© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 22/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ዲያብሎስ እጅግ በጣም አብዝቶ ማራቅ የሚፈልገው ከምሥጢራት ሁሉ የበላይ
ከሆነው “ከምሥጢረ ቁርባን” ነው፡፡ ምሥጢራት ሁሉ የሚደመደሙት በሥጋ ወደሙ ነው፡፡ መሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ንስሓ፣ ምሥጢረ ተክሊል
የሚፈጸሙት በቁርባን ነው፡፡ ይህንን የሚያውቅ የውሸት አባት ዲያብሎስ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ከሥጋ ወደሙ ያርቅሃል፡፡
አንተ ግን “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ከቶ አይጠማም” ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን
አምናለሁና ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነሳውን ሥጋና ደም እመገባለሁ በለው፡፡ /ዮሐ6፥35/ የዘላለም ሕይወትን መውረስ
እንደምትፈልግም አሳወቀው፡፡ “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል” /ዮሐ6፥41/
ስለዚህ ለዘላለም በመንግሥተ ሰማያት ለመኖር ከሰማይ የወረደውን እንጀራ እበላለሁ ብለህ ጠላትህን አሳፍረው፡፡ ጠላት ግን በድፍረት
እንድትቀርብ ሊፈትንህ ይችላል፡፡ የምትቀበለውን ሥጋና ደም የዕሩቅ ብእሲ ሥጋና ደም ነው ብሎ ሊያታልልህም ይሞክራል፡፡ አንተ ግን
አትስማው የምቀበለው ሥጋና ደም በዕለተ አርብ የተቆረሰውና የፈሰሰውን
ሥጋና ደም ነው በለው፡፡ ሥጋና ደሙም መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው እንጅ ጠላት እንደሚለው መለኮት የተለየው አይደለም፡፡
ጠላት ውጊያውን አሁንም አያቆምም “ንስሓ ሳትገባ ሳትዘጋጅ ተቀበል” ይልሃል፡፡ እርሱን ከሰማኸው የይሁዳ እጣ ፈንታ አንተ ላይም
ይደርሳል፡፡ ሳይዘጋጁ ከኃጢአት ሳይነጹ ቢቀበሉት ግሩም ፍዳን የሚያመጣ የሚባላ እሳት ነው፡፡ ይሁዳ በጸሎተ ሐሙስ ከሌሎች ሐዋርያት
ጋር ከቁርባኑ ሥርዓት ተካፋይ ነበረ፡፡ ነገር ግን በልቡ የነበረው ጌታን በ30 ብር የመሸጥ ኃጢአት እንደወጣ እንዲቀር አድርጎታል፡፡
/ማቴ26፥14-29/፣ /ማቴ27÷3-9/ ሥጋና ደሙ ግሩም ፍዳ የሚያመጣ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ በንጽሕና በትሕትና
ንስሓ ገብቶ ሊቀበሉት ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ ለሚቀበለው የዘላለም ሕይወትን የሚያወርስ ጥበብን የሚገልጽ ምሥጢርን ሁሉ የሚያድል
ነው፡፡ ለዚህም ነው ካህኑ በቅዳሴ ሰዓት “ንጹሕ የሆነ ከቁርባኑ ይቀበል ንጹሕ ያልሆነ ግን አይቀበል ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ
በተዘጋጀው በመለኮት እሳት እንዳይቃጠል በልቡናው ቂምን የያዘ ልዩ አሳብም ያለበት ቢኖር አይቅረብ እጄን ከአፍአዊ ደም ንጹሕ እንዳደረግሁ
እንዲሁም ከሁላችሁ ደም ንጹሕ ነኝ፡፡ ደፍራችሁ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም ብትቀርቡ ከእርሱ ለመቀበላችሁ መተላለፍ የለብኝም በደላችሁ
በራሳችሁ ይመለሳል እንጅ፡፡ በንጽሕና ሆናችሁ ባትቀርቡ እኔ ከበደላችሁ ንጹሕ ነኝ” ብሎ እጁን የሚታጠበው፡፡ ዲያቆኑም ተቀብሎ
“ይህን የቄሱን ቃል ያቃለለ ወይም የሳቀና የተነጋገረ ወይም በቤተክርስቲያን በክፋት የቆመ ቢኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳሳዘነው
በእርሱም እንደተነሣሣ ይወቅ ይረዳ ስለበረከት ፈንታ መርገምን ስለኃጢአት ሥርየት ፈንታ ገሃነመ እሳትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል”
ይላል፡፡ ይህ አዋጅ የሚታወጀው ከክርስቶስ ሥጋና ደም ርቀን እንድንቆም ወይም የበይ ተመልካቾች እንድንሆን ተፈልጎ ወይም ለማስፈራራት
ተብሎ አይደለም ንስሓ ገብተን፣ የበደልነውን ይቅር ብለን፣ የቀማነውን መልሰን፣ ተዘጋጅተን በንጽህና ሆነን እንድንቀበል ነው እንጅ፡፡
በድፍረት በኃጢአት እንደተጨማለቁ ተዘሎ የሚበላና የሚጠጣ አይደለም ፍዳ መቅሰፍት ያመጣልና፡፡ ጠላት ግን ይህንን አዋጅ እያሳሰበና
እንደተመቸው እየተረጎመ “ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የበቃህ አይደለህም” ብሎ ከሥጋ ወደሙ ያርቅሃል፡፡ የአዋጁ ዋና መልእክት ንስሓ
ገብታችሁ፣ ከንስሓ አባታችሁ ጋር ጨርሳችሁ ቅረቡ የሚል ነው፡፡ በዚህ ድል ስትነሳው ደግሞ “አንተ ገና ወጣት ነህ ሽማግሌዎች እንኳን
ሳይቆርቡ ያንተ ቁርባን ምንድን ነው” ይልሃል፡፡ አንተ ምክሩን አትቀበል “ሽማግሌዎች የራሳቸው ነፍስ ነው ያላችው እኔም እንደዚሁ
የራሴ ነፍስ ነው ያለኝ ስለዚህ እነርሱ ስላልቆረቡ እኔ መቁረብ የለብኝም? በወጣትነት
ዘመንህ ፈጣሪህን አስብ ተባልኩ እንጅ ሽማግሌዎች የሚሠሩትን እያየህ እንደእነርሱ ሁን አልተባልኩም፡፡ በእርግጥ በጎ ሥራ ሲሠሩ
ልመስላቸው ግድ ነው መጥፎ ሲሠሩ ግን ልመስላቸው አልሻም፡፡ እነርሱ የሚቆርቡበት የራሳቸው ጊዜ ሊኖራቸው ይችላል የእኔ ጊዜ ግን
ዛሬ ብቻ ነው” ብለህ አሳፍረው፡፡ ይህን ሁሉ ብለህ ስታሸንፈው ደግሞ እንደለመደው ከንቱ ውዳሴን ይጨምርብሃል፡፡ ቆራቢ እንድትባል
ብቻ መቁረብን ያለማምድሃል፡፡ ከዚያ በኋላ ልምድ ያደርግብህና ሳትዘጋጅ ንስሓ ሳትገባ በድፍረት መቅረብን ያለማምድሃል፡፡ ስለዚህ
በጣም ጥንቃቄ ልታደርግ ያስፈልጋል፡፡ ሥጋና ደሙን ለመቀበል የግድ ንስሓ መግባት ከንስሓ አባት ጋር መወያየትን ይጠይቃል፡፡ የዘላለም
ሕይወትን ለማግኘት ስትሻ የዘላለም ቅጣት እንዳይመጣብህ ተጠንቀቅ፡፡
No comments:
Post a Comment