Tuesday, April 25, 2017

የሃይማኖት መሠረት ክፍል ፩


© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 17/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም በፍቅር በአንድነት አደረሰን አደረሳችሁ!
ፍጡራን በተለይም ሰውና መላእክት ነጻ ፈቃዳቸው ፈጣሪን እስከ መካድ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ ነን እስከማለት የደረሰ ነው፡፡ ይህም ሊታወቅ እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን መፍጠር በጀመረበት ቀን የፈጠረው መልአክ ሳጥናኤል አኃዜ መንጦላእት አቅራቤ ስብሐት ሆኖ ከሁሉ ልቆ ቢፈጠር ፈጣሪውን ረስቶ በዝንጋዔ ኅሊና ታውሮ አነ ፈጣሪሆሙ ለእሉ ፍጡራን፤ የእነዚህ በክብር ከእኔ በታች በማዕረግ የምልቃቸውን መላእክት እኔ ፈጠርኋቸው ፈጣሪያቸው እኔ ነኝ አለ፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ለሳጥናኤል የተሰጠው ነጻ ፈቃድ ፈጣሪውን መካድ ብቻ አይደለም ፈጣሪ ነኝ እስከማለት የደረሰ ድፍረት ነው እንጅ፡፡ ይህን ነጻ ፈቃድ ያገኘው ደግሞ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ነው ከሌላ ከማንም አይደለም፡፡ ነጻ ፈቃዱን እንዴት አገኘው ቢሉ እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በኅሊናቸው አስተውለው በሰጣቸው አእምሮ ተመራምረው ይደርሱበት ዘንድ ተሠወረባቸው፡፡ መሠወሩም መላእክት ሁሉ ፈቃዳቸውን እንዲከተሉ አእምሯቸውን እንዲጠቀሙ ነው፡፡ ፈጥሮ ባይሠወራቸው ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው ብለው ሳይወዱ በግድ ባመሰገኑት እና በተከተሉት ነበረ፡፡ ስለተሠወራቸው ግን ሳጥናኤል እኔ ፈጣሪ ነኝ እስከማለት የደረሰ ነጻነትን አገኘ፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ንቁም በበሕላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ፤ አምላካችንን ፈጣሪያችንን እስከምናገኘው ድረስ በያለንበት እንጽና ሳጥናኤል አምላክ ነኝ ቢላችሁ አትሸበሩ እኛ ከእርሱ በማዕረግ ስላነስን ፈጠርኋችሁ አለን፡፡ ነገር ግን ከእኛ በማዕርግ የምታንሱ አላችሁ እኛ እናንተን መፍጠር አንችልም ስለዚህ ፈጣሪያችንን እስከምናገኘው ድረስ እንጽና ብሎ በመላእክት ዓለም የተፈጠረውን ግርግር አረጋግቶታል፡፡ ይህ ሁሉ ነጻ ፈቃድ ነው፡፡
ዛሬም በዓለማችን የሃይማኖት ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ ይህ ቢሆንም ቅሉ ሃይማኖት ግን አንዲት ናት ምክንያቱም ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ እኛን ሁሉ ሌሎች ፍጡራንንም ሁሉ በየመልካቸው በየወገናቸው የፈጠረ አንድ ፈጣሪ እንደሆነ ስለምናውቅ፡፡ ሆኖም ግን ፈጣሪ ለመላእክት የሰጣቸውን ነጻነት ለእኛም ሰጥቶናልና ሀሰቱን ከእውነት ከክህደቱን ከእምነት አጣርተን እንድንለይበት በሰጠን አእምሮ እየተመራን የመሰለንን ሁሉ እንድንከተል ትቶናል፡፡ ለዚህም ነው ሰው የመሰለውን ሁሉ እያመለከ የሚኖረው፡፡ ያ ሰው የሚያመልከው የሚሰግድለት የሚንበረከክለት ሁሉ ግን ፈጣሪ አይደለም ምክንያቱም ፈጣሪያችን አንድ እንደሆነ የታወቀ ስለሆነ፡፡ ምንም እንኳ የሃይማኖት ቁጥሩ ብዙ የብዙ ይሁን እንጅ ፈጣሪ ግን አንድ ነው፡፡ ይህ ብዙው የብዙ ብዙው ሃይማኖት ሁሉ ግን የሚያመልከው ይህን አንዱን ፈጣሪ ብቻ አይደለም፡፡ ለየራሱ የሆነ ፈጣሪ አለው እንጅ፡፡ ስለዚህ ወደ እውነተኛው ሃይማኖት ወደ ትክክለኛው የቀና መንገድ ለመሄድና የዘላለም ርስትን ለመውረስ አንድ ሃይማኖት እንደ ሃይማኖትነቱ መያዝ ያለበት ጉዳይ መኖር አለበት፡፡ በዚህም እየተመዘነ ማለፍ እና መውደቅ መመረጥ እና መደነቅ አለበት፡፡ በዓለም ዘንድ የተለያዩ ዓይነት አስተሳሰቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ፖለቲካዊ፣ ቁሳዊ፣ ባህላዊ፣ ሥጋዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሃይማኖታዊ ወዘተ አስተሳሰቦች አሉ፡፡ ከእነዚህ አስተሳሰቦች መካከል ግን ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ከሁሉ በላይ የላቀ መሆን ይኖርበታል፡፡ እስኪ ለግንዛቤ ያህል ስለእያንዳንዱ አስተሳሰብ ጥቂት ጥቂት እንጻፍ፡፡
v  ፖለቲካዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ ፈጣሪ ከመኖሩ ካለመኖሩ ጋር የሚገናኝበት ነገር የለውም፡፡ ይህ አስተሳሰብ ራስን ከሌሎች የተሻለ በማስመሰል ማቅረብን ያበረታታል፡፡ በትህትና ራስን ዝቅ በማድረግ ከእኔ የተሻሉ መሪዎች ስላሉ እኔ ልመራችሁ ላስተዳድራችሁ አልችልም ብሎ ለሌላ አሳልፎ የሚሰጥበት አመለካከት የለውም፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ብዙ ተከታይ ለማፍራት ብቻ የማያደርገውን አደርጋለሁ እያሉ መናገርን ይደግፋል፤ ያልተደረገውንም ተደርጓል እያሉ ማውራትን ያበረታታል፡፡ አበርክቶ የሚመግብ በጥበቡ የሚያስተዳድር መስሎ እንዲታይ ራሱን ከማማ ላይ የሚሰቅል ዓይነት አስተሳሰብ  ነው፡፡ የምታየውን እንዳላየህ የምትሰማውን እንዳልሰማህ የምትዳስሰውን እንዳልዳሰስህ አድርጎ በቃላት አቀናብሮ የማቅረብ ብቃት አለው፡፡ በአፉ ሲናገር ስለአንተ የሚጨነቅ የሚያስብ ይመስላል ነገር ግን ለራሱ ብቻ የሚኖር ምቾትን ተድላ ደስታን ለራሱ ብቻ ጠቅልሎ የሚሰበስብ ነው፡፡ የተከታዩን ቁጥር በማብዛት ብቻ እርካታን ያገኘ የሚመስለው ነው፡፡ ምናልባትም ሲበላ የሚነጥበው ፍርፋሪ ሰብስቦ ሌሎችን ይመግብ ይሆናል፡፡ ከእርሱ ሥራ ውጭ ሌላው ሥራ ሁሉ ብላሽ ከንቱ እና ርኩስ ነው ብሎ ያስባል፡፡ የእርሱ ሥራ ግን ሁሉ እውነት፣ ሁሉ ጽድቅ እንደሆነ ያስባል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ሕልውናው በዚህ በምድር ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ሰማያዊ አስተሳሰብ ሰማያዊ አመለካከት የለውም ሕይወት ከምድር ሕልፈት በኋላ ስላላት ዘላለማዊ ኑሮ አያስብም አይጨነቅምም፡፡
v  ቁሳዊ አስተሳስብ፡- ይህ አስተሳሰብ ካልዳሰስሁ አላምንም ካልጨበጥሁ አልከተልም የሚል ነው፡፡ ሕልውናው በሚዳሰስ በሚጨበጥ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ረቂቅ ነገሮችን ምሥጢራትን ሁሉ አይቀበልም፡፡ ሁሉ ነገሩ ከሚጨበጥ እና ከሚዳሰስ ከሚነካካ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ካላየሁ አላምንም ካልጨበጥሁ ካልዘገንሁ አልቀበልም በሚል ደዌ የተያዘ ነው፡፡ ገንዘብ ይጨበጣል ይዳሰሳል ስለዚህም ሁሉ ነገሩን ለገንዘብ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ምግብ ይጨበጣል ይዳሰሳል ይዘገናል ስለዚህም ስለምግብ ሁሉን ነገሩን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ሃብት ንብረት ይዳሰሳል ይጨበጣል ስለዚህም ሃብት እና ንብረት አወርስሃለሁ ብትለው ሁሉ ነገሩን ገልጦ ያሳይሃል፡፡ ፈጣሪየ የሚለው በእጁ የሚዳስሰውን በበቤተ ሙከራ ያረጋገጠውን ቁሳዊ ነገር ነው፡፡ እውነተኛውን ፈጣሪ ቢያገኝ እንኳ ስለቁሳዊ ነገር እንደ ይሁዳ አሳልፎ ይሰጣል እንጅ ጸንቶ አይቆምም፡፡
v  ባህላዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ ስለ ሰፈሩ ባህል ብቻ የሚጨነቅ ነው፡፡ ያ ባህል ምን እንደሆነ፤ ከየት እንደመጣ፤ መነሻው ምን እንደሆነ  የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ልማዳዊ ነውን ሃይማኖታዊ ነውን ትውፊታዊ ነውን የሚለውን ነገር አይመልስም፡፡ የራሱን የበላይነት ለማሳየት ብቻ የሚጥር ነው፡፡ የሌሎችን የሚነቅፍ የሌሎችን የማያከብር ነው፡፡ አስተሳሰቡ በሰፈር ውስጥ የታጠረ ነው፡፡ ሌሎች አማራጮችን አይመለከትም፡፡ የባህሉን የትመጣነት ከማሰብ ከመመርመር ይልቅ ስለሌሎች ባህል ከንቱነት ሌሊት ከቀን ያወራል፡፡ ባህሉ ጠቃሚ ይሁን ጎጅ ይሁን ማመዛዘን አይፈልግም፡፡ በዚህም የተነሣ ፈጣሪውን ከማወቅ ይልቅ በልማዳዊ ባህሎች ተተብትቦ ይኖራል፡፡ ለበሽታው መድኃኒቱ ባህሉ ነው፣ ለዘላለም ሕይወት የሚያበቃው ባህሉ ነው፣ ፈጣሪው ባህሉ ነው፡፡ በአለባበስ ባህሉ ይመካል፣ በአመጋገብ ባህሉ ይመካል፣ በአነጋገር ባህሉ ይመካል፣ በአረማመድ ባህሉ ይመካል፣ በጋብቻ በቀብር ባህሉ ይመካል፣ በሁሉ ነገሩ ባህሉን ያስቀድማል፡፡ ዋና ሥራው ባህሉን የመጠበቅ የማስጠበቅ አይደለም በባህሉ ስም አምልኮትን መፈጸም እንጅ፡፡ አምላኩ ባህሉ ነው፡፡
v  ሥጋዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ እንስሳዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰው ሥጋውን ብቻ ካሰበ እንስሳዊነቱ ገዝፎበታል ማለት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ስለ ሥጋው መድለብ ስለደረቱ መቅላት ስለ ውበቱ ማማር ብቻ የሚጨነቅ ነው፡፡ ሁሉን ነገር የሚያደርገው ለሥጋው ብቻ ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ለሚኖር ሰው ሕይወት ማለት በምድር ላይ የሚፈጸም ነው፡፡ ከሞት ባሻገር ስላለ ሕይወት አያስብም አለ ብሎም አይቀበልም፡፡ ገነት እና ሲዖል የሚባሉ ዓለማት እንደሌሉ ይመሠክራል፡፡ ሕይወት ማለት መብላት መጠጣት መዝፈን መጨፈር መስከር ዝሙት መፈጸም ወዘተ ነው፡፡ ለሥጋ የተፈቀዱትን ሁሉ አንድ ሳያስቀሩ መጠቀም እንደሚያሸልም ያስባል፡፡ ስለዚህም ጫት በመቃም ሲጋራ በማብነን በመዳራት በመስከር እና በመጨፈር ኅሊናውን ያሳረፈ ይመስለዋል፡፡ ብልጭልጭ ዓለም በአሸንክታቧ መረብ ከምታጠምዳቸው ዓሣዎች መካከል አንዱ የዚህ አስተሳሰብ አራማጅ ነው፡፡ ዛሬን ብላ ጠጣ ነገን አታውቀውምና በሚል ፍልስፍና የሚመራ አስተሳሰብ ነው፡፡ የሥጋ ሥራዎችን ሁሉ ሥጋ በማረው እና በፈለገው ጊዜ ያለምንም ገደብ ያለምንም ቅድመሁኔታ መፈጸም ያስፈልጋል ባይ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ እንስሳዊነት ጠባይእ ገዝፎ የሚታይበት  ምክንያትም ለዚሁ ነው፡፡
v  መንፈሳዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ የቁሳዊ አስተሳሰብ እና የሥጋዊ አስተሳሰብ ተቃራኒ ነው፡፡ ረቂቅ በሆኑ ምሥጢራት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ካልዳሰስሁ አላምንም ለሚል አስተሳሰብ ሳያዩ የሚያምኑ ብጹአን ናቸው ይልብሃል የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ አስተሳሰቡ ሙሉ በሙሉ መንፈሳዊ የሆነ ሰው መላእክትን ይመስላቸዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ስለነፍስ ብቻ የሚጨነቅ ነው፡፡ ነፍሱ የምትደሰትበትን እንጅ ሥጋው የምትደሰትበትን ነገር አይሻም፡፡ ነፍሱ በመራችው መንገድ ሁሉ ይጓዛል፡፡ መብላት መጠጣትን መስከር መጨፈርን ዝሙት መዳራትን ወዘተ አብዝቶ ይጠላል፡፡ እነዚህን የሥጋ ሥራዎች ሁሉ ኃጢአት ይሁኑም አይሁኑም አይወዳቸውም፡፡ ሥጋው በመራችው ሳይሆን ነፍሱ ባሳየችው የሚሄድ ሰው ነው፡፡
v  ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ ሁሉን የሚመረምር ከሁሉም አቅጣጫ የሚጠቅመውን ብቻ በመምረጥ የሚከተል ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከሌሎች የተለየ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከላይ ያየናቸው አስተሳሰቦች አሉ፡፡ እነዚያ አስተሳሰቦች በሙሉ የፈጣሪን መንገድ በትክክል የሚመሩ ናቸው ብለን አናምንም፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ከሥጋ እና ከነፍስ አንድ ሆኖ የተፈጠረን ሰው በባሕርይ ልዩ ልዩ የሆኑትን ሥጋ እና ነፍስ አስማምቶ ስለሚኖርበት የሚያስብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በዋናነት መንፈሳዊ አስተሳሰብን እና ሥጋዊ አስተሳሰብን በአንድነት አጣምሮ ለዘላለም መንግሥት ስለሚበቃበት ሁኔታ የሚያስብ ነው፡፡ ሌሎችን አስተሳሰቦችንም እንደአመጣጠቸው በተገቢው ሁኔታ የሚያስተናግድ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ነው እንግዲህ እልፍ አእላፋት ሃይማኖቶች እንዲፈጠሩ ያደረገው፡፡ ሆኖም ግን በመልኩ በቅርጹ ያማረ ፍሬ ሁሉ እንደማይገመጥ እነዚህ በልዩ ልዩ መልክእ እና ጠባይእ የተመሠረቱትን እምነቶች ሁሉ አዎን በጎ ናቸው ብሎ መቀበል አይቻልም፡፡ አንድ ሰው ያድነኛል ይጠቅመኛል ለዘላለም መንግሥት እበቃበታለሁ ያለውን ሃይማኖቱን መርጦ በመያዝ መማር ማስተማር ይኖርበታል እንጅ ከዚያ እዚያ ከዛፍ ዛፍ እንደሚበር ወፍ ለፌ ወለፌ ማለት አይበጅም፡፡ ይህን ሃይማኖት መርጦ እንዲከተል ግን መንፈሳዊነትን (ስለ ነፍስ ማሰብን) እንዲረዳ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ይህንን ነገር በጎ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች በሚል እንደሚከተለው እጽፋለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment