበት
አንዴ የሚጠማበት፣ አንዴ የሚነሣበት አንዴ የሚወድቅበት ነው፡፡ በዚህ መካከልም የሰው ልጅ ጽናቱ አምላክ እንደሰጠው ጻጋ መጠን
ይለያያል፡፡ አንዳንዱ “ሁሉ ነገር ለበጎ ነው” የሚለው እንደ ኢዮብ ጻድቅ ከደስታው በፊት በመከራው ወቅት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ
ሰው በመከራውም በደስታውም ፈጣሪውን የሚያመሰግን ነው፡፡እንዲህ ዓይነቱ
በጊዜውም ያለጊዜውም የሚጸና ሰው ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ “ሁሉ ነገር ለበጎ ነው ለካ” ይላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው
ደግሞ ሁሉ ነገር ለበጎ መሆኑን የተቀበለው መከራውን አልፎ ደስታ ስላገኘ ብቻ ነው፡፡ ከደስታው በፊት በመከራው ወቅት “ሁሉ ነገር
ለበጎ ነው” የሚል አስተሳሰብ አልነበረውም፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በመከራውም ሆነ ከመከራው በኋላ በደስታው ወቅት ፈጣሪውን በማማረር
ይጠመዳል፡፡ በመከራው ሰዓት ለእንደዚህ ዓይነቱ መከራ የጣልኸኝ ምን አድርጌህ ነው እያለ መከራው ለበጎ መሆኑን አይረዳም፡፡ በደስታው
ሰዓትም ደስታውን ፈጣሪው እንደሰጠው ስለማይረዳ የሌሎችን ደስታ እየናፈቀ በእነርሱ ደስታ እየቀና እንደሌሎች ያለውን ደስታ ያልሰጠኸኝ
ለምንድን ነው እያለ ፈጣሪውን ያማርራል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በመከራው ሰዓትም ሆነ በደስታው ሰዓት ፈጣሪውን አያመሰግንም አያማርርምም፡፡
ዝም ብሎ ብቻ የሆነውን ሁሉ የሚቀበል አለ፡፡ ዝናብ ሲወርድበት ዝም! ፀሐይም ሲያቃጥለው ዝም! ሲመቱት ዝም! ሲሰድቡት ዝም! ሲስቁበት
ዝም! ሲንቁት ዝም! ሲጠግብ ዝም! ሲራብ ዝም! ሲጠማ ዝም! ሲጠጣ ዝም! ሲታመም ዝም! ሲድንም ዝም! ብቻ ሁልጊዜ ዝምታ! ዝምታው
ግን ለምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ምናልባት ፈጣሪውን በውስጡ እያመሰገነ ወይም እያማረረ ይሁን አይሁን ለሌሎች በግልጽ አይታወቅም፡፡
በዚህ ምክንያት ሕይወታችን እና ሞታችን ይለያያል፡፡
እንግዲህ ሰው በኃጢአት ሲቆሽሽ፣ በበደል ሲረክስ፣ ከፈጣሪው ሲለይ፣ ከአገልግሎት ሲርቅ፣
ከቅዱሳኑ በረከት ሲያጣ፣ ዕጣኑን ማሽተት ሲተው፣ ጸሎት ማድረስ ሲያቆም፣ መስገድ ሲዘነጋ፣ መጾም ሲረሳ፣ ማስቀደስ ሲያቆም፣ ኪዳን
ማስደረስ ሲተው፣ ጸበል መጠጣት ሲረሳ ያን ጊዜ ሞተ እንለዋለን፡፡ በዚህ ሞት ያልነቃ ሰው በነፍሱም እንደሚሞት የተረዳ ነው፡፡
በእርግጥ እዚህ ጋርም ሁለት ዓይነት አስተሳሰቦች አሉብን፡፡ አንዳንዱ አውቆ የተደበቀ ነው አንዳንዱም ሳያውቅ የተጋለጠ ነው፡፡
ሳያውቅ ለዚህ ሞት የተጋለጠ ሰው ሲማር ሲሰበክ ሲያውቅ ሲመከር ይሻሻላል፡፡ አድርግ የተባለውን ሲያደርግ አታድርግ የተባለውን ሲተው
ያን ጊዜ ቅድስና ይቀርበዋል በረከት ይጎበኘዋል፡፡ ይህ ሰው ሳያውቅ የታመመ ስለሆነ በመድኃኒት ለመታከም አይከብደውም፡፡ የሞተም
ሳያውቅ ስለሆነ ለመነሣት አይቸገርም፡፡ በዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ ኃጢአት
የሚሠራው ተሳስቶ ስለሆነ ተፀፅቶ የመመለስ አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ለሞት የተዘጋጀ ስላልሆነ በመድኃኒት ታክሞ ለመዳን ጊዜ አይወስድበትም፡፡
ነገር ግን ለሞት የተዘጋጁ ሰዎች በመድኃኒት የማይድኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚጠፉና የሚያጠፉ አውቀው ነው፡፡ ለበደል ለኃጢአት
የሚሮጡት በንስሐ ላለመመለስ ጭምር ወስነው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ከምግባር ሕጸጽነቱ ይልቅ የእምነት ሕጸጽነቱ ያመዝናል፡፡
የምግባር ሕጸጽን በንስሐ መድኃኒት ማከም ይቻላል የእምነት ሕጸጽን ግን የንስሐንም መድኃኒትነት ካለመቀበል ጋር የሚመጣ ስለሆነ
ለማከም የሚያስችል መድኃኒት አይገኝለትም፡፡ የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና አማላጅነቷን፣ የመላእክትን ጥበቃ እና ምልጃ፣ የቅዱሳኑን
ጸሎትና ልመና ምልጃ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ፈጣሪነት፣ የቤተክርስቲያንን ክብር ልዕልና ቅድስና፣ አእማደ ምሥጢራትን፣ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንን፣
ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ወዘተ በመናቅና በማንቋሽሽ ላይ የተጠመዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሥርዓቷን ንደው እነርሱ እንደሚፈልጉት
ለማድረግ የሚታገሉ ናቸው፡፡ ለሞት የተዘጋጁ ስለሆነም ተመክረው ተዘክረው አይመለሱም፡፡ ታክመው ለመዳን ፍላጎትም ዓላማም የላቸውም
ምክንያቱም አውቀው የታመሙ ስለሆነ፡፡ በሽታችሁ ይህ ነውና በዚህ መድኃኒት ታከሙ ሲባሉ መድኃኒቱን እንደመድኃኒትነቱ አይቀበሉትም
ምክንያቱም በሽታቸው ሌላ እንደሆነ ያውቃሉና፡፡ የምግባር ሕጸጽ ነው ብለን ብንመክራቸውና የዚህን መድኃኒት ብናዝዝላቸው በሽታቸው
የእምነት ሕጸጽ እንደሆነ ራሳቸው ስለሚያውቁ መድኃኒቱን አይወስዱትም፡፡ ለምን በኦርጋን አንዘምርም? ለምን በልተን አንቀድስም?
ለምን ሴቶች አይቀድሱም? ለምን ከነጫማችን መቅደስ አንገባም? ለምን ተመሳሳይ ጾታ አይጋባም? ለምን ኢየሱስን አማላጅ አንልም?
ለምን ድንግል ማርያም አታማልድም አንልም? ቅዳሴው ረዝሟል ለምን አያጥርም? ጾም በዝቷል ለምን አይቀነስም? የሚሉ ጥያቄዎችን የሚጠይቁና
የሚያስፈጽሙ የተሐድሶ መንፈስ የተጠናወታቸው ግለሰቦች ለሞት የተዘጋጁ ስለሆነ ለመዳን ቦታ የላቸውም፡፡ በዚህ በሽታ የተለከፉት
አውቀው ስለሆነ መድኃኒት አይሹም፡፡ ቢመከሩ ቢዘከሩ አይሰሙም ምክንያቱም “ለሞት የተዘጋጀ በመድኃኒት አይድንም” እና ነው፡፡
No comments:
Post a Comment