© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 5/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
በክፍል ሁለት
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ፵ ቀንና ፵ ሌሊት እንደጾመ፣ የፈጸማቸውን አምስት ግብራት እንዲሁም አምስቱን የተገኘባቸውን ተመልክተናል፡፡
በዚህ ክፍል ደግሞ የተፈተነባቸውን ሦስቱን አርእሥተ ኃጣውእ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡ መልካም ንባብ!
ማቴ 4÷3 “ወቀርበ
ዘያሜክሮ” የሚፈታተነው ዲያብሎስ ቀረበ፡፡ ዲያብሎስ የቀረበው እንዲሁ አይደለም “ርኅብኩ” ሲል ሰምቶት፣ ፍሬ ዕጽን ሲሻ አይቶት፣
መልኩን አጠውልጎ ታይቶት ነው እንጅ ዲያብሎስም እንዲያው አይቀርበውም በአምሳለ ሰዓሊ በአምሳለ ሐራሲ በቀዳዳ ሽልቻ ትኩስ ዳቦ
የያዘ መስሎ ሁለት ደንጊያ ይዞ ይቀርበዋል፡፡ አመጣጡ አንዱን ላንተ አንዱን ለኔ ዳቦ አድርገህ እንብላ ሊለው ደንጊያውን ዳቦ ከማድረግማ
የያዝከውን አንበላም ቢለኝ አዳም አባቱን በመብል ምክንያት ድል እንደነሣሁት እሱንም በመብል ምክንያት ድል እነሣዋለሁ ብሎ ነው፡፡
ከዚያም ያሰበውን ተናገረ፡፡ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ አብ በሰማይ የምወደው ልጄ ብሎ ሲመሰክርለት ሰምቶ ነበርና “የእግዚአብሔር ልጅ
ከሆንክ እኒህ ደንጊያዎች ኅብስት ይሁኑ ብለህ እዘዝ” አለው፡፡ ለዓላማ ነው ይህን መጠየቁ ቢያደርገው የኔ ታዛዥ ነው ለማለት ባያደርገውም
ደካማ ነው ለማለት ነው፡፡ አንድም ቢያደርገው ሌላ ጾር እሻለታለሁ ባያደርገውም ድካሙን አይቼ እቀርበዋለሁ ብሎ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ
ግን “ሰው የሚድነው በኅብስት ብቻ እንዳይደለ በእግዚአብሔር ቃል ጭምር እንደሆነ ተጽፏል” ይለዋል፡፡ ይህን ማለቱ ሰው ምግብ የሚሆነው
ገበሬ የጣረበት ኅብስት ብቻ እንዳይደለ እግዚአብሔር ምግብ ሁን ያለው ምግብ ሆኖለት ይኖራል ለማለት ነው፡፡ አንድም ሰው የሚድነው
ገበሬ በጣረበት በጋረበት እንጀራ ብቻ አይደለም በትምህርት በዓቂበ ሕግ (ሕግን በመጠበቅ) ነው እንጅ፡፡ አንድም አንተስ ወልደ
እግዚአብሔር ከሆንህ ይህ እንደ ደንጊያ የፈዘዘው ሰውነትህ ኅብስተ ሕይወት ኅብስተ መድኃኒት ይሁን በል ሲለው ነው፡፡ ጌታም ሰው
የሚድን በዕሩቅ ብእሲ ሥጋ እንዳይደለ ተጽፏል አካላዊ ቃል በተዋሐደው ሥጋ ነው እንጅ ይለዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በዚህ
እንደተሸነፈ የተረዳ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት አገር ወደ ኢየሩሣሌም ይወስደዋል፡፡ ሰይጣን የሚወስደው ሁኖ አይደለም በፈቃዱ ሔደለት
እንጅ፡፡ በፈቃዱ የሔደለትም ካህናትን ድል ነሥቸበት በማላውቀው ገዳም ሁኖ ነው እንጅ ካህናትን ድል በምነሣበት ቤተመቅደስ ቢሆንማ
ድል እነሣው ነበር ሲል ሰምቶት ነው የዲያብሎስን ውርደት የእርሱንም አምላክነት ለማሳየት ነው፡፡ በዚያም ሌላ ፈተና ይፈትነዋል፡፡
ከዚያም ተድባብ ቢሉ ከዝንቦው ማዕዘንት ቢሉ ከምሕዋሩ ርእስ ቢሉ ከጉልላቱ ላይ ያቆመዋል፡፡ ከዚያም “አንተ በእውነት ወልደእግዚአብሔር
ከሆንህ ከዚህ ዘልለህ ከታች ውረድ” ይለዋል፡፡ ቢሰበር ዐርፈዋለሁ ባይሰበር ምትሐት አሰኘዋለሁ ብሎ አንድም ቢያደርገው ሌላ ጾር
እሻለታለሁ ባያደርገውም ደካማ አሰኘዋለሁ ብሎ አንድም ቢያደርገው የሰይጣን ታዛዥ እልበታለሁ ባያደርገውም ድካሙን አይቼ እቀርበዋለሁ
ብሎ፡፡ ጌታም መልሶ “እግዚአብሔር ፈጣሪህን አትፈታተነው የሚል ጽሑፍ አለ” ይለዋል፡፡ በዚህም ዲያብሎስ ድል ማድረግ አልቻለም
በመሆኑም ወደ ረዥም ተራራ ይወስደዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ከረዥም
ተራራ አወጣው፡፡ ነገሥታትን ድል በማልነሣበት ቤተመቅደስ ድል ነሣኝ እንጅ ነገሥታትን ድል በምነሣበት በተራራ ቢሆን ኖሮ ድል ባላደረገኝ
ነበር ሲል ሰምቶታልና ጌታ በፈቃዱ ወደ ተራራ ይወጣለታል፡፡ ከዚያም ጠጠሩን ወርቅ ብር፣ ቅጠሉን ግምጃ አስመስሎ አሳየው አንድም
ግዛቱን ሁሉ አሳየው እንስሳትን አራዊትን ፈረስ በቅሎ ሠራዊት አስመስሎ አሳየው፡፡ ጌታ ግን አያይለትም እሱ ያየለት ስለመሰለው
ነው እንጅ፡፡ ከዚያም መቼም ዲያብሎስ ደፋር ነውና የሁሉ አምላክ
መሆኑን ዘንግቶ “ብትሰግድልኝ እጅ ብትነሣኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው፡፡ ጌታም “ከእኔ ወግድ ሂድ አንተ ሰይጣን” አለው፡፡
እንዲህ ማለቱ ራስ አይቶ የሚመጣ ጠላት ክፉ ነውና ከኋላየ ወግድ ሲል ነው አንድም ከእኔ በኋላ ከሚነሡ ምእመናንም ወግድላቸው ሲል
ነው፡፡ እንዲህ ሲለው እንደ ጢስ ተኖ እንደ ትቢያ በኖ ይጠፋል፡፡ እስካሁን ወግድ ያላለው አሁን ያለው ስለምን ነው ቢሉ በመጀመሪያ
ሽሽ በሁለተኛም ሽሽ በሦስተኛው ግን ተጋደል ድል ንሣ የሚል አብነት ስላለ ነው በሦስተኛው ድል ንሡ ለማለት ነው፡፡ አንድም ጎልማሳ
በሚስቱ ንጉሥ በመንግሥቱ እንዲቀና ጌታም ለአምልኮቱ ቀናዒ ነውና በአምላክነቱ ሲመጣበት ወግድ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ጌታ “ለፈጣሪህ
ለእግዚአብሔር ብቻ ትሰግድ ዘንድ እሱንም ብቻ ታመልክ ዘንድ ተጽፏል” ይለዋል፡፡ ቅድም እንደትቢያ በኖ እንደጢስ ተኖ ጠፋ ብለን
ነበር ነገር ግን ሰይጣን እና ውሻ ምልልስ ይወዳሉና ተመልሶ መጥቶ ሲሰማው እንዲህ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ በአይሁድ ሥግው ሁኖ በመስቀል
እስኪያሰቅለው ድረስ ዲያብሎስ ተወው አልተመለሰበትም፡፡
እነዚህን አርእስተ
ኃጣውእ እንዲህ አድርጎ ለአዳምና ለሔዋን ድል ነሥቶላቸዋል፡፡ ጌታ እንዲህ ማድረጉ የአባቴ የአዳም የእናቴ የሔዋን ደም የማይቀርብኝ
ሲል ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል አድርጎላቸዋል፡፡ እነዚህ ሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ ምን ምን ናቸው ቢሉ፡
1. ስስት፡- ያልሰጡትን መሻት፤
2. ትዕቢት፡-አምላክ እሆናለሁ ማለት፤
3. ፍቅረ ንዋይ፡- በቃኝ አለማለት ነው፡፡
ዲያብሎስ ድል
የሆነው በዚህ ሁሉ ነው፡፡ ድል መንሣቱ ግን ለአዳምና ለሔዋን ብቻ አይደለም ለሁሉ ነው እንጅ፡፡
·
መነኮሳት በፈለጉ
ጊዜ አያገኙምና በትኅርምት ኗሪዎች ናቸውና ጾራቸው ስስት ነው፡፡ ለዚያም ነው በቦታቸው በገዳም በስስት ቢመጣበት በትዕግሥት ድል
የነሣላቸው፡፡
·
ካህናት አእምሯችን
ረቂቅ ማዕረጋችን ምጡቅ እያሉ ይታበያሉና ጾራቸው ትዕቢት ነው፡፡ ለዚያም ነው በቦታቸው በቤተ መቅደስ በትዕቢት ቢመጣበት በትህትና
ድል የነሣላቸው፡፡
·
ነገሥታት ቤታቸውን
ከፍ ካለ ቦታ ሠርተው የወጣ የወረደውን ያለፈ ያገደመውን እያዩ የዚህ ሁሉ እንጅ ኑሮው በኛ ነው እያሉ ገንዘብ ይሰበስባሉና ጾራቸው
ፍቅረ ንዋይ ነው፡፡ ለዚህም ነው በቦታቸው በተራራ ላይ በፍቅረ ንዋይ
ቢመጣበት በጸሊአ ንዋይ ድል የነሣላቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ኃጢአት
ከሥሩ እንደተነቀለ ዛፍ ሁናለች፡፡ ከሥሩ የተነቀለ ዛፍ እንዳይለመልም እንዳያብብ እንዳያፈራ ኃጢአትም በፍዳ የማታሲዝ ሁናለች፡፡
አሁን በፍዳ የተያዙ አሉ ቢሉ እነዚህ አዋጅ አፍራሾች ናቸው፡፡ ንጉሥ ይዘምታል ድል ነሥቶ ሲመለስ ከመንገድ የወጣህ ወታደር ብሎ
ያውጃል ያንጊዜ በደለኛ ወታደር ከመንደር ገብቶ ሲዘርፍ ቢሞት ንጉሥ ድል አላደረገም አይባልምና እነዚህም በኃጢአት የተያዙት አዋጅ
አፍራሾች ናቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ
ተወው እነሆም መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር፡፡ አርባ ቀን በትኅርምት ኖሯልና መላእክት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋእ ሰማያዊ ይዘው
መጡ አንድም ድል ነሥቷልና ለከ ኃይል ለከ ጽንእ እያሉ ቀረቡ፡፡ ድል ከነሣ በኋላ መምጣታቸው ስለምን ነው ቢሉ አስቀድመው መጥተው
ቢሆን ኖሮ መላእክትን ይዞ ድል ነሣኝ ብቻውን ቢሆን ኖሮ መቼ ድል
ይነሣኝ ነበር ባለ ነበር፡፡ አንድም እናንተም ድል ብትነሡ ይገለጽላችኋል ለማለት፡፡ አንዱን ባሕታዊ ሰይጣን መጥቶ ንጉሥ ይጠራሃል
አለው፡፡ ባህታዊውም አልብየ ንጉሥ ዘእንበለ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አለው፡፡ ሰይጣንም በያዘው በሎታ ቀጥቅጦት ሄዷል፡፡ ከዚህ
በኋላ መልአከ ዑቃቢው ተገለጸለት ባህታዊውም ማነህ አለው እሱም መልአከ ዑቃቢህ ነኝ አለው፡፡ ታዲያ እስካሁን የት ነበርህ አለው
መልአከ ዑቃቢውም አሁንም ድል ስለነሣህ ተገለጽኩልህ እንጅ ድል ባትነሣ አልገለጽልህም ነበር አለው፡፡ ስለዚህ እናንተም ድል ብትነሡ
ይገለጽላችኋል ለማለት መላእክት መጡ፡፡
ተፈጸመ፡፡
No comments:
Post a Comment