© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 12/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
የቃሉ ተናጋሪ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ቃሉን የተናገረውም
ለአንድ ከለምጹ ለነጻ ሰው ነው፡፡ ይህ ቃል የተነገረበት ምክንያት ከላይ ከቁጥር 12 ጀምረን የምናገኘው ይሆናል፡፡ “ወደ አንዲት
መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት ዐሥር ለምጻሞች ተገናኙት እነርሱም እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን አሉ፡፡ አይቶም ኺዱ ራሳችሁን
ለካህናት አሳዩ አላቸው፡፡ እነሆም ሲሄዱ ነጹ፡፡ ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ
ተመለሰ፡፡ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ እርሱም ሳምራዊ ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ ዐሥሩ አልነጹምን ዘጠኙስ ወዴት
አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ፡፡ እርሡም ተነሣና ሂድ እምነትህ አድኖሃል አለው”
ይላል እስከ ቁጥር 19 ድረስ ያለው ቃል፡፡ ስለቃሉ የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁንልን፡፡
እንግዲህ ከዚህ ቃል የምንረዳው እና የምንማረው
ነገር ምንድን ነው? እስከ ፍጻሜ ድረስ መጽናት የሚያስገኘውን ዋጋ እንረዳለን፡፡ አበርክቶ ሲመግብ ሲከተለው የነበረው ህዝብ በኋላ
መከራን በመስቀል ላይ ሲቀበል ሸሽቷል፡፡ የ5 ገበያን ሕዝብ በ
5 እንጀራ እና በ2 ዓሣ እስኪጠግቡ ድረስ አበርክቶ አብልቶ 12 መሶብ ፍርፋሪ ሲነሣ የነበረው የሕዝብ ብዛት የሚገርም ነበር፡፡
ማቴ 14÷21 ላይ “ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት 5 ሽህ ወንዶች ያህሉ ነበር” ይላል እናንተ ቃሉን ከላይ ከቁጥር 16 ጀምራችሁ
አንብቡት፡፡ በዚህ የበረከት ሰዓት ሴቶችና ሕጻናት አብረው ተሳትፈዋል ነገር ግን ወንዶች ብቻ ናቸው እንደተመገቡ ተደርጎ የተቆጠሩት
ምክንያቱም ሴቶች ሲመገቡ ወንዶች ካዩአቸው ያፍራሉ ሕጻናትም ከሚመገቡት ይልቅ የሚደፉት፣ የሚጥሉት እና የሚያበላሹት ይበዛልና ከቁጥር
ውስጥ አልተካተቱም፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ በወንዶች ብቻ ብንወስደው 5 ሺህ ህዝብ እንደተከተለው ልብ ይሏል፡፡ እንደዚሁ ያለ ተመሣሣይ
ታሪክ አለ ማቴ 15÷34-38 ድረስ ተመልከቱት፡፡ ቁጥር 38 ላይ ያለውን ልጻፍላችሁ እንዲህ ይላል “የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች
በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ” ይላል፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ደግሞ ሰባት እንጀራን እና ጥቂት ዓሣን አበርክቶ 4 ሺህ ሕዝብ
በበረከቱ መግቧል፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ እየተከተለው ያለው ህዝብ ምን ያህል እንደሆነ? ለምን ይህ ሁሉ ሕዝብ ይከተለዋል የሚለው
መልስ የሚመለሰው በመከራው ጊዜ ነው፡፡ መልኩን ለማየት ይከተለው የነበረው በአይሁድ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ ተደብድቦ፣ የእሾህ
አክሊል ደፍቶ ቀራንዮ ላይ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሲሰቀል ለንጊኖስ ጎኑን በጦር ሲወጋው ያን ጊዜ ይሸሹታል፡፡ ምክንያቱም ደም
የሸፈነውን ፊቱን መመልከት አይፈልጉምና፡፡ ሲያበረክት ለመመገብ የተከተሉትም ተርቦ ፍሬ አልባ ወደ ሆነችው ዕጸ በለስ ሲቀርብና
ፍሬ ሲያጣባት ያን ጊዜ በለስን ሲረግም ይሽሹታል አንድም በመስቀል ላይ ሆኖ ተጠማሁ ሲል የራሱን ጥማት የማያረካ እኛን እንዴት
ይመግበናል ብለው ይሸሹታል፡፡ (ማቴ 21÷19፣ ማቴ 27÷48፣ ዮሐ 19÷28) ፈውስን ሽተው የተከተሉትም እንዲሁ በአይሁድ እጅ
በፈቃዱ ተይዞ ሲሰቀል ፈያታዊ ዘጸጋም (ዳክርስ) ራስህን አድን እያለ ያልተገባን ንግግር ሲናገር ሲሰሙ ይኼስ ራሱንም ማዳን አልተቻለውም
እንኳን እኛን ሊያድን ብለው ትተውት ይሸሻሉ፡፡ (ማቴ 27÷42) ይሸሻሉ የምላችሁ በልባቸው ነው እንጅ በአካልማ ድሮ ነው ችግራቸው
ሲፈታ የሸሹት፡፡ የሰው ልጅ የሚገርመው ታሪኩ እዚህ ላይ የሚጀምር
ነው፡፡ ሲያዝ እና ሲለቀቅ በጣም ትልቅ የሆነ ልዩነትን ያሳያል፡፡ በህመም ወቅት እጅግ ከባድ መከራና ሃዘን በደረሰበት ወቅት የሚሰማው
አምላኩን የማክበርና በአምላኩ ትእዛዝ የመሄድ ስሜትና በኋላ ይህ ሁሉ አልፎ የደስታ ጊዜ ሲተካለት የሚኖረው ስሜት ይለያያል ስለዚህም
አብሮ ፈጣሪውን በደስታው ይለውጠዋል፡፡ በመከራው ጊዜ፣ በፈተናው ጊዜ በስቃዩ ጊዜ፣ በህመሙ ጊዜ፣ በረሃቡ እና በማጣቱ ጊዜ ስእለት
የማይሳልበት ቤተክርስቲያን የለም፡፡ አምላክ መሐሪ ነውና ይቅር ይለዋል፣ ይምረዋል በበረከት በደስታ በፈውስ በጥጋብ ይጎበኘዋል
ያን ጊዜ የተሳለውን ስእለት እንኳ አይመልስም ኖኅ እንደላከው ቁራ በዚያው እንደወጣ ይቀራል፡፡
ከላይ እየተመለከትነው የሚገኘው ይህንን መሰል ድርጊት ነው፡፡ በዚህ በበረከቱ ሰዓት 5ም 4ም ሺህ ሕዝብ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ አሁን
ይህ ሕዝብ መከራው ላይስ ይሳተፍ ይሆን?
ይቀጥላል….
No comments:
Post a Comment