Thursday, April 27, 2017

የሃይማኖት መሠረት ክፍል ፪

© መልካሙ በየነ

ሚያዝያ 18/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በጎ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች
በክፍል ፩ በርካታ አስተሳሰቦች እና ሃይማኖቶች እንዳሉ ተመልክተናል፡፡ እነዚህ በርካታ ሃይማኖቶች ደግሞ የየራሳቸው የሆነ አንዱ ከሌላው ልዩ የሚሆንበት አስተሳሰብ አላቸው፡፡ የአስተሳሰብ ዓይነቶችን አስቀድመን የተመለከትነው ለዚሁ ነው፡፡ እነዚያን አስተሳሰቦች ሃይማኖታዊ መሠረት አስይዘን የምንጠቀምባቸው አይደሉም ሊሆኑም አይችሉም፡፡ ሐዋርያው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ 1ኛ ቆሮ 10÷23 ላይ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም ሁሉ ተፈቅዶልኛል ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም” ብሏል፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ማለት ይህ ነው፡፡ አያችሁት! “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ብሏል፡፡ ሁሉም ዓይነት አስተሳሰብ ተፈቅዶልኛል ነጻ ፈቃዴን ፈጣሪየ አጎናጽፎኛል ማለቱ ነው፡፡  እበላ፣ እጠጣ፣ እሰክር፣ እጨፍር፣ እዘሙት፣ እገድል፣ እሰርቅ እና እደበድብ ዘንድ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ማለቱ ነው፡፡ በሥጋዊ አስተሳሰብ ውስጥ  ለታጠረ ሰው ይህ ጥቅስ የሃይማኖት መሠረቱ ነው፡፡ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” የሚለውን ጥቅስ እንዳነበበ መጽሐፉን የከደነ ሰው ሃይማኖቱ እንደዚህ ባለ በከንቱ ሥጋዊ ፍልስፍና እና በሥጋዊ ፈቃዱ ባህር ብቻ የሚዋኝ ከንቱ ዓሣን ይሆናል፡፡ ይህን የሃይማኖታቸው መሠረት ያደረጉ እንደ ፕሮቴስታንት እንደ እስልምና የመሳሰሉ ሃይማኖቶች አሉ፡፡ ፕሮቴስታንቶች ጭፈራ፣ ዳንስ፣ ዝሙትን ህጋዊ ሃይማኖታዊ ሽፋን በመስጠት ወጣቱን በጭፈራ እና በዝሙት ሽማግሌውንም በማብላት እና በማጠጣት እንዲሁም በቁሳዊ አስተሳሰብ በመጥመድ በገንዘብ እና በልዩ ልዩ አላቂ እና ድቃቂ በሆነ ነገር ሁሉ አፍነው ይዘውታል፡፡ ጭፈራውን በመንፈሳዊ መዝሙር ስም፤ እንደ ጠገበች አህያ መንከባለልን ደግሞ ለኢየሱስ ያደረጉት ትልቅ ውለታ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ሥጋዊነቱ እና ቁሳዊነቱ የጎላበት ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ጾምን ስታነሣባቸው “ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም ከአፍ የሚወጣ እንጅ” ብለው ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ላለመጾም በራሳቸው ፈቃድ በሚተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች ውስጥ ይሰገስጋሉ፡፡ “ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም” ያለው ስለምንድን ነው ብለው አይመረምሩም፡፡ ወደ አፍ የሚገባ ነገር አያረክስም ከተባለማ ጥንተ ፍጥረት አዳም አትብላ የተባለውን ትእዛዝ አፍርሶ ዕጸ በለስን ወደ አፉ በማስገባቱ አልረከሰም ማለት ነዋ፡፡ ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም እያለ የጻፈልን እጅን ታጥቦ ስለመብላት እና ስለአለመብላት እንጅ ስለመጾም እና ስለአለመጾም አይደለም፡፡ ነገር ግን ሆዳቸው ላይ ጅብ የታሰረ የሚመስላቸው ጾምን የሚፈሩ ሰዎች ይህን ጥቅስ ላለመጾማቸው ሃይማኖታዊ ሽፋን አድርገው ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ውስጥ የተተበተቡ ሰዎች መጽሐፋቸውን የሚዘጉት ላነበቡት ቃል ማብራሪያ ከላይ አርእስቱን ከታችም ህዳጉን ሳይመለከቱ ነው፡፡ ጥቅስን አንጠልጥሎ የመሮጥ እና ያችን ሃይማኖታዊ ሽፋን የመስጠት አባዜ የተጠናወታቸው ናቸው፡፡ እስልምናውንም ስንመለከት መንፈሳዊ አስተሳሰብ የሚለው የተዘነጋበት ነው፡፡ ጾም አላቸው ነገር ግን ለዚህ ጾማቸው “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት በትክክል ሲፈጽሙ የሚስተዋሉ ናቸው፡፡ ሥጋቸውን የሚያወፍሩት ደረታቸውን የሚያቀሉት በጾማቸው ወራት ነው፡፡ ጾማቸው ሊገባ ሲል በጾማቸው ጊዜ የሚመገቡትን ሥጋ፣ ቅቤ፣ሾርባ ወዘተ ቀድመው ያዘጋጃሉ፡፡ ይህን ካላደረጉ ማለትም ሥጋ፣ ቅቤ፣ ሾርባ ወዘተ ካልተመገቡ እስከ ምሽት መቆየት እንደማይችሉ ራሳቸውን አሳምነውታል፡፡ ሌሊት ዐሥራ አንድ ሰዓት ተቀስቅሰው ይህንን የላመ የጣመ ኃይል እና ሙቀት ብርታት እና ጽናት የሚሰጠውን በዓይነት በዓይነት የተዘጋጀውን ምግብ ይመገባሉ፡፡ ይህ እንስሳዊነትን ያጎላባቸዋል፡፡ ሌሊት መመገብ የተፈቀደው ለእንስሳት ብቻ ነውና፡፡ ከምሽት ሦስት ሰዓት በኋላ መመገብ ለሰው ልጅ የተፈቀደ አይደለም፡፡ እነርሱ ግን እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ለመጾም ሌሊት ዐሥራ አንድ ሰዓት ሥጋውን ቅቤውን ወተቱን ሾርባውን እያማረጡ ለራሳቸው ይመገባሉ፡፡ ታዲያ ይህ ሃይማኖታዊ ሽፋን ካልተሰጠው በቀር እንስሳዊነት አይደለምን ቁሳዊነትስ አይደለምን፡፡ ሥጋ፣ ቅቤ ካልበላሁ ይደክመኛል ወተት ሾርባ ካልጠጣሁ መጾም አይሆንልኝም የሚልን ቁሳዊነት ከንቱ ሃይማኖታዊ ሽፋንን በማላበስ የሃይማኖት መሠረት ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡  ቁርስ በልቶ ጾም የለምና፡፡ ስለዚህ ነው እውነተኛው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ከሚለው ቃል ቀጥሎ የሚመጣውን ማንበብ እንደሚኖርብን የሚያስገድደን፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ይህንን አስተሳሰብ ውድቅ ያደረገ ነው እንዲህ ይላል፡፡ “ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” የሚል ነው፡፡ ሁሉ የተፈቀደው ለሥጋዊ፣ ለቁሳዊ፣ ለፖለቲካዊ፣ ለባህላዊ ወዘተ አይነት አስተሳሰቦች ነው፡፡ አሁን የጠቀስነው ቃል ወይም ቀጥሎ የመጣው ቃል  “ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” የሚለው ግን ለመንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች የተነገረ ነው፡፡ በሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ውስጥ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” የሚለውን ቃል ብቻ አንብቦ መጽሐፉን አይዘጋም፡፡ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” እስከሚለው ድረስ አንብቦ ምሥጢሩን ይረዳ ዘንድ ደግሞ ከላይ አርእስቱን ከታችም ህዳጉን ይመለከታል እንጅ፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ምንም ይሁን ምን ከሞት በኋላ ያለው ሕይወት የሚያስጨንቀው መሆን አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምድራዊ ሕይወቱ አስተማሪ ይሆን ዘንድ ግብረ ገብነትን የተላበሰ መሆን አለበት፡፡ ግብረ ገብነት ምግባር (መታመኛ ) ነው ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት መጨነቅ ደግሞ ሃይማኖት ነው፡፡ ሃይማኖቱን ከምግባር ምግባሩን ከሃይማኖት አንድ አድርጎ አስማምቶ የሚኖር መሆን አለበት ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ፡፡ ሃይማታዊ አስተሳሰብ ከነፍስና ከሥጋ ለተፈጠረ ሰው ሁለቱን አንድ አድርጎ አስማምቶ ይኖር ዘንድ መንገድን የሚመራ መሆን አለበት፡፡ ለሥጋዊ ነገር ብቻ ያደላ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ እንስሳዊነትን የሚከተል ስለሆነ ሃይማኖት አይባልም፡፡ ሥጋን ከነፍስ ጋር ማስማማት የሚችል አስተሳሰብ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰው ከነፍስና ከሥጋ እንደመሠራቱ መጠን  ኅሊናው ውስጥ ሥጋ ልብላ ነፍስ ልጹም የሚሉበት ተቃራንያን ሃሳቦች የሚመላለሱበት ነው፡፡ እነዚህን ማስታረቅ የሚገባው መሆን አለበት፡፡ የሥጋ ፍሬ አለ የመንፈስም ፍሬ እንዲሁ አለ ሰው ግን በሥጋው እየኖረ መንፈሳዊ ፍሬን ያፈራ ዘንድ ይመከራል፡፡ በሥጋው እየኖረ ስል ነፍስ ከሥጋ ተለይታ ሰው ተብሎ መኖር ስለማይገኝ ነው፡፡ ሰው ሰው ሆኖ የሚኖረው ነፍስና ሥጋው ሳይለያዩ ተዋሕደው አንድ ሆነው ከጸኑለት ብቻ ነውና፡፡ ስለዚህ ነው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ እነዚህን አስማምቶ ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት ተጨንቆ ከቁሳዊ እና ከሥጋዊ አስተሳሰብ ርቆ ያለ ምጡቅ አስተሳሰብ ነው የምላችሁ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ አሁንም ጽሑፉን ቀጥሎበታል “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም” ይላል፡፡ የተፈቀደልን ሁሉ አይጠቅመንም ብሎ ነበር አሁን ደግሞ ጎላ አድርጎ የሚያንጽ አይደለም አለ፡፡ ሁሉ ቢፈቀድልን ሁሉን መሥራት ሁሉን ማወቅ ሁሉን መመርመር ሁሉን ማድረግ ቢፈቀድልንም ማለት ነጻ ፈቃድ ቢኖረንም ሲል ነው፡፡ ሁሉ ግን የሚያንጽ አይደለም አለ፡፡ ሁሉን ብንመረምር ሁሉን ብናደርግ ሁሉን ብንፈጽም ሁሉን ብንበላ ብንጠጣ ሁሉን ሳንመርጥ ብናደርግ መብታችን ነው ሁሉ ተፈቅዶልናልና ነገር ግን በሃይማታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ላላችሁ ወገኖቸ ይህ የምታደርጉት ሁሉ የሚያንጻችሁ በሃይማኖታችሁ የሚያጸናችሁ ርስት መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሳችሁ አይደለም ሲለን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ከእነዚህ ሥጋዊ ምኞቶች እና ሃሳቦች ሁሉ የራቀ መሆን አለበት፡፡
ይቆየን፡፡

ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment