Sunday, April 9, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል አንድ



የሊቁ አለቃ ኅሩይ ፈንታ አጭር መግለጫ

በመምህር ልዑለቃል አካሉ
መቅድመ ቃል
ይህ በታላቁ ሊቅ በአለቃ ኅሩይ የተዘጋጀው “ፍኖተ እግዚአብሔር” የተሰኘው ትምህርተ ሃይማኖት አሥራ አምስት አናቅጽ (መክፈያ ክፍሎች) ያሉት፤ የራሱ የሆነ መግቢያ እና መቅድም ኖሮት እንደ አስፈላጊነቱ እና እንደ አንቀጹ ስፋትና መጠን አልፎ አልፎ አንቀጾችን የሚከፍሉ ክፍላት(ክፍሎች) ያሉት ሆኖ የተዘጋጀ በጣም ጠቃሚ የሆነ መድበል ወይም ምዕላድ ነው:: መጽሐፉ በገጽ ብዙም ባይሆን ከፍተኛ የሆነ ትምህርተ መለኮት በከፍተኛ ደረጃ የተገለጸበት፤ የቀደሙትን ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አስተምህሮ እና የሃይማኖት ርቃቄ የሚያሳይ ነው:: ሊቁ አለቃ ኅሩይ እንዳሉት “በቅጥነተ ሕሊና” የሚታየውን ትምህርተ ሥላሴ የሚያራቅቅ፣ ከመናፍቃን ኑፋቄ የሚጠብቅ ትምህርት ይዟል:: መጽሐፉ ከቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስ እና ከልዩ ልዩ መጻሕፍተ ሊቃውንት መረጃዎችን በመጥቀስ በመረጃ የታገዘ ብስል መጽሐፍ ነው:: የመጽሐፉ ዋና ዓላማ ምሥጢረ ሥላሴን መግለጽ ነው:: ስለ “ስመ አካል”፣ ስለ “ስመ ኲነት”፣ ስለ “ስመ ግብር” በግልጽ ያስተምራል:: ይህ መጽሐፍ “”ወላዲ መለኮት” ፤ “ተወላዲ መለኮት”፤ “ሠራጺ መለኮት” ማለት እንደማይገባ ይናገራል:: (አንቀጽ አንድ) በአንድ መለኮት ሦስት ኲነት እንዳለ ይናገራል:: የመለኮት አንድነት አካላትን እንደማይጠቀልል የአካላትም ሦስትነት መለኮትን እንደማይከፍል ያስረዳል:: ይህ መጽሐፍ ሥላሴ በመለኮት አንድ የሚሆኑበትን ምሥጢር ያሳያል:: ከዚህም በተጨማሪ ሥላሴ በግብር በአካል በባሕርይ የሚጠሩበትን ስም ለይቶ ያሳያል:: ስለ ስመ ተረክቦ እግዚአብሔርም ማለት መለኮት ከማለት ጋር አንድ ሲሆን ልዩነት እንዳለው ይናገራል:: እንዲሁም የሥላሴ መንግሥት በአካል ከሦስት የማይከፈል አንድ መሆኑን ይናገራል:: “አብ” ማለት እና “ወላዲ” ማለት “ወልድ” ማለት እና “ተወላዲ” ማለት “መንፈስ ቅዱስ” ማለትና “ሠራጺ” ማለት ልዩ ልዩ እንደሆነ ይናገራል:: ወልድ ከሦስቱ አካላት አንዱ ሲሆን በተለየ አካሉ ሰው የሆነበትን ምሥጢር ያሳያል:: መለኮት የሚለውን ቃል በልዩ ልዩ ሥልት ተርጉሞ ያሳያል:: “ኃይል” “ክሂል” “ሥልጣንም” በአካል ከሦስት የማይከፈሉ መሆናቸውን ያስተምራል:: በአጠቃላይ ይህ መጽሐፍ ለትምህርተ መለኮት ደቀ መዛሙርት እና በሃይማኖት ለማደግ በትምህርተ ሥላሴ ለመራቀቅ በሃይማኖት ትምህርት ለመላቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ግሩምና ድንቅ መልዕክት የያዘ መጽሐፍ ነው:: እኔም ይህን ጽሑፍ ለማንበብ ባገኘሁት ጊዜ ለንባብ በሚያዳግት ታይፕ ተጽፎ አንድ መቶ ገጽ ያለው ሆኖ አገኘሁት:: በአነበብኩት ጊዜ በጣም የበሰለ “ትምህርተ መለኮት” የተገለጠበት ትምህርተ ሊቃውንት ሆኖ አገኘሁት:: በመሆኑም የቀደሙት ሊቃውንት አስተምህሮ ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደገና አቅንቼ ጽፌ ለአንባቢ በሚመች መንገድ አቅርቤዋለሁ:: ሊቁ የጠቀሧቸው መጻሕፍት ከታተሙት መጻሕፍት ጋር በምዕራፍ እና በቁጥር ስለማይገናኙ ከታተሙት መጻሕፍት ኃይለ ቃሉ የሚገኝበትን አብዛኛውን ምዕራፍ እና ቁጥር በመፈለግ ለማዛመድ ሞክሬአለሁ። የዚህን ጽሑፍ ባለቤት የጌታውን የታላቁ አለቃ ኅሩይ ታሪክም ከልዩ ልዩ ጽሑፎች አፈላልጌ በማግኘቴ አብሬ አሰባስቤ አሳትሜዋለሁ:: የቀደሙትን ሊቃውንት ትምህርት ለማግኘት ዕድል ያጋጠማቸው ደቀ መዛሙርት በየእጃቸው የሚያገኙትን ጹሑፎች በማሳተም ከአበው አስተምህሮ ትውልዱ እንዲሳተፍ እንዲያደርጉ ትልቅ ምሳሌ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ:: ከዚህም ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የአስተምህሮ ሂደትና ስልት እንዲሁም የአስተምህሮ ምንጮችን ለመግለጽ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ትናንት እና ዛሬ” በሚል ርዕስ ጠቅላላ መግቢያ ሠርቸለታለሁ:: ይህም ወደፊት ለሚታተሙት መድበሎች ሁሉ ተቀዳሚ እንደ እሸት የሚቆጠር ሥራና ታላቅ ምሳሌ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ::
 ========================================================
የአለቃ ኅሩይ ታሪክ
ልደት :- ከ፲፰፻፶፭-፲፱፻፵፰ (1855-1948) አለቃ ኅሩይ ፈንታ በጎንደር ክፍለ ሀገር በበጌምድር የሊቃውንት ምንጭ የድጓ ማስመስከሪያ የሊቃውንት መነሃሪያ በሆነችው በቤተልሔም ተወለዱ:: የተወለዱት በ፲፰፶፭ ዓ.ም መስከረም ፲፮ ነበር:: አባታቸው የተማሩ ሊቅ ከመሆናቸውም ባሻገር የቤተልሔምና የአካባቢዋ ሊቀ ካህናት ነበሩ:: ስማቸውም ሊቀ ካህናት ፈንታ ይባል ነበር:: እናታቸው ወይዘሮ ብሪቱ ይባሉ ነበር:: የአለቃ ኅሩይ ወላጆች ብዑላነ ጸጋ (ባለጸጎች) እንደነበሩ ይነገርላቸዋል:: ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ስለ ጌታው አለቃ ኅሩይ በጻፉት አጭር የሕይወት ታሪክ ላይ “አባታቸው የወይን ጠጅ ድረስ የሚያጠጡ ባለጸጋ ነበሩ” ብለው በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ከታደሉ ቅዱሳን ሰዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል:: መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ዝክረ ሊቃውን ት ፲፱፻፷፫ ዓ.ም

ዕድገት :- የአለቃ ኅሩይ አባት የሊቀ ካህናት ፈንታ ድንገተኛ ሞትና የእናታቸው የወ/ሮ ብሪቱ ትጋት የአለቃ ኅሩይ ዕድገት፦ ሊቀ ካህናቱ አባታቸው በድንገት ስላረፉ በሕፃንነታቸው አባታቸውን ያጡትን ሕፃን በመልካም አስተዳደግ ለማሳደግና ለቁም ነገር ለማብቃት ወ/ሮ ብሪቱ በትጋት መሥራት ጀመሩ:: እንደ አባት እንደ እናት ሆነው በቁም ነገር በሥርዓት አሳድገው ትምህርት ቤት አስገቧቸው:: ብሩህ አእምሮ የነበራቸው የቀለም ሰው ስለነበሩ በአጭር ቀን ውስጥ ከንባብ እስከ ዜማ ያለውን ትምህርት አጠናቀቁ:: መልአከ ብርሃን ይህን ሁኔታ “አእምሮአቸው እንደተዳመጠ ብራና ቀለም የሚቀበል ስለሆነ ከንባብ እስከ ዜማ ያለውን ትምህርት በትንሽ ቀን አጥንተው በዚያው ወራት ቅጽል ከባለቤት ለይተው ዘርፍ ከባለቤት አስማምተው ተነሽና ወዳቂ ጠንቅቀው ሲያነቡ ዕጨጌ ቴዎፍሎስ ሰምተው ይህ ልጅ ታላቅ መምህር ይሆናል ብለው ትንቢት ተናግረውላቸዋል” በማለት ነበር የሊቁን የቀለም ሰውነት የሃይማኖት ዐምድ እንዲሆኑ ከእግዚአብሔር በተፈጥሮ ለእውቀት የታደሉ እንደነበሩ የገለጹት:: ክብርት እናታቸው ወ/ሮ ብሪቱም በልጅነቱ አባቱን ያጣው ሕፃን ረዳት አጥቶ በችግር ተፈቶ ትምህርቱን ትቶ የእናቱን ቤት ተመኝቶ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ለትምህርት ጎጃም ሲሄዱ ጎጃም ድረስ ወደ ጎንደር ከተማም ሲሄዱ ጎንደር ከተማው ድረስ በበቅሎ በአህያ ስንቅ እያስጫኑ “ተማር የአባትህን ስም እንድታስጠራ ለቤተክርስቲያን ብርሃን እንድትሆን እኔ እናትህ እያለሁ ምንም የሚቸግርህ ነገር የለም” እያሉ እያበረታቱ በትምህርታቸው እንዲገፉበት ለዚህም ማዕረግ እንዲበቁ አደረጉአቸው:: ከዚህ የተነሳ አለቃ ኅሩይ ምንም እንኳ ሰው የተባለውን (የሆነውን) ሁሉ የሚወዱ ፍቅረ ቢጽ የተሰጣቸው ለሁሉም አክብሮትና ፍቅር ያላቸው የፍቅር ሐዋርያ ቢሆኑም ለእናታቸው ያላቸው ፍቅር የተለየ ነበር:: ይኸውም ሊታወቅ ጌታው አለቃ ኀሩይ አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ አጠገብ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በሰጧቸው ማረፊያ ቤት እያሉ የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ታላቅ ወንድማቸው ሊጠይቋቸው ከቤተልሔም ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ:: አለቃ ኅሩይ “ሁሉን ልትነግረኝ ትችላለህ እናቴን ግን ሞተች ብለህ እንዳትነግረኝ:: የእናቴን ሞት ሳልሰማ እኔ መሞት እፈልጋለሁ” ስላሏቸው የእናታቸውን ሞት ሊያረዱ የመጡት ወንድማቸው ሳይነግሯቸው ተመልሰው ሄዱ:: ሌላም ጊዜ ሲመጡ ተመሳሳይ ነገር ስለተናገሯቸው ታላቅ ወንድማቸው አዝነው “እኔ እንዲህ ሸምግዬ እያየ እንዴት እናታችን በሕይወት ትኖራለች ብሎ ይገምታል” ብለው አዝነው ተመልሰው ሄደዋል:: እንዲህ እያሉ የመጣውን ሰው ሁሉ እየመለሱ የእናታቸውን መሞት ሳይሰሙ እርሳቸው አርፈዋል:: ይህም ለእናታቸው የነበራቸውን ፍጹም ፍቅር ያስታውሰናል:: ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በቃል የነገሩኝ 1999 ዓ.ም፡፡

ትምህርት ቤት
ዕጨጌ ቴዎፍሎስና አለቃ ኅሩይ:- ከላይ እንዳየነው ዕጨጌ ቴዎፍሎስ የአለቃ ኅሩይን የተፈጥሮ ጸጋ ከተረዱ በኋላ በመንፈሳዊ አባትነታቸው አስበው የሊቀ ካህናቱን የአባታቸውን መሞት አውቀው ስለነበር ከእናታቸው ድጋፍ በተጨማሪ በችግር ምክንያት ትምህርታቸው እንዳይቋረጥ በማሰብ ቀለብ አዘውላቸው ነበር:: በወቅቱ የድጓ ምስክር ከነበሩት ከመምህር ደርሶ "ዜማ" እንዲማሩ ያደረጓቸው ዕጨጌ ቴዎፍሎስ ናቸው:: የአለቃ ኅሩይን የትምህርት ቤት ሕይወት ስለ አለቃ ኅሩይ ታሪክ ከጻፉት ሊቃውንት መካከል ጥሩ አድርገው የጻፉት “ዘወትር ከጉባኤያቸው እየተገኙ የተሰወረውን ምሥጢር የምሥጢር ባለቤት ከሆኑት ከአለቃ ኀሩይ ይረዱ ነበር” ብለው ሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌ (አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ዘጎንደር) ስለአለቃ ኅሩይ ታሪክ ሲጽፉ የጠቀሷቸው የዲማው ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ናቸው:: መልአከ ብርሃን አድማሱ “ዕጨጌ ቴዎፍሎስ ቀለብ ሰጥተው የድጓ ምስክር ከነበሩት ከመምህር ደርሶ ዜማ እንዲማሩ አድርገዋቸዋል:: እሳቸውም (አለቃ ኅሩይ) በዚህ ትምህርት ቤት ድጓ አንድ ጊዜ ከዘለቁ በኋላ ተድባበ ማርያም ሂደው አለቃ ወረደ ቃል ከሚባሉት መምህር ቅኔ ተምረው ተቀኝተው እንደገና ጎጃም ተሻግረው አጋሜና ቢሰውር ከሚባሉት ስመ ጥር መምህራን ቅኔውን አስፍተው እስከ አገባቡ ጠንቅቀው አውቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንደገና ድጓውን መላልሰው አጥንተው ለምስክርነት ተመርቀዋል:: መምህር ደርሶም በእኔ እግር ተተክቶ የድጓ ምስክር ይሆናል እያሉ ሲያስቡ ልቦናቸው ወደ መጻሕፍት ትምህርት ስላዘነበለ ጎጃም ተሻግረው ደብረ ጽላሎ ከአለቃ እንግዳ ብሉያትን አጠኑ:: ከዚያም ጎንደር ሂደው ከታላቁ መምህር ከወልደ አብ ወልደ ሚካኤል በጥቂት ቀን የሐዲሳትን ትርጓሜ አጥንተዋል:: በዚያው ጊዜ (ጎንደር ሳሉ) አዕምሮ ከሚባሉ የአቋቋም መምህር አቋቋም ተምረዋል:: ድምፃቸው በተፈጥሮ መልካም ከመሆኑም በላይ ዜማ ያሸው ስለሆነ በጎንደር ባህል ሲዘሙ ሲመረግዱ ዚቅ ሲያወርዱ መልስ ሲመልሱ “እንስማው የሚባሉ እጅግ የተመሰገኑ ነበሩ” ብለው ጽፈውላቸዋል::  ዝኒ ከማሁ አድማሱ ጀምበሬ (መልአከ ብርሃን) ዝክረ ሊቃውንት በ፲፱፻፷፫ ዓ.ም፡፡ ጎንደርን ድርቡሽ እንዳጠፋው ሊቃውንት እንደተሰደዱ ለብዙ ዘመናት የኢትዮጵያ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሥልጣኔ፣ አስተዳደር፣ ዕውቀት ማዕከል፣ የሊቃውንት መንደር፣ የመላው የኢትዮዽያ መናገሻ ማዕከል ሆና ትኖር የነበረችውን ጎንደርን የእስላም ኃይል ገብቶ ባቃጠላት ጊዜ ሊቃውንቱ እያዘኑ እያለቀሱ ከእሳትና ስለት የቀሩት ለዘር ይተርፉ ዘንድ ተሰደዱ:: እነ መምህር ወልደ አብ ወልደሚካኤልን ጨምሮ ብዙ ሊቃውንት በእስላሞች ሰይፍ ታረዱ:: ከሞት የተረፉትም ብሶታቸውንና የሀገራቸውን ጥፋት በቅኔያቸው እያስታወሱ እያለቀሱ ተሰደዱ:: በ፲፰፻፹፰ (1888) ዓ.ም ጎንደርን ድርቡሽ ባቃጠላት ጊዜ ከአንድ ሊቅ የተደረሰ የሐዘን እና የጸጸት መወድስ ቅኔ እነሆ:-
ሠናይተ ሡራሬ ጎንደር ተስፋ ነዳያን
ወተስፋ መኳንንት ጎንደር እንበለ መሥፈርት ወአቅም::
ርግበ ዮሐንስ ጎንደር ርኅርኅተ ልብ እም::
ጎንደር ዘበላዕሌሃ ኢሀሎ ሕማም::
ጎንደር እድምተ ስም::
መካነ ተድላ ጎንደር ወመካነ መብልእ ጥዑም::
ጎንደር ቤተ ኢያሱ ወቤተ በካፋ ግሩም::
ጎንደር ዘትሤንያ ለሀገረ ዳዊት ምድረ ሰላም::
መሐድምተ ትኩን እስከ ለዓለም::
እፎኑ ተመዝብረት እንበለ ፍዳሃ ከመ ሶዶም:: አድማሱ ጀምበሬ (መልአከ ብርሃን) ዝክረ ሊቃውንት ፲፱፻፷፫ ዓ.ም
 ================================================
በዚህ ክፉ ዘመን ከተሰደዱት መካከል አንዱ አለቃ ኅሩይ ከመምህር ወልደ ጊዮርጊስ ጋራ ወደ ቤተልሔም ወደ መካነ ትውልዳቸው ተመለሱ:: “ቤተልሔም ጥቂት ቀን ከቆዩ በኋላ ወደ ግሸን ሄደው የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜና አቋቋም ሲያስተምሩ ቆይተው ወደ ደብረ ሊባኖስም በመሔድ ጉባኤ ዘርግተው ሲያስተምሩ ነበር:: በዚህ ጊዜ ነበር ራስ ዳርጌ የሊቁን ብቃት በመመልከት የሥሬ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲሆኑ የጠየቁአቸው:: እርሳቸው ግን መናኝ በመሆናቸው መጽሐፍ በመመልከት ዘመናቸውን እንዲፈጽሙ ስለወሰኑ ሹመቱን አልፈልግም ብለው ትተውት ወደ አዲስ አበባ መጥተው መዝሙር ካሣ ከሚባሉት ከጎንደሩ ሊቅ መጽሕፍተ ሊቃውንትን አጠኑ:: ከዚያም ደብረ በግዕ ወርደው ከአለቃ ወልደ ማርያም ሊቃውንትን አደረሱ።” (አስመሰከሩ) በማለት መልአከ ብርሃን አድማሱ የአለቃን ታሪክ በጻፉበት አምዳቸው ዘግበዋል:: ከዚህ በመቀጠል የታላቁን ሊቅ የጌታው አለቃ ኅሩይን ትጋትና ምሥጢር ለማደላደል ለማራቀቅ ነገረ እግዚአብሔርን ያውቁ ከነበሩት ሊቃውንት ጋር በመወያየት የልቦና ደስታ ያገኙበት እንደነበር፣ ዕለት ከዕለት ከኃይል ወደ ኃይል ይራመዱበት፣ መጻሕፍትን ማንበብ ዋና የዕለት ተለት ተግባራቸው ሁኖ ይኖሩ እንደነበር ሲያስገነዝቡ “ከዚህ በኃላ ወደ ጎጃም ተሻገሩ:: በዚያን ጊዜ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ነበሩና አክብረው ተቀብለዋቸዋል:: እርሳቸው ግን በመጻሕፍት ፍቅር ብቻ የተወሰኑ ስለሆኑ ደጅ ልጥና ልሾም ልሸለም ሳይሉ ብሉያትን ከብሉይ መምህራን ከነ መምህር ሰውአገኘሁ፣ ከእነ መምህር ጸበሉ፣ ከእነ አለቃ ገብረ ኤልያስ፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን ከእነ አለቃ ተስፋ፣ ከእነ ሊቀ ጠበብት ወልደ ሥላሴ፣ ከእነ መልአከ ሰላም ገብረ ማርያም፣ ከእነ መምህር እንግዳ እሸት ጋራ እየተጨዋወቱ ሐሳብ ለሐሳብ ከተለዋወጡ በኋላ አዋልድ መጻሕፍት በያይነቱ ከሚገኙባቸው ደሴቶችና ገዳማት በነዘጌ፣ በነክብራን፣ በጣና ቂርቆስና በዲማ እየተዘዋወሩ ተመለከቱ:: ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ብዙ ተማሪ ይከተላቸው ነበርና አንድም ቀን ጉባኤ ፈትተው አያውቁም” በማለት መልአከ ብርሃን የጌታው አለቃ ኅሩይን የቀለም ሰውነት፣ አንባቢ ተመራማሪ የትርጓሜ ሰው እንደነበሩ መስክረዋል:: መልአከ ብርሃን አድማሱ በጉባኤያቸው እየተገኙ ማወቅ የሚፈልጉትን ምሥጢር ለመጠየቅ ከአለቃ ኅሩይ ጉባኤ ቤት ይገኙ ስለነበር በዓይናቸው ያዩትን በጀሮአቸው የሰሙትን የታላቁን ሊቅ የጌታው አለቃ ኅሩይን የዕውቀት ብቃት፣ የአእምሮ ምጥቀት፣ የአስተሳሰብ ብስለት፣ የትርጓሜ ስልት ባለቤትነት፣ የጠፋ መገኛ የተሰወረ መገለጫ፣ አንቀጸ መጻሕፍት መሆናቸውን ሲገልጹ “የተፈጥሮ እውቀታቸውን በትምህርት ስላስፋፉት ትምህርታቸውንም መጽሐፍ በመመልከት ስላደረጁት የጠፋ ንባብ የተሰወረ ምሥጢር ከእርሳቸው ይገኝ ነበር:: አለቃ ኅሩይንም ጠይቆ ሳይረዳ የሚሄድ አልነበርም” በማለት ሊቁ መልአከ ብርሃን ያዩትን መስክረዋል:: አለቃ ኅሩይ በ፲፱፻፬ (1904) ዓ.ም ከጎጃም ወደ ጎንደር ሄደው ነበር:: በወቅቱ የነበሩት ንጉሥ ወልደ ጊዮርጊስም አክብረው ተቀብለው ጸዳ እግዚአብሔር አብን ልቅና ልስጠዎት ይሾሙ ቢሉአቸው አይሆንም ስላሉአቸው የሹመት ፍላጎት የጠፋላቸው ቅዱስ ሰው መሆናቸውን አውቀው ሸልመው ከእነ ተማሪያቸው የሚመገቡትን ቀለብ ሰጥተዋቸው በጎንደር ለሦስት ዓመታት ጉባኤ ዘርግተው አስተምረዋል::
==============================================
የኢየሩሳሌም ጉዞ
ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ በ፲፱፻፲፮ ዓ.ም መጥተው ኢየሩሳሌምን እጅ ነሥተው ተመልሰዋል:: ከዚህ በኋላ ደብረ ሊባኖስ ገብተው ጉባኤ ዘርግተው ሲያስተምሩ ቆይተዋል:: ከዚያም በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አልጋ ወራሽ በነበሩበት ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍት እየተተረጎሙ ሲታተሙ ተጠርተው መጥተው ከሌሎች ሊቃውንት ጋር ሆነው ወንጌልን ተርጉመው አሳትመዋል:: መልአከ ብርሃን እንደገለጹት ከመጻሕፍተ ሊቃውንትም ቄርሎስን ንባቡን ከነትርጓሜው አዘጋጅተው አስረክበዋል:: ከዚህ በተጨማሪ "የቤተ ክርስቲያን ጸሎት" በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ የቀረበው በስደት ዘመን ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምበት የነበረው መጽሐፍ አዘጋጆች ከሆኑት አንዱ አለቃ ኅሩይ ነበሩ:: ሊቀሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህም “ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጻሕፋቸው “ሐዲስ ኪዳንን የተረጎሙት ንቡረ ዕድ ተክሌ (ሐዲስ ተክሌ)፣ አለቃ ኅሩይ ዘጎንደር፣ አለቃ ለማ ዘመካነ ሥላሴ፣ አለቃ ቀጸላ ዘእንጦጦ ማርያም፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው በየክፍላቸው በቅንነት ሠርተው ያበረከቱ ናቸው:: ሥራቸውም ቋሚና ዘላቂ ሆኖ እነርሱንና ንጉሠ ነገሠቱን ሲያስታውስ ይገኛል” ብለው ለቤተክርስቲያን መጻሕፍትን በመተርጎም ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዕውቅና ታላቅ ሊቅ እንደነበሩ ከላይ የተመለከትናቸው መልአከ ብርሃንና ሊቀ ሥልጣናቱ ቋሚ ምስክሮች በመሆን ሊቁን በሥራቸው እንድናውቃቸው አድርገዋል:: (ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህ ርት) ነገር ግን ባልታወቀ ምክንያት የደከሙባቸው መጻሕፍት ለኅትመት አልበቁም:: አለቃ ኅሩይ አበ ብዙኀን ናቸው:: “ዕድለ መልካም ሊቅ ስለነበሩ በጉባኤ የወለዷቸው ደቀ መዛሙርት እጅግ ብዙዎች ናቸው” ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ሊቃውንትን የሚያፈሩ ሊቃውንት የሳቸው የቀለም ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው:: ደቀ መዝሙራቸው የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ ስለ አለቃ ኅሩይ ሲጽፉ “ታላቁ ሊቅ አለቃ ኅሩይ መጻሕፍተ ሐዲሳትንና መጻሕፍተ ሊቃውንትን የዕለት ተግባራቸው አድርገው በጉባኤ ሲያስተምሩ አርባ ዘመን ያህል ቆይተዋል:: መጻሕፍተ ሐዲሳትን በማስተማርእስከ ዕለተ መቃብር ቆይተዋል:: በዚህ ድካማቸው ጊዜ ብዙ ደቀ መዛሙርትን ተክተዋል” ካሉ በኋላ ለምሳሌ ያህል የስምንት ሊቃውንትን ስም ዘርዝረዋል:: ታላቁን ሊቅ ጌታው ዶክተር አለቃ አየለን ጨምሮ ሊቀ ሊቃውንት መኀሪ ትርፌ (ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ዘጎንደር) ፣ አባ ዘካርያስ ንቡረ ዕድ መኩሪያ፣ መምህር ወንድም አገኘሁ፣ አባ ጌድዮን፣ አለቃ ገ/መድኅን፣ አባ ገ/አምላክ ከደቀ መዛሙርቶቻቸው መካከል እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው:: አለቃ ኅሩይ ፍፁም መናኝ ነበሩ:: “አለቃ ኅሩይ ከዚህ ዓለም ክብር የራቁ በመሆናቸው ከቶ አንድ ጥሪት አልነበራቸውም” ካሉ በኋላ ሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌ ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጋር ስለነበራቸው ቀረቤታና በጉባኤያቸው ተገኝተው የከበዳቸውን ምሥጢር ይጠይቁ ስለነበሩ ሊቃውንት፣ ስለተሰጣቸው ዕሤተ አንብዕ፣ ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ጋራ ስለነበራቸው ጽኑ ፍቅር እና ስለመጨረሻው ዕረፍታችው የሚከተለውን ጽፈዋል:: አለቃ ኅሩይ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የጠበቁ እውነተኛ መምህር ስለነበሩ ግርማዊነታቸው ከዕልፍኛቸው አስቀምጠው በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እየረዱ በየዕለቱ ይጎበኟቸው ነበር:: አለቃ ኅሩይ ግርማዊነታቸውን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ ከፍቅራቸው ጽንዓት የተነሳ ደዌያቸውን ሁሉ ይዘነጉት ነበር:: አለቃ ኅሩይ ዕሤተ አንብዕ የተሰጣቸው ስለነበሩ በቅድስት ሥላሴ አጠገብ ግርማዊነታቸው በሰጧቸው ቤት ሳሉ ትሕትና ገንዘባቸው የሚሆን ግርማዊነታቸው ሊጠይቋቸው ሲሄዱ ለማናገር በሩ በተከፈተ ጊዜ ዕንባቸው በሚጸልዩበት አርጋኖን ላይ ሲንጠባጠብ ታይቷል... ሊቃውንቱን የሚንከባከቡ ግርማዊነታቸው እኒህን ሊቅ እንደ ዐይናቸው ብሌን ይንከባከቧቸው ስለነበረ አስታመው አማውተው እስከ መቃብር ሸኝተው ተመልሰዋል:: ...የአለቃ ኅሩይ ሞት ሞት አይባልም ከልባቸው ፈልቆ የአርድእትን ልቡና ያረካው ትርጓሜያቸው አካል ገዝቶ ስለተገኘላቸው:: አለቃ ኅሩይ ከትዕግሥታቸው ብዛት የተነሳ የሐረሩ ሊቅ አለቃ ገብረ አብ ዲያብሎስ ቅሉ ድል ሊነሣቸው አይችልም ብለው የተናገሩት ነገር ሲነገር ይኖራል:: አለቃ ኅሩይ በነበሩበት ጊዜ በአዲስ ዓለም ማርያም የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በዕየለቱ ሊጠይቋቸው ሲመጡ የነበረ ፍቅር ልክ አልነበረውም:: ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ እንደ አረፉ በሰሙ ጊዜ ጉባኤውን አጥፈው በኀዘን ቆይተው የፍቅራቸው ብዛት ሊታወቅ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በዐረፉ በአርባ ቀን አለቃ ኅሩይ ዐርፈው በደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ:: የሐረር ሥላሴ አለቃ፣ አለቃ ለማም ከአለቃ አየለ ሃይማኖተ አበውን ለመስማት ዘወትር ከአለቃ ኅሩይ ጉባኤ ይገኙ ነበር:: የዲማው ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱም ዘወትር ከጉባኤያቸው እየተገኙ የተሰወረውን ምሥጢር የምሥጢር ባለቤት ከሆኑት ከአለቃ ኅሩይ ይረዱ ነበር:: የአለቃ ኅሩይ ታሪክ ብዙ ነበር:: ከብዙ በጥቂቱ በዚህ መጽሐፍ ገልጸነዋል። (ሠለስቱ ሐዲሳት ገጽ ፬፻፹፭) በማለት ነው አባታችን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቋሚ ምስክርነታቸውን የተውልን:: በተመሳሳይ መንገድ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬም የአለቃ ኅሩይን አጭር የሕይወት ታሪክ ሲያጠቃልሉ “በእንደዚህ ያለ አኳኋን ከቆዩ በኋላ እርጅና ከደዌ ጋር ተጭኗቸው ከቤት በዋሉ ጊዜ የሰው ውለታ የማይቀርባቸው ግ/ቀ/ኃ/ሥላሴ በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ የተሰናዳ ማረፊያ ቦታ ሰጥተው እጅግ በተመቻቸ አያያዝ ሲረዱ ቆይተው በ፺፰ ዓመታቸው በ፲፱፻፵፰ ዓ.ም ሐምሌ ፲፮ ቀን ዐርፈው በደብረ ሊባኖስ ተቀብረዋል” ብለዋል:: በሃይማኖት ወደ ሚናፍቋት በቃለ መጻሕፍት ወደ ለመዷት ወደ ርስተ ቅዱሳን ወደ ሕጽነ አብርሃም ወደ ማታልፈው መንግሥተ እግዚአብሔር ሄደዋል:: ይህንንም በተመለከተ መምህር አባ ዓለሙ በላይ የብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ባልንጀራ በቃል ከብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የሰሙትን ታሕሣስ 18፤ 2001 ዓ.ም እንደሚከተለው አጫውተውኝ ነበር፤ “አለቃ ኅሩይ ማክሰኞ ሊያርፉ እሁድ ቀን መምህር ያሬድ (አቡነ መርሐ ክርስቶስ) ምሥጢር እየጠየቁ ሳለ “እኽ ሳላመልጥህ ጠይቅ፤ ላመልጥህ ነው ጠይቀኝ” አሏቸው አለቃ፤ አቡነ መርሐም ጌታው እድሜዎ ሰፊ ነው፤ ይበቃዎታል ግን እኔ የሃይማኖተ አበውን ምሥጢሩን ሳልረዳው የተማርኩትን ከፊትዎ አንብቤ ሳልዘልቀው በመሞትዎ ብቻ ነው የማዝነው አሏቸው፤ “አዎ እኔም ለብዙ አስቤህ ነበር ግን ሐዲሳቱን አውቀኸዋል፤ ከሐዲሳቱ የወጣ ምሥጢር በሃይማኖተ አበው የለም፤ ያንኑ ምሥጢሩን በምሳሌ ማብዛት መግለጽ ነው እንጂ፤ ለሁሉም ምዕላዱን አንብበው፤ ነገር ያለበትን እና ኃይለ ቃሉን በምዕላዱ ላይ አውጥቼዋለሁ” አሏቸው፤ ሰኞ አንደበታቸው ተያዘ፤ ማክሰኞ አረፉ፤ ቀደም ብለው ራሳ ካሳ መጥተው “ቀብርዎት የት ቢሆን ይወዳሉ ቅድስት ሥላሴ ይሁን ወይስ ደብረ ሊባኖስ ነው የሚፈቅዱት” አሏቸው፤ አለቃም “ፈቃዴ ደብረ ሊባኖስ ቢሆን ነው፤ ግን ፈራሽ ሥጋ ተሸከሙ አልልም፤ እግዚአብሔር ከፈቀደው ይውደቅ” አሉ፤ ከዚህ በኋላ ሲያርፉ የቤተ ክርስቲያኑ ደወል ተደወለ፤ ቅድስት ሥላሴ ከቤተልሄሙ መቃብር ተቆፍሮ ነበር፤ ነገር ግን ራስ ካሳ በኋላ ደረሱና “የለም አይሆንም ደብረ ሊባኖስ ነው የሚሄዱ” ብለው ደብረ ሊባኖስ ወስደው ቀበሩአቸው፤ አጼ ኃይለ ሥላሴም ደብረ ጽጌ ድረስ ሸኝተው ተመልሰዋል” ብለውኛል። ቅዱስ ያሬድ የጥናት እና የተራድኦ ማዕከል የቀደሙትን አባቶቻችንን ትምህርት፣ ጥበብ፣ ታሪክ ለትውልድ ለማስተዋወቅ ለማቆየት የጀመረው የሥራ ፍሬ በታላቁ ሊቅ በጌታው አለቃ ኅሩይ ታሪክ እና ትምህርተ ሃይማኖት በመጀመሩ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል። በረከተ አበው መምህራን አይለየን!
=================================================
ቅኔዎች
ለመታሰቢያ ከቀረቡት ከአለቃ ኀሩይ ቅኔዎች ጥቂቶቹ
መወድስ ፩
ሰብዓ አዝማነ አርድተ ብካይ እም ሕዝበ ዘመኑ ዮሐንስ ለስብከተ ሐዘን ሐረየ፤
ወማዕከለ ኀዘን ፍኖቱ ለእመ ጸምአ ብካየ፤
አምነ ሳምራዊት ሰአለ ዐይነ ወንጌላዊ ከመ ይስተይ ማየ፤
ሕዋሳቲሁ ሐዋርያት እስመ ሀገረ ሞት ቦኡ ለተሳይጦ ሲሳየ፤
ተጋብኡሂ ገጻቲሁ ማዕከለ አዕይት ዝየ፤
ላዕለ ዕፅ ከመ ይሰቅሉ ህሊና ዘኢጌገየ፤
ወውስተ ካልዑ መብልዕ ሐሞተ ምሳሌ ወደየ፤
በሕለተ ወይን ትርጉሜሁ ስታየ ስሙ እስመ ዐበየ፤
መወድስ ፪
ሞተ ፍጡራን ተምህረ ገቢረ ትሕትና አንቃዕዲዮ ኢይርአይ ገጸ አረጋዊ በዐይኑ፤
ባህቱ ይብለነ ዉስተ ደብረ ዳሞ መካኑ፤
እንበለ ውእቱ አረጋዊ ሥጋ ሰብእ ለቢሶ ዘሞአኒ መኑ፤
ንንግር ወንዜኑ፤
ከመ ከመ ሊቁ ኤልያስ ለአረጋዊ መጠኑ፤
ለሕያዉኒ ገብረ ክርስቶስ ላዕካነ ምሥጢር ይኩኑ፤
ካህናተ ሰማይ ሕማማት መንበረ ሥጋሁ ዘየትጥኑ፤
ወእም ሐዋርያት ገድላት እለ ተአመኑ ዮሐንስ ዐፄ ሥጋ ዘረፈቀ ውስተ ሕፅኑ፤ (የግዕዝ ቅኔያት የሥነ -ጥበብ ቅርስ ንባብና ትርጓሜው ከኢትዮጽያ ቋን ቋዎች አካዳሚ 1980)
መወድስ ፫
አሣዕነ ገባዖን ነሥአ ውስተ ደብረ ዘይት መከልአ ምድያም ቃል መግቦተ ርእሱ ኀበ አእመረ፤
ወበአልባሰ ብርት ገባዖን ዕርቃነ መልአክ ሰወረ፤
ለኢየሩሳሌም እንዘ ቅርብት መላክ በጊዜ ነገደ ርህቅተ ምድረ፤
ኢያሱ እሰከ ሰአለ ለማዕረረ ቃሉ ድንግል ከመ ይፈኑ ገባረ፤
ወገባዖን ቀዳማዊ ድኅረ በምሳሌ አንጸረ፤
ጸወርተ ዕፀው ከመ ይኩኑ ለቤተመቅደስ ዘተመዝበረ፤
ሥጋ ወቃል ተሰናዕዎ ዕፅ አንበረ፤
እብነ ዘለፋ መልዕልተ ወርቅ ብልጣሶር ዘአንበረ፤ ( አድማሱ ጀንበሬ:: መጽሐፈ ቅኔ በ ፲፱፻፷፫ ዓ.ም)
===================================

No comments:

Post a Comment