Monday, April 3, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፲፭



© መልካሙ በየነ

መጋቢት 25/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በቅብዓት እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚጠቀሱ ብርቅ ጥቅሶች አሉ፡፡ እነዚህን ጥቅሶች በጥሬው በማንበብ ወደ ክህደት ሲያመሩ ስንመለከት በጣም እናዝናለን፡፡ “ቃል ይገድላል ትርጓሜ ያድናል” እንዲሉ እነዚህን በጥሬው የተቀመጡ ቃላትን ከሊቃውንቱ ትምህርት ጋር በማስማማት መተርጎም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ማንኛውም ትርጓሜ ትምህርተ መለኮትን የማያፋልስ መሆን አለበት፡፡ እነርሱ ግን ጥሬውን እንቆረጥማለን እያሉ ቃሉ የብረት ቆሎ ሆኖባቸው ጥርሳቸው ሲሰበር ስንመለከት አብዝተን እናዝናለን፡፡ የሚመለሱት እንዲመለሱ በጥርጥር ላይ ያሉ ወገኖቻችንም እውነታውን እንዲረዱ እነርሱ የሚያነሷቸውን ጥቅሶች በሊቃውንቱ ትርጓሜ እንዴት ተተረጎሙ የሚለውን እንመለከታለን፡፡ እዚህ ላይ ግን ልብ በሉ! እኔ ምንም አልጨምርም አልቀንስም ያለውን የተተረጎመውን ነው የምጽፈው፡፡ መልካም ንባብ!  የሊቃውንቱ አንድምታ ትርጓሜ፡፡
1.  መዝ 2÷2 “ላእለ እግዚአብሔር ወላእለ መሢሁ”
በእግዚአብሔር አብ በእኔ በእግዚአብሔር ወልድ፡፡ በእግዚአብሔር ወልድስ ይሁን ሰቅለው ገድለውታል በእግዚአብሔር አብ ምን ብለው ተነሡ ቢሉ ወልድ ቢነክ አብ ይነክ እንዲሉ ወልድን መስቀል መግደል አብን መስቀል መግደል ሆኖባቸዋልና ባያገኙት ቀርቶባቸዋል እንጂ፡፡ አንድም አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብሎ የመሰከረለት ወልድን እሩቅ ብእሲ ማለት አብን ዕሩቅ ብእሲ ማለት ነውና፡፡
      2.  መዝ 2÷7 “እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ”

“ እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ” አሁን አንተን አይሻም (ቃል ይቤ በል) ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ፣ ባህርይ ዘእም ባህርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡

“ወአነ ዮም ወለድኩከ” አሁንም “አነ” ን አይሻም ዛሬም በተዋሕዶ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡

ተውህቦ ለእግዚአብሔር ቃል ስም በሥጋ ዘበህላዌሁ ይሰመይ እንዲል ስለ ሥጋ እንግድነት  አንድም “ይቤ ሥጋ”  አንተ ሥጋ ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ አንተ ልጄ ነህ ዛሬም በተዋሕዶ ወለድኩህ ማለት በቃል ርስት፡፡ አንድም አሁንም አንተን  እና አነን  አይሻም (ሥግው ቃል ይቤ) ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ ፡፡ ዛሬም አውጻእኩከ አንሣእኩከ ሲል ነው፡፡ በትንሣኤ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ አሁን ኹለተኛ የሚወልደው ሆኖ አይደለም በምሳሌ ተናገረው እንጅ፡፡ ሰው ዘምቶ ያረጃል፤ በልቶ ያፈጃል፡፡ ሕዝብን ሰብስቦ ልጁን አስጠርቶ ልጄ “ዘምቶ ያረጀ በልቶ ያፈጀ ይሉሃል እኔ ነኝ፤ በርስቴ ውጣበት ውረድበት” ብሎ ይሰጠዋል፡፡ እሱም ወጣሁ ልጅ ነኝ ፈላሁ ጠጅ ነኝ ብሎ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ይዘምታል፡፡ በርስቱ ርስት  በጉልቱ ጉልት ጨምሮበት  ይመጣል፡፡ አባቴ በሰጠኸኝ ርስት ጉልት ጨምሬበት መጣሁ ይለዋል፡፡ እርሱም ቀድሞም ልጄ ዛሬም ልጄ ይልቅስ የዛሬው ይብለጥ ይለዋል፡፡ ጌታም ከአቤል ጀምሮ እስከ ዕለተ ዓርብ ያሉትን ነፍሳት “እለ ውስተ ሲዖል ፃዑ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከሰቱ ወርእዩ ብርሃነ ዐቢየ” በገነት አድርጎ ባረገ ጊዜ ልጄ ነህ አለው እንጅ፡፡
3.  መዝ 44÷7 “አፍቀርከ ጽድቀ ወአመጻ ጸላዕከ በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዓ ትፍሥሕት እምእለ ከማከ”
“አፍቀርከ ጽድቀ ወአመጻ ጸላዕከ በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ”
እውነትን ወደድህ ሐሰትን ጠላህ ማለት ትንቢተ ነቢያትን መፈጸምን ወደድህ አለመፈጸምን ጠላህ አንድም ሰው መሆንን ወደድህ አለመሆንን ጠላህ፡፡ ሰው እሆናለሁ ብሎ በነቢያት አናግሮ መቅረት መጥላት የነቢያትን ነገር ሐሰት ማድረግ ነውና፤ አንድም ቀጠሮ መፈጸምን ወደድህ አለመፈጸምን ጠላህ፡፡ አንድም ጻድቅ አምላክ ወልደ አምላክ የሚልህን ወደድህ፤ ወአማፄ ሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ የሚልህን ጠላህ፡፡
“በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ”
ሰው መሆንን ስለወደድህ አለመሆንን ስለጠላህ የባሕርይ አባትህ እግዚአብሔር አብ አዋሐደህ፡፡ አንድም አግዚአብሔርነትህ አምላክነትህ አዋሐደህ፡፡
“ቅብዓ ትፍሥሕት እምእለ ከማከ”
እምእለ ከማከ እንዳንተ ያሉ ነቢያት ካህናት ከተቀቡት ልዩ የሚሆን ቅብዓ ትፍሥሕትን ማለት ተዋሕዶን ተዋሐድህ፡፡ አንድም ነቢያት ካህናት ከተቀበሉት ልዩ የሚሆን ቅብዓ ትፍሥሕትን ማለት ልዩ ተዋሕዶን ተዋሐድህ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ዘይኄይስ ያለውን ዮሐንስ አፈወርቅ በዘይተ ፍሥሐ ብሎ ወስዶታል፡፡ ዘይኄይስ ማለቱ የሱ የማይነሳ ሕጸጽ የሌለበት የባህርይ የነሱ የሚነሳ ሕጸጽ ያለበት የጸጋ የሱ ከራሱ የነርሱ ግን ከርሱ ነውና፡፡
4.  ኢሳ 42÷1-2
ናሁ ቁልዔየ ዘአኀዝክዎ
እነሆ በስልጣኔ የያዝኩት ዘሩባቤል፡፡ ወእስራኤልኒ ኅሩይየ፤ የመረጥኩት  ዘሩባቤል፡፡ ዘተወክፈቶ ነፍስየ፤ ልቡናየ የወደደችው ዘሩባቤል፡፡ ወወሀብኩ መንፈስየ ዲቤሁ፤ መንፈሰ ረድኤትን ያሳደርሁበት ዘሩባቤል፡፡ ወናሁ ያመጽእ ፍትሐ ለአሕዛብ፤ እነሆ ለአሕዛብ ኦሪትን ያስተምራል፡፡ ኢይኬልሕ ወኢይጠርእ፤ አይጮኽም፤ አይገነታም (በጥርአ ቃል እንዲል፤ ጥበብ 17÷18)፡፡ ወኢይሰምዕዎ ቃሎ በአፍአ፤ በአፍአ ያሉ ሰዎች ቃሉን አይሰሙትም፡፡ የቃሉን መለዘብ መናገር ነው፡፡ አንድም ናሁ ቁልዔየ ዘአኀዝክዎ፤ በስልጣን አንድ የምንሆን ልጄ ክርስቶስ፡፡ ወእሥራኤልኒ ኅሩይየ፤ የመረጥኩት ልጄ ክርስቶስ፣ ልብነቴ የወደደችው ልጄ ክርስቶስ፣ መንፈስ ቅዱስን በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ያስቀመጥሁበት ልጄ ክርስቶስ፣ ለአሕዛብ ወንጌልን ያስተምራል፡፡ አይጮኽም አይገነታም በአፍአ ያሉ ሰዎች ቃሉን አይሰሙትም ማለት የቃሉን መለዘብ መናገር ነው፡፡ ከዚህ እንዲህ አለ፤ ከዚያ ወአልዐለ ቃሎ በምኩራብ ይላል ዮሀ 7÷28 አይጣላም ቢሉ አይጣላም፡፡ ከዚህ እንዲህ ማለቱ በሥጋዊ ነገር አይከራከርም ሲል ነው፡፡ ከዚያ ወአልዐለ ቃሎ ማለቱ መንፈሳዊውን አሰምቶ ያስተምራል ሲል ነው፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment