Saturday, April 1, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፲፫


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 23/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

የጌታ ልደታት ሁለት ናቸው እነዚህም ቅድመዓለም ከአብ እንበለ እም ድኅረዓለም ከእመቤታችን እንበለ አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ይህንንም ሊቃውንቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየደጋገሙ አስረድተዋል በመጻሕፍታቸውም ላይ አስፍረዋል፡፡ ይህንንም ከብዙ በጥቂቱ እነዚህን ለማስረጃነት ያህል እንመለከታለን፡፡ “አብ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ወልድን ወለደው” የሚለው የቅብዓቶች ሦስተኛ ልደት ግን በየትም ቦታ ተጽፎ አናገኘውም፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ይህንን ትምህርት ውድቅ የሚያደርጉ የሊቃውንቱን ትክክለኛ እና እውነተኛ ትምህርት እንጽፋለን በመቀጠልም ሁለት ልደታት እነማን እንደሆኑ በቅደም ተከተል እንጽፋለን፡፡
ለሰማያዊ ልደቱ እናት እንደሌለችው ሁሉ ለምድራዊ ልደቱም አባት የሌለው እንደሆነ ሊቃውንቱ እንዲህ ያስተምራሉ፡፡ እዚህ ላይ ለቀዳማዊ ልደቱ መለኮታዊት እናትም ሆነች ሥጋዊት እናት የለችውም ማለት ነው፡፡ ለምድራዊ ልደቱም እንደዚሁ መለኮታዊም ሆነ ሥጋዊ አባት የለውም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት የአብ አባትነት ቀድሞ ዘመን ሳይቆጠር የነበረ  አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር ነው ማለት ነው፡፡ አባትነት እንደ ቀበሌ መታወቂያ በየዘመኑ የሚታደስ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለምድራዊ ልደቱ አብ በድጋሜ አባቱ ሆነ ዳግም በማኅጸነ ማርያም ወለደው አይባልም ቢባልም ክህደት እና ጥፋት ነው፡፡ ይህንንም የምንለው በማስረጃ አስደግፈን ነውና ማስረጃውን እናስቀምጣለን፡፡

1.  ይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ም 60 ቁ 20 ላይ “ዛሬ ግን ከድንግል ብቻ ተወለደ ድንግልናዋንም ባለመለወጥ አጸና ድንቅ የሚሆን መጽነስዋ የታመነ ይሆን ዘንድ ቅድመዓለም ከአብ እንደተወለደም ለማመን መሪ ይሆን ዘንድ” በማለት ድኅረዓለም ከድንግል ማርያም ብቻ እንደተወለደ ከአብ እንዳልተወለደ ይናገራል፡፡
2.  ይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ም 35 ቁ 17 “በምድራዊ ልደቱ አባት አለው አትበሉ በሰማያዊ ልደቱም እናት አለችው አትበሉ እርሱ በምድር አባት የሌለው ነው በሰማይም እናት የሌለችው ነው”
3.  “ዘአልቦቱ እም በሰማያት ወአብ በዲበ ምድር ፤ በሰማይ እናት በምድርም አባት የለውም” አንቀጸ ብርሃን ዘቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ፡፡
4.  ይማኖተ አበው ዘሄሬኔዎስ ም 7 ክ 2 ቁ 20 “ከንጽሕት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን እንደተወለደ እንደሚነግሩን ቀድሞም ከአብ እንደተወለደ እንዲሁ ከአባት ያለእናት ከእናት ያለአባት ለመወለድ መጀመሪያ እርሱ እንደሆነ ለፍጥረት ሁሉ ይነግሩናል” 

5.  ይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ም 73 ቁ 4-5 “ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይመረመር ተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነውና ቀዳማዊ ሲሆን ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ ነው ዳግመኛም ከድንግል በሥጋ የተወለደ ነው ተብሎ ስለርሱ እንዲህ ይነገራል፡፡ የመለኮቱ መገኘት ከድንግል አይደለም፤ ከአብ ከተወለደ በኋላ ጥንታዊ (ቀዳማዊ) ልደትን ሊወለድ አልወደደም ከአብ ጋር ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ የነበረ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ስለሚሆን ስለእርሱ ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ጥንታዊ ልደትን ሁለተኛ እንደሻ ይነገር ዘንድ ይህ ሐሰት ክህደትም ነው፤ ዳግመኛ በሥጋ እንደተወለደ ስለእርሱ እንዲህ ይነገራል እንደሰው ሁሉ አስቀድሞ ቅርጽ የተፈጸመለት ሰው ተገኝቶ ከዚህ በኋላ ቃል ያደረበት አይደለም በእመቤታችን ማሕጸን እርሱ ብቻ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ እንጅ በሥጋም ይወለድ ዘንድ ወደደ በሥጋ መወለድንም ለእርሱ ብቻ ገንዘብ አደረገ” …..እዚህ ላይም በማስተዋል አንብቡት “ከአብ ከተወለደ በኋላ ጥንታዊ (ቀዳማዊ) ልደትን ሊወለድ አልወደደም ከአብ ጋር ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ የነበረ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ስለሚሆን ስለእርሱ ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ጥንታዊ ልደትን ሁለተኛ እንደሻ ይነገር ዘንድ ይህ ሐሰት ክህደትም ነው” ይላል ሊቁ ቄርሎስ፡፡ ስለዚህ አብ በማኅጸነ ማርያም ወልድን ወልዶታል ማለት ሐስት ክህደትም ነው ቄርሎስ እንደተናገረው፡፡

6.  ይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ ም 54 ቁ 11 “አብ ጥንት ፍጻሜ የሌለው ቃልን ዓለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ወለደው በኋላ ዘመንም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ንጽሕት ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወለደ”… ይህንን አጻጻፍ ልበ ብላችሁ አስተውሉት፡፡ አብ በማኅጸን ወልዶት ቢሆን ኖሮ “በኋላ ዘመንም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ወለደው” ለማለት የቀና የተመቸ አጻጻፍ ነበር ነገር ግን አብ በማኅጸነ ማርያም ከአብ አልተወለደምና “ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወለደ” ብሎ ሊቁ ኤጲፋንዮስ ከላይ ባለው መልኩ ጻፈልን፡፡

7.  ይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ ም 84 ቁ 8 “ሁለት ልደት እንዳለው በእግዚአብሔር ቃል እንዲሁ ልናምን ይገባናል አንዱ ቅድመዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው የማይመረመር ልደት ነው፡፡ ሁለተኛውም በኋላ ዘመን ከንጽሕት ድንግል ማርያም ያለአባት የተወለደው የማይመረመር የማይነገር ልደት ነው፡፡ ነገር ግን ቃል ሥጋ እንደሆነ ባሕርያችንንም ባሕርይ እንደአደረገ በዓይናችን እንዳየነው በእጃችንም እንደዳሰስነው ይህን ብቻ እናውቃለን”

እነዚህ ሰባት ማስረጃዎች በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ነጥብ የያዙ ናቸው፡፡
1.  ለሰማያዊ ልደቱ እናት ለምድራዊ ልደቱ ደግሞ አባት እንደሌለው የሚገልጹ መሆናቸው፡፡
2.  የጌታ ልደታት ሁለት መሆናቸውን እነርሱም ቅድመዓለም ከአብ በመለኮት ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን በሥጋ የተወለዳቸው ልደታት ብቻ መሆናቸውን፡፡ እዚህ ላይ “አብ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ወለደው” የሚለው የቅብዓቶች ሦስተኛ ልደት ደጋፊ የሌለው ከንቱ ፍልስፍና መሆኑን ተረድተንበታል፡፡
በቀጠዩ ክፍል የጌታ ሁለቱን ልደታት ሊቃውንት መምህራን በሃይማኖተ አበው ያሠፈሩትን ከእነዚህ ሰባት ማስረጃዎች በተጨማሪ ሌሎች ዐሥራ ዐራት ማስረጃዎችን እንጽፋለን፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ ማስረጃዎች ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ እኔ በጥቂቱ ነው የምጽፋቸው ተጨማሪውን ለማንበብ መጽሐፉን እንድትመለከቱ ከወዲሁ አሳስባለሁ፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment