© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 8/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
አምላካችን ፍጥረትን መፍጠር የጀመረው እሁድ ዕለት ሲሆን ከሥራው ሁሉ ያረፈው ደግሞ በ7ኛው
ቀን ቀዳሚት ሰንበት ነው፡፡ የፍጥረት መጀመሪያው ሰማይና ምድር የፍጥረት መጨረሻው ደግሞ አዳም ነው፡፡ አዳም እንዴት ተወለደ?
የአዳም ልደት ከኅቱም ምድር ነው፡፡ እግዚአብሔርም አለ “ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር… እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ
ፈጠረ፣ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ዘፍ1፥26-27 የአዳም ልደት እንዲህ ያለ ነው፡፡ ይህ ልደት
በሰው ዘር ውስጥ የዓለማችን ቁጥር አንድ ልደት ነው፡፡ ከምድር አፈር አዳም የተወለደበት ልደት ግሩም ነው፡፡ የአዳም ልደት ለአንዴና
ለመጨረሻ ጊዜ በአዳም መወለድ ብቻ የቀረ ነው፡፡ ከአዳም በኋላ በዚህ መልኩ የተወለደ ሰው የለም፡፡ ይህ ልደት ለእኛ ምን ጠቀመን?
ምንም አልጠቀመንም ለመዳናችን ሳይሆን ለመጥፋታችን መነሻ ነበር፡፡ አዳም ትእዛዝን የሻረ ሰው ከሆነ በኋላ እንጅ አፈር ትቢያ እንደነበረ
አልነበረምና፡፡
ሌላው እና አስገራሚው ልደት የሴቲቱ የሔዋን ልደት ነው፡፡ የሔዋን ልደት ደግሞ ከአዳም ልደት
የተለየ ልደት ነው፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት አንቀላፋም ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን
በሥጋ ዘጋው” ዘፍ2፥21 አዳም ከኅቱም ምድር እንደተገኘ ሔዋን ደግሞ ከኅቱም ገቦ (ጎን) ተገኝታለች፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ
“ኦ ዝ መንክር ነሥአ አሐደ አፅመ እም ገቦሁ ለአዳም ወለሐኮ እምኔሁ ብእሲተ ወኵሉ ፍጥረተ ዕጓለ እመሕያው” ከአዳም ጎን አንዲት ዐጽም መንሳት ምን ይደንቅ? ከእርሱ
ሴትን ፈጠረ የሰው ፍጥረትንም ሁሉ ፈጠረ በማለት የሔዋንን ልደት ያስረዳል፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) የሔዋን ልደትስ ለእኛ መዳን
ምን ጠቀመን? እንደ አዳም ሁሉ ለመጥፋታችን እንጅ ለመዳናችን የሚጠቅም ልደት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሔዋን ባደረገችው አመጽ የገነት
ደጅ ተዘጋ ስለሚል ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም፡፡ ዘፍ 3 ን ስናነብብ የምንመለከተውም የጥፋታችንን ውጥንና ፍጻሜ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ
ሁለቱ ልደታት እኛን ማዳን አልተቻላቸውምና ሌላ ልደት አስፈለገ፡፡
ሦስተኛው የሰው ልጅ ልደት የቃየን ልደት ነው፡፡ የቃየን ልደት በዘር በሩካቤ የተወለደው ልደት
ነው፡፡ ከአፈር የተፈጠረው አዳምና ከአዳም ጎን የተፈጠረችው ሔዋን ሁለቱ ባደረጉት ሩካቤ ቃየን ተወለደ፡፡ በዘር በሩካቤ የተወለደ
የመጀመሪያው ሰው ቃየን ነው፡፡ በእርግጥ ሔዋን መንታ ወልዳለች ሉድ የቃየን መንትያ ናት፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ አቤልና አቅሌማ
ተወልደዋል፡፡ (ዘፍ4 ን ተመልከት) አሁን እኛ የምንወለደው ልደት እንዲህ ያለውን ልደት ነው፡፡ ከአባትና ከእናት በዘር በሩካቤ
የምንወለደው ልደት ይህ ሦስተኛው ልደት ነው፡፡ የአዳም የሥጋ አባትና እናት ማነው? የሔዋንስ? የቃየንስ? የሥጋ አባትና እናት መቁጠር የምንጀምረው ከአዳም አባትነትና
ከሔዋን እናትነት ነው፡፡ ታዲያ ይህ ልደት ለእኛ መዳን ምን ጠቀመን? ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ዳንኤል፣ ዘካርያስ፣ ሕዝቅኤል፣ አብርሃም፣
ይስሐቅ፣ ያዕቆብ… እነዚህ ሁሉ በዚህ መልኩ የተወለዱ ቅዱሳን ናቸው ግን ጽድቃቸው ወደ ገነት ማስገባት አልተቻለውም፡፡ ምክንያቱም
በአዳም በኩል የመጣው ኃጢአት መርገም ለእነርሱም ተርፎ ስለነበር፡፡ ታዲያ ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት ያበቃን ልደት የትኛው ልደት
ነው?
ለገነት ያበቃን ልደት አዳም ከኅቱም ምድር፣ ሔዋን ከኅቱም ገቦ፣ ቃየን በዘር በሩካቤ እንደተገኙ
ሁሉ በዘር በሩካቤ የተገኘችው እመ ብርሃን ድንግል ማርያም ያለ ዘር ያለ ሩካቤ በኅቱም ድንግልና የለአባት ጸንሳ የወለደችው የጌታችን
የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው፡፡ የአዳም መርገም ያልነካት ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያም ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣
ድኅረ ጸኒስ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናት፡፡ ያለዘር ያለሩካቤ ጸንሳ የወለደችው ልደት ከእነዚህ ሦስቱ
ልደታት ሁሉ የበለጠ ልደት ሆነልን፡፡ በሔዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በድንግል ማርያም ምክንያት ተከፈተልን፡፡ ለድኅነታችን ምክንያት፣
የአዳም ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት የተፈጸመላት፣ አምላክን ጸንሳ ለመውለድ በቅታ፣ ነጽታ የተገኘች መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት
ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያም ከእናቷ ሃና እና ከአባቷ ኢያቄም መወለዷ ለእኛ ጠቅሞናል፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ ልደታት ሁሉ የበለጠውን
ትልቁን ልደት አምጥታልናለችና፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አርጋኖን በተሰኘ መጽሐፉ ድንግልን ሲያመሰግን እንዲህ ይላል “እግዚአብሔር
ከሰው ልጅ የማይተባበሩ ሦስት ልደታትን ተወለደ፡፡ እኔም አውቄ አደነቅሁ፡፡ ባራተኛው እንጅ የበጎ ዕረፍት አላገኘሁም፡፡ አዳም
ከኅቱም ምድር የተወለደ በተፈጥሮ ነው፡፡ እኔን ግን የጠቀመኝ የለም፡፡ ሔዋንም ከአዳም ግራ ጎን ተወለደች እርሷም በተፈጥሮ ነው፡፡
ለእኔ ግን የጠቀመችኝ የለም፡፡ ቃየንም እንደ ሰው ሁሉ በዘር በሩካቤ ተወለደ የጠቀመኝ የረባኝ የለም፡፡ ስንኳንስ እኔን ራሱንም
አልጠቀመም፡፡ እሊህ ሦስቱ ልደታትም ለማንም ለማን አይረቡም አይጠቅሙምም፡፡ ክርስቶስ ግን ያለዘር ያለሩካቤ ከድንግል ተወለደ ለሁሉ
የሚረባ ለሁሉ የሚጠቅም ሆነ፡፡ ለዚህ ልደት መስገድ መገዛት ይገባል፡፡ ክብር ምስጋና ለዚህ ልደት ይገባል፡፡ ጌትነትና ገናንነት፣
ኃያልነት፣ አዚዝነት፣ እልልታ፣ ግርግርታ ለዚህ ልደት ይገባል፡፡ (አርጋኖን ዘሰኑይ ምእራፍ 2 ቁጥር 4-7)
መልካም ነው:: ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ReplyDelete