Wednesday, December 9, 2015

ኃጢአትየ ዘበንእስየ ወእበድየ ኢትዝክር ሊተ፡፡ /የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ/ መዝ 24÷7

© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 29/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ልበ አምላክ የተባለው ቅዱስ ዳዊት  በመዝሙሩ አምላኩን ሲማጸን “የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፡፡ አቤቱ ስለቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ” እያለ ይጸልያል፡፡ የቅዱስ ዳዊት መዝሙር በቁም ላሉት ዕድሜን የሚያረዝም፣ ከሰይጣን ፈተና የሚጠብቅ፣ በበረከትና በምሕረት የሚያኖር ስለሆነ ሁልጊዜም እንጸልየዋለን፡፡ ይህ መዝሙር ለሁሉም የሚገባ ስለሆነ ለሙታን  ፍትሐትም ሳይቀር እንጸልየዋለን፡፡ ሁልጊዜም በቅዳሴ ጊዜ ከዳዊት መዝሙር ሶስት መስመሮችን ወቅቱን የሚዋጁ ዕለቱን የሚመለከቱ ምስባኮች በሚያምረውና በሚመስጠው የዲያቆኑ ድምጽ በሚማርክ ዜማ ይሰበካሉ፡፡ የዳዊት መዝሙር ለማንኛውም አገልግሎት የሚውል ልዩ ጸሎት ነው፡፡ ትንቢትን አቅርቦ የመናገር ጸጋ የበዛለት ነቢዩ ዳዊት ይህንን ልዩ የሆነውን ምስጋናና ጸሎት ለመንፈስ ልጆቹ ሁሉ ሰጥቶናል፡፡ እኛም የተሰጠንን ይህን ልዩ ጸሎት እየተገለገልንበት እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡
ዳዊት ከትልልቅ ወንድሞቹ ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሆኖ በመገኘቱ ከእረኝነት ወደ ንግሥና ወንበር የተቀመጠ ነቢይ ነው፡፡ ይህ ነቢይ አባቱ እሴይ እናቱ ደግሞ ሁብሊ ይባላሉ፡፡ ሰባት ልዩ ልዩ ሀብታት  ማለትም ሀብተ ትንቢት፣ ሀብተ ክህነት፣ ሀብተ መዊእ፣ ሀብተ ፈውስ፣ ሀብተ በገና፣ ሀብተ መንግሥት እና ሀብተ ኃይል ተሰጥተውታል፡፡ ይህ ጻድቅ ነው እንግዲህ  ከላይ በአርእስቱ ላይ የጻፍነውን የጸሎት ክፍል ያስተማረን፡፡ ዳዊት “የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ” አለ፡፡  እስኪ ሁላችንም ወደ ልጅነታችን ወደ ሕጻንነታችን እንመለስ በእውነት ያንን ሁሉ ኃጢአታችንን አምላክ ቢቆጥርብን ኖሮ ዛሬን መኖር እንችል ነበር? በደል ሳይመስለን የሰራነው ያ ሁሉ በደል ቢታሰብብን የዛሬዋን ጸሐይ ለመሞቅ እንታደል ይመስላችኋል? ኃጢአት ሳይመስለን የፈጸምነው ያ ሁሉ ኃጢአት ቢቆጠርብን ሰማይን ቀና ምድርን ዝቅ ብለን ለማየት እንታደል ነበርን? በፍጹም፡፡ አምላካችን ምሕረቱ ብዙ፣ ቸርነቱ ምጡቅ ስለሆነ ያንን በደል አልቆጠረብንም አላሰበብንም፡፡ በልጅነቱ ከእንስሳት ጋር ያልረከሰ፣ ሰውን በሽንገላ ከንፈር ያልተናገረ፣ ሰውን ያልበደለ ማነው? በእርግጥ ልጅነት ማለት ምን ማለት ነው? ለሚለው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት ይገባል፡፡ ጥንተ ፍጥረት አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ሄዋንም የ 15 ዓመት ቆንጆ ሆና በአምላክ አምሳያ ከተፈጠሩ እና በገነት መኖር ከጀመሩ በኋላ 7 ዓመት ከ 1 ወር ከ 17 ቀን ሲሞላቸው ሰይጣን አታለላቸውና ከገነት ተባረሩ፡፡ እስከዚያ ቀን  ድረስ ኃጢአት አልሰሩም ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን አብነት በማድረግ አንድ ሕጻን ከ 7 ዓመት ጀምሮ መጾም፣ መስገድ፣ መጸለይ፣ መመጽወት  አለበት ንስሐ መግባትም አለበት ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ግን ከዚያ በፊት መደረጉ ኃጢአት ሊኖረው አይችልም ምክንያቱም ለሚቀጥለው ሕይወታቸው ልምምድ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ከ 7 ዓመት ጀምሮ የሚሠራ ኃጢአት ይታሰብብናል ይቆጠርብናል ማለት ነው፡፡
በልጅነታችን ብዙ በድለናል፣ ብዙ ኃጢአት ሰርተናል፣ ለቤተሰቦቻችን አልታዘዝም ብለናል፣ ቤተሰቦቻችንን ሰርቀናል፣ አባት እናቶቻችንን አላከብር ብለናል ወዘተ እሱ ሁሉ ኃጢአት ነው፡፡ አስቡት እንግዲህ ንስሐ መግባት የጀመርን አሁን ነው ያውም እየገባን ከሆነ ማለቴ ነው በአብዛኛው ግን የኃጢአት ክምር ከምረናል፡፡ እንግዲህ ዳዊት ይህንን ሁሉ አታስብብን ይላል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ላይ ሆነን በልጅነታችን የሰራነውን ኃጢአት ሁሉ ማስታወስ ስለማንችል፡፡ ነገር ግን ዳዊት ይህንን የልጅነቴን ኃጢአት አታስብብኝ ማለቱ የማውቀውንም የማላውቀውንም አታስብብኝ አትቁጠርብኝ ማለቱ ነው፡፡ ይህን ጸሎት ስትጸልዩ የልጅነታችሁን በደል ታስባላችሁ ያንን ያሰባችሁትን ያወቃችሁትን በደል አምላክ እንዳይቆጥርባችሁ ትማጸናላችሁ፡፡ ከዚያ ትዝ ካለን ኃጢአት ውጭ ያለውን ደግሞ እንዲሁ እንዳይቆጥርብን እንለምነዋለን፡፡ የልጅነት ኃጢአት የሚሠራ ፈጣሪን በማስታወስ አይደለም፡፡ ፈጣሪን የምንፈራበት ይህን ባደርግ እንዲህ እሆናለሁ እንዲህ እደረጋለሁ በሚል ስጋት ውስጥ ሆነንም አይደለም የምንሠራው፡፡ በማን አለብኝነት የምንሠራው ነውና አሁንም ፈጣሪን ዘንግተን በድፍረት የምንሰራውን ኃጢአት አታስብብን ምክንያቱም አስተሳሰባችን በአእምሮ እንዳልጎለመሱ ሕጻናት ስለሆነ፡፡

አምላካችን የልጅነታችንን ኃጢአትና መተላለፍ አያስብብን፡፡ አቤቱ ስለቸርነቱ ብዛት እንደ ምሕረቱም ያስበን፡፡

No comments:

Post a Comment