Sunday, April 2, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፲፬




© መልካሙ በየነ
መጋቢት 24/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

የጌታ ሁለቱ ልደታት በሊቃውንት ትምህርት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ በክፍል ፲ ሰባት ማስረጃዎችን ዓይተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ተጨማሪ ዐሥራ ዐራት ማስረጃዎችን እንመለከታለን፡፡

1.  ይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ ም 23 ክ 1 ቁ 2 “ለመወለዱ ጥንት በሌለው አስቀድሞ ዓለም ሳይፈጠር በመለኮቱ ከአብ በተወለደ ዳግመኛም እኛን ለማዳን በኋላ ዘመን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በእግዚአብሔር ልጅ እናምናለን የቀኑ ቀጠሮ ሲደርስ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከድንግልም ተወለደ ያለ ብጹዕ ሐዋርያ እንዳስተማረን”
2.  ይማኖተ አበው ባስልዮስ ም 34 ቁ 6 “ዳግመኛ ለወልደ እግዚአብሔር ሁለት ልደታት እንዳሉት እናምን ዘንድ ይገባናል፤ አንዱ ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፤ ሁለተኛውም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን የተወለደው ልደት ነው”
3.  ይማኖተ አበው ዘአቡሊዲስ ም 41 ክ 7 ቁ 10 “እግዚአብሔር ቃል ሰው እንደሆነ በአንደበቱ የሚያምን በልቡ ግን እንደእኛ አምላክነት የሌለው ዕሩው ብእሲ ከድንግል ተገኘ ብሎ የሚያምን የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ከድንግል እንደተወለደ የማያምን ሰው የምእመናን ባላጋራቸው የመናፍቃን ተባባሪያቸው ነው”
4.  ይማኖተ አበው ዘናጣሊስ ም 46 ክ 1 ቁ 3 “ከእግዚአብሔር አብ በተወለደው በቀዳማዊ ልደቱ የእግዚአብሔር አብ ልጅ ነው፤ ከድንግል በተወለደው በደኃራዊ ልደቱ የሰው ልጅ ሆነ”
5.  ይማኖተ አበው ዘኤፍሬም ም 47 ክ 5 ቁ 30 “ዳግመኛ በዚህ አንቀጽ እንዲህ አለ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመዓለም ከአብ ተወለደ ዳግመኛም ከቅድስት ድንግል ተወለደ”
6.  ይማኖተ አበው ዘኤራቅሊስ ም 49 ቁ 36 “ቀድሞ የተወለደው ልደት ለርሱ ብቻ በርሱ ያለ ነው ኋላ ሰው የሆነበት ልደት ግን ስለእኛ ተደረገ አምላክ አምላክ እንደመሆኑ ታምራትን አደረገ ሰውም እንደመሆኑ ካባሕርዩ ሳይለወጥ ወዶ ሕማምን ገንዘብ አደረገ ከባሕርዩ ሳይለወጥ ሰው ሆኗልና”
7.  ይማኖተ አበው ዘሳዊርያኖስ ም 50 ቁ 2-3 “በማይመረመር ልደት ከአብ እንደተወለደ በአካላዊ ቃል እናምናለን ዓለም ሳይፈጠር የነበረ ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም የሚኖር ቀዳማዊ ደኃራዊ እርሱ ነው፡፡ ዳግመኛ ከአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ በምድር ላይ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እርሱ በሥጋ ተወለደ በዚህ ዓለም የተወለደ ሰው ሁሉ ከዳግማዊ አዳም ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ይኸውም እግዚአብሔር ቃል ነው”
8.  ይማኖተ አበው ዘአፍሮስዮስ ም 51 ቁ 4 “ከአብ የተወለደውን ልደት ሊናገር የሚችል የለም ከአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከእርሱ ጋር አንድ በአደረገው በሥጋ ከድንግል የተወለደው እርሱ ነው”
9.  ይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ም 53 ቁ 16 “ወልድ ዋሕድ ከአብ መወለዱ እንዴት እንደሆነ ከቅድስት ድንግልም መወለዱ እንዴት እንደሆነ አትጠይቀኝ እርሱ በባሕርዩ ከአብ ተወልዷልና ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው”
10. ይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ም 73 ክ 14 ቁ 24 “ቅድመዓለም በመለኮቱ ከአብ ተወለደ በኋላ ዘመንም ዳግመኛ እኛን ለማዳን ከድንግል ማርያም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኖ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮቱ ትክክል ነው ይህ አንዱ ሰው በመሆኑ ከእኛ ጋር አንድ ነው ሁለቱ ባሕርያት በተዋሕዶ አንድ ሆኑ”
11. ይማኖተ አበው ቴዎዶስዮስ ም 92 ቁ 11 “ዘመን ሳይቀድመው ሳይወሰን ከእግዚአብሔር አብ የተወለደ እርሱ ነው፡፡ በማይመረመር ምሥጢር ከድንግል ኹለተኛ ልደትን  በሥጋ የተወለደ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም የወለደችው ንጽሕት ድንግል በእውነት በድንግልና ጸንታ ኖረች እርስዋም እግዚአብሔር ቃልን የወለደች እንደሆነች እናምናለን ወላዲተ አምላክ እንደሆነች እንዲህ በጎላ በተረዳ ነገር እናውቃታለን”
12. ይማኖተ አበው ዲዮናስዮስ ም 93 ቁ 1 “የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ወደ እስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ አባ ሚካኤል በላከው መልእክቱ ሁሉን በፈጠረ በአንድ አብ እናምናለን ዓለም ሳይፈጠር ከአብ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእምባህርይ በተወለደ፤ በኋላ ዘመንም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም ነፍስን ሥጋን ነሥቶ ሰው በሆነ በአንድ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን ከአብ ከወልድ ጋር ቀዳማዊ ማሕየዊ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን”
13. ይማኖተ አበው አባ ገብርኤል ም 94 ቁ 10-11 “ዳግመኛ በቅድምና የነበረ ቃል ጥንት ሳይኖረው ዘመን ሳይቀድመው ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ ወልድ ዋሕድ ዓለምን የፈጠረ የሁሉ መኖር በእርሱ የሆነ በይቅርታው ብዛት የአዳምን ልጆች ይቅር ባለ ጊዜ ከምላቱ ሳይወሰን ከአብ ባሕርይ ሳይለይ ልዑል ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ባሕርያችንን እንደተዋሐደ አምናለሁ፡፡ ሁልጊዜ ንጽሕት ድንግል በምትሆን በድንግል ማኅጸን እንደ አደረ  ከአብርሃም ከተገኘ በድንግልና ከጸና ባሕርይዋ የምታውቅ የምትናገር ነፍስ ያለችው የእኛን የሚመስል የአዳምን ሥጋ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ሊዋሐደው እንደፈጠረ አምናለሁ እንዲህ ቃል ሥጋ ሆነ በባሕርይ በአካል ተዋሕዶ ከሥጋችን ሥጋን ከነፍሳችን ነፍስን ነሥቶ ስለእኛ ሰው ሆነ ያለመለወጥ ያለመጠፋፋትም እኛን መምሰልን ገንዘብ አድርጎ ያለመለወጥ ያለመቀላቀል በባሕርዩ ጸንቶ ኖረ”
14. ይማኖተ አበው ባስልዮስ ም 96 ቁ 12 “እኛስ የቀናች የጸናች የተረዳች የከበረች ምሥጢረ ሥላሴን በማመናችን ላይ የሚሰገድለት ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ቃል ወልድ ዋሕድ ሰው የመሆኑን ነገር እንናገራለን በልብ እንደምናምን በአነጋገር በቃልም እንዲህ እናምናለን፡፡ መቀዳደም ሳይኖር አጋዥ ሳይሻ ተድኅሮ ተፈልጦ ሳይኖርበት እሱ ከአብ እንደተወለደ በኋላ ዘመንም እኛን ስለማዳን ባሕርያችንን ስለማደስ እኛን ወደቀድሞ ርስታችን ስለመመለስ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ነፍስን ሥጋን ነሥቶ ሰው እንደሆነ እናምናለን”
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment